“እባክህ ስማኝ፤ እኔም እናገራለሁ።”—ኢዮብ 42:4

መዝሙሮች፦ 113, 114

1-3. (ሀ) አምላክ የሚጠቀምበት ቋንቋና ከሌሎች ጋር የሚግባባበት መንገድ ከሰው ልጆች ቋንቋ በእጅጉ የላቀ የሆነው እንዴት ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ሥር ምን እንመለከታለን?

ዘላለማዊ የሆነው አምላክ፣ ሌሎችም ሕይወት እንዲያገኙና ደስታውን እንዲጋሩ ስለፈለገ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታትን ፈጥሯል። (መዝ. 36:9፤ 1 ጢሞ. 1:11) ሐዋርያው ዮሐንስ፣ መጀመሪያ ከአምላክ ጋር የነበረውን አካል “ቃል” እንዲሁም ‘የአምላክ ፍጥረት መጀመሪያ’ ሲል ጠርቶታል። (ዮሐ. 1:1፤ ራእይ 3:14) ይሖዋ አምላክ ሐሳቡንና ስሜቱን ለዚህ የበኩር ልጁ አካፍሎታል። (ዮሐ. 1:14, 17፤ ቆላ. 1:15) ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ ስለ “መላእክት ልሳን” ተናግሯል፤ ይህም ከሰው ልጆች ቋንቋ እጅግ የሚልቅና በሰማይ ያሉ አካላት የሚግባቡበት ልሳን ነው።—1 ቆሮ. 13:1

2 ይሖዋ በምድርም ሆነ በሰማይ ስላሉት በቢሊዮን የሚቆጠሩ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት በሚገባ ያውቃል። ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች በተመሳሳይ ጊዜ ላይ በበርካታ ቋንቋዎች ወደ እሱ ይጸልዩ ይሆናል። ይሖዋ እነዚህን ሁሉ ጸሎቶች የሚሰማ ከመሆኑም ሌላ በዚያው ቅጽበት ለመላእክት መመሪያ ይሰጣል እንዲሁም ከእነሱ ጋር ይነጋገራል። ይህን ሁሉ ለማከናወን እንዲችል ሐሳቡ፣ ቋንቋውና ከሌሎች ጋር የሚግባባበት መንገድ ከሰው ልጆች በእጅጉ የላቀ ሊሆን ይገባል። (ኢሳይያስ 55:8, 9ን አንብብ።) በግልጽ ማየት እንደምንችለው ይሖዋ ለሰው ልጆች ሐሳቡን የሚያስተላልፈው እነሱ ሊረዱት በሚችሉ ቀለል ያለ መንገድ ነው።

3 እጅግ ጥበበኛ የሆነው አምላክ፣ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ለሕዝቦቹ ሐሳቡን ግልጽ በሆነ መንገድ ለማስተላለፍ የወሰዳቸውን እርምጃዎች ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን። በተጨማሪም ሐሳቡን የሚያስተላልፍበትን መንገድ እንደ አስፈላጊነቱና እንደ ሁኔታው የሚለውጠው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

 አምላክ ሐሳቡን ለሰው ልጆች የገለጸበት መንገድ

4. (ሀ) ይሖዋ ሙሴን፣ ሳሙኤልንና ዳዊትን ለማነጋገር የተጠቀመው የትኛውን ቋንቋ ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይዟል?

4 ይሖዋ፣ በኤደን ገነት ውስጥ አዳምን ያነጋገረው የሰዎችን ቋንቋ ተጠቅሞ ነው። አምላክ በዚህ ወቅት የተጠቀመው ጥንታዊ በሆነ የዕብራይስጥ ቋንቋ ሳይሆን አይቀርም። ከጊዜ በኋላ ደግሞ እንደ ሙሴ፣ ሳሙኤልና ዳዊት ላሉ ዕብራይስጥ ተናጋሪ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ሐሳቡን አስተላለፈ፤ እነሱም የአምላክን ሐሳብ በራሳቸው አገላለጽና የአጻጻፍ ስልት አሰፈሩት። እነዚህ ሰዎች አምላክ በቀጥታ የነገራቸውን ሐሳብ ከማስፈር ባሻገር ከሕዝቡ ጋር ስላለው ግንኙነት ገልጸዋል፤ ባሰፈሩት ዘገባ ውስጥ ስለ እምነታቸውና ለአምላክ ስላላቸው ፍቅር እንዲሁም ስለ ድክመቶቻቸው ብሎም ታማኝነታቸውን ስላጓደሉባቸው ሁኔታዎች ጠቅሰዋል። እነዚህ ታሪኮች በዛሬው ጊዜ እጅግ ጠቃሚ ናቸው።—ሮም 15:4

5. ይሖዋ ለሕዝቡ ሐሳቡን ለማስተላለፍ የተጠቀመበት ቋንቋ ዕብራይስጥ ብቻ ነው? አብራራ።

5 ሁኔታዎች እየተለወጡ ሲሄዱ አምላክ ሐሳቡን ለሰው ልጆች ለመግለጽ ከዕብራይስጥ በተጨማሪ በሌሎች ቋንቋዎች ተጠቅሟል። የአምላክ ሕዝቦች ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ በኋላ የአንዳንዶቹ የዕለት ተዕለት ቋንቋ አረማይክ ሆነ። ይሖዋ አስቀድሞ ይህን ስለተገነዘበ ሳይሆን አይቀርም፣ ነቢዩ ዳንኤልና ነቢዩ ኤርምያስ እንዲሁም ካህኑ ዕዝራ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ዘገባዎቻቸው ውስጥ የተወሰኑትን ክፍሎች በአረማይክ እንዲጽፉ በመንፈሱ መርቷቸዋል።—በዕዝራ 4:8፣ 7:12፣ በኤርምያስ 10:11 እና በዳንኤል 2:4 ላይ የሚገኙትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት።

6. የአምላክ ቃል ከዕብራይስጥ በተጨማሪ በሌሎች ቋንቋዎች ሊኖር የቻለው እንዴት ነው?

6 ከጊዜ በኋላ ታላቁ እስክንድር ከጥንቱ ዓለም አብዛኛውን በቁጥጥሩ ሥር ሲያደርግ ኮይኔ ወይም የጋራ መግባቢያ የነበረው ግሪክኛ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ሆነ። በርካታ አይሁዳውያን ይህን ቋንቋ መናገር ጀመሩ፤ በዚህ የተነሳ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ወደ ግሪክኛ ተተረጎሙ። በ72 ተርጓሚዎች እንደተዘጋጀ የሚታሰበው ይህ ትርጉም ሰብዓ ሊቃናት (ሴፕቱጀንት) በመባል ይታወቃል። ሰብዓ ሊቃናት የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሲሆን ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ትርጉሞች አንዱ ነው። * በሥራው የተካፈሉት ተርጓሚዎች ብዙ በመሆናቸው የተጠቀሙበት የአተረጓጎም ስልትም የተለያየ ነው፤ አንዳንዶቹ ቃል በቃል ሲተረጉሙ ሌሎቹ ግን እንዲህ አላደረጉም። ያም ቢሆን ግሪክኛ ተናጋሪ አይሁዳውያን፣ በኋላ ላይ ደግሞ ክርስቲያኖች ሰብዓ ሊቃናትን እንደ አምላክ ቃል አድርገው ተቀብለውታል።

7. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ያስተማረው በየትኛው ቋንቋ ሊሆን ይችላል?

7 የአምላክ የበኩር ልጅ ምድር ላይ በኖረበት ወቅት ይናገርና ያስተምር የነበረው በዕብራይስጥ ሳይሆን አይቀርም። (ዮሐ. 19:20፤ 20:16፤ ሥራ 26:14) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይነገር በነበረው ዕብራይስጥ ላይ አረማይክ ተጽዕኖ ያሳደረበት ይመስላል፤ በመሆኑም ኢየሱስ አንዳንድ የአረማይክ አገላለጾችን ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል። ይሁንና በየሳምንቱ በምኩራቦች ውስጥ በሚነበቡት የሙሴና የነቢያት መጻሕፍት ላይ የሚገኘውን ጥንታዊ ዕብራይስጥም ያውቅ ነበር። (ሉቃስ 4:17-19፤ 24:44, 45፤ ሥራ 15:21) በተጨማሪም ግሪክኛና ላቲን በእስራኤል ምድር ይነገሩ ነበር። ኢየሱስ እነዚህን ቋንቋዎች ይናገር አይናገር ቅዱሳን መጻሕፍት የሚገልጹት ነገር የለም።

8, 9. ክርስትና እየተስፋፋ ሲሄድ ግሪክኛ የአምላክ ሕዝቦች ዋነኛ መግባቢያ የሆነው ለምንድን ነው? ይህስ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?

8 የኢየሱስ የመጀመሪያ ተከታዮች የሚናገሩት ዕብራይስጥ ነበር፤ እሱ ከሞተ በኋላ ግን ሌሎች ቋንቋዎችንም ተናግረዋል። (የሐዋርያት ሥራ 6:1ን አንብብ።) ክርስትና እየተስፋፋ ሲሄድ ክርስቲያኖች በአብዛኛው የሚነጋገሩት በግሪክኛ ነበር። እንዲያውም ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ፣ ኢየሱስ ያስተማረውንና ያደረገውን ነገር በተመለከተ  በመንፈስ መሪነት ያሰፈሯቸው የወንጌል ዘገባዎች በስፋት የተሰራጩት በግሪክኛ ነው። በመሆኑም አብዛኞቹ ደቀ መዛሙርት የሚጠቀሙት በዕብራይስጥ ሳይሆን በግሪክኛ ነበር። * ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፋቸው ደብዳቤዎችና በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ሌሎች መጻሕፍትም የተሰራጩት በግሪክኛ ነው።

9 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጸሐፊዎች፣ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ሲጠቅሱ በአብዛኛው የሚጠቀሙት ሰብዓ ሊቃናትን መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ከዕብራይስጡ ጽሑፍ በተወሰነ መጠን የሚለዩት እነዚህ ጥቅሶች በአሁኑ ጊዜ፣ በመንፈስ መሪነት የተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል ሆነዋል። በመሆኑም ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች የትርጉም ሥራ በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ክፍል ሆነ፤ ይህም አምላክ አንዱን ባሕል ወይም ቋንቋ ከሌላው እንደማያበላልጥ ያሳያል።የሐዋርያት ሥራ 10:34ን አንብብ።

10. ይሖዋ ቃሉን ለሰዎች ያስተላለፈበትን መንገድ በተመለከተ ምን ብለን መደምደም እንችላለን?

10 አምላክ ለሰው ልጆች ሐሳቡን ስለገለጸበት መንገድ በአጭሩ የተመለከትናቸው ነጥቦች ይሖዋ ሐሳቡን የሚያስተላልፍበትን መንገድ እንደ አስፈላጊነቱና እንደ ሁኔታው እንደሚቀይር ያስተምሩናል። ስለ እሱም ሆነ ስለ ዓላማዎቹ ለማወቅ ስንል አንድን ቋንቋ እንድንማር አያስገድደንም። (ዘካርያስ 8:23ን እና ራእይ 7:9, 10ን አንብብ።) ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው በመንፈሱ መሪነት ቢሆንም ጸሐፊዎቹ የእሱን ሐሳብ ሲያሰፍሩ የተለያየ ዓይነት የአጻጻፍ ስልት እንዲጠቀሙ ፈቅዶላቸዋል።

አምላክ መልእክቱ ተጠብቆ እንዲቆይልን አድርጓል

11. የሰው ልጆች የተለያዩ ቋንቋዎችን መጠቀማቸው አምላክ ለሰዎች ሐሳቡን እንዳያስተላልፍ እንቅፋት ያልፈጠረው ለምንድን ነው?

11 የሰው ልጆች የተለያዩ ቋንቋዎችን መጠቀማቸውና የአምላክ ቃል ሲተረጎም ጥቃቅን ልዩነቶች መፈጠራቸው አምላክ ለሰዎች ሐሳቡን እንዳያስተላልፍ እንቅፋት ሆኗል? በፍጹም። ለምሳሌ ኢየሱስ ከተጠቀመባቸው ቃላት መካከል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቀጥታ የሰፈሩት ጥቂት ናቸው። (ማቴ. 27:46፤ ማር. 5:41፤ 7:34፤ 14:36) ይሁንና ይሖዋ፣ ኢየሱስ የተናገረው መልእክት በግሪክኛና ውሎ አድሮም በሌሎች ቋንቋዎች እንዲተላለፍ አድርጓል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ አይሁዳውያንና ክርስቲያኖች፣ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን በተደጋጋሚ ጊዜ በመገልበጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ተጠብቀው እንዲቆዩ አደረጉ። እነዚህ ጽሑፎችም ወደ ብዙ ቋንቋዎች ተተረጎሙ። በአራተኛው/በአምስተኛው ምዕተ ዓመት የኖረው ጆን ክሪሶስተም፣ በዘመኑ የኢየሱስ ትምህርቶች ሶርያውያን፣ ግብፃውያን፣ ሕንዳውያን፣ ፋርሳውያን፣ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች በርካታ ሕዝቦች ወደሚናገሯቸው ቋንቋዎች ተተርጉመው እንደነበር ገልጿል።

12. መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይሰራጭ ምን ጥረት ተደርጎ ነበር?

12 መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቋንቋዎች ስለተዘጋጀ፣ አንዳንዶች ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማጥፋት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፤ ለምሳሌ የሮም ንጉሠ ነገሥት ዲዮቅላጢያን በ303 ዓ.ም. የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች በሙሉ እንዲወገዱ አዝዞ ነበር። የአምላክን ቃልም ሆነ ቃሉን ለመተርጎምና ለማሰራጨት ጥረት ያደረጉ ሰዎችን ለማጥፋት በርካታ ሙከራዎች ተደርገዋል። በ16ኛው መቶ ዘመን፣ ዊልያም  ቲንደል መጽሐፍ ቅዱስን ከዕብራይስጥና ከግሪክኛ ወደ እንግሊዝኛ መተርጎም ጀመረ፤ ቲንደል ለአንድ የተማረ ሰው እንዲህ ብሎት ነበር፦ “አምላክ በሕይወት ካቆየኝ በጥቂት ዓመታት ውስጥ፣ እርፍ ጨብጦ የሚያርሰው ወጣት ቅዱሳን መጻሕፍትን ከአንተ የበለጠ እንዲያውቅ አደርገዋለሁ።” ቲንደል መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎምና ለማተም እንግሊዝን ለቆ መሸሽ ነበረበት። ቀሳውስቱ ያገኟቸውን መጽሐፍ ቅዱሶች በሙሉ በሕዝብ ፊት የማቃጠል ዘመቻ ቢያካሂዱም ብዛት ያላቸው መጽሐፍ ቅዱሶች መሰራጨት ጀመሩ። ውሎ አድሮ አንድ ሰው ቲንደልን አሳልፎ ሰጠው፤ በመሆኑም ታንቆ ከተገደለ በኋላ ተቃጠለ። እሱ የተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ ግን እስካሁን ድረስ አለ። በስፋት የተሰራጨውን ኪንግ ጄምስ ቨርዥን ለማዘጋጀት የቲንደል ትርጉም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።2 ጢሞቴዎስ 2:9ን አንብብ።

13. በጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ላይ የተደረጉት ጥናቶች ምን ያሳያሉ?

13 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ አንዳንድ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች፣ ጥቃቅን ስህተቶችና ልዩነቶች እንዳሏቸው አይካድም። ያም ሆኖ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን በሺዎች የሚቆጠሩ የቅዱሳን መጻሕፍት ቁርጥራጮችን፣ በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ቅጂዎችንና ትርጉሞችን አነጻጽረዋል፤ እንዲሁም በከፍተኛ ጥንቃቄ አጥንተዋል። ያከናወኑት ጥናት ከጥቂቶች በቀር ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ትክክለኛ መሆናቸውን አረጋግጧል። ምሁራኑ እርግጠኛ ያልሆኑባቸው ጥቂት ጥቅሶች ቢኖሩም እነዚህ ጥቅሶች አጠቃላዩን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት አይለውጡትም። በጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ላይ የተደረጉት ጥናቶች፣ ዛሬ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ በመንፈሱ መሪነት መጀመሪያ ያሰፈረውን ሐሳብ የያዘ መሆኑን ቅን ልብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንዲያምኑ አድርገዋቸዋል።—ኢሳ. 40:8 *

14. የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ምን ያህል በስፋት ተሰራጭቷል?

14 ጠላቶች የአምላክን ቃል ለማጥፋት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፤ ያም ቢሆን ይሖዋ፣ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ በስፋት በመተርጎም ረገድ የአምላክ ቃል ተወዳዳሪ የሌለው መጽሐፍ እንዲሆን አድርጓል። ብዙዎች በአምላክ በማያምኑበት ዘመን እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ በብዛት ከተሸጡ መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ ይዟል፤ እንዲሁም በከፊልም ሆነ በሙሉ ከ2,800 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል። በስፋት በመሰራጨትና እንደ ልብ በመገኘት ረገድ መጽሐፍ ቅዱስን የሚደርስበት መጽሐፍ የለም። እርግጥ ነው፣ ግልጽ ወይም እምነት የሚጣልበት በመሆን ረገድ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የሚጎድላቸው ነገር አለ። ያም ሆኖ ተስፋ የሚሰጠውንና ስለ መዳን የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና መልእክት የትኛውንም ትርጉም በማንበብ መረዳት ይቻላል።

አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማዘጋጀት አስፈለገ

15. (ሀ) በዘመናችን ቋንቋ እንቅፋት እንዳይፈጥር ምን ተደርጓል? (ለ) ጽሑፎቻችን መጀመሪያ በእንግሊዝኛ የሚዘጋጁት ለምንድን ነው?

15 ባለፈው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ጥቂት ቁጥር ያላቸው ትጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆነው በተሾሙበት ወቅት ‘ለቤተሰቡ’ አባላት በአብዛኛው ምግብ የሚያቀርቡት በእንግሊዝኛ ነበር። (ማቴ. 24:45) ይህ “ባሪያ”  መንፈሳዊውን ምግብ በብዙ ቋንቋዎች ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን አሁን ከ700 በሚበልጡ ቋንቋዎች መንፈሳዊ ምግብ እያቀረበ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው ኮይኔ ሁሉ እንግሊዝኛም የሥራና የትምህርት ቋንቋ ሆኖ በስፋት ስለሚያገለግል ጽሑፎቻችን ወደ ሌሎች ቋንቋዎች የሚተረጎሙት ከእንግሊዝኛ ነው።

16, 17. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች ምን እንደሚያስፈልግ ተሰምቷቸው ነበር? (ለ) ይህን ፍላጎታቸውን ለማሟላት ምን ተደረገ? (ሐ) አዲስ ዓለም ትርጉም በ1950 ሲወጣ ወንድም ኖር ምን ምኞት እንዳለው ገልጾ ነበር?

16 መንፈሳዊው ምግብ የሚዘጋጀው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርቶ ነው። በ20ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ በስፋት የሚሠራበት የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ በ1611 የተዘጋጀው ኪንግ ጄምስ ቨርዥን ነበር። ይሁንና ይህ እትም የሚጠቀምበት ቋንቋ በአብዛኛው ጊዜ ያለፈበት ነበር። ከዚህም ሌላ በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክ ስም የሚገኘው ጥቂት ጥቅሶች ላይ ብቻ ነው፤ በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ላይ ግን መለኮታዊው ስም በብዙ ሺዎች በሚቆጠሩ ቦታዎች ላይ ይገኛል። በዚያ ላይ ደግሞ ኪንግ ጄምስ ቨርዥን አንዳንድ የትርጉም ስህተቶች አሉት፤ እንዲሁም ተአማኒነት ባላቸው ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ውስጥ የሌሉ የተሳሳቱ ጥቅሶችን ይዟል። በወቅቱ የነበሩ ሌሎች የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችም ጉድለቶች ነበሯቸው።

17 ከዚህ አንጻር የጥንቶቹ ቅዱሳን መጻሕፍት የያዙትን ሐሳብ በትክክለኛና በዘመናዊ ቋንቋ የሚያስተላልፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነበር። በመሆኑም የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን ኮሚቴው ከ1950 እስከ 1960 ባሉት አሥር ዓመታት ውስጥ የትርጉም ሥራውን በስድስት ጥራዞች አወጣ። ወንድም ናታን ሆመር ኖር፣ የዚህ ትርጉም የመጀመሪያ ጥራዝ መውጣቱን ነሐሴ 2, 1950 በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ በገለጸበት ወቅት እንዲህ ብሏል፦ “በዘመናዊ ቋንቋ የተዘጋጀ፣ ይሖዋ ከገለጠው እውነት ጋር የሚስማማ ሆኖም የበኩረ ጽሑፉን ሐሳብ በታማኝነት በማስፈር ተጨማሪ እውነት ለማግኘት የሚረዳን ትርጉም አስፈላጊ መሆኑ ይበልጥ እየተሰማን መጥቷል፤ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በኩረ ጽሑፉን ያሰፈሩት በዘመናቸው የነበሩት ተራ የሆኑ እንዲሁም ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው አንባቢዎች ሊረዱት በሚችሉት መንገድ ነው፤ የዚያኑ ያህል ለዘመናዊ አንባቢዎች ግልጽ የሆነ ትርጉም ያስፈልጋል።” ወንድም ኖር ይህ ትርጉም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በመንፈሳዊ እንደሚረዳ ያለውን ምኞት ገልጿል።

18. የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ እንዲፋጠን ያደረጉት የትኞቹ ውሳኔዎች ናቸው?

18 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በ1963 በሌሎች ስድስት ቋንቋዎች ይኸውም በስፓንኛ፣ በደች፣ በጀርመንኛ፣ በጣሊያንኛ፣ በፈረንሳይኛና በፖርቱጋልኛ ሲወጣ የወንድም ኖር ምኞት ተሳካ። በ1989 የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራን የሚያቀላጥፍ አንድ ክፍል በዋናው መሥሪያ ቤት እንዲቋቋም አደረገ። በ2005 ደግሞ መጠበቂያ ግንብ የሚዘጋጅባቸው ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም ቅድሚያ እንዲሰጡ ተደረገ። በዚህም የተነሳ በአሁኑ ጊዜ አዲስ ዓለም ትርጉም በከፊልም ሆነ በሙሉ ከ130 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተዘጋጅቷል።

19. በ2013 ምን ታሪካዊ ክንውን ተፈጸመ? ቀጣዩ ርዕስ ምን ያብራራል?

19 ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የእንግሊዝኛ ቋንቋ እየተለወጠ በመምጣቱ የእንግሊዝኛው አዲስ ዓለም ትርጉም መሻሻል እንደሚያስፈልገው ግልጽ ሆነ። ጥቅምት 5 እና 6, 2013 ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ኦቭ ፔንስልቬንያ 129ኛውን ዓመታዊ ስብሰባ ባደረገበት ወቅት በ31 አገሮች የሚገኙ 1,413,676 ተሰብሳቢዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል። አንድ የበላይ አካል አባል፣ አዲስ ዓለም ትርጉም በእንግሊዝኛ ተሻሽሎ መውጣቱን ሲናገር ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ በጣም ተደሰቱ። አስተናጋጆች ተሻሽሎ የወጣውን መጽሐፍ ቅዱስ ሲያድሉ ብዙዎቹ ተሰብሳቢዎች ዓይናቸው በእንባ ተሞልቶ ነበር። ከአዲሱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቅሶች ሲነበቡ አድማጮች የአምላክ ቃል በእንግሊዝኛ የሰፈረበት መንገድ ከበፊቱ በጣም የተሻለ መሆኑን አስተዋሉ። የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተደረገው ማሻሻያ በዝርዝር የሚያወሳ ከመሆኑም ሌላ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች እንዴት እየተተረጎመ እንዳለ ይገልጻል።

^ አን.6 ሴፕቱጀንት (ሰብዓ) የሚለው ቃል “ሰባ” ማለት ነው። ይህ ትርጉም መዘጋጀት የጀመረው በሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. በግብፅ እንደሆነ ይነገራል፤ ሥራው ያለቀው በ150 ዓ.ዓ. ሊሆን ይችላል። ምሁራን፣ ግልጽ ያልሆኑ የዕብራይስጥ ቃላትንና ሐሳቦችን ትርጉም እንዲረዱ ሴፕቱጀንት ስለሚያግዛቸው አሁንም ቢሆን በጣም ጠቃሚ ነው።

^ አን.8 አንዳንዶች፣ ማቴዎስ መጀመሪያ ወንጌሉን የጻፈው በዕብራይስጥ እንደሆነና ምናልባትም እሱ ራሱ ወደ ግሪክኛ እንደተረጎመው ያምናሉ።

^ አን.13 አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ የሚገኘውን ተጨማሪ መረጃ ሀ3 ተመልከት፤ እንዲሁም ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ ከገጽ 7-9 ላይ የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ያህል ዕድሜ ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው?” የሚል ርዕስ ተመልከት።