በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 የሕይወት ታሪክ

“አመቺ በሆነ ጊዜም ሆነ በአስቸጋሪ ጊዜ” ያገኘናቸው በረከቶች

“አመቺ በሆነ ጊዜም ሆነ በአስቸጋሪ ጊዜ” ያገኘናቸው በረከቶች

ይሖዋን በታማኝነት በሚያገለግሉ ወዳጅ ዘመዶች መሃል መጋቢት 1930 ተወለድሁ። ያደግኩት ናምኩምባ በሚባል መንደር ነው፤ ይህ መንደር የሚገኘው በአሁኗ ማላዊ ውስጥ ባለው በሊሎንግዌ ከተማ አቅራቢያ ነው። በ1942 ሕይወቴን ለአምላክ ወስኜ ውብ ከሆኑት ወንዞቻችን በአንዱ ውስጥ ተጠመቅሁ። በቀጣዮቹ 70 ዓመታት፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠውን “ቃሉን ስበክ፤ አመቺ በሆነ ጊዜም ሆነ በአስቸጋሪ ጊዜ በጥድፊያ ስሜት አገልግል” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ጥሬያለሁ።—2 ጢሞ. 4:2

በ1948 መጀመሪያ ላይ ናታን ኖር እና ሚልተን ሄንሸል ማላዊ መጥተው ያደረጉልን የመጀመሪያ ጉብኝት ይሖዋን በሙሉ ጊዜ የማገልገል ፍላጎት እንዲያድርብኝ አደረገ። ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ተወካዮች የሆኑት እነዚያ ወንድሞች የሰጡንን ፍቅራዊ ማበረታቻ አሁንም ድረስ አስታውሰዋለሁ። ወደ 6,000 ገደማ የምንሆን የይሖዋ ምሥክሮች ጭቃ በሆነ ሜዳ ላይ ቆመን “የሁሉም ብሔራት ዘላለማዊ ገዢ” በሚል ርዕስ ወንድም ኖር የሰጠውን የሚያበረታታ ንግግር በትኩረት አዳመጥን።

ከዚያም እንደ እኔው በይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ሊዳሲ የምትባል ደስ የምትል እህት ጋር ተዋወቅኩ፤ እሷም የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ግብ እንዳላት ተረዳሁ። በ1950 የተጋባን ሲሆን በ1953 ሁለት ልጆች ወልደን ነበር። እነሱን የማሳደግ ተጨማሪ ኃላፊነት ቢኖርብንም እንኳ እኔ የዘወትር አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ወሰንን። ከሁለት ዓመታት በኋላ በልዩ አቅኚነት እንዳገለግል ተጋበዝሁ።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ጉባኤዎችን የመጎብኘት መብት አገኘሁ። ሊዳሲ ጥሩ ድጋፍ ትሰጠኝ ስለነበር ይህን ኃላፊነት እየተወጣሁ ቤተሰባችንን በቁሳዊም ሆነ በመንፈሳዊ መንከባከብ ችያለሁ። * ይሁን እንጂ የሁለታችንም ልባዊ ምኞት አብረን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ነበር። በጥንቃቄ ዕቅድ በማውጣታችንና አምስቱ ልጆቻችንም በመተባበራቸው ሊዳሲ በ1960 በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመረች።

በተለያዩ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በዚያ አመቺ ወቅት ማገልገል በመቻላችን ተደስተናል። በስተ ደቡብ ከሚገኙት ውብ የሆኑ የሙላንዬ ተራሮች አንስተን በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ሙሉ በሙሉ ተንሰራፍቶ በሚገኘው የማላዊ ሐይቅ ዳርቻ ላይ እስከሚገኙት ጸጥታ የሰፈነባቸው አካባቢዎች ድረስ እየተዘዋወርን አገልግለናል። ባገለገልንባቸው ወረዳዎች ውስጥ በአስፋፊዎችና በጉባኤዎች ቁጥር ረገድ ቀጣይ የሆነ ጭማሪ አይተናል።

በ1962 “ደፋር አገልጋዮች” በሚል ጭብጥ አስደሳች የአውራጃ ስብሰባ አድርገናል። ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስበው እንዲህ  ዓይነቶቹ መንፈሳዊ ድግሶች በማላዊ የነበርነውን የይሖዋ ሕዝቦች ከዚያ በኋላ ለሚመጣው አስቸጋሪ ጊዜ አዘጋጅተውናል። በቀጣዩ ዓመት ወንድም ሄንሸል ማላዊን በድጋሚ የጎበኘ ሲሆን ከብላንቲር ከተማ ውጭ በተደረገው ልዩ የአውራጃ ስብሰባ ላይ 10,000 የሚያህሉ ሰዎች ተገኝተው ነበር። ያ አበረታች ስብሰባ ከዚያ በኋላ የመጡብንን መከራዎች እንድንቋቋም አጠናክሮናል።

አስቸጋሪ ጊዜ መጣ

ሥራችን እገዳ ተጣለበት፤ እንዲሁም መንግሥት ቅርንጫፍ ቢሮውን ወረሰው

በ1964 የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የተነሳ ከባድ ፈተና አጋጠማቸው። ከ100 በላይ የሚሆኑ የመንግሥት አዳራሾችና ከ1,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች መኖሪያ ቤቶች በተነሳው የስደት ማዕበል ወደሙ። ይሁንና የማላዊ መንግሥት በ1967 በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እገዳ እስከጣለበት ጊዜ ድረስ በተጓዥነት ሥራችን መቀጠል ችለን ነበር። እገዳው ሲጣል በብላንቲር የነበረው ቅርንጫፍ ቢሮ ተወረሰ፤ ሚስዮናውያኑ ከአገሪቱ ተባረሩ፤ እንዲሁም እኔንና ሊዳሲን ጨምሮ ብዙ የአካባቢው የይሖዋ ምሥክሮች እስር ቤት ገባን። ከወኅኒ ከወጣን በኋላ የተጓዥነት ሥራችንን ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ቀጠልን።

ጥቅምት 1972 አንድ ቀን፣ የማላዊ ወጣቶች ማኅበር የተባለው የፖለቲካ ንቅናቄ አባላት የሆኑ መቶ ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ወደ ቤታችን መጡ። እነሱ ከመድረሳቸው በፊት ግን ከአባላቱ መካከል አንዱ ሮጦ በመምጣት ሊገድሉኝ ስላሰቡ እንድደበቅ ነገረኝ። ሚስቴና ልጆቼ በአቅራቢያው ባሉ የሙዝ ተክሎች መካከል እንዲደበቁ ነገርኳቸው። ከዚያም እኔ ሮጬ አንድ ትልቅ የማንጎ ዛፍ ላይ ወጣሁ። እዚያ ሆኜ ቤት ንብረታችን ሲወድም ተመለከትሁ።

በማላዊ ስደቱ እየተባባሰ ሲመጣ እኛን ጨምሮ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወንድሞች አገሪቱን ለቀው ተሰደዱ። ቤተሰባችን እስከ ሰኔ 1974 ድረስ በምዕራባዊ ሞዛምቢክ ውስጥ በሚገኝ አንድ የስደተኛ ሠፈር ውስጥ ቆየ። በዚያን ጊዜ እኔና ሊዳሲ ሞዛምቢክ ውስጥ በማላዊ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው በዶምዌ በልዩ አቅኚነት እንድናገለግል ተጠየቅን። ሞዛምቢክ ከፖርቱጋል ነፃ እስከወጣችበት እስከ 1975 ድረስ በዚህ ሥራ ስንካፈል ቆየን። ከዚያም ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ሆነን ወደ ማላዊ ለመመለስ ተገደድን፤ ይህም በድጋሚ ከአሳዳጆቻችን ጋር እንድንፋጠጥ አደረገን።

ወደ ማላዊ ከተመለስን በኋላ በዋና ከተማዋ ሊሎንግዌ የሚገኙ ጉባኤዎችን እንድጎበኝ ተመደብኩ። ስደትና ሌሎች ብዙ ችግሮች ቢኖሩም ባገለገልንባቸው ወረዳዎች ውስጥ የጉባኤዎች ቁጥር እየጨመረ ሄደ።

የይሖዋን ድጋፍ መቅመስ

በአንድ ወቅት አንድ መንደር ስንደርስ በዚያ ፖለቲካዊ ስብሰባ እየተካሄደ ነበር። ከፓርቲው ደጋፊዎች አንዳንዶቹ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ስላወቁ የማላዊ ወጣት ዘማቾች በመባል ከሚታወቁት የወጣቶች ንቅናቄ አባላት ጋር አስቀመጡን። ይሖዋ እንዲረዳንና በዚህ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መመሪያ እንዲሰጠን አጥብቀን ጸለይን። ስብሰባው ሲያበቃ ይደበድቡን ጀመር። በዚህ መሃል አንዲት አረጋዊት ሮጠው በመምጣት ጮክ ብለው “እባካችሁ ተዉአቸው! ይህ ሰው የወንድሜ ልጅ ነው። ተዉት ይሂድ” አሉ። ስብሰባውን  ይመራ የነበረው ሰው “ልቀቋቸው ይሂዱ!” አለ። ሴትየዋ ዘመዳችን ስላልሆኑ ምን አስበው እንደዚያ እንደተናገሩ አናውቅም። ይሁንና ይሖዋ ለጸሎታችን ምላሽ እንደሰጠ ተሰምቶናል።

የፖለቲካ ፓርቲ ካርድ

በ1981 ከማላዊ ወጣት ዘማቾች አባላት መካከል አንዳንዶቹን በድጋሚ አገኘናቸው። እነሱም ብስክሌቶቻችንን፣ ሻንጣችንን፣ በካርቶን የታሸጉ መጻሕፍትንና የወረዳ ፋይሎችን ወሰዱብን። እኛም ሮጠን ወደ አንድ ሽማግሌ ቤት ገባን። በዚህ ጊዜም ቢሆን ስለ ሁኔታው ጸለይን። በወሰዱብን ፋይሎች ላይ የሚገኙት መረጃዎች ጉዳይ አሳስቦን ነበር። ፋይሎቹን ከፍተው ሲመለከቱ በመላዋ ማላዊ ከሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች የተጻፉልኝን ደብዳቤዎች አገኙ። ይህን ሲያዩ የመንግሥት ባለሥልጣን ስለመሰልኳቸው በጣም ፈሩ። በመሆኑም ወዲያውኑ ሁሉንም ነገር በአካባቢው ላሉ ሽማግሌዎች መለሱ።

ሌላ ጊዜ ደግሞ በጀልባ አንድ ወንዝ እያቋረጥን ነበር። የጀልባው ባለቤት የዚያ አካባቢ ሊቀ መንበር ስለነበረ ተሳፋሪዎቹ የፖለቲካ ፓርቲው ካርድ ያላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ፍተሻ ማድረግ ጀመረ። እኛ ጋ ሊደርስ ሲል ባለሥልጣናቱ ይፈልጉት የነበረ አንድ ሌባ አገኘ። ይህም ከፍተኛ ብጥብጥ ስለፈጠረ የፖለቲካ ካርዱን መያዛችንን ለማየት የሚያደርገው ፍተሻ ቀረ። በዚህ ጊዜም ይሖዋ ፍቅራዊ ድጋፍ እንዳደረገልን ተሰምቶናል።

ተይዤ ታሰርኩ

የካቲት 1984 የዛምቢያን ቅርንጫፍ ቢሮ ሪፖርት ለማድረስ ወደ ሊሎንግዌ ሄድኩ። መንገድ ላይ አንድ ፖሊስ አስቆመኝና ሻንጣዬን መፈተሽ ጀመረ። በሻንጣዬ ውስጥ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን አገኘ፤ ስለዚህ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስዶ ደበደበኝ። ከዚያም በገመድ አስሮ፣ የተሰረቀ ንብረት እጃቸው ላይ የተገኘባቸው እስረኞች ያሉበት ክፍል አስገባኝ።

በቀጣዩ ቀን የፖሊስ አዛዡ ወደ ሌላ ክፍል ወስዶ “እኔ ትሮፊም ንሶምባ፣ ነፃ መለቀቅ ስለምፈልግ ከእንግዲህ የይሖዋ ምሥክር አይደለሁም” የሚል ጽሑፍ እንድፈርም አዘጋጀልኝ። እኔም “ለመታሰር ብቻ ሳይሆን ለመሞትም ጭምር ዝግጁ ነኝ። አሁንም የይሖዋ ምሥክር ነኝ” ብዬ መልስ ሰጠሁ። ሰነዱን ለመፈረምም ፈቃደኛ አልሆንኩም። ይህም የፖሊስ አዛዡን ስላናደደው እጁን ጨብጦ ጠረጴዛውን በኃይል መታው፤ በዚህ ጊዜ በቀጣዩ ክፍል ያለ አንድ ፖሊስ ምን እንደተፈጠረ ለማየት እየሮጠ መጣ። የፖሊስ አዛዡም እንዲህ ብሎ ነገረው፦ “ይህ ሰው መመሥከር አቁሜያለሁ ብሎ ለመፈረም ፈቃደኛ አይደለም። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክር ነኝ ብሎ እንዲፈርም አድርገውና እንዲታሰር ወደ ሊሎንግዌ እንልከዋለን።” በዚህ ጊዜ ሁሉ ውዷ ባለቤቴ ምን ገጥሞኝ እንደሆነ ግራ ገብቷት ነበር። ከአራት ቀናት በኋላ ግን ወንድሞች የት እንዳለሁ ነገሯት።

በሊሎንግዌ ፖሊስ ጣቢያ ጥሩ እንክብካቤ ተደርጎልኛል። የፖሊስ አዛዡ ሳህን ሙሉ ሩዝ ሰጠኝና እንዲህ አለኝ፦ “እንካ ይህን ሩዝ ብላ፤ ምክንያቱም የታሰርከው ለአምላክ ቃል ስትል ነው። እዚህ ያሉት ሌሎቹ ሰዎች ግን ሌቦች ናቸው።” ከዚያም ወደ ካቸሬ እስር ቤት ላከኝ፤ በዚያም ለአምስት ወራት ታሰርኩ።

የዚያ እስር ቤት አስተዳዳሪ እኔ በመምጣቴ ደስ አለው፤ ይህ ሰው ለእስር ቤቱ “ፓስተር” እንድሆንለት ፈልጎ ነበር።  በወቅቱ ያገለግል የነበረውን ፓስተር እንዲህ በማለት አሰናበተው፦ “አንተ ከዚህ በኋላ የአምላክን ቃል እንድትሰብክ አልፈልግም፤ ምክንያቱም አንተ ራስህ የታሰርከው ከቤተ ክርስቲያንህ ሰርቀህ ነው!” በዚህ መንገድ ለእስረኞቹ በተዘጋጁ ስብሰባዎች ላይ በየሳምንቱ መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ኃላፊነት ተሰጠኝ።

ከጊዜ በኋላ ነገሮች ይበልጥ እየተባባሱ ሄዱ። የእስር ቤቱ ባለሥልጣናት በማላዊ ስንት የይሖዋ ምሥክሮች እንዳሉ ጠየቁኝ። እኔም የሚፈልጉትን መልስ ስላልሰጠኋቸው ራሴን እስክስት ድረስ ደበደቡኝ። ሌላ ጊዜ ደግሞ ዋና መሥሪያ ቤታችን የሚገኘው የት እንደሆነ ጠየቁኝ። እኔም “የጠየቃችሁኝ ቀላል ጥያቄ ስለሆነ መልሱን እነግራችኋለሁ” አልኳቸው። ፖሊሶቹ ደስ ብሏቸው የምናገረውን ነገር ለመቅረጽ ቴፕ ከፈቱ። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት እንደሚናገር ገለጽኩላቸው። እነሱም ተገርመው “መጽሐፍ ቅዱስ የት ላይ ነው የሚናገረው?” ብለው ጠየቁኝ።

ኢሳይያስ 43:12 ላይ” ብዬ መለስኩ። እነሱም ጥቅሱን አወጡና በጥንቃቄ አነበቡት፦ “‘እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ’ ይላል ይሖዋ፤ ‘እኔም አምላክ ነኝ።’” ጥቅሱን ሦስት ጊዜ አነበቡት። ከዚያም “የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት በአሜሪካ መሆኑ ቀርቶ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው እንዴት ነው?” ብለው ጠየቁኝ። እኔም “በአሜሪካ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ይህ ጥቅስ ዋና መሥሪያ ቤታቸውን እንደሚገልጽ ይሰማቸዋል” አልኳቸው። ማወቅ የሚፈልጉትን ነገር ስለማልነግራቸው ከሊሎንግዌ በስተ ሰሜን ወደሚገኘው ዛሌካ እስር ቤት አዛወሩኝ።

በአስቸጋሪ ጊዜም ቢሆን ያገኘናቸው በረከቶች

ሐምሌ 1984 በዛሌካ እስር ቤት ውስጥ ከ81 የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘሁ። በዚህ እስር ቤት 300 እስረኞች ወለሉ ላይ ተፋፍገው ያድሩ ነበር። በዚያ የነበርነው የይሖዋ ምሥክሮች ቀስ በቀስ በትናንሽ ቡድኖች ተከፋፍለን በየዕለቱ አንድ ጥቅስ ላይ መወያየት ጀመርን፤ ጥቅሱን የሚመርጡት የተለያዩ ወንድሞች ነበሩ። ይህም በጣም አበረታቶናል።

ከዚያም የእስር ቤቱ አስተዳዳሪ ከሌሎች እስረኞች እንድንለይ አደረገን። አንድ ዘበኛ በሚስጥር እንዲህ አለን፦ “መንግሥት እናንተን አይጠላችሁም። እስር ቤት የምናቆያችሁ በሁለት ምክንያቶች የተነሳ ነው፦ አንደኛ መንግሥት፣ የወጣት ዘማቾቹ አባላት ይገድሏችኋል ብሎ ስለሚፈራ ነው፤ ሌላው ደግሞ እናንተ ወደፊት ስለሚመጣ ጦርነት ስለምትሰብኩ መንግሥት፣ በዚህ ጦርነት ወቅት ወታደሮቹ እንዳይሸሹ ስለሚሰጋ ነው።”

ወንድሞች ለፍርድ ከቀረቡ በኋላ ሲወሰዱ

ጥቅምት 1984 ሁላችንም ፍርድ ቤት ቀረብን። እያንዳንዳችን የሁለት ዓመት እስራት ተፈረደብን። እንደ ቀድሞው ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች ካልሆኑ ሰዎች ጋር ታሰርን። ይሁን እንጂ የእስር ቤቱ አስተዳዳሪ ለሁሉም እስረኞች የሚከተለውን ማስታወቂያ ተናገረ፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ሲጋራ አያጨሱም። ስለዚህ እናንተ ጠባቂዎች፣ ሲጋራ ስጡን እያላችሁ አታስቸግሯቸው፤ እንዲሁም ሲጋራችሁን ለመለኮስ የከሰል ፍም እንዲያመጡ አትላኳቸው። እነሱ የአምላክ ሕዝቦች ናቸው! ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች በቀን ሁለት ጊዜ ምግብ ሊሰጣቸው ይገባል፤ ምክንያቱም እነሱ እዚህ የገቡት ወንጀል ፈጽመው ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ባላቸው እምነት የተነሳ ነው።”

 ያተረፍነው መልካም ስም በሌሎች መንገዶችም ጠቅሞናል። ሲጨልም ወይም ሲዘንብ እስረኞች ወዲያ ወዲህ እንዲዘዋወሩ አይፈቀድላቸውም። እኛ ግን በፈለግነው ጊዜ ከሕንፃው እንድንወጣ ይፈቀድልን ነበር። ምክንያቱም ለማምለጥ እንደማንሞክር አውቀው ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት በእርሻ ላይ በምንሠራበት ወቅት ሲጠብቀን የነበረ ተረኛ ጠባቂ በድንገት ታመመ፤ ከዚያም ሕክምና እንዲደረግለት ተሸክመን ወደ እስር ቤቱ ግቢ ወሰድነው። የእስር ቤቱ ባለሥልጣናት እምነት የሚጣልብን ሰዎች እንደሆንን አውቀው ነበር። መልካም ምግባር ማሳየታችንን በመቀጠላችን የይሖዋ ስም ባሰሩን ሰዎች አፍ ሲከበር በማየት ተባርከናል።—1 ጴጥ. 2:12 *

አመቺ ጊዜ ተመልሶ መጣ

ግንቦት 11, 1985 ከዛሌካ እስር ቤት ተለቀቅሁ። ከቤተሰቤ ጋር እንደገና መገናኘት በመቻሌ በጣም ተደስቼ ነበር! ይሖዋ በእነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት ንጹሕ አቋማችንን እንድንጠብቅ ስለረዳን እናመሰግነዋለን። ስለ እነዚያ ጊዜያት ስናስብ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ እንደጻፈው ይሰማናል፦ “ወንድሞች፣ . . . ስለደረሰብን መከራ እንድታውቁ እንፈልጋለን። ከአቅማችን በላይ የሆነ ከባድ ጫና ደርሶብን ስለነበር በሕይወት የመትረፍ ተስፋችን እንኳ ተሟጦ ነበር። እንዲያውም የሞት ፍርድ ተፈርዶብናል የሚል ስሜት አድሮብን ነበር። ይህ የሆነው ግን በራሳችን ሳይሆን ሙታንን በሚያስነሳው አምላክ እንድንታመን ነው። እሱ እንዲህ ካለ ለሞት ሊዳርግ የሚችል አደገኛ ሁኔታ አድኖናል።”—2 ቆሮ. 1:8-10

ወንድም ንሶምባ እና ባለቤታቸው ሊዳሲ በአንድ የመንግሥት አዳራሽ ፊት ለፊት፣ 200

በእርግጥም አንዳንድ ጊዜ በሕይወት የምንተርፍ አይመስልም ነበር። ነገር ግን ለይሖዋ ታላቅ ስም ክብር ማምጣታችንን እንቀጥል ዘንድ የትሕትና መንፈስ እንዲኖረን የሚረዳን ድፍረትና ጥበብ እንዲሰጠን ይሖዋን ሁልጊዜ እንለምነው ነበር።

በአመቺ ወቅትም ሆነ በአስቸጋሪ ወቅት ይሖዋ በአገልግሎቱ ባርኮናል። አሁን በሊሎንግዌ በ2000 ተሠርቶ የተጠናቀቀውን ቅርንጫፍ ቢሮ በማየታችን እንዲሁም በመላው ማላዊ ከ1,000 በላይ አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች በመገንባታቸው በጣም ደስ ይለናል! ከይሖዋ ያገኘናቸው እነዚህ በረከቶች በመንፈሳዊ እጅግ የሚያበለጽጉ በመሆናቸው እኔና ሊዳሲ ሁኔታው ሕልም እንጂ እውን አይመስለንም! *

^ አን.7 በአሁኑ ጊዜ ግን ትናንሽ ልጆች ያሏቸው ወንድሞች በወረዳ የበላይ ተመልካችነት እንዲያገለግሉ አይጠሩም።

^ አን.30 በማላዊ ስለደረሰው ስደት ዝርዝር መረጃ ለማግኘት የ1999ን የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 171-223 ተመልከት።

^ አን.34 ይህ ርዕስ ለሕትመት በሚዘጋጅበት ወቅት ወንድም ንሶምባ በ83 ዓመታቸው በሞት አንቀላፍተዋል።