“ታሞ በአልጋ ላይ ተኝቶ ሳለ ይሖዋ ይደግፈዋል።”—መዝ. 41:3

መዝሙሮች፦ 23, 138

1, 2. አንዳንድ ጊዜ ምን ዓይነት ጥያቄ ይፈጠርብን ይሆናል? በዚህ ጊዜ የትኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች እናስታውሳለን?

‘ከዚህ በሽታ እድን ይሆን?’ ብለህ አስበህ ታውቃለህ? አሊያም የቤተሰብህ አባል ወይም የምትወደው ጓደኛህ ከሕመሙ መዳን አለመዳኑ አሳስቦህ ይሆናል። አንድ ሰው ከባድ የጤና እክል ሲያጋጥመው እንዲህ ብሎ ማሰቡ የተለመደ ነው። በነቢዩ ኤልያስና በነቢዩ ኤልሳዕ ዘመን የነበሩ ሁለት ነገሥታትም ተመሳሳይ ነገር አስጨንቋቸው ነበር። የንጉሥ አክዓብና የኤልዛቤል ልጅ የሆነው ንጉሥ አካዝያስ ወድቆ ከባድ ጉዳት ደርሶበት ስለነበር ‘ከደረሰብኝ ጉዳት እድን እሆን?’ ብሎ ጠይቆ ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የሶርያ ንጉሥ ቤንሃዳድ በጠና በመታመሙ “ከዚህ በሽታ እድናለሁ?” ሲል ጠይቋል።—2 ነገ. 1:2፤ 8:7, 8

2 እርግጥ ነው፣ እኛም ሆንን የምንወዳቸው ሰዎች ስንታመም ሕመሙ እንደሚሻለን ተስፋ እናደርጋለን። ብዙዎች እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ‘አምላክ የሚረዳን እንዴት ነው?’ ብለው ይጠይቃሉ። በእነዚያ ነገሥታት ዘመን አምላክ፣ የሰዎችን ሕይወትና ጤንነት የሚነኩ ተአምራት የፈጸመባቸው ጊዜያት ነበሩ። ይሖዋ በነቢያቱ አማካኝነት የሞቱ ሰዎችንም እንኳ አስነስቷል። (1 ነገ. 17:17-24፤ 2 ነገ. 4:17-20, 32-35) በዘመናችንስ ተመሳሳይ ነገር እንደሚፈጽም ለመጠበቅ የሚያበቃ ምክንያት አለን?

3-5. አምላክና ኢየሱስ ምን ዓይነት ኃይል አላቸው? ይህስ የትኞቹን ጥያቄዎች ያስነሳል?

3 አምላክ የግለሰቦችን ጤንነት የሚነካ እርምጃ መውሰድ እንደሚችል ጥያቄ የለውም። እንዲህ የማድረግ ኃይል እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል።  ለምሳሌ በአብርሃም ዘመን የነበረውን ፈርዖንን እና ከጊዜ በኋላ ደግሞ የሙሴን እህት ሚርያምን እንዲታመሙ በማድረግ ቀጥቷቸዋል። (ዘፍ. 12:17፤ ዘኁ. 12:9, 10፤ 2 ሳሙ. 24:15) እስራኤላውያን ታማኝ ካልሆኑ “በሽታዎችን ወይም መቅሰፍቶችን ሁሉ” በማምጣት እንደሚቀጣቸው አምላክ አስጠንቅቋቸው ነበር። (ዘዳ. 28:58-61) በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ በሽታን ማስወገድ ወይም ሕዝቡ እንዳይታመሙ ጥበቃ ማድረግ ይችላል። (ዘፀ. 23:25፤ ዘዳ. 7:15) በተጨማሪም ሰዎችን መፈወስ ይችላል። ኢዮብ ሞትን እስኪመኝ ድረስ በጠና ታሞ የነበረ ቢሆንም አምላክ ፈውሶታል!—ኢዮብ 2:7፤ 3:11-13፤ 42:10, 16

4 አምላክ የታመመን ሰው የመፈወስ ኃይል እንዳለው ጥርጥር የለውም። ልጁም ተመሳሳይ ኃይል አለው። ኢየሱስ የሥጋ ደዌ ወይም የሚጥል በሽታ ያለባቸውን እንዲሁም ዓይነ ስውር አሊያም ሽባ የሆኑ ሰዎችን በተአምራዊ መንገድ እንደፈወሰ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ማቴዎስ 4:23, 24ን አንብብ፤ ዮሐ. 9:1-7) ኢየሱስ ያከናወናቸው ፈውሶች በአዲሱ ዓለም በላቀ ሁኔታ ለሚያከናውነው ነገር ቅምሻ እንደሆኑ ማወቅ ምንኛ ያበረታታል። በዚያን ጊዜ “ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’ አይልም።”—ኢሳ. 33:24

5 ይሁንና በዘመናችን አምላክ ወይም ኢየሱስ በተአምራዊ መንገድ እንዲፈውሱን መጠበቅ እንችላለን? ከባድ ሕመም ወይም የጤና መቃወስ ቢያጋጥመን ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ሕክምና ስንመርጥስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

በታመሙበት ወቅት ይሖዋ ደግፏቸዋል

6. አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች ስለነበራቸው “የመፈወስ ስጦታ” ምን የምናውቀው ነገር አለ?

6 በመጀመሪያው መቶ ዘመን አምላክ ለአንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ተአምራት የመፈጸም ኃይል ሰጥቷቸው እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሥራ 3:2-7፤ 9:36-42) ከመንፈስ ቅዱስ “ልዩ ልዩ ስጦታዎች” መካከል “የመፈወስ ስጦታ” ይገኝበታል። (1 ቆሮ. 12:4-11) ሆኖም የመፈወስ ችሎታም ሆነ እንደመተንበይና በልሳን እንደመናገር ያሉት ሌሎች ስጦታዎች ከጊዜ በኋላ ቀርተዋል። (1 ቆሮ. 13:8) እነዚህ ስጦታዎች በአሁኑ ጊዜ የሉም። በመሆኑም አምላክ እኛንም ሆነ የምንወዳቸውን ሰዎች በተአምራዊ መንገድ ይፈውሰናል ብለን ለመጠበቅ የሚያበቃ ምክንያት የለንም።

7. መዝሙር 41:3 ምን ማበረታቻ ይሰጠናል?

7 ያም ቢሆን ጥንት የነበሩ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች እንዳደረጉት እኛም በምንታመምበት ጊዜ መጽናኛ፣ ጥበብና ድጋፍ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዞር ማለት እንችላለን። ንጉሥ ዳዊት እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ለተቸገረ ሰው የሚያስብ ደስተኛ ነው፤ በመከራ ቀን ይሖዋ ይታደገዋል። ይሖዋ ይጠብቀዋል፤ በሕይወትም ያኖረዋል።” (መዝ. 41:1, 2) እርግጥ ነው፣ ዳዊት ይህን ሲል በዚያ ዘመን የኖረ ለተቸገረ የሚያስብ አንድ ሰው፣ ሞትን ፈጽሞ አያይም ማለቱ እንዳልነበረ እናውቃለን። በመሆኑም ዳዊት፣ ለተቸገረ የሚያስብ ሰው በተአምራዊ ሁኔታ ሕይወቱ እንደሚቀጥልና ለዘላለም እንደሚኖር መናገሩ አይደለም። በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ሐሳብ አምላክ፣ ታማኝና ለሌሎች አሳቢ የሆኑ ሰዎችን እንደሚረዳ የሚጠቁም ነው። የሚረዳቸው እንዴት ነው? ዳዊት ይህን ሲያብራራ “ታሞ በአልጋ ላይ ተኝቶ ሳለ ይሖዋ ይደግፈዋል፤ በታመመበት ወቅት መኝታውን ሙሉ በሙሉ ትቀይርለታለህ” ብሏል። (መዝ. 41:3) ለተቸገረ አሳቢነት ያሳየ ሰው፣ አምላክ እሱንም ሆነ የታማኝነት አካሄዱን እንደማይረሳ እርግጠኛ መሆን ይችላል። በተጨማሪም አምላክ፣ ሰውነታችን ራሱን በራሱ የመጠገን ችሎታ እንዲኖረው አድርጎ ስለፈጠረን ግለሰቡ ከበሽታው ሊያገግም ይችላል።

8. ዳዊት በመዝሙር 41:4 ላይ ይሖዋ ምን እንዲያደርግለት ጠይቋል?

8 ዳዊት ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት እንዲህ ብሏል፦ “እኔም ‘ይሖዋ ሆይ፣ ሞገስ አሳየኝ። በአንተ ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁና ፈውሰኝ’ አልኩ።” (መዝ. 41:4) ዳዊት ይህን የጻፈው እሱ በታመመበትና ሁኔታዎችን መቆጣጠር ባልቻለበት ወቅት አቤሴሎም ዙፋኑን ለመቀማት የተነሳበትን ጊዜ በማሰብ ሊሆን ይችላል። ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ለፈጸመው ኃጢአት አምላክ ይቅር ቢለውም እሱ ግን በደሉንና ያስከተላቸውን መዘዞች አልረሳም። (2 ሳሙ. 12:7-14) ያም ቢሆን ንጉሡ ታሞ በአልጋ ላይ ተኝቶ ሳለ አምላክ  እንደሚደግፈው እርግጠኛ ነበር። ታዲያ ዳዊት ይህን ሲል አምላክ በተአምር እንዲፈውሰውና ዕድሜውን እንዲያራዝምለት መጠየቁ ነበር?

9. (ሀ) የዳዊት ሁኔታ ከንጉሥ ሕዝቅያስ የሚለየው እንዴት ነው? (ለ) ዳዊት ይሖዋ ምን እንደሚያደርግለት መጠበቅ ይችላል?

9 ከዓመታት በኋላ፣ “በጠና ታሞ ሞት አፋፍ ደርሶ” የነበረውን ንጉሥ ሕዝቅያስን አምላክ ከሕመሙ ፈውሶታል። አምላክ በዚህ ጊዜ ጣልቃ በመግባት ለየት ያለ እርምጃ ወስዷል። ሕዝቅያስ ከሕመሙ አገግሞ ለ15 ዓመት ኖረ። (2 ነገ. 20:1-6) በሌላ በኩል ግን ዳዊት የጸለየው ይሖዋ በተአምራዊ መንገድ እንዲፈውሰው አይደለም። በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ መረዳት እንደምንችለው ዳዊት ይሖዋን የጠየቀው፣ ለተቸገረ ሰው አሳቢነት ለሚያሳይ ግለሰብ የሚያደርገውን ነገር ለእሱም እንዲያደርግለት ነው። ይህም “ታሞ በአልጋ ላይ ተኝቶ ሳለ” አምላክ የሚሰጠውን ድጋፍ ይጨምራል። ዳዊት ኃጢአቱ ይቅር ስለተባለለት፣ አምላክ እንዲያጽናናውና እንዲደግፈው እንዲሁም ሰውነቱ በሽታውን ተቋቁሞ እንዲያገግም መጠየቅ ይችላል። (መዝ. 103:3) እኛም እንዲህ ዓይነት ጸሎት ማቅረብ እንችላለን።

10. ጢሮፊሞስና አፍሮዲጡ ካጋጠማቸው ሁኔታ ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን?

10 ዳዊት በተአምራዊ ሁኔታ እንዳልተፈወሰና ዕድሜው በብዙ ዓመታት እንዳልተራዘመ ሁሉ ከሐዋርያው ጳውሎስ የሥራ ባልደረቦች አንዱ የነበረው ጢሮፊሞስም እንዲህ አልተደረገለትም። ጳውሎስ የታመሙትን የፈወሰበት ጊዜ እንዳለ እናውቃለን። (የሐዋርያት ሥራ 14:8-10ን አንብብ።) ለምሳሌ ‘ትኩሳትና ተቅማጥ ይዞት ተኝቶ ለነበረው የፑፕልዮስ አባት’ እንዲህ አድርጓል። ጳውሎስ ለዚህ ሰው “ጸለየለት፤ እጁንም ጫነበትና ፈወሰው።” (ሥራ 28:8) ያም ሆኖ ጳውሎስ በሚስዮናዊ ጉዞው ላይ አብሮት ለነበረው ለጢሮፊሞስ እንዲህ አላደረገም። (ሥራ 20:3-5, 22፤ 21:29) ጢሮፊሞስ ታሞ ከጳውሎስ ጋር መጓዝ ባቃተው ጊዜ ሐዋርያው አልፈወሰውም፤ ከዚህ ይልቅ በሚሊጢን ቀርቶ ከበሽታው እንዲያገግም አድርጓል። (2 ጢሞ. 4:20) በተመሳሳይም አፍሮዲጡ “በጠና ታሞ ሞት አፋፍ ደርሶ” በነበረበት ወቅት ጳውሎስ ተአምራዊ ኃይል በመጠቀም ወዳጁን እንደፈወሰው የሚጠቁም ነገር የለም።—ፊልጵ. 2:25-27, 30

ተገቢ እርምጃዎችን ውሰዱ

11, 12. ሉቃስ ለጳውሎስ ጠቃሚ እርዳታ ሊያበረክት የቻለው እንዴት ነው? ሉቃስ ስለነበረው ብቃት ምን ማለት እንችላለን?

11 ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር ከተጓዙት መካከል የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን የጻፈው “የተወደደው ሐኪም ሉቃስ” ይገኝበታል። (ቆላ. 4:14፤ ሥራ 16:10-12፤ 20:5, 6) ሉቃስ ለጳውሎስ ከጤና ጋር የተያያዘ ምክር ሰጥቶት ሊሆን እንደሚችል እንዲሁም ለጳውሎስም ሆነ በሚስዮናዊ አገልግሎቱ ወቅት አብረውት ለተጓዙት ሌሎች ሰዎች የሕክምና እርዳታ አድርጎላቸው እንደሚሆን ማሰቡ ምክንያታዊ ነው። ሉቃስ እንዲህ ማድረግ ያስፈለገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ጳውሎስም እንኳ በጉዞው ላይ እያለ ታሞ ነበር። (ገላ. 4:13) ኢየሱስ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም” ብሎ ከተናገረው ሐሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ ሉቃስም በዚህ ወቅት የሕክምና እርዳታ መስጠት ይችል ነበር።—ሉቃስ 5:31

12 ሉቃስ የሕክምና ሥልጠና ያገኘው የት ወይም መቼ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም። ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ሲጽፍ ሉቃስ የሕክምና ባለሙያ መሆኑን የጠቀሰው ሉቃስን ስለሚያውቁት ሊሆን ይችላል ተብሎ ይታሰባል። በቆላስይስ አቅራቢያ ባለችው በሎዶቅያ የሕክምና ትምህርት ቤት ነበረ። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ ሉቃስ የሕክምና ባለሙያ እንጂ የሕክምና ችሎታ ሳይኖረው ጤና ነክ ምክር የሚሰጥ ሰው አልነበረም። ሉቃስ የወንጌል ዘገባውንና የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን ሲጽፍ የተጠቀመባቸው የሕክምና ቃላት እንዲሁም ኢየሱስ የፈወሳቸው ሰዎች ላለባቸው ሕመም ትኩረት መስጠቱ ይህን ይጠቁማሉ።

13. ከጤና ጋር በተያያዘ የሚሰጡ አስተያየቶችን በተመለከተ ምን ዓይነት ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ተገቢ ነው?

13 በዛሬው ጊዜ አንድ ክርስቲያን ‘በመፈወስ ስጦታ’ ተጠቅሞ ከሕመማችን ሊያድነን አይችልም። ይሁንና አንዳንድ ወንድሞች ምክር ባንጠይቃቸውም እንኳ በአሳቢነት ተነሳስተው ከጤና ጋር የተያያዙ አስተያየቶችን ይሰጣሉ። በእርግጥ አንዳንዶች የሚሰጡት  ሐሳብ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ጢሞቴዎስ በአካባቢው ያለው ውኃ በመበከሉ የተነሳ ሳይሆን አይቀርም፣ ሆዱን ባመመው ጊዜ ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት ምክር ሰጥቶታል። * (1 ጢሞቴዎስ 5:23ን አንብብ።) ይህ ግን የእምነት ባልንጀራችን፣ አንዳንድ ዕፀዋትን ወይም መድኃኒቶችን እንዲወስድ አሊያም አንድን የአመጋገብ ሥርዓት እንዲከተል ለማሳመን ከመሞከር በጣም የተለየ ነው፤ ምናልባትም ይህ ዓይነቱ ሕክምና ውጤታማ ላይሆን እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የጤና ምክር የሚሰጡ ሰዎች ‘አንድ ዘመዴ እንዲህ ዓይነት ሕመም ነበረበት፤ . . . ሲወስድ ግን ተሻለው’ እንደሚለው ዓይነት ሐሳብ ሲሰነዝሩ ይሰማል። ምክሩ የተሰጠው በአሳቢነት ሊሆን ይችላል፤ ያም ቢሆን በሰፊው የሚሠራበት መድኃኒትም ሆነ የሕክምና ዓይነት እንኳ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ማስታወስ ይኖርብናል።—ምሳሌ 27:12ን አንብብ።

ጠንቃቃ መሆን ጥበብ ነው

14, 15. (ሀ) አንዳንዶች የታመሙ ሰዎችን መጠቀሚያ የሚያደርጓቸው እንዴት ነው? (ለ) ምሳሌ 14:15 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ጤናን አስመልክተው ከሚሰጡ ምክሮች ጋር በተያያዘ ጠቃሚ የሆነው እንዴት ነው?

14 ክርስቲያኖች በሕይወታችን መደሰትና በአምላክ አገልግሎት ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ እንድንችል ጤናማ መሆን እንፈልጋለን፤ ይህ ደግሞ ተፈጥሯዊ ነው። ያም ቢሆን ፍጹማን ባለመሆናችን ለበሽታ የተጋለጥን ነን። ስንታመም እርዳታ ማግኘት የምንችልባቸው የተለያዩ የሕክምና ዘዴዎች አሉ። እያንዳንዱ ሰው የሚፈልገውን ሕክምና የመምረጥ መብት አለው። የሚያሳዝነው ይህ ዓለም፣ ሰዎች በሚታመሙበት ወቅት አጋጣሚውን ተጠቅመው ገንዘብ ለማጋበስ በሚሞክሩ ስግብግቦች የተሞላ ነው። አንዳንዶች ፈውስ ያስገኛሉ የሚባሉ “መድኃኒቶችን” የሚሸጡ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜም ሕክምናው ጠቃሚ እንደሆነ የሚገልጽ የሐሰት ወሬ ያስወራሉ። ሌሎች ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ደግሞ ትርፍ ለማጋበስ ሲሉ ውድ የሆኑ መድኃኒቶችን እንድንጠቀም ያበረታታሉ። ከሕመሙ እፎይታ ማግኘት ወይም ዕድሜውን ማራዘም የሚፈልግ የታመመ ሰው እነዚህን “መድኃኒቶች” ለማግኘት ሊጓጓ ይችላል። ይሁንና የአምላክ ቃል “ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል” የሚል ምክር እንደሚሰጥ አንዘንጋ።—ምሳሌ 14:15

15 “ብልህ” ሰው፣ በተለይ ብቃቱ አጠያያቂ የሆነ ግለሰብ የሚነግረውን “ቃል” ወይም የሚሰጠውን ምክር ለማመን አይቸኩልም። “ብልህ” ሰው እንደሚከተለው ብሎ ያስባል፦ ‘ግለሰቡ ይህ ቫይታሚን፣ ዕፀዋት ወይም የአመጋገብ ሥርዓት ሌሎችን እንደረዳ ተናግሯል፤ ይሁንና ይህን የሚያረጋግጡ በቂ ምሥክሮች አሉ? ደግሞም የሰዎች ሁኔታ የተለያየ ነው። ሕክምናው እኔን እንደሚረዳኝ ለማመን የሚያበቃ ምክንያት አለኝ? በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርምር ማድረግ አሊያም በዚህ መስክ ሥልጠና ያገኙ ወይም ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን ማማከር ይኖርብኝ ይሆን?’—ዘዳ. 17:6

16. ስለ ጤና ከሚሰጡ ምክሮች ጋር በተያያዘ “ጤናማ አስተሳሰብ” ለመያዝ የትኞቹ ጥያቄዎች ይረዱናል?

16 የአምላክ ቃል “በዚህ ሥርዓት ውስጥ ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ . . . እንድንኖር” ይመክረናል። (ቲቶ 2:12) አንድ የሕክምና ዘዴ ከተለመደው ወጣ ያለ ወይም ሚስጥራዊ በሚመስልበት ጊዜ “ጤናማ አስተሳሰብ” መያዝ ወይም አስተዋይ መሆን በጣም አስፈላጊ ይሆናል። ሕክምናውን የሚሰጠው ወይም የሚያስተዋውቀው ግለሰብ ይህ ሕክምና እንዴት እንደሚሠራ አጥጋቢ በሆነ መንገድ ማብራራት ይችላል? ይህ ሕክምና ተቀባይነት ካላቸው እውነታዎች ጋር ይስማማል? ደግሞስ ብቃት ባላቸው ብዙ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት አለው? (ምሳሌ 22:29) ወይስ ግለሰቡ በስሜት ተነሳስተን ውሳኔ እንድናደርግ እየገፋፋን ነው? ምናልባትም ሕክምናው የተገኘው ወይም ጥቅም ላይ የዋለው ራቅ ባለ ቦታ እንደሆነና ዘመናዊ ሕክምና ገና እንዳልደረሰበት ይነገር ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ያለ ሕክምና መኖሩን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች አሉ? አንዳንድ የሕክምና መሣሪያዎች ወይም ዘዴዎች ደግሞ ‘ሚስጥራዊ ንጥረ ነገሮችን’ ወይም ‘የማይታወቅ ኃይልን’ እንደሚጠቀሙ ይገለጻል። እንዲህ ዓይነቱ ሕክምና አደገኛ ሊሆን ይችላል፤ አምላክ ‘ከአስማታዊ ድርጊት’ እና  ከመናፍስት ጠሪዎች እንድንርቅ እንደሚያስጠነቅቀን ማስታወስ አስፈላጊ ነው።—ኢሳ. 1:13፤ ዘዳ. 18:10-12

“ጤና ይስጣችሁ!”

17. ምኞታችን ምንድን ነው?

17 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካል ለጉባኤዎች አንድ ጠቃሚ ደብዳቤ ልኮ ነበር። ደብዳቤው ክርስቲያኖች ሊርቋቸው የሚገቡ ነገሮችን ከዘረዘረ በኋላ የሚከተለውን ሐሳብ በመስጠት ይደመድማል፦ “ከእነዚህ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ከራቃችሁ መልካም ይሆንላችኋል። ጤና ይስጣችሁ!” (ሥራ 15:29) መጨረሻ ላይ የሰፈረው የመሰናበቻ ሐሳብ “ጠንካራ ሁኑ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። እኛም ‘ጤናማ’ እና ጠንካራ ሆነን ታላቁን አምላካችንን ማገልገል እንደምንፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም።

ጤናማ እና ጠንካራ ሆነን አምላክን ማገልገል እንፈልጋለን (አንቀጽ 17ን ተመልከት)

18, 19. በአዲሱ ዓለም ምን እንደምናገኝ መጠበቅ እንችላለን?

18 የምንኖረው በዚህ ሥርዓት ውስጥ ከመሆኑም ሌላ ሁላችንም ፍጹማን አይደለንም፤ በመሆኑም ሕመም ማናችንም ልናመልጠው የማንችለው ነገር ነው። በአሁኑ ወቅት ከሕመማችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ እንደምንድን አንጠብቅም። ይሁንና ራእይ 22:1, 2 ፍጹም ጤና የምናገኝበት ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። ሐዋርያው ዮሐንስ “የሕይወት ውኃ ወንዝ” እና “ሕዝቦችን ለመፈወስ የሚያገለግሉ” ቅጠሎች ያሏቸውን “የሕይወት ዛፎች” በራእይ ተመልክቶ ነበር። ይህ በዛሬው ጊዜም ሆነ ወደፊት የሚኖርን ከዕፀዋት የተዘጋጀ መድኃኒት አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ለመስጠት በኢየሱስ በኩል ያደረገውን ዝግጅት ያመለክታል፤ በእርግጥም ይህ በጉጉት የምንጠብቀው ነገር ነው።—ኢሳ. 35:5, 6

19 ይህን ግሩም ተስፋ እየተጠባበቅን ባለንበት በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ ስለ እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብና ስንታመም ስሜታችንን እንደሚረዳልን እናውቃለን። ልክ እንደ ዳዊት ሁሉ እኛም በምንታመምበት ጊዜ አምላካችን እንደሚደግፈን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንዲሁም “እኔ በበኩሌ ንጹሕ አቋሜን በመጠበቄ ትደግፈኛለህ፤ በፊትህም ለዘላለም ታኖረኛለህ” በማለት የተናገረውን የዳዊትን ቃላት ማስተጋባት እንችላለን።—መዝ. 41:12

^ አን.13 ዚ ኦሪጅንስ ኤንድ ኤንሸንት ሂስትሪ ኦቭ ዋይን የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “የታይፎይድ በሽታ አምጪ ተሕዋስያንን እና ሌሎች አደገኛ የሆኑ በዓይን የማይታዩ ሕይወት ያላቸው ነገሮችን የወይን ጠጅ ወዲያውኑ እንደሚገድላቸው በቤተ ሙከራ ማረጋገጥ ተችሏል።”