“ንቁ ሆናችሁ ኑሩ! ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል።”—1 ጴጥ. 5:8

1. አንድ መንፈሳዊ ፍጡር፣ ሰይጣን የሆነው እንዴት እንደሆነ አብራራ።

በአንድ ወቅት በይሖዋ ፊት ጥሩ አቋም ነበረው። ይሁንና ይህ መንፈሳዊ ፍጡር፣ ሰዎች እንዲያመልኩት መመኘት ጀመረ። ይህን ተገቢ ያልሆነ ምኞት ከማስወገድ ይልቅ ስላሰላሰለበትና እንዲያድግ ስለፈቀደለት ምኞቱ ኃጢአትን ወለደ። (ያዕ. 1:14, 15) እያወራን ያለነው ‘በእውነት ውስጥ ጸንቶ ስላልቆመው’ ስለ ሰይጣን እንደሆነ የታወቀ ነው። ሰይጣን በይሖዋ ላይ ያመፀ ከመሆኑም ሌላ “የውሸት አባት” ሆነ።—ዮሐ. 8:44

2, 3. “ሰይጣን፣” “ዲያብሎስ፣” “እባብ” እና “ዘንዶ” የሚሉት መጠሪያዎች የይሖዋ ቀንደኛ ጠላት ስለሆነው አካል ምን ይገልጻሉ?

2 ሰይጣን ካመፀበት ጊዜ ጀምሮ የይሖዋ ቀንደኛ ጠላት እንደሆነ ታይቷል፤ የሰው ልጆች ወዳጅ ሆኖ እንደማያውቅም ግልጽ ነው። ለሰይጣን የተሰጡት መጠሪያዎች ምን ያህል በክፋት እንደተዘፈቀ ይጠቁማሉ። ሰይጣን የሚለው ቃል “ተቃዋሚ” ማለት ሲሆን ይህ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር የአምላክን ሉዓላዊነት እንደማይደግፍ ያሳያል፤ እንዲያውም የይሖዋን ሉዓላዊ ገዢነት የሚጠላ ከመሆኑም ሌላ አጥብቆ ይቃወመዋል። ሰይጣን ከምንም በላይ የሚፈልገው ነገር የይሖዋ ሉዓላዊ ገዢነት ሲያበቃ ማየት ነው።

3 ሰይጣን በራእይ 12:9 ላይ ዲያብሎስ ተብሎ ተጠርቷል፤ ይህም “ስም አጥፊ” ማለት ነው። ይህ መጠሪያ ሰይጣን፣ ይሖዋን ውሸታም ብሎ በመጥራት ስሙን እንዳጎደፈ ያስታውሰናል። “የጥንቱ እባብ” የሚለው አገላለጽ ሰይጣን፣ ኤደን ውስጥ በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን ያታለለበትን አሳዛኝ ቀን  እንድናስብ ያደርገናል። “ታላቁ ዘንዶ” የሚለው አገላለጽ ደግሞ አስፈሪ የሆነን አውሬ በአእምሯችን እንድንስል የሚያደርግ ሲሆን ይህም ሰይጣን በጭካኔ ተነሳስቶ የይሖዋን ዓላማ ለማደናቀፍና ሕዝቦቹን ለማጥፋት የሚያደርገውን ጥረት በሚገባ የሚገልጽ ነው።

4. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

4 በግልጽ ለማየት እንደምንችለው ንጹሕ አቋማችንን እንድናጎድፍ ለማድረግ ከተነሱ ጠላቶች ሁሉ ቀንደኛው ሰይጣን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ፤ ንቁ ሆናችሁ ኑሩ! ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል” ብሎ የሚመክረን መሆኑ የተገባ ነው። (1 ጴጥ. 5:8) ምግባረ ብልሹ የሆነውን የይሖዋንና የሕዝቦቹን ጠላት ማለትም የሰይጣንን ሦስት መለያዎች በዚህ ርዕስ ላይ እንመለከታለን፤ ይህን ማወቃችን በእሱ ላለመሸነፍ ይበልጥ የመጠንቀቅን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ ያደርገናል።

ሰይጣን ኃያል ነው

5, 6. (ሀ) መንፈሳዊ ፍጥረታት “ብርቱዎችና ኃያላን” እንደሆኑ የሚያሳይ ምሳሌ ስጥ። (ለ) ሰይጣን “ለሞት የመዳረግ አቅም” እንዳለው የሚገለጸው ከምን አንጻር ነው?

5 መላእክት ተብለው የሚጠሩት መንፈሳዊ ፍጥረታት “ብርቱዎችና ኃያላን” ናቸው። (መዝ. 103:20) መላእክት ከሰው ልጆች የላቁ ፍጥረታት በመሆናቸው በማሰብ ችሎታቸውም ሆነ በጥንካሬያቸው ከእኛ ይበልጣሉ። በእርግጥ ታማኝ የሆኑ መላእክት ኃይላቸውን የሚጠቀሙበት ለበጎ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የይሖዋ መልአክ የጠላት ወታደሮች የሆኑ 185,000 አሦራውያንን በአንድ ሌሊት ገድሏል፤ ይህን ማድረግ ለአንድ ሰው ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው፤ ሙሉ ሠራዊትም ቢሆን እንዲህ ያለ ጀብዱ ማከናወን ሊከብደው ይችላል። (2 ነገ. 19:35) በሌላ ወቅት ደግሞ አንድ የይሖዋ መልአክ ከሰው በላይ በሆነው ኃይሉና ብልሃቱ በመጠቀም የኢየሱስን ሐዋርያት ከወህኒ አስወጥቷቸዋል። ይህ መንፈሳዊ ፍጡር፣ ጠባቂዎቹን አልፎና የተቆለፉትን በሮች ከፍቶ ሐዋርያቱን ካስወጣ በኋላ በሮቹን መልሶ ቆለፈ፤ ይህን ሁሉ ሲያደርግ ጠባቂዎቹ በሩ ላይ ቆመው ነበር!—ሥራ 5:18-23

6 ታማኝ የሆኑ መንፈሳዊ ፍጥረታት ኃይላቸውን የሚጠቀሙበት መልካም ነገር ለማድረግ ነው፤ በተቃራኒው ግን ዲያብሎስ ኃይሉን የሚጠቀመው ለክፋት ነው። ደግሞም ከፍተኛ ኃይል ብሎም ተጽዕኖ የማሳደር ችሎታ አለው! ቅዱሳን መጻሕፍት ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዢ” እንዲሁም “የዚህ ሥርዓት አምላክ” ብለው ጠርተውታል። (ዮሐ. 12:31፤ 2 ቆሮ. 4:4) እንዲያውም ሰይጣን ዲያብሎስ “ለሞት የመዳረግ አቅም” አለው። (ዕብ. 2:14) ይህ ሲባል ሁሉንም ሰው በቀጥታ ይገድላል ማለት አይደለም። ሆኖም እሱ የሚያንጸባርቀው የነፍሰ ገዳይነት መንፈስ በመላው ዓለም ላይ ተስፋፍቷል። በተጨማሪም ሔዋን የሰይጣንን ውሸት በማመኗ እንዲሁም አዳም የአምላክን ትእዛዝ በመጣሱ ኃጢአትና ሞት ለሰው ዘር በሙሉ ተዳርሷል። (ሮም 5:12) ከዚህ አንጻር ዲያብሎስ “ለሞት የመዳረግ አቅም” እንዳለው ሊገለጽ ይችላል። ኢየሱስ እንደተናገረው ሰይጣን “ነፍሰ ገዳይ” ነው። (ዮሐ. 8:44) በእርግጥም ሰይጣን ኃያል ጠላታችን ነው!

7. አጋንንት ኃያል መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነው?

7 ዲያብሎስን ስንቃወም፣ እሱ ብቻ ሳይሆን የአጽናፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ገዢነት በሚመለከት በተነሳው ጥያቄ ረገድ ከእሱ ጋር የወገኑት ሁሉ ጠላቶቻችን ይሆናሉ። ከእነዚህም መካከል ብዛት ያላቸው ሌሎች ዓመፀኛ መንፈሳዊ ፍጥረታት ወይም አጋንንት ይገኙበታል። (ራእይ 12:3, 4) አጋንንት፣ በቁጥጥራቸው ሥር ያሉትን ሰዎች ለከፍተኛ ሥቃይ በመዳረግ ከሰው በላይ ኃይል እንዳላቸው በተደጋጋሚ አሳይተዋል። (ማቴ. 8:28-32፤ ማር. 5:1-5) እንግዲያው የእነዚህን ክፉ መላእክትም ሆነ ‘የአጋንንት አለቃ’ የሆነውን የሰይጣንን ኃይል ፈጽሞ አቅልላችሁ አትመልከቱ። (ማቴ. 9:34) የይሖዋን ድጋፍ ካላገኘን በቀር ከዲያብሎስ ጋር በምናደርገው ውጊያ በጭራሽ ማሸነፍ አንችልም።

ሰይጣን አረመኔ ነው

8. (ሀ) የሰይጣን ዓላማ ምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ምስል ተመልከት።) (ለ) ይህ ዓለም የሰይጣንን አረመኔያዊ መንፈስ እንደሚያንጸባርቅ የሚጠቁም ምን ያስተዋልከው ነገር አለ?

8 ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ዲያብሎስ “እንደሚያገሳ  አንበሳ” እንደሆነ ተናግሯል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው “እንደሚያገሳ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “በጣም የተራበን አውሬ ማጓራት” ያመለክታል። በእርግጥም ይህ ቃል የሰይጣንን አረመኔያዊ መንፈስ ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ነው! መላው ዓለም በቁጥጥሩ ሥር ቢሆንም ሰይጣን ተጨማሪ ሰለባዎች ይፈልጋል። (1 ዮሐ. 5:19) እሱ ዓለምን የሚመለከተው ከምግብ በፊት እንደሚቀርብ የመብላት ፍላጎትን የሚቀሰቅስ ነገር አድርጎ ነው። አሁን ትኩረቱን ወደ “ዋናው ምግብ” ይኸውም ወደ ቅቡዓን ቀሪዎችና ተባባሪዎቻቸው ወደሆኑት “ሌሎች በጎች” ያዞረ ያህል ነው። (ዮሐ. 10:16፤ ራእይ 12:17) የሰይጣን ዓላማ የይሖዋን ሕዝቦች መዋጥ ነው። ከመጀመሪያው መቶ ዘመን አንስቶ እስከ አሁን ድረስ በኢየሱስ ተከታዮች ላይ ያመጣው የስደት ማዕበል አረመኔ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ነው።

9, 10. (ሀ) ሰይጣን፣ አምላክ ከእስራኤል ብሔር ጋር በተያያዘ ያለውን ዓላማ ለማሰናከል የሞከረው እንዴት ነው? (ምሳሌ ስጥ።) (ለ) ሰይጣን በጥንቱ የእስራኤል ብሔር ላይ ትኩረት ያደረገበት ለየት ያለ ምክንያት ምን ነበር? (ሐ) በዛሬው ጊዜ አንድ የይሖዋ አገልጋይ ከባድ ኃጢአት ሲፈጽም ዲያብሎስ ምን የሚሰማው ይመስልሃል?

9 ሰይጣን የአምላክን ዓላማ ለማደናቀፍ በሚያደርገው ጥረት አረመኔ መሆኑን ያሳየበት ሌላም መንገድ አለ። የተራበ አንበሳ ለሚያድነው እንስሳ ምንም ዓይነት አዘኔታ የለውም። እንስሳውን ከመግደሉ በፊት ርኅራኄ አይሰማውም፤ ከበላው በኋላም ቢሆን በድርጊቱ አይጸጸትም። በተመሳሳይም ዲያብሎስ ሊውጣቸው ለሚሞክር ሰዎች ፈጽም አዘኔታ አያሳይም። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን እንደ ፆታ ብልግና እና ስግብግብነት ባሉት ኃጢአቶች እንዲወድቁ ለማድረግ ሰይጣን ዲያብሎስ ምን ያህል አድፍጦ ሲጠባበቅ እንደነበር አስብ። ዚምሪ በፆታ ብልግና፣ ግያዝ ደግሞ በስግብግብነት መሸነፋቸው ያስከተለባቸውን አሳዛኝ መዘዝ በምታነብበት ጊዜ፣ የሚያገሳው አንበሳ ባገኘው ድል ሲፈነጥዝ ይታይሃል?—ዘኁ. 25:6-8, 14, 15፤ 2 ነገ. 5:20-27

አንድ የአምላክ አገልጋይ ኃጢአት ሲፈጽም ሰይጣን በደስታ ይፈነጥዛል (አንቀጽ 10ን ተመልከት)

10 ሰይጣን በጥንቱ የእስራኤል ብሔር ላይ ትኩረት ያደረገበት ለየት ያለ ምክንያት ነበረው። እሱን የሚጨፈልቀውና የይሖዋን ሉዓላዊነት የሚያረጋግጠው መሲሕ የሚወለደው ከዚህ ብሔር ነው። (ዘፍ. 3:15) ዲያብሎስ፣ እስራኤላውያን እየበዙ እንዲሄዱ አልፈለገም፤ በመሆኑም እነሱን በኃጢአት ለመበከል ጭካኔ የተሞላበት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ዳዊት ምንዝር ሲፈጽም ወይም ነቢዩ ሙሴ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ ሲከለከል ሰይጣን አዝኖላቸዋል ብሎ ማሰብ የማይመስል  ነገር ነው። በተቃራኒው ግን አንድ የአምላክ አገልጋይ ከባድ ኃጢአት ሲፈጽም ሰይጣን በደስታ እንደሚፈነጥዝ ጥርጥር የለውም። እንዲያውም እነዚህን ድሎች ይሖዋን ለመንቀፍ ሳይጠቀምባቸው አይቀርም።—ምሳሌ 27:11

11. ዲያብሎስ ትኩረቱን በሣራ ላይ ያነጣጠረው ለምን ሊሆን ይችላል?

11 ዲያብሎስ፣ በተለይ መሲሑ ለሚመጣበት የዘር ሐረግ ጥላቻ ነበረው። ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃም “ታላቅ ብሔር” እንደሚሆን ከተነገረው ብዙም ሳይቆይ ምን እንደተከናወነ እስቲ እንመልከት። (ዘፍ. 12:1-3) አብርሃምና ሣራ በግብፅ በነበሩበት ጊዜ ፈርዖን ሣራን ወደ ቤቱ አስመጣት፤ ይህን ያደረገው የራሱ ሚስት ሊያደርጋት አስቦ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይሁንና ይሖዋ ጣልቃ በመግባት ሣራን ከዚህ ሥነ ምግባራዊ አደጋ ታደጋት። (ዘፍጥረት 12:14-20ን አንብብ።) ይስሐቅ ከመወለዱ ጥቂት ቀደም ብሎም በጌራራ ተመሳሳይ ሁኔታ ተከስቶ ነበር። (ዘፍ. 20:1-7) በእነዚህ ክስተቶች ውስጥ የሰይጣን እጅ ነበረበት? ዲያብሎስ፣ የበለጸገችውን የዑር ከተማ ትታ በድንኳን ትኖር የነበረችው ሣራ በፈርዖንና በአቢሜሌክ የተንቆጠቆጡ ቤተ መንግሥቶች እንደምትደለል አስቦ ይሆን? ሣራ፣ ባሏንም ሆነ ይሖዋን ከድታ እነዚህን ሰዎች በማግባት በትዳሯ ላይ ምንዝር እንደምትፈጽም ጠብቆ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚናገረው ነገር የለም፤ ሆኖም ሣራ፣ ቃል የተገባለትን ዘር ለማስገኘት ብቁ ሳትሆን ብትቀር ዲያብሎስ በጣም ይደሰት እንደነበር ለማመን የሚያበቃ ምክንያት አለን። እንደ ሣራ ያለች ጥሩ ሴት ትዳሯ ቢፈርስ፣ መልካም ስሟ ቢጎድፍ እንዲሁም በይሖዋ ፊት ያላትን ጥሩ አቋም ብታጣ ሰይጣን ቅንጣት ታክል የጥፋተኝነት ስሜት አይሰማውም። በእርግጥም ሰይጣን አረመኔ ነው!

12, 13. (ሀ) ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ ሰይጣን ምን አረመኔያዊ ድርጊት ፈጸመ? (ለ) በዛሬው ጊዜ ይሖዋን ስለሚወዱና እሱን ለማገልገል ጥረት ስለሚያደርጉ ወጣቶች ሰይጣን ምን የሚሰማው ይመስልሃል?

12 ኢየሱስ የተወለደው አብርሃም ከኖረ ከበርካታ ዘመናት በኋላ ነው። ሰይጣን ይህን ጨቅላ ሕፃን፣ የሚያምርና የሚያሳሳ እንደሆነ አድርጎ እንደማይመለከተው የታወቀ ነው። ምክንያቱም ይህ ሕፃን ሲያድግ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ እንደሚሆን ያውቃል። በእርግጥም ኢየሱስ የአብርሃም ዘር ዋነኛ ክፍል ነው፤ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ‘የዲያብሎስን ሥራ ያፈርሳል።’ (1 ዮሐ. 3:8) ሰይጣን አንድን ሕፃን መግደል ዘግናኝ ድርጊት እንደሆነ ይሰማው ይሆን? ዲያብሎስ የሥነ ምግባር ደንብ የለውም። ከሕፃኑ ኢየሱስ ጋር በተያያዘም ሳይውል ሳያድር እርምጃ ወሰደ። እንዴት?

13 ንጉሥ ሄሮድስ፣ ኮከብ ቆጣሪዎች ‘የተወለደውን የአይሁዳውያን ንጉሥ’ በተመለከተ ሲያጠያይቁ በሰማ ጊዜ በጣም ተበሳጨ፤ በመሆኑም ይህን ሕፃን ለመግደል ቆርጦ ተነሳ። (ማቴ. 2:1-3, 13) ሕፃኑ በምንም መንገድ እንዳያመልጥ ሲል በቤተልሔምና በአካባቢዋ የሚገኙ ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሆናቸው ወንዶች ልጆች በሙሉ እንዲገደሉ አዘዘ። (ማቴዎስ 2:13-18ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ለማሰብ ከሚከብደው ከዚህ እልቂት ተርፏል፤ ሆኖም ይህ ክንውን ጠላታችን ስለሆነው ስለ ሰይጣን ምን ይጠቁመናል? ዲያብሎስ ለሰው ሕይወት ምንም ደንታ እንደሌለው ግልጽ ነው። ለሕፃናት እንኳ የሚራራ አንጀት የለውም። እውነትም ሰይጣን “እንደሚያገሳ አንበሳ” ነው። ምን ያህል አረመኔ እንደሆነ ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም!

ሰይጣን አታላይ ነው

14, 15. ሰይጣን “የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ [ያሳወረው]” እንዴት ነው?

14 ሰዎች አፍቃሪ አምላክ ከሆነው ከይሖዋ የሚርቁት በሰይጣን ሲታለሉ ብቻ ነው። (1 ዮሐ. 4:8) ሰይጣን የሚጠቀምበት ማታለያ ሰዎች “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ” እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል። (ማቴ. 5:3 የግርጌ ማስታወሻ) በዚህ መንገድ ሰይጣን፣ “የአምላክ አምሳል ስለሆነው ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውና ክብራማ የሆነው ምሥራች የሚፈነጥቀው ብርሃን በእነሱ ላይ እንዳያበራ . . . የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ አሳውሯል።”—2 ቆሮ. 4:4

15 ሰይጣን በዋነኝነት ከሚጠቀምባቸው ማታለያዎች አንዱ የሐሰት ሃይማኖት ነው። ሰዎች የቀድሞ አባቶቻቸውን አሊያም የፍጥረት ሥራዎችን ወይም  እንስሳትን በሌላ አባባል ‘እሱ ብቻ እንዲመለክ ከሚፈልገው’ ከይሖዋ ውጪ ማንኛውንም አካል ወይም ግዑዝ ነገር ሲያመልኩ ሰይጣን በጣም ይደሰታል። (ዘፀ. 20:5) አምላክን በትክክለኛው መንገድ እያመለኩ እንዳሉ የሚሰማቸው ብዙ ሰዎች እንኳ በሐሰት እምነቶችና ትርጉም የለሽ በሆኑ የአምልኮ ሥርዓቶች ተተብትበዋል። ያሉበት አሳዛኝ ሁኔታ ይሖዋ እንደሚከተለው በማለት ከለመናቸው ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ነው፦ “ምግብ ላልሆነ ነገር ለምን ገንዘባችሁን ታወጣላችሁ? እርካታ ለማያስገኝ ነገርስ ለምን ገቢያችሁን ታባክናላችሁ? እኔን በጥሞና አዳምጡ፤ መልካም የሆነውንም ብሉ፤ ምርጥ ምግብ በመብላትም ሐሴት ታደርጋላችሁ።”—ኢሳ. 55:2

16, 17. (ሀ) ኢየሱስ፣ ጴጥሮስን “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ ሰይጣን” ያለው ለምንድን ነው? (ለ) ሰይጣን እኛን በማታለል የጥድፊያ ስሜታችንን እንድናጣ ሊያደርገን የሚችለው እንዴት ነው?

16 ዲያብሎስ፣ ቀናተኛ የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮችን እንኳ ሊያታልል ይችላል። ለምሳሌ፣ ኢየሱስ ሊገደል እንደሆነ ለደቀ መዛሙርቱ ሲነግራቸው ምን እንደተፈጠረ እንመልከት። ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው በመውሰድ “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን፤ በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም” አለው፤ ጴጥሮስ ይህን ያለው ለኢየሱስ አስቦ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ግን ጴጥሮስን “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ ሰይጣን!” በማለት ጠንከር ያለ መልስ ሰጠው። (ማቴ. 16:22, 23) ኢየሱስ፣ ጴጥሮስን “ሰይጣን” ብሎ የጠራው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስ በቅርቡ ምን እንደሚከናወን ያውቃል። ቤዛዊ መሥዋዕት ሆኖ የሚሞትበትና ዲያብሎስ ውሸታም መሆኑን የሚያረጋግጥበት ጊዜ ተቃርቧል። በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ወሳኝ በሆነው በዚህ ወቅት ኢየሱስ “በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን” ሊባል አይገባም። ኢየሱስ በዚህ ጊዜ ከተዘናጋ ሰይጣን የሚፈልገው ነገር ተሳካለት ማለት ነው።

17 እኛም ወደዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እየተቃረብን በመሆኑ የምንኖረው ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ ነው። ሰይጣን እንድንዘናጋ ይኸውም ‘በራሳችን ላይ ከመጨከን’ ይልቅ በዚህ ዓለም ውስጥ ለእኛ ተስማሚ የሆነውን ቦታ ለማግኘት በመጣር የጥድፊያ ስሜታችንን እንድናጣ ይፈልጋል። ይህ እንዲደርስባችሁ አትፍቀዱ! ከዚህ ይልቅ “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ።” (ማቴ. 24:42) ሰይጣን፣ መጨረሻው ሩቅ እንደሆነ ወይም ጨርሶ እንደማይመጣ ለሚያስፋፋው አታላይ ፕሮፓጋንዳ ፈጽሞ ጆሮ አትስጡ።

18, 19. (ሀ) ሰይጣን ስለ ራሳችን ባለን አመለካከት ረገድ ሊያታልለን የሚሞክረው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ የማስተዋል ስሜታችንን እንድንጠብቅና ንቁ ሆነን እንድንኖር የሚረዳን እንዴት ነው?

18 ሰይጣን በሌላም መንገድ ሊያታልለን ይሞክራል። አምላክ ሊወደን እንደማይችልና ኃጢአታችን ይቅር የማይባል እንደሆነ ሊያሳምነን ይፈልጋል። ሰይጣን ከሚያስፋፋው አታላይ ፕሮፓጋንዳ አንዱ ይህ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ይሖዋ በፍጹም ሊወደው የማይችለው አካል ማን ነው? ሰይጣን ነው። በጭራሽ ይቅር ሊባል የማይችለውስ ማን ነው? አሁንም ሰይጣን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ዕብ. 6:10) ይሖዋ እሱን ለማስደሰት የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል፤ ለእሱ የምናቀርበው አገልግሎትም ከንቱ አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 15:58ን አንብብ።) እንግዲያው በሰይጣን አታላይ ፕሮፖጋንዳ ላለመታለል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።

19 እስካሁን እንደተመለከትነው ሰይጣን ኃያል፣ አረመኔና አታላይ ነው። እንዲህ ካለው የማይገፋ ጠላት ጋር በምናደርገው ውጊያ ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ በሚገባ አስታጥቆናል። የአምላክ ቃል ሰይጣን ስለሚጠቀምባቸው ዘዴዎች የሚያስተምረን ሲሆን “እሱ የሚሸርበውን ተንኮል እናውቃለን።” (2 ቆሮ. 2:11) የሰይጣንን ዘዴዎች በደንብ ከተረዳን የማስተዋል ስሜታችንን መጠበቅና ንቁ ሆነን መኖር እንችላለን። ይሁንና ሰይጣን የሚሸርበውን ተንኮል ማወቅ ብቻ በቂ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ዲያብሎስን . . . ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል” ይላል። (ያዕ. 4:7) የሚቀጥለው ርዕስ ሰይጣንን ተዋግተን ማሸነፍ የምንችልባቸውን ሦስት አቅጣጫዎች ያብራራል።