በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

‘ይህ የአንተ ፈቃድ ነው’

‘ይህ የአንተ ፈቃድ ነው’

“እነዚህን ነገሮች ከጥበበኞችና ከአዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት [ገለጥክላቸው]።”—ሉቃስ 10:21

1. ኢየሱስ “በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት” እንዲያደርግ ያነሳሳው ምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

ኢየሱስ ክርስቶስ ‘በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት ያደረገበትን’ ጊዜ ማሰብ ትችላለህ? ፊቱ በፈገግታ ሲሞላና ዓይኖቹ በደስታ ሲያበሩ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ ይሆናል። እንዲህ እንዲሰማው ያደረገው ምንድን ነው? የአምላክን መንግሥት ምሥራች እንዲሰብኩ 70 ደቀ መዛሙርቱን ልኳቸው ነበር። በመሆኑም ተልእኳቸውን እንዴት እንደፈጸሙ ለማወቅ ጓጉቷል። የተማሩና ብልሆች የሆኑትን ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ጨምሮ ምሥራቹን የሚቃወሙ በርካታ ኃያላን ጠላቶች ነበሩ። ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ ብዙዎች ኢየሱስን እንደ ተራ አናጺ እንዲቆጥሩትና ደቀ መዛሙርቱንም “ያልተማሩ ተራ ሰዎች” እንደሆኑ አድርገው እንዲመለከቷቸው ተጽዕኖ አድርገዋል። (ሥራ 4:13፤ ማር. 6:3) ያም ቢሆን ደቀ መዛሙርቱ ተልእኳቸውን አከናውነው ሲመለሱ ፊታቸው በደስታ ያበራ ነበር። ከአጋንንት ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም እንኳ ምሥራቹን ሰብከዋል! ለመሆኑ ደስተኛና ደፋር እንዲሆኑ ያስቻላቸው ምንድን ነው?—ሉቃስ 10:1, 17-21ን አንብብ።

2. (ሀ) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደ ሕፃናት የሆኑት ከምን አንጻር ነው? (ለ) የክርስቶስ ተከታዮች ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን መንፈሳዊ እውነቶች መገንዘብ እንዲችሉ የረዳቸው ምንድን ነው?

2 ኢየሱስ ወደ ይሖዋ ምን ብሎ እንደጸለየ ልብ በል፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፣ እነዚህን ነገሮች ከጥበበኞችና ከአዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለገለጥክላቸው በሕዝብ ፊት አወድስሃለሁ። አዎ፣ አባት ሆይ፣ ይህን ማድረጉ የአንተ ፈቃድ ሆኖ ተገኝቷል።” (ማቴ. 11:25, 26) እዚህ ላይ  ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ቃል በቃል ሕፃናት እንደሆኑ መናገሩ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ከዚህ ይልቅ ደቀ መዛሙርቱ በአካባቢያቸው ካሉ ራሳቸውን እንደ ጠቢባን አድርገው ከሚመለከቱ አዋቂዎችና ምሁራን አንጻር እንደ ሕፃናት ሊቆጠሩ እንደሚችሉ መግለጹ ነበር። ከሁሉ በላይ ደግሞ ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ እንደ ሕፃናት ትሑትና ለመማር ፈቃደኛ እንዲሆኑ አስተምሯል። (ማቴ. 18:1-4) ታዲያ ትሑት መሆናቸው የጠቀማቸው እንዴት ነው? ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን መንፈሳዊ እውነቶች መገንዘብ እንዲችሉ ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ረድቷቸዋል፤ በአንጻሩ ግን እነሱን የናቋቸውን ጥበበኞችና አዋቂዎች ሰይጣንና በውስጣቸው ያለው ትዕቢት አሳውረዋቸዋል።

3. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

3 ኢየሱስ በጣም መደሰቱ የሚያስደንቅ አይደለም! ይሖዋ፣ የትምህርት ደረጃቸው ወይም ተሰጥኦዋቸው ምንም ይሁን ምን ትሑት እስከሆኑ ድረስ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን መግለጹ ኢየሱስን አስደስቶታል። ኢየሱስ የተደሰተው አባቱ እንዲህ ባለ መንገድ ማስተማርን የሚመርጥ በመሆኑ ነው። ይሖዋ አልተለወጠም፤ ይሁንና አሁንም ቢሆን እንዲህ ባለ መንገድ ማስተማርን እንደሚመርጥ ያሳየው እንዴት ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቃችን ልክ እንደ ኢየሱስ እኛም ከልብ እንድንደሰት ያደርገናል።

ጥልቅ እውነቶችን ሁሉም ሰው በሚረዳው መንገድ ማቅረብ

4. ቀለል ባለ ቋንቋ የተዘጋጀው የመጠበቂያ ግንብ እትም ፍቅራዊ ዝግጅት የሆነው እንዴት ነው?

4 ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ የይሖዋ ድርጅት የሚያቀርባቸው መንፈሳዊ ትምህርቶች ይበልጥ ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ ማስተማርን የሚያበረታቱ ናቸው። ሦስት ምሳሌዎችን እንመልከት። የመጀመሪያው ምሳሌ፣ ቀለል ባለ ቋንቋ የተዘጋጀው የመጠበቂያ ግንብ እትም ነው። * በእርግጥም ይህ እትም፣ ቋንቋ ለሚከብዳቸውና ማንበብ ለሚቸገሩ ሰዎች ፍቅራዊ ዝግጅት መሆኑ እየታየ ነው። የቤተሰብ ራሶች፣ መንፈሳዊ ምግብ የምናገኝበት ዋነኛ መንገድ የሆነው ይህ መጽሔት ሲጠና ልጆቻቸው አሁን ይበልጥ ተሳትፎ ማድረግ እንደቻሉ ተናግረዋል። ብዙዎች ለዚህ ዝግጅት ያላቸውን አድናቆት ልብ በሚነካ መንገድ ገልጸዋል። አንዲት እህት የመጠበቂያ ግንብ ጥናት በሚካሄድበት ወቅት ሐሳብ ለመስጠት ስለምትፈራ መልስ ከመመለስ ወደኋላ ትል እንደነበር ጽፋለች። አሁን ግን እንዲህ አይሰማትም። ቀለል ባለ ቋንቋ የተዘጋጀውን የመጠበቂያ ግንብ እትም መጠቀም ከጀመረች በኋላ ያለውን ሁኔታ ስትገልጽ “አሁን ከአንድ ጊዜ በላይ እመልሳለሁ፤ ፍርሃቴም ጠፍቷል! ይሖዋንም ሆነ እናንተን አመሰግናለሁ” በማለት ጽፋለች።

5. የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ያሉት አንዳንድ ጥቅሞች የትኞቹ ናቸው?

5 ሁለተኛው ምሳሌ ደግሞ የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅምት 5, 2013 በተደረገው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ በእንግሊዝኛ መውጣቱ ነው። * በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙትን ብዙዎቹን ጥቅሶች ከቀድሞው ይልቅ በጥቂት ቃላት ለማስቀመጥ ተሞክሯል፤ ያም ቢሆን የጥቅሶቹ ትርጉም አልተለወጠም፤ እንዲያውም ይበልጥ ግልጽ ሆኗል። ለምሳሌ ያህል፣ በእንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ ኢዮብ 10:1 ከ27 ወደ 19 ቃላት ምሳሌ 8:6 ደግሞ ከ20 ወደ 13 ቃላት ተቀንሷል። ሁለቱም ጥቅሶች በአዲሱ እትም ይበልጥ ግልጽ ናቸው። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ያገለገለ አንድ ቅቡዕ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የኢዮብ መጽሐፍን በአዲሱ እትም አንብቤ መጨረሴ ነው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደገባኝ ተሰምቶኛል!” ብዙዎች ተመሳሳይ ሐሳብ ሰጥተዋል።

6. ከማቴዎስ 24:45-47 ጋር በተያያዘ ስለተደረገው ማስተካከያ ምን ይሰማሃል?

6 በሦስተኛ ደረጃ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተደረጉ አንዳንድ ማስተካከያዎችን እንመልከት። ለምሳሌ ያህል፣ በሐምሌ 15, 2013 መጠበቂያ ግንብ ላይ  በወጣው ትምህርት ላይ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ አስመልክቶ የተደረገው ማስተካከያ አስደስቶናል። (ማቴ. 24:45-47) ታማኙ ባሪያ፣ የበላይ አካሉ እንደሆነና “አገልጋዮቹ” ወይም “ቤተሰቦቹ” የተባሉት ደግሞ መንፈሳዊ ምግብ የሚቀርብላቸውን ሁሉ ይኸውም ቅቡዓኑን እና ‘ሌሎች በጎችን’ እንደሚያመለክቱ ተብራርቷል። (ዮሐ. 10:16) እንዲህ ያሉ እውነቶችን መማርም ሆነ ለአዲሶች ማስተማር በእጅጉ የሚያረካ ነው! ይሖዋ፣ ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ ማስተማርን እንደሚመርጥ ያሳየባቸው ሌሎች መንገዶችስ አሉ?

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ ማብራራት

7, 8. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱ ትንቢታዊ ጥላነት ያላቸው ነገሮች አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?

7 ይሖዋን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ስታገለግል የቆየህ ክርስቲያን ከሆንክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት በብዙዎቹ ታሪኮች ላይ ማብራሪያ የሚሰጥበት መንገድ ቀስ በቀስ እየተለወጠ እንደመጣ አስተውለህ ይሆናል። የተለወጠው እንዴት ነው? ቀደም ባሉት ዓመታት ጽሑፎቻችን፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ ታሪኮች ጥላነት እንዳላቸው መግለጻቸው የተለመደ ነበረ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው ዘገባ ወደፊት ለሚመጣ ነገር ጥላ እንደሆነና የዚያ ዘገባ ትንቢታዊ ፍጻሜ ደግሞ እውነተኛው ነገር እንደሆነ ይገለጽ ነበር። እንዲህ ያለ አተረጓጎም ለመስጠት ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት አለን? አዎን። ለምሳሌ ኢየሱስ ‘ስለ ነቢዩ ዮናስ ምልክት’ ተናግሯል። (ማቴዎስ 12:39, 40ን አንብብ።) ኢየሱስ፣ ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ ያሳለፈው ጊዜ እሱ ራሱ በመቃብር ውስጥ ለሚያሳልፈው ጊዜ ትንቢታዊ ጥላ እንደሆነ ገልጿል፤ ይሖዋ፣ ለዮናስ ጥበቃ ባያደርግለት ኖሮ የዓሣው ሆድ መቃብሩ ይሆን ነበር።

8 መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢታዊ ጥላነት ያላቸው ሌሎች ታሪኮችንም ይዟል። ሐዋርያው ጳውሎስ የተወሰኑትን ጠቅሷል። ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃም ከአጋርና ከሣራ ጋር የነበረው ግንኙነት ይሖዋ ከእስራኤል ብሔርና ከድርጅቱ ሰማያዊ ክፍል ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያሳይ ትንቢታዊ ጥላ ነው። (ገላ. 4:22-26) በተመሳሳይም የማደሪያው ድንኳን፣ ቤተ መቅደሱ፣ የስርየት ቀን፣ ሊቀ ካህናቱና ሌሎች የሙሴ ሕግ ገጽታዎች “ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ” ናቸው። (ዕብ. 9:23-25፤ 10:1) እንደነዚህ ያሉትን ትንቢታዊ ጥላነት ያላቸው ዘገባዎች ማጥናታችን ትኩረት የሚስብ ከመሆኑም በላይ እምነታችንን ያጠናክርልናል። ይሁንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ እያንዳንዱ ባለታሪክ፣ ክንውን ወይም አንድ ግዑዝ ነገር ጥላ የሆነለት ግለሰብ ወይም ሌላ ነገር እንዳለ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው?

9. ስለ ናቡቴ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ቀደም ሲል ይብራራ የነበረው እንዴት ነው?

9 ቀደም ባሉት ዓመታት፣ ብዙ ጊዜ እንዲህ ያሉ ማብራሪያዎች ይሰጡ ነበር። የናቡቴን ታሪክ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ክፉዋ ንግሥት ኤልዛቤል፣ ባሏ አክዓብ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ እንዲወስድ ለማድረግ ስትል ናቡቴ በሐሰት ተከስሶ የተዛባ ፍርድ እንዲሰጠውና በግፍ እንዲገደል አስደረገች። (1 ነገ. 21:1-16) ይህ ታሪክ ትንቢታዊ ድራማ እንደሆነ በ1932 ተገልጾ ነበር። አክዓብና ኤልዛቤል ሰይጣንንና ድርጅቱን እንደሚያመለክቱ፣ ናቡቴ ኢየሱስን እንደሚያመለክትና የናቡቴ ሞት ለኢየሱስ መገደል ምሳሌ እንደሆነ ተብራርቶ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ “ስምህ ይቀደስ” (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ከተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በኋላ በ1961 ሲወጣ ናቡቴ ቅቡዓኑን፣ ኤልዛቤል ሕዝበ ክርስትናን እንደምታመለክት ተገለጸ። በመሆኑም ኤልዛቤል በናቡቴ ላይ ያደረሰችው ስደት ቅቡዓኑ በመጨረሻዎቹ ቀናት የደረሰባቸውን ስደት ያመለክታል። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች በዚህ መልኩ መብራራታቸው ለብዙ ዓመታት የአምላክን ሕዝቦች እምነት አጠናክሯል። ታዲያ ነገሮች የተለወጡት ለምንድን ነው?

10. (ሀ) ባሪያው ልባም መሆኑ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች በሚብራሩበት መንገድ ረገድ ይበልጥ ጠንቃቃ እንዲሆን የረዳው እንዴት ነው? (ለ) በአሁኑ ጊዜ ጽሑፎቻችን ይበልጥ ትኩረት የሚያደርጉት በምን ላይ ነው?

10 ባለፉት ዓመታት “ታማኝና ልባም ባሪያ” ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ልባም እንዲሆን ይሖዋ  ረድቶታል። ታማኙ ባሪያ፣ ልባም መሆኑ ደግሞ ግልጽ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት እስከሌለ ድረስ አንድ ታሪክ ትንቢታዊ ድራማ እንደሆነ በመግለጽ ረገድ ይበልጥ ጠንቃቃ እንዲሆን አድርጎታል። ከዚህም በተጨማሪ ትንቢታዊ ጥላነት ስላላቸው ታሪኮች ቀደም ሲል የተሰጡትን አንዳንድ ማብራሪያዎች ብዙዎች ለመረዳት እንደሚከብዳቸው ባሪያው አስተውሏል። በማብራሪያዎቹ ውስጥ የሚካተቱት ዝርዝር ጉዳዮች ይኸውም ትንቢታዊ ጥላ የሆኑት ነገሮችና እውነተኛዎቹ ነገሮች እንዲሁም ይህን እንድናምን የሚያደርጉን ምክንያቶች ግልጽ አይደሉም፤ እነዚህን ነገሮች ማስታወስም ሆነ ከትምህርቱ ጥቅም ማግኘት ያስቸግራል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ትንቢታዊ ጥላነት ባላቸው ነገሮች ላይ ትኩረት ስናደርግ፣ እየመረመርን ባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ያለው ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ትምህርት ሊድበሰበስ አሊያም ጨርሶ ላይገባን ይችላል። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ የሚወጡ ጽሑፎቻችን ትኩረት የሚያደርጉት እንደ እምነት፣ ጽናት፣ ለአምላክ ማደርና እንደነዚህ ስላሉት ሌሎች አስፈላጊ ባሕርያት ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች በምናገኘው ግልጽ ብሎም ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ትምህርት ላይ ነው። *

የናቡቴ ምሳሌ ጠቃሚ ትምህርት ይሰጠናል (አንቀጽ 11ን ተመልከት)

11. (ሀ) ስለ ናቡቴ የሚገልጸውን ታሪክ አሁን የምንረዳው እንዴት ነው? የዚህ ሰው ምሳሌ ለሁላችንም ጠቃሚ የሆነው እንዴት ነው? (ለ) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የወጡ ጽሑፎቻችን ጥላነት ባላቸው ዘገባዎች ላይ ብዙም የማያተኩሩት ለምንድን ነው? (በዚህ እትም ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።)

11 ታዲያ ስለ ናቡቴ የሚናገረውን ታሪክ አሁን የምንረዳው እንዴት ነው? ይበልጥ ግልጽና ቀላል በሆነ መንገድ ነው። ይህ ጻድቅ ሰው የሞተው ለኢየሱስ ወይም ለቅቡዓኑ ትንቢታዊ ጥላ በመሆኑ ሳይሆን ንጹሕ አቋሙን በመጠበቁ ነው። አንዳንዶች በሥልጣናቸው ተጠቅመው ግፍ ቢያደርሱበትም ለይሖዋ ሕግ ታዝዟል። (ዘኁ. 36:7፤ 1 ነገ. 21:3) ማንኛችንም ብንሆን ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ስደት ሊደርስብን ስለሚችል የእሱ ምሳሌ ትምህርት ይሰጠናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12ን አንብብ።) በመሆኑም ሁሉም ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን እምነት የሚያጠናክር ትምህርት በቀላሉ ሊረዱት፣ ሊያስታውሱትና ከትምህርቱ ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ።

12. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ ታሪኮች ጋር በተያያዘ ምን ድምዳሜ ላይ መድረስ የለብንም? (ለ) ጥልቅ ስለሆኑ ነገሮችም እንኳ ግልጽ ማብራሪያ ማግኘት የቻልነው ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

12 ይህ ሲባል ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች በቀጥታ ከሚያስተላልፉት ትምህርት ውጪ ሌላ  ትርጉም የላቸውም ማለት ነው? አይደለም። አንድ ታሪክ፣ ሌላን ታሪክ እንደሚያስታውሰን ወይም ለሌላ ነገር ምሳሌ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጽሑፎቻችን ላይ ይወጣል። ሆኖም በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ለእውነተኛው ነገር ትንቢታዊ ጥላ እንደሆኑ ተደርጎ በእርግጠኝነት መገለጹ እየቀረ መጥቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ናቡቴ ስደትን ተቋቁሞ እስከ ሞት ድረስ ንጹሕ አቋሙን መጠበቁ ክርስቶስና ቅቡዓኑ ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቃቸውን ያስታውሰናል። ይህ ታሪክ በርካታ የጌታ “ሌሎች በጎች” ያሳዩትን ታማኝነትም ያስታውሰናል። እንዲህ ያለው ግልጽና ቀላል የሆነ ንጽጽር መለኮታዊው ትምህርት ተለይቶ ከሚታወቅባቸው መንገዶች አንዱ ነው። *

የኢየሱስን ምሳሌዎች ቀለል ባለ መንገድ ማብራራት

13. አንዳንዶቹ የኢየሱስ ምሳሌዎች በአሁኑ ወቅት ይበልጥ ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ እንደተብራሩ የሚያሳየው ምንድን ነው?

13 በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ከሚጠቀምባቸው የማስተማሪያ ዘዴዎች መካከል ምሳሌዎች ይገኙበታል። (ማቴ. 13:34) ምሳሌዎች፣ አእምሯችንን በሚያሠራና ልባችንን በሚነካ መንገድ ትምህርቱን ሕያው አድርጎ ለማቅረብ ያስችላሉ። ታዲያ ጽሑፎቻችን የኢየሱስን ምሳሌዎች የሚያብራሩበት መንገድስ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ቀላልና ግልጽ ሆኗል? ምን ጥያቄ አለው! ኢየሱስ ስለ እርሾው፣ ስለ ሰናፍጩ ዘርና ስለ መረቡ የተናገራቸውን ምሳሌዎች በተመለከተ በሐምሌ 15, 2008 መጠበቂያ ግንብ ላይ ይበልጥ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ በማግኘታችን አልተደሰትንም? እነዚህ ምሳሌዎች ከአምላክ መንግሥት እና በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮችን በመሰብሰቡ ሥራ ከተገኘው አስደናቂ ስኬት ጋር የተያያዙ እንደሆኑ የበለጠ ግልጽ ሆኖልናል።

14. (ሀ) ስለ ደጉ ሳምራዊ የሚናገረውን ምሳሌ እንዴት እናብራራው ነበር? (ለ) ኢየሱስ የተናገረውን ምሳሌ አሁን የምንረዳው እንዴት ነው?

14 ኢየሱስ ስለተናገራቸው ዝርዝር ሐሳብ የያዙ ታሪኮች ወይም ምሳሌዎችስ ምን ማለት ይቻላል? እርግጥ አንዳንዶቹ፣ ምሳሌያዊ ትርጉም እና ትንቢታዊ ፍጻሜ አላቸው፤ ሌሎቹ ደግሞ ተግባራዊ መሆን በሚችል ትምህርት ላይ ያተኮሩ ናቸው። ይሁንና እንዴት መለየት እንችላለን? ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የዚህ ጥያቄ መልስ ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ የተናገረውን ምሳሌ እንዴት እናብራራ እንደነበር እንመልከት። (ሉቃስ 10:30-37) ሳምራዊው ሰው ኢየሱስን፣ ከኢየሩሳሌም ቁልቁል ወደ ኢያሪኮ የሚወስደው መንገድ በኤደን ከተነሳው ዓመፅ ወዲህ የሰው ዘር የተከተለውን እያሽቆለቆለ የሚሄድ ጎዳና፣ መንገዱ ላይ ያሉት ዘራፊዎች ትላልቅ ኩባንያዎችንና ስግብግብ ነጋዴዎችን፣ ካህኑና ሌዋዊው ደግሞ ሕዝበ ክርስትናን እንደሚያመለክቱ በ1924 በወጣ አንድ መጠበቂያ ግንብ ላይ ተብራርቶ ነበር። በዛሬው ጊዜ ግን ጽሑፎቻችን ይህን ምሳሌ የሚጠቀሙት፣ ክርስቲያኖች በሙሉ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች በተለይም በመንፈሳዊ ሁኔታ ድጋፍ የሚፈልጉትን ያለ አድልዎ እንዲረዱ ለማበረታታት ነው። ይሖዋ ትምህርቶቹን ለእኛ ግልጽ ማድረጉ አያስደስተንም?

15. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

15 በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ኢየሱስ ስለ አሥሩ ደናግል የተናገረውን ምሳሌ እንመረምራለን። (ማቴ. 25:1-13) ኢየሱስ፣ ትልቅ ትርጉም ያለውን ይህን ምሳሌ በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚኖሩ ተከታዮቹ እንዲረዱት የፈለገው እንዴት ነው? በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ግዑዝ ነገርና ክንውን ምሳሌያዊ ትርጉም ያለው ትንቢታዊ ጥላ እንደሆነ እንድናስብ ፈልጎ ነበር? ወይስ ተከታዮቹ ከምሳሌው የሚያገኙትን ጠቃሚ ትምህርት በመጨረሻዎቹ ቀናት እንዲጠቀሙበት አስቦ ነው? እስቲ እንመልከት።

^ አን.4 ቀለል ባለ ቋንቋ የተዘጋጀው እትም በእንግሊዝኛ መውጣት የጀመረው ሐምሌ 2011 ነው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ይህ እትም በሌሎች ጥቂት ቋንቋዎችም ተዘጋጅቷል።

^ አን.5 የተሻሻለውን እትም በሌሎች ቋንቋዎችም ለማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ ነው።

^ አን.10 ለምሳሌ በእምነታቸው ምሰሏቸው የተባለው መጽሐፍ ስለ 14 የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች በጥልቀት ያብራራል። መጽሐፉ የሚያተኩረው በምሳሌያዊ ወይም በትንቢታዊ ትርጉሞች ላይ ሳይሆን ትምህርቱን ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይ ነው።

^ አን.12 እርግጥ ነው፣ የአምላክ ቃል “ለመረዳት የሚከብዱ” የሚመስሉ ትምህርቶችንም ይዟል፤ ከእነዚህ መካከል ጳውሎስ የጻፋቸው አንዳንድ ሐሳቦች ይገኙበታል። ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን በሙሉ የመራቸው የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ነው። ይኸው መንፈስ በዛሬው ጊዜ የምንገኝ እውነተኛ ክርስቲያኖች መለኮታዊ እውነቶችን እንድንገነዘብ አስችሎናል፤ ይህ መንፈስ የመረዳት ችሎታችን ውስን ቢሆንም፣ ‘የአምላክ ጥልቅ ነገሮች’ እንኳ ይበልጥ ቀላልና ግልጽ እንዲሆኑልን አድርጓል።—2 ጴጥ. 3:16, 17፤ 1 ቆሮ. 2:10