በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ሁሉም ሃይማኖቶች ጥሩ ናቸው?

ሁሉም ሃይማኖቶች ጥሩ ናቸው?

የምንኖረው ሃይማኖቶች እንደ አሸን በበዙበት ዓለም ውስጥ ነው። በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በዓለም ዙሪያ 19 ዋና ዋና ሃይማኖቶችና 10,000 የሚያህሉ ትንንሽ ሃይማኖታዊ ቡድኖች አሉ። ይህም ሰዎች በሃይማኖት ረገድ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ብዙ ምርጫ እንዲኖራቸው አድርጓል። ታዲያ የትኛውንም ሃይማኖት ብትመርጥ ልዩነት የለውም ማለት ነው?

አንዳንድ ሰዎች እነዚህ ሃይማኖቶች ወደ አንድ ተራራ ጫፍ እንደሚያደርሱ የተለያዩ መንገዶች እንደሆኑ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች ሁሉም መንገዶች ወደ አንድ ቦታ የሚያደርሱ ናቸው ብለው ስለሚያምኑ የትኛውንም መንገድ ቢመርጡ ልዩነት እንደሌለው ይሰማቸዋል። እንዲሁም ሁሉን ቻይ የሆነ አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ በመግለጽ ሁሉም ሃይማኖቶች ዞሮ ዞሮ ወደ እሱ የሚያደርሱ እንደሆኑ ይናገራሉ።

ሁሉም መንገዶች ወደ አምላክ የሚያደርሱ ናቸው?

በታሪክ ዘመናት ውስጥ ከፍተኛ አክብሮት ካተረፉት ሃማኖታዊ አስተማሪዎች መካከል አንዱ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን በሚመለከት ምን ብሏል? ደቀ መዛሙርቱን “በጠባቡ በር ግቡ” ብሏቸዋል። እንዲህ ያላቸው ለምንድን ነው? “ወደ ጥፋት የሚወስደው መንገድ ትልቅ፣ በሩም ሰፊ ነውና፤ ብዙዎችም በዚያ ይገባሉ። ወደ ሕይወት የሚያደርሰው ግን መንገዱ ቀጭን፣ በሩም ጠባብ ነው፤ የሚገቡበትም ጥቂቶች ብቻ ናቸው።”—ማቴዎስ 7:13, 14 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

ኢየሱስ ይህን ሲል አንዳንድ ሃይማኖቶች “ወደ ጥፋት” የሚያደርሱ ናቸው ማለቱ ነበር? ወይስ በአምላክ የማያምኑ ሰዎች በሰፊው መንገድ ላይ እንደሚጓዙ፣ በአምላክ የሚያምኑ ሰዎች ደግሞ ሃይማኖታቸው ምንም ይሁን ምን ወደ ሕይወት በሚያደርሰው ቀጭን መንገድ ላይ እንደሚገኙ ማስተማሩ ነበር?

ኢየሱስ ሁለት መንገዶች ብቻ እንዳሉ ከገለጸ በኋላ “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:15 የ1954 ትርጉም) ከዚያም እንዲህ አለ፦ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፣ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።” (ማቴዎስ 7:21 የ1954 ትርጉም) አንድ ሰው  ነቢይ ከተባለ ወይም ኢየሱስ ‘ጌታው’ እንደሆነ አድርጎ የሚናገር ከሆነ ይህ ሰው በአምላክ የማያምን ሳይሆን ሃይማኖተኛ ሰው ነው ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው። ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ ሁሉም ሃይማኖቶች ጥሩ ሊሆኑ እንደማይችሉና በሁሉም የሃይማኖት አስተማሪዎች ላይ እምነት መጣል እንደማይቻል ማስጠንቀቁ ነበር።

ቀጭኑን መንገድ ለይቶ ማወቅ ይቻላል?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ ሰው ትክክለኛውን የሃይማኖት ጎዳና እንዲያገኝ ሊረዳው የሚችል አስተማማኝ መንፈሳዊ ካርታ ነው

ሁሉም መንገዶች ወደ አምላክ የማያደርሱ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ ከሚገኙት በሺህ የሚቆጠሩ መንገዶች መካከል ወደ ሕይወት የሚያደርሰውን ቀጭኑን መንገድ ለይተን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ የሚከተለውን ምሳሌ ተመልከት፦ አንድ ትልቅ ከተማ ውስጥ መንገድ ጠፋብህ እንበል። ከዚያም ሰው ለመጠየቅ አሰብክ። የጠየቅከው የመጀመሪያው ሰው ወደ ግራ ታጥፈህ ሂድ አለህ፤ ሁለተኛው ሰው ደግሞ ወደ ቀኝ ታጠፍ አለህ። ሦስተኛ ሰው ስትጠይቅ ደግሞ አንተ ደስ ባለህ መንገድ ብትሄድ ልዩነት እንደሌለው ነገረህ። መጨረሻ ላይ ያገኘኸው አንድ ሰው ግን አስተማማኝ የሆነ ካርታ አውጥቶ ትክክለኛውን መንገድ አሳየህ። እንዲያውም መንገዱ እንዳይጠፋብህ ማመሳከር እንድትችል ካርታውን ሰጠህ። ከዚህ በኋላ ያሰብክበት ቦታ እንደምትደርስ እርግጠኛ አትሆንም?

እኛም በተመሳሳይ ጥሩውን ሃይማኖት ለመምረጥ አስተማማኝ የሆነ መንፈሳዊ ካርታ ያስፈልገናል። ለመሆኑ እንዲህ ያለ ካርታ አለ? እንዴታ! ይህ ካርታ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፤ ይህ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ቅዱስ መጽሐፍ በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እርሱ እውነትን ለማስተማር፣ የተሳሳቱትን ለመገሠጽ፣ ስሕተትን ለማረምና ለትክክለኛ ኑሮ የሚበጀውን መመሪያ ለመስጠት ይጠቅማል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16 የ1980 ትርጉም

መንፈሳዊ ካርታ አድርገህ ልትጠቀምበት የምትችል በራስህ ቋንቋ የተተረጎመ መጽሐፍ ቅዱስ ሊኖርህ እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። የዚህ መጽሔት አዘጋጆች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም የተባለ አስተማማኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በአማርኛ ቋንቋ አዘጋጅተዋል። ይሁንና የይሖዋ ምሥክር ካልሆንክ ጥሩውን ሃይማኖት ከመጥፎው ለይቶ ለማወቅ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ለመጠቀም ትፈልግ ይሆናል። በመሆኑም በዚህ ተከታታይ ርዕስ ውስጥ በሌሎች ሃይማኖቶች ዘንድ በስፋት ተቀባይነት ያገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ተጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን ርዕሶች በምታነብበት ጊዜ ከዚህ በፊት የምታወቀውን ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ከሚለው ጋር አወዳድር። ኢየሱስ ጥሩውን ሃይማኖት ከመጥፎው የምንለይበትን መንገድ በተመለከተ የተናገረውን ሐሳብ አስታውስ። እንዲህ ብሏል፦ “ጥሩ ዛፍ ሁሉ ጥሩ ፍሬ፣ መጥፎ ዛፍ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል። ጥሩ ዛፍ መጥፎ ፍሬ፣ መጥፎም ዛፍ ጥሩ ፍሬ ማፍራት አይችልም።” (ማቴዎስ 7:17, 18 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጥሩውን ዛፍ’ ለይቶ ለማወቅ ያስችላሉ ብሎ የሚጠቅሳቸውን ሦስት ጥሩ ፍሬዎች እንመልከት።