በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ልጆቻችሁን አስተምሩ

ስለ ኢየሱስ የጻፉ ሰዎች

ስለ ኢየሱስ የጻፉ ሰዎች

ስለ ኢየሱስ የሚናገሩ ታሪኮች ሲነበቡ መስማት ያስደስትሃል?— * አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ የጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሌለ ሲያውቁ ይገረማሉ። ያም ሆኖ ስምንት የሚያህሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ስለ ኢየሱስ ብዙ ነገሮች ጽፈዋል። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ በኖረበት ዘመን የኖሩ ሲሆን ያስተማረውንም ጽፈዋል። የእነዚህን ስምንት ሰዎች ስም መጥቀስ ትችላለህ?— የመጀመሪያዎቹ አራቱ ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ ናቸው። የተቀሩት ደግሞ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ይሁዳና ጳውሎስ ናቸው። ስለ እነዚህ ሰዎች ምን የምታውቀው ነገር አለ?—

እስቲ በመጀመሪያ ከኢየሱስ 12 ሐዋርያት መካከል ስለ ኢየሱስ ጽፈው ስለነበሩት ስለ ሦስቱ ጸሐፊዎች እንመልከት። የእነዚህን ሰዎች ስም ታውቃለህ?— ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ማቴዎስ ናቸው። ጴጥሮስ ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ ሁለት ደብዳቤዎችን ጽፏል። ኢየሱስ ስላደረጋቸውና ስለተናገራቸው ነገሮች የሚያውቀውን ጽፎላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስህን 2 ጴጥሮስ 1:16-18 ላይ አውጣና ይሖዋ አምላክ ከሰማይ ኢየሱስን ሲያነጋግረው ጴጥሮስ የሰማውን ነገር አንብብ።—ማቴዎስ 17:5

ሐዋርያው ዮሐንስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ አምስቱን ጽፏል። ደቀ መዛሙርቱ ከጌታቸው ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ራት በበሉበት ወቅት ከኢየሱስ አጠገብ ነበር። ከዚህም በላይ ኢየሱስ በሞተበት ወቅት ዮሐንስ ከእሱ ጋር ነበር። (ዮሐንስ 13:23-26፤ 19:26) ስለ ኢየሱስ ሕይወት ከሚናገሩትና ወንጌሎች ተብለው ከሚጠሩት አራት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች አንዱን የጻፈው ዮሐንስ ነው። በተጨማሪም ዮሐንስ፣ ኢየሱስ የሰጠውን ራእይ እንዲሁም በስሙ የተሰየሙትን ሦስት ደብዳቤዎች ጽፏል። (ራእይ 1:1) ሦስተኛው ጸሐፊ ደግሞ የኢየሱስ ሐዋርያ የነበረው ማቴዎስ ነው። እሱም ቀረጥ ሰብሳቢ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ሌሎቹ ሁለት ሰዎች ኢየሱስን የሚያውቁበት ሁኔታ ከሌሎቹ ለየት ይላል። እነዚህ ጸሐፊዎች የኢየሱስ ታናናሽ ወንድሞች ናቸው። (ማቴዎስ 13:55) ወንድሞቹ መጀመሪያ ላይ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አልነበሩም። ኢየሱስ ቅንዓት በሞላበት መንገድ ሲሰብክ አእምሮውን ስቷል ብለው እስከ መናገር ደርሰው ነበር። (ማርቆስ 3:21) እነዚህ ወንድሞቹ እነማን ነበሩ?— አንደኛው ያዕቆብ ነው። የያዕቆብን መጽሐፍ የጻፈው እሱ ነው። ሌላው ደግሞ የይሁዳን መጽሐፍ የጻፈው ይሁዳ ነው።—ይሁዳ 1

ስለ ኢየሱስ ሕይወት የጻፉት ሌሎች ደግሞ ማርቆስና ሉቃስ ናቸው። የማርቆስ እናት የሆነችው ማርያም በኢየሩሳሌም ውስጥ ትልቅ ቤት ነበራት፤ ሐዋርያው ጴጥሮስን ጨምሮ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በማርያም ቤት ይሰበሰቡ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 12:11, 12) ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ የፋሲካ በዓልን ባከበረበት ምሽት ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ሲሄዱ የተከተላቸው ወጣት ማርቆስ ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ በተያዘበት ጊዜ ወታደሮች ማርቆስን ሊይዙት ሲሞክሩ ልብሱን ጥሎ ሸሽቷል።—ማርቆስ 14:51, 52

ሉቃስ ደግሞ በጣም የተማረ የሕክምና ዶክተር ነበር፤ ደቀ መዝሙር የሆነው ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ሳይሆን አይቀርም። ስለ ኢየሱስ ሕይወት በሚገባ  ካጠና በኋላ ግልጽና ትክክለኛ ታሪክ ጽፏል። ከጊዜ በኋላ የሐዋርያው ጳውሎስ የጉዞ ጓደኛ ከመሆኑም በላይ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን ጽፏል።—ሉቃስ 1:1-3፤ የሐዋርያት ሥራ 1:1

ስለ ኢየሱስ ከጻፉት መካከል ስምንተኛው ጸሐፊ ጳውሎስ ነው። ጳውሎስ፣ የታወቀ የሕግ ሰው የሆነው የገማልያል ተማሪ ነበር። የፈሪሳውያንን ሕግ እየተማረ ያደገውና በዚያን ጊዜ ሳኦል ተብሎ ይጠራ የነበረው ጳውሎስ የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ይጠላ የነበረ ከመሆኑም በላይ እነሱን በማስገደል ተባብሯል። (የሐዋርያት ሥራ 7:58 እስከ 8:3፤ 22:1-5፤ 26:4, 5) ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ እውነቱን የተማረው እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ?—

ጳውሎስ የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ለማሳሰር ወደ ደማስቆ እየሄደ ሳለ በድንገት ከሰማይ በመጣ ኃይለኛ ብርሃን ታወረ። ከዚያም “ሳኦል፣ ሳኦል ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምፅ ሰማ። እየተናገረ የነበረው ኢየሱስ ነው! ጳውሎስን ወደ ደማስቆ እንዲሄድ ነገረው። ከዚያም ኢየሱስ ጳውሎስን ሄዶ እንዲያናግረው ሐናንያ የተባለውን ደቀ መዝሙር ላከው፤ በኋላም ጳውሎስ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ሆነ። (የሐዋርያት ሥራ 9:1-18) ጳውሎስ ከሮም እስከ ዕብራውያን ድረስ ያሉትን 14 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጽፏል።

ስለ ኢየሱስ የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ራስህ ማንበብ ጀምረሃል? ወይም ሌላ ሰው እያነበበልህ ነው?— አሁን በልጅነትህ ልታደርጋቸው ከሚገቡ ነገሮች ሁሉ የተሻለው መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ስለ ኢየሱስ መማር ነው።

^ አን.3 ይህን ርዕስ የምታነበው ከልጆች ጋር ከሆነ፣ ይህ ሰረዝ የተደረገው ቆም ብለህ ጥያቄውን ለልጆቹ እንድታቀርብላቸው ለማስታወስ ተብሎ ነው።