በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ጥር 2015

የጌታ ራትን የምናከብረው ለምንድን ነው?

የጌታ ራትን የምናከብረው ለምንድን ነው?

“ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት።”—1ቆሮ. 11:24

1, 2. ኢየሱስ፣ ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. ምሽት ላይ ምን አደረገ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

ጊዜው ቢመሽም ጨረቃዋ ሙሉ በመሆኗ ኢየሩሳሌም በብርሃኗ ደምቃለች። ዕለቱ ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. ነው። ኢየሱስና ሐዋርያቱ፣ እስራኤላውያን ከ1,500 ዓመታት በፊት ከግብፅ ባርነት ነፃ የወጡበትን ቀን ለማሰብ የፋሲካን በዓል አክብረው መጨረሳቸው ነው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ከ11 ታማኝ ሐዋርያቱ ጋር በመሆን አንድ ልዩ በዓል አቋቋመ። ኢየሱስ ይህ ዕለት ከመገባደዱ በፊት እንደሚሞት ያውቃል፤ በዓሉን ያቋቋመው ለሞቱ መታሰቢያ እንዲሆን ነው። *ማቴ. 26:1, 2

2 ኢየሱስ ቂጣ አንስቶ ከባረከ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት “እንኩ፣ ብሉ” አላቸው። ከዚያም የወይን ጠጅ የያዘ ጽዋ አንስቶ በድጋሚ ካመሰገነ በኋላ “ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ” አለ። (ማቴ. 26:26, 27) ኢየሱስ ከዚያ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሌሎች ምግቦችን አንስቶ አልሰጣቸውም፤ ሆኖም በዚያ ልዩ ምሽት ለታማኝ ተከታዮቹ ብዙ የሚነግራቸው ነገር አለው።

3. በዚህ ርዕስ ላይ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ ይኸውም “የጌታን ራት” ያቋቋመው በዚህ  መንገድ ነው። (1 ቆሮ. 11:20) ይህን በዓል በተመለከተ አንዳንዶች እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች ያነሱ ይሆናል፦ የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ የምናከብረው ለምንድን ነው? ቂጣውና የወይን ጠጁ ምን ያመለክታሉ? ለበዓሉ መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈል የሚገባቸው እነማን ናቸው? ክርስቲያኖች ቅዱስ ጽሑፋዊ ተስፋቸውን እንዴት ይመለከቱታል?

የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ የምናከብረው ለምንድን ነው?

4. የኢየሱስ ሞት ምን አጋጣሚ ከፍቶልናል?

4 የአዳም ዘሮች በመሆናችን ኃጢአትንና ሞትን ወርሰናል። (ሮም 5:12) ማንኛውም ፍጽምና የጎደለው ሰው ለራሱም ሆነ ለሌሎች ቤዛ በመሆን ለአምላክ ተገቢውን ዋጋ መክፈል አይችልም። (መዝ. 49:6-9) ኢየሱስ ግን ተቀባይነት ያለውን ብቸኛውን ቤዛ ይኸውም ፍጹም ሥጋውንና ደሙን በሞቱ አማካኝነት ከፍሏል። ኢየሱስ የቤዛውን ዋጋ ለአምላክ በማቅረቡ የሰው ልጆች ከኃጢአትና ከሞት ነፃ መውጣት ብሎም የዘላለም ሕይወት ስጦታን ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ከፍቷል።—ሮም 6:23፤ 1 ቆሮ. 15:21, 22

5. (ሀ) አምላክና ክርስቶስ ለሰው ልጆች ፍቅር እንዳላቸው እንዴት እናውቃለን? (ለ) በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ መገኘት ያለብን ለምንድን ነው?

5 የቤዛው ዝግጅት አምላክ ዓለምን ይኸውም የሰው ልጆችን እንደሚወድድ ያረጋግጣል። (ዮሐ. 3:16) ኢየሱስ መሥዋዕት መሆኑ እሱም እንደሚወድደን ያሳያል። ደግሞም ኢየሱስ፣ ሰው ከመሆኑ በፊት የአምላክ “ዋና ባለሙያ” ሆኖ ይሠራ በነበረበት ጊዜ “በሰው ልጆች ደስ [ይሰኝ] ነበር”! (ምሳሌ 8:30, 31) አምላክና ልጁ ላደረጉልን ነገር ያለን አመስጋኝነት በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ እንድንገኝ ሊያነሳሳን ይገባል፤ “ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” የሚለውን ትእዛዝ በዚህ መንገድ እንፈጽማለን።1 ቆሮ. 11:23-25

ቂጣውና የወይን ጠጁ ምን ያመለክታሉ?

6. በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚቀርቡትን ቂጣና የወይን ጠጅ እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?

6 ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ሲያቋቁም ቂጣውና የወይን ጠጁ በተአምራዊ መንገድ ወደ ሥጋውና ወደ ደሙ እንዲቀየሩ አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ስለ ቂጣው ሲናገር “ይህ ሥጋዬ ማለት ነው” ብሏል። የወይን ጠጁን በተመለከተ ደግሞ “ይህ ለብዙዎች የሚፈስ ‘የቃል ኪዳን ደሜ’ ማለት ነው” አለ። (ማር. 14:22-24) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ቂጣውና የወይን ጠጁ ምሳሌያዊ ናቸው።

7. በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚቀርበው ቂጣ ምን ያመለክታል?

7 በ33 ዓ.ም. በተቋቋመው ትልቅ ቦታ በሚሰጠው በዚያ በዓል ላይ ኢየሱስ የተጠቀመው ከፋሲካ የተረፈውን ያልቦካ ቂጣ ነበር። (ዘፀ. 12:8) በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ እንከንን ወይም ኃጢአትን ለማመልከት እርሾ የሚለው ቃል የገባበት ጊዜ አለ። (ማቴ. 16:6, 11, 12፤ ሉቃስ 12:1) በመሆኑም ኢየሱስ ኃጢአት የሌለበትን ሥጋውን ለማመልከት ያልቦካ ቂጣ መጠቀሙ ተገቢ ነው። (ዕብ. 7:26) በዚህም ምክንያት በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚቀርበው እንዲህ ያለ ቂጣ ነው።

8. በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚቀርበው የወይን ጠጅ ምን ይወክላል?

8 ኢየሱስ ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. የተጠቀመው የወይን ጠጅ ደሙን ይወክላል፤ ዛሬም በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚቀርበው የወይን ጠጅ የሚያመለክተው ይህንኑ ነው። ከኢየሩሳሌም ውጭ በሚገኝ ጎልጎታ በተባለ ስፍራ የኢየሱስ ደም ‘ለብዙዎች የኃጢአት ይቅርታ’ ለማስገኘት ፈስሷል። (ማቴ. 26:28፤ 27:33) በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚቀርበው ቂጣና የወይን ጠጅ ኢየሱስ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች የከፈለውን ውድ መሥዋዕት ይወክላል፤ እኛም ይህን ፍቅራዊ ዝግጅት ስለምናደንቅ በየዓመቱ ለሚከበረው የጌታ ራት በግለሰብ ደረጃ መዘጋጀታችን ተገቢ ነው።

ለበዓሉ መዘጋጀት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች

9. (ሀ) የመታሰቢያውን በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ማንበባችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ስለ ቤዛው ምን ይሰማሃል?

9 ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር በተባለው ቡክሌት ላይ የሚገኘውን የመታሰቢያው  በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ በማንበብ ኢየሱስ ከሞቱ በፊት ባከናወናቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰል እንችላለን። ይህን ማድረጋችን ደግሞ ለጌታ ራት ልባችንን ለማዘጋጀት ይረዳናል። * አንዲት እህት እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “የመታሰቢያውን በዓል በጉጉት እንጠብቀዋለን። ከዓመት ወደ ዓመት፣ በዓሉ ልዩ ትርጉም እንዳለው ይሰማናል። . . . የአባቴ አስከሬን በተቀመጠበት ቤት ውስጥ ሆኜ የምወደውን አባቴን ትኩር ብዬ ስመለከት ለቤዛው እውነተኛ የሆነ ልባዊ አድናቆት እንዳደረብኝ ትዝ ይለኛል። . . . [ከቤዛው ጋር የተያያዙትን] ሁሉንም ጥቅሶችና ጥቅሶቹ እንዴት እንደሚብራሩ አውቅ ነበር! ይሁን እንጂ በዚህ ውድ ቤዛ አማካኝነት ወደፊት የሚፈጸሙልንን ነገሮች ሳስብ ልቤ በደስታ የዘለለው የሞትን አስከፊነት በተገነዘብኩበት በዚያ ጊዜ ነበር።” በእርግጥም ለመታሰቢያው በዓል ስንዘጋጅ የኢየሱስ መሥዋዕት ከኃጢአትና ከሞት መቅሠፍት እንዴት እንደሚገላግለን ማሰባችን የተገባ ነው።

ለመታሰቢያው በዓል ልብህን ለማዘጋጀት በሚረዱህ መሣሪያዎች ተጠቀም (አንቀጽ 9ን ተመልከት)

10. ለመታሰቢያው በዓል ስንዘጋጅ ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ ምን ማድረግ እንችላለን?

10 ለመታሰቢያው በዓል መዘጋጀት የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ የአገልግሎት እንቅስቃሴያችንን ከፍ ማድረግ ለምሳሌ በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ረዳት አቅኚ ሆነን ማገልገል ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንም ሆነ ሌሎች በጌታ ራት ላይ እንዲገኙ ስንጋብዝ ስለ አምላክና ስለ ልጁ እንዲሁም ይሖዋን ለሚያስደስቱና እሱን ለሚያወድሱ ሰዎች ስለተዘጋጀላቸው በረከቶች መናገራችን ደስታ ያመጣልናል።መዝ. 148:12, 13

11. አንዳንድ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የማይገባቸው ሆኖ ሳለ በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርበው ቂጣና የወይን ጠጅ የተካፈሉት እንዴት ነው?

11 ለጌታ ራት በምትዘጋጅበት ወቅት፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበረው የክርስቲያን ጉባኤ የጻፈውን ሐሳብ ልብ ማለትህ ጠቃሚ ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:27-34ን አንብብ።) የማይገባው ሆኖ ሳለ ከቂጣው የሚበላ ወይም ከጽዋው የሚጠጣ ማንኛውም ክርስቲያን “ከጌታ [ከኢየሱስ ክርስቶስ] አካልና ደም ጋር በተያያዘ ተጠያቂ ይሆናል” በማለት ጳውሎስ ተናግሯል። በመሆኑም አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈል የሚኖርበት “የሚገባው እንደሆነ ለማወቅ በቅድሚያ ራሱን [ከመረመረ]” በኋላ ነው። አለዚያ “በራሱ ላይ ፍርድ የሚያመጣበትን ይበላል እንዲሁም ይጠጣል።” በቆሮንቶስ የነበሩ ብዙዎቹ ክርስቲያኖች ተገቢ ያልሆነ ምግባር ስለነበራቸው “ደካማና ታማሚ” ሆነዋል፤ እንዲሁም ‘ጥቂት የማይባሉት [በመንፈሳዊ ሁኔታ] በሞት አንቀላፍተዋል።’ አንዳንዶች በመታሰቢያው በዓል ላይ ከመገኘታቸው በፊት ወይም በበዓሉ ወቅት ከመጠን በላይ በልተውና ጠጥተው ሊሆን ይችላል፤  በመሆኑም አእምሯቸው ንቁ አልነበረም፤ በመንፈሳዊ ሁኔታም ደክመው ነበር። በዚህ ምክንያት ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈል የማይገባቸው ሆነው ሳሉ ይህንን ማድረጋቸው የአምላክን ሞገስ አሳጥቷቸዋል።

12. (ሀ) ጳውሎስ የመታሰቢያውን በዓል ከምን ጋር አመሳስሎታል? ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ለሚካፈሉ ሰዎች ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል? (ለ) ከቂጣውና ከወይኑ የሚካፈል አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት ቢፈጽም ምን ማድረግ ይኖርበታል?

12 ጳውሎስ የመታሰቢያውን በዓል በኅብረት ከሚበላ ማዕድ ጋር በማመሳሰል ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ለሚካፈሉት ሰዎች እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል፦ “የይሖዋን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ መጠጣት አትችሉም፤ ‘ከይሖዋ ማዕድ’ እና ከአጋንንት ማዕድ መካፈል አትችሉም።” (1 ቆሮ. 10:16-21) በጌታ ራት ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚካፈል ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት ከፈጸመ መንፈሳዊ እርዳታ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። (ያዕቆብ 5:14-16ን አንብብ።) እንዲህ ያለው ቅቡዕ ክርስቲያን “ለንስሐ የሚገባ ፍሬ” ካፈራ በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይኑ መውሰዱ ለኢየሱስ መሥዋዕት ንቀት ማሳየት አይሆንበትም።—ሉቃስ 3:8

13. አምላክ ስለሰጠን ተስፋ በጸሎት ማሰብ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

13 ለመታሰቢያው በዓል ስንዘጋጅ አምላክ በግለሰብ ደረጃ የሰጠንን ተስፋ በጸሎት ልናስብበት ይገባል። ራሱን ለይሖዋ የወሰነና የልጁ ታማኝ ተከታይ የሆነ ማንኛውም ክርስቲያን፣ ቅቡዕ ለመሆኑ ግልጽ ማስረጃ ሳይኖረው ከቂጣውና ከወይን ጠጁ በመካፈል ለኢየሱስ መሥዋዕት አክብሮት እንደጎደለው የሚያሳይ ነገር አያደርግም። ታዲያ አንድ ክርስቲያን ከቂጣውና ከወይኑ መካፈል የሚገባው መሆን አለመሆኑን ማወቅ የሚችለው እንዴት ነው?

ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈል የሚገባቸው እነማን ናቸው?

14. አዲሱ ቃል ኪዳን በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርቡት ቂጣና የወይን ጠጅ ከመካፈል ጋር ምን ግንኙነት አለው?

14 ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈል የሚገባቸው ሰዎች በአዲሱ ቃል ኪዳን የታቀፉ መሆናቸውን ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ናቸው። የወይን ጠጁን በተመለከተ ኢየሱስ “ይህ ጽዋ በደሜ አማካኝነት የሚመሠረተው አዲሱ ቃል ኪዳን ማለት ነው” ብሏል። (1 ቆሮ. 11:25) አምላክ፣ ከእስራኤላውያን ጋር ከገባው ከሕጉ ቃል ኪዳን የተለየ አዲስ ቃል ኪዳን እንደሚገባ በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት አስቀድሞ ተናግሯል። (ኤርምያስ 31:31-34ን አንብብ።) አምላክ አዲሱን ቃል ኪዳን የገባው ከመንፈሳዊ እስራኤላውያን ጋር ነው። (ገላ. 6:15, 16) ይህ ቃል ኪዳን የጸናው ክርስቶስ መሥዋዕት ሲሆን በፈሰሰው ደሙ አማካኝነት ነው። (ሉቃስ 22:20) ኢየሱስ የዚህ አዲስ ቃል ኪዳን መካከለኛ ሲሆን ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ደግሞ በዚህ ቃል ኪዳን በመታቀፋቸው ሰማያዊ ውርሻ ያገኛሉ።—ዕብ. 8:6፤ 9:15

15. በመንግሥት ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉት እነማን ናቸው? ታማኝ ሆነው ከጸኑስ ምን መብት ያገኛሉ?

15 ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈል የሚገባቸው ግለሰቦች በመንግሥት ቃል ኪዳን ውስጥ እንደታቀፉ ያውቃሉ። (ሉቃስ 12:32ን አንብብ።) የሥቃዩ ተካፋይ በመሆን ከኢየሱስ ጎን የቆሙት ቅቡዓን ተከታዮቹ ከእሱ ጋር በሰማይ እንደሚገዙ ተገልጿል። (ፊልጵ. 3:10) እነዚህ ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በመንግሥት ቃል ኪዳን ውስጥ ስለታቀፉ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ለዘላለም ነገሥታት ሆነው ይገዛሉ። (ራእይ 22:5) እነዚህ ግለሰቦች በጌታ ራት ወቅት ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈላቸው የተገባ ነው።

16. የሮም 8:15-17ን ትርጉም በአጭሩ አብራራ።

16 በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርቡት ቂጣና የወይን ጠጅ መካፈል የሚችሉት፣ የአምላክ ልጆች መሆናቸውን መንፈሱ የመሠከረላቸው ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። (ሮም 8:15-17ን አንብብ።) ጳውሎስ “አባ፣ አባት!” ብለው እንደሚጣሩ ገልጿል። “አባ” የሚለው የአረማይክ ቃል አንድ ልጅ ለአባቱ ያለውን ፍቅርና አክብሮት ያመለክታል። “እንደ ልጅ የመቆጠር መብት የሚያስገኝ መንፈስ” የተቀበሉት ክርስቲያኖችም በመንፈስ የተወለዱ የአምላክ ልጆች ናቸው። የአምላክ መንፈስ ከመንፈሳቸው ጋር ሆኖ ስለሚመሠክር የይሖዋ  ቅቡዓን ልጆች መሆናቸውን እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ምድር ላይ መኖር አይፈልጉም ማለት አይደለም። እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ከሆኑ በሰማያዊው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር ወራሾች እንደሚሆኑ እርግጠኞች ናቸው። በዛሬው ጊዜ፣ ከ144,000 ዎቹ ይኸውም የክርስቶስን ፈለግ ከተከተሉትና “ቅዱስ ከሆነው [ከይሖዋ] የመንፈስ ቅብዓት” ካገኙት ክርስቲያኖች መካከል በምድር ላይ የቀሩት ጥቂቶች ናቸው። (1 ዮሐ. 2:20፤ ራእይ 14:1) እነዚህ ክርስቲያኖች “አባ፣ አባት!” ብለው የሚጣሩት መንፈሱ ስለመሠከረላቸው ነው። ከይሖዋ ጋር ያላቸው ዝምድና እንዴት አስደሳች ነው!

ቅዱስ ጽሑፋዊ ተስፋህን ከፍ አድርገህ ተመልከት

17. ቅቡዓን ያላቸው ተስፋ ምንድን ነው? እንዲህ ዓይነት ተስፋ እንዳላቸውስ እንዴት ያውቃሉ?

17 ቅቡዕ ክርስቲያን ከሆንክ በሰማይ የመኖር ተስፋህ በግልህ በምታቀርበው ጸሎት ላይ አዘውትረህ የምትጠቅሰው ጉዳይ እንደሚሆን የታወቀ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ ላለው ሙሽራ ይኸውም ለኢየሱስ ክርስቶስ ‘ስለመታጨት’ ሲናገር ይህ ጥቅስ በአንተ ላይ እንደሚሠራ ይሰማሃል፤ እንዲሁም የክርስቶስ “ሙሽራ” ከሚሆኑት አንዱ ለመሆን ትጓጓለህ። (2 ቆሮ. 11:2፤ ዮሐ. 3:27-29፤ ራእይ 21:2, 9-14) አምላክ ለመንፈሳዊ ልጆቹ ስላለው ፍቅር በቃሉ ውስጥ ሲናገር “ይህ የተባለው ስለ እኔ ነው” ብለህ ታስባለህ። በተጨማሪም የይሖዋ ቃል ለአምላክ ቅቡዓን ልጆች መመሪያ ሲሰጥ ይህን መመሪያ እንድትታዘዝና በልብህ “ይህ ሐሳብ እኔን የሚመለከት ነው” እንድትል መንፈስ ቅዱስ ያነሳሳሃል። በዚህ መንገድ የአምላክ መንፈስና የአንተ መንፈስ በአንድነት በመሆን ሰማያዊ ተስፋ እንዳለህ ይመሠክራሉ።

18. “ሌሎች በጎች” ምን ተስፋ አላቸው? አንተስ ስለዚህ ተስፋ ምን ይሰማሃል?

18 በሌላ በኩል ደግሞ ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” አባል ከሆንክ አምላክ በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ዘርግቶልሃል። (ራእይ 7:9፤ ዮሐ. 10:16) በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ፍላጎት አለህ፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት በምድር ላይ ስለሚኖረው ሕይወት በሚናገረው ሐሳብ ላይ ማሰላሰል ያስደስትሃል። በቤተሰብህና በሌሎች ጻድቅ ሰዎች ተከብበህ በሰላም ለመኖር ትጓጓለህ። የሰው ዘር ከምግብ እጥረት፣ ከድህነት፣ ከመከራ፣ ከሕመምና ከሞት የሚገላገልበትን ጊዜ ለማየት ትናፍቃለህ። (መዝ. 37:10, 11, 29፤ 67:6፤ 72:7, 16፤ ኢሳ. 33:24) ከሞት ተነስተው በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ የሚያገኙትን ሰዎች ለመቀበል ትጓጓለህ። (ዮሐ. 5:28, 29) ይሖዋ በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ስለሰጠህ ምንኛ አመስጋኝ ነህ! በመሆኑም በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርበው ቂጣና የወይን ጠጅ ባትካፈልም እንኳ ለኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ያለህን አድናቆት ለማሳየት በበዓሉ ላይ ትገኛለህ።

በበዓሉ ላይ ትገኛለህ?

19, 20. (ሀ) አምላክ የሰጠህ ተስፋ እንዲፈጸምልህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? (ለ) በጌታ ራት ላይ የምትገኘው ለምንድን ነው?

19 ተስፋህ ወደ ሰማይ መሄድም ሆነ በምድር ላይ መኖር ይህ ተስፋ እውን መሆን የሚችለው በይሖዋ አምላክ፣ በኢየሱስ ክርስቶስና በቤዛው ላይ እምነት ካሳደርክ ብቻ ነው። በመታሰቢያው በዓል ላይ ስትገኝ ስለ ተስፋህ እንዲሁም የኢየሱስ ሞት ስላለው የላቀ ዋጋ የማሰላሰል አጋጣሚ ይኖርሃል። እንግዲያው ዓርብ፣ ሚያዝያ 3, 2015 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ በዓለም ዙሪያ በመንግሥት አዳራሾችና በሌሎች ቦታዎች በሚከበረው የጌታ ራት ላይ ከሚገኙት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አንዱ ለመሆን ግብ አውጣ።

20 በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘት ለኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ያለህ አድናቆት እንዲያድግ ያደርጋል። በበዓሉ ላይ የሚቀርበውን ንግግር በጥሞና መከታተልህ ይሖዋ ለሰው ልጆች ስላለው ፍቅርና ከእኛ ጋር በተያያዘ ስላለው ታላቅ ዓላማ ለሰዎች በመናገር ለእነሱ ያለህን ፍቅር ለማሳየት ሊያነሳሳህ ይችላል። (ማቴ. 22:34-40) እንግዲያው የጌታ ራት በምንም ዓይነት እንዳያመልጥህ ጥረት አድርግ።

^ አን.1 በዕብራውያን አቆጣጠር አንድ ቀን የሚጀምረው ፀሐይ ስትጠልቅ ሲሆን የሚያበቃውም በቀጣዩ ቀን ፀሐይ ስትጠልቅ ነው።

^ አን.9 አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ የሚገኘውን ተጨማሪ መረጃ ለ12 ተመልከት።