የዚህ ጥያቄ መልስ ‘አዎን’ የሚል ከሆነ እንዲህ የሚል ሌላ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፦ የምናሳየው ምግባር በአምላክ ስሜት ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል? ማለትም አምላክ በምናደርጋቸው ነገሮች ሊደሰት ወይም ሊያዝን ይችላል? አንዳንድ የጥንት ፈላስፎች አምላክ ሊደሰት ወይም ሊያዝን እንደማይችል ይናገሩ ነበር። እነዚህ ሰዎች ማንም ሰው በአምላክ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ስለማይችል አምላክ ስሜት የለውም የሚል የመከራከሪያ ነጥብ ያነሳሉ። ከዚህ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ጥልቅ ስሜት ያለውና የምናደርገው ነገር በእጅጉ የሚያሳስበው አምላክ እንደሆነ ይገልጻል። እስቲ በዚህ ረገድ በመዝሙር 78:40, 41 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ እንመልከት።

መዝሙር 78 አምላክ ከጥንቶቹ እስራኤላውያን ጋር ስለነበረው ግንኙነት ይነግረናል። ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ የባርነት ሕይወት ከታደጋቸው በኋላ በብሔር ደረጃ ከእሱ ጋር የተለየ ዝምድና እንዲመሠርቱ ግብዣ አቅርቦላቸው ነበር። ሕጎቹን ጠብቀው የሚኖሩ ከሆነ ‘የተወደደ ርስቱ’ እንደሚሆኑና ዓላማውን ዳር ለማድረስ ፈጽሞ በተለየ መንገድ እንደሚጠቀምባቸው ቃል ገብቶ ነበር። ሕዝቡም በዚህ ተስማምቶ በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ ታቀፈ። ታዲያ ሕዝቡ ከገባው ቃል ጋር ተስማምቶ ኖረ?​—ዘፀአት 19:3-8

ለይሖዋ የእሱን ልብ ደስ በሚያሰኝ መንገድ ከመኖር የበለጠ ልንሰጠው የምንችለው ውድ ነገር የለም

መዝሙራዊው “በምድረ በዳ ስንት ጊዜ ዐመፁበት!” በማለት ተናግሯል። (ቁጥር 40) በሚቀጥለው ቁጥር ላይ ደግሞ “ደግመው ደጋግመው እግዚአብሔርን ተፈታተኑት” የሚል ሐሳብ ይገኛል። (ቁጥር 41) ጸሐፊው እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ጊዜ ያምፁ እንደነበር መግለጹን ልብ በል። እንዲህ ያለው መጥፎ ዝንባሌ የጀመረው ከግብፅ ከወጡ ብዙም ሳይቆዩ ገና በምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ ነው። ሕዝቡ፣ አምላክ እነሱን ለመንከባከብ ያለውን አቅምና ፍላጎት በመጠራጠር በእሱ ላይ ማመፅ ጀመረ። (ዘኍልቍ 14:1-4) ለመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የተዘጋጀ አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “ዐመፁበት” የሚለው ቃል “‘በአምላክ ላይ ልባቸውን አደነደኑ’ ወይም ‘አምላክን “እንቢ” አሉ’ ተብሎ ሊተረጎም” እንደሚችል ገልጿል። እንደዚያም ሆኖ ይሖዋ ንስሐ ሲገቡ በምሕረት ተነሳስቶ ይቅር ይላቸው ነበር። ይሁንና ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው በመመለስ እንደገና ዓመፁ፤ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በተደጋጋሚ ጊዜ ይከሰት ነበር።​—መዝሙር 78:10-19, 38

ይሖዋ ወጥ አቋም የሌለው ይህ ሕዝብ በሚያምፅበት ጊዜ ምን ተሰምቶት ነበር? ቁጥር 40 “አሳዘኑት” ይላል። ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ደግሞ “ለመሪር ሐዘን ዳረጉት” በማለት ይገልጻል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ይህን ጉዳይ ሲያብራራ “ይህ ሐረግ የማይታዘዝና ዓመፀኛ የሆነ አንድ ልጅ የሚያደርገው ነገር ሥቃይ እንደሚያስከትል ሁሉ የዕብራውያኑ ድርጊትም ለሥቃይ ምክንያት እንደሆነ የሚገልጽ ትርጉም አለው” ብሏል። በጥባጭ የሆነ ልጅ ወላጆቹን እንደሚያበሳጭ ሁሉ ዓመፀኛ የሆኑት እነዚህ እስራኤላውያንም ‘የእስራኤልን ቅዱስ አስቈጥተውታል።’​—ቁጥር 41

ከዚህ ጥቅስ ምን እንማራለን? ይሖዋ እሱን ከሚያመልኩት ሰዎች ጋር ጥብቅ ዝምድና እንዳለውና በቀላሉ በእነሱ ተስፋ እንደማይቆርጥ ማወቅ የሚያጽናና ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ ስሜት እንዳለውና የምናሳየው ምግባር በስሜቱ ላይ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል መዘንጋት አይኖርብንም። ታዲያ አንተ ይህን ማወቅህ ምን ስሜት ሊያሳድርብህ ይገባል? ይህ ሁኔታ ትክክል የሆነውን ነገር እንድታደርግ አነሳስቶሃል?

የኃጢአት ጎዳና በመከተል የይሖዋን ልብ ከማሳዘን ይልቅ የጽድቅን መንገድ በመከተል ልቡን ደስ ለማሰኘት መምረጥ እንችላለን። ደግሞም አምላክ እሱን ከሚያመልኩት ሰዎች የሚፈልገው ይህንኑ ነው፤ አዎን፣ አምላክ “ልጄ ሆይ፤ ጠቢብ ሁን፤ ልቤን ደስ አሰኘው” የሚል ግብዣ አቅርቧል። (ምሳሌ 27:11) ለይሖዋ የእሱን ልብ ደስ በሚያሰኝ መንገድ ከመኖር የበለጠ ልንሰጠው የምንችለው ውድ ነገር የለም።

በሐምሌ ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦