“በጎችህ በምን ሁኔታ እንዳሉ ደህና አድርገህ ዕወቅ።”—ምሳሌ 27:23

በጥንቷ እስራኤል የእረኞች ሕይወት አድካሚ ነበር። እረኞች ሐሩርና ቁር የሚፈራረቅባቸው ከመሆኑም ሌላ መንጎቻቸውን ሊጎዱ ከሚችሉ አራዊትም ሆነ ሰዎች መጠበቅ ነበረባቸው። የበጎቻቸውን ሁኔታ አዘውትረው የሚከታተሉ ሲሆን የታመሙ ወይም የተጎዱ ካሉ እርዳታ ያደርጉላቸዋል። በተለይ ደግሞ እንክብካቤ ለሚያሻቸውና እንደ ትላልቆቹ በጎች ጠንካራ ላልሆኑት ግልገሎች ልዩ ትኩረት ይሰጣሉ።—ዘፍ. 33:13

1, 2. (ሀ) አንድ እስራኤላዊ እረኛ ምን ኃላፊነቶች ነበሩት? (ለ) ወላጆች እንደ እረኛ የሆኑት እንዴት ነው?

2 በአንዳንድ ጉዳዮች ረገድ ክርስቲያን ወላጆች ልክ እንደ እረኞች ናቸው ማለት ይቻላል፤ እረኞች የሚያስፈልጓቸው ዓይነት ባሕርያት ማዳበር ይኖርባቸዋል። ልጆቻቸውን “በይሖዋ ተግሣጽ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ በውስጣቸው በመቅረጽ” የማሳደግ ኃላፊነት አለባቸው። (ኤፌ. 6:4) ይህን ማድረግ ቀላል ነው? በጭራሽ! ልጆች የሰይጣን ፕሮፓጋንዳ የሚዥጎደጎድባቸው ከመሆኑም ሌላ ከራሳቸው አለፍጽምና ጋር መታገል ያስፈልጋቸዋል። (2 ጢሞ. 2:22፤ 1 ዮሐ. 2:16) ታዲያ ልጆች ካሏችሁ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው? ልጆቻችሁን እንደ እረኛ ሆናችሁ ለመንከባከብ የሚረዷችሁን ሦስት ነገሮች እስቲ እንመልከት፤ እነዚህም ልጆቻችሁን ማወቅ፣ መመገብና መምራት ናቸው።

 ልጆቻችሁን እወቋቸው

3. ወላጆች፣ ልጆቻቸው “በምን ሁኔታ እንዳሉ” ማወቅ የሚችሉት እንዴት ነው?

3 ጥሩ እረኛ እያንዳንዱን በግ በጥንቃቄ በመመርመር ጤናማ መሆኑን ያረጋግጣል። እናንተም ለልጆቻችሁ እንዲሁ ማድረግ ትችላላችሁ። መጽሐፍ ቅዱስ “በጎችህ በምን ሁኔታ እንዳሉ ደህና አድርገህ ዕወቅ” ይላል። (ምሳሌ 27:23) ለዚህም ልጆቻችሁ የሚያደርጉትን ነገር ብቻ ሳይሆን አስተሳሰባቸውንና ስሜታቸውንም ጭምር ማወቅ ያስፈልጋችኋል። ታዲያ ይህንን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? በጣም ውጤታማ ከሆኑት መንገዶች አንዱ ከልጆቻችሁ ጋር አዘውትራችሁ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ነው።

4, 5. (ሀ) ልጆች ለወላጆቻቸው ስሜታቸውን ለመግለጽ እንዲነሳሱ ሊረዷቸው የሚችሉት ነጥቦች የትኞቹ ናቸው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) (ለ) ልጆቻችሁ ከእናንተ ጋር ማውራት ቀላል እንዲሆንላቸው ምን አድርጋችኋል?

4 አንዳንድ ወላጆች፣ ልጆቻቸው ወደ አሥራዎቹ ዕድሜ ሲገቡ ከእነሱ ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ይበልጥ አስቸጋሪ እንደሚሆን ይናገራሉ። በዚህ ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆች ራሳቸውን ያገልሉ እንዲሁም ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን መግለጽ ይከብዳቸው ይሆናል። ልጆቻችሁ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ የሚያሳዩ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ከልጆቻችሁ ጋር ቁም ነገር አዘል የሆነ ረጅም ውይይት ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ ዘና ባለ መንገድ ከእነሱ ጋር ለመጨዋወት አጋጣሚዎችን ፈልጉ። (ዘዳ. 6:6, 7) ከልጆቻችሁ ጋር አንዳንድ ነገሮችን አብራችሁ ለማከናወን ተጨማሪ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋችሁ ይሆናል። በእግራችሁ አሊያም በመኪና ወጣ ብላችሁ መንሸራሸር፣ አንድ ዓይነት ጨዋታ አብራችሁ መጫወት ወይም የቤት ውስጥ ሥራ መሥራት ትችላላችሁ። እንዲህ ያሉ በዕለት ተዕለት ሕይወት የሚፈጠሩ አጋጣሚዎችን መጠቀም በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ስሜታቸውን አውጥተው መናገር ቀላል እንዲሆንላቸው ሊያደርግ ይችላል።

5 ይህንንም አድርጋችሁ ልጃችሁ ከእናንተ ጋር ለማውራት ፈቃደኛ ባይሆንስ? ለየት ያለ ዘዴ መጠቀም ትችላላችሁ። ለምሳሌ ያህል፣ ልጃችሁ ውሎዋ እንዴት እንደነበር ከመጠየቅ ይልቅ እናንተ ቀኑን እንዴት እንዳሳለፋችሁ መናገር ትችላላችሁ። ይህን ስታደርጉ እሷም ስለ ውሎዋ ለመናገር ትነሳሳ ይሆናል። አሊያም ደግሞ ልጃችሁ ስለ አንድ ጉዳይ ያላትን አመለካከት ለማወቅ ከፈለጋችሁ እሷ ላይ የማያነጣጥሩ ጥያቄዎችን ተጠቀሙ። ጓደኞቿ ስለዚህ ጉዳይ ምን አመለካከት እንዳላቸው ልትጠይቋት ትችላላችሁ። ከዚያም በዚህ ጉዳይ ላይ ለጓደኞቿ ምን ምክር እንደምትሰጥ ጠይቋት።

6. ወላጆች ለልጆቻቸው ጊዜያቸውን መስጠትና በቀላሉ የሚቀረቡ መሆን አለባቸው ሲባል ምን ማለት ነው?

6 እርግጥ ነው፣ ልጆቻችሁ የልባቸውን አውጥተው እንዲያዋሯችሁ ከፈለጋችሁ ጊዜያችሁን ሰጥታችሁ እንደምታዳምጧቸውና በቀላሉ ሊቀርቧችሁ እንደሚችሉ እንዲሰማቸው ልታደርጉ ይገባል። ወጣቶች ወላጆቻቸው ሁልጊዜ ሥራ እንደሚበዛባቸውና እነሱን ለመስማት ጊዜ እንደሌላቸው ከተሰማቸው ችግራቸውን ይደብቃሉ። በሌላ በኩል ደግሞ እናንተ ወላጆችስ በቀላሉ የምትቀረቡ ናችሁ? “በፈለግከኝ ጊዜ ልታናግረኝ ትችላለህ” ማለት ብቻ በቂ አይደለም። በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጆቻችሁ ችግሮቻቸውን አቅልላችሁ አሊያም ከመጠን በላይ አክብዳችሁ እንደማትመለከቱ ሊሰማቸው ይገባል። ብዙ ወላጆች በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ። የ19 ዓመቷ ኬይላ እንዲህ ብላለች፦ “ከአባቴ ጋር ስለ ማንኛውም ነገር ማውራት እችላለሁ፤ ስናገር አያቋርጠኝም እንዲሁም የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማኝ አያደርግም። ከዚህ ይልቅ ጸጥ ብሎ ያዳምጠኛል። ምንጊዜም ጥሩ ምክር ይሰጠኛል።”

7. (ሀ) ወላጆች የፍቅር ጓደኛ እንደ መያዝ ባሉት ጉዳዮች ላይ ምን ዓይነት ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? (ለ) ወላጆች ሳያስቡት ልጆቻቸውን ሊያበሳጯቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

7 ለማውራት በሚከብዱ ጉዳዮች ለምሳሌ የፍቅር ጓደኛ መያዝን በመሳሰሉ ርዕሶች ላይ በምትነጋገሩበት ጊዜ እንኳ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ላይ ከመጠን በላይ ትኩረት አታድርጉ፤ ከዚህ ይልቅ ልጆቻችሁ ጉዳዩን መያዝ የሚችሉበትን ትክክለኛ መንገድ አስተምሯቸው። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፦ አንድ ምግብ ቤት ገባችሁ እንበል፤ የምግብ ማዘዣውን ስትመለከቱ ስለ ምግብ መበከል በሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ብቻ እንደተሞላ አስተዋላችሁ። ከዚያ ወጥታችሁ ወደ ሌላ ምግብ ቤት እንደምትሄዱ ጥያቄ የለውም። ልጆቻችሁም ምክር ፈልገው ወደ እናንተ  ሲመጡ ማስጠንቀቂያዎችን ብታዥጎደጉዱባቸው ተመሳሳይ ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ። (ቆላስይስ 3:21ን አንብብ።) የተሻለ የሚሆነው ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበሩ ነው። ኤምሊ የተባለች ወጣት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ስለ ፍቅር ጓደኝነት ሲያናግሩኝ መጥፎ ነገር እንደሆነ አድርገው አያወሩም። ከአንድ ሰው ጋር መተዋወቅና የትዳር ጓደኛ ማግኘት አስደሳች ነገር እንደሆነ ብዙ ጊዜ ይነግሩኛል። ይህም ከእነሱ ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ መነጋገር ቀላል እንዲሆንልኝ አድርጓል። እንዲያውም የፍቅር ጓደኛ ቢኖረኝ ጉዳዩን ከእነሱ ከመደበቅ ይልቅ በግልጽ ልነግራቸው እፈልጋለሁ።”

8, 9. (ሀ) ወላጆች ልጆቻቸው ሲናገሩ ጣልቃ ሳይገቡ ማዳመጣቸው ምን ጥቅሞች አሉት? (ለ) ልጆቻችሁን በማዳመጥ ረገድ ምን ያህል ተሳክቶላችኋል?

8 ወላጆች፣ ኬይላ እንደተናገረችው በትዕግሥት ልጆቻችሁን በማዳመጥ በቀላሉ የምትቀረቡ መሆናችሁን ማሳየት ትችላላችሁ። (ያዕቆብ 1:19ን አንብብ።) ካትያ የተባለች አንዲት ነጠላ ወላጅ እንዲህ ብላለች፦ “ቀደም ሲል ልጄን መታገሥ ይከብደኝ ነበር። ሐሳቧን ተናግራ ሳትጨርስ አቋርጣታለሁ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በጣም ስለሚደክመኝ ወይም ስልችት ስለሚለኝ አላዳምጣትም። እኔ ለውጥ ሳደርግ ግን ልጄም ተለወጠች። አሁን እሷም የውስጧን አውጥታ ትነግረኛለች።”

ልጆቻችሁን ለማወቅ አዳምጧቸው (ከአንቀጽ 3-9ን ተመልከት)

9 ሮናልድ የተባለ አባትም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ከምትገኝ ልጁ ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ነገር አጋጥሞታል። እንዲህ ብሏል፦ “ልጄ በትምህርት ቤቷ የሚገኝ አንድ ልጅ እንደወደደች ስትነግረኝ መጀመሪያ ላይ በጣም ተበሳጨሁ። ሆኖም ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚይዘው በትዕግሥትና በምክንያታዊነት እንደሆነ ሳስብ ለልጄ እርማት ከመስጠቴ በፊት ስሜቷን እንድትገልጽ አጋጣሚ ብሰጣት የተሻለ እንደሚሆን ተሰማኝ። እንዲህ በማድረጌም በኋላ ላይ ደስ ብሎኛል! የልጄን ስሜት ለመጀመሪያ ጊዜ መረዳት ቻልኩ። ሐሳቧን ተናግራ ስትጨርስ፣ ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ እሷን ማናገር አልከበደኝም። የሚገርመው የሰጠኋትን ምክር ደስ ብሏት ተቀበለች። ባሕርይዋን ለማስተካከል እንደምትፈልግም ገለጸችልኝ።” ከልጆቻችሁ ጋር አዘውትራችሁ ማውራታችሁ ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን ይበልጥ ለመረዳት ያስችላችኋል። ይህ ደግሞ በሕይወታቸው ውስጥ በሚያደርጓቸው ውሳኔዎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ለማሳደር ያስችላችኋል። *

ልጆቻችሁን መግቧቸው

10, 11. ልጆቻችሁ ከእውነት ጎዳና ቀስ በቀስ እየራቁ እንዳይሄዱ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው?

10 አንድ ጥሩ እረኛ አንዳንድ በጎች ከመንጋው ተለይተው ሊባዝኑ እንደሚችሉ ያውቃል። አንድ በግ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚያጋጥመው የተሻለ የሚመስል ሣር ሲያይ ያንን ለማግኘት ብሎ ሳያውቀው ቀስ በቀስ ከመንጋው እየራቀ በመሄዱ ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይም አንድ ልጅ በመጥፎ  ጓደኞች ወይም ወራዳ በሆነ መዝናኛ ተስቦ ቀስ በቀስ እየራቀ በመሄድ በመንፈሳዊ አደገኛ የሆነ ጎዳና ሊከተል ይችላል። (ምሳሌ 13:20) ልጃችሁ እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ እንዳይገባ መከላከል የምትችሉት እንዴት ነው?

11 ልጆቻችሁን በምታሠለጥኑበት ጊዜ የሆነ ድክመት እንዳለባቸው ካስተዋላችሁ ሳትዘገዩ እርምጃ ውሰዱ። ልጆቻችሁ ያሏቸውን ክርስቲያናዊ ባሕርያት በማስተዋል እነዚህን ይበልጥ ለማጠናከር ጥረት አድርጉ። (2 ጴጥ. 1:5-8) ቋሚ የሆነ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ይህን ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥርላችኋል። የጥቅምት 2008 የመንግሥት አገልግሎታችን ስለ ቤተሰብ አምልኮ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “የቤተሰብ ራሶች ቋሚና የታሰበበት የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም እንዲኖራቸው በማድረግ ይሖዋ የጣለባቸውን ኃላፊነት መወጣት ይገባቸዋል።” እናንተስ ልጆቻችሁን እንደ እረኛ ለመንከባከብ ፍቅር በሚንጸባረቅበት በዚህ ዝግጅት ሙሉ በሙሉ እየተጠቀማችሁ ነው? የልጆቻችሁን መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ቅድሚያ የምትሰጡ ከሆነ ልጆቹ ይህን እንደሚያደንቁ እርግጠኛ ሁኑ።—ማቴ. 5:3፤ ፊልጵ. 1:10

በሚገባ መግቧቸው (ከአንቀጽ 10-12ን ተመልከት)

12. (ሀ) ቋሚ የቤተሰብ አምልኮ አንዳንድ ወጣቶችን የጠቀማቸው እንዴት ነው? (“ ፕሮግራሙን ወደውታል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) ከቤተሰብ አምልኮ ምን ጥቅም አግኝተሃል?

12 በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ካሪሳ የተባለች ወጣት የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ቤተሰቧን እንዴት እንደጠቀመው ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ሁላችንም አብረን ቁጭ ብለን ማውራታችን ያስደስተኛል። እንዲህ ማድረጋችን እርስ በርስ ያቀራርበናል፤ እንዲሁም የማንረሳው ጊዜ እናሳልፋለን። አባቴ የቤተሰብ ጥናት ፕሮግራማችን ቋሚ እንዲሆን አድርጓል። ፕሮግራሙን በቁም ነገር የሚመለከተው መሆኑ ያበረታታል፤ እኔም ይህን ፕሮግራም ከፍ አድርጌ እንድመለከተው አነሳስቶኛል። በተጨማሪም በአባትነቱና በመንፈሳዊ ነገሮች አመራር የሚሰጥ የቤተሰቡ ራስ በመሆኑ ይበልጥ እንዳከብረው አድርጎኛል።” ብሪትኒ የተባለች አንዲት ወጣት እህት እንዲህ ብላለች፦ “የቤተሰብ አምልኮ ከወላጆቼ ጋር በጣም አቀራርቦኛል። ይህ ፕሮግራም ወላጆቼ ስለ ችግሮቼ ማወቅ እንደሚፈልጉ እንዲሁም ስለ እኔ በጥልቅ እንደሚያስቡ አስገንዝቦኛል። ጠንካራና አንድነት ያለው ቤተሰብ እንዲኖረን አድርጓል።” በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጥሩ እረኛ መሆን የምትችሉበት ዋነኛው መንገድ ልጆቻችሁን በመንፈሳዊ መመገብ በተለይም የቤተሰብ አምልኮ እንዲኖራችሁ ማድረግ ነው። *

ልጆቻችሁን ምሯቸው

13. አንድ ልጅ ይሖዋን የማገልገል ፍላጎት እንዲኖረው መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው?

13 ጥሩ እረኛ መንጋውን ለመምራትና ከአደጋ ለመጠበቅ በትር ይጠቀማል። እረኛው ካሉት ኃላፊነቶች አንዱ በጎቹን ‘በመልካም የግጦሽ መሬት’ ላይ ማሰማራት ነው። (ሕዝ. 34:13, 14) ወላጆች፣ እናንተስ በመንፈሳዊ ሁኔታ ግባችሁ ይኸው አይደል? ልጆቻችሁን በመምራት ይሖዋን እንዲያገለግሉ መርዳት እንደምትፈልጉ የታወቀ ነው። ልጆቻችሁ “አምላኬ ሆይ፤ ፈቃድህን ላደርግ እሻለሁ፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ አለ” ብሎ እንደጻፈው መዝሙራዊ እንዲሰማቸው ትፈልጋላችሁ። (መዝ. 40:8) እንዲህ ያለ የአድናቆት ስሜት ያላቸው ወጣቶች ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው ይጠመቃሉ። እርግጥ ነው፣ ራሳቸውን መወሰን ያለባቸው ይህን እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ብስለት እንዲሁም ይሖዋን ለማገልገል የሚያነሳሳ ልባዊ ፍላጎት ሲኖራቸው ነው።

14, 15. (ሀ) ክርስቲያን ወላጆች ምን ግብ ሊኖራቸው ይገባል? (ለ) በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ እውነተኛውን አምልኮ እንደተጠራጠረ የሚገልጸው ለምን ሊሆን ይችላል?

14 ይሁንና ልጆቻችሁ መንፈሳዊ እድገት የማያደርጉ ቢሆኑስ? ምናልባትም ስለ እምነታቸው ጥርጣሬ ቢያድርባቸውስ? ለይሖዋ አምላክ ፍቅር እንዲሁም ላደረጋቸው በርካታ ነገሮች አድናቆት እንዲያድርባቸው ለመርዳት ጥረት አድርጉ። (ራእይ 4:11) እንዲህ ካደረጋችሁ ይሖዋን ለማምለክ ዝግጁ እንደሆኑ ሲሰማቸው ይህን እርምጃ ለመውሰድ ሊወስኑ ይችላሉ።

15 ሆኖም ልጆቻችሁ እውነትን መጠራጠር ቢጀምሩስ? እነሱን ለመርዳት አሁን ምን ማድረግ ትችላላችሁ? እንደ እረኛ በመሆን ልትጠብቋቸው እንዲሁም ይሖዋን ማገልገል ከሁሉ የተሻለ ሕይወት  ለመምራት እንደሚያስችላቸውና ዘላቂ ደስታ እንደሚያስገኝላቸው እንዲገነዘቡ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው? ልጆቻችሁ እውነትን እንዲጠራጠሩ ያደረጋቸውን ትክክለኛ ምክንያት ለማወቅ ሞክሩ። ለምሳሌ፣ ልጃችሁ እውነትን እንደሚጠራጠር የገለጸው መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረው ነገር ሳይስማማ ቀርቶ ነው? ወይስ በእኩዮቹ ፊት ስለ እምነቱ ለመናገር ድፍረት አጥቶ? ሴት ልጃችሁስ በአምላክ መሥፈርቶች ላይ ጥያቄ ያነሳችው መሥፈርቶቹን መከተል የጥበብ አካሄድ መሆኑን ሳታምን ቀርታ ነው? ወይስ ብቸኛ እንደሆነች ወይም ሌሎች እንደሚያገልሏት ተሰምቷት?

በሚሄዱበት መንገድ ምሯቸው (ከአንቀጽ 13-18ን ተመልከት)

16, 17. ወላጆች፣ ልጆቻቸው እውነትን የራሳቸው እንዲያደርጉ ሊረዷቸው የሚችሉት በየትኞቹ መንገዶች ነው?

16 ልጆቻችሁ እምነታችሁን እንዲጠራጠሩ ያደረጋቸው ምክንያት ምንም ይሁን ምን ጥርጣሬያቸውን እንዲያስወግዱ ልትረዷቸው ትችላላችሁ። እንዴት? በርካታ ወላጆች ጠቃሚና ውጤታማ ሆኖ ያገኙት አንዱ ዘዴ የልጆቻቸውን ስሜት ለማወቅ እንዲህ ብሎ መጠየቅ ነው፦ “የይሖዋ ምሥክር መሆን ከባድ እንደሆነ ይሰማሃል? ምን ጥቅም ያለው ይመስልሃል? ምን መሥዋዕትነት የሚያስከፍል ይመስልሃል? ይሖዋን በማገልገልህ ዛሬም ሆነ ወደፊት የምታገኛቸው በርካታ ጥቅሞች ከምትከፍለው መሥዋዕት እንደሚበልጡ ይሰማሃል? እንዴት?” እርግጥ ነው፣ እነዚህን ጥያቄዎች የምታቀርቡት በራሳችሁ አነጋገር እንዲሁም ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድና በአሳቢነት እንጂ በማፋጠጥ ሊሆን አይገባም። በውይይታችሁ መሃል ማርቆስ 10:29, 30 ላይ ያለውን ሐሳብ ማንሳት ትችላላችሁ። አንዳንድ ወጣቶች ክርስቲያን መሆን ስለሚያስከፍለው መሥዋዕትነትና ስለሚያስገኘው ጥቅም ወረቀት ላይ መጻፍ ይፈልጉ ይሆናል። ጥቅሙንና መሥዋዕቱን በሁለት ረድፍ አስፍረው ሲመለከቱት ችግሮቻቸውን ማወቅና መፍትሔ ማግኘት ይችላሉ። ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እና ከአምላክ ፍቅርየተባሉትን መጻሕፍት ማስጠናት የሚያስፈልገን ከሆነ ከልጆቻችን ጋርም ይህን ማድረግ እንዳለብን ጥያቄ የለውም! እናንተስ ይህን እያደረጋችሁ ነው?

17 ልጆቻችሁ ማንን እንደሚያገለግሉ ውሎ አድሮ መወሰናቸው አይቀርም። የእናንተ እምነት እንዲሁ በውስጣቸው ይሰርጻል ብላችሁ አታስቡ። እውነትን የራሳቸው ማድረግ አለባቸው። (ምሳሌ 3:1, 2) አንድ ልጅ ይህን ማድረግ ካስቸገረው መሠረታዊ ከሆኑት ነገሮች ለምን አትጀምሩም? እንደሚከተሉት ባሉት ጥያቄዎች ላይ እንዲያስብ እርዱት። “አምላክ መኖሩን ያሳመነኝ ምንድን ነው? ይሖዋ አምላክ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠኝ ያሳመነኝ ምንድን ነው? የይሖዋ መመሪያዎች ለእኔው ጥቅም እንደሆኑ የማምነው ለምንድን ነው?” ልጆቻችሁ የይሖዋ መንገድ ከሁሉ የተሻለ ሕይወት እንደሚያስገኝላቸው ራሳቸው እንዲያረጋግጡ በትዕግሥት በመምራት ጥሩ እረኛ ሁኑላቸው። *ሮም 12:2

18. ወላጆች ታላቁን እረኛ ማለትም ይሖዋን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው?

18 ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ታላቁን እረኛ መምሰል ይፈልጋሉ። (ኤፌ. 5:1፤ 1 ጴጥ. 2:25) በተለይ ደግሞ ወላጆች፣ በጎቻቸው ማለትም ውድ የሆኑት ልጆቻቸው በምን ሁኔታ እንዳሉ ማወቅና ይሖዋ ያዘጋጀላቸውን በረከት እንዲወርሱ ለመምራት የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ አለባቸው። እንግዲያው ለልጆቻችሁ እንደ እረኛ በመሆን እነሱን በእውነት ውስጥ ለማሳደግ ጥረት ማድረጋችሁን ቀጥሉ!

^ አን.9 ተጨማሪ ሐሳቦች ለማግኘት የነሐሴ 1, 2008 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 10-12 ተመልከት።

^ አን.12 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በጥቅምት 15, 2009 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 29-31 ላይ የወጣውን “የቤተሰብ አምልኮ ከጥፋት ለመዳን ወሳኝ ነው!” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.17 ይህን በተመለከተ በየካቲት 1, 2012 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 18-21 ላይ ተጨማሪ ሐሳብ ይገኛል።