በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው?

“ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እንዲሁም ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅ ለመምከር ይጠቅማል፤ ይኸውም የአምላክ ሰው ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

ሐዋርያው ጳውሎስ መጽሐፍ ቅዱስ ያለውን ላቅ ያለ ዋጋ ለመግለጽ የተጠቀመበት እንዴት ያለ ግሩም ሐሳብ ነው! እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ ይህን ሐሳብ የተናገረው በዚያ ዘመን ይገኝ የነበረውንና በአሁኑ ጊዜ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ብሉይ ኪዳን ብለው የሚጠሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለማመልከት ነው። ይሁን እንጂ ሐሳቡ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የኢየሱስ ታማኝ ደቀ መዛሙርት የጻፏቸውን ጨምሮ ለ66ቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ሙሉ በሙሉ ይሠራል።

አንተስ መጽሐፍ ቅዱስን ልክ እንደ ጳውሎስ ከፍ አድርገህ ትመለከተዋለህ? መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ሰዎች በአምላክ መንፈስ ተመርተው ጽፈውታል ብለህ ታምናለህ? በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ አመለካከት ነበራቸው። ከዚያ በኋላ በነበሩት ዘመናትም እውነተኛ ክርስቲያኖች ተመሳሳይ እምነት ነበራቸው። ለምሳሌ ያህል፣ በአሥራ አራተኛው መቶ ዘመን የኖረው ጆን ዊክሊፍ የተባለ እንግሊዛዊ ቄስ መጽሐፍ ቅዱስን “ፈጽሞ ስህተት የማይገኝበት የእውነት ሕግ” እንደሆነ አድርጎ ተመልክቶታል። ዘ ኒው ባይብል ዲክሽነሪ ከላይ ያለውን የጳውሎስ ሐሳብ አስመልክቶ አስተያየት ሲሰጥ በመለኮታዊ “መሪነት [መጻፉ] መጽሐፍ ቅዱስ የያዛቸው ነገሮች በሙሉ እውነት ለመሆናቸው ዋስትና ይሰጣል” ብሏል።

ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው አመለካከት ተለወጠ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ተአማኒነት ላይ ያላቸው እምነት እየጠፋ ነው። ዘ ዎርልድስ ሬሊጅንስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉም ክርስቲያኖች [አሁንም ድረስ] መጽሐፍ ቅዱስን ሊመሩበት እንዲሁም እምነታቸው በዚህ መጽሐፍ ላይ ሊመሠረት እንደሚገባ በሐሳብ  ደረጃ ያምናሉ።” በተግባር ሲታይ ግን ሁኔታው እንደዚያ አይደለም። በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን የሚመለከቱት “ተአማኒነት እንደሌለው የሰው ወግ” አድርገው ነው። እነዚህ ሰዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉትን ሰዎች ጥሩ መንፈሳዊ አቋም እንዳላቸው አምነው ቢቀበሉም ጸሐፊዎቹ በዛሬው ጊዜ የበራልን ጥልቅ መንፈሳዊ እውነት ምን ትርጉም እንዳለው ለማብራራት የሚሞክሩ የሚሳሳቱ ተራ ሰዎች አድርገው ይመለከቷቸዋል።

እንደ እውነቱ ከሆነ በዛሬው ጊዜ አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲመራ የሚፈልጉት በጣም ጥቂቶች ናቸው። ለምሳሌ፣ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጊዜ ያለፈባቸውና ተግባራዊ ሊሆኑ የማይችሉ እንደሆኑ ሲናገሩ ብዙ ጊዜ ሰምተህ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። በርካታ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎችንና መመሪያዎችን ሲበርዙ ምንም ስህተት እንደሠሩ ሆኖ አይታያቸውም፤ አንዳንድ ጊዜ ሕጉ ለእነሱ ሳይመች ሲቀር ከናካቴው ችላ ሲሉት ይታያሉ። ራሳቸውን ክርስቲያን አድርገው የሚቆጥሩ አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዝሙት፣ ስለ ምንዝር፣ ሐቀኝነትን ስለ ማጉደልና ስለ ስካር የሚሰጠውን መመሪያ ሆን ብለው ይጥሳሉ።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

ይህ የሆነው ለምንድን ነው? በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሰር ቻርልስ ማርስተን የተባሉ አርኪኦሎጂስት መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነው (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ አንደኛውን ምክንያት ገልጸዋል። እሳቸው እንደተናገሩት “ዘመናዊ ጸሐፊዎች” በመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት ላይ የሚሰነዝሯቸውን “በርካታ ግምታዊ ሐሳቦች [ሰዎች] ምንም ሳያንገራግሩ ለመቀበል” ፈጣኖች ናቸው። በዛሬው ጊዜስ ሰዎች እንዲህ ናቸው? ምሑራን፣ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጡ ለማድረግ የሚሰነዝሯቸውን አስተያየቶችና ሐሳቦች እንዴት ልትመለከታቸው ይገባል? የሚቀጥለው ርዕስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል ተመልከት።