በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ጥቅምት 2015

ወደ አምላክ መቅረቤ ጠቅሞኛል

ወደ አምላክ መቅረቤ ጠቅሞኛል

ዘጠኝ ዓመት ሲሆነኝ ቁመቴ መጨመር አቆመ። በዚያን ጊዜ የምንኖረው ኮት ዲቩዋር ውስጥ ነበር፤ ጊዜው ደግሞ የዛሬ 34 ዓመት ነው፤ ዛሬም ቁመቴ 1 ሜትር ብቻ ነው። የደረሰብኝ የጤና እክል በታወቀበት ወቅት ወላጆቼ ነጋ ጠባ ስለ ቁመናዬ በማሰብ እንዳልጨነቅ ሲሉ በሥራ እንድጠመድ አበረታቱኝ። ቤታችን ደጃፍ ላይ ፍራፍሬ መሸጫ አዘጋጀሁ፤ ቦታውንም በሥርዓትና በንጽሕና እይዝ ነበር። ይህም ብዙ ደንበኞች እንዳፈራ አስቻለኝ።

እርግጥ፣ በሥራ መጠመዴ ችግሮቼን በሙሉ አላስወገደልኝም። አሁንም ቢሆን በቁመቴ አጭር ነው፤ በዕለት ተዕለት ሕይወቴ የማከናውናቸው ቀላል የሚመስሉ ነገሮች እንኳ ያታግሉኝ ነበር። ለምሳሌ ገበያ ሄጄ ከዕቃ መደርደሪያ ላይ የምፈልገውን ነገር ማንሳት አልችልም። ሁሉም ነገር የተሠራው ከእኔ በእጥፍ የሚበልጥ ቁመት ላላቸው ሰዎች ይመስላል። ያለሁበት ሁኔታ ትካዜ ላይ ይጥለኝ ነበር፤ ይሁንና 14 ዓመት ሲሞላኝ ይህ ሁኔታ ተለወጠ።

አንድ ቀን፣ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሁለት ሴቶች ፍራፍሬ ከገዙኝ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳጠና ጋበዙኝ። ብዙም ሳይቆይ፣ ለአካላዊ ሁኔታዬ ከምሰጠው ትኩረት ይበልጥ ይሖዋንና ዓላማውን ማወቅ አስፈላጊ ነገር እንደሆነ ተገነዘብኩ። ይህን ማወቄ እጅግ ጠቅሞኛል። መዝሙር 73:28 በጣም የምወደው ጥቅስ ነው። የዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የመጀመሪያ ክፍል “እኔ ግን ወደ አምላክ መቅረብ ይበጀኛል” ይላል።

ቤተሰባችን በድንገት ወደ ቡርኪና ፋሶ በመዛወሩ ሕይወቴ በከፍተኛ ሁኔታ ተለወጠ። በኮት ዲቩዋር እያለሁ እዚያች ቦታ ላይ ፍራፍሬ ስሸጥ አላፊ አግዳሚው ሁሉ ያውቀኝ ነበር። አሁን በምንኖርበት አዲስ አካባቢ ግን ለቦታው እንግዳ ስሆን ብዙዎች ደግሞ ሲያዩኝ ይገረሙ ጀመር። ሰዎች አፍጥጠው ይመለከቱኛል። በመሆኑም ከሰዎች ዓይን ለመራቅ ስል ለሳምንታት ከቤት ሳልወጣ እቆያለሁ። የተወሰኑ ቀናት ካለፉ በኋላ ግን ወደ ይሖዋ መቅረቤ ምን ያህል እንደጠቀመኝ ትዝ ይለኛል። ለይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ደብዳቤ በመጻፌ ናኒ የምትባል አንዲት እህት መጥታ እንድታነጋግረኝ ዝግጅት ተደረገ፤ ናኒ በሚገባ ልትረዳኝ የምትችልና ትንሽ ሞተር ብስክሌት ያላት ሚስዮናዊ ናት።

በአካባቢያችን ያሉ አሸዋማ መንገዶች የሚያንሸራትቱ ሲሆን በዝናብ ወቅት ደግሞ ይጨቀያሉ። ናኒ እኔን ለማስጠናት ስትመጣ ብዙ ጊዜ ከሞተር ብስክሌቷ ላይ ትወድቅ ነበር፤ ይህ ግን አልበገራትም። ለተወሰነ ጊዜ ካጠናን በኋላ ወደ ስብሰባ ልትወስደኝ እንደምትችል ነገረችኝ። ይህ ደግሞ ደፍሬ ከቤት መውጣትና የሰዎችን ዓይን መቋቋም እንደሚጠይቅብኝ ተገነዘብኩ። ከዚህም ሌላ ቀድሞውንም ለመንዳት አስቸጋሪ በሆነችው በዚህች ሞተር ብስክሌት ላይ መፈናጠጤ ክብደት ይጨምርባታል።  ይሁን እንጂ በምወደው ጥቅስ ላይ የሚገኘው “ሉዓላዊውን ጌታ ይሖዋን መጠጊያዬ አድርጌዋለሁ” የሚለው የመጨረሻው ክፍል በያዘው ማበረታቻ ግብዣዋን ተቀበልኩ።

እኔና ናኒ አንዳንድ ጊዜ ጭቃ ውስጥ እንወድቅ የነበረ ቢሆንም ወደ ስብሰባ መሄዳችን የሚክስ ነበር። መንግሥት አዳራሹ ውስጥ ያሉት ወንድሞችና እህቶች የሚያሳዩኝ ሞቅ ያለ ፈገግታ መንገድ ላይ ከሚያፈጡብኝ ሰዎች ምንኛ የተለየ ነው! ከዘጠኝ ወር በኋላ ደግሞ ተጠመቅኩ።

የምወደው ጥቅስ ሁለተኛው ክፍል “ሥራዎቹን ሁሉ እንዳውጅ” የሚል ሐሳብ ይዟል። ከምንም በላይ ፈተና የሚሆንብኝ አገልግሎት መውጣት እንደሆነ ገብቶኝ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ወደ ቤት ያገለገልኩበትን ወቅት መቼም አልረሳውም። ልጆችም ሆኑ ትላልቅ ሰዎች አፍጥጠው ያዩኝ፣ ከኋላ ከኋላ ይከተሉኝ እንዲሁም አረማመዴን ለመኮረጅ ይሞክሩ ነበር። ይህ በእርግጥ ስሜት የሚጎዳ ቢሆንም እነሱም እንደ እኔ በገነት መኖር እንደሚያስፈልጋቸው ሁልጊዜ ራሴን ማስታወስ ነበረብኝ፤ ይህም እንድጸና አስችሎኛል።

በእጅ የሚንቀሳቀስ ባለ ሦስት እግር ብስክሌት ማግኘቴ ችግሬን አቀለለልኝ። የአገልግሎት ጓደኛዬ ዳገቱን እስክወጣ ትገፋኝና ቁልቁለቱን መውረድ ስንጀምር እሷም ከኋላዬ ተፈናጣ አብረን እንወርዳለን። መጀመሪያ ላይ ተፈታታኝ ሆኖብኝ የነበረው አገልግሎት የኋላ ኋላ የደስታ ምንጭ ስለሆነልኝ በ1998 የዘወትር አቅኚ ለመሆን በቃሁ።

ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የነበሩኝ ሲሆን ከእነሱ መካከል አራቱ ተጠምቀዋል። በተጨማሪም ከእህቶቼ መካከል አንዷ እውነትን ተቀብላለች! ስሜቴ በሚደቆስበት ጊዜ ሌሎች ያደረጉትን እድገት መስማቴ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል። አንድ ቀን በወባ በሽታ ታምሜ ሳለሁ ከኮት ዲቩዋር ደብዳቤ ደረሰኝ። ቡርኪና ፋሶ ውስጥ አንድን የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ቤቱ በር ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስጀምሬው ነበር፤ ከዚያም ለአንድ ወንድም ሰጠሁት። ይህ ጥናት ከጊዜ በኋላ በኮት ዲቩዋር መኖር ጀመረ። እድገት አድርጎ ያልተጠመቀ አስፋፊ መሆኑን ስሰማ በጣም ተደሰትኩ!

መተዳደሪያ የማገኘው እንዴት ነው? አካል ጉዳተኞችን የሚረዳ አንድ ድርጅት ልብስ መስፋት ሊያስተምረኝ እንደሚችል ሐሳብ አቀረበልኝ። አንዲት አስተማሪ ትጉ ሠራተኛ መሆኔን አስተውላ “ሳሙና መሥራት ብናስተምርሽ ይሻላል” አለችኝ። በመሆኑም ሳሙና መሥራት ተማርኩ። ቤቴ ሆኜ ልብስ ማጠቢያና ቤት ማጽጃ ሳሙና እሠራለሁ። ሰዎች ሳሙናውን ስለሚወዱት ሌሎችም ከእኔ እንዲገዙ ያበረታታሉ። ደግሞም ባለ ሦስት እግር ሞተር ብስክሌት ተጠቅሜ ሳሙናውን ራሴ አደርስላቸዋለሁ።

የሚያሳዝነው ነገር በ2004 አከርካሪ አጥንቴ የተጣመመ መሆኑ የሚያስከትልብኝ ሥቃይ በጣም እየተባባሰ በመሄዱ አቅኚነቴን ማቋረጥ ግድ ሆነብኝ። ያም ሆኖ በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ማድረጌን ቀጥያለሁ።

ሰዎች ወደ ሌሎች በሚጋባው ፈገግታዬ እንደምታወቅ ይነግሩኛል። በእርግጥም ወደ አምላክ መቅረቤ ስለጠቀመኝ ደስተኛ የምሆንበት አጥጋቢ ምክንያት አለ።—ሴረ ማይገ እንደተናገረችው