በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  መስከረም 2015

 የሕይወት ታሪክ

የይሖዋ በረከት ሕይወቴ በደስታ እንዲሞላ አድርጓል

የይሖዋ በረከት ሕይወቴ በደስታ እንዲሞላ አድርጓል

በ1927 ካናዳ ውስጥ በሰስካችዋን ግዛት ዋካ በምትባል አንዲት ትንሽ ከተማ ተወለድኩ። አባቴና እናቴ ሰባት ልጆች የወለዱ ሲሆን አራት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ነበርን፤ ስለዚህ ከሕፃንነቴ ጀምሮ ያደግኩት በሰዎች ተከብቤ ነው ማለት ይቻላል።

በ1930ዎቹ ተከስቶ የነበረው ታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት የእኛንም ቤተሰብ ነክቷል። ሀብታም ባንሆንም የምንበላውን አጥተን አናውቅም። የተወሰኑ ዶሮዎችና አንዲት ላም ስለነበሩን እንቁላል፣ ወተት፣ አይብና ቅቤ ከቤታችን ጠፍቶ አያውቅም። ቤተሰባችን በግብርና የሚተዳደር እንደመሆኑ መጠን ሁላችንም ሥራ ነበረን።

ስለዚያ ጊዜ ብዙ አስደሳች ትዝታዎች አሉኝ፤ ለምሳሌ ቤቱ ጣፋጭ በሆነ የፖም መዓዛ ይሞላ እንደነበር አስታውሳለሁ። አባቴ በመከር ወቅት የግብርና ምርቶችን ለመሸጥ ወደ ከተማ ሲሄድ ብዙውን ጊዜ ወዲያው የተለቀሙ የፖም ፍሬዎችን በሣጥን ይዞ ይመጣ ነበር። ገና ሲገምጡት ውኃው አፍ የሚሞላ ፖም በየቀኑ እንበላ ነበር!

ቤተሰባችን እውነትን ሰማ

ወላጆቼ እውነትን ሲሰሙ የስድስት ዓመት ልጅ ነበርኩ። ወላጆቼ የመጀመሪያ ልጅ የነበረው ጆኒ ገና እንደተወለደ ብዙም ሳይቆይ በመሞቱ በጣም አዝነው ነበር። በመሆኑም ወላጆቼ የአካባቢውን ቄስ “አሁን ጆኒ የት ነው ያለው?” ብለው ጠየቁት። ቄሱም ሕፃኑ ክርስትና ስላልተነሳ ወደ ሰማይ እንዳልሄደ ነገራቸው። በተጨማሪም ቄሱ ወላጆቼ ገንዘብ ከከፈሉት ጆኒ ሰማይ እንዲገባ እንደሚጸልይለት ተናገረ። እንዲህ የተባላችሁት እናንተ ብትሆኑ ኖሮ ምን ይሰማችሁ ነበር? አባቴና እናቴ ቄሱ ያልጠበቁትን መልስ ስለሰጣቸው ከዚያ በኋላ ያንን ቄስ አነጋግረውት አያውቁም። ሆኖም ጆኒ ስላለበት ሁኔታ ማሰባቸውን አልተዉም።

አንድ ቀን እናቴ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ሙታን የት ናቸው? (እንግሊዝኛ) የተባለውን ቡክሌት አገኘች። በጉጉት አነበበችው። አባቴ ቤት ሲመጣ እናቴ በደስታ “ጆኒ ያለበትን ቦታ አወቅኩት! አሁን ተኝቷል፤ አንድ ቀን ግን ከእንቅልፉ ይነቃል” አለችው። አባቴም ያን ዕለት ምሽት ይህን ቡክሌት ሙሉውን አነበበው። እናቴና አባቴ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን አንቀላፍተው እንዳሉና ወደፊት ደግሞ ትንሣኤ እንደሚኖር የሚናገር መሆኑን ማወቃቸው አጽናናቸው።—መክ. 9:5, 10፤ ሥራ 24:15

ወላጆቼ ያወቁት ይህ የሚያስደስትና የሚያጽናና ተስፋ ሕይወታችን እንዲለወጥ አደረገ። እነሱም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በዋካ ካለው አነስተኛ ጉባኤ ጋር መሰብሰብ ጀመሩ፤ አብዛኞቹ የዚህ ጉባኤ አባላት ዩክሬናውያን ናቸው። ብዙም ሳይቆይ እናቴና አባቴ በስብከቱ ሥራ መካፈል ጀመሩ።

ከጊዜ በኋላ ወደ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ተዛወርን፤ በዚያ ያለው ጉባኤም በጥሩ ሁኔታ ተቀበለን። እሁድ ለምናደርጋቸው ስብሰባዎች በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን መጠበቂያ ግንብ የምንዘጋጅበትን ጊዜ እወደው ነበር። ሁላችንም ለይሖዋና ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጥልቅ ፍቅር ነበረን። ሕይወታችን ምን ያህል አስደሳች እንደነበረና ይሖዋም እንዴት እንደባረከን ማየት ችያለሁ።

 ልጆች ሳለን ስለ እምነታችን ለሌሎች መናገር ይከብደን ነበር። ይሁንና እኔና ታናሽ እህቴ ኢቫ ብዙ ጊዜ የወሩን የመስክ አገልግሎት አቀራረብ ተዘጋጅተን በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ሠርቶ ማሳያ እናቀርብ ነበር። ለሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መናገር ያሳፍረን የነበረ ቢሆንም እንዲህ ማድረጋችን ጠቅሞናል። መስበክ እንድንችል በዚህ መንገድ ሥልጠና በማግኘታችን በጣም አመስጋኝ ነኝ!

ከማልረሳቸው የልጅነት ትዝታዎቼ አንዱ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ቤታችን ያርፉ የነበረበትን ጊዜ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቻችን ወንድም ጃክ ናታን ጉባኤያችንን በሚጎበኝበት ጊዜ እኛ ቤት ስለሚያርፍ ደስ ይለን ነበር። * የተለያዩ አስደሳች ታሪኮችን ይነግረን ነበር፤ ደግሞም ከልብ ያመሰግነን ስለነበር ይሖዋን በታማኝነት እንድናገለግለው አነሳስቶናል።

“ሳድግ እንደ ወንድም ናታን መሆን እፈልጋለሁ” ብዬ አስብ ነበር። በወቅቱ የእሱ ምሳሌነት ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት እያዘጋጀኝ እንደነበረ አልተገነዘብኩም። አሥራ አምስት ዓመት ሲሞላኝ ይሖዋን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ አደረግኩ። በ1942 እኔና ኢቫ ተጠመቅን።

የእምነት ፈተናዎች

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአገር ፍቅር ስሜት በጣም በጦፈበት ጊዜ ሚስ ስኮት የተባለች የይሖዋ ምሥክሮችን የምትጠላ አንዲት አስተማሪ ሁለቱን እህቶቼንና ወንድሜን ከትምህርት ቤት አባረረቻቸው። ለምን? ምክንያቱም ለሰንደቅ ዓላማ ሰላምታ ለመስጠት ፈቃደኞች አልነበሩም። ከዚያም ሚስ ስኮት አስተማሪዬን እኔንም ከትምህርት ቤት እንድታባርረኝ አጥብቃ አሳሰበቻት። አስተማሪዬ ግን “የምንኖረው ነፃነት ባለበት አገር ውስጥ ነው፤ በመሆኑም የአገር ፍቅር ስሜት በሚንጸባረቅባቸው ሥነ ሥርዓቶች አለመካፈል መብት አለን” አለቻት። ሚስ ስኮት አስተማሪዬ ላይ ጫና ለማሳደር ብትሞክርም አስተማሪዬ ኮስተር ብላ “በቃ ይህ የእኔ ውሳኔ ነው” አለቻት።

ሚስ ስኮት ግን “በፍጹም፣ ያንቺ ውሳኔ አይደለም። ሜሊታን የማታባርሪያት ከሆነ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት አደርጋለሁ” በማለት መለሰችላት። አስተማሪዬም እኔን ከትምህርት ቤት ማባረር ትክክል እንዳልሆነ ብታምንም ሥራዋን ላለማጣት ከፈለገች እኔን ከማባረር ሌላ አማራጭ እንደሌላት ለወላጆቼ ገለጸችላቸው። ይሁን እንጂ ቤት ሆነን ትምህርታችንን መቀጠል እንድንችል የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን አገኘን። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ 32 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ አንድ ቦታ ተዛወርንና ሌላ ትምህርት ቤት ገባን።

በጦርነቱ ሳቢያ ጽሑፎቻችን ቢታገዱም መጽሐፍ ቅዱስ ይዘን ከቤት ወደ ቤት እንሄድ ነበር። በዚህም የተነሳ የመንግሥቱን ምሥራች በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ አውጥተን በመስበክ ረገድ ጥሩ ችሎታ አዳበርን። ይህ ደግሞ በመንፈሳዊ እንድናድግና የይሖዋን ድጋፍ እንድንመለከት ረድቶናል።

ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መግባት

በፀጉር ሥራ ጥሩ ተሰጥኦ የነበረኝ ሲሆን የተወሰኑ ሽልማቶችንም ለማግኘት በቅቻለሁ

እኔና ኢቫ ትምህርታችንን ስንጨርስ አቅኚ ሆንን። መተዳደሪያ ለማግኘት በአንድ መደብር ውስጥ ሥራ ጀመርኩ። ከጊዜ በኋላ ግን ቀድሞም ቢሆን እወደው በነበረው የፀጉር ሥራ የስድስት ወር ሥልጠና ወሰድኩ። በአንድ ፀጉር ቤት ውስጥ በሳምንት ሁለት ቀን የምሠራበትና ይህን ሙያ በወር ሁለት ጊዜ የማስተምርበት ሥራ አገኘሁ። በዚህ መንገድ ወጪዬን በመሸፈን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ቀጠልኩ።

በ1955 በኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና በኑረምበርግ፣ ጀርመን “ድል አድራጊው መንግሥት” በሚል ርዕስ በሚደረጉት ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ፈልጌ ነበር። ወደ ኒው ዮርክ ከመሄዴ በፊት ግን ከዋናው መሥሪያ ቤት ከመጣው ከወንድም ናታን ኖር ጋር ተዋወቅኩ። እሱና ባለቤቱ በቫንኩቨር፣ ካናዳ በተደረገው የክልል ስብሰባ ላይ  ተገኝተው ነበር። በጉብኝታቸው ወቅት የእህት ኖርን ፀጉር እንድሠራ ተጠየቅኩ። ወንድም ኖር ባለቤቱን ፀጉሯን ቆንጆ አድርጌ ስለሠራሁ ሊያገኘኝ ፈለገ። እየተጫወትን ሳለን ወደ ጀርመን ከመሄዴ በፊት ኒው ዮርክ ለመሄድ እንዳሰብኩ ነገርኩት። እሱም ብሩክሊን በሚገኘው ቤቴል ለዘጠኝ ቀናት እንድሠራ ጋበዘኝ።

እዚያ መሄዴ ሕይወቴን ለወጠው። በኒው ዮርክ ሳለሁ ቴዎዶር (ቴድ) ጃራዝ ከሚባል አንድ ወጣት ወንድም ጋር ተዋወቅኩ። እሱም ገና ከመተዋወቃችን “አቅኚ ነሽ?” ብሎ ሲጠይቀኝ ገረመኝ። እኔም “አይደለሁም” ብዬ መለስኩለት። ጓደኛዬ ላቮን ግን ጭውውታችን ድንገት ጆሮዋ ውስጥ ጥልቅ ሲል በመሃል አቋርጣ “አዎ፣ አቅኚ ናት” አለችው። ቴድ በመገረም ላቮንን “እንዴ፣ ስለዚህ ጉዳይ የሚያውቀው ማን ነው? እሷ ናት ወይስ አንቺ?” ብሎ ጠየቃት። እኔም አቅኚ እንደነበርኩና አሁን ከስብሰባው እንደተመለስኩ አቅኚነቴን ለመቀጠል እንዳሰብኩ ነገርኩት።

መንፈሳዊ ሰው አገባሁ

በ1925 በኬንታኪ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የተወለደው ቴድ ሕይወቱን ለይሖዋ ወስኖ የተጠመቀው በ15 ዓመቱ ነበር። ከቤተሰቡ መካከል ወደ እውነት የመጣ አንድም ሰው ባይኖርም እሱ ግን ከተጠመቀ ከሁለት ዓመት በኋላ የዘወትር አቅኚ ሆነ። ለ67 ዓመት ገደማ የዘለቀውን የሙሉ ጊዜ አገልግሎቱን የጀመረው በዚህ መንገድ ነበር።

ቴድ ሐምሌ 1946 በ20 ዓመቱ ከጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ሰባተኛው ክፍል ተመረቀ። ከዚያ በኋላ በክሌቭላንድ፣ ኦሃዮ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ አገልግሏል። ከአራት ዓመት ገደማ በኋላ ደግሞ በአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካች ሆኖ እንዲያገለግል ተመደበ።

ቴድ በኑረምበርግ፣ ጀርመን በተደረገው የክልል ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ስለነበረ የተወሰነ ጊዜ አብረን አሳለፍን። በዚህ ጊዜ ተዋደድን። የእሱም ግብ ይሖዋን በሙሉ ነፍስ ማገልገል እንደሆነ ሳውቅ ደስ አለኝ። ቴድ ኃላፊነቱን በቁም ነገር የሚወጣ ኮስታራ ሰው ቢሆንም ደግና በቀላሉ የሚቀረብ ነው። ከራሱ ይልቅ የሌሎችን ጥቅም የሚያስቀድም ሰው መሆኑን መመልከት ችዬ ነበር። ከስብሰባው በኋላ ቴድ ወደ አውስትራሊያ የተመለሰ ሲሆን እኔም ወደ ቫንኩቨር ሄድኩ፤ ይሁን እንጂ ደብዳቤ እንጻጻፍ ነበር።

ቴድ በአውስትራሊያ ለአምስት ዓመት ያህል ካገለገለ በኋላ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለሰ፤ ከዚያም በአቅኚነት ለማገልገል ወደ ቫንኩቨር መጣ። ቤተሰቤ ቴድን በጣም እንደወደደው ስመለከት ደስ አለኝ። ታላቅ ወንድሜ ማይክል ለእኔ በጣም ያስብልኝ ስለነበረ ብዙ ጊዜ አንድ ወጣት ወንድም በእኔ ላይ ዓይኑን ሲጥል ካየ ጉዳዩ እንዳሳሰበው ይገልጽልኝ ነበር። ይሁንና ማይክል፣ ቴድን ወዲያውኑ ወደደው። “ሜሊታ፣ አሁን ጥሩ ሰው አግኝተሻል። እንዳያመልጥሽ በደንብ ያዥው” አለኝ።

በ1956 ከተጋባን በኋላ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ብዙ ዓመት በደስታ አብረን አሳልፈናል

እኔም ብሆን ቴድን በጣም ወድጄው ነበር። ታኅሣሥ 10, 1956 ተጋባን። በመጀመሪያ በቫንኩቨር ቀጥሎ ደግሞ በካሊፎርኒያ በአቅኚነት አገልግለናል፤ ከዚያም በሚዙሪና በአርካንሶ በወረዳ ሥራ እንድናገለግል ተመደብን። በአብዛኛው የዩናይትድ ስቴትስ ግዛት 18 ለሚያህሉ ዓመታት በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ስናገለግል በየሳምንቱ የተለያየ ሰው ቤት እናርፍ ነበር። በአገልግሎት አስደሳች ተሞክሮዎችን ያገኘን ከመሆኑም በላይ ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል። በየሳምንቱ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መጓጓዝ ቀላል ባይሆንም ይህን ሥራ በጣም እንወደው ነበር።

በተለይ ቴድን በጣም የማደንቀው ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና በቁም ነገር የሚመለከት መሆኑ ነው። የአጽናፈ ዓለም ገዢ ለሆነው አምላክ የሚያቀርበውን ቅዱስ አገልግሎት ከፍ አድርጎ ይመለከት ነበር። አብረን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብም ሆነ ማጥናት ያስደስተን ነበር። ማታ ማታ ከመተኛታችን በፊት ከአልጋችን አጠገብ ተንበርክከን ቴድ ይጸልያል። ከዚያም በየግላችን እንጸልያለን። ቴድ አንድ የሚያስጨንቅ ነገር ሲያጋጥመው ይገባኝ ነበር። እንደገና ከአልጋ ወርዶ ይንበረከክና ድምፁን ሳያሰማ ለረጅም ሰዓት ይጸልያል። ትላልቅም ሆነ ትናንሽ ለሆኑ ጉዳዮች ወደ ይሖዋ የመጸለይ  ልማድ ያለው መሆኑ ከማደንቅለት ነገሮች መካከል አንዱ ነው።

ከተጋባን ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ቴድ በመታሰቢያው ላይ ከሚቀርበው ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን መካፈል ሊጀምር እንደሆነ ገለጸልኝ። “ይሖዋ የሚፈልገውን ነገር እያደረግኩ ስለመሆኔ እርግጠኛ ለመሆን ስለዚህ ጉዳይ በጥብቅ ስጸልይበት ቆይቻለሁ” አለኝ። በሰማይ እንዲያገለግል በአምላክ መንፈስ መቀባቱ ያን ያህል አላስገረመኝም። እንዲያውም ከክርስቶስ ወንድሞች አንዱን የመደገፍ ውድ መብት እንዳገኘሁ አድርጌ ቆጠርኩት።—ማቴ. 25:35-40

ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ የምንችልበት ሌላ አጋጣሚ

በ1974 ቴድ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል እንዲሆን ሲጋበዝ ፈጽሞ ያልጠበቅነው ነገር ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በብሩክሊን ቤቴል እንድናገለግል ተጠራን። ቴድ የበላይ አካል አባል በመሆን የተጣለበትን ኃላፊነት ሲወጣ እኔ ደግሞ በጽዳት ሥራ ወይም በፀጉር ሥራ እካፈል ነበር።

ቴድ ካሉበት ኃላፊነቶች መካከል አንዱ የተለያዩ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን መጎብኘት ይገኝበታል። ቴድ በተለይ እገዳ ባለባቸው አገሮች የሚካሄደው የስብከት ሥራ ይበልጥ ያሳስበው ነበር። አንድ ጊዜ እረፍት በጣም አስፈልጎን ለዚሁ ዓላማ ስዊድን አገር ሳለን ቴድ “ሜሊታ፣ ፖላንድ ውስጥ የስብከቱ ሥራ ታግዷል፤ ስለዚህ እዚያ ያሉትን ወንድሞች ብረዳቸው ደስ ይለኛል” አለኝ። ስለዚህ ቪዛ አስመትተን ወደ ፖላንድ ሄድን። ቴድ ሥራውን በኃላፊነት ከሚመሩ አንዳንድ ወንድሞች ጋር ተገናኘ፤ ከዚያም ማንም ሰው የሚነጋገሩትን ነገር እንዳይሰማ ራቅ ወዳለ አካባቢ በእግራቸው ሄዱ። ወንድሞች ተሰብስበው ለአራት ቀን ሰፊ ውይይት አደረጉ፤ እኔም ቴድ መንፈሳዊ ቤተሰቡን መርዳት በመቻሉ ምን ያህል እርካታ እንዳገኘ ሳይ ተደሰትኩ።

ከዚያ በኋላ ለጉብኝት ወደ ፖላንድ የሄድነው ኅዳር 1977 ነበር። ዋናው መሥሪያ ቤት ባደረገው ዝግጅት መሠረት የበላይ አካል አባላት የሆኑት ወንድም ፍራንዝ፣ ዳንኤል ሲድሊክና ቴድ ለመጀመሪያ ጊዜ አብረው ፖላንድን ጎበኙ። በዚያን ጊዜ ሥራችን ገና እንደታገደ ቢሆንም ሦስቱ የበላይ አካል አባላት የበላይ ተመልካቾችን፣ አቅኚዎችንና ከተለያዩ ከተሞች የመጡ ለረጅም ዓመት በእውነት ቤት የቆዩትን ማነጋገር ችለው ነበር።

በሩሲያ ሥራችን ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ ከተመዘገበ በኋላ ቴድና ሌሎች ወንድሞች በሞስኮ፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ቢሮ ፊት ለፊት

በቀጣዩ ዓመት ወንድም ሚልተን ሄንሼልና ቴድ ፖላንድን የጎበኙ ሲሆን ለእኛም ሆነ ለሥራችን ቀና አመለካከት ማዳበር ከጀመሩ ባለሥልጣናት ጋር ተነጋግረው ነበር። በ1982 የፖላንድ መንግሥት ወንድሞቻችን የአንድ ቀን ትልቅ ስብሰባ እንዲያደርጉ ፈቀደላቸው። በቀጣዩ ዓመት የክልል ስብሰባዎች ተደረጉ፤ ወንድሞች በአብዛኛው እነዚህን ስብሰባዎች ያደረጉት አዳራሾችን ተከራይተው ነበር። በ1985 እገዳው ገና ያልተነሳ ቢሆንም በትላልቅ ስታዲየሞች አራት የክልል ስብሰባዎችን እንድናደርግ ተፈቀደልን። ከዚያም ግንቦት 1989 ከእነዚህ የበለጡ ትላልቅ ስብሰባዎችን ለማድረግ በዝግጅት ላይ እያለን የፖላንድ መንግሥት ለይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና ሰጠ። ቴድን እንደዚህ ያስደሰተው ነገር የለም ማለት ይቻላል።

በፖላንድ የተደረገ የክልል ስብሰባ

 የጤና ችግሮችን መቋቋም

በ2007 በደቡብ አፍሪካ በሚደረገው የቅርንጫፍ ቢሮ ውሰና ላይ ለመገኘት በጉዞ ላይ ነበርን። እንግሊዝ ስንደርስ ቴድ ከደም ግፊት ጋር በተያያዘ ችግር አጋጠመውና ሐኪሙ ጉዞውን ለሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፍ ሐሳብ አቀረበለት። ቴድ ሕመሙ ሲሻለው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለስን። ሆኖም ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ በጭንቅላቱ ውስጥ ደም በመፍሰሱ በቀኝ ጎኑ በኩል ሽባ ሆነ።

ቴድ ቶሎ ስላልተሻለው መጀመሪያ ላይ ወደ ቢሮው መሄድ አይችልም ነበር። ይሁንና በሽታው በአንደበቱ ላይ ምንም ችግር ስላልፈጠረበት አመስጋኞች ነበርን። ቴድ የአቅም ገደቦች ቢኖሩበትም መደበኛ ሥራውን ለማከናወን ይጥር ነበር፤ እንዲያውም ሳሎናችን ውስጥ ሆኖ የበላይ አካሉ በሚያደርገው ሳምንታዊ ስብሰባ ላይ በስልክ ይሳተፍ ነበር።

ቴድ በቤቴል ክሊኒክ ውስጥ ይሰጠው የነበረው የፊዝዮቴራፒ ሕክምና በእጅጉ እንደጠቀመው ይሰማው ነበር። ቀስ በቀስ አብዛኛው የሰውነቱ ክፍል ዳግመኛ መንቀሳቀስ ጀመረ። አንዳንዶቹን ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶቹን ይወጣ የነበረ ሲሆን ሁልጊዜ ደስተኛ ለመሆን ይጥር ነበር።

ከሦስት ዓመት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በጭንቅላቱ ውስጥ ደም ፈሰሰ፤ ከዚያም ረቡዕ ሰኔ 9, 2010 አረፈ። ቴድ አንድ ቀን ምድራዊ ሕይወቱን ማጠናቀቁ እንደማይቀር ባውቅም ለእኔ እሱን ማጣት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በቃላት መግለጽ አልችልም። ያም ሆኖ አቅሜ በፈቀደው መጠን ቴድን መርዳት በመቻሌ ይሖዋን በየቀኑ አመሰግነዋለሁ። ከ53 የሚበልጡ ዓመታትን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አብረን በደስታ አሳልፈናል። ቴድ ወደ ሰማዩ አባቴ ይበልጥ መቅረብ እንድችል ስለረዳኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። አሁን አዲሱ የሥራ ምድቡ ታላቅ ደስታና እርካታ እንደሚያመጣለት ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም።

አዳዲስ ተፈታታኝ ሁኔታዎች

በቤቴል የውበት ሳሎን ውስጥ መሥራትም ሆነ ሌሎችን ማሠልጠን በመቻሌ ደስተኛ ነኝ

ከባለቤቴ ጋር በሥራ ተጠምደን በርካታ አስደሳች ዓመታት ስላሳለፍን አሁን ያጋጠሙኝን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መጋፈጥ ለእኔ ቀላል አይደለም። እኔና ቴድ ወደ ቤቴልም ሆነ ወደ መንግሥት አዳራሻችን የሚመጡ እንግዶችን መቀበል ያስደስተን ነበር። አሁን የምወደው ቴድ ከጎኔ ባለመኖሩና እኔም አቅሜ እየደከመ በመሆኑ እንደቀድሞው ከሌሎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ አልችልም። ያም ሆኖ በቤቴልና በጉባኤ ከምወዳቸው ወንድሞቼና እህቶቼ ጋር መሆን ደስ ይለኛል። የቤቴል ሕይወት ቀላል አይደለም፤ ሆኖም በዚህ መንገድ አምላክን ማገልገል መቻል ደስታ ያስገኛል። ለስብከቱ ሥራ ያለኝ ፍቅር አሁንም ቢሆን አልቀነሰም። ቶሎ የሚደክመኝና ረጅም ሰዓት መቆም የማልችል ብሆንም በመንገድ ላይ መመሥከርና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት ያስደስተኛል።

በዓለም ላይ እየደረሱ ያሉትን እጅግ አሰቃቂ ነገሮች ስመለከት እንዲህ ካለ ጥሩ የትዳር ጓደኛ ጋር በይሖዋ አገልግሎት በማሳለፌ በጣም ደስተኛ ነኝ! በእርግጥም የይሖዋ በረከት ሕይወቴ በደስታ እንዲሞላ አድርጓል።—ምሳሌ 10:22

^ አን.13 የወንድም ጃክ ናታን የሕይወት ታሪክ በመስከረም 1, 1990 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 10-14 [መግ 17-111 ከገጽ 10-13] ላይ ወጥቷል።