በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  የካቲት 2015

ለአገልግሎት ያላችሁ ቅንዓት እንዳይቀዘቅዝ ጥረት አድርጉ

ለአገልግሎት ያላችሁ ቅንዓት እንዳይቀዘቅዝ ጥረት አድርጉ

በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ካሉት ሥራዎች ሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ሥራ ምሥራቹን መስበክ ነው። የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆንህ መጠን ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መሳተፍን እንደ ታላቅ ክብር እንደምትቆጥረው የተረጋገጠ ነው። ይሁን እንጂ አቅኚዎችም ሆኑ አስፋፊዎች ለአገልግሎት ያላቸውን ቅንዓት ይዘው መቀጠል አንዳንድ ጊዜ ፈታኝ ይሆንባቸዋል ቢባል መስማማትህ አይቀርም።

ለአገልግሎት ያላችሁ ቅንዓት እንዳይቀዘቅዝ ምን ሊረዳችሁ ይችላል?

አንዳንድ አስፋፊዎች ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ ሊያነጋግራቸው ፈቃደኛ የሆነ ሰው ማግኘት አዳጋች ይሆንባቸዋል። እንዲያውም አብዛኞቹ ሰዎች ቤታቸው ላይገኙ ይችላሉ። የቤቱን ባለቤቶች ስናገኛቸው ደግሞ ለመንግሥቱ መልእክት የሚሰጡት ምላሽ ግድ የለሽነት የሚንጸባረቅበት ሊሆን ይችላል፤ አልፎ ተርፎም ይቃወሙን ይሆናል። ሌሎች አስፋፊዎች ደግሞ የሚሰብኩበት ክልል በጣም ሰፊና ፍሬያማ ቢሆንም ክልሉን በተጣራ ሁኔታ መሸፈን ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በሌላ በኩል አንዳንድ የጉባኤ አባላት፣ ካሰቡት በላይ ለረጅም ዓመታት ሲሰብኩ በመቆየታቸው ተስፋ ቆርጠዋል።

ሁሉም የይሖዋ ሕዝቦች ለስብከቱ ሥራ ያላቸውን ቅንዓት ሊያቀዘቅዙ የሚችሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች የሚያጋጥሟቸው መሆኑ ሊያስደንቀን ይገባል? በፍጹም። ደግሞስ “ክፉው” ሰይጣን ዲያብሎስ በሚገዛው ዓለም ውስጥ ሕይወት አድን የሆነውን የአምላክን የእውነት መልእክት ማወጅ ቀላል እንዲሆንልን መጠበቅ ምክንያታዊ ነው?—1 ዮሐ. 5:19

አንተ በግልህ ምሥራቹን በማወጅ ረገድ የሚያጋጥምህ ተፈታታኝ ሁኔታ ምን ይሁን ምን እንድታሸንፈው ይሖዋ ሊረዳህ እንደሚችል እርግጠኛ ሁን። ይሁንና ለክርስቲያናዊው አገልግሎት ያለህን ቅንዓት ለማሳደግ ምን ማድረግ ትችላለህ? እስቲ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦችን እንመርምር።

ብዙም ተሞክሮ የሌላቸውን መርዳት

በየዓመቱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክር ይሆናሉ። ራስህን ለአምላክ ወስነህ የተጠመቅከው በቅርቡ ከሆነ ከአንተ  ይበልጥ ለረጅም ጊዜ ሲሰብኩ የኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸውን ተሞክሮ ቢያካፍሉህ ደስ እንደሚልህ ጥርጥር የለውም። የመንግሥቱ አስፋፊ ከሆንክ ብዙ ዓመታት አልፈው ከሆነ ደግሞ አዳዲሶችን ማሠልጠን ተገቢ እንዲሁም የሚክስ እንደሆነ አይሰማህም?

ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ውጤታማ ወንጌላውያን መሆን እንዲችሉ መመሪያ ማግኘት እንደሚያስፈልጋቸው ስለተገነዘበ ሥራው እንዴት መከናወን እንዳለበት አሳይቷቸዋል። (ሉቃስ 8:1) በዛሬው ጊዜም ቢሆን ሌሎችን ውጤታማ አገልጋዮች እንዲሆኑ ማሠልጠን ግድ ይላል።

አንድ አዲስ አስፋፊ በአገልግሎት ስለተካፈለ ብቻ የማስተማር ችሎታ እንደሚያዳብር ሊሰማን አይገባም። አስፋፊው፣ ደግና አፍቃሪ ከሆነ አሠልጣኝ በግለሰብ ደረጃ መመሪያ ማግኘት ያስፈልገዋል። እንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና ብዙም ተሞክሮ የሌለው አስፋፊ (1) የመግቢያ ሐሳብ መዘጋጀትና መለማመድ፣ (2) ከቤት ወደ ቤትም ሆነ መንገድ ላይ ከሰዎች ጋር ውይይት መጀመር፣ (3) ጽሑፍ ማስተዋወቅ፣ (4) ፍላጎት ያሳየውን ግለሰብ ተመልሶ መጠየቅ እንዲሁም (5) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር የሚችለው እንዴት እንደሆነ ማሳየትን ይጨምራል። ሠልጣኙ፣ ተሞክሮ ያለው ወንድም በአገልግሎት ላይ የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎች መመልከትና መኮረጅ ከቻለ ጥሩ ውጤት መገኘቱ አይቀርም። (ሉቃስ 6:40) አዲሱ አስፋፊ፣ ከሚያዳምጠውና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ሊረዳው ከሚችል ሰው ጋር በማገልገሉ እንደሚደሰት ጥርጥር የለውም። ብዙም ተሞክሮ የሌለው አስፋፊ፣ አድናቆትና ጠቃሚ ሐሳብ ማግኘቱም እንደሚጠቅመው የታወቀ ነው።—መክ. 4:9, 10

ከአገልግሎት ጓደኛችሁ ጋር ተጨዋወቱ

አንዳንድ ቀን በመስክ አገልግሎት ላይ ከሰዎች ጋር ውይይት ለመጀመር ምንም ያህል ጥረት ብታደርጉም አይሳካላችሁ ይሆናል፤ በዚያን ዕለት ጥሩ ጭውውት የምታደርጉት ከአገልግሎት ጓደኛችሁ ጋር ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲሰብኩ የላካቸው “ሁለት ሁለት” አድርጎ መሆኑን አስታውሱ። (ሉቃስ 10:1) ደቀ መዛሙርቱ አብረው በሚያገለግሉበት ወቅት እርስ በርስ መበረታታት ይችሉ ነበር። በመሆኑም ከእምነት ባልንጀራችን ጋር በአገልግሎት የምናሳልፈው ጊዜ “እርስ በርሳችን እንድንበረታታ” ጥሩ አጋጣሚ ይሰጠናል።—ሮም 1:12

ስለ የትኞቹ ነገሮች ማውራት ትችላላችሁ? ከሁለት አንዳችሁ በአገልግሎት ላይ በቅርቡ ያገኛችሁት የሚያበረታታ ተሞክሮ አለ? በግል ወይም በቤተሰብ ጥናታችሁ ላይ አንድ ጠቃሚ ነጥብ አግኝታችኋል? በስብሰባ ላይ የሚያንጽ ሐሳብ ሰምታችኋል? አንዳንድ ጊዜ፣ አገልግሎት የምትወጡት በአብዛኛው አብሯችሁ ከማያገለግል አስፋፊ ጋር ሊሆን ይችላል። ታዲያ ይህ አስፋፊ ወደ እውነት የመጣው እንዴት እንደሆነ ታውቃላችሁ? በይሖዋ ድርጅት ውስጥ መሆኑን ያሳመነው ምንድን ነው? ምን መብቶች ወይም ተሞክሮዎች አሉት? ምናልባት እናንተም በይሖዋ አገልግሎት ያገኛችሁትን ተሞክሮ ልታካፍሉት ትችሉ ይሆናል። በመስኩ ላይ የምናገኘው ምላሽ ምንም ሆነ ምን፣ ከአንድ ክርስቲያን ጋር አብረን ማገልገላችን ‘እርስ በርስ ለመተናነጽ’ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥርልናል።—1 ተሰ. 5:11

 ቋሚ የሆነ ጥሩ የጥናት ፕሮግራም ይኑራችሁ

ለአገልግሎቱ ያላችሁ ቅንዓት እንዳይቀዘቅዝ ለማድረግ ጥሩ የጥናት ልማድ ማዳበርና በዚህ ልማዳችሁ መቀጠል አስፈላጊ ነው። “ታማኝና ልባም ባሪያ” በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ ትምህርት ይሰጠናል። (ማቴ. 24:45) ስለዚህ መንፈሳዊ ምግብ ስትመገቡ ልታጠኗቸው የምትችሉ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች አሉ። የግል ጥናት ልናደርግ ከምንችልባቸው ርዕሶች አንዱን እንደ ምሳሌ እንመልከት፦ ‘የመንግሥቱ ስብከት ሥራ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?’ በሚለው ጥያቄ ላይ ምርምር ማድረግ እንችላለን። አንዳንዶቹ ምክንያቶች በዚህ ርዕስ ላይ በሚገኘው ሣጥን ውስጥ ተዘርዝረዋል።

በሣጥኑ ውስጥ የተዘረዘሩትን ነጥቦች መመርመርህ በስብከቱ ሥራ በቅንዓት ለመቀጠል ሊያነሳሳህ ይችላል። በሣጥኑ ውስጥ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ ሌሎች ምክንያቶችን መጥቀስ ትችላለህ? ስለዚህ ጉዳይ በግል ጥናትህ ላይ ለምን ምርምር አታደርግም? ከዚያም የስብከቱ ሥራ አስፈላጊ እንደሆነ በሚያሳዩት ምክንያቶችና ድጋፍ ሆነው በቀረቡት ጥቅሶች ላይ አሰላስል። እንዲህ ማድረግህ ለአገልግሎቱ ያለህን ቅንዓት እንደሚያጠናክረው ጥርጥር የለውም።

የሚቀርቡትን ሐሳቦች ለመቀበል ዝግጁ ሁኑ

የይሖዋ ድርጅት አገልግሎታችንን ለማሻሻል የሚረዱ ጠቃሚ ሐሳቦችን አዘውትሮ ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል፣ ከቤት ወደ ቤት ከመስበክ በተጨማሪ ደብዳቤ በመጻፍ፣ በስልክ፣ መንገድ ላይ ወይም ሕዝብ በሚበዛባቸው ሌሎች ቦታዎች፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድ እና በንግድ አካባቢዎች ምሥራቹን መስበክ እንደምንችል ሐሳብ ተሰጥቶናል። በተጨማሪም እምብዛም ባልተሠራበት የአገልግሎት ክልል ለመመሥከር ሁኔታዎቻችንን ማመቻቸት እንችል ይሆናል።

ታዲያ እነዚህን ሐሳቦች ለመቀበል ፈጣን ነህ? አንዳንዶቹን ሥራ ላይ ለማዋል ሞክረህ ታውቃለህ? ብዙዎች እንዲህ በማድረጋቸው ባገኙት ውጤት በጣም ተደስተዋል። እስቲ ሦስት ምሳሌዎችን እንመልከት።

የመጀመሪያው ምሳሌ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት ማስጀመር እንደሚቻል በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጣው ሐሳብ ያስገኘውን ውጤት የሚመለከት ነው። ይህ ምክር  ኤፕርል የምትባል አንዲት እህት ሦስት የሥራ ባልደረቦቿ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ እንድትጋብዛቸው አነሳስቷታል። ሦስቱም ግብዣዋን ተቀብለው ማጥናትና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ሲጀምሩ በጣም የተገረመች ከመሆኑም ሌላ ደስታዋ ወደር አልነበረውም።

ሁለተኛው ምሳሌ፣ መጽሔቶቻችንን ከማበርከት ጋር የተያያዘ ነው። በመጽሔቶቻችን ላይ የቀረቡ ርዕሰ ጉዳዮች ትኩረታቸውን ሊስቧቸው የሚችሉ ሰዎችን እንድንፈልግ ስንበረታታ ቆይተናል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች፣ የመኪና ጎማዎችን የሚመለከት ርዕስ የያዘውን ንቁ! በአንድ አካባቢ ላሉ የጎማ ድርጅቶች ሥራ አስኪያጆች በሙሉ እንዳበረከተላቸው ሪፖርት አድርጓል። በተጨማሪም እሱና ባለቤቱ “የሐኪሞችን ችግር ተረዱላቸው” የሚለውን የንቁ! እትም በወረዳው ውስጥ በሚገኙ ከ100 በላይ ክሊኒኮች አስተዋውቀዋል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ እንዲህ ይላል፦ “ይህን ማድረጋችን ሰዎች እኛንም ሆነ ጽሑፎቻችንን እንዲያውቁ ለማድረግ በጣም ጠቅሞናል። እዚያ ከምናገኛቸው ሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ከመሠረትን በኋላ ለእነሱ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ የበለጠ አጋጣሚ ተፈጥሮልናል።”

ሦስተኛው ምሳሌ ደግሞ በስልክ ከመመሥከር ጋር የተያያዘ ነው። ጁዲ የምትባል አንዲት እህት በስልክ ስለ መመሥከር ለተሰጠው ማበረታቻ አድናቆቷን ለመግለጽ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት ጽፋለች። ብዙ የጤና ችግሮች ያሉባቸውና የ86 ዓመት አረጋዊት የሆኑት እናቷ በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ አዘውትረው እንደሚካፈሉ ገልጻለች፤ እናቷ አንዲት የ92 ዓመት አረጋዊትን በስልክ መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት በመቻላቸው በጣም ተደስተዋል።

በጽሑፎቻችን ላይ የሚወጡት የስብከቱን ሥራ የሚመለከቱ ጠቃሚ ሐሳቦች በእርግጥም ውጤት ያስገኛሉ። በመሆኑም ተግባራዊ አድርጓቸው! ከአገልግሎት የምታገኙት ደስታና ቅንዓታችሁ እንዳይቀዘቅዝ ሊረዷችሁ ይችላሉ።

ምክንያታዊ ግቦች አውጡ

በስብከቱ ሥራችን የምናገኘው ስኬት በዋነኝነት የሚለካው ባበረከትነው ጽሑፍ ብዛት፣ መጽሐፍ ቅዱስን በምናስጠናቸው ሰዎች ቁጥር ወይም የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ በረዳናቸው ሰዎች ብዛት አይደለም። ለመሆኑ ኖኅ ከቅርብ ቤተሰቦቹ ውጪ የይሖዋ አምላኪዎች እንዲሆኑ ስንት ሰዎችን ረድቷል? ማንንም አልረዳም። ያም ቢሆን ውጤታማ ሰባኪ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችን ነው።—1 ቆሮ. 4:2

ብዙ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ለስብከቱ ሥራ ያላቸውን ቅንዓት ለማቀጣጠል ምክንያታዊ ግቦች ማውጣት ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዘበዋል። የትኞቹን ግቦች ማውጣት ይቻላል? በዚህ ርዕስ ላይ ባለው ሣጥን ውስጥ የተወሰኑት ተጠቅሰዋል።

አገልግሎታችሁን የሚክስና ውጤታማ ለማድረግ እንዲረዳችሁ ይሖዋን በጸሎት ጠይቁት። ግባችሁ ላይ ስትደርሱ፣ አንድ ነገር ማከናወን የሚያስገኘውን ደስታ ትቀምሳላችሁ፤ እንዲሁም ምሥራቹን ለመስበክ የቻላችሁትን ሁሉ እያደረጋችሁ እንዳላችሁ ማወቅ የሚያስገኘውን እርካታ ልታጣጥሙ ትችላላችሁ።

እውነት ነው፣ ምሥራቹን መስበክ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ለመሆን ልታደርጓቸው የምትችሏቸው ነገሮች አሉ። ከአገልግሎት ጓደኛችሁ ጋር እርስ በርስ ተበረታቱ፤ ቋሚ የሆነ ጥሩ የጥናት ልማድ ይኑራችሁ፤ ታማኙ ባሪያ የሚያቀርባቸውን ጠቃሚ ሐሳቦች ተግባራዊ አድርጉ፤ እንዲሁም ምክንያታዊ ግቦች አውጡ። ከሁሉም በላይ ደግሞ አምላክ ከምሥክሮቹ አንዱ በመሆን ምሥራቹን የማወጅ ወደር የሌለው መብት እንደሰጣችሁ አስታውሱ። (ኢሳ. 43:10) በአገልግሎቱ ያላችሁን ቅንዓት ይዛችሁ ስትቀጥሉ ታላቅ ደስታ ታገኛላችሁ!