በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ታኅሣሥ 2009

 ልጆቻችሁን አስተምሩ

ኤርምያስ መናገሩን አላቆመም

ኤርምያስ መናገሩን አላቆመም

ተስፋ ከመቁረጥህ የተነሳ የጀመርከውን ነገር ለማቆም ያሰብክበት ጊዜ አለ?— * ብዙዎች ያስባሉ። ወጣቱ ኤርምያስም እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። ይሁን እንጂ ሌሎች የተናገሩት ወይም ያደረጉት ነገር ተስፋ አላስቆረጠውም። ኤርምያስ በአምላክ የተወደደ የነበረ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ ያዘዘውን ማድረጉን ለማቆም የተፈተነው ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ኤርምያስ ከመወለዱ በፊት እውነተኛው አምላክ ይሖዋ እሱን የማያስደስቱትን ሰዎች እንዲያስጠነቅቅ ኤርምያስን ነቢይ እንዲሆን መረጠው። ከዓመታት በኋላ ኤርምያስ ይሖዋን ምን እንዳለው ታውቃለህ?— “እንዴት እንደምናገር አላውቅም፤ ገና ሕፃን ልጅ ነኝ” ብሎት ነበር።

ይሖዋ ለኤርምያስ ምን መልስ የሰጠው ይመስልሃል?— በደግነት ሆኖም ጠንከር ባለ መንገድ “‘ገና ሕፃን ልጅ ነኝ’ አትበል፤ ወደምልክህ ሁሉ ሄደህ፣ ያዘዝሁህን ሁሉ ትናገራለህ፤ . . . አትፍራቸው” አለው። እንዳይፈራ የነገረው ለምንድን ነው? ይሖዋ “እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝ” ብሎታል።—ኤርምያስ 1:4-8

ያም ሆኖ ኤርምያስ ከላይ እንደጠቀስነው ቆየት ብሎ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተሰምቶታል። እንዲህ የተሰማው አምላክን በማገልገሉ ምክንያት ሌሎች ስላፌዙበት ነበር። “ቀኑን ሙሉ ማላገጫ ሆንሁ፤ ሁሉም ተዘባበቱብኝ” ሲል ተናግሯል። በዚህም ምክንያት አምላክ ያዘዘውን መናገሩን ለማቆም ወሰነ። “ከእንግዲህ [የይሖዋን] ስም አላነሣም፤ በስሙም አልናገርም” አለ። ይሁንና ኤርምያስ በእርግጥ አምላክ ያዘዘውን ማድረጉን ተወ?

ኤርምያስ “ቃሉ በልቤ እንደ እሳት፣ በዐጥንቴም ውስጥ እንደ ረመጥ ሆነብኝ፤ ዐፍኜ መያዝ አቃተኝ” በማለት ተናገረ። (ኤርምያስ 20:7-9) ኤርምያስ የፈራበት ጊዜ የነበረ ቢሆንም ለይሖዋ ከፍተኛ ፍቅር ስለነበረው አምላክ ያዘዘውን ከመፈጸም ወደኋላ አላለም። ኤርምያስ የይሖዋን ፈቃድ መፈጸሙን መቀጠሉ ጥበቃ ያስገኘለት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ከክፉ መንገዳቸው ካልተመለሱ ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ ለሕዝቡ እንዲነግር ኤርምያስን ላከው። ኤርምያስ ይህን ማስጠንቀቂያ ለሕዝቡ ሲነግራቸው በንዴት  “ሞት ይገባዋል” ብለው ጮኹ። ይሁንና ኤርምያስ ‘አምላካቸውን ይሖዋን እንዲታዘዙ’ ተማጸናቸው። ከዚያም ‘ይህን ሁሉ ቃል እንድናገር አምላክ በእርግጥ ስለ ላከኝ ብትገድሉኝ፣ የንጹሕ ሰው ደም ማፍሰሳችሁ ይሆናል’ አላቸው። ከዚያ በኋላ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?—

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ባለሥልጣኖቹና ሕዝቡም ሁሉ ለካህናትና ለነቢያት፣ ‘ይህ ሰው በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ተናግሮአልና ሊገደል አይገባውም’ አሉ።” ኤርምያስ፣ ፈርቶ የተሰጠውን ተልዕኮ ከመፈጸም ወደኋላ ስላላለ ይሖዋ ጠብቆታል። አሁን ደግሞ ከኤርምያስ የተለየ እርምጃ የወሰደ ኦርዮ የተባለ አንድ ሌላ ነቢይ ምን እንደደረሰበት እንመልከት።

‘ኦርዮም እንደ ኤርምያስ በኢየሩሳሌም ከተማ ላይ ትንቢት ተናግሮ’ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ንጉሥ ኢዮአቄም በኦርዮ በተናደደ ጊዜ ግን ኦርዮ ምን እንዳደረገ ታውቃለህ?— በጣም ስለፈራ የአምላክን ፈቃድ ማድረጉን ትቶ ወደ ግብፅ ሸሸ። ንጉሡም ኦርዮን ፈልገው እንዲያመጡት ወደ ግብፅ ሰዎችን ላከ። ሰዎቹ ኦርዮን ይዘው በመጡ ጊዜ ክፉው ንጉሥ ምን እንዳደረገ ታውቃለህ?— ኦርዮን በሰይፍ ገደለው!—ኤርምያስ 26:8-24

ኤርምያስ የይሖዋን ጥበቃ ያገኘው፣ ኦርዮ ግን የተገደለው ለምን ይመስልሃል?— ኤርምያስ ልክ እንደ ኦርዮ ፈርቶ እንደነበር ግልጽ ነው። ሆኖም የተሰጠውን ተልዕኮ ከመፈጸም ወደኋላ አላለም። ይሖዋን ማገልገሉን አላቆመም። ከኤርምያስ ታሪክ ምን ትምህርት ማግኘት የምንችል ይመስልሃል?— አንዳንድ ጊዜ የአምላክን ትእዛዝ መፈጸም ከባድ ሊሆንብን ይችላል፤ ሆኖም ምንጊዜም በአምላክ መታመንና ትእዛዛቱን መፈጸም ይኖርብናል።

^ አን.3 ይህን ርዕስ የምታነበው ከልጆች ጋር ከሆነ፣ ይህ ሰረዝ የተደረገው ቆም ብለህ ጥያቄውን ለልጆቹ እንድታቀርብላቸው ለማስታወስ ተብሎ ነው።