ጊዜው 1970 ነው። ፊኒክስቪል፣ ፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው ቫሊ ፎርጅ አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ ተኝቼ ነበር። አንድ ነርስ፣ የደም ግፊቴን በየግማሽ ሰዓቱ ይለካል። በወቅቱ 20 ዓመቴ ሲሆን ወታደር ነበርኩ፤ ሆስፒታል የገባሁትም ከባድ ተላላፊ በሽታ ስለያዘኝ ነው። በዕድሜ ብዙም የማይበልጠኝ ይህ ነርስ የተጨነቀ ይመስል ነበር። የደም ግፊቴ መውረዱን ሲቀጥል “ሰው ሲሞት አይተህ አታውቅም አይደል?” አልኩት። ወዲያው ፊቱ ተለዋወጠ፤ ከዚያም “በፍጹም፣ አይቼ አላውቅም” ብሎ መለሰ።

በዚያን ጊዜ በሕይወት የምተርፍ አይመስልም ነበር። ይሁንና መጀመሪያውኑ ሆስፒታል የገባሁት ለምንድን ነው? እስቲ ከሕይወት ታሪኬ ጥቂቱን ላውጋችሁ።

ስለ ጦርነት ማወቅ

የታመምኩት በቬትናም በተካሄደው ጦርነት ወቅት የቀዶ ሕክምና ክፍል ረዳት ሆኜ በመሥራት ላይ ሳለሁ ነው። የታመሙትንና የቆሰሉትን ሰዎች መርዳት ያስደስተኝ ነበር፤ ግቤም የቀዶ ሕክምና ባለሞያ መሆን ነበር። ቬትናም የደረስኩት ሐምሌ 1969 ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቬትናም ለመጡ ሰዎች እንደሚደረገው ሁሉ እኔም የሰዓት ልዩነቱንና ወበቁን እስክለምደው ድረስ አንድ ሳምንት የትውውቅ ጊዜ ተሰጠኝ።

የተመደብኩት በዶንግ ታም በሚገኘው በሜኮንግ ዴልታ የቀዶ ሕክምና ሆስፒታል ውስጥ ነበር፤ በዚያ መሥራት ከጀመርኩ ብዙም ሳይቆይ በቁስለኞች የተሞሉ በርካታ ሄሊኮፕተሮች መምጣት ጀመሩ። ከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት ስለነበረኝና መሥራት ስለምወድ ወዲያውኑ በሥራው መሳተፍ ፈለግኩ። የቆሰሉት ሰዎች ለቀዶ ሕክምና ከተዘጋጁ በኋላ ለዚህ ዓላማ ወደሚያገለግሉት ከብረት የተሠሩና የአየር ማቀዝቀዣ ያላቸው ትናንሽ ቤቶች በፍጥነት ይወሰዳሉ። ከዚያም የቀዶ ጥገና ሐኪሙ፣ ማደንዘዣ የሚሰጠው ባለሞያ እንዲሁም በቀዶ ሕክምና ክፍል የሚሠሩት ሁለት ነርሶች ጠባብ በሆነችው ክፍል ውስጥ ታጭቀው የሰዎችን ሕይወት ለማትረፍ ይረባረባሉ። ይሁንና በትላልቅ ጥቁር ከረጢቶች የሚመጡት ጭነቶች ከሄሊኮፕተሮቹ ላይ እንደማይወርዱ አስተዋልኩ። እነዚያ ከረጢቶች የያዙት በውጊያ ላይ በፈንጂ ሰውነታቸው የተቆራረጠ ወታደሮችን የአካል ክፍሎች እንደሆነ ተነገረኝ። ስለ ጦርነት ያወቅኩት በዚህ መንገድ ነበር።

አምላክን ለማግኘት ያደረግሁት ፍለጋ

ወጣት እያለሁ ስለ እውነት በተወሰነ መጠን አውቅ ነበር

ወጣት ሳለሁ የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያስተምሩት እውነት በተወሰነ መጠን አውቅ ነበር። ውዷ እናቴ እስከ ጥምቀት  ባትደርስም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጥንታለች። እኔም እናቴ ስታጠና ቁጭ ብዬ ማዳመጥ በጣም ያስደስተኝ ነበር። በዚያው ጊዜ አካባቢ ከእንጀራ አባቴ ጋር በአንድ የመንግሥት አዳራሽ አጠገብ አለፍን። “ያ ምንድን ነው?” ብዬ ጠየቅሁት። እሱም “እነዚያ ሰዎች አጠገብ እንዳትደርስ!” በማለት መለሰልኝ። የእንጀራ አባቴን እወደውና አምነው ስለነበር ምክሩን ተቀበልኩ። በመሆኑም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተራራቅሁ።

ከቬትናም ከተመለስኩ በኋላ ከአምላክ ጋር ዝምድና መመሥረት እንደሚያስፈልገኝ ተሰማኝ። የሚረብሹ ትዝታዎች ስሜቴን አደንዝዘውት ነበር። በቬትናም የሚካሄደውን ነገር የሚረዳ ያለ አይመስልም። ምንም ያላጠፉ ሕፃናት በጦርነቱ እያለቁ እንደሆነ የሚገልጹ ሪፖርቶች ስለነበሩ ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ሰዎች የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮችን ‘ሕፃናት ገዳዮች’ እያሉ ሲጠሯቸው ትዝ ይለኛል።

መንፈሳዊ ረሃቤን ለማርካት ስል ወደተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት መሄድ ጀመርኩ። ለአምላክ ሁልጊዜም ፍቅር ነበረኝ፤ ሆኖም በአብያተ ክርስቲያናቱ ያየሁት ነገር አላረካኝም። በመጨረሻም በዴልሬይ ቢች፣ ፍሎሪዳ ወደሚገኝ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ሄድኩ። ዕለቱ እሁድ፣ የካቲት 1971 ነበር።

ወደ መንግሥት አዳራሹ ስገባ የሕዝብ ንግግሩ ሊያበቃ ተቃርቦ ነበር፤ በመሆኑም ከዚያ በመቀጠል በተካሄደው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ተገኘሁ። በእርግጥ ያን ዕለት ስለ ምን እንደተጠና አላስታውስም፤ ይሁን እንጂ ትናንሽ ልጆች መጽሐፍ ቅዱሳቸውን እየገለጡ ጥቅስ ሲያወጡ እንዳየሁ ትዝ ይለኛል። ይህም በጣም አስደነቀኝ! በጥሞና አዳምጥና የሚከናወነውን ነገር እታዘብ ነበር። ከመንግሥት አዳራሹ እየወጣሁ ሳለ ዕድሜው 80 ዓመት ገደማ የሚሆነው አንድ ተወዳጅ ወንድም ወደ እኔ መጣ። ጂም ጋርድነር ይባላል። እሱም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ አወጣና “ይህን መጽሐፍ ልስጥህ?” አለኝ። ከዚያም ሐሙስ ጠዋት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሊያስጀምረኝ ተቀጣጠርን።

በዚያ ዕለት ማለትም እሁድ ሌሊት ሥራ ገቢ ነበርኩ። በቦካ ረቶን፣ ፍሎሪዳ በሚገኝ አንድ የግል ሆስፒታል ውስጥ ተቀጥሬ በድንገተኛ ክፍል እሠራ ነበር። የሥራ ፈረቃዬ ከምሽቱ 5:00 እስከ ጠዋቱ 1:00 ነበር። ሥራ ያልበዛበት ሌሊት በመሆኑ እውነት የተባለውን መጽሐፍ ማንበብ ቻልኩ። ኃላፊነት ያላት አንዲት ነርስ ወደ እኔ መጣችና መጽሐፉን ከእጄ ነጥቃ ሽፋኑን እያየች “መቼም እንደ እነሱ ልሆን ነው እንዳትለኝ!” ብላ ጮኸችብኝ። እኔም መጽሐፌን መልሼ ተቀበልኳትና “መጽሐፉን ገና አልጨረስኩትም፤ እንደ እነሱ መሆኔ ግን የሚቀር አይመስለኝም!” አልኳት። ነርሷ ትታኝ ሄደች፤ መጽሐፉን በዚያች ሌሊት አንብቤ ጨረስኩት።

መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናኝ ጂም ጋርድነር የተባለ ከቻርልስ ቴዝ ራስል ጋር የሚተዋወቅ ቅቡዕ ወንድም ነው

ከወንድም ጋርድነር ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት መጀመሪያ ስንገናኝ “ለመሆኑ የምናጠናው ምንድን ነው?” ብዬ ጠየቅኩት። እሱም “የሰጠሁህን መጽሐፍ” በማለት መለሰልኝ። “እሱንማ አንብቤ ጨርሼዋለሁ” አልኩት። ወንድም ጋርድነር “እስቲ የመጀመሪያውን ምዕራፍ እንመልከት” በማለት በደግነት መለሰልኝ። መጽሐፉን ሳነብ ምን ያህል ብዙ ነገር ሳላስተውል እንዳለፍኩ በጥናታችን ወቅት ተገነዘብኩ፤ ይህም በጣም አስገረመኝ። እሱም፣ ኢየሱስ የተናገራቸው ነገሮች  በቀይ ቀለም ከተጻፉበት ኪንግ ጀምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱሴ ላይ ብዙ ጥቅሶችን አስነበበኝ። ስለ እውነተኛው አምላክ ስለ ይሖዋ በመጨረሻ መማር ቻልኩ። በቁልምጫ ጂም እያልኩ የምጠራው ወንድም ጋርድነር በዚያን ዕለት ጠዋት ከእውነት መጽሐፍ ላይ ሦስት ምዕራፎችን አስጠናኝ። ከዚያ በኋላም በየሳምንቱ ሐሙስ ጠዋት ሦስት ምዕራፎችን እናጠና ነበር። ጥናታችንን በጣም ወደድኩት። ቻርልስ ቴዝ ራስልን በቅርብ ያውቀው የነበረው ይህ ቅቡዕ ወንድም ያስተማረኝ መሆኑ ምንኛ መታደል ነው!

ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የምሥራቹ አስፋፊ እንድሆን ተፈቀደልኝ። ጂም ከቤት ወደ ቤት የሚከናወነውን አገልግሎት ጨምሮ በሚያሳስቡኝ ብዙ ነገሮች ረገድ ረድቶኛል። (ሥራ 20:20) ከጂም ጋር አብሬ ሳገለግል የስብከቱን ሥራ እየወደድኩት መጣሁ። አሁንም ቢሆን አገልግሎትን እንደ ትልቅ መብት እቆጥረዋለሁ። ከአምላክ ጋር አብሮ መሥራት እንዴት የሚያስደስት ነገር ነው!—1 ቆሮ. 3:9

ለይሖዋ ያደረብኝ የመጀመሪያ ፍቅር

አሁን ደግሞ ትልቅ ቦታ የምሰጠውን አንድ ጉዳይ ይኸውም ለመጀመሪያ ጊዜ ለይሖዋ ፍቅር ያደረብኝ እንዴት እንደሆነ ላውጋችሁ። (ራእይ 2:4) ለይሖዋ ያለኝ ይህ ፍቅር፣ ከጦርነት ጋር የተያያዙ አሰቃቂ ትዝታዎችንና ሌሎች ብዙ መከራዎችን እንድቋቋም ረድቶኛል።—ኢሳ. 65:17

ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር ከጦርነት ጋር የተያያዙ አሰቃቂ ትዝታዎችንና ሌሎች ብዙ መከራዎችን እንድቋቋም ረድቶኛል

ሐምሌ 1971 በያንኪ ስታዲየም በተደረገ “መለኮታዊው ስም” የተሰኘ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተጠመቅሁ

በ1971 የጸደይ ወቅት አንድ ቀን ያጋጠመኝን ነገር አልረሳውም። እንጀራ አባቴ፣ የይሖዋ ምሥክር የሆነ ሰው በቤቱ እንዲኖር አልፈለገም። በመሆኑም ወላጆቼ እንድኖርበት ፈቅደውልኝ ከነበረው ኮንዶሚኒየም ተባርሬ ነበር። በወቅቱ ብዙ ገንዘብ አልነበረኝም። የምሠራበት ሆስፒታል ደሞዜን የሚከፍለኝ በየሁለት ሳምንቱ ነው፤ ሆኖም ይሖዋን የሚያስከብር ሥርዓታማ ልብስ ለብሼ በአገልግሎት ለመካፈል ስል አብዛኛውን ገንዘቤን ልብስ ለመግዛት ተጠቅሜበት ነበር። ጥቂት ተቀማጭ ገንዘብ ቢኖረኝም ገንዘቡ የሚገኘው  ባደግሁበት በሚሺገን ግዛት ውስጥ ባለ ባንክ ነበር። በመሆኑም ለጥቂት ቀናት በመኪናዬ ውስጥ ለማደር ተገደድኩ። ጺሜን የምላጨውና የምተጣጠበው በነዳጅ ማደያ መጸዳጃ ቤት ነበር።

በመኪናዬ ውስጥ እያደርኩ በነበርኩበት ጊዜ አንድ ቀን፣ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባው ከመጀመሩ ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብዬ መንግሥት አዳራሽ ደረስኩ። የሆስፒታል ፈረቃዬን ጨርሼ መውጣቴ ነው። ማንም ሊያየኝ በማይችልበት በመንግሥት አዳራሹ ጀርባ ተቀምጬ ሳለሁ በቬትናም ያጋጠሙኝ ነገሮች ትዝታ፣ ይኸውም የተቃጠለ ሰውነት ጠረን እንዲሁም ያየሁት ደምና ቁስል ወደ አእምሮዬ መጣ። “የምተርፍ ይመስልሃል? እተርፋለሁ?” የሚሉ ወጣቶች ድምፅ ይሰማኝ እና መልካቸው ቁልጭ ብሎ ይታየኝ ጀመር። እንደሚሞቱ ባውቅም እውነቱን ፊቴ ላይ እንዳያነቡት የቻልኩትን ያህል እየተጠነቀቅኩ ላጽናናቸው እሞክር ነበር። ከመንግሥት አዳራሹ ጀርባ ተቀምጬ እያለሁ ስሜቴ በጣም ተረበሸ።

በተለይ በመከራና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በማልፍበት ጊዜ ለይሖዋ ያደረብኝን የመጀመሪያ ፍቅር ፈጽሞ ላለማጣት የተቻለኝን ሁሉ አድርጌያለሁ

ስቅስቅ ብዬ እያለቀስኩ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። (መዝ. 56:8) ስለ ትንሣኤ ተስፋ በጥልቅ ማሰብ ጀመርኩ። በዚያው ቅጽበት አንድ ነገር ወደ አእምሮዬ መጣ፦ ይሖዋ አምላክ ያየሁትን ሁሉ እልቂት እንዲሁም እኔም ሆንኩ ሌሎች የደረሰብንን የስሜት ሥቃይ በትንሣኤ አማካኝነት ያጠፋዋል። አምላክ እነዚያን ወጣቶች ከሞት የሚያስነሳቸው ሲሆን ስለ እሱ እውነቱን ለመማር አጋጣሚ ያገኛሉ። (ሥራ 24:15) በዚያው ቅጽበት ለይሖዋ ውስጤ ድረስ የዘለቀ ጥልቅ ፍቅር አደረብኝ። ያ ዕለት ለእኔ ምንጊዜም ልዩ ነው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፣ በተለይ በመከራና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በማልፍበት ጊዜ ለይሖዋ ያደረብኝን የመጀመሪያ ፍቅር ፈጽሞ ላለማጣት የተቻለኝን ሁሉ አድርጌያለሁ።

የይሖዋን ጥሩነት አይቻለሁ

በጦርነት ላይ ሰዎች አሰቃቂ ነገሮችን ይፈጽማሉ። እኔም ብሆን የተለየሁ አልነበርኩም። ይሁን እንጂ ከምወዳቸው ጥቅሶች በሁለቱ ላይ ማሰላሰሌ ረድቶኛል። አንደኛው ራእይ 12:10, 11 ነው፤ ጥቅሱ ዲያብሎስ ድል የሚነሳው በምሥክርነታችን ቃል ብቻ ሳይሆን በበጉ ደም አማካኝነትም እንደሆነ ይናገራል። ሁለተኛው ደግሞ ገላትያ 2:20 ነው። ይህ ጥቅስ ክርስቶስ ኢየሱስ “ለእኔ” እንደሞተልኝ አስገንዝቦኛል። ይሖዋ እኔን የሚመለከተኝ በኢየሱስ ደም አማካኝነት እንደነጻሁ አድርጎ ስለሆነ ያጠፋሁትን ሁሉ ይቅር ብሎኛል። ይህን ሐቅ ማወቄ ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረኝ ያስቻለኝ ከመሆኑም ሌላ ሌሎችም ስለ መሐሪው አምላካችን ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ ለመርዳት የቻልኩትን ሁሉ እንዳደርግ አነሳስቶኛል!—ዕብ. 9:14

ሕይወቴን ወደኋላ መለስ ብዬ ሳየው ይሖዋ ምንጊዜም እንደተንከባከበኝ ይሰማኛል። ለምሳሌ ያህል፣ ጂም መኪናዬ ውስጥ እያደርኩ መሆኑን ያወቀ ዕለት የእንግዳ ማረፊያ ቤት ካላት አንዲት እህት ጋር አገናኘኝ። ይሖዋ፣ የማርፍበት ጥሩ ቦታ እንዳገኝ ጂምንና ያችን ውድ እህት እንደተጠቀመባቸው እርግጠኛ ነኝ። ይሖዋ በጣም ደግ ነው! ታማኝ አምላኪዎቹን ይንከባከባቸዋል።

ቀናተኛ ብቻ ሳይሆን ዘዴኛም መሆን

ግንቦት 1971 የሆነ ጉዳይ ለመፈጸም ወደ ሚሺገን መሄድ አስፈልጎኝ ነበር። በዴልሬይ ቢች፣ ፍሎሪዳ ያለውን ጉባኤ ለቅቄ ከመሄዴ በፊት የመኪናዬን ዕቃ ማስቀመጫ በጽሑፎች ከሞላሁት በኋላ ኢንተርስቴት 75 በተባለው ጎዳና አድርጌ ወደ ሰሜን አቀናሁ። የያዝኳቸው ጽሑፎች ጉዞዬን ገና ሳላጋምስ አለቁ። በሁሉም ስፍራ የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት ሰብኬያለሁ። በወህኒ ቤቶች ምሥራቹን ተናግሬያለሁ፤ ሌላው ቀርቶ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ትራክቶችን ሰጥቻለሁ። ከእነዚያ የእውነት ዘሮች መካከል የጸደቀ ይኖር ይሆን እያልኩ ዛሬም ድረስ አስባለሁ።—1 ቆሮ. 3:6, 7

ይሁን እንጂ አንድ የማልክደው ነገር አለ፤ መጀመሪያ እውነትን በተማርኩበት ጊዜ በተለይም ለቅርብ የቤተሰቤ አባላት ስመሠክር ያን ያህል ዘዴኛ አልነበርኩም። ለይሖዋ ያደረብኝ የመጀመሪያ ፍቅሬ በውስጤ እንደ እሳት ይነድ ስለነበር የምሰብከው በድፍረት ሆኖም ዘዴኛነት በጎደለው መንገድ ነበር። ወንድሞቼን ጆንን እና ሮንን በጣም ስለምወዳቸው እውነትን እንዲቀበሉ ለማስገደድ ሞክሬ ነበር። ለስሜታቸው ሳልጠነቀቅ በመቅረቴ ከጊዜ በኋላ ይቅርታ ጠይቄያቸዋለሁ። ይሁን እንጂ እውነትን እንዲቀበሉ መጸለዬን መቼም ቢሆን አላቋርጥም። ከዚያ ወዲህ ይሖዋ ስላሠለጠነኝ በምሰብክበትና በማስተምርበት ጊዜ ይበልጥ ዘዴኛ ሆኛለሁ።—ቆላ. 4:6

 ሌላም ፍቅር

ለይሖዋ ያደረብኝ የመጀመሪያ ፍቅር እንዳለ ሆኖ የምወዳቸውን ሰዎችም ሳልጠቅስ ማለፍ አልፈልግም። ከይሖዋ ቀጥሎ የምወዳት ውዷ ባለቤቴ ሱዛን ናት። በመንግሥቱ ሥራ ስካፈል የምታግዘኝ አጋር እንደምታስፈልገኝ ይሰማኝ ነበር። ሱዛን ጠንካራና መንፈሳዊ የሆነች ሴት ናት። እየተጠናናን እያለ አንድ ቀን ልጠይቃት ቤቷ ስሄድ ያጋጠመኝን መቼም አልረሳውም። ሱዛን በክራንስተን፣ ሮድ አይላንድ በሚገኘው የወላጆቿ ቤት በረንዳ ላይ ተቀምጣ መጠበቂያ ግንብ ከመጽሐፍ ቅዱሷ ጋር በማጣቀስ እያነበበች ነበር። በጣም ያስደነቀኝ ነገር የምታነበው የጥናት ርዕሶቹን ባይሆንም ከጥቅሶቹ ጋር እያመሳከረች ማጥናቷ ነው። ‘በእርግጥም መንፈሳዊ ሴት ናት!’ ብዬ አሰብኩ። ታኅሣሥ 1971 የተጋባን ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከጎኔ ሆና ስትደግፈኝ በመኖሯ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ስለ እሷ በጣም የማደንቀው ነገር፣ እኔን የምትወደኝ ቢሆንም አብልጣ የምትወደው ግን ይሖዋን መሆኑን ነው።

ከባለቤቴ ከሱዛን እንዲሁም ከልጆቻችን ከፖልና ከጄሲ ጋር

እኔና ሱዛን፣ ጄሲ እና ፖል የሚባሉ ሁለት ወንዶች ልጆች በመውለድ ተባርከናል። ልጆቻችን እያደጉ ሲሄዱ ይሖዋ ከእነሱ ጋር ነበር። (1 ሳሙ. 3:19) እውነትን የራሳቸው በማድረጋቸው እኔንና ሱዛንን አስከብረውናል። እነሱም ለይሖዋ ያደረባቸውን የመጀመሪያ ፍቅር ስላልረሱ እሱን ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። እያንዳንዳቸው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ አሳልፈዋል። በተጨማሪም ልጆቼ ባገቧቸው ስቴፋኒና ራኬል የተባሉ ውብ እህቶች ኩራት ይሰማኛል፤ የልጆቼን ሚስቶች የማያቸው እንደ ራሴ ልጆች አድርጌ  ነው። ሁለቱም ልጆቼ ያገቡት ይሖዋን በፍጹም ልባቸውና ነፍሳቸው የሚወዱ መንፈሳዊ ሴቶችን ነው።—ኤፌ. 6:6

በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ባገለገልኩበት ወቅት የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ስመራ

ከተጠመቅሁ በኋላ በሮድ አይላንድ ለ16 ዓመታት ያገለገልኩ ሲሆን በዚያም ጥሩ ወዳጆችን አፍርቻለሁ። አብሬያቸው ስላገለገልኳቸው ግሩም ሽማግሌዎች በጣም ብዙ አስደሳች ትዝታዎች አሉኝ። በተጨማሪም በጎ ተጽዕኖ ላሳደሩብኝ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች እጅግ አመስጋኝ ነኝ፤ እነዚህ ወንድሞች በጣም ብዙ ስለሆኑ በስም መጥቀስ አልችልም። ለይሖዋ ያደረባቸውን የመጀመሪያ ፍቅር ጠብቀው ከኖሩ ወንድሞች ጋር አብሮ መሥራት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! በ1987 የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ያስፈልጉ ወደነበረበት ወደ ኖርዝ ካሮላይና ተዛወርን፤ እዚያም ሌሎች ወዳጆችን አፍርተናል። *

እምብዛም ባልተሠራባቸው ክልሎች በቤተሰብ ሆነን መስበክ ያስደስተን ነበር

ነሐሴ 2002 እኔና ሱዛን በዩናይትድ ስቴትስ ያለው የፓተርሰን ቤቴል ቤተሰብ አባላት እንድንሆን የቀረበልንን ግብዣ ተቀበልን። እዚያም እኔ በአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ የሠራሁ ሲሆን ሱዛን ደግሞ በልብስ ንጽሕና መስጫ ክፍል ሠርታለች። ሱዛን የተመደበችበትን ሥራ ትወደው ነበር! ከዚያም ነሐሴ 2005 የበላይ አካሉ አባል ሆኜ የማገልገል መብት አገኘሁ። ይህ ኃላፊነት ለእኔ እንደሚገባኝ ሆኖ አልተሰማኝም። ውዷ ባለቤቴም ይህ መብት የሚያስከትለው ኃላፊነትና ሥራው እንዲሁም ወደተለያዩ ቦታዎች መጓዝ ከአቅሟ በላይ እንደሆነ ተሰምቷት ነበር። ሱዛን በአውሮፕላን መጓዝ የሚጨንቃት ቢሆንም ብዙ ጊዜ ይህን እናደርጋለን። ሱዛን፣ የሌሎቹ የበላይ አካል አባላት ሚስቶች ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ የሰጧት አስተያየት እኔን ለመደገፍ የተቻላትን ሁሉ ለማድረግ እንደረዳት ትናገራለች። በእርግጥም ድጋፏ አልተለየኝም፤ ይህም ይበልጥ እንድወዳት አድርጎኛል።

በቢሮዬ ውስጥ ለእኔ በጣም ትልቅ ትርጉም ያላቸው ብዙ ፎቶግራፎች አሉኝ! ፎቶግራፎቹ ያሳለፍኩትን እጅግ አስደሳች ሕይወት ያስታውሱኛል። ለይሖዋ ያዳበርኩትን የመጀመሪያ ፍቅር ለማስታወስ የቻልኩትን ሁሉ በማድረጌ እስካሁን እንኳ ብዙ ግሩም በረከቶችን አግኝቻለሁ!

ከቤተሰቤ ጋር ጊዜ ማሳለፍ በጣም ያስደስተኛል

^ አን.31 ወንድም ሞሪስ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ስላሳለፈው ሕይወት የሚገልጽ ተጨማሪ መረጃ በመጋቢት 15, 2006 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 26 ላይ ማግኘት ይቻላል።