በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

“አምላኩ ይሖዋ የሆነለት ሕዝብ”

“አምላኩ ይሖዋ የሆነለት ሕዝብ”

“አምላኩ ይሖዋ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው!”መዝ. 144:15 NW

1. አንዳንዶች አምላክ በምድር ላይ የራሱ ሕዝብ ያለው ስለመሆኑ ምን ይሰማቸዋል?

በዛሬው ጊዜ በርካታ ሰዎች፣ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉትም ሆነ ከዚያ ውጪ የሆኑት ዋና ዋና ሃይማኖቶች የሰው ልጆችን የሚጠቅም አንዳች ነገር እንዳላደረጉ ይናገራሉ። አንዳንዶች እነዚህ ሃይማኖቶች የሚያስተምሩትም ሆነ የሚያደርጉት ነገር ሰዎች ስለ አምላክ የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌላቸው ያምናሉ። ያም ቢሆን በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ ቅን ሰዎች እንዳሉ ብሎም አምላክ ለእነዚህ ሰዎች ትኩረት እንደሚሰጣቸውና በምድር ላይ እንዳሉ አገልጋዮቹ አድርጎ እንደሚመለከታቸው ያስባሉ። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች ለአምላክ የተለየ ሕዝብ ሆነው እሱን ለማምለክ ከሐሰት ሃይማኖት መውጣት እንዳለባቸው ሆኖ አይሰማቸውም። ይሁንና አምላክ በዚህ ረገድ ምን አመለካከት አለው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የይሖዋን እውነተኛ አምላኪዎች ታሪክ በጥቂቱ በመቃኘት የዚህን ጥያቄ መልስ ማግኘት እንችላለን።

የቃል ኪዳን ሕዝብ

2. ለይሖዋ የተለየ ሕዝብ የሆኑት እነማን ናቸው? እነሱን ከሌሎች ብሔራት የሚለያቸውስ ምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

2 ይሖዋ ከ20ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. አንስቶ በምድር ላይ ለእሱ የተለየ  ሕዝብ ነበረው። “በእምነታቸው የተነሳ እንደ ጻድቃን ለተቆጠሩት ሁሉ አባት” የተባለው አብርሃም በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላት ላሉት ቤተሰቡ ራስ ነበር። (ሮም 4:11፤ ዘፍ. 14:14) በከነዓን የነበሩ ገዢዎች አብርሃምን “እንደ ኀያል መስፍን” ይመለከቱትና ያከብሩት ነበር። (ዘፍ. 21:22፤ 23:6) ይሖዋ ከአብርሃምና ከዘሮቹ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል። (ዘፍ. 17:1, 2, 19) አምላክ አብርሃምን እንዲህ ብሎት ነበር፦ “አንተና ከአንተም በኋላ የሚመጣው ዘርህ የምትጠብቁት ኪዳን ይህ ነው፤ በመካከላችሁ ያለ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። . . . ይህም በእኔና በእናንተ መካከል ላለው ኪዳን ምልክት ይሆናል።” (ዘፍ. 17:10, 11) በመሆኑም አብርሃምና በቤቱ ያሉ ወንዶች ሁሉ ተገረዙ። (ዘፍ. 17:24-27) ግርዘት፣ የአብርሃም ዘሮች ከይሖዋ ጋር ቃል ኪዳን የገቡ ብቸኛ ሕዝብ መሆናቸውን ለይቶ የሚያሳውቅ ምልክት ነበር።

3. የአብርሃም ዘሮች ሕዝብ የሆኑት እንዴት ነው?

3 የአብርሃም የልጅ ልጅ የሆነው ያዕቆብ ወይም እስራኤል 12 ወንዶች ልጆች ነበሩት። (ዘፍ. 35:10, 22ለ-26) ከጊዜ በኋላ እነዚህ ልጆች የ12ቱ የእስራኤል ነገዶች የቤተሰብ ራስ ሆነዋል። (ሥራ 7:8) ያዕቆብና ቤተሰቡ በሚኖሩበት አካባቢ ድርቅ በመከሰቱ ወደ ግብፅ ተሰደዱ፤ በዚያ የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ የፈርዖን የምግብ ክፍል ኃላፊና ቀኝ እጅ ሆኖ ይሠራ ነበር። (ዘፍ. 41:39-41፤ 42:6) ከጊዜ በኋላ የያዕቆብ ዘሮች በዝተው ‘የብዙ ሕዝብ ጉባኤ’ ሆኑ።—ዘፍ. 48:4 የ1954 ትርጉም፤ የሐዋርያት ሥራ 7:17ን አንብብ።

ይሖዋ የተቤዠው ሕዝብ

4. መጀመሪያ ላይ በግብፃውያንና በያዕቆብ ዘሮች መካከል የነበረው ግንኙነት ምን ይመስል ነበር?

4 የያዕቆብ ዘሮች፣ በግብፅ የአባይ ወንዝ ወደ ሜድትራንያን ባሕር በሚገባበት አካባቢ ባለው ጌሤም የተባለ ቦታ ከ200 ዓመታት በላይ ቆይተዋል። (ዘፍ. 45:9, 10) ከእነዚህ ዓመታት ግማሽ ያህሉን ከግብፃውያን ጋር በሰላም አብረው የኖሩ ይመስላል፤ የያዕቆብ ዘሮች ከብቶቻቸውን እያረቡ በትናንሽ ከተሞች ውስጥ ይኖሩ ነበር። በዚያን ጊዜ የነበረው ፈርዖን ዮሴፍን ያውቀውና ያከብረው ስለነበር ጥሩ አቀባበል አድርጎላቸዋል። (ዘፍ. 47:1-6) እርግጥ ግብፃውያን ለበግ አርቢዎች ጥላቻ ነበራቸው። (ዘፍ. 46:31-34) ያም ቢሆን የፈርዖንን ትእዛዝ ማክበር ስለነበረባቸው ከእስራኤላውያን ጋር ይኖሩ ነበር።

5, 6. (ሀ) በግብፅ የአምላክ ሕዝብ ሁኔታ የተለወጠው እንዴት ነው? (ለ) ሙሴ ከሞት የተረፈው እንዴት ነው? ይሖዋ ለሕዝቦቹ ሁሉ ምን አደረገ?

5 ከጊዜ በኋላ ግን የአምላክ ሕዝብ ያለበት ሁኔታ ተለወጠ። “በግብፅም፣ ስለ ዮሴፍ የማያውቅ አዲስ ንጉሥ ነገሠ። እርሱም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ ‘እነሆ፤ እስራኤላውያን በቍጥር በልጠውናል፤ ከእኛም ይልቅ እየበረቱ ነው።’” ከዚህም የተነሳ ግብፃውያን እስራኤላውያንን “ጭካኔ በተሞላበት [ሁኔታ] ያሠሯቸው ጀመር። ጭቃ በማስቦካት፣ ጡብ በማሠራትና በእርሻም ሁሉ እያስጨነቁ ከባድ ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ ሕይወታቸውን አስመረሩ፤ ግብፃውያኑ በሚያሠሯቸው ከባድ ሥራ ሁሉ ፈጽሞ አይራሩላቸውም ነበር።”—ዘፀ. 1:8, 9, 13, 14

6 ፈርዖን ይህም እንዳይበቃው ዕብራውያኑ የሚወልዷቸው ልጆች ወንድ ከሆኑ እንዲገደሉ አዋጅ አወጣ። (ዘፀ. 1:15, 16) ሙሴ የተወለደው በዚህ ወቅት ነበር። ሙሴ ሦስት ወር ሲሞላው እናቱ በአባይ ወንዝ ዳር ቄጠማ መካከል አስቀመጠችው፤ እዚያም የፈርዖን ልጅ አገኘችው። ከጊዜ በኋላም እንደ ልጇ አድርጋ ወሰደችው። ደስ የሚለው ነገር ሙሴን በሕፃንነቱ ያሳደገችው ታማኝ የሆነችው እናቱ ዮካብድ ናት፤ ሙሴም ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ ሆነ። (ዘፀ. 2:1-10፤ ዕብ. 11:23-25) ይሖዋ የሕዝቡን ሥቃይ ‘ስለተመለከተ’ ሙሴን መሪ አድርጎ በመሾም ከጨቋኞቻቸው እጅ ነፃ ሊያወጣቸው ወሰነ። (ዘፀ. 2:24, 25፤ 3:9, 10) በዚህ መንገድ እስራኤላውያን ይሖዋ ‘የሚቤዠው’ ሕዝብ  ይሆናሉ።—ዘፀ. 15:13፤ ዘዳግም 15:15ን አንብብ።

የአምላክ ሕዝብ ብሔር ሆነ

7, 8. የይሖዋ ሕዝብ የተቀደሰ ብሔር የሆነው እንዴት ነው?

7 ይሖዋ እስራኤላውያንን በብሔር ደረጃ ባያቋቁማቸውም የእሱ ሕዝብ እንዲሆኑ መርጧቸው ነበር። በመሆኑም ሙሴና አሮን ለፈርዖን እንዲህ የሚል መልእክት እንዲያስተላልፉ ይሖዋ ነግሯቸው ነበር፦ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ‘በምድረ በዳ በዓል እንዲያደርግልኝ ሕዝቤን ልቀቅ’ ይላል።”—ዘፀ. 5:1

8 እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ ለማውጣት ይሖዋ አሥር መቅሰፍቶች ማምጣት ብሎም ፈርዖንንና ሠራዊቱን ቀይ ባሕር ውስጥ ማስመጥ ግድ ሆኖበት ነበር። (ዘፀ. 15:1-4) ይህ ከተከናወነ ሦስት ወር ሳይሞላ ይሖዋ በሲና ተራራ ከእስራኤላውያን ጋር የሚከተለውን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ቃል ኪዳን ገባ፦ “በፍጹም ብትታዘዙኝና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ እነሆ ከአሕዛብ ሁሉ እናንተ የተወደደ ርስቴ ትሆናላችሁ፤ . . . የተቀደሰ ሕዝብ [“ብሔር፣” NW] ትሆናላችሁ።”—ዘፀ. 19:5, 6

9, 10. (ሀ) በዘዳግም 4:5-8 ላይ እንደተገለጸው ሕጉ እስራኤላውያንን ከሌሎች ሕዝቦች የተለዩ እንዲሆኑ ያደረጋቸው እንዴት ነው? (ለ) እስራኤላውያን ‘ለይሖዋ ቅዱስ ሕዝብ’ የሚሆኑት እንዴት ነው?

9 ዕብራውያን በግብፅ ውስጥ ባሪያ ከመሆናቸው በፊት በየነገዱ ተከፋፍለው ይኖሩ ነበር፤ የሚተዳደሩትም በቤተሰብ ራሶች ነበር። ከእነሱ በፊት እንደነበሩት የይሖዋ አገልጋዮች ሁሉ እነዚህ የቤተሰብ ራሶች ለቤተሰባቸው አስተዳዳሪ፣ ፈራጅና ካህን ሆነው ያገለግላሉ። (ዘፍ. 8:20፤ 18:19፤ ኢዮብ 1:4, 5) ይሁንና ይሖዋ ለእስራኤላውያን ከሌሎች ብሔራት ሁሉ የሚለያቸው ሕግ በሙሴ አማካኝነት ሰጣቸው። (ዘዳግም 4:5-8ን አንብብ፤ መዝ. 147:19, 20) በሕጉ ሥር ብሔሩን በክህነት የሚያገለግሉት ሰዎች የተለዩ ነበሩ፤ ፍርድ ነክ ጉዳዮችን ደግሞ በእውቀታቸውና በጥበባቸው የተከበሩ “ሽማግሌዎች” ይከታተሉ ነበር። (ዘዳ. 25:7, 8) ሕጉ፣ በአዲሱ ብሔር ውስጥ የታቀፉት ሰዎች ከሃይማኖታዊና ከማኅበራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚመሩባቸውን ደንቦች ይዞ ነበር።

10 እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው ትንሽ ቀደም ብሎ ይሖዋ ሕጉን በድጋሚ ነገራቸው፤ ሙሴም እንዲህ አላቸው፦ “ሕዝቡና ርስቱ መሆንህን፣ ትእዛዙንም ሁሉ እንደምትጠብቅ በዛሬው ዕለት ተናግሮአል፤ ከፈጠራቸው ሕዝቦች ሁሉ በላይ በምስጋና፣ በስም፣ በክብርም ከፍ እንደሚያደርግህና በሰጠውም ተስፋ መሠረት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ እንደምትሆን ተናግሮአል።”—ዘዳ. 26:18, 19

የባዕድ አገር ሰዎችም ይሖዋን ማምለክ ይችላሉ

11-13. (ሀ) ከአምላክ የተመረጠ ሕዝብ ጋር እነማን ተቀላቅለው ነበር? (ለ) እስራኤላዊ ያልሆነ ሰው ይሖዋን ማምለክ ከፈለገ ምን ማድረግ ይችል ነበር?

11 ይሖዋ በምድር ላይ የተመረጠ ብሔር ያለው ቢሆንም እስራኤላዊ ያልሆኑ ሰዎች በሕዝቦቹ መካከል እንዳይኖሩ አልከለከለም። ሕዝቡን ከግብፅ ሲያወጣቸው ግብፃውያንን ጨምሮ “ቍጥሩ የበዛ ሌላ ድብልቅ ሕዝብ” አብሯቸው እንዲወጣ ፈቅዷል። (ዘፀ. 12:38) ሰባተኛው መቅሰፍት ሊመጣ ሲል የይሖዋን ቃል የፈሩ አንዳንድ ‘የፈርዖን ሹማምንት’ ነበሩ፤ የግብፅን ምድር ለቅቆ ከወጣው ድብልቅ ሕዝብ መካከል እነዚህ ሰዎች እንደሚኖሩ ምንም ጥርጥር የለውም።—ዘፀ. 9:20

12 እስራኤላውያን የከነዓንን ምድር ለመውረስ ዮርዳኖስን ሊሻገሩ በተቃረቡበት ወቅት ሙሴ፣ በመካከላቸው ያሉትን ‘መጻተኞች እንዲወዱ’ ለሕዝቡ ነግሯቸው ነበር። (ዘዳ. 10:17-19) የአምላክ የተመረጠ ሕዝብ፣ በሙሴ አማካኝነት የተሰጡትን ሕጎች ለመታዘዝ ፈቃደኛ የሆነን ማንኛውም መጻተኛ የማኅበረሰቡ ክፍል አድርጎ መቀበል ነበረበት። (ዘሌ. 24:22) አንዳንድ መጻተኞች “ሕዝብሽ ሕዝቤ፤ አምላክሽ አምላኬ  ይሆናል” በማለት ለኑኃሚን እንደተናገረችው እንደ ሞዓባዊቷ ሩት የይሖዋ አምላኪዎች ሆነዋል። (ሩት 1:16) እነዚህ የሌላ አገር ሰዎች ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሲሆን ወንዶቹ ይገረዙ ነበር። (ዘፀ. 12:48, 49) ይሖዋም የመረጠው ሕዝብ አባል አድርጎ ተቀብሏቸዋል።—ዘኁ. 15:14, 15

እስራኤላውያን መጻተኞችን ይወዱ ነበር (ከአንቀጽ 11-13ን ተመልከት)

13 የሰለሞን ቤተ መቅደስ ለይሖዋ ሲወሰን ሰለሞን ካቀረበው ጸሎት መመልከት እንደሚቻለው እስራኤላዊ ላልሆኑ የይሖዋ አምላኪዎች የተደረገ ዝግጅት ነበር፤ ሰለሞን እንዲህ ብሏል፦ “ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ ባዕድ ሰው ስለ ታላቁ ስምህ፣ ስለ ኀያሉ እጅህና ስለ ተዘረጋው ክንድህ ሰምቶ ከሩቅ አገር በመምጣት ወደዚህ ቤተ መቅደስ በሚጸልይበት ጊዜ፣ በሰማይ በማደሪያህ ሆነህ ስማ፤ የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንደገዛ ሕዝብህ እንደ እስራኤል፣ ስምህን በማወቅ እንዲፈሩህ፣ የሠራሁትም ይህ ቤት ስምህ የሚጠራበት ቤት መሆኑን እንዲያውቁ ባዕዱ ሰው የሚጠይቅህን ሁሉ አድርግ።” (2 ዜና 6:32, 33) ኢየሱስ ከመጣም በኋላ፣ እስራኤላዊ ያልሆኑና ይሖዋን ማምለክ የሚፈልጉ ሰዎች ከይሖዋ የቃል ኪዳን ሕዝብ ጋር መተባበር ይችሉ ነበር።—ዮሐ. 12:20፤ ሥራ 8:27

ምሥክር የሆነ ብሔር

14-16. (ሀ) እስራኤላውያን ለይሖዋ የሚመሠክር ብሔር የሚሆኑት እንዴት ነበር? (ለ) በዘመናችን ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች ምን የማድረግ ግዴታ አለባቸው?

14 እስራኤላውያን አምላካቸውን ይሖዋን ሲያመልኩ ሌሎች ብሔራት ደግሞ የተለያዩ አማልክት ነበሯቸው። በነቢዩ ኢሳይያስ ዘመን ይሖዋ በዓለም ላይ የነበረውን ሁኔታ ከፍርድ ሸንጎ ጋር አነጻጽሮታል። ይሖዋ የሌሎች ብሔራት አማልክት፣ አምላክነታቸውን የሚያረጋግጥ ምሥክር እንዲያቀርቡ ሲጠይቃቸው እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ሕዝብ ሁሉ በአንድነት ይሰብሰብ፤ ሰውም ይከማች፤ ከእነርሱ [ከአማልክቶቻቸው መካከል] አስቀድሞ ይህን የነገረን፣ የቀድሞውን ነገር ያወጀልን ማን ነው? ሌሎችን ሰምተው፣ ‘እውነት ነው’ እንዲሉ፣ ትክክለኝነታቸውም እንዲረጋገጥ ምስክሮቻቸውን ያቅርቡ።”—ኢሳ. 43:9

15 ይሁን እንጂ የሌሎች ብሔራት አማልክት፣ አምላክነታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ አልቻሉም። እነዚህ አማልክት መናገር የማይችሉና ሰው ካልተሸከማቸው በስተቀር የማይንቀሳቀሱ ጣዖታት ናቸው። (ኢሳ. 46:5-7)  በሌላ በኩል ግን ይሖዋ ሕዝቡን እስራኤላውያንን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ፣ እርሱ እኔ እንደ ሆንሁ ትረዱ ዘንድ፣ እናንተ ምስክሮቼ፣ የመረጥሁትም ባሪያዬ ናችሁ . . . ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም፤ ከእኔም በኋላ አይኖርም። እኔ፣ እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ነኝ፤ ከእኔም ሌላ የሚያድን የለም። . . . እኔ አምላክ እንደ ሆንሁ፣ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ።”—ኢሳ. 43:10-12

16 የይሖዋ የተመረጠ ሕዝብ “የአጽናፈ ዓለም ልዑል የሆነው አምላክ ማን ነው?” ከሚለው ጉዳይ ጋር በተያያዘ በጽንፈ ዓለም የፍርድ ሸንጎ ፊት እንደቀረቡ ምሥክሮች በመሆን እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ብቻ መሆኑን በግልጽ ሊመሠክሩ ነው። ይሖዋ ‘ምስጋናዬን ያውጅ ዘንድ ለራሴ ያበጀሁት ሕዝብ’ በማለት ጠርቷቸዋል። (ኢሳ. 43:21) ስሙን የሚሸከም ሕዝብ ነበሩ። ይሖዋ ከግብፅ ባርነት ስለተቤዣቸው በሌሎች የምድር ሕዝቦች ፊት የእሱን አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት የመደገፍ ግዴታ ነበረባቸው። ሕዝቡ ነቢዩ ሚክያስ በአሁኑ ዘመን ስላሉ የአምላክ ሕዝቦች የገለጸው ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይገባ ነበር፤ ሚክያስ እንዲህ ብሏል፦ “አሕዛብ ሁሉ፣ በአማልክቶቻቸው ስም ይሄዳሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ስም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም እንሄዳለን።”—ሚክ. 4:5

ከዳተኛ ሕዝብ

17. እስራኤል በይሖዋ ዓይን “ብልሹ የዱር ወይን” የሆነው እንዴት ነው?

17 የሚያሳዝነው ግን እስራኤላውያን ለአምላካቸው ታማኝ አልነበሩም። የእንጨትና የድንጋይ አማልክት የሚያመልኩ ብሔራት ተጽዕኖ እንዲያደርጉባቸው ፈቀዱ። በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነቢዩ ሆሴዕ እስራኤል እንደተበላሸ ወይን እንደሆነ ገልጾ ነበር። አክሎም “እስራኤል . . . ብዙ መሠዊያዎችን ሠራ፤ . . . ልባቸው አታላይ ነው፤ ስለዚህም በደላቸውን ይሸከማሉ” በማለት ጽፏል። (ሆሴዕ 10:1, 2) ሆሴዕ ይህን ካለ ከ150 ዓመታት ገደማ በኋላ ኤርምያስ፣ ይሖዋ ታማኝ ላልሆኑት ሕዝቦቹ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ አስፍሯል፦ “እኔ፣ እንደ ምርጥ የወይን ተክል፣ ጤናማና አስተማማኝ ዘር አድርጌ ተክዬሽ ነበር፤ ታዲያ ብልሹ የዱር ወይን ተክል ሆነሽ፣ እንዴት ተለወጥሽብኝ?” አክሎም ለይሁዳ ሕዝብ “ልታመልካቸው ያበጀሃቸው አማልክት ወዴት ናቸው? በመከራህ ጊዜ ሊያድኑህ የሚችሉ ከሆነ፣ ይሁዳ ሆይ፤ እስቲ ይምጡና ያድኑህ፤ . . . ሕዝቤ ግን . . . ረስቶኛል” ብሏል።—ኤር. 2:21, 28, 32

18, 19. (ሀ) ይሖዋ ለስሙ የሚሆን አዲስ ሕዝብ እንደሚኖረው አስቀድሞ የተናገረው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

18 የእስራኤል ሕዝብ እውነተኛውን አምልኮ በመከተልና ከይሖዋ ታማኝ ምሥክሮች የሚጠበቀውን በማድረግ መልካም ፍሬ ከማፍራት ይልቅ በጣዖት አምልኮ ስለተዘፈቀ የበሰበሰ ፍሬ አፍርቷል። በዚህም የተነሳ ኢየሱስ በጊዜው ለነበሩት ግብዝ የሃይማኖት መሪዎች “የአምላክ መንግሥት ከእናንተ ተወስዶ ፍሬውን ለሚያፈራ ሕዝብ ይሰጣል” ብሏቸዋል። (ማቴ. 21:43) የዚህ አዲስ ብሔር ማለትም የመንፈሳዊ እስራኤል አባላት የሚሆኑት፣ ይሖዋ በነቢዩ ኤርምያስ ባስነገረው “አዲስ ቃል ኪዳን” ውስጥ የታቀፉት ሰዎች ብቻ ናቸው። በዚህ አዲስ ቃል ኪዳን የሚታቀፉትን መንፈሳዊ እስራኤላውያንን በተመለከተ ይሖዋ “እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ” የሚለውን ትንቢት ተናግሮ ነበር።—ኤር. 31:31-33

19 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ይሖዋ፣ ሥጋዊ እስራኤላውያን ታማኝነታቸውን ካጓደሉ በኋላ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መንፈሳዊ እስራኤላውያን ሕዝቡ እንዲሆኑ አደረገ። ይሁንና በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የእሱ ሕዝብ የሆኑት እነማን ናቸው? ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮችን መለየት የሚችሉት እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ላይ ያተኮረ ነው።