የ1931 የጸደይ ወቅት ነው። በፓሪስ የሚገኘው ፕሌዬል የሚባል የታወቀ የሙዚቃ ትርዒት አዳራሽ መግቢያ ከ23 አገሮች በመጡ ልዑካን ተጨናንቋል። ትላልቅ ታክሲዎች፣ ሽክ ብለው የለበሱ ተሳፋሪዎቻቸውን ከአዳራሹ ፊት ለፊት እያወረዷቸው ነው፤ ብዙም ሳይቆይ ዋናው አዳራሽ ጢም አለ። ወደ 3,000 የሚጠጉት ተሰብሳቢዎች ወደዚህ የመጡት የሙዚቃ ትርዒት ለማየት ሳይሆን በዚያን ጊዜ ለስብከቱ ሥራችን አመራር ይሰጥ የነበረው ወንድም ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ የሚሰጠውን ንግግር ለመስማት ነው። ወንድም ራዘርፎርድ ያቀረባቸው ቀስቃሽ ንግግሮች ወደ ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛና ፖሊሽ ተተረጎሙ። የወንድም ራዘርፎርድ የሚያስገመግም ድምፅ በአዳራሹ ውስጥ አስተጋባ።

በፓሪስ የተደረገው ይህ ስብሰባ፣ በፈረንሳይ በሚካሄደው የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ረገድ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ሆኗል። ወንድም ራዘርፎርድ ከመላው ዓለም ለመጡ አድማጮቹ በተለይም ለወጣት ክርስቲያኖች፣ ፈረንሳይ ውስጥ ኮልፖርተሮች ሆነው እንዲያገለግሉ ጥሪ አቀረበላቸው። በወቅቱ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የነበረ ጆን ኩክ የሚባል አንድ እንግሊዛዊ ልዑክ፣ ወንድም ራዘርፎርድ የሰጠውን ስሜት ቀስቃሽ ምክር ፈጽሞ አይረሳውም፤ “እናንተ ወጣቶች፣ ኮልፖርተሮች እንዳትሆኑ ከፀሐይ በታች ምንም ነገር ሊያግዳችሁ አይገባም!” ብሏቸው ነበር። *

ከጊዜ በኋላ ሚስዮናዊ ከሆነው ከጆን ኩክ በተጨማሪ ሌሎች ብዙዎችም ለዚህ የመቄዶንያ ጥሪ ምላሽ ሰጥተዋል። (ሥራ 16:9, 10) እንዲያውም በ1930 በፈረንሳይ 27 የነበረው የኮልፖርተሮች ቁጥር በ1931 ወደ 104 አድጓል፤ ይህም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የተገኘ ልዩ ጭማሪ ነው። ከእነዚያ ቀደምት አቅኚዎች መካከል ብዙዎቹ ፈረንሳይኛ አይችሉም ነበር፤ ታዲያ ቋንቋ አለመቻላቸው፣ ብዙ ቁሳዊ ነገሮች የሌሏቸው መሆኑና ከሌሎች ርቀው ማገልገላቸው ያስከተሏቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መቋቋም የቻሉት እንዴት ነው?

ቋንቋ አለመቻል የሚያስከትለውን ችግር መወጣት

ከሌላ አገር የመጡት ኮልፖርተሮች ስለ መንግሥቱ ተስፋ ለመናገር የሚጠቀሙት በምሥክርነት መስጫ ካርድ ነበር። በፓሪስ በድፍረት ይሰብክ የነበረ አንድ ጀርመንኛ ተናጋሪ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “አምላካችን ኃያል እንደሆነ እናውቃለን። በአገልግሎት ላይ ስንሆን ልባችን በጉሮሯችን ሊወጣ የሚደርሰው ሰው ፈርተን ሳይሆን ‘ቩሌ ቩ ሊር ሰት ካርት፣ ስል ቩ ፕሌ? [እባክዎ፣ ይህን ካርድ ያንብቡት!]’ የሚሉትን ቃላት እንዳንረሳ ስለምንጨነቅ ነበር። ሥራችን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማን ነበር።”

ቀደምት ኮልፖርተሮች ፈረንሳይ ውስጥ ምሥራቹን ለማዳረስ በብስክሌቶችና በሞተር ብስክሌቶች ተጠቅመዋል

ኮልፖርተሮች በአፓርታማ ሕንፃዎች ላይ ሲሰብኩ ብዙውን ጊዜ ጠባቂዎች ያባርሯቸው ነበር። ሁለት እንግሊዛውያን እህቶች አንድ ቀን አፓርታማ ላይ ሲያገለግሉ አንድ ቁጡ የጥበቃ ሠራተኛ አገኛቸው፤ ሰውየው ማንን እየፈለጉ እንደሆነ ጠየቃቸው፤ እህቶች የሚያውቁት ፈረንሳይኛ ደግሞ በጣም ትንሽ ነበር። አንደኛዋ እህት የተቆጣውን ጠባቂ ለማረጋጋት መላ እየፈለገች ሳለ በአንድ በር ላይ የተቀረጸ ጽሑፍ ተመለከተች። ጽሑፉ“ቱርኔ ለ ቡቶ” [ደወሉን ይጫኑት] ይላል። እህት ጽሑፉ የቤቱ ባለቤት ስም እንደሆነ ስላሰበች ፈገግ ብላ “የመጣነው ማዳም ‘ቱርኔ ለ ቡቶ’ ጋ ነው” አለችው። እነዚያ ቀናተኛ ኮልፖርተሮች ተጫዋች መሆናቸው በእጅጉ ጠቅሟቸዋል!

 ዝቅተኛ ኑሮና ብቸኝነት አልበገራቸውም

በ1930ዎቹ ዓመታት ውስጥ በፈረንሳይ ለአብዛኞቹ ሰዎች ሕይወት አስቸጋሪ ነበር፤ ከሌላ አገር ለመጡ ኮልፖርተሮችም ሁኔታው ተመሳሳይ ነበር። ሞና ብዦስካ የምትባል አንዲት እንግሊዝኛ ተናጋሪ እህት፣ እሷና የአቅኚነት ጓደኛዋ ያጋጠማቸውን ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “በጥቅሉ ሲታይ ከመኖሪያ ጋር በተያያዘ እጅግ መሠረታዊ ከሆኑት ነገሮች ሌላ ምንም አልነበረንም፤ ካሉብን ከባድ ችግሮች አንዱ በክረምት ወቅት ማሞቂያ የሌለን መሆኑ ነበር። ብዙውን ጊዜ፣ የሚያቆራምደውን ቅዝቃዜ ችለን ለመኖር እንገደዳለን፤ ጠዋት ላይ ውኃ መቅጃ ውስጥ ያለው ውኃ ወደ በረዶነት ስለሚቀየር ለመተጣጠብ በረዶውን መስበር ነበረብን።” እነዚያ ቀደምት አቅኚዎች ምቾታቸው መጓደሉ ተስፋ አስቆርጧቸው ይሆን? በፍጹም! ከእነሱ መካከል አንዱ እንደሚከተለው በማለት ስሜታቸውን ጥሩ አድርጎ ገልጾታል፦ “ምንም ያልነበረን ቢሆንም ምንም አላጣንም።”—ማቴ. 6:33

በ1931 በፓሪስ በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ የተገኙ እንግሊዛውያን አቅኚዎች

እነዚያ ደፋር ኮልፖርተሮች ከሌሎች ርቀው መኖር የሚያስከትለውን ፈተናም መቋቋም ነበረባቸው። በ1930ዎቹ መጀመሪያ ላይ በፈረንሳይ የነበሩት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ከ700 የማይበልጥ ሲሆን አብዛኞቹ የሚኖሩት በመላ አገሪቱ ተበታትነው ነበር። ታዲያ ከሌሎች ርቀው የሚኖሩት ኮልፖርተሮች ደስተኞች ሆነው እንዲቀጥሉ የረዳቸው ምን ነበር? ከአቅኚነት ጓደኛዋ ጋር እንዲህ ያለ ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሟት የነበረችው ሞና እንደሚከተለው በማለት ገልጻለች፦ “ብቸኝነትን ለመቋቋም የማኅበሩን ጽሑፎች ዘወትር አብረን እናጠና ነበር። በዚያን ወቅት ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግም ሆነ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ስላልጀመርን ምሽት ላይ ጊዜ ነበረን፤ በመሆኑም ለቤተሰባችን በተለይም ለሌሎች አቅኚዎች ደብዳቤ በመጻፍ ተሞክሯችንን እናካፍላቸውና እርስ በርስ እንበረታታ ነበር።”—1 ተሰ. 5:11

የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉት እነዚያ ኮልፖርተሮች ብዙ እንቅፋቶች ቢኖሩባቸውም አዎንታዊ አመለካከት ነበራቸው። ለቅርንጫፍ ቢሮ ከላኩት ደብዳቤ ይህን ማየት ይቻላል፤ አንዳንድ ጊዜ እነዚህን ደብዳቤዎች የጻፉት በፈረንሳይ ለአሥርተ ዓመታት በአቅኚነት ካገለገሉ በኋላ ነው። ከ1931 እስከ 1935 ባሉት ዓመታት ከባለቤቷ ጋር በመሆን ፈረንሳይ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር የተጓዘች አኒ ክረጂን የምትባል ቅቡዕ እህት፣ እነዚያን ዓመታት መለስ ብላ በማስታወስ የሚከተለውን ጽፋለች፦ “እጅግ አስደሳችና የማይረሳ ጊዜ አሳልፈናል! አቅኚዎች በጣም እንቀራረብ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ‘እኔ ተከልኩ፤ አጵሎስ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን አምላክ ነው።’ ከብዙ ዓመታት በፊት በስብከቱ ሥራ የመርዳት አጋጣሚ ላገኘን ክርስቲያኖች ይህን ማወቅ እጅግ የሚያስደስት ነው።”—1 ቆሮ. 3:6

በእርግጥም እነዚያ ቀደምት አቅኚዎች፣ አገልግሎታቸውን ማስፋት የሚፈልጉ ሌሎች ክርስቲያኖችም ከግምት ሊያስገቡት የሚገባ የጽናትና የቅንዓት ምሳሌ ትተዋል። በዛሬው ጊዜ በፈረንሳይ 14,000 የሚያህሉ የዘወትር አቅኚዎች አሉ። ብዙዎቹ የሚያገለግሉት በውጭ አገር ቋንቋዎች በሚመሩ ቡድኖች ወይም ጉባኤዎች ውስጥ ነው። * እነዚህ አቅኚዎች፣ ከእነሱ በፊት እንደነበሩት አቅኚዎች ሁሉ ከፀሐይ በታች ምንም ነገር እንዲያግዳቸው አይፈቅዱም!—በፈረንሳይ ካለው የታሪክ ማኅደራችን

^ አን.4 በፈረንሳይ ለሚኖሩ ፖላንዳውያን ምሥራቹ እንዴት እንደደረሰ ለማወቅ በነሐሴ 15, 2015 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ይሖዋ ወደ ፈረንሳይ ያመጣችሁ እውነትን እንድትማሩ ነው” የሚል ርዕስ ተመልከት።

^ አን.13 በ2014 በፈረንሳይ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር ያሉ ከ900 በላይ በውጭ አገር ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎችና ቡድኖች 70 ቋንቋዎችን የሚናገሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎችን ረድተዋል።