በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ሐምሌ 2015

‘መዳናችሁ እየቀረበ ነው’!

‘መዳናችሁ እየቀረበ ነው’!

“መዳናችሁ እየቀረበ ስለሆነ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ቀና አድርጉ።”—ሉቃስ 21:28

መዝሙሮች፦ 133, 43

1. በ66 ዓ.ም. ምን ነገሮች ተከናወኑ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

ኢየሩሳሌም ውስጥ በ66 ዓ.ም. የምትኖር ክርስቲያን እንደሆንክ አድርገህ አስብ። በከተማዋ ውስጥ ብዙ ነገር እየተከናወነ ነው። በመጀመሪያ ፍሎረስ የተባለው የሮም አገረ ገዢ፣ ቅዱስ ከሆነው የቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት 17 ታላንት ወሰደ። አይሁዳውያኑም ወዲያውኑ ዓመፅ በማስነሳት በኢየሩሳሌም ያሉትን የሮም ወታደሮች ከፈጁ በኋላ ከሮም አገዛዝ ነፃ መውጣታቸውን አወጁ። ሆኖም የሮም መንግሥት በአፋጣኝ እርምጃ ወሰደ። በሦስት ወር ውስጥ ሮማዊው የሶርያ አገረ ገዢ ሴስቲየስ ጋለስ፣ 30,000 ወታደሮችን አስከትሎ መጣ። ወታደሮቹ በኢየሩሳሌም ዳርቻ ላይ ያሉትን አካባቢዎች ወዲያውኑ ስለያዙ ዓማፂያኑ ሸሽተው በቤተ መቅደሱ ውስጥ ተሸሸጉ። ከዚያም የሮም ወታደሮች በቤተ መቅደሱ ዙሪያ የሚገኘውን ግንብ ማፍረስ ጀመሩ! ከተማዋ በሽብር ተውጣለች። ታዲያ ይህን ሁሉ ስትመለከት ምን ይሰማሃል?

2. ክርስቲያኖች በ66 ዓ.ም. ምን እርምጃ መውሰድ ነበረባቸው? ይህን ማድረግ የቻሉትስ እንዴት ነው?

2 ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ ታስታውስ ይሆናል፤ የወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ እንደዘገበው ኢየሱስ “ኢየሩሳሌም በጦር ሠራዊት ተከባ ስታዩ መጥፊያዋ እንደቀረበ እወቁ” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 21:20) ይሁንና ‘ኢየሱስ ከዚህ ማስጠንቀቂያ ጋር አያይዞ የሰጠውን መመሪያ መታዘዝ የምችለው  እንዴት ነው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በከተማዋ ውስጥ ያሉም ከዚያ ይውጡ፤ በገጠር ያሉም ወደ እሷ አይግቡ።” (ሉቃስ 21:21) ታዲያ በርካታ ወታደሮች ኢየሩሳሌምን ከበው እያለ ከተማዋን ለቀህ መውጣት የምትችለው እንዴት ነው? አንድ አስገራሚ ነገር ተከናወነ። ዓይንህ እያየ የሮም ወታደሮች ማፈግፈግ ጀመሩ! አስቀድሞ እንደተነገረው ጥቃቱ ‘እንዲያጥር’ ተደረገ። (ማቴ. 24:22) አሁን የኢየሱስን መመሪያዎች ለመታዘዝ የሚያስችል አጋጣሚ ተከፍቶልሃል። በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ካሉ ሌሎች ታማኝ ክርስቲያኖች ጋር በመሆን በዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ ወዳሉት ተራሮች ወዲያውኑ ሸሸህ። * ከዚያም በ70 ዓ.ም. ሌላ የሮም ሠራዊት ወደ ኢየሩሳሌም በማምራት ከተማዋን አወደማት። አንተ ግን የኢየሱስን መመሪያዎች በመታዘዝህ ሕይወትህ ሊተርፍ ችሏል።

3. ከጥንቶቹ ክርስቲያኖች ጋር የሚመሳሰል ምን ነገር በቅርቡ ያጋጥመናል? በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 በጣም በቅርቡ እያንዳንዳችን እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጥመናል። ኢየሱስ፣ ክርስቲያኖችን ያስጠነቀቀው ስለ ኢየሩሳሌም ጥፋት ብቻ አይደለም፤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተከናወኑትን እነዚያን ነገሮች፣ ‘ታላቁ መከራ’ በድንገት ሲጀምር የሚፈጸሙትን ክንውኖች ለማመልከትም ተጠቅሞባቸዋል። (ማቴ. 24:3, 21, 29) ደስ የሚለው ግን ከዚህ ዓለም አቀፋዊ ጥፋት የሚተርፍ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” አለ። (ራእይ 7:9, 13, 14ን አንብብ።) መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ ስለሚፈጸሙት ስለ እነዚህ ነገሮች ምን ይነግረናል? መዳናችን ከዚህ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ለዚህ ጥያቄ መልስ ትኩረት ልንሰጥ ይገባል። ወደፊት የሚፈጸሙት እነዚህ ክንውኖች እኛን በግለሰብ ደረጃ እንዴት እንደሚነኩን በዝርዝር እንመልከት።

የታላቁ መከራ መጀመሪያ

4. ታላቁ መከራ መጀመሩን የሚጠቁመው ምንድን ነው? ይህስ የሚከናወነው እንዴት ነው?

4 ታላቁ መከራ የሚጀምረው እንዴት ነው? በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ስለ “ታላቂቱ ባቢሎን” ጥፋት የሚገልጸው ዘገባ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። (ራእይ 17:5-7) የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ ከአመንዝራ ጋር መመሳሰላቸው ምንኛ ተገቢ ነው! ቀሳውስት ከዚህ ክፉ ዓለም መሪዎች ጋር አመንዝረዋል። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስንና መንግሥቱን በታማኝነት ከመደገፍ ይልቅ በፖለቲካው ዓለም ተደማጭነት ለማግኘት ሲሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ችላ ብለዋል። የተከተሉት ጎዳና፣ ንጹሕ ከሆኑትና በደናግል ከተመሰሉት የአምላክ ቅቡዓን በእጅጉ የተለየ ነው። (2 ቆሮ. 11:2፤ ያዕ. 1:27፤ ራእይ 14:4) ሆኖም በዝሙት አዳሪ የተመሰለችውን ድርጅት የሚያጠፋት ማን ነው? ይሖዋ “ደማቅ ቀይ” በሆነው አውሬ “አሥር ቀንዶች” ልብ ውስጥ “ሐሳቡን” ያኖራል። እነዚህ ቀንዶች፣ ‘በደማቅ ቀይ አውሬ’ ለተመሰለው ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ የሚሰጡትን በአሁኑ ጊዜ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ይወክላሉ።ራእይ 17:3, 16-18ን አንብብ።

5, 6. ታላቂቱ ባቢሎን ስትጠፋ ሃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎች በሙሉ አብረው አይጠፉም ብለን የምንደመድመው ለምንድን ነው?

5 በታላቂቱ ባቢሎን ውስጥ የተካተቱት ሃይማኖቶች ይጠፋሉ ሲባል የእነዚህ ሃይማኖቶች አባላት የነበሩ ሁሉ አብረው ይጠፋሉ ማለት ነው? ላይሆን ይችላል። ነቢዩ ዘካርያስ ያን ጊዜ አስመልክቶ በመንፈስ መሪነት ጽፏል። ዘገባው ቀደም ሲል የሐሰት ሃይማኖት አባል የነበረ አንድ ሰው እንደሚከተለው ብሎ እንደሚናገር ይገልጻል፦ “‘እኔ ነቢይ አይደለሁም። ይልቁንም አራሽ ነኝ፤ ምክንያቱም አንድ ሰው ልጅ ሳለሁ ባሪያ አድርጎ ገዝቶኛል።’ አንድ ሰውም ‘በትከሻዎችህ መካከል ያሉት ቁስሎች ምንድን ናቸው?’ ብሎ ቢጠይቀው ‘በወዳጆቼ ቤት ሳለሁ የቆሰልኩት  ነው’ ይላል።” (ዘካ. 13:4-6) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች እንኳ ሃይማኖታቸውን የሚተዉ ከመሆኑም ሌላ የሐሰት ሃይማኖት አባል የነበሩ መሆናቸውን ይክዳሉ።

6 ታዲያ የአምላክ ሕዝቦች በዚህ ጊዜ ምን ይሆናሉ? ኢየሱስ “ቀኖቹ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ባልዳነ ነበር፤ ሆኖም ለተመረጡት ሲባል ቀኖቹ ያጥራሉ” ብሏል። (ማቴ. 24:22) ቀደም ሲል እንደተመለከትነው በ66 ዓ.ም. መከራው ‘አጥሯል።’ ይህም ‘የተመረጡት’ ማለትም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ኢየሩሳሌምንና አካባቢዋን ለቀው ለመሸሽ አጋጣሚ እንዲያገኙ አድርጓል። በተመሳሳይም ወደፊት የሚመጣው ታላቅ መከራ የመጀመሪያ ምዕራፍ “ለተመረጡት” ሲባል ‘ያጥራል።’ ፖለቲካዊ ኃይሎችን የሚያመለክቱት “አሥር ቀንዶች” የአምላክን ሕዝቦች እንዲያጠፉ አይፈቀድላቸውም። ከዚህ ይልቅ መከራው ለአጭር ጊዜ ጋብ ይላል።

የፈተና እና የፍርድ ጊዜ

7, 8. የሐሰት ሃይማኖቶች ከጠፉ በኋላ ምን አጋጣሚ ይከፈታል? የአምላክ ታማኝ ሕዝቦች በዚያን ጊዜ ከሌሎች የተለዩ የሚሆኑት እንዴት ነው?

7 የሐሰት ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ከጠፉ በኋላ ምን ይሆናል? በዚያን ጊዜ የልባችን እውነተኛ ዝንባሌ ይገለጣል። አብዛኛው የሰው ዘር “ተራራ ላይ ባሉ ዓለቶች” የተመሰሉትን ሰብዓዊ ድርጅቶች መሸሸጊያ ለማድረግ ይሞክራል። (ራእይ 6:15-17) የአምላክ ሕዝቦች ግን ይሖዋ ወዳዘጋጀው መጠለያ በምሳሌያዊ ሁኔታ ይሸሻሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለተወሰነ ጊዜ ያህል ክፍተት የተገኘው ብዙ አይሁዳውያን ወደ ክርስትና እንዲለወጡ አልነበረም። ከዚህ በተለየ፣ ቀድሞውንም ክርስቲያን የነበሩት ሰዎች በታዛዥነት እርምጃ የሚወስዱበት ጊዜ ነበር። በተመሳሳይም ወደፊት ታላቁ መከራ ለተወሰነ ጊዜ ሲቋረጥ አዳዲስ አማኞች ወደ ክርስትና እንደሚጎርፉ አንጠብቅም። ከዚህ ይልቅ በዚህ ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ ይሖዋን እንደሚወዱና የክርስቶስን ወንድሞች እንደሚደግፉ ለማሳየት አጋጣሚ ያገኛሉ።—ማቴ. 25:34-40

8 በዚያ የፈተና ወቅት የሚፈጸሙትን ሁሉንም ነገሮች ሙሉ በሙሉ ባንረዳም እንኳ በተወሰነ መጠን መሥዋዕት የሚያስከፍለን ነገር እንደሚኖር እንጠብቃለን። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ ንብረታቸውን ትተው መሄድ እንዲሁም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ መኖር አስፈልጓቸው ነበር። (ማር. 13:15-18) እኛስ ታማኝነታችንን ለመጠበቅ ስንል ቁሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች እንሆናለን? ለይሖዋ ታማኝ መሆናችንን ለማሳየት ስንል የሚጠበቅብንን ነገር ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ እንሆናለን? እስቲ አስበው! በጥንት ጊዜ የነበረውን የዳንኤልን ምሳሌ በመከተል፣ ምንም መጣ ምን በዚያ ጊዜ አምላካችንን ማገልገላችንን የምንቀጥለው እኛ ብቻ እንሆናለን።—ዳን. 6:10, 11

9, 10. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች በዚያን ጊዜ ምን ዓይነት መልእክት ያውጃሉ? (ለ) የአምላክ ሕዝቦች ጠላቶች ምን እርምጃ ይወስዳሉ?

9 ይህ ጊዜ “የመንግሥቱ ምሥራች” የሚሰበክበት አይደለም። በዚህ ወቅት ምሥራቹን የምንሰብክበት ጊዜ አልፏል። “መጨረሻው” በቅርቡ ይመጣል! (ማቴ. 24:14) የአምላክ ሕዝቦች ኃይለኛ የሆነ የፍርድ መልእክት እንደሚያውጁ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ መልእክት የሰይጣን ክፉ ዓለም ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ እንደሆነ ማወጅን ይጨምር ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን መልእክት ከበረዶ ድንጋይ ጋር በማመሳሰል እንዲህ ብሏል፦ “ከዚያም ታላቅ የበረዶ ድንጋይ ከሰማይ በሰዎች ላይ ወረደ፤ እያንዳንዱ የበረዶ ድንጋይ አንድ ታላንት ይመዝን ነበር፤ መቅሰፍቱ እጅግ ታላቅ ስለነበር ሰዎቹ ከበረዶው መቅሰፍት የተነሳ አምላክን ተሳደቡ።”—ራእይ 16:21

10 ጠላቶቻችን ይህን ማስተዋላቸው አይቀርም። ነቢዩ ሕዝቅኤል የማጎጉ ጎግ ይኸውም ግንባር  የፈጠሩ ብሔራት ምን እንደሚያደርጉ በመንፈስ መሪነት ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በዚያ ቀን ሐሳብ ወደ ልብህ ይገባል፤ ክፉ ዕቅድም ታወጣለህ፤ እንዲህ ትላለህ፦ “ከለላ የሌላቸው ሰፈሮች የሚገኙበትን ምድር እወራለሁ። ያለ ስጋት ተረጋግተው በሚኖሩት ላይ እመጣለሁ፤ ሁሉም የሚኖሩት ቅጥር፣ መቀርቀሪያና በር በሌላቸው ሰፈሮች ነው።” ዓላማህ ብዙ ሀብት መበዝበዝና መዝረፍ፣ ደግሞም አሁን የሰው መኖሪያ የሆኑትን ባድማ የነበሩ ስፍራዎችና ከብሔራት ሁሉ መካከል ዳግመኛ የተሰበሰበውን ሕዝብ ማጥቃት ነው፤ ይህ ሕዝብ ሀብትና ንብረት አከማችቷል፤ በምድርም እምብርት ላይ ይኖራል።’” (ሕዝ. 38:10-12) የአምላክ ሕዝቦች ‘በምድር እምብርት ላይ’ ያሉ ያህል ለየት ብለው ይታያሉ። ብሔራቱ ይህን አይተው ማለፍ አይችሉም። አዎ፣ የይሖዋን ቅቡዓንና አጋሮቻቸውን ለማጥቃት ይጓጓሉ።

11. (ሀ) በታላቁ መከራ ወቅት የሚከናወኑትን ነገሮች ቅደም ተከተል በተመለከተ ምን ማስታወስ ይኖርብናል? (ለ) ሰዎች በሰማይ የሚኖረውን ምልክት ሲያዩ ምን ይሰማቸዋል?

11 ቀጥሎ የሚከናወኑትን ነገሮች ስንመረምር የአምላክ ቃል እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙበትን ትክክለኛ ቅደም ተከተል እንደማይገልጽ ማስታወስ ይኖርብናል። አንዳንድ ክንውኖች በተመሳሳይ ጊዜ ላይ የሚፈጸሙ ይመስላል። ኢየሱስ የዚህን ሥርዓት መደምደሚያ አስመልክቶ በተናገረው ትንቢት ላይ እንዲህ ብሏል፦ “በፀሐይ፣ በጨረቃና በከዋክብት ላይ ምልክቶች ይታያሉ፤ በምድርም ላይ ሕዝቦች ከባሕሩ ድምፅና ነውጥ የተነሳ የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ይጨነቃሉ። የሰማያት ኃይላት ስለሚናወጡ ሰዎች ከፍርሃትና በዓለም ላይ የሚመጡትን ነገሮች ከመጠበቅ የተነሳ ይዝለፈለፋሉ። ከዚያም የሰው ልጅ በኃይልና በታላቅ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።” (ሉቃስ 21:25-27፤ ማርቆስ 13:24-26ን አንብብ።) ይህ ትንቢት ሲፈጽም ቃል በቃል በሰማይ ላይ የሚታይ አስፈሪ ምልክትና ክንውን ይኖር ይሆን? ይህ ወደፊት የምናየው ነገር ነው። የሚኖረው ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ምልክቶቹ የአምላክን ጠላቶች ያስደነግጧቸዋል፤ እንዲሁም ልባቸውን ያሸብሩታል።

መዳን እንደምናገኝ ስለምንተማመን ብሩህ አመለካከት ይኖረናል (አንቀጽ 12, 13ን ተመልከት)

12, 13. (ሀ) ኢየሱስ “በኃይልና በታላቅ ክብር” ሲመጣ ምን ይከናወናል? (ለ) የአምላክ አገልጋዮች በዚያ ጊዜ ምን ይሰማቸዋል?

12 ኢየሱስ “በኃይልና በታላቅ ክብር” ሲመጣ ምን ይከናወናል? ታማኝ የሆኑ ሰዎች በዚያ ወቅት ይሸለማሉ፤ ታማኝ ያልሆኑት ደግሞ ይቀጣሉ። (ማቴ. 24:46, 47, 50, 51፤ 25:19, 28-30) በማቴዎስ ዘገባ ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ የተለያዩ ገጽታዎች ስላሉት ምልክት በተናገረው ሐሳብ መደምደሚያ ላይ የበጎቹንና የፍየሎቹን ምሳሌ ተናግሯል፤ እንዲህ ብሏል፦ “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ በክብራማ ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል። ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ሁሉ እሱም ሰዎችን አንዱን ከሌላው ይለያል። በጎቹን በቀኙ፣ ፍየሎቹን ግን በግራው ያደርጋቸዋል።” (ማቴ. 25:31-33) በጎቹና ፍየሎቹ ምን ዓይነት ፍርድ ይሰጣቸዋል? ኢየሱስ ምሳሌውን የደመደመው “[ፍየሎቹ] ወደ ዘላለም ጥፋት ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ” በማለት ነው።—ማቴ. 25:46

13 ፍየሎቹ “ወደ ዘላለም ጥፋት” እንደሚሄዱ ሲገነዘቡ ምን ያደርጋሉ? “በሐዘን ደረታቸውን ይደቃሉ።” (ማቴ. 24:30) ይሁንና የክርስቶስ ወንድሞችና ታማኝ አጋሮቻቸው በዚያ ወቅት ምን ይሰማቸዋል? በይሖዋ አምላክና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ ስለሚተማመኑ ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት የሰጠውን ትእዛዝ ተግባራዊ ያደርጋሉ፦ “እነዚህ ነገሮች መከሰት ሲጀምሩ መዳናችሁ እየቀረበ ስለሆነ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ቀና አድርጉ።” (ሉቃስ 21:28) በእርግጥም መዳን እንደምናገኝ ስለምንተማመን ብሩህ አመለካከት ይኖረናል።

 በመንግሥቱ ደምቆ ማብራት

14, 15. የማጎጉ ጎግ ጥቃት መሰንዘር ከጀመረ በኋላ የትኛው የመሰብሰብ ሥራ ይከናወናል? ይህ የመሰብሰብ ሥራስ ምን ያካትታል?

14 የማጎጉ ጎግ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር ከጀመረ በኋላ ምን ይከናወናል? የማቴዎስና የማርቆስ ዘገባዎች ተመሳሳይ ሐሳብ ይዘዋል፦ “[የሰው ልጅ] መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፣ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ ለእሱ የተመረጡትን ይሰበስባል።” (ማር. 13:27፤ ማቴ. 24:31) እዚህ ላይ የተገለጸው መሰብሰብ፣ ቅቡዓኑ መቀባት የጀመሩበትን ጊዜም ሆነ በምድር የቀሩት ታማኝ ቅቡዓን የመጨረሻው ማኅተም የሚደረግባቸውን ጊዜ አያመለክትም። (ማቴ. 13:37, 38) ይህ ማኅተም የሚደረግባቸው ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ነው። (ራእይ 7:1-4) ታዲያ ኢየሱስ የጠቀሰው የመሰብሰብ ሥራ ምንድን ነው? ከ144,000ዎቹ መካከል የቀሩት በሰማይ ሽልማታቸውን ስለሚያገኙበት ጊዜ መናገሩ ነበር። (1 ተሰ. 4:15-17፤ ራእይ 14:1) ይህ ክንውን የሚፈጸመው የማጎጉ ጎግ ጥቃት መሰንዘር ከጀመረ በኋላ ነው። (ሕዝ. 38:11) ከዚያም ኢየሱስ “በዚያ ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ደምቀው ያበራሉ” በማለት የተናገረው ሐሳብ ይፈጸማል።—ማቴ. 13:43 *

15 ይህ ሲባል ታዲያ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ይነጠቃሉ” ማለት ነው? ብዙ የሕዝበ ክርስትና አባላት “መነጠቅ” የሚለው ትምህርት ክርስቲያኖች ሥጋዊ አካላቸውን እንደለበሱ ከምድር መወሰዳቸውን እንደሚያመለክት ያምናሉ። ከዚያም ኢየሱስ በሚታይ መንገድ በመመለስ ምድርን እንደሚገዛ ይጠብቃሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ” እንደሚታይ እንዲሁም ኢየሱስ “በሰማይ ደመና” እንደሚመጣ በግልጽ ይናገራል። (ማቴ. 24:30) ሁለቱም  አገላለጾች የሚያመለክቱት በዓይን የማይታይ ሁኔታን ነው። በተጨማሪም “ሥጋና ደም የአምላክን መንግሥት አይወርስም።” በመሆኑም ወደ ሰማይ የሚወሰዱ ሰዎች “የመጨረሻው መለከት በሚነፋበት ወቅት ድንገት፣ በቅጽበተ ዓይን [መለወጥ]” ይኖርባቸዋል። * (1 ቆሮንቶስ 15:50-53ን አንብብ።) በምድር የቀሩት ታማኝ ቅቡዓን በቅጽበት ወደ ሰማይ ይሰበሰባሉ።

16, 17. የበጉ ሠርግ በሰማይ ከመከናወኑ በፊት ምን መፈጸም አለበት?

16 ሁሉም የ144,000 አባላት በሰማይ ከተሰበሰቡ በኋላ ለበጉ ሠርግ የመጨረሻው ዝግጅት መጀመር ይችላል። (ራእይ 19:9) ይህ አስደሳች ሥነ ሥርዓት ከመካሄዱ በፊት ግን አንድ ሌላ ነገር ይፈጸማል። ቀሪዎቹ የ144,000 አባላት ወደ ሰማይ ከመወሰዳቸው ትንሽ ቀደም ብሎ ጎግ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝር አስታውስ። (ሕዝ. 38:16) ታዲያ ይህ ጥቃት ምን ያስከትላል? በምድር ላይ ያሉት የአምላክ ሕዝቦች ለጥቃት የተጋለጡ ይመስላሉ። እነዚህ የአምላክ ሕዝቦች በንጉሥ ኢዮሳፍጥ ዘመን የተሰጠውን መመሪያ ይታዘዛሉ፦ “እናንተ ይህን ጦርነት መዋጋት አያስፈልጋችሁም። ቦታ ቦታችሁን ይዛችሁ ዝም ብላችሁ ቁሙ፤ ይሖዋ ለእናንተ ሲል የሚወስደውን የማዳን እርምጃ ተመልከቱ። ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፣ አትፍሩ ወይም አትሸበሩ።” (2 ዜና 20:17) በሰማይ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። ራእይ 17:14 ቅቡዓን በሙሉ ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ የአምላክ ሕዝቦች ጠላቶች ስለሚያደርጉት ነገር ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “እነዚህ ከበጉ ጋር ይዋጋሉ፤ ሆኖም በጉ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለሆነ ድል ይነሳቸዋል። ከእሱ ጋር ያሉት የተጠሩት፣ የተመረጡትና የታመኑትም ድል ያደርጋሉ።” ኢየሱስ በሰማይ ካሉት 144,000 ተባባሪ ገዢዎቹ ጋር በመሆን በምድር ላይ ያሉትን የአምላክ ሕዝቦች ይታደጋል።

17 ይህን ተከትሎ የሚነሳው የአርማጌዶን ጦርነት የይሖዋ ቅዱስ ስም እንዲከበር ያደርጋል። (ራእይ 16:16) በፍየል የተመሰሉት ሰዎች በሙሉ በዚያ ወቅት “ወደ ዘላለም ጥፋት” ይሄዳሉ። በመጨረሻም ማንኛውም ዓይነት ክፋት ከምድር ላይ ይወገዳል፤ እጅግ ብዙ ሕዝብም የታላቁን መከራ የመጨረሻ ምዕራፍ በሕይወት ያልፋሉ። ዝግጅቱ ሁሉ ከተጠናቀቀ በኋላ በራእይ መጽሐፍ መደምደሚያ ላይ እንደተገለጸው የበጉ ሠርግ ይከናወናል። (ራእይ 21:1-4) * ከጥፋቱ ተርፈው በምድር ላይ የሚኖሩ ሁሉ የአምላክን ሞገስ የሚያገኙ ከመሆኑም ሌላ የእሱን ፍቅር የሚያሳዩ የተትረፈረፉ በረከቶችን ያጣጥማሉ። ይህ እንዴት ያለ አስደሳች ሠርግ ይሆናል! በእርግጥም በታላቅ ጉጉት የምንጠባበቀው ቀን አይደለም?2 ጴጥሮስ 3:13ን አንብብ።

18. ከፊታችን አስደናቂ ነገሮች የሚጠብቁን ከመሆኑ አንጻር ቁርጥ አቋማችን ምን ሊሆን ይገባል?

18 ከፊታችን እንዲህ ያሉ አስደናቂ ነገሮች የሚጠብቁን ከመሆኑ አንጻር በአሁኑ ጊዜ እያንዳንዳችን ምን ልናደርግ ይገባል? ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እነዚህ ሁሉ ነገሮች በዚህ ሁኔታ የሚቀልጡ ከሆነ ቅዱስ ሥነ ምግባር በመከተልና ለአምላክ ያደራችሁ መሆናችሁን የሚያሳዩ ተግባሮች በመፈጸም ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ ልታስቡበት ይገባል! . . . የይሖዋን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና በአእምሯችሁ አቅርባችሁ እየተመለከታችሁ ልትኖሩ ይገባል! ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እነዚህን ነገሮች እየተጠባበቃችሁ ስለሆነ በመጨረሻ በእሱ ፊት ቆሻሻና እድፍ ሳይኖርባችሁ በሰላም እንድትገኙ የተቻላችሁን ጥረት አድርጉ።” (2 ጴጥ. 3:11, 12, 14) እንግዲያው ቁርጥ አቋማችን የሰላሙን ንጉሥ መደገፍና ምንጊዜም በመንፈሳዊ ንጹሕ ሆኖ መኖር ይሁን።

^ አን.2 የሚያዝያ 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 25-26 ተመልከት።

^ አን.15 በዚያ ጊዜ በሕይወት ያሉት ቅቡዓን ሥጋዊ አካላቸውን ይዘው ወደ ሰማይ አይሄዱም። (1 ቆሮ. 15:48, 49) የኢየሱስ አካል እንደተወገደ ሁሉ የእነሱም አካል ሳይወገድ አይቀርም።

^ አን.17 የሚከናወኑት ነገሮች ቅደም ተከተል በመዝሙር 45 ላይም ተገልጿል። ንጉሡ በመጀመሪያ ጦርነት ያካሂዳል፤ ከዚያ በኋላ ሠርጉ ይከናወናል።