በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

አምላክ እየቀጣን ነው?

አምላክ እየቀጣን ነው?

“ይህ ቴምባትሱ (የአምላክ ቁጣ) ይመስለኛል፤ እርግጥ የአደጋው ሰለባ የሆኑት ሰዎች ያሳዝናሉ።” አንድ ታዋቂ የጃፓን ፖለቲከኛ ይህን ያሉት ጃፓን በመጋቢት 2011 በተከሰተው በሬክተር ስኬል 9.0 የደረሰ የመሬት መናወጥና ሱናሚ ከተመታች በኋላ ነበር።

በጥር 2010 በሄይቲ በደረሰው የመሬት መናወጥ ሳቢያ ከ220,000 በላይ ሰዎች ሲሞቱ አንድ ታዋቂ የቴሌቪዥን ሰባኪ፣ ይህ ሁሉ የደረሰባቸው “ከዲያብሎስ ጋር ስለተዋዋሉ” እንደሆነና “ወደ አምላክ መመለስ” እንዳለባቸው ተናግሯል።

በማኒላ፣ ፊሊፒንስ በተፈጠረ ግርግር ምክንያት 79 ሰዎች በሞቱ ጊዜ አንድ የካቶሊክ ቄስ ይህ የሆነው “አምላክ የሞተውንና ስሜት አልባ የሆነውን ሕሊናችንን ማንቃት ስለፈለገ ነው” በማለት ተናግረዋል። በዚያ አካባቢ የሚገኝ አንድ ጋዜጣ እንዲህ በማለት ዘግቧል፦ “ሃያ አንድ በመቶ የሚሆኑት አዋቂዎች፣ አምላክ በአገሪቱ ላይ በተደጋጋሚ በሚደርሱት እንደ መሬት መንሸራተትና አውሎ ነፋስ የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች አማካኝነት ቁጣውን እየገለጸ እንደሆነ ይሰማቸዋል።”

‘አምላክ በተፈጥሮ አደጋዎች አማካኝነት መጥፎ ሰዎችን ይቀጣል’ የሚለው አመለካከት በዘመናችን የመጣ ነገር አይደለም። በ1755 በሊዝበን፣ ፖርቱጋል ወደ 60,000 የሚጠጉ ሰዎች በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በእሳትና በሱናሚ ምክንያት ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ቮልቴር የተባለው ታዋቂ ፈላስፋ “ሊዝበን በአደጋ የወደመችው ልቅ ሥነ ምግባር ከሚታይባት ከፓሪስ የበለጠ ኃጢአተኛ ሆና ነው?” በማለት ጠይቋል። በተመሳሳይም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ ‘አምላክ የሰው ልጆችን ለመቅጣት በተፈጥሮ አደጋዎች ይጠቀማል?’ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። እንዲያውም በብዙ አገሮች ሰዎች፣ እንዲህ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን የሚያመጣው አምላክ እንደሆነ ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው።

ከዚህ አንጻር የሚከተሉትን ጥያቄዎች መጠየቃችን አስፈላጊ ነው፦ በእርግጥ አምላክ ሰዎችን ለመቅጣት በተፈጥሮ አደጋዎች ይጠቀማል? ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያየነው ያለው የተፈጥሮ አደጋዎች ውርጅብኝ የአምላክ ቅጣት ነው?

አንዳንዶች፣ አምላክ በተፈጥሮ ኃይላት ተጠቅሞ ሰዎችን ያጠፋባቸውን ወቅቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በመጥቀስ ለተፈጥሮ አደጋዎች ተጠያቂው እሱ እንደሆነ ይናገራሉ። (ዘፍጥረት 7:17-22፤ 18:20፤ 19:24, 25፤ ዘኍልቍ 16:31-35) ይሁንና እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በጥንቃቄ ስንመረምር እነዚህ ክንውኖች አሁን እየደረሱ ካሉት አደጋዎች የሚለዩባቸው ሦስት ዋና ዋና መንገዶች እንዳሉ እንመለከታለን። በመጀመሪያ ደረጃ፣ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል። ሁለተኛ፣ አምላክ ያመጣው ጥፋት ጥሩም ሆነ መጥፎ ሰዎችን በጅምላ ከሚያጠፉት በዛሬው ጊዜ ከሚከሰቱት የተፈጥሮ አደጋዎች የተለየ ነው። አምላክ የሚያጠፋው ከክፉ ሥራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆኑ ወይም ማስጠንቀቂያውን ለመስማት እምቢተኞች የሆኑ ሰዎችን ብቻ ነው። ሦስተኛ፣ አምላክ ጥሩ ሰዎች ከጥፋቱ የሚተርፉበትን መንገድ አዘጋጅቷል።ዘፍጥረት 7:1, 23፤ 19:15-17፤ ዘኍልቍ 16:23-27

በዘመናችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፉትን ስፍር ቁጥር የሌላቸው የተፈጥሮ አደጋዎች ያመጣው አምላክ እንደሆነ የሚያሳይ አንድም ማስረጃ የለም። ታዲያ እንዲህ ያሉ አደጋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲበዙ ያደረገው ምን ሊሆን ይችላል? ለእነዚህ አደጋዎች ቅድመ ዝግጅት ማድረግና አደጋው ያስከተለውን ሁኔታ መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? አደጋ የማይኖርበት ጊዜስ ይመጣ ይሆን? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ በቀጣዮቹ ርዕሶች ላይ እናገኛለን።