በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ጥር 2015

ትዳራችሁ ጠንካራና አስደሳች እንዲሆን ጥረት አድርጉ

ትዳራችሁ ጠንካራና አስደሳች እንዲሆን ጥረት አድርጉ

“[ይሖዋ] ቤትን ካልሠራ፣ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ።”—መዝ. 127:1ሀ

1-3. ባለትዳሮች ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ምስል ተመልከት።)

“ከልባችሁ ጥረት የምታደርጉና ትዳራችሁ እንዲሰምር እንደምትፈልጉ የምታሳዩ ከሆነ ይሖዋ ይባርካችኋል።” ይህን የተናገረው ካገባ 38 ዓመት የሆነውና ጥሩ ትዳር ያለው አንድ ወንድም ነው። በእርግጥም ባልና ሚስት አብረው አስደሳች ጊዜ ሊያሳልፉ እንዲሁም በአስቸጋሪ ጊዜያት ሊደጋገፉ ይችላሉ።ምሳሌ 18:22

2 ያም ሆኖ ባለትዳሮች “በሥጋቸው ላይ መከራ” ቢያጋጥማቸው የሚያስገርም አይሆንም። (1 ቆሮ. 7:28) ለምን? በዕለት ተዕለት ሕይወት የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ብቻ እንኳ በትዳራቸው ላይ ጫና ሊያሳድሩ ይችላሉ። ፍጽምና የጎደላቸው በመሆናቸው አንዳቸው የሌላውን ስሜት የሚጎዳ ነገር ይናገሩ፣ የሌላውን ሐሳብ መረዳት ይከብዳቸው አሊያም ሐሳባቸውን በሚገባ አይገልጹ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ጥሩ በሆኑ ትዳሮች ውስጥም እንኳ ችግሮች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል። (ያዕ. 3:2, 5, 8) በርካታ ባለትዳሮች ደግሞ ልጆቻቸውን ከመንከባከብ በተጨማሪ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን የሚያሟጥጥ ሥራ ለመሥራት ይገደዳሉ። አንዳንድ ባልና ሚስት ትዳራቸውን ለማጠናከር የሚያስፈልጋቸውን ጊዜ እንዳያገኙ ውጥረትና ድካም እንቅፋት ይሆኑባቸዋል። በኢኮኖሚ፣ በጤና ወይም በሌሎች ችግሮች የተነሳ አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ፍቅርና አክብሮት እየተሸረሸረ ሊሄድ ይችላል። ከዚህም  በተጨማሪ ጥሩ መሠረት ያለው የሚመስል ትዳር እንኳ እንደ ዝሙት፣ ብልግና፣ ጠላትነት፣ ጠብ፣ ቅናት፣ በቁጣ መገንፈል፣ የከረረ ጭቅጭቅና መከፋፈል ባሉት “የሥጋ ሥራዎች” ሊናጋ ይችላል።ገላ. 5:19-21

3 ከዚህም ሌላ “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” በስፋት የሚታዩት ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅባቸውና አምላካዊ ፍርሃት የማይታይባቸው ባሕርያት ለትዳር ጠንቅ ናቸው። (2 ጢሞ. 3:1-4) በዚህ ላይ ደግሞ ትዳርን ለማፍረስ ቆርጦ የተነሳ አንድ ክፉ ጠላት አለ። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል።—1 ጴጥ. 5:8፤ ራእይ 12:12

4. ትዳርን ጠንካራና አስደሳች ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

4 በጃፓን የሚኖር አንድ ባለትዳር እንዲህ ብሏል፦ “ከገንዘብ ጋር በተያያዘ በጣም የሚያስጨንቅ ሁኔታ አጋጥሞኝ ነበር። ከዚህም ሌላ ከባለቤቴ ጋር ሐሳባችንን በግልጽ አንወያይም ነበር፤ በመሆኑም እሷም በጣም ተረብሻ ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ በቅርቡ ከባድ የጤና ችግር አጋጠማት። ውጥረት በሚፈጥሩት በእነዚህ ሁኔታዎች የተነሳ አንዳንድ ጊዜ እንጋጭ ነበር።” በትዳር ውስጥ አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች መፈጠራቸው አይቀሬ ቢሆንም እነዚህን ችግሮች መወጣት የማይቻል ነገር አይደለም። ባለትዳሮች በይሖዋ እርዳታ ትዳራቸውን ጠንካራና አስደሳች ማድረግ ይችላሉ። (መዝሙር 127:1ን አንብብ።) በዚህ ርዕስ ላይ፣ ጠንካራና ዘላቂ ትዳር ለመገንባት የሚረዱ አምስት ነገሮችን እንመለከታለን፤ እነዚህን ነገሮች ቤት ለመገንባት በምንጠቀምበት ጡብ ልንመስላቸው እንችላለን። ጡቦቹን ለማያያዝ ፍቅር ምን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም እናያለን።

በትዳራችሁ ውስጥ ይሖዋ እንዲኖር አድርጉ

5, 6. ባልና ሚስት በትዳራቸው ውስጥ ይሖዋ እንዲኖር ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

5 ጋብቻን ላቋቋመው አምላክ ታማኝ መሆንና ለእሱ መገዛት ጠንካራ ትዳር ለመገንባት የሚያስችል የመሠረት ድንጋይ ነው። (መክብብ 4:12ን አንብብ።) ባልና ሚስት በትዳራቸው ውስጥ አምላክ እንዲኖር ለማድረግ ፍቅር የሚንጸባረቅባቸውን የይሖዋን መመሪያዎች መከተል ይኖርባቸዋል። አምላክ ለጥንት ሕዝቦቹ “ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዘወር ብትል ጆሮህ ከኋላህ፣ ‘መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ’ የሚል ድምፅ ይሰማል” እንዳላቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢሳ. 30:20, 21) በዛሬው ጊዜ ያሉ ባለትዳሮች የአምላክን ቃል አብረው በማንበብ የይሖዋን ድምፅ ‘መስማት’ ይችላሉ። (መዝ. 1:1-3) በተጨማሪም አስደሳችና በመንፈሳዊ የሚያንጽ የቤተሰብ አምልኮ ትዳርን ለማጠናከር ይረዳል። የሰይጣን ዓለም የሚያዥጎደጉደውን ጥቃት የሚቋቋም ትዳር ለመገንባት የሚረዳው ሌላው ግሩም መሣሪያ ደግሞ በየዕለቱ አብሮ መጸለይ ነው።

ባለትዳሮች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን አብረው ሲያከናውኑ ከአምላክ ጋርም ሆነ እርስ በርስ ይበልጥ ይቀራረባሉ እንዲሁም ደስተኞች ይሆናሉ (አንቀጽ 5,  6ን ተመልከት)

6 በጀርመን የሚኖረው ጌርሃት እንዲህ ብሏል፦ “በግል ችግሮችም ሆነ ባለመግባባት የተነሳ ደስታችን ሲቀንስ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ምክር ታጋሾችና ይቅር ባዮች እንድንሆን ረድቶናል። እነዚህ ባሕርያት ትዳርን የተሳካ ለማድረግ በጣም አስፈላጊ ናቸው።” ባለትዳሮች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን አብረው በማከናወን በትዳራቸው ውስጥ አምላክ እንዲኖር ለማድረግ ሲጥሩ ከአምላክ ጋርም ሆነ እርስ በርስ ይበልጥ ይቀራረባሉ እንዲሁም ደስተኞች ይሆናሉ።

ባሎች፣ የራስነት ሥልጣናችሁን በፍቅር ተጠቀሙበት

7. ባሎች የራስነት ሥልጣናቸውን እንዴት ሊጠቀሙበት ይገባል?

7 አንድ ባል የራስነት ሥልጣኑን የሚጠቀምበት መንገድ ጠንካራና አስደሳች ትዳር ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። መጽሐፍ ቅዱስ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴት ሁሉ ራስ ደግሞ ወንድ” እንደሆነ ይናገራል። (1 ቆሮ. 11:3) ይህ ጥቅስ ባሎች የራስነት ሥልጣናቸውን መጠቀም ያለባቸው ክርስቶስ ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ሥልጣኑን ከተጠቀመበት መንገድ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ሊሆን እንደሚገባ ይጠቁማል። ኢየሱስ ጨካኝ ወይም አምባገነን አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ  ምንጊዜም አፍቃሪ፣ ደግ፣ ምክንያታዊ፣ ገርና በልቡ ትሑት ነበር።ማቴ. 11:28-30

8. አንድ ባል የሚስቱን ፍቅርና አክብሮት ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው?

8 ክርስቲያን ባሎች፣ ሚስቶቻቸው አክብሮት እንዲያሳዩአቸው መጠየቅ አያስፈልጋቸውም። ከዚህ ይልቅ “ከእነሱ ጋር በእውቀት መኖራችሁን ቀጥሉ” የሚለውን ምክር በተግባር ያውላሉ፤ በሌላ አባባል ለእነሱ አሳቢነት ያሳያሉ እንዲሁም ሁኔታቸውን ለመረዳት ይጥራሉ። ባሎች ‘ከእነሱ ይበልጥ ተሰባሪ ዕቃ ለሆኑት ለሴቶች ክብር መስጠት’ ይኖርባቸዋል። (1 ጴጥ. 3:7) በተጨማሪም ከሌሎች ሰዎች ጋርም ሆነ ለብቻቸው ሲሆኑ ሚስቶቻቸውን በአክብሮት በማነጋገርና በደግነት በመያዝ እነሱን እንደ ውድ አድርገው እንደሚመለከቷቸው ያሳያሉ። (ምሳሌ 31:28) አንድ ባል የራስነት ሥልጣኑን እንዲህ ባለ ፍቅር የሚንጸባረቅበት መንገድ ሲጠቀምበት የሚስቱን ፍቅርና አክብሮት ያገኛል፤ አምላክም ትዳሩን ይባርከዋል።

ሚስቶች በትሕትና ተገዙ

9. አንዲት ሚስት ለባሏ በትሕትና እንደምትገዛ የምታሳየው እንዴት ነው?

9 ሁላችንም ለይሖዋ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነና በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ ፍቅር ካለን ከኃይለኛው የአምላክ እጅ በታች ራሳችንን ዝቅ ለማድረግ እንነሳሳለን። (1 ጴጥ. 5:6) ለባሏ ተገዢ የሆነች ሚስት ለይሖዋ ሥልጣን አክብሮት የምታሳይበት አንዱ መንገድ ከባለቤቷ ጋር መተባበርና እሱን መደገፍ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሚስቶች ሆይ፣ በጌታ ዘንድ ተገቢ ስለሆነ ለባሎቻችሁ ተገዙ” ይላል። (ቆላ. 3:18) አንዲት ሚስት፣ ባሏ በሚያደርጋቸው አንዳንድ ውሳኔዎች የማትደሰትበት ጊዜ ሊኖር እንደሚችል የታወቀ ነው። ይሁንና ውሳኔዎቹ ከአምላክ ሕግ ጋር የማይጋጩ እስከሆኑ ድረስ የባሏን ውሳኔ በመቀበል ለእሱ እንደምትገዛ ታሳያለች።—1 ጴጥ. 3:1

10. ሚስት በፍቅር መገዛቷ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

10 ሚስት የባሏ ‘አጋር’ በመሆኗ የተከበረ ድርሻ አላት። (ሚል. 2:14) ቤተሰቡን በሚመለከቱ ውሳኔዎች ረገድ ሐሳቧንና ስሜቷን በአክብሮት በመግለጽ ጠቃሚ አስተዋጽኦ ታበረክታለች፤ ይህን የምታደርገው ግን ለባሏ እንደምትገዛ በሚያሳይ መንገድ ነው። ጥበበኛ ባል፣ ሚስቱ ስትናገር በጥሞና ያዳምጣል። (ምሳሌ 31:10-31) ሚስት በፍቅር መገዛቷ ደግሞ በቤተሰብ ውስጥ ደስታ፣ ሰላምና  አንድነት እንዲሰፍን ያደርጋል፤ ባልና ሚስት አምላክን እንደሚያስደስቱ ማወቃቸው እርካታ ያስገኝላቸዋል።ኤፌ. 5:22

በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ

11. ይቅር ባይነት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

11 ዘላቂ የሆነ ትዳር ለመገንባት በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ጡቦች አንዱ ይቅር ባይነት ነው። ባሎችና ሚስቶች “እርስ በርስ መቻቻላችሁንና እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ” የሚለውን መመሪያ ተግባራዊ ሲያደርጉ ጥምረታቸው ይጠናከራል። (ቆላ. 3:13) በሌላ በኩል ግን ቂም የሚይዙ ከሆነና ቅር በተሰኙ ቁጥር ያንን እያነሱ የትዳር ጓደኛቸውን የሚያጠቁ ከሆነ ትዳራቸው ይናጋል። አንድ ሕንፃ ስንጥቅ ካለው ጥንካሬ እያጣ እንደሚሄድ ሁሉ ቅሬታና ምሬት በልባችን ውስጥ ሥር ከሰደደም ይቅር ማለት እየከበደን ሊሄድ ይችላል። በአንጻሩ ግን ባለትዳሮች ይሖዋ ይቅር እንደሚለን ይቅር ከተባባሉ ጥምረታቸው እያደር ይጠነክራል።—ሚክ. 7:18, 19

12. ‘ፍቅር የኃጢአትን ብዛት የሚሸፍነው’ እንዴት ነው?

12 እውነተኛ ፍቅር “የበደል መዝገብ የለውም።” እንዲያውም “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።” (1 ቆሮ. 13:4, 5፤ 1 ጴጥሮስ 4:8ን አንብብ።) በሌላ አባባል ፍቅር ካለን ሌሎች ሲበድሉን ምን ያህል ጊዜ ይቅር እንደምንል ገደብ አናበጅም። ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ስንት ጊዜ ይቅር ማለት እንዳለበት ሲጠይቀው ኢየሱስ “እስከ ሰባ ሰባት ጊዜ” የሚል መልስ ሰጥቶታል። (ማቴ. 18:21, 22) ይህን ሲናገር የክርስቲያኖች ይቅርታ በቁጥር ሊገደብ እንደማይገባ መጠቆሙ ነበር።ምሳሌ 10:12 *

13. ቂም የመያዝን ዝንባሌ ለማስወገድ ምን ሊረዳን ይችላል?

13 አኔት እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ባልና ሚስት ይቅር ማለት የማይፈልጉ ከሆነ ምሬትና አለመተማመን ይፈጠራል፤ ይህ ደግሞ ለትዳር ጠንቅ ነው። ይቅር ማለት ትዳርን የሚያጠናክር ሲሆን እርስ በርስ ይበልጥ እንድትቀራረቡ ያደርጋል።” ቂም የመያዝን ዝንባሌ ማስወገድ እንድትችሉ አመስጋኝና አድናቂ ለመሆን ጥረት አድርጉ። የትዳር ጓደኛችሁን ከልባችሁ የማድነቅ ልማድ ይኑራችሁ። (ቆላ. 3:15) እንዲህ ስታደርጉ ይቅር ባይ የሆኑ ሰዎች የሚኖራቸውን የአእምሮ ሰላም፣ አንድነት እንዲሁም መለኮታዊ በረከት ማግኘት ትችላላችሁ።ሮም 14:19

ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ አድርጉ

14, 15. ወርቃማው ሕግ ምንድን ነው? በትዳር ውስጥ ይህን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ ጠቃሚ የሆነው እንዴት ነው?

14 ሁላችንም ሌሎች በአክብሮት እንዲይዙን እንፈልጋለን። ለምናደርገው ነገር እውቅና ሲሰጡንና ስሜታችንን ግምት ውስጥ ሲያስገቡ ደስ ይለናል። ይሁንና ሰዎች “ብድሬን ካልመለስኩማ . . .!” ሲሉ ሰምተህ ታውቃለህ? አንዳንዶች እንዲህ የሚሰማቸው ለምን እንደሆነ መረዳት ባይከብደንም መጽሐፍ ቅዱስ “በእኔ ላይ እንደሠራብኝ እሠራለታለሁ” እንዳንል ምክር ይሰጠናል። (ምሳሌ 24:29) ኢየሱስ፣ ችግሮች ሲፈጠሩ መፍታት የሚቻልበትን የተሻለ መንገድ ሲጠቁም “ልክ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ እንደምትፈልጉት ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው” ብሏል፤ ይህ የሥነ ምግባር መመሪያ በጣም የታወቀ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ወርቃማው ሕግ በመባል ይጠራል። (ሉቃስ 6:31) ኢየሱስ፣ ሰዎችን መያዝ ያለብን እኛን እንዲይዙን በምንፈልገው መንገድ እንደሆነና ክፉን በክፉ መመለስ እንደሌለብን መግለጹ ነበር። ወደ ጋብቻ ስንመጣ ደግሞ ከትዳር ጓደኛችን የምንጠብቀውን ነገር በሙሉ እኛም ልናደርግለት ይገባል ማለት ነው።

15 ያገቡ ሰዎች ለትዳር ጓደኛቸው ስሜት ትኩረት የሚሰጡ ከሆነ ግንኙነታቸው ይጠናከራል።  በደቡብ አፍሪካ የሚገኝ አንድ ባል እንዲህ ብሏል፦ “ወርቃማውን ሕግ በሥራ ለማዋል ጥረት እናደርጋለን። የተበሳጨንባቸው ጊዜያት እንደነበሩ አይካድም፤ ሆኖም ሁለታችንም፣ እኛ መያዝ በምንፈልግበት መንገድ ይኸውም በአክብሮት የትዳር ጓደኛችንን ለመያዝ ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን።”

16. ባለትዳሮች ምን ማድረግ አይኖርባቸውም?

16 የትዳር ጓደኛችሁን ድክመቶች ወይም የማትወዷቸውን ባሕርያት በቀልድ መልክም እንኳ ቢሆን በሰው ፊት አትናገሩ። ትዳር፣ ከሁለታችሁ ጠንካራ የሆነው ወይም በሌላው ላይ መጮህ አሊያም የሚያቆስል ነገር መናገር የሚችለው ማን እንደሆነ የምትፎካከሩበት መድረክ እንዳልሆነ አስታውሱ። ሁላችንም ስህተት እንደምንሠራና አንዳንድ ጊዜ ሌሎችን ቅር እንደምናሰኝ የታወቀ ነው። ይሁንና ባሎችም ሆኑ ሚስቶች አሽሙር የተቀላቀለበትና ሌላውን የሚያናንቅ ነገር ለመናገር ይባስ ብሎም አንዳቸው በሌላው ላይ እጃቸውን ለመሰንዘር የሚያበቃቸው ምንም ዓይነት ምክንያት ሊኖር አይችልም።—ምሳሌ 17:27ን እና 31:26ን አንብብ።

17. ባሎች ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

17 በአንዳንድ ባሕሎች ሚስቶችን መጨቆን ወይም መምታት የወንድነት መገለጫ እንደሆነ ተደርጎ ቢታይም መጽሐፍ ቅዱስ “ታጋሽ ሰው ከጦረኛ፣ ስሜቱን የሚገዛም ከተማን በጕልበቱ ከሚይዝ ይበልጣል” ይላል። (ምሳሌ 16:32) በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠውን ታላቅ ሰው ይኸውም የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል ስሜትን መቆጣጠር መንፈሰ ጠንካራ መሆን ይጠይቃል። በሚስቱ ላይ በቃላትም ሆነ በጉልበት ጥቃት የሚሰነዝር ባል ወንድ ነው ሊባል አይችልም፤ እንዲህ ማድረጉ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ያሳጣዋል። ጠንካራና ደፋር ሰው የነበረው መዝሙራዊው ዳዊት “ስትቈጡ ኀጢአት አትሥሩ፤ በዐልጋችሁም ላይ ሳላችሁ፣ ልባችሁን መርምሩ፤ ጸጥም በሉ” ብሏል።መዝ. 4:4

“ፍቅርን ልበሱ”

18. የትዳር ጓደኛሞች ፍቅርን ማዳበራቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

18 አንደኛ ቆሮንቶስ 13:4-7ን አንብብ። በትዳር ውስጥ ከምንም በላይ አስፈላጊ የሆነው ባሕርይ ፍቅር ነው። “ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ። ይሁንና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ላይ ፍቅርን ልበሱ፤ ምክንያቱም ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነው።” (ቆላ. 3:12, 14) የራስን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረግ የሚያነሳሳ የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር፣ አንድ ትዳር የተገነባባቸው ጡቦች እርስ በርስ እንዲያያዙ በማድረግ የትዳሩን ጥምረት ያጠናክረዋል። የትዳር ጓደኛሞች የግል ድክመት ቢኖርባቸው አሊያም የጤና ወይም የኢኮኖሚ ችግር ቢያጋጥማቸው እንዲሁም ከአማቶቻቸው ጋር ለመግባባት ቢቸገሩ እንኳ እንዲህ ዓይነት ፍቅር ካላቸው ጥምረታቸው ፈጽሞ የማይበጠስ ይሆናል።

19,  20. (ሀ) ባልና ሚስት ትዳራቸው ጠንካራና አስደሳች እንዲሆን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

19 ትዳር እንዲሰምር ለማድረግ ፍቅር፣ ታማኝነትና ልባዊ ጥረት አስፈላጊ እንደሆኑ የታወቀ ነው። የትዳር ጓደኛሞች ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ትዳራቸውን ከማፍረስ ወይም ላለመፋታት ብለው ብቻ አብረው ከመኖር ይልቅ ትዳራቸውን አስደሳች ለማድረግ መጣር ይኖርባቸዋል። ክርስቲያን ባለትዳሮች ለይሖዋም ሆነ ለትዳር ጓደኛቸው ፍቅር ካላቸው የሚያጋጥሟቸውን አለመግባባቶች መፍታት ይችላሉ፤ ምክንያቱም “ፍቅር ፈጽሞ አይከስምም።”—1 ቆሮ. 13:8፤ ማቴ. 19:5, 6፤ ዕብ. 13:4

20 በተለይ “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ጠንካራና ደስተኛ ትዳር መገንባት በጣም ፈታኝ ነው። (2 ጢሞ. 3:1) ይሁንና በይሖዋ እርዳታ ይህን ማድረግ ይቻላል። እንደዚያም ሆኖ ባለትዳሮች በሥነ ምግባር እያዘቀጠ የሚሄደው ይህ ዓለም የሚያሳድረውን ተጽዕኖ መቋቋም ያስፈልጋቸዋል። በሚቀጥለው ርዕስ ባልና ሚስቶች ትዳራቸውን ከሥነ ምግባር ብልግና ለመጠበቅ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንመለከታለን።

^ አን.12 ባልና ሚስት እርስ በርስ ይቅር ለመባባልና ችግሮቻቸውን ለመፍታት ጥረት የሚያደርጉ ቢሆንም አንደኛው የትዳር ጓደኛ ምንዝር ከፈጸመ ታማኝ የሆነው ወገን ይቅር ለማለት አሊያም ፍቺ ለመፈጸም መብት እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ማቴ. 19:9) “ከአምላክ ፍቅር” በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 219-221 ላይ የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍቺና ስለ መለያየት ምን ይላል?” የሚለውን ርዕስ እንዲሁም በነሐሴ 8, 1995 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ከገጽ 10-11 ላይ የሚገኘውን “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት፦ ምንዝር—ይቅር ማለት አለብኝ ወይስ የለብኝም?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።