በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ነሐሴ 2009

ጥሩ ሃይማኖት ሰዎች ለአምላክ ቃል አክብሮት እንዲኖራቸው ያስተምራል

ጥሩ ሃይማኖት ሰዎች ለአምላክ ቃል አክብሮት እንዲኖራቸው ያስተምራል

ኢየሱስ፣ ሰዎች የአምላክ ቃል ለሆነው ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት እንዲኖራቸው አበረታትቷል። በዲያብሎስ በተፈተነበት ወቅት የሰጠው መልስ የዚህን ሐሳብ እውነተኝነት ያረጋግጣል። (ማቴዎስ 4:4-11) ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ድንጋዮችን ዳቦ እንዲያደርግ ሰይጣን በጠየቀው ጊዜ ምን ምላሽ ሰጠ? ሙሴ በመንፈስ መሪነት ከጻፈው ከዘዳግም 8:3 ላይ በመጥቀስ ሰይጣን ያለውን ሳይፈጽም ቀርቷል። ሰይጣን በዓለም መንግሥታት ሁሉ ላይ ገዢ እንደሚያደርገው በመግለጽ አንድ ጊዜ ብቻ ተደፍቶ እንዲያመልከው ኢየሱስን በጠየቀው ጊዜ ኢየሱስ ምን ምላሽ ሰጠ? በዘዳግም 6:13 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት በመጥቀስ ያቀረበለትን ግብዣ ሳይቀበል ቀርቷል።

ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ቢሆንም እንኳ በሚያስተምርበት ጊዜ ለትምህርቱ መሠረት አድርጎ የተጠቀመው መጽሐፍ ቅዱስን እንደነበር ልብ በል። የሰውን ወግ አስበልጦ የአምላክን ቃል በፍጹም ችላ አላለም። (ዮሐንስ 7:16-18) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የነበሩ በርካታ ሃይማኖታዊ መሪዎች እንደ እሱ ለአምላክ ቃል አክብሮት አልነበራቸውም። ለምን? ከቅዱሳን መጻሕፍት ይልቅ ለሰው ወግ የበለጠ ቦታ ይሰጡ ስለነበር ነው። ኢየሱስ ለእነዚህ የሃይማኖት መሪዎች እንደሚከተለው በማለት በግልጽ ነግሯቸዋል፦ “ለወጋችሁ ብላችሁ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ። እናንት ግብዞች፤ ኢሳይያስ ስለ እናንተ እንዲህ ብሎ በትንቢት የተናገረው ትክክል ነው፤ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ በከንቱ ያመልኩኛል፣ ትምህርታቸውም የሰው ሥርዓት ነው።’”—ማቴዎስ 15:6-9 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ሃይማኖቶች ክርስቲያን የሆኑትም ሆኑ ያልሆኑት ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት እንዳላቸው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ የሰዎች ወግ በአምላክ  ቃል ውስጥ ከሚገኘው ንጹሕ ትምህርት ጋር በሚጋጭበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ደግፈው የሚቆሙ ምን ያህል ሃይማኖቶች ታውቃለህ? እስቲ ሁለት ምሳሌዎችን ብቻ እንመልከት።

ርዕሰ ጉዳይ፦ ሃይማኖታዊ የማዕረግ ስሞች።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል?

ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን ሃይማኖታዊ መሪዎች በማዕረግ ስሞች የመጠራትና ታዋቂ የመሆን ፍላጎት እንደነበራቸው በመመልከቱ አውግዟቸዋል። ኢየሱስ፣ እነዚህ ሰዎች “በምሳም የከበሬታ ስፍራ፣ በምኲራብም የከበሬታ ወንበር፣ በገበያም ሰላምታና፦ መምህር ሆይ መምህር ሆይ ተብለው [መጠራት]” እንደሚወዱ ተናግሯል። ከዚያም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፦ “መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ። አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም፦ አባት ብላችሁ አትጥሩ።”—ማቴዎስ 23:1-10 የ1954 ትርጉም

ጥያቄ፦

አንተ የምታወቃቸው የሃይማኖት መሪዎች በአክብሮት ስም መጠራት እንዲሁም በኅብረተሰቡ ዘንድ ታዋቂ መሆን ይፈልጋሉ? ወይስ ኢየሱስ የሰጠውን ትእዛዝ በመከተል እንዲህ ከማድረግ ይቆጠባሉ?

ርዕሰ ጉዳይ፦ ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል?

“በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ነገሮች በማናቸውም ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ። አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም።”—ዘፀአት 20:4, 5 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

ሐዋርያው ዮሐንስ “ልጆች ሆይ፣ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ” በማለት ለክርስቲያኖች ጽፏል።—1 ዮሐንስ 5:21 የ1954 ትርጉም

ጥያቄ፦

አንተ የምታውቀው ሃይማኖት ምስሎችንና ጣዖታትን ለአምልኮ እንዳንጠቀም የሚከለክለውን ግልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ያከብራል?

ትክክለኛውን መንገድ ማግኘት ትችላለህ

በዛሬው ጊዜ ሊያሳስቱ የሚችሉ በርካታ ሃይማኖቶች ቢኖሩም ወደ ሕይወት የሚያደርሰውን ትክክለኛውን መንገድ ማግኘት ትችላለህ። “በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ነውር የሌለበት ሃይማኖት” የትኛው እንደሆነ ለይተህ እንድታውቅ የሚያስችሉ በርካታ ምልክቶች አሉ። (ያዕቆብ 1:27 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) በእነዚህ ርዕሶች ላይ የተመለከትናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ወደ እውነተኛው ሃይማኖት የሚመሩህ ምልክቶች ናቸው።

የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ ርዕሶች ውስጥ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጡህ ለምን አትጠይቃቸውም? የሚሰጡህን መልስ በምታገናዝብበት ጊዜ በመጀመሪያ መቶ ዘመን በቤርያ ከተማ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የተዉትን ግሩም ምሳሌ ተከተል። እነዚህ ሰዎች ሐዋርያው ጳውሎስ ሲሰብክ ከሰሙ በኋላ፦ “የቃሉንም እውነተኝነት ለማረጋገጥ በየቀኑ ቅዱሳት መጻሕፍትን ይመረምሩ ነበር።” (የሐዋርያት ሥራ 17:11 የታረመው የ1980 ትርጉም) አንተም ልክ እንደ ቤርያ ሰዎች ለአምላክ ቃል አክብሮት ካለህና ቃሉን በትጋት ካጠናህ ወደ ሕይወት የሚያደርሰውን መንገድ ታገኛለህ። ይሁን እንጂ ወደ ሕይወት በሚያደርሰው መንገድ ላይ መሄድ አለመሄዱ ለአንተ የተተወ ምርጫ ነው።

ሰዎች የሚማሩት ነገር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ የሚያበረታታው የትኛው ሃይማኖት ነው?