ምናልባት በአካባቢህ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በኩል ስታልፍ ‘በውስጡ የሚካሄደው ምን ይሆን?’ ብለህ ጠይቀህ ይሆናል። በሳምንታዊ ስብሰባዎቻቸው ላይ ማንኛውም ሰው መገኘት እንደሚችል ታውቅ ነበር? እንግዶች በሚመጡበት ጊዜ ጥሩ አቀባበል ይደረግላቸዋል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ጥያቄዎች ይኖሩህ ይሆናል። የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ላይ የሚሰበሰቡት ለምንድን ነው? በስብሰባዎቹ ላይ የሚከናወነው ምንድን ነው? የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ እንግዶች ስለ ስብሰባዎቹ ምን ይላሉ?

‘ሕዝቡን ሰብስብ’

ከጥንት ጊዜ አንስቶ ሰዎች አምላክን ለማምለክና ስለ እሱ ለመማር አንድ ላይ ይሰበሰቡ ነበር። ከዛሬ 3,500 ዓመታት ገደማ በፊት እስራኤላውያን እንዲህ ተብለው ነበር፦ “ይሰሙና አምላካችሁን እግዚአብሔርን መፍራት ይማሩ ዘንድ፣ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ በጥንቃቄ እንዲከተሉ ሕዝቡን ይኸውም ወንዶችን፣ ሴቶችን፣ ልጆችንና በከተሞችህ የሚኖረውንም መጻተኛ ሰብስብ።” (ዘዳግም 31:12) በመሆኑም በእስራኤል የሚኖሩ ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች ይሖዋ አምላክን ማምለክና መታዘዝ የሚችሉበትን መንገድ በተመለከተ ትምህርት ይሰጣቸው ነበር።

ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ የክርስቲያን ጉባኤ በተቋቋመ ጊዜ ስብሰባዎች የእውነተኛው አምልኮ አቢይ ክፍል መሆናቸው ቀጥሎ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት አንድ ላይ መሰብሰባችንን ቸል አንበል።” (ዕብራውያን 10:24, 25) የቤተሰብ አባላት አንድ ላይ ሆነው ጊዜ ሲያሳልፉ በቤተሰቡ መካከል ያለው ትስስር እንደሚጠናከር ሁሉ አምላክን ማገልገል የሚፈልጉ ክርስቲያኖችም ለአምልኮ አንድ ላይ በሚሰበሰቡበት ጊዜ በመካከላቸው ያለው ፍቅር ይጠናከራል።

የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ክንውኖች መሠረት በማድረግ በሳምንት ሁለት ጊዜ በመንግሥት አዳራሻቸው ውስጥ ይሰበሰባሉ። በዚያ የሚቀርቡት ትምህርቶች በስብሰባው ላይ የተገኙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች እንዲገነዘቡ፣ እንዲረዱና ተግባራዊ እንዲያደርጉ ይረዷቸዋል። በተቻለ መጠን በዓለም ዙሪያ ተመሳሳይ መንፈሳዊ ትምህርት የሚቀርብ ሲሆን እያንዳንዱ ስብሰባም ራሱን የቻለ ዓላማ አለው። በስብሰባው ላይ የተገኙ ሁሉ ከስብሰባዎቹ በፊትና በኋላ የሚያንጽ ጭውውት በማድረግ ‘እርስ በርስ ይበረታታሉ።’ (ሮም 1:12) ለመሆኑ በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ የሚከናወነው ምንድን ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ንግግር

በአብዛኛው አዲሶች ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገኙት ለሕዝብ ተብሎ በሚዘጋጀው ስብሰባ ላይ ነው። ይህ ስብሰባ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ንግግር የሚቀርብበት ሲሆን ብዙውን ጊዜ ቅዳሜ ወይም እሁድ ላይ ይካሄዳል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕዝብ ንግግር የሰጠባቸው በርካታ ወቅቶች ነበሩ፤ ከእነዚህም መካከል በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው የተራራው ስብከት ይገኝበታል። (ማቴዎስ 5:1፤ 7:28, 29) ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ በአቴና ለሚኖሩ ሰዎች ንግግር አቅርቦ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 17:22-34) የይሖዋ ምሥክሮች ይህን አርዓያ በመከተል ለሁሉም ሰው ተብሎ የተዘጋጀ ንግግር የሚቀርብበት ስብሰባ ያደርጋሉ፤ በዚያ ከሚገኙት መካከል አንዳንዶቹ በስብሰባው ላይ ሲገኙ የመጀመሪያቸው ሊሆን ይችላል።

ስብሰባው የሚጀመረው ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ * ከተባለው ቡክሌት ላይ አንድ መዝሙር በመዘመር ይሆናል። ፈቃደኛ የሆኑ ሁሉ ቆመው መዝሙሩን በጋራ እንዲዘምሩ ይጋበዛሉ። አጭር ጸሎት ከቀረበ በኋላ ጥሩ የማስተማር ችሎታ ያለው አንድ ተናጋሪ የ30 ደቂቃ ንግግር ያቀርባል። ( “ለሕዝብ የሚቀርቡ ጠቃሚ ንግግሮች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ንግግሩ ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነው። ተናጋሪው አድማጮች ለንግግሩ ድጋፍ የሚሰጡትን ጥቅሶች እንዲያወጡና በሚነበቡበት ጊዜ እንዲከታተሉ ይጋብዛል። ስለዚህ የራስህን መጽሐፍ ቅዱስ ይዘህ መምጣት ወይም ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት አንድ ቅጂ እንዲሰጡህ የይሖዋ ምሥክሮችን መጠየቅ ትችላለህ።

የመጠበቂያ ግንብ ጥናት

በአብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ከሕዝብ ንግግር በኋላ በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕስ ላይ በጥያቄና  መልስ ውይይት የሚደረግበት አንድ ሰዓት የሚፈጅ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ይካሄዳል። በዚህ ስብሰባ ላይ የሚገኙ ሁሉ ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጉጉት የተቀበሉትን’ በጳውሎስ ዘመን የነበሩትን የቤርያ ሰዎች ምሳሌ እንዲከተሉ ማበረታቻ ይሰጣቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 17:11

የመጠበቂያ ግንብ ጥናት የሚጀመረው በመዝሙር ነው። የሚብራራው ትምህርትም ሆነ ጥናቱን የሚመራው ሰው የሚያቀርባቸው ጥያቄዎች በመጠበቂያ ግንብ መጽሔት የጥናት እትም ላይ ይወጣሉ። የዚህን የጥናት እትም ቅጂ ለማግኘት በስብሰባው ላይ ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች አንዱን ልትጠይቅ ትችላለህ። በቅርቡ ከተጠኑት ርዕሰ ጉዳዮች መካከል “እናንት ወላጆች፣ ልጆቻችሁን በፍቅር አሠልጥኗቸው፣” “ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ” እንዲሁም “መከራና ሥቃይ ሁሉ በቅርቡ ይወገዳል” የሚሉት ይገኙበታል። ስብሰባው የሚካሄደው በጥያቄና መልስ ቢሆንም እንኳ አድማጮች ተሳትፎ የሚያደርጉት በፈቃደኝነት ነው። አብዛኛውን ጊዜ ሐሳብ የሚሰጡት ትምህርቱንም ሆነ ድጋፍ ሆነው የቀረቡትን ጥቅሶች አስቀድመው ያነበቡና ያሰላሰሉበት ሰዎች ናቸው። ስብሰባው የሚደመደመው በመዝሙርና በጸሎት ነው።—ማቴዎስ 26:30፤ ኤፌሶን 5:19

የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

የይሖዋ ምሥክሮች በየሳምንቱ አንድ ቀን ምሽት ላይ በድምሩ 1 ሰዓት ከ45 ደቂቃ የሚፈጅ ሦስት ክፍሎች ያሉት ፕሮግራም ለማካሄድ በመንግሥት አዳራሽ እንደገና ይሰበሰባሉ። የስብሰባው የመጀመሪያ ክፍል የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲሆን ስብሰባው 25 ደቂቃ ይወስዳል። ይህ ስብሰባ በዚያ የተገኙት ሰዎች ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱሳቸው ጋር ይበልጥ እንዲተዋወቁ፣ አስተሳሰባቸውንና አመለካከታቸውን እንዲያስተካክሉ እንዲሁም የተሻሉ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) እንደ መጠበቂያ ግንብ ጥናት ሁሉ ይህም ስብሰባ በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተመሥርቶ በጥያቄና መልስ በሚደረግ ውይይት ይካሄዳል። ተሰብሳቢዎች ሐሳብ የሚሰጡት በፈቃደኝነት ነው። በአብዛኛው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት  የሚያገለግለው ጽሑፍ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ወይም ብሮሹር ነው።

በዚህ ስብሰባ ወቅት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ጽሑፍ የምንጠቀመው ለምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የአምላክን ቃል ማንበብ ብቻውን በቂ አልነበረም። “ሕዝቡ የሚነበበውን መረዳት እንዲችሉ ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ካነበቡላቸው በኋላ ይተረጕሙላቸውና ይተነትኑላቸው ነበር።” (ነህምያ 8:8) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢሳይያስን፣ የዳንኤልንና የራእይን መጽሐፍ የሚያብራሩ ጽሑፎች መጠናታቸው በዚህ ስብሰባ ላይ የተገኙ ሰዎች እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንዲረዱ አስችሏቸዋል።

ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት

ከጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቀጥሎ የሚደረገው ስብሰባ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ነው። ይህ የ30 ደቂቃ ስብሰባ ክርስቲያኖች ‘የማስተማር ጥበብ’ እንዲያዳብሩ ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 4:2) ለምሳሌ ያህል፣ ልጅህ ወይም ጓደኛህ ስለ አምላክ ወይም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄ ጠይቆህ ጥሩ መልስ መስጠት የከበደህ ጊዜ ነበር? ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከባድ ለሆኑ ጥያቄዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ እምነት የሚገነቡ መልሶች እንዴት መስጠት እንደምትችል ያሠለጥንሃል። በመሆኑም እኛም እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ “ልዑል እግዚአብሔር የተባ አንደበት ሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ደካሞችን ብርቱ ለማድረግ ምን ማለት እንዳለብኝ ዐውቃለሁ” ማለት እንችላለን።—ኢሳይያስ 50:4

ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የሚጀምረው በተወሰነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተመሥርቶ በሚቀርብ ንግግር ሲሆን በስብሰባው ላይ የተገኙት ሰዎች ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አንብበው እንዲመጡ ከሳምንት በፊት ማበረታቻ ይሰጣቸዋል። ተናጋሪው ንግግሩን ከጨረሰ በኋላ አድማጮች ካነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ያገኙትን ጠቃሚ ሐሳብ በአጭሩ እንዲገልጹ ይጋብዛቸዋል። ይህ ክፍል ከቀረበ በኋላ በትምህርት ቤቱ የተመዘገቡ ተማሪዎች የተመደበላቸውን ክፍል ያቀርባሉ።

ተማሪዎች መድረክ ላይ ወጥተው የተመደበላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በንባብ ያቀርባሉ ወይም አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳይ ለሌላ ሰው እንዴት ማስተማር እንደሚችሉ በሠርቶ ማሳያ መልክ ያቀርባሉ። እያንዳንዱ ክፍል ከቀረበ በኋላ ጥሩ ልምድ ያለው አንድ ምክር ሰጪ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም በተባለው መጽሐፍ ላይ ተመሥርቶ ተማሪው የሠራበትን ጥሩ ነጥብ በመጥቀስ ያመሰግነዋል።  በኋላም ሁለቱ ለብቻቸው ሆነው ተማሪው በምን ነጥቦች ላይ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለበት ሐሳብ ሊሰጠው ይችላል።

የአድማጮችን ትኩረት እንደሳበ በፍጥነት የሚያልቀው ይህ ስብሰባ፣ ክፍል የሚያቀርቡትን ብቻ ሳይሆን በንባብ፣ ንግግር በማቅረብና በማስተማር ችሎታቸው ረገድ ማሻሻል የሚፈልጉ በስብሰባው ላይ የተገኙትን ሁሉ ለመርዳት የተዘጋጀ ነው። ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ካበቃ በኋላ የአገልግሎት ስብሰባ የሚጀምረው በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ የተመሠረተ አንድ መዝሙር በመዘመር ይሆናል።

የአገልግሎት ስብሰባ

የፕሮግራሙ የመጨረሻ ክፍል የአገልግሎት ስብሰባ ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ በሚቀርቡት ንግግሮች፣ ሠርቶ ማሳያዎች፣ ቃለ ምልልሶችና አድማጮች በሚሰጡት ሐሳብ አማካኝነት በስብሰባው ላይ የተገኙ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት ማስተማር እንዳለባቸው ይማራሉ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለስብከት ከመላኩ በፊት አንድ ላይ ሰብስቦ ዝርዝር መመሪያ ሰጥቷቸዋል። (ሉቃስ 10:1-16) ለወንጌላዊነቱ ሥራ በሚገባ ተዘጋጅተው ስለነበር ብዙ አስደሳች ተሞክሮዎች ማግኘት ችለዋል። የኢየሱስ ተከታዮች ከስብከት ከተመለሱ በኋላ ያጋጠማቸውን ነገር ነገሩት። (ሉቃስ 10:17) ደቀ መዛሙርቱ ያጋጠሟቸውን ተሞክሮዎች አንዳቸው ለሌላው የማካፈል ልማድ ነበራቸው።—የሐዋርያት ሥራ 4:23፤ 15:4

በአገልግሎት ስብሰባ ላይ የሚቀርበው የ35 ደቂቃ ፕሮግራም በየወሩ በሚታተም የመንግሥት አገልግሎታችን በሚባል ጽሑፍ ላይ ይወጣል። በቅርብ ጊዜ ከቀረቡት ትምህርቶች መካከል “ይሖዋን በቤተሰብ ደረጃ ማምለክ፣” “በተደጋጋሚ የምንሄደው ለምንድን ነው?” እና “በአገልግሎታችሁ ክርስቶስን ምሰሉ” የሚሉት ይገኙበታል። ፕሮግራሙ የሚደመደመው በመዝሙር እንዲሁም አስቀድሞ የተመደበ አንድ የጉባኤው አባል በሚያቀርበው ጸሎት ነው።

እንግዶች የሰጡት አስተያየት

የጉባኤ አባላት ማንም ሰው ባይተዋርነት እንዳይሰማው ጥረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ አንድሩ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙ መጥፎ ነገሮች ሰምቶ ነበር። ሆኖም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስብሰባ ሲመጣ በተደረገለት አቀባበል በጣም ተደነቀ። አንድሩ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “በስብሰባው ላይ መገኘት በጣም ያስደስታል። ሰዎቹ በቀላሉ የሚቀረቡ መሆናቸውና ለእኔ ያሳዩኝ አሳቢነት በጣም ገርሞኝ ነበር።” በካናዳ የምትኖረው በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኘው አሸል በሐሳቡ በመስማማት “ስብሰባው ደስ የሚል ነበር! በትኩረት ለመከታተልም አያስቸግርም” ብላለች።

በብራዚል የሚኖረው ዡዜ በሚኖርበት አካባቢ በኃይለኝነቱ የሚታወቅ ሰው ነበር። ያም ሆኖ በአካባቢው በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ በሚደረግ ስብሰባ ላይ እንዲገኝ ተጋበዘ። “የድሮ ባሕርዬን የሚያውቁ ቢሆኑም እንኳ በመንግሥት አዳራሹ የነበሩት ሰዎች ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልኝ” ሲል ተናግሯል። በጃፓን የምትኖረው አጹሺ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “እውነቱን ለመናገር ለመጀመሪያ ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ስገኝ ትንሽ ከብዶኝ ነበር። ይሁንና እነዚህ ሰዎች እንደማንኛውም ዓይነት ሰው መሆናቸውን ተገነዘብኩ። እነሱም እንግድነት እንዳይሰማኝ ከልብ ጥረት አድርገዋል።”

ስብሰባችን ላይ ብትገኝ ደስ ይለናል

ከላይ የተጠቀሱት አስተያየቶች እንደሚያሳዩት በመንግሥት አዳራሽ በሚካሄዱት ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጥቅም እንደሚያስገኝልህ አያጠራጥርም። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ስለ አምላክ ትማራለህ፤ ደግሞም እዚያ በምታገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት አማካኝነት ይሖዋ አምላክ “የሚበጅህ” ምን እንደሆነ ያስተምርሃል።—ኢሳይያስ 48:17

የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ክፍያ አይጠየቅም፤ በስብሰባው ወቅትም መዋጮ አይሰበሰብም። በአካባቢህ በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚደረግ ስብሰባ ላይ መገኘት ትፈልጋለህ? እንግዲያው በአክብሮት ተጋብዘሃል።

^ አን.10 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ጽሑፎች በሙሉ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ናቸው።