በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ታኅሣሥ 2014

ሐሳብህን መቀየር ይኖርብህ ይሆን?

ሐሳብህን መቀየር ይኖርብህ ይሆን?

ጥቂት ወጣት ክርስቲያኖች ሲኒማ ቤት ሄደው አንድ ፊልም ለማየት አሰቡ። አብረዋቸው የሚማሩ ብዙ እኩዮቻቸው ፊልሙን አይተው እንደወደዱት ሰምተው ነበር። ሲኒማ ቤቱ ደርሰው የተለጠፉትን ማስታወቂያዎች ሲመለከቱ ግን ከባድ የጦር መሣሪያ የያዙ ሰዎችና ሰውነትን የሚያጋልጥ ልብስ የለበሱ ሴቶች ምስል አዩ። ታዲያ እነዚህ ወጣቶች ምን ያደርጉ ይሆን? ማስታወቂያው ባያስደስታቸውም ወደ ሲኒማ ቤቱ ገብተው ፊልሙን ያያሉ?

ይህ ሁኔታ መንፈሳዊነታችንንና ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና በጥሩም ሆነ በመጥፎ ሊነኩብን የሚችሉ ውሳኔዎች ለማድረግ የሚያስገድዱ በርካታ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሙን ያሳያል። አንዳንድ ጊዜ አንድ ነገር ለማድረግ ታስብ ይሆናል፤ ሁኔታውን እንደገና ስታጤነው ግን ሐሳብህን ትለውጣለህ። ታዲያ እንዲህ ማድረግህ ወላዋይነት ነው ወይስ ተገቢ ሊሆን ይችላል?

ሐሳብህን መቀየር ተገቢ የማይሆንበት ጊዜ

ለይሖዋ ያለን ፍቅር ሕይወታችንን ለእሱ ወስነን እንድንጠመቅ አነሳስቶናል። ለአምላክ ታማኝ ሆነን ለመኖር ከልባችን እንፈልጋለን። ይሁን እንጂ ጠላታችን ሰይጣን ዲያብሎስ ታማኝነታችንን እንድናላላ ለማድረግ ቆርጦ ተነስቷል። (ራእይ 12:17) እኛ ግን ይሖዋን ለማገልገልና ትእዛዛቱን ለመጠበቅ ወስነናል። ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን በገባነው ቃል ረገድ ሐሳባችንን ብንለውጥ ምንኛ የሚያሳዝን ይሆናል! እንዲህ ማድረግ ሕይወታችንን ሊያሳጣን ይችላል።

ከ2,600 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አንድ ታላቅ የወርቅ ምስል አቁሞ ሁሉም ሰው ለምስሉ እንዲሰግድ ትእዛዝ አወጣ። ለምስሉ የማይሰግድ ማንኛውም ሰው ወደሚንበለበለው የእሳት እቶን ይወረወራል። ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የተባሉ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሦስት የይሖዋ አምላኪዎች ንጉሡ ያለውን አላደረጉም። ለምስሉ ስላልሰገዱ ወደ እሳቱ እቶን ተወረወሩ። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ በተአምር አድኗቸዋል፤ እነሱ ግን አምላክን ለማገልገል ያደረጉትን ውሳኔ ከመለወጥ ይልቅ ሕይወታቸውን ለማጣት ፈቃደኞች ነበሩ።—ዳን. 3:1-27

ከጊዜ በኋላ ነቢዩ ዳንኤል ወደ አንበሶች ጉድጓድ  የመጣል አደጋ ቢጋረጥበትም ከመጸለይ ወደኋላ አላለም። አዎን፣ ወደ ይሖዋ በቀን ሦስት ጊዜ ጸሎት የማቅረብ ልማዱን አላቋረጠም። ዳንኤል እውነተኛውን አምላክ ለማምለክ ያደረገውን ቁርጥ ውሳኔ አልለወጠም። በዚህም የተነሳ ይሖዋ ይህን ነቢይ “ከአንበሶች አፍ አድኖታል።”—ዳን. 6:1-27

በዘመናችን ያሉት የአምላክ አገልጋዮችም ለይሖዋ የገቡትን ቃል ጠብቀው ይኖራሉ። በአፍሪካ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ተማሪዎች ለብሔራዊ አርማ አምልኮ አከል ክብር በሚሰጥበት ሥነ ሥርዓት ላይ ለመካፈል ፈቃደኞች አልሆኑም። ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ሆነው በሥነ ሥርዓቱ ካልተሳተፉ ከትምህርት ቤት እንደሚባረሩ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የትምህርት ሚኒስቴሩ ከተማዋን ሲጎበኙ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑት ተማሪዎች አንዳንዶቹን አነጋገሯቸው። እነዚህ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች በትሕትና፣ ሆኖም ምንም ሳይፈሩ አቋማቸውን አስረዱ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ጉዳዩ አልተነሳም። በመሆኑም ተማሪ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና የሚያበላሽ ነገር እንዲያደርጉ ጫና ይደረግብናል ብለው ሳይሰጉ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ችለዋል።

ባለቤቱ በካንሰር ስትሠቃይ ከቆየች በኋላ በድንገት የሞተችበትን ጆሴፍንም እንመልከት። የጆሴፍ ቤተሰቦች ከቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ጆሴፍ ያለውን አቋም የተረዱለት ሲሆን ፍላጎቱን አክብረውለታል። ይሁንና የባለቤቱ ቤተሰቦች እውነት ውስጥ ስላልሆኑ ከቀብር ሥነ ሥርዓቱን ጋር በተያያዘ አንዳንድ ልማዶችን ለመፈጸም ፈለጉ። ከእነዚህ ልማዶች አንዳንዶቹ አምላክን የማያስደስቱ ናቸው። ጆሴፍ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ አቋሜን ለማላላት ፈቃደኛ ስላልሆንኩ በልጆቼ ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ ሞከሩ፤ ይሁን እንጂ ሁሉም ልጆቼ በአቋማቸው ጸኑ። በተጨማሪም በአካባቢው ልማድ መሠረት ዘመዶቻችን በቤቴ አስከሬን እየጠበቁ የማደር ሥርዓት ለማከናወን ሞክረው ነበር። እኔም እንዲህ ያለውን ልማድ በቤቴ ውስጥ እንዲያከናውኑ እንደማልፈቅድ ገለጽኩላቸው። ይህ ልማድ ከእኔም ሆነ ከባለቤቴ እምነት ጋር እንደሚጋጭ ያውቁ ነበር፤ በመሆኑም በጉዳዩ ላይ ብዙ ከተነጋገርን በኋላ ይህን ሥርዓት ሌላ ቦታ አደረጉት።

“በዚህ አስቸጋሪ የሐዘን ወቅት ይሖዋ፣ ሕጉን እንዳንጥስ እንዲረዳን ወደ እሱ ምልጃ አቀረብኩ። ይሖዋም ጸሎቴን በመስማት የሚደረግብንን ጫና ተቋቁመን ጸንተን እንድንቆም ረድቶናል።” ጆሴፍና ልጆቹ ከአምልኳቸው ጋር በተያያዘ ሐሳባቸውን መለወጥ ጨርሶ የሚያስቡት ነገር አልነበረም።

ሐሳብህን መቀየር ተገቢ ሊሆን የሚችልበት ጊዜ

በ32 ዓ.ም. የተከበረው የፋሲካ በዓል ካለፈ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ በሲዶና አካባቢ እያለ አንዲት ሲሮፊንቃዊት ሴት ወደ እሱ መጣች። እሷም ከሴት ልጇ አጋንንት እንዲያስወጣላት እየደጋገመች ለመነችው። መጀመሪያ ላይ ኢየሱስ ምንም መልስ አልሰጣትም። ለደቀ መዛሙርቱ “እኔ የተላክሁት ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች እንጂ ለሌላ ለማንም አይደለም” አላቸው። ሴትየዋ መወትወቷን በቀጠለች ጊዜ ኢየሱስ “የልጆችን ዳቦ ወስዶ ለቡችሎች መጣል ተገቢ አይደለም” አላት። እሷም “አዎን ጌታ ሆይ፣ ግን እኮ ቡችሎችም ከጌቶቻቸው ማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” በማለት ትልቅ እምነት እንዳላት አሳየች። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ጥያቄዋን ተቀብሎ ልጇን ፈወሰላት።—ማቴ. 15:21-28

ይህም ሐሳብን ለመለወጥ ሁኔታው በሚፈቅድበት ጊዜ እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኛ በመሆን ረገድ ኢየሱስ ይሖዋን እንደሚመስል ያሳያል። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን የወርቅ ጥጃ ሠርተው ባመለኩ ጊዜ አምላክ ሊደመስሳቸው አስቦ ነበር፤ ሆኖም ሙሴ፣ ይሖዋ ውሳኔውን እንዲለውጥ ምልጃ በማቅረቡ ልመናውን ሰምቶ ይህን ከማድረግ ተቆጥቧል።—ዘፀ. 32:7-14

ሐዋርያው ጳውሎስም የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ ተከትሏል። ጳውሎስና ጓደኞቹ በመጀመሪያው የሚስዮናዊነት ጉዟቸው ወቅት ዮሐንስ ማርቆስን ይዘውት ሄደው ነበር፤ ማርቆስ፣ ጳውሎስንና በርናባስን ትቷቸው በመመለሱ ጳውሎስ ከዚያ በኋላ እሱን ይዞ መሄድ አልፈለገም። ከጊዜ በኋላ ግን ማርቆስ እንደጎለመሰና ጠቃሚ ባልደረባው እንደሚሆን ጳውሎስ የተገነዘበ ይመስላል። በመሆኑም ጳውሎስ “ማርቆስ ለአገልግሎት ስለሚጠቅመኝ ከአንተ ጋር ይዘኸው ና” በማለት ለጢሞቴዎስ ጽፎለታል።—2 ጢሞ. 4:11

ስለ እኛስ ምን ሊባል ይችላል? መሐሪ፣ ታጋሽና  አፍቃሪ የሆነውን የሰማዩ አባታችንን በመምሰል እኛም ሐሳባችንን መለወጥ ተገቢ እንደሆነ የሚሰማን ጊዜ ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ሌሎች ያለንን አመለካከት ልንለውጥ እንችላለን። ከይሖዋና ከኢየሱስ በተለየ መልኩ እኛ ፍጽምና የጎደለን ነን። ታዲያ ይሖዋና ኢየሱስ እንኳ ሐሳባቸውን ለመለወጥ ፈቃደኞች ከሆኑ እኛስ ሌሎች ያሉበትን ሁኔታ ስንረዳ ሐሳባችንን ብንለውጥ ተገቢ አይሆንም?

ከቲኦክራሲያዊ ግቦች ጋር በተያያዘም ሐሳባችንን መለወጥ ተገቢ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ አንዳንዶች ለመጠመቅ ያመነቱ ይሆናል። ወይም ደግሞ አንዳንድ ክርስቲያኖች አቅኚ በመሆን አገልግሎታቸውን ለማስፋት ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸው ቢሆንም ይህን ለማድረግ ፈራ ተባ ይሉ ይሆናል። አንዳንድ ወንድሞች ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ለኃላፊነት ቦታ ለመብቃት የመጣጣር ፍላጎት የሌላቸው ይመስላሉ። (1 ጢሞ. 3:1) የአንተስ ሁኔታ ከላይ ከተጠቀሱት ጋር የሚመሳሰል ነው? ይሖዋ እንዲህ ዓይነቶቹ መብቶች ላይ እንድትደርስ በፍቅር ይጋብዝሃል። ታዲያ ሐሳብህን በመለወጥ፣ ራስህን ለአምላክና ለሌሎች መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ ለምን አታጣጥምም?

ሐሳብህን መቀየርህ በረከት ሊያስገኝልህ ይችላል

ኤላ የምትባል እህት፣ በአፍሪካ በሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ስለምታከናውነው አገልግሎት እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ወደ ቤቴል ስመጣ ረጅም ጊዜ መቆየት መቻሌን እርግጠኛ አልነበርኩም። ይሖዋን በሙሉ ነፍስ የማገልገል ፍላጎት ነበረኝ፤ ሆኖም ከቤተሰቤ ጋር በጣም ስለምቀራረብ መጀመሪያ ላይ ይናፍቁኝ ነበር! ይሁንና ቤቴል ውስጥ አብራኝ የምትኖረው እህት ስላበረታታችኝ ለመቆየት ወሰንኩ። በቤቴል አሥር ዓመት ካሳለፍኩ በኋላ በዚሁ ምድቤ በመቀጠል ወንድሞቼንና እህቶቼን ለረጅም ጊዜ ማገልገሌን ለመቀጠል ወስኛለሁ።”

ሐሳብህን መቀየር የግድ አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ

ቃየን በወንድሙ ቀንቶ በተቆጣ ጊዜ የሆነውን ነገር ታስታውሳለህ? አምላክ፣ ቃየን መጥፎ ነገር ሊያደርግ እንዳሰበ ስለተመለከተ መልካም ቢያደርግ በእሱ  ዘንድ ሞገስ ማግኘት እንደሚችል ነግሮት ነበር። አምላክ፣ ‘በደጁ እያደባች’ ያለችውን ኃጢአት እንዲያሸንፋት መከረው። ቃየን አመለካከቱንና ሐሳቡን መለወጥ ይችል የነበረ ቢሆንም የአምላክን ምክር ችላ ለማለት መረጠ። የሚያሳዝነው ነገር ቃየን ወንድሙን በመግደል ነፍስ ያጠፋ የመጀመሪያው ሰው ሆነ!—ዘፍ. 4:2-8

ቃየን ሐሳቡን ቀይሮ ቢሆን ኖሮ ውጤቱ ምን ይሆን ነበር?

የንጉሥ ዖዝያንንም ምሳሌ እንመልከት። መጀመሪያ ላይ ዖዝያን በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን የሚያደርግና ሁልጊዜ አምላክን የሚፈልግ ሰው ነበር። የሚያሳዝነው ነገር፣ ዖዝያን ከጊዜ በኋላ ትዕቢተኛ በመሆኑ መልካም ስሙን አበላሸ። ካህን ባይሆንም የዕጣን መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ። ካህናቱ ይህን የትዕቢት ተግባር ከመፈጸም እንዲቆጠብ ባስጠነቀቁት ጊዜ ሐሳቡን ቀይሮ ይሆን? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ ዖዝያን “ተቈጣ”፤ ካህናቱ የሰጡትን ማስጠንቀቂያ ችላ አለ። በዚህም የተነሳ ይሖዋ በለምጽ መታው።—2 ዜና 26:3-5, 16-20

አዎን፣ እኛም ሐሳባችንን መለወጣችን የግድ አስፈላጊ የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ። አንድ ዘመናዊ ምሳሌ እንመልከት። ዦአኪም የተጠመቀው በ1955 ነው፤ ይሁን እንጂ በ1978 ተወገደ። ከ20 የሚበልጡ ዓመታት ካለፉ በኋላ የንስሐ ዝንባሌ ስላሳየ ወደ ጉባኤው ተመለሰ። ይህን ሁሉ ጊዜ ወደ ጉባኤ ለመመለስ ሳይጠይቅ የቆየው ለምን እንደሆነ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ በቅርቡ ጠይቆት ነበር። ዦአኪም እንዲህ ብሏል፦ “ተናድጄ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ትዕቢተኛ ነበርኩ። ያንን ያህል ረጅም ጊዜ ሳልመለስ መቆየቴ አሁን ይቆጨኛል። እውነትን የሚያስተምሩት የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ተወግጄ እያለሁም አውቅ ነበር።” ዦአኪም ሐሳቡን መለወጥና ንስሐ መግባት ያስፈልገው ነበር።

እኛም ሐሳባችንንና አካሄዳችንን መለወጥ የሚጠይቅብን ሁኔታ ያጋጥመን ይሆናል። እንግዲያው ይሖዋ የሚደሰትብን ዓይነት ሰዎች እንድንሆን ሐሳባችንንና አካሄዳችንን ለመለወጥ ፈቃደኞች እንሁን።—መዝ. 34:8