ሁሊያን የተባለ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ልጄ መወገዱን የሚገልጽ ማስታወቂያ ስሰማ ሰማይ ምድሩ ተደበላለቀብኝ። የመጀመሪያ ልጄ በመሆኑ በጣም እንቀራረብ ነበር፤ አብረን ብዙ ነገሮችን አድርገናል። በሁሉ ነገር ምሳሌ የሚሆን ልጅ ነበር፤ ይሁንና በድንገት መጥፎ ባሕርይ ማሳየት ጀመረ። ባለቤቴ ዘወትር ታለቅስ ነበር፤ እንዴት ብዬ እንደማጽናናት ግራ ገብቶኝ ነበር። ‘የወላጅነት ኃላፊነታችንን ሳንወጣ ቀርተን ይሆን’ የሚለው ጉዳይ ዘወትር ያስጨንቀን ነበር።”

አንድን ክርስቲያን ማስወገድ ይህን ያህል ስሜታዊ ሥቃይ የሚፈጥር ሆኖ ሳለ ውገዳ ፍቅራዊ ዝግጅት ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? እንዲህ ያለ ከባድ እርምጃ ለመውሰድ መሠረት የሚሆን ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አለ? አንድ ሰው እንዲወገድ የሚያደርገው ምንድን ነው?

ለውገዳ የሚያደርሱ ሁለት ነገሮች

አንድ የይሖዋ ምሥክር የሚወገደው ሁለት ነገሮች ተከታትለው ሲፈጸሙ ነው። የመጀመሪያው አንድ የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር ከባድ ኃጢአት መፈጸሙ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለሠራው ኃጢአት ንስሐ አለመግባቱ ነው።

ይሖዋ ፍጹም እንድንሆን ባይጠብቅም አገልጋዮቹ እንዲያሟሉ የሚፈልግባቸው የቅድስና ደረጃ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ሴሰኛ፣ ጣዖት አምላኪ፣ ሌባ፣ ቀማኛ፣ ነፍሰ ገዳይ እንዳንሆን ወይም መናፍስታዊ ድርጊት እንዳንፈጽም ይሖዋ አዞናል።—1 ቆሮ. 6:9, 10፤ ራእይ 21:8

ይሖዋ ያወጣቸው የቅድስና መሥፈርቶች ምክንያታዊና ለእኛው ጥቅም ሲባል የተሰጡ እንደሆኑ ይሰማሃል? እምነት የሚጣልባቸው፣ ሰላማዊና ጨዋ ከሆኑ ሰዎች ጋር አብሮ መኖር የማይፈልግ ማን አለ? በመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መካከል እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሊፈጠር የቻለው ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን በቃሉ ውስጥ ከሚገኙ መመሪያዎች ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ቃል ስለገባን ነው።

ይሁንና አንድ የተጠመቀ ክርስቲያን በሰብዓዊ ድክመት የተነሳ ከባድ ኃጢአት ቢፈጽምስ? በጥንት ጊዜ የነበሩ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲህ ያለ ስህተት የሠሩበት ወቅት ነበር፤ ያም ቢሆን አምላክ ሙሉ በሙሉ አልተዋቸውም። በዚህ ረገድ ንጉሥ ዳዊት ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። ዳዊት ምንዝር ከመፈጸሙም ሌላ ነፍስ አጥፍቷል፤ ያም ቢሆን ‘ይሖዋ ኃጢአቱን ይቅር’ እንዳለው ነቢዩ ናታን ነግሮታል።—2 ሳሙ. 12:13

ዳዊት ልባዊ ንስሐ በመግባቱ አምላክ ኃጢአቱን ይቅር ብሎታል። (መዝ. 32:1-5) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የሚገኝ አንድ የይሖዋ አገልጋይ የሚወገደው ንስሐ ካልገባ ወይም መጥፎ ድርጊት መፈጸሙን ከቀጠለ ብቻ ነው። (ሥራ 3:19፤ 26:20) በፍርድ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግሉት ሽማግሌዎች ግለሰቡ ልባዊ ንስሐ መግባቱን ካላሳየ ሊያስወግዱት ይገባል።

አንድ ሰው ሲወገድ በተለይ ከግለሰቡ ጋር በጣም የምንቀራረብ ከሆነ መጀመሪያ ላይ፣ እርምጃው ተመጣጣኝ እንዳልሆነ አልፎ ተርፎም ደግነት የጎደለው እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። ያም ቢሆን የይሖዋ ቃል እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ ፍቅር  የሚንጸባረቅበት መሆኑን አምነን እንድንቀበል የሚያደርግ አጥጋቢ ምክንያት ይሰጠናል።

ውገዳ ምን ጥቅሞች አሉት?

ኢየሱስ “ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በውጤቷ ተረጋግጧል” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 11:19 የግርጌ ማስታወሻ) ንስሐ ያልገባን ኃጢአተኛ በማስወገድ የጥበብ እርምጃ መውሰድ ጽድቅ የሚንጸባረቅበት ውጤት ያስገኛል። እስቲ የሚከተሉትን ሦስት ጥቅሞች እንመልከት፦

ኃጢአት የፈጸመውን ግለሰብ ማስወገድ የይሖዋን ስም ያስከብራል። በይሖዋ ስም የምንጠራ እንደመሆናችን መጠን ምግባራችን ስሙ በጥሩ ወይም በመጥፎ እንዲነሳ ማድረጉ አይቀርም። (ኢሳ. 43:10) አንድ ልጅ የሚያደርገው ነገር ወላጆቹን ሊያስከብር ወይም ሊያሰድብ እንደሚችል ሁሉ በስሙ የሚጠሩ ሕዝቦቹም የሚያደርጉት ነገር ይሖዋን ሊያስመሰግን ወይም ሊያስነቅፍ ይችላል። በይሖዋ ስም የሚጠሩት ሕዝቦች እሱ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የሚከተሉ ከሆነ የአምላክ ስም ይከበራል። በሕዝቅኤል ዘመን የነበረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፤ በዚያን ጊዜ የአይሁድ ሕዝብ ባደረጉት ነገር የአምላክ ስም በዙሪያቸው በነበሩት ብሔራት ዘንድ ተሰድቧል።—ሕዝ. 36:19-23

ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት የምንፈጽም ከሆነ የአምላክን ቅዱስ ስም እናሰድባለን። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለክርስቲያኖች እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል፦ “ታዛዥ ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን ቀድሞ እውቀት ባልነበራችሁ ጊዜ ትከተሉት በነበረው ምኞት መሠረት መቀረጻችሁን አቁሙ፤ ከዚህ ይልቅ የጠራችሁ ቅዱስ አምላክ፣ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እናንተም በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ ‘እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ’ ተብሎ ተጽፏልና።” (1 ጴጥ. 1:14-16) ምግባራችን ንጹሕና ቅዱስ መሆኑ የአምላክን ስም ያስከብራል።

አንድ የይሖዋ ምሥክር መጥፎ ድርጊት ከፈጸመ ወንድሞችም ሆኑ እሱን የሚያውቁ ሌሎች ሰዎች ጉዳዩን ማወቃቸው አይቀርም። ውገዳ የይሖዋ ሕዝቦች የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በጥብቅ በመከተል ንጽሕናቸው የሚጠብቁ መሆናቸውን ያሳያል። በስዊዘርላንድ ውስጥ አንድ ሰው በመንግሥት አዳራሽ ወደሚካሄድ አንድ ስብሰባ መጥቶ የጉባኤው አባል መሆን እንደሚፈልግ ተናገረ። የዚህ ግለሰብ እህት ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት በመፈጸሟ ተወግዳ ነበር። በመሆኑም ሰውየው “መጥፎ ድርጊት ሲፈጸም በቸልታ የማያልፈው” ድርጅት አባል መሆን ፈልጎ ነበር።

ውገዳ የጉባኤው ንጽሕና እንዲጠበቅ ያደርጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሆን ብሎ ኃጢአት የሚሠራ ሰው በመካከላቸው እንዲኖር መፍቀዳቸው አደጋ እንዳለው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን አስጠንቅቋቸው ነበር። እንዲህ ያሉ ሰዎች የሚያሳድሩትን መጥፎ ተጽዕኖ ሊጥ እንዲቦካ ከሚያደርገው እርሾ ጋር በማነጻጸር “ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንደሚያቦካው አታውቁም?” ብሏል። ከዚያም “ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱት” ብሏቸዋል።—1 ቆሮ. 5:6, 11-13

ጳውሎስ የጠቀሰው ‘ክፉ ሰው’ ዓይን ያወጣ የሥነ ምግባር ብልግና ፈጽሟል። ሌሎች የጉባኤው አባላትም ድርጊቱን በቸልታ አልፈውት ነበር። (1 ቆሮ. 5:1, 2) እንዲህ ያለ ከባድ ኃጢአት በዝምታ ከታለፈ ሌሎች ክርስቲያኖችም በቆሮንቶስ ከተማ ውስጥ የሚታየውን ልቅ ሥነ ምግባር ለመከተል ሊፈተኑ ይችላሉ። ሆን ተብሎ የሚፈጸምን ኃጢአት በቸልታ መመልከት ለአምላክ መሥፈርቶች ልል መሆንን ያበረታታል። (መክ. 8:11) በተጨማሪም ‘በባሕር ውስጥ የተደበቀ ዓለት’ መርከቦችን እንደሚሰባብር ሁሉ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞችም የሌሎቹን የጉባኤ አባላት እምነት ሊያጠፉ ይችላሉ።—ይሁዳ 4, 12

ውገዳ ኃጢአት የሠራው ሰው ወደ ልቡ እንዲመለስ ሊረዳው ይችላል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ የአባቱን ቤት ጥሎ ስለወጣና መረን የለቀቀ ሕይወት በመምራት ገንዘቡን ሁሉ ስላባከነ ወጣት ተናግሯል። አባካኙ ልጅ ከአባቱ ቤት መውጣቱ ምን ያህል ሥቃይ እንዳለው የተረዳው ከደረሰበት መከራ ነው። በመጨረሻም ልጁ ወደ ልቦናው በመመለስ ንስሐ የገባ ከመሆኑም ሌላ በራሱ ተነሳስቶ ወደ ቤተሰቡ ተመልሷል። (ሉቃስ 15:11-24) ልጁ አካሄዱን አስተካክሎ ሲመለስ አፍቃሪ የሆነው አባቱ ደስታውን የገለጸበት መንገድ የይሖዋን ስሜት እንድንረዳ ያስችለናል። ይሖዋ “በክፉው ሰው ሞት ደስ አልሰኝም፤ ይልቁንም ክፉው ሰው አካሄዱን አስተካክሎ በሕይወት እንዲኖር እፈልጋለሁ” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል።—ሕዝ. 33:11

በተመሳሳይም ከመንፈሳዊ ቤተሰባቸው ማለትም ከክርስቲያን ጉባኤ የተወገዱ ሰዎች መወገዳቸው ምን ኪሳራ እንዳስከተለባቸው ሊገነዘቡ ይችላሉ። ኃጢአት መሥራታቸው ያስከተለባቸውን አስከፊ መዘዝ መገንዘባቸው እንዲሁም ከይሖዋ ጋር  የነበራቸውን ዝምድናና ከሕዝቦቹ ጋር ያሳለፉትን ጥሩ ጊዜ ማስታወሳቸው ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ ሊያነሳሳቸው ይችላል።

ጥሩ ውጤት እንዲገኝ ከተፈለገ ፍቅር ማሳየትና ጥብቅ አቋም መያዝ አስፈላጊ ነው። መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “ጻድቅ ቢመታኝ፣ የታማኝ ፍቅር መግለጫ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፤ ቢወቅሰኝ በራስ ላይ እንደሚፈስ ዘይት አድርጌ አየዋለሁ።” (መዝ. 141:5) ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፦ ተራራ ላይ በሚወጣበት ጊዜ በቅዝቃዜው ምክንያት በጣም የተዳከመን አንድ ሰው በዓይነ ሕሊናችን እንመልከት። ይህ ሰው ቅዝቃዜው ሰውነቱን እያደነዘዘው ከመሆኑም ሌላ እንቅልፍ እየተጫጫነው ነው። እንቅልፍ ከወሰደው መሞቱ አይቀርም። በመሆኑም እርዳታ የሚሰጡ ሰዎች እስኪመጡ ድረስ አብሮት ያለው ሰው ግለሰቡን ለማንቃት አልፎ አልፎ በጥፊ ይመታዋል። ጥፊው ሊያመው ቢችልም መመታቱ ሕይወቱን ሊያተርፍለት ይችላል። በተመሳሳይም ዳዊት ሥቃይ ሊያስከትልበት የሚችል ቢሆንም ጻድቅ ሰው የሚሰጠው ተግሣጽ እንደሚጠቅመው ተረድቶ ነበር።

ብዙ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ውገዳ ኃጢአት የፈጸመው ግለሰብ ከስህተቱ እንዲታረም ያደርጋል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው የሁልያን ልጅ ከአሥር ዓመት በኋላ አኗኗሩን በማስተካከል ወደ ጉባኤ ተመልሶ በአሁኑ ጊዜ ሽማግሌ ሆኖ እያገለገለ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “መወገዴ የተከተልኩት ጎዳና ያስከተለብኝን መዘዝ እንድቀምስ አድርጎኛል። እንዲህ ዓይነት ተግሣጽ ያስፈልገኝ ነበር።”—ዕብ. 12:7-11

ከተወገዱ ግለሰቦች ጋር በተያያዘ ፍቅር ማሳየት

የውገዳ እርምጃ ሐዘን እንደሚያስከትል አይካድም፤ እንዲህ ሲባል ግን የተወገደው ሰው ማንሰራራት አይችልም ማለት አይደለም። የውገዳ እርምጃው ግቡን እንዲመታ ሁላችንም የበኩላችንን ሚና መጫወት ይኖርብናል።

ንስሐ የገቡ ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ ለመርዳት ጥረት ይደረጋል

ሽማግሌዎች የውገዳ ውሳኔ ማስተላለፍ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ የይሖዋን ፍቅር ለማንጸባረቅ ጥረት ማድረግ አለባቸው። ለግለሰቡ ውሳኔውን በሚያሳውቁት ጊዜ ወደ ጉባኤ ለመመለስ ከፈለገ ሊወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎችን በግልጽና በደግነት ሊነግሩት ይገባል። ሽማግሌዎች አኗኗራቸውን የመለወጥ ፍላጎት ያላቸው የተወገዱ ሰዎች ወደ ይሖዋ መመለስ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ለማስታወስ በየተወሰነ ጊዜ ይጎበኟቸዋል። *

የቤተሰብ አባላት የውገዳውን ውሳኔ በማክበር ለጉባኤውና የተሳሳተ ጎዳና ለተከተለው ሰው ፍቅር ማሳየት ይችላሉ። ሁልያን “ልጄ ቢሆንም የተከተለው ጎዳና ግንኙነታችንን ገድቦት ነበር” በማለት ተናግሯል።

ሁሉም የጉባኤው አባላት ከተወገደው ግለሰብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማቋረጥ ፍቅር ማሳየት ይችላሉ። (1 ቆሮ. 5:11፤ 2 ዮሐ. 10, 11) በዚህ መንገድ ይሖዋ በሽማግሌዎች አማካኝነት የሰጠውን ተግሣጽ እንደሚደግፉ ያሳያሉ። በተጨማሪም የተወገደው ሰው ቤተሰቦች ከፍተኛ የስሜት ሥቃይ ሊያድርባቸውና እነሱም ከእምነት ባልንጀሮቻቸው እንደተገለሉ ሆኖ ሊሰማቸው ስለሚችል የጉባኤው አባላት ለቤተሰቡ ከወትሮው የበለጠ ፍቅር ሊያሳዩአቸውና ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል።—ሮም 12:13, 15

በመጨረሻም ሁልያን እንዲህ ብሏል፦ “ውገዳ አንድ ሰው በይሖዋ መመሪያዎች እንዲሄድ የሚያደርግ አስፈላጊ ዝግጅት ነው። ሥቃይ ቢኖረውም ውሎ አድሮ ጥሩ ውጤት ያስገኛል። የልጄን መጥፎ ምግባር በቸልታ ባልፈው ኖሮ በጭራሽ አያገግምም ነበር።”

^ አን.24 የሚያዝያ 15, 1991 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 21-23 ተመልከት።