በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ግንቦት 2015

ተስፋ የተሰጠበትን ነገር ‘አዩት’

ተስፋ የተሰጠበትን ነገር ‘አዩት’

“የተስፋውን ቃል ፍጻሜ ባያዩም እምነታቸውን እንደጠበቁ ሞቱ፤ ሆኖም ከሩቅ አይተው በደስታ ተቀበሉት።”—ዕብ. 11:13

1. አይተነው የማናውቀውን ነገር በዓይነ ሕሊናችን የመመልከት ችሎታ ምን ጥቅም ያስገኝልናል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

አይተነው የማናውቀውን ነገር በዓይነ ሕሊናችን የመመልከት ችሎታ ከአምላክ ያገኘነው ስጦታ ነው። ይህ ችሎታ ወደፊት የሚፈጸሙ መልካም ነገሮችን በተስፋ እንድንጠባበቅ እንዲሁም አስቀድመን ዕቅድ በማውጣት ችግር ውስጥ ከመግባት እንድንርቅ ይረዳናል። ይሖዋ ወደፊት የሚሆኑ ነገሮችን አስቀድሞ ስለሚያውቅ ስለ እነዚህ ነገሮች በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ብዙ ጊዜ ነግሮናል። እኛም ወደፊት የሚፈጸሙ ነገሮችን በአእምሯችን መሳል እንችል ይሆናል። እንዲያውም እምነት ለማዳበር የሚረዳን የማይታዩ ነገሮችን በምናብ የመመልከት ችሎታችን ነው።—2 ቆሮ. 4:18

2, 3. (ሀ) በዓይነ ሕሊናችን የምንመለከተው ነገር በምን ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል? ለምንስ? (ለ) በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 ፈጽሞ አይተነው ስለማናውቀው ነገር በአእምሯችን የሚኖረን ምስል አንዳንድ ጊዜ በእውነታ ላይ የተመሠረተ ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት ትንሽ ልጅ ቢራቢሮ እየጋለበች እንዳለች አድርጋ በዓይነ ሕሊናዋ ብትስል ይህ ሊሆን የማይችል ነገር ነው። በሌላ በኩል ግን ሐና፣ ልጇ በማደሪያው ድንኳን እንዲያገለግል ወደዚያ ስትወስደው ስለሚኖረው ሁኔታ ብታሰላስል በዓይነ ሕሊናዋ የምትመለከተው ነገር በእውነታ ላይ የተመሠረተ ነው። በአእምሮዋ የምትስለው ነገር በውሳኔዋ ላይ የተመሠረተ ሲሆን እንዲህ ማድረጓ በግቧ ላይ እንድታተኩር ረድቷታል። (1 ሳሙ. 1:22) እኛም አምላክ የሰጣቸውን ተስፋዎች በዓይነ ሕሊናችን ስንመለከት፣ እያሰላሰልን ያለነው መፈጸሙ በማይቀር ነገር ላይ ነው።—2 ጴጥ. 1:19-21

 3 በጥንት ዘመን የኖሩ በርካታ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች አምላክ ተስፋ የሰጣቸውን ነገሮች በአእምሯቸው ይስሉ እንደነበር ጥርጥር የለውም። እነዚህ ግለሰቦች ወደፊት የሚያገኙትን በረከት በዓይነ ሕሊናቸው መሳላቸው የጠቀማቸው እንዴት ነው? እኛስ አምላክ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ቃል በገባቸው አስደናቂ ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

ተስፋቸውን “ማየታቸው” አበረታቷቸዋል

4. አቤል ወደፊት የሚመጣውን ነገር በዓይነ ሕሊናው ለመሳል ምን መሠረት ነበረው?

4 የመጀመሪያው ታማኝ ሰው ይኸውም አቤል፣ ይሖዋ ተስፋ የሰጠውን ነገር በዓይነ ሕሊናው አይቶ ነበር? አምላክ ለእባቡ በተናገረው ሐሳብ ውስጥ የሚገኘው ተስፋ ከጊዜ በኋላ እንዴት እንደሚፈጸም አቤል ያውቅ ነበር ማለት አይቻልም፤ አምላክ “በአንተና በሴቲቱ መካከል እንዲሁም በዘርህና በዘሯ መካከል ጠላትነት እንዲኖር አደርጋለሁ፤ እሱ ራስህን ይጨፈልቃል፤ አንተም ተረከዙን ታቆስላለህ” ብሎ ነበር። (ዘፍ. 3:14, 15) ይሁንና አቤል በዚህ ተስፋ ላይ ብዙ ጊዜ አሰላስሎ እንዲሁም አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከመሥራታቸው በፊት የነበራቸው ዓይነት የፍጽምና ደረጃ ላይ የሰው ዘር መድረስ እንዲችል አንድ ሰው ‘ተረከዙ እንደሚቆስል’ ተገንዝቦ ሊሆን ይችላል። አቤል ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያሰበው ነገር ምንም ይሁን ምን አምላክ የሰጠው ተስፋ እንደሚፈጸም እምነት ነበረው፤ በመሆኑም ይሖዋ መሥዋዕቱን ተቀብሎታል።—ዘፍጥረት 4:3-5ን እና ዕብራውያን 11:4ን አንብብ።

5. ሄኖክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በዓይነ ሕሊናው መመልከቱ አበረታትቶት ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

5 ታማኝ የሆነው ሄኖክ፣ በአምላክ ላይ ክፉ ነገሮችን በሚናገሩ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች መካከል ቢኖርም በይሖዋ ላይ እምነት ነበረው። ሄኖክ በአምላክ መንፈስ መሪነት የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል፦ “ይሖዋ ከአእላፋት ቅዱሳን መላእክቱ ጋር መጥቷል፤ የመጣውም በሁሉ ላይ ለመፍረድ፣ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለአምላክ አክብሮት በጎደለው መንገድ የፈጸሙትን ክፉ ድርጊትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ኃጢአተኞች በእሱ ላይ የተናገሩትን ክፉ ቃል ለማጋለጥ ነው።” (ይሁዳ 14, 15) ሄኖክ፣ እምነት ያለው ሰው እንደመሆኑ መጠን ፈሪሃ አምላክ ከሌላቸው ሰዎች የጸዳ ዓለም የሚመጣበትን ጊዜ በዓይነ ሕሊናው ተመልክቶ ሊሆን ይችላል።ዕብራውያን 11:5, 6ን አንብብ።

6. ኖኅ ከጥፋት ውኃው በኋላ ስለ ምን ነገር ሊያስብ ይችላል?

6 ኖኅ ከጥፋት ውኃው ሊተርፍ የቻለው እምነት ስለነበረው ነው። (ዕብ. 11:7) ከጥፋት ውኃው በኋላም እምነቱ የእንስሳት መሥዋዕት እንዲያቀርብ አነሳስቶታል። (ዘፍ. 8:20) እንደ አቤል ሁሉ ኖኅም፣ ውሎ አድሮ የሰው ልጅ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ እንደሚወጣ እምነት ነበረው። ከጥፋቱ በኋላ ናምሩድ በይሖዋ ላይ ባመፀበት ጊዜ በነበረው ብሩህ ነገር የማይታይበት ወቅትም እንኳ ኖኅ እምነቱንና ተስፋውን አላጣም። (ዘፍ. 10:8-12) ኖኅ፣ የሰው ዘር ከጨቋኝ አገዛዝ፣ ከወረሰው ኃጢአትና ከሞት ነፃ ስለሚወጣበት ጊዜ ማሰቡ ልቡን በደስታ እንደሚሞላው የታወቀ ነው። እኛም እንዲህ ያለውን አስደናቂ ጊዜ በዓይነ ሕሊናችን ማየት እንችላለን፤ ደግሞም ይህ ጊዜ በጣም ቀርቧል!—ሮም 6:23

ተስፋው ሲፈጸም “አይተዋል”

7. አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ወደፊት ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚኖር ማየት ይችሉ ነበር?

7 አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ በእነሱ ዘር አማካኝነት የምድር ብሔራት ሁሉ በረከት እንደሚያገኙ አምላክ ቃል ስለገባላቸው ወደፊት አስደናቂ ሕይወት እንደሚኖር በአእምሯቸው መሳል ይችሉ ነበር። (ዘፍ. 22:18፤ 26:4፤ 28:14) የእነዚህ አባቶች ዘሮች፣ በቁጥር የሚበዙ ከመሆኑም ሌላ በተስፋይቱ ምድር ውስጥ ይኖራሉ። (ዘፍ. 15:5-7) አምላካዊ ፍርሃት ያላቸው እነዚህ ሰዎች፣ ዘሮቻቸው ቃል የተገባላቸውን ምድር ሲወርሱ በእምነት ዓይን መመልከት ይችሉ ነበር። ሰዎች ፍጽምናቸውን ካጡበት ጊዜ ጀምሮ ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ፣ አዳም ያጣቸውን በረከቶች መልሰው ማግኘት እንደሚችሉ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል።

8. አብርሃም ታላቅ እምነት እንዳለው የሚያሳዩ ነገሮችን ለማከናወን የረዳው ምንድን ነው?

 8 አብርሃም ታላቅ እምነት እንዳለው የሚያሳዩ ተግባሮችን ለማከናወን የረዳው አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች በዓይነ ሕሊናው መመልከት መቻሉ ሳይሆን አይቀርም። አብርሃምና ሌሎች ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በሕይወት ዘመናቸው “የተስፋውን ቃል ፍጻሜ ባያዩም” እንኳ “ከሩቅ አይተው በደስታ [እንደተቀበሉት]” ቅዱሳን መጻሕፍት ይናገራሉ። (ዕብራውያን 11:8-13ን አንብብ።) አብርሃም ተስፋ የሚያደርገው ነገር እውን እንደሚሆን የሚያረጋግጥ ብዙ ማስረጃ ስለነበረው ገና ያላየውን ነገር እንኳ በዓይነ ሕሊናው መሳል ችሏል!

9. አብርሃም፣ አምላክ ቃል በገባው ነገር ላይ ያለው እምነት የጠቀመው እንዴት ነው?

9 አብርሃም፣ አምላክ ቃል በገባው ነገር ላይ ያለው እምነት መለኮታዊውን ፈቃድ ለመፈጸም ብርታት ሰጥቶታል። ዑርን ለቆ የወጣውና በሄደባቸው የከነዓን ከተሞች ውስጥ ቋሚ መኖሪያ ሳያበጅ የኖረው እምነት ስለነበረው ነው። እንደ ዑር ሁሉ የእነዚህ ከተሞች ገዢዎችም ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች በመሆናቸው ከተሞቹ መጥፋታቸው እንደማይቀር ተገንዝቦ ነበር። (ኢያሱ 24:2) አብርሃም በኖረባቸው በርካታ ዓመታት ሁሉ “አምላክ ንድፍ ያወጣላትንና የገነባትን፣ እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ ይጠባበቅ ነበር።” (ዕብ. 11:10) አብርሃም፣ ዘላለማዊ በሆነና ይሖዋ በሚያስተዳድረው ቦታ ሲኖር ይታየው ነበር። አቤል፣ ሄኖክ፣ ኖኅ፣ አብርሃምና እንደ እነሱ ያሉ ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ሙታን እንደሚነሱ ያምኑ ነበር፤ እንዲሁም ‘እውነተኛ መሠረት ባለው ከተማ’ ይኸውም በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር በምድር ላይ ለመኖር ይጓጉ ነበር። እነዚህ ሰዎች እንደዚህ ባሉት በረከቶች ላይ ማሰላሰላቸው በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት አጠናክሮላቸዋል።ዕብራውያን 11:15, 16ን አንብብ።

10. ሣራ የወደፊቱን ጊዜ በዓይነ ሕሊናዋ መመልከቷ የጠቀማት እንዴት ነው?

10 የአብርሃም ሚስት የሆነችውን ሣራንም እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ጠንካራ እምነት ስለነበራት በ90 ዓመቷ ልጅ ባይኖራትም ወደፊት እንደምትወልድ ተስፋ ታደርግ ነበር። ዘሯ፣ አምላክ ቃል የገባውን በረከት እንደሚያገኝ “ይታያት” ነበር ሊባል ይችላል። (ዕብ. 11:11, 12) እንዲህ ያለ ተስፋ እንዲኖራት ያደረገው ምንድን ነው? ይሖዋ ለባለቤቷ ለአብርሃም “እኔም እባርካታለሁ፤ ከእሷም ወንድ ልጅ እሰጥሃለሁ። እባርካታለሁ፤ እሷም ብዙ ብሔር ትሆናለች፤ የሕዝቦች ነገሥታትም ከእሷ ይወጣሉ” ብሎት ነበር። (ዘፍ. 17:16) ሣራ ይስሐቅን ከወለደች በኋላ ደግሞ አምላክ ለአብርሃም የሰጣቸውን ሌሎች ተስፋዎች ፍጻሜ በዓይነ ሕሊናዋ ለመሳል የሚያበቃ አጥጋቢ ምክንያት አግኝታለች። እኛም አምላክ ቃል የገባቸውንና በእርግጠኝነት የሚፈጸሙትን አስደናቂ ነገሮች በዓይነ ሕሊናችን መመልከት መቻላችን እንዴት ያለ ግሩም ስጦታ ነው!

ሽልማቱን በትኩረት መመልከት

11, 12. ሙሴ ለይሖዋ ፍቅር ያዳበረው እንዴት ነው?

11 በይሖዋ ላይ እምነት የነበረው ሌላው ሰው ደግሞ ሙሴ ነው፤ ሙሴ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅርም ነበረው። ወጣት ሆኖ በግብፅ ንጉሣዊ ቤተሰብ መሃል ሲኖር የሥልጣንና የሀብት ፍቅር በቀላሉ ሊያድርበት ይችል ነበር። ይሁንና የሙሴ ወላጆች ስለ ይሖዋ እንዲሁም ዕብራውያንን ከባርነት ነፃ አውጥቶ ተስፋይቱን ምድር ለመስጠት ስላለው ዓላማ ሙሴን አስተምረውት መሆን አለበት። (ዘፍ. 13:14, 15፤ ዘፀ. 2:5-10) ሙሴ የአምላክ ሕዝቦች ወደፊት ስለሚያገኟቸው በረከቶች አዘውትሮ የሚያስብ ከሆነ ትልቅ ቦታ የማግኘት ፍላጎት የሚያድርበት ይመስልሃል? ወይስ ለይሖዋ ፍቅር ያዳብራል?

12 ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲህ ይላሉ፦ “ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ ተብሎ ለመጠራት በእምነት እንቢ አለ፤ በኃጢአት ከሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ከአምላክ ሕዝብ ጋር መንገላታትን መረጠ፤ ምክንያቱም ቅቡዕ ሆኖ የሚደርስበት ነቀፋ በግብፅ ከሚገኝ ውድ ሀብት የላቀ እንደሆነ አስቧል፤ የሚከፈለውን ወሮታ በትኩረት ተመልክቷልና።”—ዕብ. 11:24-26

13. ሙሴ፣ አምላክ ስለገባው ቃል በጥልቅ ማሰላሰሉ የጠቀመው እንዴት ነው?

 13 ሙሴ፣ ይሖዋ ለእስራኤላውያን ቃል ስለገባው ነገር በጥልቅ ባሰላሰለ መጠን በአምላክ ላይ ያለው እምነትና ለእሱ ያለው ፍቅር እያደገ ሄዷል። ፈሪሃ አምላክ እንዳላቸው ሌሎች ሰዎች ሁሉ እሱም፣ ይሖዋ የሰውን ዘር ከሞት ባርነት ነፃ የሚያወጣበትን ጊዜ በዓይነ ሕሊናው ተመልክቶ ሊሆን ይችላል። (ኢዮብ 14:14, 15፤ ዕብ. 11:17-19) ሙሴ፣ ለዕብራውያንም ሆነ ለመላው የሰው ዘር ርኅራኄ ያለውን አምላክ መውደዱ የሚያስገርም አይደለም። በመላው ሕይወቱ ይሖዋን እንዲያገለግል የረዳው፣ እምነትና ፍቅር ያለው መሆኑ ነው። (ዘዳ. 6:4, 5) ፈርዖን እንደሚገድለው ቢዝትበትም እንኳ እምነቱ፣ ለአምላክ ያለው ፍቅርና ምናልባትም ወደፊት የሚጠብቀውን ግሩም ሕይወት በአእምሮው መሳሉ ፈርዖንን በድፍረት ለመጋፈጥ አጠናክሮታል።—ዘፀ. 10:28, 29

የመንግሥቱ ተስፋዎች ሲፈጸሙ በዓይነ ሕሊና መመልከት

14. የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ አንዳንድ ሰዎች ምን ያልማሉ?

14 ዛሬ ብዙ ሰዎች የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ በአእምሯቸው የሚስሉት ነገር በእውነታ ላይ የተመሠረተ አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ሰዎች ያላቸው ቁሳዊ ነገር ጥቂት ቢሆንም የናጠጡ ሀብታሞች ሆነው ምንም የሚያሰጋቸው ነገር ሳይኖር ስለ መኖር ያልማሉ፤ ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ሕይወት “በችግርና በሐዘን የተሞላ” እንደሆነ ይናገራል። (መዝ. 90:10) ሌሎች ደግሞ በሰብዓዊ አገዛዝ ሥር ያለምንም ጭንቀት ለመኖር ይመኛሉ፤ ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው ልጅ ብቸኛው ተስፋ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ይናገራል። (ዳን. 2:44) ብዙ ሰዎች አምላክ ይህን ክፉ ሥርዓት እንደማያጠፋው ይሰማቸዋል፤ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። (ሶፎ. 1:18፤ 1 ዮሐ. 2:15-17) ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያለውን ዓላማ ችላ የሚሉ ሰዎች ተስፋ የሚያደርጉት ነገር የሕልም እንጀራ ከመሆን አያልፍም።

በአዲሱ ዓለም የሚኖርህን ሕይወት በዓይነ ሕሊናህ መመልከት ትችላለህ? (አንቀጽ 15ን ተመልከት)

15. (ሀ) ክርስቲያኖች ተስፋቸውን በዓይነ ሕሊናቸው መመልከታቸው የሚጠቅማቸው እንዴት ነው? (ለ) አምላክ የገባው ቃል ሲፈጸም ምን ለማግኘት ትጓጓለህ?

15 በሌላ በኩል ግን ክርስቲያኖች ተስፋችን በሰማይ መኖርም ይሁን በምድር፣ ይህን በዓይነ ሕሊናችን መመልከታችን ያበረታታናል። አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች ስታገኝ ይታይሃል? አምላክ የሰጠው ተስፋ በሚፈጽምበት ወቅት ምን እንደምታደርግ ማሰላሰልህ ልብህን በደስታ እንደሚሞላው ጥርጥር የለውም። በምድር ላይ ለዘላለም ስትኖር በዓይነ ሕሊናህ ማየት ትችል ይሆናል። ከሌሎች ጋር ተባብረህ ምድርን ወደ ገነት ስትለውጥ ይታይህ። ጎረቤቶችህም እንደ አንተ ይሖዋን ይወዳሉ። ጤናማና ጠንካራ ከመሆንህም ሌላ አዎንታዊ አመለካከት አለህ። ምድርን ወደ ቀድሞው ሁኔታዋ የመመለሱን ሥራ በበላይነት የሚመሩትም ስለ አንተ ከልባቸው ስለሚያስቡ ሕይወት አስደሳች ነው። በተጨማሪም የምታከናውናቸው ነገሮች በሙሉ ሌሎችን የሚጠቅሙና አምላክን የሚያስከብሩ ስለሆኑ ባለህ ተሰጥኦና ችሎታ መጠቀም ያስደስትሃል። ለምሳሌ ያህል፣ ከሞት የሚነሱትን ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ ትረዳለህ። (ዮሐ. 17:3፤ ሥራ 24:15) ይህ፣ እንዲያው ከንቱ ምኞት አይደለም። በዓይነ ሕሊናችን የምንስለው እንዲህ ያለው አስደሳች ሕይወት ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ ወደፊቱ ጊዜ በሚናገሩት እውነት ላይ የተመሠረተ ነው።—ኢሳ. 11:9፤ 25:8፤ 33:24፤ 35:5-7፤ 65:22

ስለ ተስፋችን መነጋገራችን ምን ጥቅም አለው?

16, 17. ስለ ተስፋችን መነጋገራችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

16 ይሖዋ የገባውን ቃል ሲፈጽም እኛ ምን ማድረግ እንደምንፈልግ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር መነጋገራችን የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ በዓይነ ሕሊናችን የምንስለው ነገር ይበልጥ እውን እየሆነልን እንዲሄድ ያደርጋል። በአዲሱ ዓለም ውስጥ በግለሰብ ደረጃ ሕይወታችን ምን እንደሚመስል በእርግጠኝነት ማወቅ ባንችልም ወደፊት ስለሚፈጸሙ ነገሮች ማውራታችን፣ እርስ በርስ ለመበረታታት አልፎ ተርፎም አምላክ ቃል የገባው ነገር እንደሚፈጸም  ያለንን እምነት ለመግለጽ ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም የሚገኙ ወንድሞቹን በጎበኘበት ወቅት ‘እርስ በርስ እንደተበረታቱ’ የታወቀ ነው፤ እኛም በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንችላለን።—ሮም 1:11, 12

17 የወደፊቱን ጊዜ በዓይነ ሕሊናችን መመልከታችን አሁን የሚያጋጥሙን ችግሮች የሚፈጥሩብንን አሉታዊ አስተሳሰብ ለመቆጣጠር ይረዳናል። በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ኢየሱስን “እነሆ፣ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ ታዲያ የምናገኘው ምን ይሆን?” በማለት ያሳሰበውን ነገር ጠይቆት ነበር። ኢየሱስም ጴጥሮስና በቦታው የነበሩት ሌሎች ተከታዮቹ የወደፊቱን ጊዜ በአእምሯቸው እንዲስሉ ለመርዳት እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ሁሉም ነገር አዲስ በሚሆንበት ጊዜ የሰው ልጅ፣ ክብራማ በሆነው ዙፋኑ ላይ ሲቀመጥ እኔን የተከተላችሁኝ እናንተ በ12 ዙፋኖች ላይ ተቀምጣችሁ በ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ ትፈርዳላችሁ። እንዲሁም ስለ ስሜ ሲል ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለም ሕይወትም ይወርሳል።” (ማቴ. 19:27-29) ጴጥሮስና ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት፣ ምድርን በሚያስተዳድረውና ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች አስደናቂ በረከቶችን በሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ውስጥ በሚኖራቸው ድርሻ ላይ ማሰላሰል ይችሉ ነበር።

18. አምላክ ቃል ስለገባቸው ነገሮች ፍጻሜ ማሰባችን በዛሬው ጊዜ የሚጠቅመን እንዴት ነው?

18 በየትኛውም ጊዜ በምድር ላይ የኖሩ የአምላክ አገልጋዮች፣ አምላክ ቃል ስለገባቸው ነገሮች ፍጻሜ በማሰባቸው ተጠቅመዋል። አቤል ስለ አምላክ ዓላማ ያወቀው ነገር የተሻለ የወደፊት ሕይወት እንደሚመጣ ለማሰብ፣ እምነት ለማዳበርና አስተማማኝ ተስፋ እንዳለው ለማመን አስችሎታል። አብርሃም ታላቅ እምነት እንዳለው የሚያሳዩ ነገሮችን ያከናወነው፣ ተስፋ ከተሰጠበት “ዘር” ጋር በተያያዘ አምላክ ስለተናገረው ትንቢት ፍጻሜ በዓይነ ሕሊናው በማየቱ ነው። (ዘፍ. 3:15) ሙሴ “የሚከፈለውን ወሮታ በትኩረት ተመልክቷል”፤ በመሆኑም እምነትና ለይሖዋ ፍቅር ማዳበር ችሏል። (ዕብ. 11:26) እኛም ይሖዋ ቃል የገባቸውን ነገሮች ፍጻሜ በዓይነ ሕሊናችን የመመልከት ችሎታችንን የምንጠቀምበት ከሆነ በአምላክ ላይ ያለን እምነትና ለእሱ ያለን ፍቅር እያደገ መሄዱ አይቀርም። ከአምላክ ያገኘነውን ይህን ስጦታ ጥሩ አድርገን መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።