በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

በተስፋ ጠብቁ!

በተስፋ ጠብቁ!

“ቢዘገይ እንኳ በተስፋ ጠብቀው!”—ዕን. 2:3

መዝሙሮች፦ 128, 45

1, 2. ከጥንት ዘመን ጀምሮ የይሖዋ አገልጋዮች ምን ዓይነት አመለካከት ነበራቸው?

ከጥንት ዘመን ጀምሮ የይሖዋ አገልጋዮች በመንፈስ መሪነት የተነገሩ ትንቢቶችን ፍጻሜ ለማየት ይጠባበቁ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኤርምያስ ይሁዳ ባድማ እንደምትሆን ተንብዮ ነበር፤ ትንቢቱ በ607 ዓ.ዓ. ይሁዳ በባቢሎናውያን እጅ ስትጠፋ በትክክል ተፈጽሟል። (ኤር. 25:8-11) ኢሳይያስ፣ ይሖዋ ሕዝቡን ቀድሞ ወደነበሩበት ሁኔታ እንደሚመልስ በመንፈስ ተመርቶ ሲናገር “እሱን በተስፋ የሚጠባበቁ ሁሉ ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ኢሳ. 30:18) ጥንት ስለነበሩት የአምላክ ሕዝቦች ትንቢት የተናገረው ሚክያስም “ይሖዋን በጉጉት እጠባበቃለሁ” በማለት የራሱን አቋም ገልጿል። (ሚክ. 7:7) የአምላክ አገልጋዮች ስለ መሲሑ ወይም ስለ ክርስቶስ የተነገሩ ትንቢቶችን ፍጻሜም ለዘመናት በተስፋ ሲጠባበቁ ቆይተዋል።—ሉቃስ 3:15፤ 1 ጴጥ. 1:10-12 *

2 ከመሲሑ ጋር የተያያዙ ትንቢቶች አሁንም እየተፈጸሙ በመሆናቸው በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦችም የእነዚህን ትንቢቶች ፍጻሜ ለማየት በተስፋ ይጠባበቃሉ። በቅርቡ ይሖዋ በመሲሐዊው መንግሥት አማካኝነት ክፉዎችን በማጥፋት የሰው ልጆችን መከራ ያስወግዳል፤ እንዲሁም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ካለው ከዚህ ያልተረጋጋ ዓለም ሕዝቡን ነፃ ያወጣል። (1 ዮሐ. 5:19) በመሆኑም የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በፍጥነት እየተቃረበ እንደሆነ በመገንዘብ ምንጊዜም ንቁ ሆነን እንጠብቅ።

3. የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ ለረጅም ጊዜ ስንጠባበቅ ከቆየን የትኛው ጥያቄ ሊፈጠርብን ይችላል?

 3 የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የአምላክ ፈቃድ “በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም” ላይ ሲፈጸም ለማየት እንጓጓለን። (ማቴ. 6:10) አንዳንዶች የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ ረጅም ለሚመስል ጊዜ ሲጠባበቁ ቆይተዋል፤ በመሆኑም ‘አሁንም በተስፋ መጠበቃችንን ለመቀጠል የሚያበቃ አጥጋቢ ምክንያት አለን?’ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። እስቲ መልሱን እየተመለከትን እንሂድ።

በተስፋ መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው?

4. ነቅተን ለመጠበቅ የሚያነሳሳን አንዱ ትልቅ ምክንያት ምንድን ነው?

4 መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ የሚመጣውን የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ በምንጠባበቅበት ጊዜ ሊኖረን ስለሚገባው አመለካከት በግልጽ ይናገራል። ኢየሱስ ተከታዮቹን “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ” እንዲሁም “ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ማቴ. 24:42፤ ሉቃስ 21:34-36) ኢየሱስ እንዲህ እንድናደርግ መናገሩ በራሱ በተስፋ ለመጠባበቅ የሚያነሳሳን አጥጋቢ ምክንያት ነው! ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የይሖዋ ድርጅት ምሳሌ ይሆነናል። በየጊዜው በሚያወጣቸው ጽሑፎች አማካኝነት ‘የይሖዋን ቀን መምጣት እንድንጠብቅና በአእምሯችን አቅርበን እንድንመለከት’ እንዲሁም አምላክ ባዘጋጀው አዲስ ዓለም ላይ ትኩረት እንድናደርግ በተደጋጋሚ ሲያሳስበን ቆይቷል።2 ጴጥሮስ 3:11-13ን አንብብ።

5. በተለይ በአሁኑ ጊዜ ንቁዎች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

5 ጥንት የነበሩት ክርስቲያኖች በተስፋ መጠባበቃቸው አስፈላጊ የነበረ ቢሆንም በተለይ በአሁኑ ጊዜ ይህን ማድረግ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም የምንኖረው ክርስቶስ በሥልጣኑ በተገኘበት ጊዜ ላይ ነው። ከ1914 ጀምሮ የመገኘቱ ምልክት በግልጽ እየታየ ነው። ብዙ ገጽታዎች ያሉት ይህ ምልክት የዓለም ሁኔታ እየተባባሰ መሄዱን እንዲሁም የመንግሥቱ የስብከት ሥራ በዓለም ዙሪያ መከናወኑን ይጨምራል፤ የምልክቱ መፈጸም ደግሞ የምንኖረው “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” በተባለው ጊዜ ላይ መሆኑን ያሳያል። (ማቴ. 24:3, 7-14) ኢየሱስ የሥርዓቱ መደምደሚያ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ መጨረሻው እስከሚመጣ ድረስ ምን ያህል ጊዜ እንደሚያልፍ አልተናገረም፤ በመሆኑም ይበልጥ ንቁዎች መሆን ይኖርብናል።

6. ወደ መጨረሻው እየተቃረብን ስንሄድ የዓለም ሁኔታ እንደሚባባስ መጠበቅ የምንችለው ለምንድን ነው?

6 “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” የሚለው ሐሳብ የዓለም ሁኔታ ከዚህ ይበልጥ የከፋ ደረጃ ላይ የሚደርስበትን ወደፊት የሚመጣ ጊዜም ያመለክት ይሆን? የሚል ጥያቄ ይፈጠርብን ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ክፋት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚባባስ ይነግረናል። (2 ጢሞ. 3:1, 13፤ ማቴ. 24:21፤ ራእይ 12:12) በመሆኑም ዓለም በአሁኑ ጊዜ መጥፎ ሁኔታ ላይ ቢሆንም ወደፊት ከዚህም እየከፋ እንደሚሄድ መጠበቅ እንችላለን።

7. በመጨረሻዎቹ ቀናት በዓለም ላይ ስለሚኖረው ሁኔታ ማቴዎስ 24:37-39 ምን ይጠቁመናል?

7 ይሁንና ‘ታላቁ መከራ’ ከመጀመሩ በፊት ነገሮች ምን ያህል የከፉ እንደሚሆኑ ትጠብቃለህ? (ራእይ 7:14) ለምሳሌ በየአገሩ ጦርነት እንደሚነሳ፣ ማንም ሰው የሚላስ የሚቀመስ እንደማያገኝና በየቤቱ የታመመ ሰው እንደሚኖር ትጠብቃለህ? ሁኔታዎች እዚህ ደረጃ ላይ ከደረሱ ተጠራጣሪዎች እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ እንዳለ አምነው ለመቀበል ይገደዳሉ። ሆኖም ኢየሱስ አብዛኞቹ ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ከመጠመዳቸው የተነሳ እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ የመገኘቱን ምልክት ፈጽሞ ‘እንደማያስተውሉ’ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:37-39ን አንብብ።) ቅዱሳን መጻሕፍት፣ በመጨረሻዎቹ ቀናት በዓለም ላይ የሚኖረው ሁኔታ እጅግ መጥፎ ከመሆኑ የተነሳ ሰዎች መጨረሻው መቅረቡን እንዲያምኑ የሚያደርግ ነገር እንደሚኖር አይገልጹም።—ሉቃስ 17:20፤ 2 ጴጥ. 3:3, 4

8. ኢየሱስ “ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት የሰጠውን ትእዛዝ ለሚከተሉ ሁሉ ምን ነገር ግልጽ ነው?

8 በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ ገጽታዎች ያሉት  የሥርዓቱ መደምደሚያ ምልክት ዓላማውን እንዲመታ፣ ኢየሱስ “ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት የሰጠውን ምክር ለሚታዘዙት ሰዎች የምልክቱ ፍጻሜ ግልጽ መሆን መቻል አለበት። (ማቴ. 24:27, 42) ይህም ከ1914 ጀምሮ እየታየ ያለ ነገር ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የምልክቱ ገጽታዎች ፍጻሜያቸውን እያገኙ ነው። አሁን የምንኖረው “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” በተባለው ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ይህ አጭር ጊዜ ወደዚህ ሥርዓት ፍጻሜ የሚያመራ ሲሆን ያለንበት ክፉ ሥርዓት ሲጠፋ ይደመደማል።

9. የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ በተስፋ እንድንጠባበቅ የሚያነሳሱን የትኞቹ ምክንያቶች ናቸው?

9 ታዲያ ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች በተስፋ መጠባበቅ የሚገባቸው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስን ለመታዘዝ ስንል በተስፋ እንጠባበቃለን። በተጨማሪም የመገኘቱን ምልክት እናስተውላለን። በተስፋ የምንጠባበቀው በየዋህነት ሁሉንም ነገር ስለምናምን አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ንቁ እንድንሆንና እንዳንዘናጋ እንዲሁም የዚህን ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ በተስፋ እንድንጠባበቅ የሚያነሳሱ አሳማኝ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎች ስላሉን ነው።

መጠበቅ ያለብን ለምን ያህል ጊዜ ነው?

10, 11. (ሀ) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለምን ነገር አዘጋጅቷቸዋል? (ለ) ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ መጨረሻው የሚመጣበት ጊዜ ካሰቡት በላይ እንደቆየ ቢሰማቸው ምን እንዲያደርጉ አሳስቧቸዋል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

10 ብዙዎቻችን ለአሥርተ ዓመታት በመንፈሳዊ ነቅተን ስንጠባበቅ ቆይተናል። የሆነ ሆኖ ጊዜ እያለፈ መሄዱ በተስፋ ለመጠባበቅ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ እንዲያላላው ልንፈቅድ አይገባም። ኢየሱስ ይህን ሥርዓት ለማጥፋት ሲመጣ ዝግጁ ሆነን መገኘት ይኖርብናል። ኢየሱስ ተከታዮቹን እንደሚከተለው ብሎ እንዳሳሰባቸው አስተውሉ፦ “የተወሰነው ጊዜ መቼ እንደሆነ ስለማታውቁ ምንጊዜም በንቃት ተከታተሉ፤ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ። ይህም ለባሪያዎቹ ሥልጣን ከሰጠና ለእያንዳንዱ የሥራ ድርሻውን ከመደበ በኋላ በር ጠባቂውን ነቅቶ እንዲጠብቅ በማዘዝ ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደሄደ ሰው ነው። ስለዚህ የቤቱ ጌታ፣ በምሽት ይሁን በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮኽ ይሁን ንጋት ላይ፣ መቼ እንደሚመጣ ስለማታውቁ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ፤ አለዚያ ድንገት ሲመጣ ተኝታችሁ ያገኛችኋል። ይሁንና ለእናንተ የምነግራችሁን ለሁሉም እናገራለሁ፤ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ።”—ማር. 13:33-37

11 የኢየሱስ ተከታዮች፣ ክርስቶስ ከ1914 አንስቶ በሥልጣኑ ላይ መገኘቱን ስለተገነዘቡ በማንኛውም ጊዜ ሊመጣ እንደሚችል በማሰብ ዝግጁ ሆነው እየጠበቁ ነው። ይህን የሚያደርጉት የመንግሥቱን የስብከት ሥራ በማጧጧፍ ነው። ኢየሱስ የሚመጣው በኋላ ላይ ይኸውም “ዶሮ ሲጮኽ” አሊያም “ንጋት ላይ” ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል። ይህ ከሆነ ታዲያ ተከታዮቹ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ኢየሱስ “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ” ብሏል። እንግዲያው ረጅም ጊዜ ስለጠበቁ ብቻ መጨረሻውን አርቀው ቢመለከቱ ወይም በተስፋ መጠባበቃቸውን ቢያቆሙ ተገቢ አይሆንም።

12. ዕንባቆም ይሖዋን ምን ጠየቀ? ምንስ ምላሽ ተሰጠው?

12 ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ ትንቢት እንዲናገር የታዘዘውን የነቢዩ ዕንባቆምን ሁኔታ እንመልከት። ዕንባቆም ትንቢት መናገር ሲጀምር፣ በዚህች ከተማ ላይ ስለሚደርሰው ጥፋት ለዓመታት ሲታወጅ ቆይቶ ነበር። ሁኔታዎቹ በጣም ከመክፋታቸው የተነሳ ‘ክፉው ጻድቁን ከብቦት እንዲሁም ፍትሕ ተጣምሞ’ ነበር። በመሆኑም ዕንባቆም “ይሖዋ ሆይ፣ እርዳታ ለማግኘት ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው?” ብሎ መጠየቁ የሚያስገርም አይደለም። ይሖዋ ለጥያቄው ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አስቀድሞ የተነገረው ጥፋት ‘እንደማይዘገይ’ ለታማኙ ነቢይ ማረጋገጫ ሰጥቶታል። አምላክ ዕንባቆምን “በተስፋ ጠብቀው!” ብሎታል።ዕንባቆም 1:1-4ን እና 2:3ን አንብብ።

13. ዕንባቆም ምን ብሎ ሊያስብ ይችል ነበር? እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ጥበብ የማይሆነውስ ለምንድን ነው?

13 ዕንባቆም ተስፋ ቆርጦ እንደሚከተለው ብሎ ቢያስብ ኖሮስ? ‘ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ ለዓመታት ስሰማ ኖሬአለሁ። ጥፋቱ የሚመጣው ገና ወደፊት ቢሆንስ? ከተማዋ በድንገት የምትጠፋ ይመስል ትንቢት መናገሬን መቀጠል ምክንያታዊ  አይደለም። ይህን ሥራ ለሌሎች ብተወውስ?’ ዕንባቆም በእንደዚህ ዓይነት ሐሳቦች ላይ ቢያውጠነጥን ኖሮ የይሖዋን ሞገስ ያጣ ነበር፤ ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን ስትጠፋ ደግሞ ሕይወቱን ሊያጣ ይችል ነበር!

14. በተስፋ መጠባበቃችን በኋላ ላይ ለሐዘን እንደማይዳርገን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

14 እስቲ በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንዳለን አድርገን እናስብ፤ ከሥርዓቱ መደምደም ጋር የተያያዙ ትንቢቶች በሙሉ ልክ ይሖዋ እንደተናገረው ተፈጽመዋል። በዚያ ወቅት በእነዚህ ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል፤ እንዲሁም ቃል የገባቸውን ሌሎች ነገሮች እንደሚፈጽም ይበልጥ እንተማመናለን። (ኢያሱ 23:14ን አንብብ።) በእርግጥም “ጊዜያትንና ወቅቶችን የመወሰን ሥልጣን ያለው” አምላክ፣ “የሁሉም ነገር መጨረሻ [እንደቀረበ]” እንድንገነዘብና ነቅተን እንድንኖር ለሰጠን ማሳሰቢያ አመስጋኞች እንደምንሆን ጥርጥር የለውም።—ሥራ 1:7፤ 1 ጴጥ. 4:7

በተስፋ እንደምንጠብቅ በድርጊት ማሳየት!

ምሥራቹን በቅንዓት ትሰብካለህ? (አንቀጽ 15ን ተመልከት)

15, 16. ከምንኖርበት ጊዜ አንጻር፣ አገልግሎታችንን ማጧጧፍ ጥበብ የሚሆነው ለምንድን ነው?

15 የይሖዋ ድርጅት አምላክን በጥድፊያ ስሜት ማገልገል እንደሚገባን ማሳሰቡን እንደሚቀጥል መጠበቅ እንችላለን። እነዚህ ማሳሰቢያዎች የሚሰጡን በአምላክ አገልግሎት ሥራ የበዛልን እንድንሆን ለማበረታታት ብቻ ሳይሆን ክርስቶስ በሥልጣኑ መገኘቱን የሚያሳየው ምልክት በመፈጸም ላይ መሆኑን እንድናስተውል ለመርዳትም ጭምር ነው። ከምንኖርበት ጊዜ አንጻር ጥበብ የሚሆነው ምን ዓይነት እርምጃ መውሰዳችን ነው? ምሥራቹን በቅንዓት በመስበክ ከሁሉ አስቀድመን የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ መፈለግ እንደሆነ ጥርጥር የለውም!—ማቴ. 6:33፤ ማር. 13:10

16 አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ስለ አምላክ መንግሥት የምሥራች በመስበክ፣ ሰዎች በዓለም ላይ መምጣቱ ከማይቀረው ጥፋት እንዲድኑ መርዳት እንችላለን።” ይህች እህታችን በሌሎች እርዳታ ከሞት መትረፍ ምን ማለት እንደሆነ ይገባታል፤ ምክንያቱም እሷና ባሏ በታሪክ ውስጥ ከተመዘገቡት የከፉ የባሕር ላይ አደጋዎች ከአንዱ በሕይወት መትረፍ ችለዋል። እነዚህ ባልና ሚስት በ1945 በሰመጠችው ቪልሄም ጉስትሎፍ የተባለች የመንገደኞች የቅንጦት መርከብ ላይ ተሳፍረው ነበር። በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንኳ አንድ ሰው በጣም አስፈላጊ ስለሆነው ነገር የተሳሳተ አመለካከት ሊኖረው ይችላል። እህት በቦታው የነበረችን አንዲት ሴት ታስታውሳለች፤ ሴትየዋ “ወይኔ ሻንጣዎቼ! ወይኔ ጌጣጌጦቼ! ጌጣጌጦቼ ሁሉ ታችኛው ክፍል ውስጥ እኮ ናቸው። ያለኝን በሙሉ አጣሁ!” እያለች ትጮኽ ነበር። ከዚህ በተቃራኒ አንዳንዶቹ ተሳፋሪዎች ሰዎችን ለመርዳት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው፣ በጣም ቀዝቃዛ ወደሆነው ባሕር የወደቁትን ሰዎች ለማዳን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ራስ ወዳድ እንዳልሆኑት እንደነዚህ ተሳፋሪዎች ሁሉ እኛም ሰዎችን ለመርዳት የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። የስብከቱን ሥራ አጣዳፊነት በአእምሯችን በመያዝ ሰዎች መምጣቱ  ከማይቀረው ጥፋት እንዲተርፉ ለመርዳት ጊዜው ከማለቁ በፊት አቅማችን የፈቀደውን ያህል እንጥራለን።

ምንም ነገር ትኩረትህን በመከፋፈል የጥድፊያ ስሜትህን እንዳያጠፋው ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች ታደርጋለህ? (አንቀጽ 17ን ተመልከት)

17. መጨረሻው በማንኛውም ጊዜ ሊመጣ እንደሚችል ለማመን የሚያበቁን የትኞቹ ምክንያቶች ናቸው?

17 በዚህ ምድር ላይ የሚታዩት ክንውኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ እንዳለ እንዲሁም ይህ ክፉ ሥርዓት በቅርቡ መጥፋቱ አይቀሬ እንደሆነ በግልጽ ይጠቁማሉ። በመሆኑም በራእይ 17:16 ላይ የተጠቀሱት “አሥሩ ቀንዶችና አውሬው” በዓለም ላይ ካሉት ሁኔታዎች የተነሳ በታላቂቱ ባቢሎን (የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ ታመለክታለች) ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንዲነሳሱ ረጅም ጊዜ ያስፈልጋል ብለን ማሰብ አይኖርብንም። መንግሥታት ይህን እርምጃ እንዲወስዱ ሐሳቡን ‘በልባቸው የሚያኖረው’ አምላክ እንደሆነና ይህም በቅጽበት እንዲሁም በማንኛውም ሰዓት ሊከሰት እንደሚችል ምንጊዜም እናስታውስ! (ራእይ 17:17) ይህ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ የሚጠፋበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። በመሆኑም ለሚከተለው የኢየሱስ ማስጠንቀቂያ ትኩረት መስጠታችን የተገባ ነው፦ “ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት እንዲሁም ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ ያ ቀን ድንገት ሳታስቡት እንደ ወጥመድ ይመጣባችኋል።” (ሉቃስ 21:34, 35፤ ራእይ 16:15) እንግዲያው ይሖዋ “እሱን በተስፋ ለሚጠባበቁት ሲል እርምጃ” እንደሚወስድ በመተማመን በጥድፊያ ስሜት ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ኢሳ. 64:4

18. በቀጣዩ ርዕስ ላይ የትኛው ጥያቄ ይብራራል?

18 የዚህን ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ ስንጠባበቅ ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ በመንፈስ ተመርቶ ለጻፈው ለሚከተለው ሐሳብ ትኩረት እንስጥ፦ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ . . . እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ላይ ራሳችሁን ገንቡ፤ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ጸልዩ፤ ይህን የምታደርጉት የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝላችሁን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት እየተጠባበቃችሁ ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ እንድትኖሩ ነው።” (ይሁዳ 20, 21) ሆኖም አምላክ ቃል የገባውን አዲስ ዓለም በተስፋ እንደምንጠባበቅና ይህን ጊዜ ለማየት በጣም እንደምንጓጓ እንዴት ማሳየት እንችላለን? ይህ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።

^ አን.1 ስለ መሲሑ የተነገሩ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችንና ፍጻሜያቸውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ገጽ 200 ላይ ማግኘት ይቻላል።