ሌሎች የሰጡህን መመሪያ ለመታዘዝ እምቢተኛ የሆንክበት ጊዜ አለ? * ምናልባትም ወላጆችህ እንዳታይ የከለከሉህን የቴሌቪዥን ፕሮግራም በመመልከት ትእዛዛቸውን ጥሰህ ይሆናል። ቆየት ብለህ ስለ ጉዳዩ ስታስብ ግን ወላጆችህን ባለመታዘዝህ ተጸጽተህ ይሆናል። ንዕማን የሚባል አንድ ሰው መጀመሪያ ላይ የተሰጠውን መመሪያ ለመታዘዝ እምቢተኛ ሆኖ ነበር። ይህ ሰው ታዛዥ መሆን እንዲችል የረዳው ምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

የምንኖረው ከ3,000 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ነው እንበል። ንዕማን የሚባለው ሰው ትልቅ ቦታ ያለው የሶርያ የጦር አዛዥ ነው። ንዕማን የለመደው ሌሎችን ማዘዝ ሲሆን ከበታቹ ያሉት ወታደሮችም እሱ ያለውን ሁሉ ያደርጋሉ። ይሁንና ንዕማን አስከፊ በሆነ የለምጽ ወይም የሥጋ ደዌ በሽታ ተያዘ። በሽታው መልኩን ያበላሸው ከመሆኑም ሌላ በጣም ሳያሠቃየው አይቀርም።

ከእስራኤል የመጣች አንዲት ትንሽ ልጅ የንዕማንን ሚስት ታገለግል ነበር። አንድ ቀን ይህች ልጅ በትውልድ አገሯ ስለሚገኝ ኤልሳዕ የሚባል ነቢይ ለእመቤቷ ነገረቻት። ይህ ነቢይ ንዕማንን ሊፈውሰው እንደሚችል ገለጸችላት። ንዕማን ልጅቷ የተናገረችውን ሲሰማ ወዲያውኑ ወደ ኤልሳዕ ለመሄድ ተነሳ። ብዙ ስጦታዎችን ይዞ ከወታደሮቹ ጋር ወደ እስራኤል ምድር ተጓዘ። ከዚያም የመጣበትን ምክንያት ለማሳወቅ ወደ እስራኤል ንጉሥ ሄደ።

ኤልሳዕ ይህን ሲሰማ ንዕማንን ወደ እሱ እንዲልከው ለንጉሡ መልእክት ላከበት። ንዕማን የኤልሳዕ ቤት ሲደርስ ነቢዩ ወጥቶ አላናገረውም፤ ከዚህ ይልቅ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄዶ ሰባት ጊዜ ቢታጠብ ከበሽታው እንደሚድን መልእክተኛ ልኮ ነገረው። ንዕማን ይህን ሲሰማ ምን የተሰማው ይመስልሃል?

 ንዕማን በዚህ ስለተናደደ የአምላክን ነቢይ ለመታዘዝ እምቢተኛ ሆነ። ወታደሮቹን ‘ለመታጠብ ከፈለግሁ በአገሬ ከዚህ የተሻሉ ወንዞች አሉ’ አላቸው። በመሆኑም ንዕማን ወደ አገሩ ለመሄድ ተነሳ። ይሁንና ወታደሮቹ ምን እንዳሉት ታውቃለህ?— ‘ነቢዩ ከዚህ ከበድ ያለ ነገር እንድታደርግ ቢነግርህ ኖሮ አታደርገውም ነበር? ታዲያ ይህን ቀላል ነገር ለምን አታደርግም?’ አሉት።

ንዕማንም ወታደሮቹ የነገሩትን ሰማ። ስድስት ጊዜ ውኃው ውስጥ ብቅ ጥልቅ አለ። ለሰባተኛ ጊዜ ከውኃው ሲወጣ ግን ንዕማን ዓይኑን ማመን አቃተው፤ የቆዳ በሽታው ሙሉ በሙሉ ለቅቆታል! ንዕማን፣ ኤልሳዕን ሊያመሰግነው ስለፈለገ ወዲያውኑ 48 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ ወደሚገኘው የነቢዩ ቤት ጉዞ ጀመረ። ንዕማን ለኤልሳዕ ውድ ስጦታዎች ሊሰጠው ቢፈልግም ነቢዩ ስጦታዎቹን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም።

ከዚያም ንዕማን ኤልሳዕን አንድ ነገር እንዲሰጠው ጠየቀው። ንዕማን የጠየቀው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ‘ሁለት የበቅሎ ጭነት ዐፈር እንድወስድ ፍቀድልኝ’ አለው። አፈሩን ለመውሰድ የፈለገው ለምን ይመስልሃል?— ንዕማን የአምላክ ሕዝቦች ከሚገኙበት ከእስራኤል ምድር በወሰደው አፈር ላይ ለአምላክ መሥዋዕት ማቅረብ ስለፈለገ ነበር። ከዚያም ንዕማን ከይሖዋ በቀር ሌላ አምላክ እንደማያመልክ ቃል ገባ! እምቢተኝነቱን በመተው እውነተኛውን አምላክ ለመታዘዝ ፈቃደኛ ሆነ።

አንተስ የንዕማንን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው?— አንዳንድ ጊዜ እንደ እሱ እምቢተኛ እየሆንክ የምታስቸግር ከሆነ በባሕሪህ ላይ ለውጥ ማድረግ ትችላለህ። ሌሎች በዚህ ረገድ የሚሰጡህን እርዳታ በመቀበል ይህንን ባሕርይ ማስተካከል ትችላለህ።

ከመጽሐፍ ቅዱስህ ላይ የሚከተሉትን አንብብ

^ አን.3 ይህን ርዕስ የምታነበው ከትንሽ ልጅ ጋር ከሆነ፣ ይህ ሰረዝ ቆም ብለህ ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ እንድታበረታታው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።