“ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።”—ማቴ. 22:39

መዝሙሮች፦ 73, 36

1, 2. ቅዱሳን መጻሕፍት ፍቅር ትልቅ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ የሚያሳዩት እንዴት ነው?

ፍቅር የይሖዋ አምላክ ዋነኛ ባሕርይ ነው። (1 ዮሐ. 4:16) የመጀመሪያ የፍጥረት ሥራው ኢየሱስ ነው፤ እሱም ከአባቱ ጋር ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት በሰማይ ሲኖር ፍቅር ስለሚንጸባረቅባቸው የአምላክ መንገዶች ተምሯል። (ቆላ. 1:15) ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈውን ጊዜ ጨምሮ መላ ሕይወቱ፣ ይሖዋ የፍቅር አምላክ መሆኑን እንደተገነዘበና በዚህ ረገድ እሱን እንደሚመስል ያሳያል። በመሆኑም የይሖዋና የኢየሱስ አገዛዝ ምንጊዜም ፍቅር የሚንጸባረቅበት እንደሚሆን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

2 ኢየሱስ ከሕጉ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው እንደሆነ ሲጠየቅ እንዲህ ብሏል፦ “‘አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።’ ይህ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው። ሁለተኛውም ይህንኑ የሚመስል ሲሆን ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል።”—ማቴ. 22:37-39

3. ‘ባልንጀራችን’ ማን ነው?

3 ኢየሱስ ይሖዋን ከመውደድ ቀጥሎ ሁለተኛውን ቦታ የሚይዘው ለባልንጀራችን ያለን ፍቅር መሆኑን እንደገለጸ ልብ በል። ይህም ከሁሉም ሰው ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ፍቅር ማሳየት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚያጎላ ነው። ይሁንና ‘ባልንጀራችን’ ማን ነው? ባለትዳር ከሆንን ከማንም የሚቀርበን ባልንጀራችን የትዳር ጓደኛችን ነው። ከዚህም በተጨማሪ የክርስቲያን ጉባኤ  አባላት ይኸውም እውነተኛውን አምላክ አብረውን የሚያመልኩ ሰዎች የቅርብ ባልንጀሮቻችን ናቸው። በአገልግሎት የምናገኛቸው ሰዎችም ባልንጀራችን ሊባሉ ይችላሉ። ለመሆኑ ይሖዋን የሚያመልኩና የልጁን ትምህርቶች የሚከተሉ ሰዎች ለባልንጀራቸው ፍቅር ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

ለትዳር ጓደኛችሁ ፍቅር አሳዩ

4. የሰው ልጆች ፍጽምና ቢጎድላቸውም ስኬታማ ትዳር ሊኖራቸው ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?

4 ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ ሁለቱን በማጋባት የመጀመሪያውን ጋብቻ መሥርቷል። ዓላማው አስደሳችና ዘላቂ ጥምረት እንዲኖራቸው ብሎም ምድርን በዘሮቻቸው እንዲሞሉ ነበር። (ዘፍ. 1:27, 28) ይሁንና በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ የተነሳው ዓመፅ የመጀመሪያውን ጋብቻ ያበላሸው ሲሆን በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ኃጢአትና ሞት አስከትሏል። (ሮም 5:12) ያም ቢሆን ስኬታማ ትዳር መምራት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ቅዱሳን መጻሕፍት ይነግሩናል። በዚህ ረገድ የሚሰጡን ምክር ከሁሉ የላቀ ነው፤ ምክንያቱም የምክሩ ምንጭ የጋብቻ መሥራች የሆነው ይሖዋ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17ን አንብብ።

5. ፍቅር በትዳር ውስጥ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

5 የአምላክ ቃል እንደሚያሳየው ሰዎች አስደሳች ግንኙነት እንዲመሠርቱ ከተፈለገ በመካከላቸው ፍቅር ይኸውም የጠበቀ ቅርርብ ወይም ጥልቅ የመውደድ ስሜት መኖሩ እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህ በትዳር ውስጥም እንደሚሠራ ጥያቄ የለውም። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ጉባኤ በጻፈው መልእክት ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። ፍቅር አይቀናም። ጉራ አይነዛም፣ አይታበይም፣ ጨዋነት የጎደለው ምግባር አያሳይም፣ የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም፣ በቀላሉ አይበሳጭም። ፍቅር የበደል መዝገብ የለውም። ፍቅር በዓመፅ አይደሰትም፤ ከዚህ ይልቅ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል። ሁሉን ችሎ ያልፋል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል። ፍቅር ለዘላለም ይኖራል።” (1 ቆሮ. 13:4-8) በመንፈስ መሪነት በተጻፈው በዚህ ጥቅስ ላይ ማሰላሰልና ምክሩን ተግባራዊ ማድረግ በትዳራችን የበለጠ ደስተኛ ለመሆን እንደሚረዳን ጥርጥር የለውም።

የአምላክ ቃል ትዳር እንዲሰምር ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ ይነግረናል (አንቀጽ 6, 7ን ተመልከት)

6, 7. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ራስነት ሥልጣን ምን ይላል? (ለ) አንድ ክርስቲያን ባል፣ ሚስቱን መያዝ ያለበት እንዴት ነው?

6 አምላክ ከማንኛውም ዝግጅት ጋር በተያያዘ የራስነት ሥርዓት እንዲኖር አድርጓል፤ በዚህም የተነሳ ፍቅር በጣም አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስ ራስ ደግሞ አምላክ እንደሆነ እንድታውቁ እወዳለሁ” ብሏል። (1 ቆሮ. 11:3) ያም ሆኖ የራስነት  ሥልጣን አምባገነናዊ በሆነ መንገድ ሊሠራበት አይገባም። ለምሳሌ፣ የክርስቶስ ራስ የሆነው ይሖዋ የራስነት ሥልጣኑን የሚጠቀምበት ደግነት በሚንጸባረቅበትና ከራስ ወዳድነት በራቀ መንገድ ነው፤ ኢየሱስ ደግሞ ለይሖዋ ሥልጣን ይገዛል። አምላክ የራስነት ሥልጣኑን በፍቅር የሚጠቀምበት ሲሆን ኢየሱስም የይሖዋን ራስነት ያከብራል፤ ምክንያቱም “እኔ አብን [እወደዋለሁ]” ብሏል። (ዮሐ. 14:31) ይሖዋ ከሚወደው ልጁ ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ኃይለኛ ወይም አምባገነን ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ እንዲህ ሊሰማው አይችልም ነበር።

7 ባል የሚስቱ ራስ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ሚስቱን ‘እንዲያከብራት’ ያዛል። (1 ጴጥ. 3:7) ባሎች ለሚስቶቻቸው አክብሮት ማሳየት ከሚችሉባቸው መንገዶች አንዱ፣ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባትና በአንዳንድ ጉዳዮች ረገድ የእነሱን ምርጫ ማስቀደም ነው። ደግሞም የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደና ራሱን ለጉባኤው አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ እናንተም ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ።” (ኤፌ. 5:25) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ሕይወቱን ሳይቀር ሰጥቷል። አንድ ባል እንደ ኢየሱስ የራስነት ሥልጣኑን በፍቅር የሚጠቀምበት ከሆነ ሚስቱ እሱን መውደድና ማክበር እንዲሁም ለእሱ መገዛት ይበልጥ ቀላል ይሆንላታል።ቲቶ 2:3-5ን አንብብ።

ለእምነት ባልንጀሮቻችሁ ፍቅር አሳዩ

8. የይሖዋ አምላኪዎች ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?

8 በዓለም ዙሪያ ይሖዋን የሚያመልኩ እንዲሁም ስለ እሱና ስለ ዓላማው የሚመሠክሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ታዲያ እያንዳንዱ የይሖዋ አምላኪ ለእምነት ባልንጀራው ምን አመለካከት ሊኖረው ይገባል? የአምላክ ቃል “ለሁሉም፣ በተለይ ደግሞ በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች መልካም እናድርግ” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (ገላ. 6:10፤ ሮም 12:10ን አንብብ።) ሐዋርያው ጴጥሮስም እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እንግዲህ ለእውነት በመታዘዝ ራሳችሁን ስላነጻችሁ ግብዝነት የሌለበት የወንድማማች መዋደድ አላችሁ፤ በመሆኑም እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ።” ከዚህም በተጨማሪ ጴጥሮስ የእምነት ባልንጀሮቹን “ከሁሉም በላይ አንዳችሁ ለሌላው የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ” ብሏቸዋል።—1 ጴጥ. 1:22፤ 4:8

9, 10. በአምላክ ሕዝቦች መካከል ፍቅር ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው?

9 አብረውን ይሖዋን ለሚያገለግሉ ባልንጀሮቻችን ጥልቅ ፍቅር ስላለን ልዩ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ሊኖረን ችሏል። በተጨማሪም ይሖዋን ስለምንወድና ሕግጋቱን ስለምንታዘዝ፣ አምላክ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀ ኃይል በሆነው በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ይደግፈናል። ይህ መንፈስ፣ ዓለም አቀፍ በሆነ እውነተኛ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ እንድንታቀፍና አስደናቂ አንድነት እንዲኖረን አስችሎናል።1 ዮሐንስ 4:20, 21ን አንብብ።

10 ጳውሎስ በክርስቲያኖች መካከል ፍቅር መኖሩ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ሲያጎላ እንዲህ ብሏል፦ “ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ። አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ። ይሁንና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ላይ ፍቅርን ልበሱ፤ ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነውና።” (ቆላ. 3:12-14) አስተዳደጋችን ወይም ዜግነታችን ምንም ይሁን ምን “ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ” የተባለው ፍቅር በመካከላችን በመኖሩ ምንኛ አመስጋኞች ነን!

11. ፍቅርና አንድነት የይሖዋን ድርጅት ለይቶ የሚያሳውቀው እንዴት ነው?

11 የይሖዋ አገልጋዮች በመካከላቸው እውነተኛ ፍቅርና አንድነት መኖሩ የእውነተኛው ሃይማኖት ተከታዮች መሆናቸውን ያሳውቃል፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐ. 13:34, 35)  ሐዋርያው ዮሐንስም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የአምላክ ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ በግልጽ ይታወቃሉ፦ በጽድቅ ጎዳና የማይመላለስ ሁሉ የአምላክ ወገን አይደለም፤ ወንድሙን የማይወድም የአምላክ ወገን አይደለም። ከመጀመሪያ የሰማችሁት መልእክት እርስ በርሳችን መዋደድ አለብን የሚል ነውና።” (1 ዮሐ. 3:10, 11) የይሖዋ ምሥክሮች የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች መሆናቸውን የሚያሳውቀው፣ ልዩ የሆነ አንድነት የሚያስገኝ ፍቅር ያላቸው መሆኑ ነው፤ ይሖዋ እነዚህን ሕዝቦች በመላው ምድር የመንግሥቱን ምሥራች ለማወጅ እየተጠቀመባቸው ነው።—ማቴ. 24:14

“እጅግ ብዙ ሕዝብ” መሰብሰብ

12, 13. በዛሬው ጊዜ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ምን እያደረገ ነው? የዚህ ቡድን አባላት በቅርቡ ምን ያገኛሉ?

12 አብዛኞቹ የይሖዋ አገልጋዮች “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች [የተውጣጣው] . . . እጅግ ብዙ ሕዝብ” አባላት ናቸው። እነሱም በአምላክ ‘ዙፋንና በበጉ [በኢየሱስ ክርስቶስ] ፊት ቆመዋል።’ እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? “ታላቁን መከራ አልፈው የመጡ ናቸው”፤ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ስላላቸው “[ልብሳቸውን] በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል።” ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባላት ለይሖዋና ለልጁ ፍቅር አላቸው፤ እንዲሁም ለአምላክ “ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት እያቀረቡለት ነው።”—ራእይ 7:9, 14, 15

13 በቅርቡ አምላክ ይህን ክፉ ዓለም ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ያጠፋዋል። (ማቴ. 24:21፤ ኤርምያስ 25:32, 33ን አንብብ።) ሆኖም ይሖዋ አገልጋዮቹን ስለሚወዳቸው በቡድን ደረጃ ከጥፋቱ ተርፈው እሱ ወዳዘጋጀው አዲስ ዓለም እንዲገቡ ያደርጋል። ወደ 2,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት የተነገረው የሚከተለው ትንቢት ይፈጸማል፦ “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።” አንተስ “ቀድሞ የነበሩት ነገሮች” አልፈው በገነት ውስጥ ለመኖር ትጓጓለህ?—ራእይ 21:4

14. እጅግ ብዙ ሕዝብ ምን ያህል ታላቅ ሆኗል?

14 የመጨረሻዎቹ ቀናት በ1914 ሲጀምሩ በዓለም ዙሪያ የነበሩት የይሖዋ አገልጋዮች በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩ ነበሩ። አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ቅቡዓን ቀሪዎች ለባልንጀሮቻቸው ባላቸው ፍቅር ተነሳስተውና በአምላክ መንፈስ እየተመሩ የመንግሥቱን ስብከት ሥራ በጽናት አከናውነዋል። በመሆኑም ምድራዊ ተስፋ ያለው እጅግ ብዙ ሕዝብ እየተሰበሰበ ነው። በአሁኑ ጊዜ በመላው ምድር ከ115,400 በላይ በሚሆኑ ጉባኤዎች ውስጥ የታቀፉ ከ8,000,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ያሉ ሲሆን ቁጥራችንም መጨመሩን ቀጥሏል። ለምሳሌ በ2014 የአገልግሎት ዓመት ከ275,500 የሚበልጡ ሰዎች ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል፤ ይህም በአማካይ በየሳምንቱ 5,300 የሚያህሉ ሰዎች ይጠመቃሉ ማለት ነው።

15. በዛሬው ጊዜ የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ምን ያህል በስፋት እየተከናወነ እንዳለ ግለጽ።

15 የስብከቱ ሥራችን ምን ያህል በስፋት እንደሚከናወን ማየቱ አስደናቂ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችን በአሁኑ ጊዜ ከ700 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ይዘጋጃሉ። መጠበቂያ ግንብ በዓለም ላይ በስፋት በመሰራጨት ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው መጽሔት ነው። በየወሩ በ247 ቋንቋዎች ከ52,000,000 በላይ በሆኑ ቅጂዎች ይታተማል። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፋችን ደግሞ ከ250 በሚበልጡ ቋንቋዎች ከ200,000,000 በላይ ቅጂዎች ታትሟል።

16. የይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል መንፈሳዊ ብልጽግና ማግኘት የቻለው ለምንድን ነው?

16 በዛሬው ጊዜ የምናየው አስደናቂ እድገት የተገኘው በአምላክ ላይ እምነት ስላለን እንዲሁም ይሖዋ በመንፈሱ መሪነት በተአምር ያስጻፈውን መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ ስለምንቀበል ነው። (1 ተሰ. 2:13) “የዚህ ሥርዓት አምላክ” የሆነው  ሰይጣን የይሖዋን ሕዝብ የሚጠላና የሚቃወም ቢሆንም እንኳ መንፈሳዊ ብልጽግና ማግኘታችን አስገራሚ ነው።—2 ቆሮ. 4:4

ምንጊዜም ለሰዎች ፍቅር አሳዩ

17, 18. የአምላክ አገልጋዮች ለማያምኑ ሰዎች ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?

17 የይሖዋ አገልጋዮች፣ ብቻውን እውነተኛ የሆነውን አምላክ ለማያመልኩ ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? የስብከቱን ሥራ ስናከናውን ሰዎች የተለያየ ምላሽ ይሰጡናል፤ አንዳንዶች ይቀበሉናል፤ ሌሎች ደግሞ ይቃወሙናል። ሰዎች የሚሰጡት ምላሽ ምንም ይሁን ምን የይሖዋ አገልጋዮች ምንጊዜም ሊኖራቸው የሚገባውን አቋም የአምላክ ቃል ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ምንጊዜም በጨው የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው ይሁን።” (ቆላ. 4:6) ስለ ተስፋችን፣ ምክንያት እንድናቀርብ ለሚጠይቀን ሰው መልስ የምንሰጠው “በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት” ሊሆን ይገባል፤ ምክንያቱም ባልንጀራችንን እንወዳለን።—1 ጴጥ. 3:15

18 የምናነጋግራቸው ሰዎች መልእክቱን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ተቆጥተው ቢጮኹብንም እንኳ ለባልንጀራችን ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። ኢየሱስ “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም። መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ለሚፈርደው [ለይሖዋ] ራሱን በአደራ” ሰጥቷል፤ እኛም የኢየሱስን ምሳሌ እንከተላለን። (1 ጴጥ. 2:23) ከእምነት ባልንጀሮቻችንም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ትሕትና በማሳየት የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ እናደርጋለን፦ “ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ አትመልሱ። ከዚህ ይልቅ ባርኩ።”—1 ጴጥ. 3:8, 9

19. ኢየሱስ ተቃዋሚዎችን በተመለከተ የትኛውን መሠረታዊ ሥርዓት ሰጥቷል?

19 የይሖዋ ሕዝቦች ትሕትና የሚያዳብሩ ከሆነ ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ የተናገረውን አስፈላጊ መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ያደርጋሉ። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “‘ባልንጀራህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፦ ጠላቶቻችሁን ውደዱ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ፤ ይህን ብታደርጉ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ፤ እሱ በክፉዎችም ሆነ በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣልና፤ በጻድቃንም ሆነ ጻድቃን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ዝናብ ያዘንባል።” (ማቴ. 5:43-45) በእርግጥም የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን፣ ሰዎች ለእኛ ያላቸው አመለካከት ምንም ይሁን ምን ‘ጠላቶቻችንን መውደድን’ መማር አለብን።

20. አዲሱ ዓለም አምላክንና ባልንጀራቸውን በሚወዱ ሰዎች እንደሚሞላ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

20 የይሖዋ ሕዝቦች እሱንና ባልንጀራቸውን እንደሚወዱ በአመለካከታቸውም ሆነ በድርጊታቸው፣ በሁሉም የሕይወታቸው ዘርፎች ማሳየት ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የመንግሥቱን መልእክት የማይቀበሉ ሰዎችም እንኳ በሚቸገሩበት ጊዜ ፍቅር እናሳያቸዋለን። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እርስ በርስ ከመዋደድ በቀር በማንም ላይ ምንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤ ሰውን የሚወድ ሁሉ ሕጉን ፈጽሟልና። ምክንያቱም ‘አታመንዝር፣ አትግደል፣ አትስረቅ፣ አትጎምጅ’ የሚሉት ሕጎችና ሌሎች ትእዛዛት በሙሉ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ በሚለው በዚህ ቃል ተጠቃለዋል። ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።” (ሮም 13:8-10) የምንኖረው በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው አንድነት የጠፋበት እንዲሁም ዓመፅና ክፋት የተስፋፋበት ዓለም ውስጥ ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን እውነተኛ ፍቅር እናሳያለን። (1 ዮሐ. 5:19) ሰይጣን፣ አጋንንቱና ዓመፀኛ ሰዎች ከጠፉ በኋላ በምድር ላይ የሚኖረው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ፍቅር የሚንጸባረቅበት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ምድር፣ አምላክንና ባልንጀራቸውን በሚወዱ ሰዎች ስትሞላ ሕይወት ምንኛ አስደሳች ይሆናል!