በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው የማጎጉ ጎግ ማን ነው?

የማጎጉ ጎግ የሚለው ስያሜ፣ ሰይጣን ዲያብሎስ ከሰማይ ከተባረረ በኋላ የተሰጠው ስም እንደሆነ የሚገልጽ ማብራሪያ ለበርካታ ዓመታት በጽሑፎቻችን ላይ ይወጣ ነበር። ይህ ማብራሪያ የተመሠረተው በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዘረውን ዓለም አቀፋዊ ጥቃት የሚመራው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ በሚገልጸው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በሚገኘው ሐሳብ ላይ ነበር። (ራእይ 12:1-17) በመሆኑም ጎግ የሰይጣን ሌላ ትንቢታዊ ስም መሆን እንዳለበት እናስብ ነበር።

ይሁን እንጂ ይህ ማብራሪያ መልስ የሚያሻቸው አንዳንድ ጥያቄዎችን አስነስቷል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ይሖዋ፣ ጎግ ድል ስለሚነሳበት ጊዜ ሲናገር ጎግን “ለተለያዩ አዳኝ አሞሮች ሁሉና ለዱር አራዊት መብል አድርጌ እሰጥሃለሁ” ብሎታል። (ሕዝ. 39:4) አክሎም “በዚያ ቀን በእስራኤል ምድር፣ . . . ለጎግ የመቃብር ቦታ እሰጠዋለሁ፤ . . . ጎግንና ስፍር ቁጥር የሌለውን ሠራዊቱን ሁሉ በዚያ ይቀብራሉ” ብሏል። (ሕዝ. 39:11) ይሁንና አንድ መንፈሳዊ ፍጡር “ለተለያዩ አዳኝ አሞሮች ሁሉና ለዱር አራዊት መብል” ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ደግሞስ ሰይጣን በምድር ላይ “የመቃብር ቦታ” ሊሰጠው የሚችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የሚያሳየው ሰይጣን ለ1,000 ዓመታት በጥልቁ ውስጥ እንደሚታሰር እንጂ በአራዊት እንደሚበላ ወይም እንደሚቀበር አይደለም።—ራእይ 20:1, 2

በ1,000 ዓመቱ መጨረሻ ላይ ሰይጣን ከጥልቁ ሲፈታ “በአራቱም የምድር ማዕዘናት ያሉትን ብሔራት፣ ጎግንና ማጎግን ለማሳሳትና ለጦርነቱ አንድ ላይ ለመሰብሰብ [እንደሚወጣ]” መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ራእይ 20:8) ይሁን እንጂ ሰይጣን ራሱ ጎግ ከሆነ፣ ጎግን ሊያሳስተው የሚችለው እንዴት ነው? እንግዲያው በሕዝቅኤልም ሆነ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው “ጎግ” ሰይጣንን አያመለክትም።

ታዲያ የማጎጉ ጎግ ማን ነው? ይህን ጥያቄ ለመመለስ፣ ቅዱሳን መጻሕፍትን መመርመርና በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት የሚሰነዝረው ማን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የማጎጉ ጎግ’ ስለሚሰነዝረው ጥቃት ብቻ ሳይሆን ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ እና “የምድር ነገሥታት” ስለሚሰነዝሯቸው ጥቃቶች ጭምር ይናገራል። (ሕዝ. 38:2, 10-13፤ ዳን. 11:40, 44, 45፤ ራእይ 17:14፤ 19:19) ታዲያ እነዚህ የተለያዩ ጥቃቶች ናቸው? ሁኔታው እንደዚያ አይመስልም። መጽሐፍ ቅዱስ እየተናገረ ያለው የተለያዩ ስሞች ስለተሰጡት አንድ ጥቃት እንደሆነ ግልጽ ነው። እንዲህ ብለን መደምደም የምንችለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የአርማጌዶን ጦርነት  እንዲነሳ በሚያደርገው በዚህ የመጨረሻ ጥቃት ላይ የምድር ብሔራት በሙሉ እንደሚካፈሉ ቅዱሳን መጻሕፍት ይናገራሉ።—ራእይ 16:14, 16

በአምላክ ሕዝቦች ላይ ስለሚሰነዘረው የመጨረሻ ጥቃት የሚገልጹትን እነዚህን ጥቅሶች በሙሉ ስናነጻጽር፣ የማጎጉ ጎግ የሚለው መጠሪያ የሚያመለክተው ሰይጣንን ሳይሆን ግንባር የፈጠሩ ብሔራትን እንደሆነ ግልጽ ይሆንልናል። ታዲያ ግንባር የፈጠሩትን እነዚህን ብሔራት የሚመራው ምሳሌያዊው ‘የሰሜን ንጉሥ’ ይሆን? ይህን በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ይሁን እንጂ ይህ መደምደሚያ፣ ይሖዋ ስለ ጎግ ከተናገረው ከሚከተለው ሐሳብ ጋር የሚስማማ ይመስላል፦ “አንተ ከስፍራህ ይኸውም ርቆ ከሚገኘው የሰሜን ምድር ትመጣለህ፤ አንተና ከአንተ ጋር ያሉ ብዙ ሕዝቦች ትመጣላችሁ፤ ሁሉም በፈረሶች ላይ የተቀመጡ፣ ታላቅ ጉባኤና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራዊት ናቸው።”—ሕዝ. 38:6, 15

በተመሳሳይም ከሕዝቅኤል ጋር በአንድ ዘመን የኖረው ነቢዩ ዳንኤል ስለ ሰሜኑ ንጉሥ የሚከተለውን ተናግሯል፦ “ከምሥራቅና ከሰሜን የሚመጣ ወሬ ይረብሸዋል፤ እሱም ለማጥፋትና ብዙዎችን ለመደምሰስ በታላቅ ቁጣ ይወጣል። ንጉሣዊ ድንኳኖቹንም በታላቁ ባሕርና ቅዱስ በሆነው ውብ ተራራ መካከል ይተክላል፤ እሱም ወደ ፍጻሜው ይመጣል፤ የሚረዳውም አይኖርም።” (ዳን. 11:44, 45) ይህ ሐሳብ የሕዝቅኤል መጽሐፍ ጎግ ስለሚፈጽመው ነገር ከሚናገረው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ግልጽ ነው።—ሕዝ. 38:8-12, 16

ለመሆኑ ይህ የመጨረሻ ጥቃት ምን ያስከትላል? ዳንኤል እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “በዚያ ዘመን ለሕዝብህ [ከ1914 አንስቶ] የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል [ኢየሱስ ክርስቶስ በአርማጌዶን] ይነሳል። ብሔራት ከተቋቋሙበት ጊዜ አንስቶ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሆኖ የማያውቅ የጭንቀት ጊዜ [ታላቁ መከራ] ይመጣል። በዚያን ወቅት ሕዝብህ ይኸውም በመጽሐፍ ላይ ተጽፎ የተገኘ እያንዳንዱ ሰው ይተርፋል።” (ዳን. 12:1) የአምላክ ወኪል የሆነው ኢየሱስ የሚወስደው ይህ እርምጃ በራእይ 19:11-21 ላይም ተገልጿል።

ይሁን እንጂ በራእይ 20:8 ላይ የተጠቀሰው ‘ጎግና ማጎግ’ ማንን ያመለክታል? በ1,000 ዓመቱ ፍጻሜ ላይ በሚኖረው የመጨረሻ ፈተና ወቅት በይሖዋ ላይ የሚያምፁት ሰዎች፣ በታላቁ መከራ መጨረሻ ላይ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩትና ‘የማጎጉ ጎግ’ የተባሉት ብሔራት የሚያሳዩት ዓይነት የነፍሰ ገዳይነት መንፈስ ያንጸባርቃሉ። የሁለቱም ቡድኖች የመጨረሻ ዕጣ ተመሳሳይ ይኸውም ዘላለማዊ ጥፋት ነው! (ራእይ 19:20, 21፤ 20:9) እንግዲያው በሺህ ዓመቱ ፍጻሜ ላይ የሚያምፁ ሁሉ ‘ጎግና ማጎግ’ ተብለው መጠራታቸው ተገቢ ይመስላል።

እኛም ንቁ የአምላክ ቃል ተማሪዎች እንደመሆናችን መጠን በቅርቡ ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ ሆኖ የሚነሳው ማን እንደሚሆን ለማየት በጉጉት እንጠባበቃለን። ይሁን እንጂ ግንባር የፈጠሩትን ብሔራት የሚመራው ማንም ይሁን ማን፣ ስለ ሁለት ነገሮች እርግጠኞች ነን፦ (1) የማጎጉ ጎግና ሠራዊቱ ድል ተደርገው ይጠፋሉ፤ (2) በመግዛት ላይ ያለው ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክን ሕዝቦች በማዳን እውነተኛ ሰላምና ደህንነት ወዳለበት አዲስ ዓለም እየመራ ያስገባቸዋል።—ራእይ 7:14-17