በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ሚያዝያ 2015

ከይሖዋ ጋር ያለህ ወዳጅነት ምን ያህል ጠንካራ ነው?

ከይሖዋ ጋር ያለህ ወዳጅነት ምን ያህል ጠንካራ ነው?

“ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።”—ያዕ. 4:8

1. ከይሖዋ ጋር ያለንን ግንኙነት ምንጊዜም ማጠናከር የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

ራስህን ወስነህ የተጠመቅህ የይሖዋ ምሥክር ነህ? ከሆነ አንድ ውድ ነገር አለህ፤ ይህም በግለሰብ ደረጃ ከአምላክ ጋር የመሠረትከው ወዳጅነት ነው። ይሁንና የሰይጣን ዓለም ብቻ ሳይሆን ፍጹም ያልሆነው ሥጋችንም በዚህ ወዳጅነት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። እንዲህ ያለው ፈታኝ ሁኔታ የሚያጋጥማቸው ሁሉም ክርስቲያኖች ናቸው። እንግዲያው ከይሖዋ ጋር ያለን ግንኙነት በተቻለ መጠን ጠንካራ መሆን አለበት።

2. (ሀ) ግንኙነት ሲባል ምን ያመለከታል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።) (ለ) ከይሖዋ ጋር ያለንን ግንኙነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?

2 አንተስ ከይሖዋ ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ያህል ጠንካራ ነው? ይበልጥ ልታጠናክረው ትፈልጋለህ? ያዕቆብ 4:8 ይህን ማድረግ የምትችልበትን መንገድ ሲገልጽ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” ይላል። ይህ ጥቅስ ከሁለቱም ወገኖች የሚጠበቅ ነገር መኖሩን እንደሚጠቁም ልብ በል። * ወደ አምላክ ለመቅረብ እርምጃ ስንወስድ እሱም በበኩሉ ወደ እኛ ይቀርባል። እንዲህ ያለውን እርምጃ በተደጋጋሚ ስንወስድ ይሖዋ ይበልጥ እውን ይሆንልናል፤ ከእሱ ጋር ያለን ግንኙነትም የበለጠ እየተጠናከረ  ስለሚሄድ ኢየሱስ “የላከኝ በእውን ያለ ነው፤ . . . አውቀዋለሁ” ብሎ ሲናገር የነበረው ዓይነት የመተማመን ስሜት ይኖረናል። (ዮሐ. 7:28, 29) ይሁን እንጂ ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ ትችላለህ?

ከአምላክ ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 3ን ተመልከት)

3. ከይሖዋ ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

3 ወደ ይሖዋ ለመቅረብ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ከእሱ ጋር አዘውትረን የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ነው። ለመሆኑ ከአምላክ ጋር መነጋገር የምትችለው እንዴት ነው? ከአንተ ርቆ ከሚኖር ወዳጅህ ጋር የሐሳብ ልውውጥ የምታደርገው እንዴት ነው? አዘውትራችሁ እንደምትጻጻፉ እንዲሁም ስልክ እንደምትደዋወሉ የታወቀ ነው። ይሖዋን የምታነጋግረውም ወደ እሱ አዘውትረህ በመጸለይ ነው። (መዝሙር 142:2ን አንብብ።) በተጨማሪም በጽሑፍ የሰፈረውን የአምላክ ቃል ዘወትር በማንበብና ባነበብከው ላይ በማሰላሰል ይሖዋ ሲያነጋግርህ ማዳመጥ ትችላለህ። (ኢሳይያስ 30:20, 21ን አንብብ።) በእኛና በይሖዋ መካከል እንዲህ ያለ የሐሳብ ልውውጥ መኖሩ ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና የሚያጠናክረውና እሱ እውነተኛ ወዳጃችን እንዲሆን የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት—ይሖዋ አንተን የሚያነጋግርበት መንገድ

4, 5. ይሖዋ በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ አማካኝነት በግለሰብ ደረጃ የሚያነጋግርህ እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

4 መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ለመላው የሰው ዘር የላከውን መልእክት የያዘ መሆኑን እንደምታምን ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንተ በግልህ ወደ ይሖዋ እንዴት መቅረብ እንደምትችል የሚገልጽ ሐሳብስ ይዟል? በሚገባ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ ስታነብና ስታጠና፣ ለመልእክቱ ምን ምላሽ እንደምትሰጥና እንዴት ተግባራዊ እንደምታደርገው ቆም ብለህ አስብ፤ ይህን ማድረግህ ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት እንዲያነጋግርህ እንደፈቀድክ ያሳያል። ይህ ደግሞ ከእሱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖርህ ያደርጋል።—ዕብ. 4:12፤ ያዕ. 1:23-25

5 ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ “በምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ” በማለት የሰጠውን ምክር ካነበብክ በኋላ አሰላስልበት። አሁንም ቢሆን ሕይወትህ ከአምላክ መንግሥት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ከሆነ ይሖዋ እንደሚደሰትብህ ይሰማሃል። በሌላ በኩል ግን ሕይወትህን ቀላል ማድረግና ከመንግሥቱ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ይበልጥ ማተኮር እንደሚያስፈልግህ ከተሰማህ፣ ይሖዋ ወደ እሱ መቅረብ እንድትችል በግለሰብ ደረጃ ልትሠራበት የሚገባውን ነገር እንደጠቆመህ አድርገህ ልትወስደው ይገባል።—ማቴ. 6:19, 20

6, 7. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን እኛ ለይሖዋ ባለን ፍቅር እንዲሁም እሱ ለእኛ ባለው ፍቅር ረገድ ምን ለውጥ ያመጣል? (ለ) የግል ጥናት ስናደርግ ዓላማችን ምን መሆን አለበት?

6 ቅዱሳን መጻሕፍትን ማጥናታችን መንፈሳዊነታችንን ለማሻሻል የሚረዱንን ነገሮች ከመጠቆም  ባለፈ ሌላም ጥቅም አለው። ተወዳጅ ስለሆኑት የይሖዋ ባሕርያት ያለን አድናቆት እንዲጨምር የሚረዳን ሲሆን ይህም እሱን ይበልጥ እንድንወደው ያደርጋል። ለአምላክ ያለን ፍቅር እየጨመረ ሲሄድ ደግሞ እሱም በምላሹ ይበልጥ ይወድደናል፤ ይህም ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና ያጠናክረዋል።1 ቆሮንቶስ 8:3ን አንብብ።

7 ይሁንና ወደ ይሖዋ ለመቅረብ በትክክለኛ ዓላማ ተነሳስተን ማጥናታችን አስፈላጊ ነው። ዮሐንስ 17:3 “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው” ይላል። እንግዲያው የምናጠናው፣ እውቀት ለመቅሰም ብቻ ሳይሆን የይሖዋን ማንነት በተሻለ መንገድ ‘ለማወቅ’ ሊሆን ይገባል።ዘፀአት 33:13ን አንብብ፤ መዝ. 25:4

8. (ሀ) በ2 ነገሥት 15:1-5 ላይ ይሖዋ ከንጉሥ አዛርያስ ጋር በተያያዘ ስለወሰደው እርምጃ ምን ጥያቄ ይነሳል? (ለ) ይሖዋን ማወቃችን እሱ ስለወሰዳቸው እርምጃዎች ትክክለኛነት ጥርጣሬ እንዳያድርብን የሚረዳን እንዴት ነው?

8 ይሖዋን ይበልጥ እያወቅነው መሄዳችን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ዘገባዎችን ስናነብ ይሖዋ አንድ እርምጃ የወሰደበትን ምክንያት መረዳት ባንችል እንኳ ነገሩ ከሚገባ በላይ እንዳያስጨንቀን ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ የይሁዳ ንጉሥ ከሆነው ከአዛርያስ ጋር በተያያዘ ስለወሰደው እርምጃ ስታነብ ምን ይሰማሃል? (2 ነገ. 15:1-5) “ሕዝቡ . . . ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ላይ ይሠዋ እንዲሁም የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ” የነበረ ቢሆንም አዛርያስ “በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር” እንዳደረገ ልብ በል። ያም ሆኖ “ይሖዋ ንጉሡን ቀሰፈው፤ እስከ ዕለተ ሞቱም ድረስ የሥጋ ደዌ በሽተኛ ሆኖ ኖረ።” ይሖዋ እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? ይህ ዘገባ ምንም ፍንጭ አይሰጠንም። ታዲያ ይህ ሊረብሸን ይገባል? አሊያም ይሖዋ፣ አዛርያስን የቀጣው ያለ ምንም ምክንያት እንደሆነ ማሰብ ይኖርብናል? ይሖዋ ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድ በደንብ የምናውቅ ከሆነ እንዲህ አይሰማንም። ምክንያቱም ይሖዋን ማወቅ እሱ ምንጊዜም ተግሣጽ የሚሰጠው “በተገቢው መጠን” እንደሆነ መገንዘብንም ይጨምራል። (ኤር. 30:11) እንዲህ ያለው እውቀት፣ ይሖዋ በአዛርያስ ላይ ይህን እርምጃ የወሰደው ለምን እንደሆነ ባናውቅም እንኳ ፍርዱ ጽድቅ የሚንጸባረቅበት መሆኑን እንድንተማመን ያደርገናል።

9. ይሖዋ፣ አዛርያስን በሥጋ ደዌ በሽታ የቀሰፈው ለምን እንደሆነ ፍንጭ የሚሰጠን ምንድን ነው?

9 እርግጥ ነው፣ ከዚህ ታሪክ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ዝርዝር ሐሳብ በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ እናገኛለን። ንጉሥ አዛርያስ፣ ንጉሥ ዖዝያ ተብሎም ተጠርቷል። (2 ነገ. 15:7, 32) በ2 ዜና መዋዕል 26:3-5, 16-21 ላይ የሚገኘው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ዘገባ እንደሚገልጸው ዖዝያ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ለተወሰነ ጊዜ አድርጓል፤ ከጊዜ በኋላ ግን “ለጥፋት እስኪዳረግ ድረስ ልቡ ታበየ።” ከቦታው በማለፍ በትዕቢት ተነሳስቶ የክህነት አገልግሎት ለማከናወን ሞከረ። ሰማንያ አንድ ካህናት ዖዝያን ፊት ለፊት በመጋፈጥ እርማት ሰጡት። ታዲያ ዖዝያ ምን ምላሽ ሰጠ? በወቅቱ ያደረገው ነገር ምን ያህል እንደታበየ የሚያሳይ ነው። ዘገባው እንደሚገልጸው ዖዝያ በካህናቱ ላይ “እጅግ ተቆጣ።” በእርግጥም ይሖዋ፣ በሥጋ ደዌ በሽታ የቀሰፈው መሆኑ ምንም አያስገርምም!

10. ይሖዋ ለሚያደርገው ለእያንዳንዱ ነገር ሁልጊዜ ማብራሪያ የማያስፈልገን ለምንድን ነው? የይሖዋ መንገድ ጽድቅ የሚንጸባረቅበት እንደሆነ ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?

10 ነጥቡ ምንድን ነው? ከአንዳንድ አጫጭር የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ጋር በተያያዘ እንደሚያጋጥመን ሁሉ በዚህ ታሪክ ረገድም ነጥቡን ግልጽ የሚያደርግ ተጨማሪ ሐሳብ በአምላክ ቃል ውስጥ ባይካተት ኖሮ ምን ይሰማህ ነበር? የአምላክን ጽድቅ ትጠራጠር ነበር? ወይስ ይሖዋ ምንጊዜም ትክክል የሆነውን እንደሚያደርግ እንዲያውም ትክክል ወይም ስህተት ለሆነው ነገር መመዘኛው እሱ እንደሆነ የሚያረጋግጥልን በቂ መረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሚገኝ ይሰማህ ነበር? (ዘዳ. 32:4) የይሖዋን ማንነት ይበልጥ እያወቅን ስንሄድ ለእሱ ያለን ፍቅርና ነገሮችን ለሚያከናውንበት መንገድ ያለን አድናቆት ስለሚጨምር እሱ ለሚያደርገው  ለእያንዳንዱ ነገር ማብራሪያ አያስፈልገንም። አምላክ በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ በኩል የሚነግርህን ነገር ባጠናህና በዚያ ላይ ባሰላሰልክ መጠን አድናቆትህም የዚያኑ ያህል እንደሚጨምር እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (መዝ. 77:12, 13) ይህ ደግሞ ይሖዋ ይበልጥ እውን እንዲሆንልህ የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ወደ እሱ የበለጠ ትቀርባለህ።

መጸለይ—ይሖዋን የምታነጋግርበት መንገድ

11-13. ይሖዋ ጸሎትህን እንደሚሰማ እርግጠኛ የሆንከው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

11 ስንጸልይ ወደ ይሖዋ እንቀርባለን። በጸሎት አማካኝነት እናወድሰዋለን፣ እናመሰግነዋለን እንዲሁም መመሪያ እንዲሰጠን እንጠይቀዋለን። (መዝ. 32:8) ይሁንና ከይሖዋ ጋር ያለህ ግንኙነት ጠንካራ መሆን እንዲችል ስትጸልይ እንደሚሰማህ እርግጠኛ መሆን አለብህ።

12 አንዳንዶች ጸሎት አእምሮን ከማረጋጋት ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው ይሰማቸዋል። ጸሎታችን መልስ እንዳገኘ የምናስበው ሐሳባችንን አውጥተን ስለተናገርን፣ ችግራችንን ለይተን ስላወቅንና አእምሯችን መፍትሔ በማግኘት ላይ ትኩረት ስላደረገ እንደሆነ ይናገራሉ። ጸሎት እንዲህ ያለ ጥቅም እንዳለው ባይካድም ይሖዋ ከልብህ የምታቀርበውን ጸሎት እንደሚሰማ እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

13 እስቲ ይህን አስብ፦ ይሖዋ ሰብዓዊ አገልጋዮቹ የሚያቀርቡለትን ጸሎት ሲመልስ ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ተመልክቷል። እሱም በምድር ላይ አገልግሎቱን ሲያከናውን በሰማይ ላለው አባቱ ስሜቱን አውጥቶ ለመግለጽ በጸሎት ተጠቅሟል። እንዲያውም በአንድ ወቅት ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ አድሯል፤ ታዲያ ኢየሱስ፣ ይሖዋ እንደሚሰማው እርግጠኛ ባይሆን ኖሮ እንዲህ ያደርግ ነበር? (ሉቃስ 6:12፤ 22:40-46) ጸሎት አእምሮን ከማረጋጋት ያለፈ ጥቅም እንደሌለው ቢሰማው ኖሮ ደቀ መዛሙርቱን እንዲጸልዩ ያስተምራቸው ነበር? ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ጸሎት፣ ከይሖዋ ጋር የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችል መንገድ እንደሆነ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። በአንድ ወቅት ኢየሱስ “አባት ሆይ፣ ስለሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። እውነት ነው፣ ሁልጊዜ እንደምትሰማኝ አውቃለሁ” በማለት ጸልዮአል። እኛም ይሖዋ “ጸሎት ሰሚ” አምላክ እንደሆነ መተማመን እንችላለን።—ዮሐ. 11:41, 42፤ መዝ. 65:2

14, 15. (ሀ) ስንጸልይ የምንፈልገውን ነገር ለይተን መጥቀሳችን ምን ጥቅም ያስገኛል? (ለ) አንዲት እህት ከይሖዋ ጋር ያላትን ዝምድና እንድታጠናክር ጸሎት የረዳት እንዴት ነው?

14 ስትጸልይ የምትፈልገውን ነገር ለይተህ የምትጠቅስ ከሆነ ይሖዋ የሚሰጥህ ምላሽ በግልጽ  የሚታይ ባይሆንም እንኳ አንተ ለጸሎትህ መልስ እንዳገኘህ በቀላሉ ታስተውላለህ። ጸሎትህ ምላሽ ማግኘቱ ደግሞ ይሖዋ ይበልጥ እውን እንዲሆንልህ ያደርጋል። በተጨማሪም የሚያሳስቡህን ነገሮች ለይሖዋ ግልጥልጥ አድርገህ በነገርከው መጠን እሱ ወደ አንተ ይበልጥ እየቀረበ ይሄዳል።

15 እስቲ የካቲን ምሳሌ እንመልከት። * ካቲ በመስክ አገልግሎት አዘውትራ ብትሳተፍም አገልግሎት አትወድም ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “የመስክ አገልግሎት አያስደስተኝም ነበር። ፈጽሞ አልወደውም ነበር። ጡረታ ስወጣ አንድ ሽማግሌ የዘወትር አቅኚ ልሆን እንደምችል ጠቆመኝ፤ እንዲያውም የአቅኚነት ማመልከቻ ቅጽ ሰጠኝ። እኔም አቅኚ ለመሆን ወሰንኩ፤ ሆኖም ይሖዋ አገልግሎቱን እንድወድ እንዲረዳኝ በየዕለቱ እጸልይ ጀመር።” ታዲያ ይሖዋ ጸሎቷን መለሰላት? እንዲህ ብላለች፦ “አቅኚነት ከጀመርኩ ሦስተኛ ዓመቴን ይዣለሁ። በአገልግሎት ረጅም ሰዓት ስለማሳልፍ እንዲሁም ከሌሎች እህቶች ለመማር ስለምጥር የመስበክ ችሎታዬን ቀስ በቀስ ማሻሻል ችያለሁ። አሁን በአገልግሎት ከመደሰትም አልፌ በጣም እወደዋለሁ። ከዚህም በላይ ከይሖዋ ጋር ያለኝ ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሯል።” በእርግጥም ጸሎት ካቲ ከይሖዋ ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታጠናክር ረድቷታል።

የበኩላችንን ማድረግ

16, 17. (ሀ) ከይሖዋ ጋር ያለን ግንኙነት ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ስለ የትኛው ተፈታታኝ ሁኔታ እንመረምራለን?

16 ከይሖዋ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዲኖረን የምናደርገው ጥረት በሕይወታችን ሙሉ የሚቀጥል ነው። ይሖዋ ወደ እኛ እንዲቀርብ የምንፈልግ ከሆነ እኛም ወደ እሱ ለመቅረብ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። እንግዲያው በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና በጸሎት አማካኝነት ከአምላካችን ጋር አዘውትረን የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋችንን እንቀጥል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ከይሖዋ ጋር ያለን ግንኙነት እየተጠናከረ ስለሚሄድ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ለመወጣት ያስችለናል።

ከይሖዋ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዲኖረን የምናደርገው ጥረት በሕይወታችን ሙሉ የሚቀጥል ነው (አንቀጽ 16, 17ን ተመልከት)

17 ይሁንና ስላጋጠሙን ችግሮች አጥብቀን ብንጸልይም እንኳ ችግሮቹ ካልተወገዱ ይህ በራሱ ፈተና ሊሆንብን ይችላል። በዚህ ጊዜ በይሖዋ ላይ ያለን የመተማመን ስሜት ሊፈተን ይችላል። ይሖዋ በእርግጥ ጸሎታችንን ይሰማን እንደሆነ አልፎ ተርፎም እኛን እንደ ወዳጆቹ አድርጎ የሚመለከተን መሆኑን መጠራጠር እንጀምር ይሆናል። ታዲያ በዚህ ጊዜ ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ዝምድና እንዳለን መተማመንና ያጋጠሙንን ችግሮች መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይህ ጉዳይ ይብራራል።

^ አን.2 ወዳጅነት በሁለት ሰዎች መካከል ያለውን መቀራረብ ያመለክታል። በመሆኑም ወዳጅነቱን ለማጠናከር ሁለቱም የሚጫወቱት ሚና አለ።

^ አን.15 ስሟ ተቀይሯል።