በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ነሐሴ 2009

 ልጆቻችሁን አስተምሩ

ረዓብ ዜናውን ሰምታ ነበር

ረዓብ ዜናውን ሰምታ ነበር

የዛሬ 3,500 ዓመት ገደማ እየኖርን እንዳለ አድርገን እናስብ። መኖሪያችን ያለው በከነዓን ምድር በምትገኘው ኢያሪኮ የተባለች ከተማ ውስጥ ነው። ረዓብ የተባለች አንዲት ልጅም በዚህች ከተማ ውስጥ ትኖራለች። ይህች ልጅ የተወለደችው ሙሴ በባርነት ሥር የነበሩትን እስራኤላውያንን ከግብፅ እየመራ ካወጣቸውና ቀይ ባሕርን ከፍሎ በደረቅ ምድር ካሻገራቸው በኋላ ነበር። በዚያን ወቅት ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን ወይም ኢንተርኔት አልነበረም፤ ያም ሆኖ ረዓብ እሷ ከምትኖርበት በጣም ርቆ በሚገኝ ቦታ ስለተፈጸመው ስለዚህ ተአምር ሰምታ ነበር። ስለ ተአምሩ የሰማችው እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ?— *

ይህን ተአምር አስመልክተው ለረዓብ የነገሯት ከቦታ ቦታ የሚጓዙ ሰዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም። ረዓብ ካደገች በኋላ ይሖዋ ለሕዝቡ ያደረገውን ነገር አልረሳችም። ከዚያም በኋላ ቢሆን ስለ እስራኤላውያን አስገራሚ ነገሮችን ሰምታለች። እስራኤላውያን ለ40 ዓመታት ያህል በምድረ በዳ ከቆዩ በኋላ ወደ ከነዓን ምድር የገቡ ሲሆን እነሱን የሚቃወማቸውን የትኛውንም ሕዝብ ማሸነፍ እንዲችሉ አምላክ እየረዳቸው ነበር። በዚህ ጊዜ ረዓብ፣ እስራኤላውያን ከኢያሪኮ ማዶ በሚገኘው የዮርዳኖስ ወንዝ አቅራቢያ እንደ ሰፈሩ ሰማች!

አንድ ቀን ምሽት ረዓብ የማታውቃቸው ሁለት ሰዎች ትሠራበት ወደነበረው የእንግዳ ማረፊያ ቤት መጡ። እሷም እንዲገቡ ጋበዘቻቸው። ሌሊት ላይ የኢያሪኮ ንጉሥ፣ የእስራኤላውያን ሰላዮች ወደ ከተማዪቱ እንደገቡና ረዓብ በምትሠራበት ቤት እንዳረፉ ሰማ። በዚህም ምክንያት ንጉሡ፣ ረዓብ ወደ ቤቷ የገቡትን ሰዎች አሳልፋ እንድትሰጥ ወደ እሷ መልእክተኞችን ላከ። ረዓብ ሰዎቹን በተመለከተ አስቀድማ የተረዳችው ነገር ምን እንደሆነና ምን እርምጃ እንደወሰደች ታውቃለህ?—

ረዓብ የንጉሡ መልእክተኞች ወደ እሷ ከመምጣታቸው በፊት እንግዶቹ እስራኤላውያን ሰላዮች እንደሆኑ አውቃ ነበር። ሰላዮቹን ጣሪያ ሥር ከደበቀቻቸው በኋላ ለንጉሡ መልእክተኞች “በእርግጥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጥተዋል፤ . . . ጨልሞ የቅጥሩ በር ከመዘጋቱ በፊት ወጥተው ሄደዋል” በማለት መልስ ሰጠቻቸው። ከዚያም “ፈጥናችሁ ተከታተሏቸው” አለቻቸው።

ረዓብ ሰላዮቹን በጠላቶቻቸው ከመያዝ ያዳነቻቸው ለምን ይመስልሃል?— ይህን ያደረገችበትን ምክንያት ለሰላዮቹ ስትነግራቸው እንዲህ ብላለች፦ ‘እግዚአብሔር ይህችን ምድር እንደሰጣችሁ ዐውቃለሁ። ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር ቀይ ባሕርን በፊታችሁ እንዴት እንዳደረቀ  ሰምተናል።’ ረዓብ እስራኤላውያን በጠላቶቻቸው ላይ ድል እንዲቀዳጁ አምላክ ያደረገላቸውን ሌሎች ነገሮችም ሰምታ ነበር።

ረዓብ ሰላዮቹ ጥቃት እንዳይደርስባቸው መከላከሏ ይሖዋን እንዳስደሰተው በዕብራውያን 11:31 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ መረዳት እንችላለን። ሰላዮቹን እንደሚከተለው በማለት በለመነቻቸው ጊዜም ይሖዋ ተደስቶባታል፦ ‘እኔ በጎነትን እንዳሳየኋችሁ ሁሉ፣ እናንተም ኢያሪኮን በምትይዙበት ወቅት የአባቴንና የእናቴን፣ የወንድሞቼንና የእኅቶቼን ነፍስ እንደምታተርፉልኝ ማሉልኝ።’ ሰላዮቹም የሚሰጧትን መመሪያዎች ከተከተለች ያለቻቸውን እንደሚፈጽሙላት ቃል ገቡላት። እነዚህ መመሪያዎች ምን እንደሆኑ ታውቃለህ?—

ሰላዮቹ ‘ይህን ቀይ ፈትል በመስኮት ላይ አስረሽ ካንጠለጠልሽውና ቤተ ሰዎችሽን ሁሉ ወደ ቤትሽ ካመጣሻቸው ሁሉም ይተርፋሉ’ አሏት። ረዓብም ልክ ሰላዮቹ እንደነገሯት አደረገች። ከዚያ በኋላ ምን እንደተፈጸመ ታውቃለህ?—

እስራኤላውያን ከኢያሪኮ ቅጥር ውጪ ሰፈሩ። ከዚያም ለስድስት ቀናት ያህል በቀን አንድ ጊዜ ከተማዪቱን የዞሯት ሲሆን በዚህ ወቅት ምንም ድምፅ አላሰሙም ነበር። በሰባተኛው ቀን ከተማይቱን ሰባት ጊዜ የዞሯት ከመሆኑም ሌላ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ጮኹ። በዚህ ወቅት ቀይ ፈትል በመስኮቱ ላይ ከተንጠለጠለበት ከግንቡ ጋር የተያያዘ ቤት በቀር የከተማይቱ ቅጥር ፈረሰ! ረዓብና ቤተሰቦቿ ግን ከጥፋት ተረፉ።—ኢያሱ 2:1-24፤ 6:1-5, 14, 15, 20-25

ረዓብ ካደረገችው ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን?— ረዓብ፣ አምላክ ሕዝቦቹን ለማዳን ስላደረጋቸው ነገሮች የሚናገሩ ዜናዎችን በመስማት ብቻ ሳትወሰን ሕዝቦቹን ከጉዳት ለመጠበቅ የሚያስችላትን አጋጣሚ ስታገኝ ረድታቸዋለች። አዎን፣ ረዓብ ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር በመሆን እሱን ለማገልገል መርጣለች! አንተስ እንዲህ ታደርጋለህ?— እንዲህ ማድረግ እንድትችል እንጸልያለን።

^ စာပိုဒ်၊ 3 ይህን ርዕስ የምታነበው ከትንሽ ልጅ ጋር ከሆነ ይህ ሰረዝ ቆም ብለህ ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ እንድታበረታታው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።