“ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።”—ያዕ. 4:8

1. ሰዎች ምን ተፈጥሯዊ ፍላጎት አላቸው? ይህንን ፍላጎታቸውን የሚያረካላቸውስ ማነው?

የሰው ልጆች ከሌሎች ጋር የመቀራረብ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ሁለት ሰዎች ይቀራረባሉ ሊባል የሚችለው “እርስ በርስ በጣም የሚዋደዱና በደንብ የሚተዋወቁ ከሆነ” ነው። ማንኛችንም ብንሆን ከሚወዱን፣ ከሚያደንቁንና ስሜታችንን ከሚረዱልን የቤተሰባችን አባላት ወይም ጓደኞቻችን ጋር የመቀራረብ ተፈጥሯዊ ፍላጎት አለን። ሆኖም ሁላችንም ከማንም ይበልጥ የቀረበ ዝምድና ልንመሠርት የሚገባው ከታላቁ ፈጣሪያችን ከይሖዋ ጋር ነው።—መክ. 12:1

2. ይሖዋ ምን ቃል ገብቶልናል? ብዙ ሰዎች ይህን ሐሳብ ማመን የሚከብዳቸው ለምንድን ነው?

2 ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ‘ወደ እሱ እንድንቀርብ’ አበረታቶናል፤ እንዲህ ካደረግን ‘እሱም ወደ እኛ እንደሚቀርብ’ ቃል ገብቶልናል። (ያዕ. 4:8) ይህ እንዴት የሚያበረታታ ሐሳብ ነው! ይሁንና ብዙ ሰዎች ‘አምላክ ወደ እኛ መቅረብ ይፈልጋል’ የሚለው ሐሳብ ፈጽሞ የማይመስል ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች ወደ እሱ ለመቅረብ ብቁ እንዳልሆኑ ወይም አምላክ ከእነሱ በጣም የራቀ እንደሆነ ያስባሉ። ታዲያ ወደ ይሖዋ መቅረብ ይቻላል?

3. ስለ ይሖዋ የትኛውን እውነታ መገንዘብ ይኖርብናል?

3 እንደ እውነቱ ከሆነ ይሖዋ “ከእያንዳንዳችን የራቀ” አይደለም፤ ይሖዋን የሚፈልግ ሰው እሱን ማወቅ ይችላል። (የሐዋርያት ሥራ 17:26, 27 እና መዝሙር 145:18ን አንብብ።) እኛ የሰው ልጆች ፍጽምና የጎደለን ብንሆንም ይሖዋ እንደ ቅርብ ወዳጆቹ አድርጎ ሊቀበለን ዝግጁና ፈቃደኛ ነው። (ኢሳ. 41:8፤ 55:6) መዝሙራዊው ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት ስለ ይሖዋ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ጸሎትን የምትሰማ ሆይ፤ የሰው ልጆች ሁሉ ወደ አንተ ይመጣሉ። አንተ የመረጥኸው፣ ወደ ራስህ ያቀረብኸው፣ . . . ምስጉን ነው!” (መዝ. 65:2, 4) የይሁዳ ንጉሥ ስለነበረው ስለ ንጉሥ አሳ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ወደ አምላክ መቅረብ ለሚፈልግ ሰው ጥሩ ትምህርት ይዟል፤ በተጨማሪም ዘገባው ይሖዋ ወደ እሱ መቅረብ ለሚፈልግ ሰው ምን ምላሽ እንደሚሰጥ ይጠቁማል። *

በጥንት ጊዜ ከኖረ የአምላክ አገልጋይ የምናገኘው ትምህርት

4. ንጉሥ አሳ ለይሁዳ ሕዝብ ምን ምሳሌ ትቷል?

4 ንጉሥ አሳ በዘመኑ ተስፋፍቶ የነበረውን የቤተ መቅደስ ዝሙት አዳሪነትንና የጣዖት አምልኮን ከምድሪቱ ጠራርጎ በማጥፋት ለንጹሕ አምልኮ ከፍተኛ ቅንዓት አሳይቷል። (1 ነገ. 15:9-13) ይህን ማድረጉ የመናገር ነፃነት ስለሰጠው “የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን እንዲፈልጉ፣ ሕጉንና ትእዛዙንም እንዲፈጽሙ የይሁዳን ሕዝብ አዘዘ።” ይሖዋም አሳ ከነገሠ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ አሥር ዓመታት ሙሉ በሙሉ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ ይህን ንጉሥ ባርኮታል። አሳ ለዚህ ሰላም መገኘት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “አምላካችንን እግዚአብሔርን ስለ ፈለግነው ምድሪቱ አሁንም የኛው ናት፤ እኛ ፈለግነው፤ እርሱም በሁሉም አቅጣጫ ዕረፍት ሰጠን።” (2 ዜና 14:1-7) ከዚህ በኋላ የሆነውን ነገር እንመልከት።

5. አሳ በአምላክ ላይ ያለውን እምነት የሚፈትን ምን ሁኔታ አጋጠመው? ውጤቱስ ምን ሆነ?

5 እስቲ ራስህን በአሳ ቦታ አስቀምጠህ ለማሰብ ሞክር። ኢትዮጵያዊው ዝሪ 1,000,000 ሰራዊትና 300 ሠረገሎች ይዞ ይሁዳን ሊወጋ ወጣ። (2 ዜና 14:8-10) እንዲህ ያለ ታላቅ ሰራዊት ግዛትህን ለመውረር ቢመጣ ምን ታደርጋለህ? የአንተ ሰራዊት 580,000 ብቻ ነው! የጠላት ሰራዊት በእጥፍ እንደሚበልጥህ ስትረዳ አምላክ እንዲህ ያለው ወረራ እንዲፈጸም ለምን ፈቀደ ብለህ ታስባለህ? ከፊትህ የተጋረጠውን ይህን አደገኛ ሁኔታ በራስህ መንገድ ለመፍታት ትሞክራለህ? አሳ የወሰደው እርምጃ ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና እንዳለውና በእሱ እንደሚተማመን የሚያሳይ ነው። በዚህ ጊዜ አሳ ወደ ይሖዋ እንዲህ ሲል ጮኸ፦ “አምላካችን እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ በአንተ ታምነናልና፣ ይህን ታላቅ ሰራዊት በስምህ እንገጥመዋለን፤ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ አምላካችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያሸንፍህም።” ታዲያ አምላክ አሳ ላቀረበው ልባዊ ጸሎት ምን ምላሽ ሰጠ? ይሖዋ “ኢትዮጵያውያንን . . . መታቸው።” ከዚያ ጦርነት አንድም የጠላት ወታደር አልተረፈም።—2 ዜና 14:11-13

6. ከአሳ ምን ትምህርት እናገኛለን?

6 አሳ አምላክ መመሪያ እንደሚሰጠውና ጥበቃ እንደሚያደርግለት ሙሉ በሙሉ እንዲተማመን ያደረገው ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ አሳ “በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ” እንዲሁም “ልቡ ለእግዚአብሔር የተገዛ ነበር” ይላል። (1 ነገ. 15:11, 14) እኛም ለአምላክ መገዛት ማለትም አምላክን በሙሉ ልብ ማገልገል ይኖርብናል። አሁንም ሆነ ወደፊት ከይሖዋ ጋር የቀረበ ወዳጅነት እንዲኖረን የምንፈልግ ከሆነ ይህን ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። ይሖዋ ወደ እሱ እንድንቀርብ ቅድሚያውን ወስዶ ዝግጅት ስላደረገልንና ከእሱ ጋር የቀረበ ዝምድና እንድንመሠርት እንዲሁም ይህን ዝምድና ጠብቀን እንድንቆይ ስለሚረዳን በጣም አመስጋኞች ነን! አምላክ ይህን ያደረገባቸውን ሁለት መንገዶች እስቲ እንመልከት።

ይሖዋ በቤዛው አማካኝነት ወደ እኛ ቀርቧል

7. (ሀ) ይሖዋ ወደ እሱ እንድንቀርብ የትኞቹን ዝግጅቶች አድርጓል? (ለ) አምላክ ወደ እሱ እንድንቀርብ ካደረገባቸው መንገዶች መካከል ከሁሉ የላቀው የትኛው ነው?

7 ይሖዋ መኖሪያችን የሆነችውን ውብ ምድር በመፍጠር ለሰው ዘር ያለውን ፍቅር አሳይቷል።  አሁንም ቢሆን በሕይወት ለመቀጠል የሚያስፈልጉንን ነገሮች በማቅረብ ፍቅሩን እያሳየ ነው። (ሥራ 17:28፤ ራእይ 4:11) ከሁሉም በላይ ደግሞ ይሖዋ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ምንጊዜም ያሟላልናል። (ሉቃስ 12:42) በተጨማሪም አምላክ የምናቀርበውን ጸሎት እሱ ራሱ እንደሚሰማ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (1 ዮሐ. 5:14) ይሁን እንጂ አምላክ ወደ እሱ እንድንቀርብ ያደረገበትና እኛም ወደ እሱ መቅረብ የቻልንበት ከሁሉ የላቀው መንገድ ቤዛው ነው። (1 ዮሐንስ 4:9, 10, 19ን አንብብ።) ይሖዋ “አንድያ ልጁን” ወደ ምድር የላከው እኛን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት ነው።—ዮሐ. 3:16

8, 9. ኢየሱስ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ምን ሚና አለው?

8 ይሖዋ፣ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የኖሩ ሰዎችም እንኳ ከቤዛው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዝግጅት አድርጓል። ይሖዋ ዓላማው ሳይፈጸም እንደማይቀር እርግጠኛ ስለነበር ለሰው ዘር አዳኝ እንደሚያመጣ ትንቢት ከተናገረበት ጊዜ አንስቶ ቤዛውን እንደተከፈለ አድርጎ ተመልክቶታል። (ዘፍ. 3:15) ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ክርስቶስ ኢየሱስ ለከፈለው ቤዛ’ አምላክን አመስግኗል። ጳውሎስ አክሎ አምላክ ‘በቀደሙት ዘመናት የተፈጸሙትን ኃጢአቶች ይቅር ማለቱን’ ተናግሯል። (ሮም 3:21-26) በእርግጥም ኢየሱስ፣ እኛ ወደ አምላክ መቅረብ እንድንችል ከፍተኛ ሚና አለው!

9 ትሑት የሆኑ ሰዎች ስለ ይሖዋ ማወቅም ሆነ ከእሱ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመሥረት የሚችሉት በኢየሱስ አማካኝነት ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሐቅ ጎላ አድርጎ የሚገልጸው እንዴት ነው? ጳውሎስ “አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ለእኛ እንዲሞት በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል” በማለት ጽፏል። (ሮም 5:6-8) የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የተዘጋጀልን ብቁ ስለሆንን ሳይሆን ይሖዋ ስለወደደን ነው። ኢየሱስ “የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም” ብሏል። በሌላ ወቅትም “በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 6:44፤ 14:6) ይሖዋ ሰዎችን በኢየሱስ በኩል ወደ ራሱ የሚስበው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ሲሆን እነዚህ ሰዎች ከፍቅሩ ሳይወጡ በመኖር የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። (ይሁዳ 20, 21ን አንብብ።) እስቲ አሁን ደግሞ ይሖዋ ወደ እሱ እንድንቀርብ ያደረገበትን ሌላኛውን መንገድ እንመልከት።

ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ወደ እኛ ቀርቧል

10. መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አምላክ እንድንቀርብ የሚረዳ ምን ትምህርት ይዟል?

10 በዚህ ርዕስ ውስጥ እንኳ እስከዚህ አንቀጽ ድረስ ከ14 የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፎች የተወሰዱ የተለያዩ ጥቅሶች ተጠቅሰዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ባይኖር ኖሮ ወደ ፈጣሪያችን መቅረብ እንደምንችል እንዴት እናውቅ ነበር? ያለ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቤዛውም ሆነ በኢየሱስ በኩል ወደ ይሖዋ መቅረብ እንድንችል ስለተደረገልን ዝግጅት እንዴት ማወቅ እንችል ነበር? ይሖዋ ግሩም ስለሆኑት ባሕርያቱና አስደናቂ ስለሆኑት ዓላማዎቹ የሚገልጸውን መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈሱ አማካኝነት አስጽፏል። ለምሳሌ ያህል በዘፀአት 34:6, 7 ላይ ይሖዋ “ሩኅሩኅ ቸር . . . ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣ ፍቅርን ለሺዎች የሚጠብቅ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል” አምላክ መሆኑን ለሙሴ ነግሮታል። እንዲህ ወዳለ አምላክ መቅረብ የማይፈልግ ማን አለ? መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ስለ ይሖዋ እያወቅን በሄድን መጠን ይበልጥ እውን እንደሚሆንልንና ወደ እሱ የበለጠ እንደቀረብን እንደሚሰማን ይሖዋ አምላክ ያውቃል።

11. የአምላክን ባሕርያትም ሆነ ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድ ለማወቅ ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

11 ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለው መጽሐፍ መቅድም ከአምላክ ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ከማንኛውም ሰው ጋር ወዳጅነት ልንመሠርት የምንችለው በቅድሚያ ግለሰቡን በሚገባ ስናውቀው ብሎም ልዩ የሚያደርጉትን ባሕርያት  ስናደንቅና ከፍ አድርገን መመልከት ስንጀምር ነው። በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን የአምላክ ባሕርያትና የተለያዩ ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድ ማጥናት በጣም አስፈላጊ ነው።” እንግዲያው ይሖዋ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን የሰው ልጆች በሚረዱት መንገድ በማስጻፉ በጣም አመስጋኞች ነን!

12. ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጻፍ ሰዎችን የተጠቀመው ለምንድን ነው?

12 ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጻፍ መላእክትን መጠቀም ይችል ነበር። መላእክትም ቢሆኑ ስለ እኛም ሆነ ስለምናደርጋቸው ነገሮች የማወቅ ከፍተኛ ጉጉት አላቸው። (1 ጴጥ. 1:12) መላእክት፣ አምላክ ለሰው ልጆች ለማስተላለፍ የፈለገውን መልእክት መጻፍ እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ነገሮችን ከሰዎች አመለካከት አንጻር ማስቀመጥ ይችሉ ነበር? ፍላጎታችንን፣ ድክመታችንንና ምኞታችንን መረዳት ይችሉ ነበር? በፍጹም! ይሖዋ በዚህ ረገድ የአቅም ገደብ እንዳለባቸው ያውቃል። ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን በሰዎች በማስጻፉ መጽሐፉ ስሜታችንን የሚነካ ሊሆን ችሏል። መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉትንም ሆነ በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱትን ሰዎች አስተሳሰብና ስሜት መረዳት እንችላለን። ሐዘናቸው፣ ጥርጣሬያቸው፣ ፍርሃታቸውና ጉድለታቸው የሚገባን ከመሆኑም በላይ ሲደሰቱ ወይም ሲሳካላቸው እኛም እንደሰታለን። እንደ ነቢዩ ኤልያስ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉ ሰዎች በሙሉ “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት” ያላቸው ሰዎች ናቸው።—ያዕ. 5:17

ይሖዋ ከዮናስና ከጴጥሮስ ጋር በተያያዘ ያደረገው ነገር ይበልጥ ወደ እሱ እንድትቀርብ የሚገፋፋህ እንዴት ነው? (አንቀጽ 13, 15ን ተመልከት)

13. የዮናስ ጸሎት ልብ የሚነካ እንዲሆን ያስቻለው ምንድን ነው?

13 ለምሳሌ፣ ነቢዩ ዮናስ አምላክ የሰጠውን ሥራ ትቶ ወደ ሌላ አካባቢ በሸሸ ጊዜ የተሰማውን ስሜት አንድ መልአክ ሙሉ በሙሉ መረዳት ይችል ነበር? ይሖዋ፣ ዮናስ በጥልቅ ባሕር ውስጥ ሆኖ ወደ አምላክ ያቀረበውን ልባዊ ጸሎት ጨምሮ የራሱን ታሪክ እንዲጽፍ ማድረጉ በእርግጥም ተገቢ ነው። ዮናስ “ነፍሴ በዛለች ጊዜ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተን ዐሰብሁ” በማለት ተናግሯል።—ዮናስ 1:3, 10፤ 2:1-9

14. ኢሳይያስ ስለ ራሱ የጻፈውን መረዳት የቻልከው ለምንድን ነው?

 14 ይሖዋ፣ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ ራሱ እንዲጽፍ ያደረገውን ሐሳብ ደግሞ እንመልከት። ነቢዩ የአምላክን ክብር በራእይ ከተመለከተ በኋላ ኃጢአተኛ መሆኑን በማሰብ እንዲህ ብሎ ለመጻፍ ተገፋፍቷል፦ “ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው ነኝ፤ የምኖረውም ከንፈሮቹ በረከሱበት ሕዝብ መካከል ነው፤ ዐይኖቼም ንጉሡን፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን አይተዋልና ጠፍቻለሁ፣ ወዮልኝ!” (ኢሳ. 6:5) እንዲህ ብሎ መናገር የሚችል መልአክ ሊኖር ይችላል? ኢሳይያስ ግን እንዲህ ብሎ መናገር ችሏል፤ እኛም ስሜቱን መረዳት እንችላለን።

15, 16. (ሀ) የሌሎች ሰዎችን ስሜት መረዳት የቻልነው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ። (ለ) ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ምን ሊረዳን ይችላል?

15 መላእክት እንደ ያዕቆብ “ብቁ አይደለሁም” ሊሉ ወይም እንደ ጴጥሮስ “ኃጢአተኛ” እንደሆኑ ሊሰማቸው ይችላል? (ዘፍ. 32:10፤ ሉቃስ 5:8) ጻድቅ የሆኑ መላእክት እንደ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ፍርሃት ሊሰማቸው ወይም እንደ ጳውሎስና እንደ ሌሎች የይሖዋ አገልጋዮች ለተቃዋሚዎቻቸው ምሥራቹን ለመስበክ ‘እንደ ምንም ብለው ድፍረት ማግኘት’ ሊያስፈልጋቸው ይችላል? (ዮሐ. 6:19፤ 1 ተሰ. 2:2) በጭራሽ! ምክንያቱም መላእክት በሁሉም ረገድ ፍጹም ከመሆናቸውም በላይ ከሰዎች እጅግ የላቁ ናቸው። ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች የሚሰማቸውን ነገር ሲገልጹ ስሜታቸው በቀላሉ ይገባናል፤ ምክንያቱም እኛም እንደ እነሱ ሰዎች ነን። የአምላክን ቃል ስናነብ ‘ደስ ከተሰኙ ሰዎች ጋር ደስ ይለናል፤ ከሚያለቅሱ ሰዎች ጋር ደግሞ እናለቅሳለን።’—ሮም 12:15

16 ይሖዋ ጥንት ከነበሩት ታማኝ አገልጋዮቹ ጋር ስለነበረው ግንኙነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማንበባችንና በዚያ ላይ ማሰላሰላችን ጠቃሚ ነው፤ ምክንያቱም ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎችን በትዕግሥትና በፍቅር ወደ እሱ ስለሚስበው አምላክ በርካታ አስደናቂ ነገሮችን ለመማር ያስችለናል። እንዲህ ማድረጋችን ይሖዋን ይበልጥ እንድናውቀውና ከልባችን እንድንወደው ይረዳናል። ይህ ደግሞ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ያደርገናል።—መዝሙር 25:14ን አንብብ።

ከአምላክ ጋር የማይበጠስ ዝምድና መሥርቱ

17. (ሀ) አዛርያስ ለንጉሥ አሳ ምን ግሩም ምክር ሰጥቶታል? (ለ) ንጉሥ አሳ የአዛርያስን ምክር ችላ ያለው እንዴት ነው? ይህስ ምን አስከተለ?

17 ንጉሥ አሳ በኢትዮጵያ ሰራዊት ላይ ታላቅ ድል ከተቀዳጀ በኋላ የአምላክ ነቢይ የነበረው አዛርያስ ለንጉሥ አሳና ለሕዝቡ ግሩም ምክር ሰጥቷቸዋል። አዛርያስ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር ስትሆኑ፣ እርሱም ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ብትፈልጉት ይገኝላችኋል፤ ብትተውት ግን፣ ይተዋችኋል።” (2 ዜና 15:1, 2) ይሁንና ንጉሥ አሳ ከጊዜ በኋላ ይህን ጥሩ ምክር ችላ ብሏል። በስተ ሰሜን ያለው ተቀናቃኙ የእስራኤል መንግሥት ሊወጋው ሲመጣ እርዳታ ለማግኘት ወደ ሶርያ ዞር ብሏል። ይሖዋ በድጋሚ እንዲረዳው ከመጠየቅ ይልቅ ይሖዋን የማያመልኩ ሰዎችን እርዳታ ጠየቀ። በእርግጥም ይሖዋ ለአሳ “የሞኝነት ሥራ ስለ ሠራህ ከእንግዲህ ወዲያ ጦርነት አይለይህም” ማለቱ ተገቢ ነው። ከዚያ በኋላ ያለው የንጉሥ አሳ የግዛት ዘመን በጦርነት የተሞላ ነበር። (2 ዜና 16:1-9) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?

18, 19. (ሀ) በተወሰነ መጠን ከአምላክ እንደራቅን ከተሰማን ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ የምንችለው እንዴት ነው?

18 እኛም ከይሖዋ ፈጽሞ መራቅ የለብንም። በተወሰነ መጠን ከይሖዋ እንደራቅን ከተሰማን በሆሴዕ 12:6 ላይ ከተገለጸው ምክር ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል፤ ሆሴዕ እንዲህ ብሏል፦ “ወደ አምላክህ ተመለስ፤ ፍቅርንና ፍትሕን ጠብቅ፤ ዘወትርም በአምላክህ ታመን።” እንግዲያው ስለ ቤዛው በአድናቆት በማሰላሰልና የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንቅረብ።—ዘዳግም 13:4ን አንብብ።

19 መዝሙራዊው “ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል” በማለት ጽፏል። (መዝ. 73:28) እንግዲያው ሁላችንም ስለ ይሖዋ አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅና እሱን እንድንወደው የሚገፋፉንን በርካታ ምክንያቶች ለመገንዘብ ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥል። እንዲህ ስናደርግ ይሖዋ አሁንም ሆነ ለዘላለም ይበልጥ ወደ እኛ ይቀርባል!

^ አን.3 ንጉሥ አሳን በሚመለከት በነሐሴ 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን ‘የድካማችሁን ዋጋ ታገኛላችሁ’ የሚለውን ርዕስ ተመልከት።