በይሖዋ ማዕድ አንድ ላይ መመገብ የቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ጉልህ ገጽታ ሆኖ ቆይቷል። የአምላክ ሕዝቦች ለመንፈሳዊ ግብዣ ሲሰበሰቡ ሰብዓዊ ምግብ አብረው መመገባቸውም ብዙውን ጊዜ ደስታቸውን ይጨምርላቸዋል።

መስከረም 1919 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የስምንት ቀን ትልቅ ስብሰባ አድርገው ነበር። ልዑካኑ በሆቴሎች አርፈው እዚያው እንዲመገቡ ታስቦ የነበረ ቢሆንም ከተጠበቀው በላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሰብሳቢዎች መጡ። የሆቴሎቹ አስተናጋጆች የሚስተናገደው ሕዝብ ብዛት ከአቅማቸው በላይ ስለሆነባቸው ሁሉም ሥራ አቆሙ። በጭንቀት የተዋጠው የምግብ ቤቱ ሥራ አስኪያጅ፣ ወጣት የሆኑ የስብሰባው ልዑካን በምግብ መስተንግዶው ሥራ መርዳት ይችሉ እንደሆነ ጠየቀ፤ ብዙዎችም ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኑ። ሳዲ ግሪን ከእነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች መካከል አንዷ ነበረች። “በአስተናጋጅነት ስሠራ ይህ የመጀመሪያዬ ቢሆንም አስደሳች ጊዜ አሳልፈናል” በማለት ታስታውሳለች።

ሴራ ሊዮን፣ 1982

በቀጣዮቹ ዓመታት በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ምግብ ለማቅረብ በተደረጉት ዝግጅቶች፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ደስተኛ የሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን አገልግለዋል። በተጨማሪም በርካታ ወጣቶች ከእምነት አጋሮቻቸው ጋር አብረው መሥራታቸው መንፈሳዊ ግቦችን እንዲያወጡ ረድቷቸዋል። ግላዲስ ቦልተን በ1937 በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ ካፊቴሪያ ውስጥ ሠርታለች። እንዲህ ብላለች፦ “ከሌሎች ቦታዎች ከመጡ ወንድሞች ጋር ተዋወቅሁ፤ እንዲሁም ያሉባቸውን ችግሮች እንዴት እንደሚቋቋሙ መስማት ቻልኩ። አቅኚ ለመሆን ማሰብ የጀመርኩት ያን ጊዜ ነው።”

ቤዩላ ኮቪ የተባለች ተሰብሳቢ “ሠራተኞቹ በትጋት መሥራታቸው ሁሉም ነገር ያለምንም ችግር እንዲከናወን አስችሏል” ብላለች። እርግጥ ነው፣ ሥራው የራሱ የሆነ ተፈታታኝ ሁኔታ ነበረው። አንጄሎ ማሬና የተባለ ወንድም በ1969 ለሚደረገው ስብሰባ የካፊቴሪያ አገልጋይ ሆኖ እንደተመደበ ያወቀው በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ወደሚገኘው ዶጀር ስታዲየም ሲደርስ ነበር። “በሕይወቴ እንደዚያ ቀን ደንግጬ አላውቅም!” በማለት በግልጽ ተናግሯል። ለስብሰባው የሚደረገው ዝግጅት፣ ወደ ኩሽናው የነዳጅ መስመር ለማስገባት 400 ሜትር ርቀት የሚሸፍን ቦይ መቆፈርንም ይጨምር ነበር!

ፍራንክፈርት፣ ጀርመን 1951

በ1982 በሴራ ሊዮን በተደረገ ስብሰባ ላይ የነበሩት ታታሪ ሠራተኞች በቦታው ባሉት ቁሳቁሶች ተጠቅመው ካፊቴሪያ ለመሥራት መጀመሪያ አካባቢውን መመንጠር አስፈልጓቸው ነበር። በ1951 በፍራንክፈርት፣ ጀርመን በተካሄደ ስብስባ ላይ ደግሞ ዘዴኛ የሆኑ  ወንድሞች የባቡር ሞተር ከተከራዩ በኋላ ከዚያ በሚያገኙት የእንፋሎት ኃይል በመጠቀም 40 ድስቶችን ጥደው ማብሰል ችለዋል። አስተናጋጆቹ በሰዓት ለ30,000 ሰዎች ምግብ ያቀርቡ ነበር። በዕቃ ማጠቢያ ክፍል ውስጥ የሚያገለግሉትን 576 ሠራተኞች ሥራ ለማቅለል ሲባል ተሰብሳቢዎቹ የራሳቸውን ቢላና ሹካ አምጥተዋል። በያንጎን፣ ምያንማር ደግሞ አሳቢ የሆኑት ምግብ አብሳዮች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለመጡት ልዑካን ሲሉ ምግቡ ላይ የሚጨምሩትን የሚያቃጥል ቅመም ከወትሮው ቀነስ አድርገውታል።

“ቆመው እኮ ነው የሚበሉት”

አኒ ፖጊኒስ በ1950 በዩናይትድ ስቴትስ በተደረገው ስብሰባ ከካፊቴሪያው ምግብ ለማግኘት ፀሐይ ላይ ከተሰለፉት በርካታ ሰዎች መካከል መሆኗ በረከት አስገኝቶላታል። “ከአውሮፓ በመርከብ የመጡ ሁለት እህቶች ሞቅ ያለ ጭውውት ትኩረቴን ስቦት ነበር” ብላለች። ሁለቱም ይሖዋ በስብሰባው ላይ እንዲገኙ እንዴት እንደረዳቸው እየገለጹ ነበር። አኒ እንዲህ ብላለች፦ “በዚያ ቦታ የእነዚህን ሁለት እህቶች ያህል የተደሰተ ሰው አልነበረም። ተሰልፈው መጠበቃቸውም ሆነ ሙቀቱ ምንም አልመሰላቸውም።”

ሶል፣ ኮሪያ 1963

በአብዛኞቹ ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ሰፋፊ በሆኑት የድንኳን ካፊቴሪያዎች ውስጥ የተደረደሩት ጠረጴዛዎች ቁመታቸው ረጅም በመሆኑ ሰዎች የሚመገቡት ቆመው ነው፤ ይህ ደግሞ በፍጥነት በልተው ለሌላ ሰው ቦታ እንዲለቁ ያደርጋቸዋል። ይህ ባይሆንማ በሺዎች የሚቆጠሩት ተሰብሳቢዎች በምሳ እረፍት ተመግበው መጨረስ እንዴት ይችሉ ነበር? የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ አንድ ሰው “ይህ ግራ የሚገባ ሃይማኖት ነው፤ ቆመው እኮ ነው የሚበሉት” በማለት ተናግሯል።

ወታደራዊና የሲቪል ባለሥልጣናት በወንድሞች ቅልጥፍና እና አደረጃጀት በጣም ተደንቀው ነበር። የዩናይትድ ስቴትስ ሠራዊት አባላት በኒው ዮርክ ሲቲ፣ ያንኪ ስታዲየም የነበረውን ካፊቴሪያችንን ከጎበኙ በኋላ የብሪታንያ የጦር ሠራዊት አባል የሆኑትን ሜጀር ፎልክነርንም እንዲሁ እንዲያደርጉ አበረታቷቸው። በመሆኑም ሜጀር ፎልክነር ከባለቤታቸው ጋር በ1955 በትዊክንሃም፣ እንግሊዝ ወደተደረገው “ድል አድራጊው መንግሥት” የተባለ ትልቅ ስብሰባ መጡ። እኚህ ሰው ካፊቴሪያውን የሚያንቀሳቅሰው ፍቅር እንደሆነ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ፈቃደኛ ሠራተኞች፣ ወደ ትላልቅ ስብሰባዎች ለሚመጡ ወንድሞች ገንቢና ብዙ ገንዘብ የማያስወጡ ምግቦችን ለብዙ አሥርተ ዓመታት በፍቅር ተነሳስተው ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ይሁንና ይህን ከባድ ሥራ የሚያከናውኑት በርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች ብዙውን ጊዜ ለረጅም ሰዓት መሥራት ነበረባቸው፤ በዚያ ላይ ደግሞ የስብሰባው የተወሰነ ክፍል አንዳንድ ጊዜም ሙሉው ፕሮግራም ያመልጣቸዋል። በመሆኑም በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የሚኖረው የምግብ አቅርቦት ከ1970ዎቹ መጨረሻ አንስቶ በብዙ ቦታዎች ቀለል እንዲል ተደረገ። ከዚያም ከ1995 ጀምሮ ተሰብሳቢዎች የራሳቸውን ምግብ ይዘው እንዲመጡ ተነገራቸው። ይህም ምግብ ያዘጋጁና ያቀርቡ የነበሩት ሰዎች መንፈሳዊ ፕሮግራሙን መከታተልና ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንዲችሉ አድርጓል። *

የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለማገልገል ተግተው በሚሠሩት በእነዚህ ወንድሞች ይሖዋ ምንኛ ይደሰት ይሆን! አንዳንዶች በካፊቴሪያ ውስጥ ይሠሩ የነበሩበት አስደሳች ጊዜ ትዝታ ብቻ ሆኖ በመቅረቱ ያዝኑ ይሆናል። ሆኖም ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ መሆን እንችላለን፦ አሁንም ቢሆን በትላልቅ ስብሰባዎቻችን ላይ ዋነኛው ቅመም ፍቅር ነው።—ዮሐ. 13:34, 35

^ አን.12 እርግጥ ፈቃደኛ ሠራተኞች በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ በሌሎች የሥራ ክፍሎች እገዛ ማድረግ የሚችሉባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ።