በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  መጋቢት 2015

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ቀደም ሲል ጽሑፎቻችን ጥላ ስለሚሆኑ ነገሮችና ስለ እውነተኛዎቹ ነገሮች ብዙ ጊዜ ይጠቅሱ ነበር፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን እንዲህ ዓይነቱ ማብራሪያ እየቀረ መጥቷል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?

የመስከረም 15, 1950 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) እንደገለጸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ አንድ ግለሰብ፣ ክንውን ወይም ግዑዝ ነገር ወደፊት ለሚፈጸም የላቀ ነገር ጥላ የሚሆንበት ጊዜ አለ።

ከብዙ ዓመታት በፊት ጽሑፎቻችን እንደ ረዓብ፣ ርብቃ፣ ኢዮብ፣ ኤሊሁ፣ ዮፍታሔና ዲቦራ የመሳሰሉ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም ሌሎች ብዙዎች የቅቡዓኑ አሊያም ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ ጥላዎች እንደሆኑ ገልጸው ነበር። (ራእይ 7:9) ለምሳሌ ርብቃ፣ ኢዮብና ዮፍታሔ ቅቡዓንን እንደሚወክሉ በሌላ በኩል ደግሞ ረዓብና ዲቦራ ለእጅግ ብዙ ሕዝብ ጥላ እንደሆኑ ይታሰብ ነበር። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንዲህ ዓይነት ንጽጽሮችን ጽሑፎቻችን ላይ ማግኘት የተለመደ አይደለም። ለምን?

ጥላ

በጥንቷ እስራኤል በፋሲካ ላይ የሚሠዋው በግ ጥላነት ነበረው።—ዘኁ. 9:2

እውነተኛው ነገር

ክርስቶስ ‘የፋሲካችን በግ’ እንደሆነ ጳውሎስ ገልጿል።—1 ቆሮ. 5:7

ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚጠቁሙት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ግለሰቦች ለላቀ ነገር ጥላ ሆነው አገልግለዋል። በገላትያ 4:21-31 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁለት ሴቶችን የሚመለከት “ምሳሌያዊ ድራማ” ጠቅሷል። የአብርሃም አገልጋይ የነበረችው አጋር፣ በሙሴ ሕግ አማካኝነት ከይሖዋ ጋር በቃል ኪዳን የታሰረችውን ሥጋዊ እስራኤልን እንደምትወክል ወይም እንደምታመለክት ገልጿል። “ነፃይቱ ሴት” የተባለችው ሣራ ግን በምሳሌያዊ ሁኔታ የአምላክን ሚስት፣ ማለትም የድርጅቱን ሰማያዊ ክፍል ታመለክታለች። ጳውሎስ ለዕብራውያን በጻፈው ደብዳቤ ላይ፣ ንጉሥና ካህን የነበረው መልከ ጼዴቅ ኢየሱስን እንደሚወክል የተናገረ ሲሆን በሁለቱ መካከል ያሉትን ተመሳሳይነቶች ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ዕብ. 6:20፤ 7:1-3) በተጨማሪም ጳውሎስ፣ ኢሳይያስንና ወንዶች ልጆቹን ከኢየሱስና ከቅቡዓን ተከታዮቹ ጋር አመሳስሏቸዋል። (ዕብ. 2:13, 14) ጳውሎስ እነዚህን ሐሳቦች የጻፈው በመንፈስ ተመርቶ በመሆኑ ጥላነት ስላላቸው ሰዎች የተናገረውን ሐሳብ ያለ አንዳች ማንገራገር እንቀበላለን።

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው የሌላው ጥላ እንደሆነ በሚያመለክትበት ጊዜም እንኳ ጥላ በሆነው ግለሰብ ሕይወት ውስጥ ያሉት ዝርዝር ነገሮች ወይም ሁኔታዎች በሙሉ ለአንድ የላቀ ነገር ጥላ ሆነው ያገለግላሉ ብለን መደምደም የለብንም። ለምሳሌ ጳውሎስ፣ መልከ ጼዴቅ የኢየሱስ ጥላ  እንደሆነ ቢገልጽም አብርሃም በአንድ ወቅት አራት ነገሥታትን ድል አድርጎ ሲመለስ መልከ ጼዴቅ ለአብርሃም ስላመጣለት ምግብና የወይን ጠጅ ምንም አልተናገረም። በመሆኑም ይህ ክንውን ልዩ ትርጉም እንዳለው ለመግለጽ የሚያነሳሳ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የለም።—ዘፍ. 14:1, 18

ከክርስቶስ ሞት በኋላ በነበሩት ዘመናት የኖሩ አንዳንድ ጸሐፊዎች፣ ለሁሉም ነገር ጥላ የመፈለግ አባዜ ተጠናውቷቸው ነበር። ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ ኦሪጀን፣ አምብሮስና ጀሮም ስላስተማሯቸው ነገሮች ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ የተመዘገበው እያንዳንዱ ክስተትና ሁኔታ፣ ያን ያህል ትልቅ ቦታ የማይሰጠው ነገርም እንኳ ጥላነት እንዳለው ይሰማቸው ነበር፤ ደግሞም ጥላ የሆኑ ነገሮች ያገኙ ነበር። በጣም ቀላልና ተራ የሆነ ክስተትም እንኳ በውስጡ ረቂቅ እውነት ደብቆ እንደያዘ ይታሰብ ነበር። . . . ሌላው ቀርቶ መድኃኒታችን [ኢየሱስ] ከሞት ከተነሳ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ በተገለጠበት ዕለት ደቀ መዛሙርቱ ያጠመዷቸው 153 ዓሦች ቁጥር ልዩ ትርጉም እንዳለው ለማስረዳት አንዳንዶች ብዙ ጥረዋል!”

የሂፖው ኦገስቲን፣ ኢየሱስ በአምስት የገብስ ዳቦና በሁለት ዓሣ 5,000 ሰዎችን እንደመገበ በሚገልጸው ዘገባ ላይ ሰፊ ትንታኔ ሰጥቷል። ገብስ ከስንዴ ዝቅ ተደርጎ ስለሚታይ ኦገስቲን፣ አምስቱ የገብስ ዳቦዎች አምስቱን የሙሴ መጻሕፍት እንደሚወክሉ ገልጿል (ከስንዴ እንደሚያንስ የሚታሰበው “ገብስ” “ብሉይ ኪዳን” ዝቅ ያለ እንደሆነ ያመለክታል)። ሁለቱ ዓሦችስ ምን ያመለክታሉ? ምክንያቱን ባናውቅም ኦገስቲን ዓሦቹን ከንጉሥና ከካህን ጋር አመሳስሏቸዋል። ትንቢታዊ ጥላዎችን ማግኘት የሚወድ አንድ ሌላ ምሁር ደግሞ ያዕቆብ የዔሣውን ብኩርና በቀይ ወጥ መግዛቱ፣ ኢየሱስ ቀይ በሆነው ደሙ ለሰው ዘር በሰማይ ውርሻ መግዛቱን ያመለክታል እስከ ማለት ደርሷል!

እንዲህ ዓይነቶቹ ትርጓሜዎች ከእውነታው የራቁ መስለው ከታዩህ ችግሩን መረዳት አያዳግትህም። ሰዎች፣ ወደፊት ለሚመጡ ነገሮች ጥላ የሆኑት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች እንደሆኑና የትኞቹ ደግሞ ጥላነት እንደሌላቸው ማወቅ አይችሉም። ስለዚህ የማያሻማው አካሄድ ይህ ነው፦ ቅዱሳን መጻሕፍት አንድ ግለሰብ፣ ክንውን ወይም ግዑዝ ነገር ጥላ እንደሆነ ከተናገሩ ይህን እንቀበላለን። ከዚህ ውጭ ግን በግልጽ የተጠቀሰ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ሳይኖረን አንድ ግለሰብ ወይም ዘገባ ለሌላ ነገር ጥላ እንደሆነ ከመግለጽ መቆጠብ ይኖርብናል።

ታዲያ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኙት ክንውኖችና ምሳሌዎች ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? በሮም 15:4 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ “በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል” ብሏል። ጳውሎስ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ቅቡዓን ወንድሞቹ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከተመዘገቡት ክንውኖች ትልቅ ትምህርት ማግኘት እንደሚችሉ መናገሩ ነበር። ይሁን እንጂ በሁሉም ዘመን የኖሩ የአምላክ ሕዝቦች፣ ቅቡዓንም ሆኑ “ሌሎች በጎች” እንዲሁም “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” የሚኖሩትም ሆኑ ከዚያ በፊት የኖሩት “ቀደም ብሎ [ከተጻፈው] ነገር ሁሉ” ትምህርት ማግኘት ይችላሉ፤ ደግሞም አግኝተዋል።—ዮሐ. 10:16፤ 2 ጢሞ. 3:1

ከእነዚህ የቅዱሳን መጻሕፍት ዘገባዎች አብዛኞቹ በአንድ ቡድን ማለትም በቅቡዓን ወይም በእጅግ ብዙ ሕዝብ ላይ ብቻ እንዲሁም በአንድ የተወሰነ ዘመን ብቻ ፍጻሜ እንዳገኙ አድርገን መውሰድ የለብንም፤ ከዚህ ይልቅ ዘገባዎቹ በማንኛውም ዘመን የኖሩ የሁለቱም ቡድን አባላት የሆኑ የአምላክ ሕዝቦችን እንደሚጠቅሙ አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል። ለምሳሌ ያህል፣ የኢዮብ መጽሐፍ የያዘው ዘገባ ተፈጻሚነቱን ያገኘው በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቅቡዓኑ ካጋጠሟቸው ነገሮች ጋር በተያያዘ ብቻ እንደሆነ አድርገን ማሰብ አያስፈልገንም። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እንዲሁም ቅቡዓንም ሆኑ የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት የሆኑ በርካታ የአምላክ አገልጋዮች፣ በኢዮብ ላይ እንደደረሱት ዓይነት ፈተናዎች ያጋጠሟቸው ሲሆን እነሱም ‘ይሖዋ ያደረገላቸውን አይተዋል፤ በዚህም ይሖዋ ከአንጀት የሚራራና መሐሪ እንደሆነ ተመልክተዋል።’—ያዕ. 5:11

እስቲ አስበው፦ በጉባኤያችን ውስጥ እንደ ኢዮብ በትዕግሥት የጸኑ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች፣ እንደ ኤሊሁ ጥበበኞች የሆኑ ወጣት ሽማግሌዎች፣ እንደ ዮፍታሔ ቀናተኛ የሆኑ ደፋር አቅኚዎች እንዲሁም እንደ ዲቦራ ታማኝ የሆኑ አረጋውያን ሴቶች አናገኝም? ይሖዋ “ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ” ተመዝግቦ እንዲቆይልን በማድረጉ ምንኛ አመስጋኞች ነን!

እስካሁን በተመለከትናቸው ምክንያቶች የተነሳ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሚወጡ ጽሑፎቻችን ጥላነት ያላቸውን ነገሮች እና እውነተኛዎቹን ነገሮች ለመጠቆም ከመጣር ይልቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ለምናገኘው ትምህርት አጽንኦት እየሰጡ ነው።