የኖኅ ልጅ የሆነው ሴም ይኖርበት የነበረው ዓለም በጠፋ ጊዜ በሕይወት የተረፈ ሲሆን ከዚያ በኋላ በነበረው ዓለም ውስጥ ኖሯል። ከጥፋት ውኃ በፊት የነበረው ዓለም የጠፋው ለምን እንደሆነና ሴምና ቤተሰቦቹ ከጥፋቱ በሕይወት ተርፈው በሌላ ዓለም ውስጥ መኖር የቻሉት እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ?— * እስቲ ይህን በተመለከተ እንወያይ።

ሴም ወጣት በነበረበት ጊዜ “የሰው ዐመፅ” በዝቶ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። በወቅቱ የነበሩት ሰዎች የሚያስቡት ነገር “ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ” ነበር። በዚህ ጊዜ አምላክ ምን እንዳደረገ ታውቃለህ?— ያንን ክፉ ዓለም በውኃ አጠፋው። ሐዋርያው ጴጥሮስ “በዚያ ጊዜ የነበረው ዓለም በውኃ ተጥለቅልቆ ጠፍቷል” ሲል ጽፏል።—ዘፍጥረት 6:5፤ 2 ጴጥሮስ 3:6

አምላክ ያንን ዓለም ያጠፋው ለምን እንደሆነ ገባህ?— ሰዎቹ ክፉዎች ስለነበሩና ሐሳባቸው “ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ” ስለነበር ነው። ኢየሱስ ስለ እነዚህ ሰዎች ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ ‘ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ዘመን ሰዎች ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ያገቡና ይዳሩ ነበር። የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም።’ማቴዎስ 24:37-39

እነዚህ ሰዎች ሳያስተውሉ ወይም ሳያዩ የቀሩት ነገር ምንድን ነው?— የሴም አባት ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” የነበረ ቢሆንም ሰዎቹ እሱ የሚነግራቸውን ነገር ሰምተው አልታዘዙም። ኖኅ ግን አምላክን በመስማት ራሱንም ሆነ ቤተሰቡን ከጥፋት ውኃው ለማዳን የሚያስችል መርከብ ሠራ። አምላክ የሰጣቸውን መመሪያ ሰምተው የታዘዙት ኖኅና ሚስቱ እንዲሁም ሴም፣ ካምና ያፌት የተባሉት ልጆቹና ሚስቶቻቸው ብቻ ናቸው። ሌሎቹ ሰዎች ግን አምላክ የሚላቸውን ከማድረግ ይልቅ እነሱ ራሳቸው የሚፈልጉትን ብቻ ስላደረጉ በጥፋት ውኃው ተጥለቅልቀው ጠፉ።—2 ጴጥሮስ 2:5፤ 1 ጴጥሮስ 3:20

የጥፋት ውኃው ከጀመረ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ሴምና ቤተሰቡ ከመርከቡ ወጡ። ክፉ ሰዎች በሙሉ የጠፉ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ሁኔታዎች መለወጥ ጀመሩ። የካም ልጅ የሆነው ከነዓን (ካም የሴም ወንድም ነው) አንድ በጣም መጥፎ ነገር አደረገ፤ በዚህም ምክንያት ኖኅ “ከነዓን የተረገመ ይሁን” ሲል ተናገረ። የካም የልጅ ልጅ የሆነው ናምሩድም መጥፎ ሰው ነበር። እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን ከመቃወሙም በላይ ሰዎች ስማቸውን ለማስጠራት ባቤል የሚባል ትልቅ ግምብ  እንዲገነቡ አስተባበረ። ሴምና አባቱ በዚህ ሁኔታ ምን የተሰማቸው ይመስልሃል?—ዘፍጥረት 9:25፤ 10:6-10፤ 11:4, 5

እነሱም ሆኑ ይሖዋ በጣም አዝነዋል። ይሖዋ ምን እንዳደረገ ታውቃለህ?— ሰዎቹ እርስ በርሳቸው መግባባት እንዳይችሉ ቋንቋቸውን ደባለቀው። በመሆኑም ሰዎቹ ግንባታውን አቁመው የራሳቸውን ቋንቋ ከሚናገሩ ሰዎች ጋር በመሆን ወደተለያየ ስፍራ ተበተኑ። (ዘፍጥረት 11:6-9) ይሁንና አምላክ የሴምንና የቤተሰቡን ቋንቋ አልደባለቀውም። ይህ ደግሞ እርስ በርስ ተደጋግፈው በአንድነት አምላክን እንዲያመልኩ አስችሏቸዋል። ሴም ለስንት ዓመት ይሖዋን እንዳገለገለ ታውቃለህ?—

ሴም የሞተው በ600 ዓመቱ ነው። ከጥፋት ውኃው በፊት 98 ዓመት የኖረ ሲሆን ከዚያ በኋላ ደግሞ 502 ዓመት ኖሯል። ሴም፣ ኖኅ መርከቡን ሲሠራ እንደረዳውና ስለሚመጣው የውኃ መጥለቅለቅ ለሰዎች እንዳስጠነቀቀ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሁን እንጂ ሴም ከጥፋት ውኃው በኋላ በኖረባቸው ከ500 የሚበልጡ ዓመታት ምን ሲያደርግ የነበረ ይመስልሃል?— ኖኅ ስለ ይሖዋ ሲናገር “የሴም አምላክ” ብሏል። ሴም በእነዚያ ዓመታት ይሖዋን ማምለኩንና የቤተሰቡ አባላት እንዲህ እንዲያደርጉ መርዳቱን ቀጥሎ መሆን አለበት። የሴም ዘር ከሆኑት ሰዎች መካከል አብርሃም፣ ሣራና ይስሐቅ ይገኙበታል።—ዘፍጥረት 9:26፤ 11:10-31፤ 21:1-3

ከሴም ዘመን አንስቶ በክፋት እየባሰ ስለመጣው አሁን ስለምንኖርበት ዓለም እስቲ ቆም ብለህ አስብ። ይህ ዓለም ምን ይጠብቀዋል?— መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ዓለም “በማለፍ ላይ” እንደሆነ ይናገራል። ይሁንና “የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” የሚለውን ተስፋ ልብ በል። የአምላክን ፈቃድ የምናደርግ ከሆነ በዚህ ዓለም ላይ ከሚመጣው ጥፋት ተርፈው ወደ አምላክ አዲስ ዓለም ከሚገቡት ሰዎች መካከል መሆን እንችላለን። ያን ጊዜ በአምላክ እርዳታ በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ እንኖራለን!—1 ዮሐንስ 2:17፤ መዝሙር 37:29፤ ኢሳይያስ 65:17

^ አን.3 ይህን ርዕስ የምታነበው ከትንሽ ልጅ ጋር ከሆነ ይህ ሰረዝ ቆም ብለህ ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ እንድታበረታታው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።