በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ኅዳር 2008

 ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?

የጋብቻ ቃል ኪዳንን አክብሮ መኖር

የጋብቻ ቃል ኪዳንን አክብሮ መኖር

ሚስት፦ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባለቤቴ ማይክል ለእኔ ያለው ስሜት እየቀዘቀዘ መሄዱንና ልጆቻችንንም እንደ በፊቱ ሞቅ ባለ መንፈስ እንደማያነጋግራቸው አስተዋልኩ። * ባሕርይው መለወጥ የጀመረው ቤታችን ኢንተርኔት ካስገባን በኋላ ስለነበር የብልግና ምስሎች ያሉባቸውን ድረ ገጾች እያየ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ጀመርኩ። አንድ ቀን ምሽት ልጆቹ ከተኙ በኋላ ስለ ሁኔታው በግልጽ እንዲነግረኝ ጠየቅሁት። እሱም የብልግና ምስሎች ያሉባቸውን ድረ ገጾች እንደሚመለከት ሳይደብቅ ነገረኝ። በጣም አዘንኩ። እንዲህ ዓይነቱ ነገር ይደርስብኛል ብዬ በፍጹም አልጠበቅሁም። በእሱ ላይ ያለኝ እምነት ሙሉ በሙሉ ጠፋ። ይባስ ብሎ አንድ የሥራ ባልደረባዬ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለእኔ የፍቅር ስሜት ማሳየት ጀምሯል።”

ባል፦ “ከጥቂት ጊዜ በፊት ባለቤቴ ማሪያ በኮምፒውተራችን ውስጥ ያስቀመጥኩትን አንድ ፎቶግራፍ ተመልክታ ስለ ሁኔታው ጠየቀችኝ። የብልግና ምስሎች ያሉባቸውን ድረ ገጾች የማየት ልማድ እንዳለኝ በግልጽ ስነግራት በጣም ተበሳጨች። በዚህ ጊዜ በጣም አፈርኩ፤ እንዲሁም በደለኛ እንደሆንኩ ተሰማኝ። ትዳራችን ያበቃለት መሰለኝ።”

የማይክልና የማሪያ ችግር ምን ነበር? የማይክል ዋነኛ ችግር የብልግና ምስሎችን መመልከቱ ነው ብለህ ታስብ ይሆናል። ይሁንና ማይክልም ውሎ አድሮ እንደተገነዘበው፣ ይህ ድርጊቱ ትዳራቸው ከዚያ የበለጠ ችግር እንዳለበት ይኸውም ማይክል ለጋብቻ ቃል ኪዳኑ የነበረው አክብሮት እየቀነሰ እንደመጣ የሚያሳይ ነበር። * ማይክልና ማሪያ በተጋቡበት ወቅት ፍቅርና ደስታ የሞላበት ሕይወት እንደሚያሳልፉ ታይቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ ብዙ ባለትዳሮች እንደሚያጋጥማቸው ሁሉ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን አክብረው ለመኖር ያላቸው ቁርጠኝነት የተዳከመ ከመሆኑም በላይ ቀስ በቀስ እየተራራቁ መጡ።

ጊዜ እያለፈ ሲሄድ አንተና የትዳር ጓደኛህ እየተራራቃችሁ እንደመጣችሁ ይሰማሃል? በመካከላችሁ ያለው ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር ማድረግ ትፈልጋለህ? ከሆነ ለሚከተሉት ሦስት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ይኖርብሃል፦ የጋብቻ ቃል ኪዳንን አክብሮ መኖር ሲባል ምን ማለት ነው? የጋብቻ ቃል ኪዳንህን አክብረህ ለመኖር የምታደርገውን ጥረት ምን ሊያዳክምብህ ይችላል? ከትዳር ጓደኛህ ጋር የመሠረትከውን ዝምድና ይበልጥ ለማጠናከር ምን ማድረግ ትችላለህ?

የጋብቻ ቃል ኪዳንን አክብሮ መኖር ሲባል ምን ማለት ነው?

የጋብቻ ቃል ኪዳንን አክብሮ መኖር ሲባል ምን ማለት ይመስልሃል? ብዙዎች፣ አንድ ሰው የጋብቻ ቃል ኪዳኑን አክብሮ የሚኖረው እንዲህ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት የሚሰማው ከሆነ ነው ብለው ያስባሉ። ለምሳሌ ያህል፣  አንድ ባልና ሚስት ለልጆቻቸው ሲሉ ወይም የጋብቻ መሥራች የሆነው አምላክ እንደሚጠብቅባቸው ስለሚሰማቸው ብቻ የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን አክብረው ለመኖር ጥረት ያደርጉ ይሆናል። (ዘፍጥረት 2:22-24) እነዚህ ሰዎች እንዲህ ብለው ማሰባቸው ተገቢ ከመሆኑም በላይ በትዳር ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች በጽናት ለማለፍ እንደሚረዳቸው ግልጽ ነው። ይሁንና ትዳራቸው ደስታ የሰፈነበት እንዲሆን ከተፈለገ አንዳቸው ለሌላው ያለባቸውን ግዴታ ከማሰብ የበለጠ ነገር ማድረግ ያስፈልጋቸዋል።

ይሖዋ አምላክ የጋብቻን ዝግጅት ያቋቋመው ከፍተኛ ደስታና እርካታ የሚያስገኝ እንዲሆን በማሰብ ነው። የአምላክ ዓላማ፣ ባል ‘በሚስቱ እንዲደሰት’ እንዲሁም ሚስት ባሏን እንድትወድና ባሏም እንደ ገዛ ሥጋው አድርጎ እንደሚወዳት እንዲሰማት ነበር። (ምሳሌ 5:18፤ ኤፌሶን 5:28) በባልና ሚስት መካከል እንዲህ ያለ ቅርርብ እንዲፈጠር እርስ በርስ መተማመን አለባቸው። የዕድሜ ልክ ጓደኝነት መመሥረታቸውም የዚያኑ ያህል አስፈላጊ ነው። ባልና ሚስት አንዳቸው የሌላውን አመኔታ ለማትረፍና የልብ ወዳጆች ለመሆን ጥረት ካደረጉ የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን አክብረው ለመኖር ያላቸው ቁርጠኝነት ይበልጥ ይጠናከራል። እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “አንድ ሥጋ” የሆኑ ያህል በጣም ይቀራረባሉ።—ማቴዎስ 19:5

በመሆኑም የጋብቻ ቃል ኪዳንን አክብሮ ለመኖር የሚደረገው ጥረት ጠንካራ ቤት የተገነባባቸውን ብሎኬቶች ለማያያዝ ከሚያገለግል የሲሚንቶ ቡኬት ጋር ይመሳሰላል። ቡኬቱ የሚዘጋጀው አሸዋ፣ ሲሚንቶና ውኃ በመደባለቅ ነው። በተመሳሳይም ባልና ሚስት የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን አክብረው ለመኖር የሚነሳሱት እንዲህ የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው ሲሰማቸው፣ እርስ በርስ ሲተማመኑና የልብ ጓደኛሞች ሲሆኑ ነው። ይሁን እንጂ የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን አክብረው ለመኖር የሚያደርጉትን ጥረት ምን ሊያዳክምባቸው ይችላል?

ተፈታታኝ የሚያደርጉት ነገሮች

የጋብቻ ቃል ኪዳንን አክብሮ ለመኖር ጠንክሮ መሥራትና የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ ያስፈልጋል። የትዳር ጓደኛህን ለማስደሰት ከፈለግህ የራስህን ፍላጎት ለመተው ፈቃደኛ መሆን ይኖርብሃል። ይሁንና የሌላውን ሰው ፍላጎት ማስቀደም ማለትም ‘እኔ ምን ጥቅም አገኝበታለሁ?’ ብለው ሳይጠይቁ ለሌሎች መልካም ማድረግ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት የለውም፤ እንዲያውም አንዳንዶች እንዲህ እንዲያደርጉ የሚጠበቅባቸው መሆኑ ያበሳጫቸዋል። እስቲ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ደስታ የሰፈነበት የትዳር ሕይወት ያላቸው ስንት ራስ ወዳድ ሰዎች አውቃለሁ?’ በጣም ጥቂት እንደሚሆኑ አያጠራጥርም፤ ለዚያውም ከተገኙ። ለምን? ራስ ወዳድ የሆነ ሰው የግል ጥቅሙን መሥዋዕት እንዲያደርግ የሚያስገድድ ነገር ሲያጋጥመው በተለይም ላደረገው ትንሽ ነገር ወዲያውኑ የሚያገኘው ጥቅም ከሌለ የጋብቻ ቃል ኪዳኑን አክብሮ መኖር እንደሚቸግረው የታወቀ ነው። አንድ ባልና ሚስት መጀመሪያ ላይ ምንም ያህል ቢዋደዱም የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን አክብረው ለመኖር ጠንክረው ካልሠሩ ግንኙነታቸው መሻከሩ አይቀርም።

የአምላክ ቃል ጋብቻን የተሳካ እንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እንደሚጠይቅ መናገሩ ትክክል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ያገባ ሰው . . . ሚስቱን ደስ ለማሰኘት የዚህን ዓለም ነገር ያስባል፤” እንዲሁም “ያገባች ሴት . . . ባሏን ደስ ለማሰኘት የዚህን ዓለም ነገር ታስባለች” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 7:33, 34) የራስ ወዳድነት ባሕርይ የማይታይባቸው ሰዎች እንኳ አንዳንድ ጊዜ የትዳር ጓደኛቸውን ጭንቀት ላይረዱና የሚከፍለውንም መሥዋዕትነት ላያደንቁ ይችላሉ። የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው ለሌላው አድናቆት የማያሳዩ ከሆነ ደግሞ በትዳር ውስጥ ‘የሚያጋጥማቸው ችግር’ የባሰ ይሆናል።—1 ቆሮንቶስ 7:28

ትዳራችሁ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ እንዲያልፍና በጥሩ ጊዜያት ደግሞ እየተጠናከረ እንዲሄድ ከተፈለገ ጋብቻችሁን ዘላቂ ጥምረት እንደሆነ አድርጋችሁ ልትመለከቱት ይገባል። እንዲህ ዓይነቱን አመለካከት ማዳበር እንዲሁም የትዳር ጓደኛችሁ የጋብቻ ቃል ኪዳኑን አክብሮ ለመኖር ጥረት እንዲያደርግ ወይም እንድታደርግ ማበረታታት የምትችሉት እንዴት ነው?

ከትዳር ጓደኛህ ጋር ያለህን ዝምድና ለማጠናከር ምን ማድረግ ትችላለህ?

ይህን ለማድረግ ቁልፉ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር በትሕትና ተግባራዊ ማድረግ ነው። እንዲህ ማድረግህ ለትዳር ጓደኛህ ብቻ ሳይሆን ለአንተም “የሚበጅ” ነው። (ኢሳይያስ 48:17) ተግባራዊ ልታደርጋቸው የምትችላቸውን ሁለት ነገሮች ተመልከት።

ከትዳር ጓደኛህ ጋር የምታሳልፈው ጊዜ ሊኖርህ ይገባል

1. ለትዳርህ ቅድሚያ ስጥ።

ሐዋርያው ጳውሎስ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]”  በማለት ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 1:10 NW) ባልና ሚስት አንዳቸው ሌላውን የሚይዙበት መንገድ በአምላክ ፊት ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። ሚስቱን የሚያከብር ባል በአምላክ ዘንድ ይከበራል። ባሏን የምታከብር ሚስትም ‘በአምላክ ፊት ዋጋዋ እጅግ የከበረ’ ነው።—1 ጴጥሮስ 3:1-4, 7

ትዳርህን ምን ያህል ከፍ አድርገህ ትመለከተዋለህ? አንድ ነገር በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ከተሰማህ በዚያ ላይ ብዙ ጊዜ እንደምታጠፋ የታወቀ ነው። ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ባለፈው ወር ከትዳር ጓደኛዬ ጋር ምን ያህል ጊዜ አሳልፌያለሁ? ባለቤቴ አሁንም የልብ ጓደኛዬ መሆኗን ለማሳየት ምን ያደረግኩት ነገር አለ?’ ከትዳር ጓደኛህ ጋር ያሳለፍከው ጊዜ ትንሽ ከነበረ ወይም ጭራሹኑ አብራችሁ ጊዜ ካላሳለፋችሁ ባለቤትህ ትዳርህን የምታከብር ሰው መሆንህን ለማመን ልትቸገር ትችላለች።

የትዳር ጓደኛህ ለትዳርህ ማንኛውንም መሥዋዕትነት እንደምትከፍል ይሰማታል? ይህን እንዴት ማወቅ ትችላለህ?

እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ በትንሽ ወረቀት ላይ የሚከተሉትን አምስት ነገሮች ጻፍ፦ ገንዘብ፣ ሥራ፣ ትዳር፣ መዝናኛ እና ጓደኞች። ከዚያም የትዳር ጓደኛህ ቅድሚያ የምትሰጠውን ነገር በማሰብ በቅደም ተከተል ቁጥር ስጣቸው። እሷም ስለ አንተ ተመሳሳይ ነገር እንድታደርግ ጠይቃት። ስትጨርሱ ወረቀቶቹን ተለዋወጡ። የትዳር ጓደኛህ፣ ትዳርህን ለማጠናከር በቂ ጊዜና ጉልበት እንደማታጠፋ የሚሰማት ከሆነ ምን ለውጦችን ማድረግ እንዳለብህ ተወያዩ። በተጨማሪም ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘የትዳር ጓደኛዬ ይበልጥ አስፈላጊ ናቸው ብላ ለምታስባቸው ነገሮች የበለጠ ትኩረት ለመስጠት ምን ማድረግ እችላለሁ?’

ታማኝነትን ማጉደል የሚጀምረው በልብ ውስጥ ነው

2. ለትዳርህ ያለህን ታማኝነት እንድታጓድል ከሚያደርግ ማንኛውም ነገር ራቅ።

ኢየሱስ ክርስቶስ “ሴትን በምኞት ዓይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:28) አንድ ሰው ከትዳር ውጪ የጾታ ግንኙነት መፈጸሙ የጋብቻ ጥምረቱን የሚያናጋ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ድርጊት ለፍቺ መሠረት ሊሆን እንደሚችል ይገልጻል። (ማቴዎስ 5:32) ይሁን እንጂ ኢየሱስ የተናገረው ከላይ ያለው ሐሳብ፣ አንድ ሰው ምንዝር ከመፈጸሙ ከረጅም ጊዜ በፊትም እንኳ መጥፎ ምኞት በልቡ ውስጥ ሊኖር እንደሚችል ይጠቁማል። እንዲህ ዓይነቱን መጥፎ ምኞት ማውጠንጠን በራሱ ታማኝነት ማጉደል ነው።

የጋብቻ ቃል ኪዳንህን አክብረህ ለመኖር እንድትችል የብልግና ምስሎችን ፈጽሞ ላለመመልከት ለራስህ ቃል ግባ። ሰዎች የተለየ አመለካከት ቢኖራቸውም የብልግና ምስሎችን መመልከት የጋብቻ ጥምረትን የሚጎዳ መርዝ ነው። አንዲት ሚስት ባሏ የብልግና ምስሎችን የማየት ልማድ ያለው መሆኑ ምን እንዲሰማት እንዳደረገ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ የብልግና ምስሎችን መመልከት ለፍቅር ሕይወታችን ጣዕም እንደሚጨምር ይናገራል።  ይሁንና ይህ እሱን እንደማላረካው ሆኖ እንዲሰማኝ ስለሚያደርግ ዋጋቢስ እንደሆንኩ ይሰማኛል። እሱ የብልግና ምስሎችን ሲመለከት እኔ ግን እንቅልፍ እስኪወስደኝ ድረስ አነባለሁ።” ይህ ሰው የጋብቻ ቃል ኪዳኑን አክብሮ ለመኖር እየጣረ ነው? ወይስ ትዳሩን እያበላሸ? ሚስቱ ትዳሯን አክባሪ እንድትሆን ሁኔታዎችን ቀላል እያደረገላት ያለ ይመስልሃል? የልብ ወዳጁ አድርጎ እንደሚመለከታትስ ያሳያል?

ታማኙ ኢዮብ ‘ከዓይኑ ጋር ቃል ኪዳን እንደገባ’ በመናገር ለጋብቻ ቃል ኪዳኑና ለአምላኩ ታማኝ ሆኖ መኖር እንደሚፈልግ ገልጿል። ኢዮብ “ወደ ኰረዳዪቱ ላለመመልከት” ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። (ኢዮብ 31:1) ኢዮብን መምሰል የምትችለው እንዴት ነው?

ከብልግና ምስሎች ከመራቅ በተጨማሪ የትዳር ጓደኛህ ካልሆነች ሴት ጋር ተገቢ ያልሆነ ቅርርብ ላለመፍጠር ልብህን መጠበቅ ይኖርብሃል። እውነት ነው፣ ብዙዎች የትዳር ጓደኛ ያልሆነን ሰው ማሽኮርመም በትዳር ላይ ምንም ጉዳት እንደማያስከትል ይሰማቸዋል። ሆኖም የአምላክ ቃል “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም፤ ማንስ ሊረዳው ይችላል?” በማለት ያስጠነቅቀናል። (ኤርምያስ 17:9) በዚህ ጉዳይ ልብህ እያሳተህ ነው? ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ይበልጥ ትኩረት የምሰጠው ለባለቤቴ ነው ወይስ ለሌላ ሴት? አንድ የሚያስደስት ነገር ሲያጋጥመኝ መጀመሪያ የምናገረው ለሚስቴ ነው ወይስ ለሌላ ሰው? ባለቤቴ ከአንዲት ሴት ጋር ያለኝን ግንኙነት ገደብ እንዳበጅለት ብትነግረኝ ምን ይሰማኛል? ይከፋኛል? ወይስ የነገረችኝን ነገር ለማስተካከል ፈቃደኛ እሆናለሁ?’

እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ የትዳር ጓደኛህ ያልሆነች ሴት እንደማረከችህ ከተሰማህ አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር ከእሷ ጋር ላለመገናኘት ጥረት አድርግ። መገናኘት ካለባችሁም ግንኙነታችሁ ማከናወን በሚገባችሁ ጉዳይ ላይ ብቻ ያተኮረ ይሁን። ይህች ሴት ከትዳር ጓደኛህ የተሻለች እንደሆነች በሚሰማህ ነጥቦች ላይ አታተኩር። ከዚህ ይልቅ ባለቤትህ ባላት ጥሩ ባሕርያት ላይ ትኩረት አድርግ። (ምሳሌ 31:29) መጀመሪያ ላይ ሚስትህን እንድትወዳት ያደረገህ ምን እንደሆነ አስብ። ‘እውነት ባለቤቴ አሁን እነዚህ ባሕርያት የሏትም ወይስ እኔ ማየት ተስኖኛል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

ቅድሚያውን ውሰድ

በመግቢያው ላይ የተጠቀሱት ማይክልና ማሪያ ለችግራቸው መፍትሔ ማግኘት እንደሚያስፈልጋቸው ስለተሰማቸው ምክር ለመጠየቅ ወሰኑ። እርግጥ ነው፣ ምክር ለመጠየቅ መፈለጋቸው የመጀመሪያ እርምጃ ብቻ ነው። ይሁንና ችግር እንዳለባቸው አምነው እርዳታ ለማግኘት መፈለጋቸው፣ የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን ለመጠበቅና ትዳራቸውን የተሳካ ለማድረግ ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ መሆናቸውን በግልጽ የሚያሳይ ነው።

ትዳርህ ሰላም የሰፈነበትም ይሁን ችግር ያለበት ባለቤትህ ትዳራችሁን የተሳካ ለማድረግ ጠንክረህ እንደምትሠራ ሊሰማት ይገባል። በዚህ ረገድ የትዳር ጓደኛህን አመኔታ ለማትረፍ የቻልከውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብሃል። እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኛ ነህ?

^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል።

^ አን.5 በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው የብልግና ምስሎችን ስለሚመለከት ወንድ ቢሆንም ተመሳሳይ ድርጊት የምትፈጽም ሴትም ለጋብቻ ቃል ኪዳኗ ያላት አክብሮት መቀነሱን ታሳያለች።

ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ . . .

  • ከትዳር ጓደኛዬ ጋር የበለጠ ጊዜ ለማሳለፍ የትኞቹን ነገሮች መተው አለብኝ?

  • ትዳራችንን የተሳካ ለማድረግ ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ እንደሆንኩ ለባለቤቴ ላረጋግጥላት የምችለው እንዴት ነው?