በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  መስከረም 2014

“ብዙ መከራ” ቢኖርም አምላክን በታማኝነት አገልግሉ

“ብዙ መከራ” ቢኖርም አምላክን በታማኝነት አገልግሉ

“ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት በብዙ መከራ ውስጥ ማለፍ አለብን።”—ሥራ 14:22

የዘላለም ሕይወት ሽልማት ከማግኘትህ በፊት “ብዙ መከራ” ሊያጋጥምህ እንደሚችል ማሰቡ ያስፈራሃል? ያን ያህል አትፈራ ይሆናል። ወደ እውነት የመጣኸው በቅርቡም ይሁን ከረጅም ዓመታት በፊት በሰይጣን ዓለም ውስጥ እስካለን ድረስ መከራ የማይቀር ነገር እንደሆነ ታውቃለህ።—ራእይ 12:12

2. (ሀ) ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ሁሉ ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች በተጨማሪ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት መከራ ይደርስባቸዋል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) (ለ) ከሚደርስብን መከራ በስተጀርባ ያለው ማን ነው? እንዲህ የምንለውስ ለምንድን ነው?

2 “በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና” ማለትም ፍጽምና በጎደላቸው የሰው ልጆች ሁሉ ላይ ከሚደርሱት ችግሮች በተጨማሪ ክርስቲያኖች የተለየ ዓይነት መከራ ያጋጥማቸዋል። (1 ቆሮ. 10:13) ይህ ፈተና ምንድን ነው? ክርስቲያኖች የአምላክን ሕግጋት ለመጠበቅ ባላቸው ጥብቅ አቋም የተነሳ ከፍተኛ ተቃውሞ ያጋጥማቸዋል። ኢየሱስ ተከታዮቹን “ባሪያ ከጌታው አይበልጥም . . . እኔን ስደት አድርሰውብኝ ከሆነ እናንተንም ስደት ያደርሱባችኋል” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 15:20) ከዚህ ተቃውሞ በስተጀርባ ያለው ማን ነው? ሰይጣን ነው፤ ሰይጣን የአምላክን ሕዝቦች “[ለመዋጥ] በመፈለግ እንደሚያገሳ አንበሳ” እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (1 ጴጥ. 5:8) ሰይጣን፣ የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት የታማኝነት አቋም ለማላላት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። እስቲ በሐዋርያው ጳውሎስ ላይ የደረሰውን ሁኔታ እንመልከት።

 በልስጥራ የደረሰበት መከራ

3-5. (ሀ) ጳውሎስ በልስጥራ ምን ዓይነት መከራ አጋጠመው? (ለ) ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱ መከራ እንደሚያጋጥማቸው የተናገረው ሐሳብ የሚያበረታታ የሆነው እንዴት ነው?

3 ጳውሎስ በእምነቱ ምክንያት በተደጋጋሚ ጊዜያት ስደት ደርሶበታል። (2 ቆሮ. 11:23-27) በልስጥራ እያለ እንዲህ ዓይነት ስደት አጋጥሞት ነበር። ጳውሎስ፣ ከእናቱ ማህፀን ጀምሮ ሽባ የነበረ አንድ ሰው ከፈወሰ በኋላ ሕዝቡ እሱንና ባልደረባውን በርናባስን አማልክት ብለው አወደሷቸው። ጳውሎስና በርናባስ በስሜት የሚመራው ሕዝብ እንዳያመልካቸው መለመን አስፈልጓቸው ነበር! ብዙም ሳይቆይ ግን ተቃዋሚ የሆኑ አይሁዳውያን መጡና የበርናባስንና የጳውሎስን ስም በማጥፋት የሕዝቡን አእምሮ መበከል ጀመሩ። የሕዝቡ አመለካከት ወዲያውኑ ተቀየረ! ሕዝቡ ጳውሎስን በድንጋይ ከወገሩት በኋላ እንደሞተ በማሰብ ትተውት ሄዱ።—ሥራ 14:8-19

4 ቀጥሎም ጳውሎስና በርናባስ ደርቤን ጎበኙ፤ ከዚያም “ወደ ልስጥራ፣ ወደ ኢቆንዮንና ወደ አንጾኪያ ተመለሱ። ደቀ መዛሙርቱን በማጠናከርና በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ በማበረታታት ‘ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት በብዙ መከራ ውስጥ ማለፍ አለብን’ አሏቸው።” (ሥራ 14:21, 22) የተናገሩት ነገር ግራ የሚያጋባ ሊመስል ይችላል። ምክንያቱም “በብዙ መከራ ውስጥ ማለፍ” የሚለው ሐሳብ የሚያበረታታ ሳይሆን የሚያስጨንቅ ይመስላል። ታዲያ ጳውሎስና በርናባስ መከራ እንደሚደርስባቸው ለደቀ መዛሙርቱ በመንገር ‘ያጠናከሯቸው’ እንዴት ነው?

5 ጳውሎስ የተናገረውን ሐሳብ ልብ ብለን ከመረመርነው የዚህን ጥያቄ መልስ ማግኘት እንችላለን። ጳውሎስ “በብዙ መከራ ውስጥ ማለፍ አለብን” ብቻ አላለም። ከዚህ ይልቅ “ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት በብዙ መከራ ውስጥ ማለፍ አለብን” በማለት ተናግሯል። በመሆኑም ጳውሎስ ታማኝ መሆን የሚያስገኘውን ወሮታ በማጉላት ደቀ መዛሙርቱን አጠናክሯቸዋል። ይህ ሽልማት የሕልም እንጀራ አይደለም። ኢየሱስም ቢሆን “እስከ መጨረሻው የጸና . . . እሱ ይድናል” ብሏል።—ማቴ. 10:22

6. የሚጸኑ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ሽልማት ያገኛሉ?

6 ከጸናን ሽልማት እናገኛለን። የቅቡዓን ክርስቲያኖች ሽልማት በሰማይ የሚያገኙት የማይጠፋ ሕይወት ሲሆን ከኢየሱስ ጋር አብረው ይገዛሉ። “ሌሎች በጎች” ደግሞ ‘ጽድቅ በሚሰፍንበት’ ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። (ዮሐ. 10:16፤ 2 ጴጥ. 3:13) እስከዚያው ግን ጳውሎስ እንደገለጸው ብዙ መከራ ማሳለፍ ይኖርብናል። ሊያጋጥሙን የሚችሉ ሁለት ዓይነት ፈተናዎችን እስቲ እንመልከት።

ቀጥተኛ ጥቃት

7. ቀጥተኛ ጥቃት የሚባለው ምን ዓይነት መከራ ነው?

7 ኢየሱስ “ሰዎች ለፍርድ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ በምኩራብም ትገረፋላችሁ፤ . . . በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ያቆሟችኋል” በማለት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ማር. 13:9) ከዚህ ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው አንዳንድ ክርስቲያኖች የሚደርስባቸው መከራ አካላዊ ጥቃት ነው፤ ይህም የሚሆነው በሃይማኖት ወይም በፖለቲካ መሪዎች አነሳሽነት ሊሆን ይችላል። (ሥራ 5:27, 28) እስቲ አሁንም የጳውሎስን ምሳሌ እንመልከት። ጳውሎስ እንዲህ ያለ ስደት እንደሚያጋጥመው ማወቁ በፍርሃት እንዲርድ አድርጎት ይሆን? በፍጹም።የሐዋርያት ሥራ 20:22, 23ን አንብብ።

8, 9. ጳውሎስ ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረገ ያሳየው እንዴት ነው? በዘመናችንስ አንዳንዶች እንዲህ ዓይነት አቋም እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው?

8 ጳውሎስ የሰይጣንን ቀጥተኛ ጥቃት በድፍረት የተቋቋመ ሲሆን እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ሩጫዬን እስካጠናቀቅኩ እንዲሁም የአምላክን ጸጋ ምሥራች በሚገባ ለመመሥከር ከጌታ ኢየሱስ የተቀበልኩትን አገልግሎት እስከፈጸምኩ ድረስ ለነፍሴ ምንም አልሳሳም።” (ሥራ 20:24) በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ጳውሎስ መከራ እንደሚደርስበት በማሰብ አልተሸበረም። ከዚህ ይልቅ ምንም ይምጣ ምን ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። ምንም ዓይነት መከራ ቢደርስበትም ዋነኛ ፍላጎቱ ምሥራቹን ‘በሚገባ መመሥከር’ ነበር።

9 በዛሬው ጊዜም በርካታ ወንድሞችና እህቶች እንዲህ ያለ አቋም አላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች በገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት ወደ 20 ዓመት ገደማ ታስረዋል። በዚያች አገር ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸው ሰዎች  ሌላ ዓይነት አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት ዝግጅት ስለሌለ የእነዚህ ወንድሞች ጉዳይ ጨርሶ በፍርድ ቤት አልታየም። በእስር ቤት ቤተሰቦቻቸው እንኳ እንዲጎበኟቸው አልተፈቀደላቸውም፤ አንዳንድ እስረኞች ተደብድበዋል አልፎ ተርፎም የተለያየ ዓይነት ሥቃይ ደርሶባቸዋል።

10. በድንገት የሚከሰቱ መከራዎችን መፍራት የሌለብን ለምንድን ነው?

10 በሌላ የምድር ክፍል የሚኖሩ ወንድሞቻችን ደግሞ በድንገት የሚከሰቱ መከራዎችን መቋቋም አስፈልጓቸዋል። አንተም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ አትፍራ። የዮሴፍን ታሪክ አስታውስ። ዮሴፍ ለባርነት ቢሸጥም ይሖዋ ‘ከመከራው ሁሉ ነፃ አውጥቶታል።’ (ሥራ 7:9, 10) ለአንተም ተመሳሳይ ነገር ሊያደርግልህ ይችላል። “ይሖዋ፣ ለአምላክ ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት እንደሚያድን” የሚያውቅ መሆኑን ፈጽሞ አትዘንጋ። (2 ጴጥ. 2:9) ይሖዋ ከዚህ ክፉ ሥርዓት እንደሚያድንህና በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር ለዘላለም እንድትኖር እንደሚያደርግህ በማወቅ ምንጊዜም በእሱ ትታመናለህ? እንዲህ ለማድረግም ሆነ የሚደርስብህን ስደት በድፍረት ለመቋቋም የሚያስችል በቂ ምክንያት አለህ።—1 ጴጥ. 5:8, 9

ስውር ጥቃት

11. ሰይጣን የሚሰነዝረው ስውር ጥቃት ከቀጥተኛው ጥቃት የሚለየው እንዴት ነው?

11 ሊያጋጥመን የሚችለው ሌላው ዓይነት መከራ ደግሞ ስውር ጥቃት ነው። ለመሆኑ ይህ ዓይነቱ መከራ ተቃዋሚዎች አካላዊ ጥቃት በመሰንዘር ከሚያደርሱብን ቀጥተኛ ጥቃት የሚለየው እንዴት ነው? ቀጥተኛ ጥቃት በአንድ ጊዜ ቤትህን ድምጥማጡን እንደሚያጠፋ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ነው። ስውር ጥቃት ደግሞ ሳይታዩ ገብተው ቤትህን ውስጥ ውስጡን ቀስ በቀስ በመሰርሰር ከሚያፈርሱ ምስጦች ጋር ሊመሳሰል ይችላል። እንዲህ ዓይነት ጥቃት የተሰነዘረበት ሰው ምንም ማድረግ የማይችልበት ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ አደጋ ላይ መሆኑን ላያውቅ ይችላል።

12. (ሀ) ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው ስውር ዘዴዎች አንዱ ምንድን ነው? ውጤታማ የሆነውስ ለምንድን ነው? (ለ) የተስፋ መቁረጥ ስሜት በጳውሎስ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል?

12 ሰይጣን እንደ ስደት ያለ ቀጥተኛ ጥቃት ሊሰነዝር አሊያም ቀስ በቀስ እምነትህን በሚሸረሽር ስውር ጥቃት ሊጠቀም ይችላል፤ ዞሮ ዞሮ ዋና ዓላማው ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና ማበላሸት ነው። ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው ውጤታማ የሆኑ ስውር ዘዴዎች አንዱ ተስፋ መቁረጥ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ተስፋ የቆረጠባቸው ጊዜያት እንደነበሩ ገልጿል። (ሮም 7:21-24ን አንብብ።) ጠንካራ መንፈሳዊ አቋም ያለውና ምናልባትም የመጀመሪያው መቶ ዘመን የበላይ አካል አባል የነበረው ጳውሎስ “ጎስቋላ ሰው ነኝ” ያለው ለምንድን ነው? ጳውሎስ እንዲህ የተሰማው ፍጽምና ስለጎደለው እንደሆነ ተናግሯል። ትክክል የሆነውን ለማድረግ ልባዊ ፍላጎት ቢኖረውም ይህን እንዳያደርግ የሚታገለው ሌላ ኃይል ነበረ። አንተም አልፎ አልፎ እንዲህ ካለ ስሜት ጋር የምትታገል ከሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ እንኳ ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞት እንደነበር ማወቅህ አያጽናናህም?

13, 14. (ሀ) አንዳንድ የአምላክ ሕዝቦች ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርጓቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) እምነታችን እንዲዳከም የሚፈልገው ማን ነው? ለምንስ?

13 በርካታ ወንድሞችና እህቶች አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ሊቆርጡ፣ በጭንቀት ሊዋጡ አልፎ ተርፎም የዋጋ ቢስነት ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ዲቦራ * የተባለች ቀናተኛ አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “የሠራሁትን ስህተት ባሰብኩ ቁጥር ስለ ራሴ መጥፎ ስሜት ይሰማኛል። የፈጸምኳቸውን ስህተቶች ሁሉ ሳስታውስ ማንም ሰው ሌላው ቀርቶ ይሖዋ እንኳ ሊወደኝ እንደማይችል አስባለሁ።”

14 እንደ ዲቦራ ያሉ ቀናተኛ የይሖዋ አገልጋዮች ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። አንዳንዶች ስለ ራሳቸውም ሆነ በሕይወታቸው ውስጥ ስላጋጠሟቸው ሁኔታዎች አሉታዊ ነገር ማሰብ ይቀናቸዋል። (ምሳሌ 15:15) ሌሎች ደግሞ በስሜታቸው ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር የጤና እክል ሊኖርባቸው ይችላል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በእነዚህ ስሜቶች ተጠቅሞ እኛን ለማጥቃት የሚፈልገው ማን እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ተስፋ ቆርጠን ሁሉን ነገር እርግፍ አድርገን እንድንተው የሚፈልገው ማን ነው? እሱ ጥፋት እንደተፈረደበት ሁሉ  እኛም እንደ እሱ ምንም ተስፋ የሌለን ሆኖ እንዲሰማን የሚፈልገውስ ማን ነው? (ራእይ 20:10) ሰይጣን እንደሆነ የታወቀ ነው። ሰይጣን የሚጠቀመው በቀጥተኛ ጥቃትም ሆነ በስውር ጥቃት ዓላማው እኛን ማስጨነቅ፣ ቅንዓታችንን ማዳከም እንዲሁም ተስፋ እንድንቆርጥ ማድረግ ነው። የአምላክ ሕዝቦች በመንፈሳዊ ጦርነት ውስጥ እንዳሉ ፈጽሞ መርሳት የለብህም!

15. ምን ቁርጥ አቋም ሊኖረን ይገባል?

15 ተስፋ ቆርጠህ በትግሉ እጅ ላለመስጠት ቁርጥ አቋም ይኑርህ። ምንጊዜም በሽልማትህ ላይ ትኩረት አድርግ። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ተስፋ አንቆርጥም፤ ምንም እንኳ ውጫዊው ሰውነታችን እየተመናመነ ቢሄድም ውስጣዊው ሰውነታችን ግን ከቀን ወደ ቀን እየታደሰ እንደሚሄድ ምንም ጥርጥር የለውም። ምክንያቱም መከራው ጊዜያዊና ቀላል ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድና ዘላለማዊ የሆነ ክብር ያስገኝልናል።”—2 ቆሮ. 4:16, 17

ለመከራ ከአሁኑ ተዘጋጁ

ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች ስለ እምነታቸው በድፍረት ለመናገር ይሠለጥናሉ (አንቀጽ 16ን ተመልከት)

16. ለመከራ ከአሁኑ መዘጋጀት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

16 ከላይ እንደተመለከትነው ሰይጣን የተለያዩ “መሠሪ ዘዴዎች” ይጠቀማል። (ኤፌ. 6:11) ሁላችንም በ1 ጴጥሮስ 5:9 ላይ የሚገኘውን “በእምነት ጸንታችሁ በመቆም [ዲያብሎስን] ተቃወሙት” የሚለውን ማሳሰቢያ መከተል ይኖርብናል። ጸንተን መቆም እንድንችል ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ከአሁኑ ራሳችንን በማሠልጠን አእምሯችንን እና ልባችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፦ በጦር ሠራዊት ውስጥ የሚገኙ ወታደሮች ጦርነት እንደሚነሳ የሚጠቁም ነገር ባይኖርም እንኳ ለውጊያ የሚያዘጋጃቸውን ከባድ ሥልጠና ያደርጋሉ። ከይሖዋ መንፈሳዊ ሠራዊት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ወደፊት ምን ዓይነት ውጊያ እንደሚገጥመን አናውቅም። ታዲያ አንጻራዊ ሰላም ባለበት በአሁኑ ጊዜ ራሳችንን በደንብ ማሠልጠናችን ጥበብ አይሆንም? ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “በእምነት ውስጥ እየተመላለሳችሁ መሆናችሁን ለማወቅ ዘወትር ራሳችሁን መርምሩ፤ ማንነታችሁን ለማወቅ  ራሳችሁን ዘወትር ፈትኑ” በማለት ጽፏል።—2 ቆሮ. 13:5

17-19. (ሀ) ራሳችንን መመርመር የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ወጣቶች በትምህርት ቤት ስለ እምነታቸው በድፍረት ለመናገር መዘጋጀት የሚችሉት እንዴት ነው?

17 ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የጻፈውን ምክር ተግባራዊ የምናደርግበት አንዱ መንገድ ራሳችንን በቁም ነገር መመርመር ነው። ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ፦ ‘በጸሎት እጸናለሁ? የእኩዮች ተጽዕኖ ሲያጋጥመኝ ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢዬ አድርጌ እታዘዘዋለሁ? በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሬ እገኛለሁ? ስለማምንባቸው ነገሮች በድፍረት እናገራለሁ? የእምነት ባልንጀሮቼ ስህተቶቼን እንደሚያልፉልኝ ሁሉ እኔም እነሱ ሲሳሳቱ ለመታገሥ ጥረት አደርጋለሁ? በጉባኤዬ ውስጥ አመራር ለሚሰጡት እንዲሁም በዓለም አቀፉ የአምላክ ጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ላላቸው ወንድሞች እገዛለሁ?’

18 ከላይ ካሉት ጥያቄዎች መካከል ሁለቱ ስለ እምነታችን በድፍረት ከመናገርና የእኩዮችን ተጽዕኖ ከመቋቋም ጋር የተያያዙ እንደሆኑ ልብ በል። በርካታ ወጣት ክርስቲያኖች በትምህርት ቤት እንዲህ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ስለ እምነታቸው ለመናገር እንዳይፈሩ ወይም እንዳያፍሩ ከዚህ ይልቅ በድፍረት እንዲናገሩ ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል። በዚህ ረገድ ጠቃሚ ሐሳቦች በመጽሔቶቻችን ላይ ወጥተዋል። በሐምሌ 2009 ንቁ! ላይ የወጣውን የሚከተለውን ሐሳብ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ አንድ አብሮህ የሚማር ልጅ “በዝግመተ ለውጥ የማታምነው ለምንድን ነው?” ቢልህ እንዲህ ብለህ ልትመልስለት ትችላለህ፦ “በዝግመተ ለውጥ እንዳምን የሚያደርግ ምን ምክንያት አለ? እውቀት አላቸው የሚባሉት ሳይንቲስቶች ራሳቸው እንኳ በዚህ ጉዳይ እርስ በርሳቸው አይስማሙም!” እናንት ወላጆች፣ ልጆቻችሁ እኩዮቻቸው በትምህርት ቤት እንዲህ ያሉ ተጽዕኖዎች ሲያሳድሩባቸው ለመቋቋም ዝግጁ እንዲሆኑ የሚረዳቸው የልምምድ ፕሮግራም ይኑራችሁ።

19 ስለ እምነታችን በድፍረት መናገር ወይም ይሖዋ የሚያዝዘንን ሌሎች ነገሮች ማድረግ ቀላል የማይሆንባቸው ጊዜያት እንዳሉ የታወቀ ነው። በሥራ ስንደክም ውለን ማታ ወደ ስብሰባ ለመሄድ ራሳችንን ማስገደድ ሊኖርብን ይችላል። ጠዋት ላይ አገልግሎት ለመውጣት ከሞቀ አልጋችን መነሳት ያታግለን ይሆናል። ይሁንና ከአሁኑ ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ማዳበርህ ወደፊት ከባድ ፈተናዎች ሲያጋጥሙህ ለመወጣት ዝግጁ እንድትሆን እንደሚረዳህ መዘንጋት አይኖርብህም።

20, 21. (ሀ) በቤዛው ዝግጅት ላይ ማሰላሰል መጥፎ ስሜቶችን ለመቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) ከመከራዎች ጋር በተያያዘ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?

20 ስውር ስለሆኑ ጥቃቶችስ ምን ማለት ይቻላል? ለምሳሌ ያህል፣ የተስፋ መቁረጥ ስሜትን መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ለማድረግ ከሚረዱን በጣም ጠቃሚ ዘዴዎች አንዱ በቤዛው ዝግጅት ላይ ማሰላሰል ነው። ሐዋርያው ጳውሎስም ያደረገው ይህንኑ ነው። አንዳንድ ጊዜ፣ ጎስቋላ ሰው እንደሆነ ይሰማው ነበር። ያም ቢሆን ክርስቶስ የሞተው ፍጹም ለሆኑ ሰዎች ሳይሆን ለኃጢአተኞች እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ጳውሎስም ከእነዚህ ኃጢአተኞች አንዱ እንደሆነ ያውቃል። እንዲያውም “አሁን በሥጋ የምኖረውን ሕይወት የምኖረው በወደደኝና ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ በሰጠው በአምላክ ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው” ሲል ጽፏል። (ገላ. 2:20) በእርግጥም ጳውሎስ በቤዛው ላይ እምነት ነበረው። ቤዛው በግለሰብ ደረጃ እሱን እንደሚጠቅመው ተሰምቶት ነበር።

21 አንተም ቤዛውን ይሖዋ በግልህ እንደሰጠህ ስጦታ አድርገህ የምትመለከተው ከሆነ በእጅጉ ትጠቀማለህ። እርግጥ ይህ ሲባል፣ የሚሰማህ የተስፋ መቁረጥ ስሜት በቅጽበት ይጠፋል ማለት አይደለም። አንዳንዶቻችን አዲሱ ዓለም ውስጥ እስክንገባ ድረስ፣ ሰይጣን ከሚጠቀምበት እንዲህ ካለው ስውር ጥቃት ጋር መታገል ይኖርብን ይሆናል። ሆኖም ሽልማቱን የሚያገኙት ተስፋ ሳይቆርጡ የጸኑ እንደሆኑ አስታውስ። የአምላክ መንግሥት ሰላምን ወደሚያሰፍንበትና ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ ወደሚያደርግበት ክብራማ ጊዜ በጣም ቀርበናል። በብዙ መከራዎች ውስጥ ማለፍ ቢኖርብህም እንኳ ወደዚህ መንግሥት ለመግባት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።

^ አን.13 ስሟ ተቀይሯል።