በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  የካቲት 2015

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የሽቶ መዓዛ የሚረብሻቸው ወንድሞችና እህቶች እንዳይቸገሩ ለመርዳት ምን ማድረግ ይቻላል?

የሽቶ መዓዛ የሚረብሻቸው ሰዎች አስቸጋሪ የሆነ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። እንደዚህ ዓይነቶቹ ግለሰቦች በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር ስለሚገናኙ ከሽቶ መራቅ ቀላል ላይሆንላቸው ይችላል። ሆኖም ክርስቲያኖች በሚያደርጓቸው ሳምንታዊ የጉባኤ ስብሰባዎችና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ወንድሞችና እህቶች ሽቶና ጥሩ መዓዛ ያላቸው ሌሎች ነገሮችን እንዳይጠቀሙ መጠየቅ ይቻል እንደሆነ አንዳንዶች ጥያቄ አቅርበዋል።

ማንኛውም ክርስቲያን፣ ሌሎች በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ከባድ እንዲሆንባቸው ማድረግ እንደማይፈልግ የተረጋገጠ ነው። ሁላችንም በስብሰባዎቻችን ላይ የሚቀርቡት ማበረታቻዎች ያስፈልጉናል። (ዕብ. 10:24, 25) በመሆኑም የሽቶ መዓዛ በጣም ስለሚረብሻቸው በስብሰባ ላይ ለመገኘት የሚቸገሩ ክርስቲያኖች፣ በጉዳዩ ላይ ከጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር መወያየት ሊፈልጉ ይችላሉ። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ወንድሞችንና እህቶችን የሽቶ አጠቃቀም በተመለከተ ሕግ ማውጣት ቅዱስ ጽሑፋዊም ሆነ ተገቢ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ ያም ቢሆን የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ በዚህ ረገድ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ሁኔታ የጉባኤው አባላት እንዲገነዘቡ ለማድረግ ጉዳዩን የተመለከተ መረጃ መስጠት ይችሉ ይሆናል። የጉባኤ ሽማግሌዎች ያሉትን ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት፣ በአገልግሎት ስብሰባ ወቅት ለጉባኤው እንደሚያስፈልግ ተጠቀሙበት በሚለው ክፍል ላይ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከዚህ ቀደም ከወጡ ጽሑፎች የተወሰዱ ሐሳቦችን ለማቅረብ ይወስኑ ይሆናል፤ አለዚያም ጉዳዩን የተመለከተ ማስታወቂያ በጥበብ ለመናገር ሊመርጡ ይችላሉ። * ይሁን እንጂ ሽማግሌዎች እንዲህ ዓይነቱን ማስታወቂያ አዘውትረው መናገር አይችሉም። ስለ ችግሩ የማያውቁ፣ ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎችና እንግዶች በስብሰባዎቻችን ላይ ምንጊዜም መኖራቸው አይቀርም፤ እነዚህ ሰዎች እንዲሳቀቁ ደግሞ አንፈልግም። ማንም ሰው ቢሆን ልከኛ በሆነ መንገድ ሽቶ በመጠቀሙ እንዲሸማቀቅ መደረግ የለበትም።

ችግሩ ባለባቸው ጉባኤዎች ውስጥ ሁኔታው የሚፈቅድ ከሆነ የሽማግሌዎች አካል፣ የሽቶ መዓዛ የሚረብሻቸው ሰዎች በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ከሌሎች ተለይተው እንዲቀመጡ ዝግጅት ሊያደርግ ይችል ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ የድምፅ መሣሪያ የተገጠመለት ሌላ ክፍል ይኖር ይሆናል፤ እነዚህ ወንድሞች እዚያ ሆነው ከስብሰባው ጥቅም ማግኘት ይችላሉ። ጉባኤው ለችግሩ መፍትሔ ማግኘት ካቃተውና ሽቶ የሚረብሻቸው ግለሰቦች በጣም ከተቸገሩ፣ ከቤታቸው መውጣት ለማይችሉ ወንድሞች እንደሚደረገው ሁሉ ለእነዚህ ክርስቲያኖችም በስብሰባ ላይ የሚቀርበውን ትምህርት መቅዳት አሊያም ቤታቸው ሆነው መከታተል እንዲችሉ ትምህርቱን በስልክ ማስተላለፍ ይቻል ይሆናል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ ወንድሞችና እህቶች ትላልቅ ስብሰባ ላይ በሚገኙበት ጊዜ ለዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ በጽሑፎቻችን ላይ ማበረታቻ ሲወጣ ቆይቷል። አብዛኞቹ ትላልቅ ስብሰባዎች የሚደረጉት ዝግ በሆኑ መሰብሰቢያ ቦታዎች ስለሆነ ተሰብሳቢዎች በእነዚህ ወቅቶች ኃይለኛ ሽቶዎች ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ሐሳብ ቀርቧል። በተለይም ከትላልቅ ስብሰባዎች ጋር በተያያዘ፣ ሽቶ ለሚያስቸግራቸው ወንድሞች ስብሰባዎቹ በሚደረጉባቸው ቦታዎች ለብቻቸው ቦታ ማዘጋጀት ስለማይቻል ሌሎቹ ተሰብሳቢዎቹ አሳቢነት እንዲያሳዩ ማበረታቻ ተሰጥቷል። ይሁን እንጂ ይህ መመሪያ የተሰጠው ለጉባኤ ስብሰባዎች አጠቃላይ ደንብ እንዲሆን ታስቦ አይደለም፤ ደግሞም በዚህ መንገድ ሊወሰድ አይገባውም።

በዚህ ሥርዓት ውስጥ እስካለን ድረስ ሁላችንም የወረስነው አለፍጽምና ባስከተላቸው መዘዞች የተነሳ መሠቃየታችን አይቀርም። በመሆኑም ሌሎች ሥቃያችንን ለማቅለል የሚያደርጉትን ጥረት በጣም እናደንቃለን! አንድ የእምነት ባልንጀራቸው በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ቀላል እንዲሆንለት ሲሉ ሽቶ ወይም ጥሩ መዓዛ ያላቸው ሌሎች ነገሮችን ከመጠቀም መቆጠብ ለአንዳንዶች የራስን ጥቅም መሥዕዋት ማድረግ ሊጠይቅ ይችላል። ሆኖም ፍቅር እንዲህ እንድናደርግ ያነሳሳናል።

 ጳንጥዮስ ጲላጦስ በሕይወት የኖረ ሰው መሆኑን ዓለማዊ ምንጮች ይደግፋሉ?

በዚህ ጽላት ላይ የጲላጦስ ስም በላቲን ተቀርጿል

ጳንጥዮስ ጲላጦስ፣ ኢየሱስ ለፍርድ በቀረበበት ወቅት እንዲሁም ከመገደሉ ጋር ተያይዞ በነበረው ሚና የተነሳ በመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ዘንድ ይታወቃል። (ማቴ. 27:1, 2, 24-26) ይሁን እንጂ የጲላጦስ ስም በዘመኑ በተጻፉ ሌሎች የታሪክ መዛግብት ላይም ብዙ ጊዜ ተጠቅሷል። ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ እንደሚናገረው ስለ እሱ የሚገልጹት ዓለማዊ የታሪክ መዛግብት “ስለ ማንኛውም ሮማዊ የይሁዳ አገረ ገዥ ከተጻፈው ይበልጥ ብዙና ዝርዝር ሐሳብ የያዙ ናቸው።”

የጲላጦስ ስም በተደጋጋሚ የሚገኘው በአይሁዳዊው የታሪክ ምሁር በጆሴፈስ ጽሑፎች ላይ ነው፤ ጆሴፈስ፣ ጲላጦስ በይሁዳ ሲገዛ ካጋጠሙት ችግሮች ጋር የተያያዙ ሦስት ክንውኖችን ጠቅሷል። አይሁዳዊው የታሪክ ምሁር ፋይሎ ደግሞ አራተኛ ክንውን ጽፏል። የሮማውያን ነገሥታትን ታሪክ የዘገበው ሮማዊው ጸሐፊ ታሲተስም በጢባርዮስ የግዛት ዘመን ጳንጥዮስ ጲላጦስ፣ ኢየሱስ እንዲገደል ትእዛዝ መስጠቱን አስፍሯል።

በ1961 በቂሳርያ፣ እስራኤል በሚገኘው ጥንታዊ የሮማውያን ቲያትር ቤት የቁፋሮ ሥራ ሲያከናውኑ የነበሩ የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች የጲላጦስ ስም በላቲን በግልጽ የተጻፈበት የድንጋይ ጽላት አግኝተዋል። በቁፋሮ የተገኘው የጽላቱ ስባሪ (በሥዕሉ ላይ የሚታየው) ቢሆንም መጀመሪያ ላይ የሚከተለውን ሐሳብ የያዘ እንደነበረ ይታሰባል፦ “የይሁዳ አገረ ገዥ ጳንጥዮስ ጲላጦስ (ይህን) ታይቤሪየም ለተከበሩ አማልክት ሰጥቷል።” እዚህ ላይ የተጠቀሰው ሕንፃ የሮም ንጉሠ ነገሥት ለሆነው ለጢባርዮስ ክብር የተሰጠ ቤተ መቅደስ ሳይሆን አይቀርም።

አንዲት እህት፣ ወንድ አስፋፊ ባለበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምትመራ ከሆነ ራሷን መሸፈን ያስፈልጋታል?

ሐምሌ 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ ላይ በወጣ “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ላይ አንዲት እህት፣ የተጠመቀም ሆነ ያልተጠመቀ ወንድ አስፋፊ ባለበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምትመራ ከሆነ ራሷን መሸፈን እንደሚኖርባት ተገልጾ ነበር። ይሁንና በዚህ ርዕስ ላይ የተደረገ ተጨማሪ ምርምር ቀደም ሲል በወጣው መመሪያ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ አመላክቷል።

አንዲት እህት፣ በቋሚነት የሚካሄድ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስትመራ አንድ የተጠመቀ አስፋፊ ቢገኝ የራስ መሸፈኛ ማድረግ እንደሚያስፈልጋት ጥርጥር የለውም። እንዲህ ማድረጓ ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ላቋቋመው የራስነት ዝግጅት አክብሮት እንዳላት ያሳያል፤ ምክንያቱም ጥናቱን ስትመራ ወንድሞች ሊያከናውኑት የሚገባውን ኃላፊነት እየተወጣች ነው። (1 ቆሮ. 11:5, 6, 10) ሌላው አማራጭ ደግሞ አብሯት ያለው ወንድም ጥናቱን ለመምራት ብቁ ከሆነና አቅሙ ከፈቀደለት ጥናቱን እሱ እንዲመራ ማድረግ ነው።

በሌላ በኩል ግን እህት በቋሚነት የሚካሄድ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስትመራ አብሯት ያለው ያልተጠመቀ አስፋፊ ከሆነ የራስ መሸፈኛ የማድረግ ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ የለባትም፤ በጥናቱ ላይ አብሯት ያለው ባሏ ከሆነ ግን ራሷን ትሸፍናለች። ይሁን እንጂ አንዳንድ እህቶች አብሯቸው ያለው ያልተጠመቀ አስፋፊ ቢሆንም የራስ መሸፈኛ እንዲያደርጉ ሕሊናቸው ይገፋፋቸው ይሆናል።

^ አን.2 ስለዚህ ጉዳይ መረጃ ለማግኘት “ኤም ሲ ኤስ ያለባቸውን ሰዎች መርዳት” የሚለውን በጥቅምት 2000 ንቁ! ከገጽ 8-10 ላይ የወጣውን ርዕስ ተመልከት።