በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ሐምሌ 2014

የይሖዋ ሕዝብ “ከክፋት ይራቅ”

የይሖዋ ሕዝብ “ከክፋት ይራቅ”

“የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ከክፋት ይራቅ።”—2 ጢሞ. 2:19

1. በአምልኳችን ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ምንድን ነው?

ይሖዋ የሚለው ስም በጥንታዊ ሕንፃዎች፣ በቤተ መዘክሮች ወይም በሌሎች ቦታዎች ላይ ተጽፎ አይተህ ታውቃለህ? ከሆነ ነገሩ ትኩረትህን ስቦትና አስደንቆህ እንደሚሆን ጥያቄ የለውም። ምክንያቱም የአምላክ የግል ስም በአምልኳችን ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው፤ የምንጠራው እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን ነው! በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ የእኛን ያህል በመለኮታዊው ስም የሚጠቀም ሌላ ሕዝብ የለም። ይሁንና በአምላክ ስም የመጠራት መብታችን ትልቅ ኃላፊነት እንደሚያስከትልም እንገነዘባለን።

2. በአምላክ ስም የመጠራት መብታችን ምን ኃላፊነት ያስከትልብናል?

2 በመለኮታዊው ስም መጠቀማችን ብቻውን የአምላክን ሞገስ አያስገኝልንም። ከይሖዋ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን መኖር ይጠበቅብናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የይሖዋ ሕዝቦች ‘ከክፉ መሸሽ’ እንዳለባቸው የሚናገረው ለዚህ ነው። (መዝ. 34:14) ሐዋርያው ጳውሎስ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ከክፋት ይራቅ” ብሎ በጻፈ ጊዜ ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በግልጽ አስፍሮታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:19ን አንብብ።) የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን የምንታወቀው የይሖዋን ስም በመጥራታችን ነው። ይሁን እንጂ ከክፋት መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?

ከክፋት “ራቁ”

3, 4. የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንን ግራ የሚያጋባቸው የትኛው ጥቅስ ነው? ለምንስ?

3 ጳውሎስ በ2 ጢሞቴዎስ 2:19 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ የጻፈው የትኛውን  ቅዱስ ጽሑፋዊ ታሪክ በአእምሮው ይዞ እንደሆነ እስቲ እንመልከት። በጥቅሱ ላይ ስለ “ጠንካራው የአምላክ መሠረት” የተገለጸ ሲሆን በዚህ መሠረት ላይ የተቀረጹ ሁለት ሐሳቦች አሉ። “ይሖዋ የእሱ የሆኑትን ያውቃል” የሚለው የመጀመሪያው ሐሳብ ከዘኍልቍ 16:5 የተወሰደ ይመስላል። (የመጀመሪያውን የጥናት ርዕስ ተመልከት።) “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ከክፋት ይራቅ” የሚለው ሁለተኛው ሐሳብ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንን ለረጅም ጊዜ ግራ አጋብቷቸዋል። ለምን?

4 ጳውሎስ የተጠቀመባቸው ቃላት ይህን ሐሳብ የጠቀሰው ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ይሁን እንጂ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ጳውሎስ ከጻፈው ሐሳብ ጋር የሚመሳሰል ጥቅስ አይገኝም። ታዲያ ሐዋርያው “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ከክፋት ይራቅ” የሚለውን ሐሳብ የጻፈው በአእምሮው ምን ይዞ ነው? ይህን ሐሳብ ከመናገሩ በፊት ያለው ሐረግ ከዘኍልቍ ምዕራፍ 16 የተወሰደ ሲሆን ታሪኩ ቆሬ ስላስነሳው ዓመፅ ይገልጻል። ታዲያ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ከክፋት ይራቅ” የሚለው ሐሳብስ በዚያ ወቅት ዓመፅ ሲነሳ ከተከናወኑት ነገሮች ጋር የሚያያዝ ይሆን?

5-7. ጳውሎስ በ2 ጢሞቴዎስ 2:19 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ሲጽፍ እየጠቀሰ የነበረው በሙሴ ዘመን የተፈጸመውን የትኛውን ሁኔታ ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

5 የኤልያብ ልጆች የሆኑት ዳታንና አቤሮን ከቆሬ ጋር በመተባበር በሙሴና በአሮን ላይ ዓመፅ እንዳስነሱ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘኍ. 16:1-5) እነዚህ ሰዎች ለሙሴ ያላቸውን ንቀት በግልጽ ያሳዩ ሲሆን ከአምላክ ያገኘውን ሥልጣን ለመቀበልም ፈቃደኞች አልነበሩም። ዓመፀኞቹ የሚኖሩት በይሖዋ ሕዝቦች መካከል በመሆኑ የታማኝ እስራኤላውያንን መንፈሳዊ ጤንነት አደጋ ላይ ጥለው ነበር። ይሁንና ይሖዋ፣ ታማኝ አምላኪዎቹን ከዓመፀኞቹ የሚለይበት ቀን ሲደርስ ግልጽ የሆነ መመሪያ ሰጠ።

6 ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ ‘ማኀበሩን “ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳኖች ራቁ” በላቸው።’ ሙሴ ተነሥቶ ወደ ዳታንና አቤሮን ሄደ፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ተከተሉት። እርሱም፣ ‘ከእነዚህ ክፉ ሰዎች ድንኳን ራቁ! የእነርሱ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትንኩ፤ ያለበለዚያ በእነርሱ ኀጢአት ሁሉ እናንተም ትጠፋላችሁ’ ሲል ማኀበሩን አስጠነቀቀ። ስለዚህ እነርሱ ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳን ራቁ።” (ዘኍ. 16:23-27) ከዚያም ይሖዋ ዓመፀኞቹን በሙሉ አጠፋቸው። በአንጻሩ ግን ከእነዚህ ሰዎች ራሳቸውን በመለየት ከክፋት እንደሚርቁ ያሳዩት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በሕይወት ተረፉ።

7 ይሖዋ የሰዎችን ልብ ያነብባል! የእሱ የሆኑት የሚያሳዩትን ታማኝነትም ይመለከታል። ያም ቢሆን ታማኝ አገልጋዮቹ ራሳቸውን ከክፉዎች በመለየት ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ነበረባቸው። ከዚህ አንጻር ጳውሎስ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ከክፋት ይራቅ” ብሎ ሲጽፍ በዘኍልቍ 16:5, 23-27 ላይ የሚገኘውን ዘገባ መጥቀሱ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለው መደምደሚያ ጳውሎስ “ይሖዋ የእሱ የሆኑትን ያውቃል” በማለት ከተናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማል።—2 ጢሞ. 2:19

“ከማይረባና ትርጉም የለሽ ከሆነ ክርክር ራቅ”

8. በይሖዋ ስም መጠቀም ወይም የክርስቲያን ጉባኤ አባል መሆን ብቻውን በቂ ያልሆነው ለምንድን ነው?

8 ጳውሎስ በሙሴ ዘመን የተፈጸሙትን እነዚህን ነገሮች የጠቀሰው፣ ጢሞቴዎስ ከይሖዋ ጋር ያለውን ውድ ዝምድና ለመጠበቅ ቁርጥ ያለ እርምጃ መውሰዱ አስፈላጊ እንደሆነ ለማሳሰብ ነበር። በሙሴ ዘመን የይሖዋን ስም ከመጥራት ያለፈ ነገር ማድረግ ያስፈልግ እንደነበረ ሁሉ በጳውሎስ ዘመንም የክርስቲያን ጉባኤ አባል መሆን ብቻውን በቂ አልነበረም። ታማኝ የይሖዋ አምላኪዎች ቆራጥ አቋም በመውሰድ ከክፋት መራቅ ነበረባቸው። ታዲያ ይህ ለጢሞቴዎስ ምን መልእክት ይዞ ነበር? በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦችስ ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ከጻፈው ምክር ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

9. ‘የማይረባና ትርጉም የለሽ የሆነ ክርክር’ በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው እንዴት ነው?

9 የአምላክ ቃል፣ ክርስቲያኖች ሊርቋቸው  የሚገቡ አንዳንድ ክፉ ነገሮችን ለይቶ ይጠቅሳል። ለምሳሌ ያህል፣ በ2 ጢሞቴዎስ 2:19 ዙሪያ ባለው ሐሳብ ላይ ጳውሎስ ‘ስለ ቃላት መነታረክ’ ተገቢ እንዳልሆነ እንዲሁም ‘ከከንቱ ንግግሮች መራቅ’ እንደሚገባው ለጢሞቴዎስ ነግሮታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:14, 16ን አንብብ።) በዚያ ወቅት አንዳንድ የጉባኤው አባላት የክህደት ትምህርቶችን እያስፋፉ ነበር። ሌሎች ደግሞ አከራካሪ ሐሳቦችን ያመጡ የነበረ ይመስላል። እነዚህ አከራካሪ ሐሳቦች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በቀጥታ የማይጋጩ ቢሆኑም እንኳ ክፍፍል ይፈጥራሉ። ይህ ደግሞ በቃላት ላይ መነታረክንና መጨቃጨቅን ስለሚያስከትል በጉባኤው ውስጥ ጤናማ መንፈሳዊ ሁኔታ እንዳይኖር ያደርጋል። ጳውሎስ “ከማይረባና ትርጉም የለሽ ከሆነ ክርክር [የመራቅን]” አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የገለጸው ለዚህ ነው።—2 ጢሞ. 2:23 አ.መ.ት

10. ከሃዲዎች ሲያጋጥሙን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

10 በዛሬው ጊዜ ባለው የይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤ ውስጥ በአብዛኛው ክህደት አያጋጥምም። ያም ቢሆን ከየትም ይምጣ ከየት ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ትምህርት ካጋጠመን ቆራጥ በመሆን እንዲህ ካለው ትምህርት ወዲያውኑ መራቅ ይኖርብናል። ከከሃዲዎች ጋር ፊት ለፊት በመነጋገርም ሆነ ድረ ገጻቸው ላይ አስተያየት በማስፈር አሊያም በሌላ መንገድ ክርክር መግጠም የጥበብ አካሄድ አይደለም። እንዲህ ያለ ውይይት የምናደርገው ግለሰቡን ለመርዳት አስበን ቢሆንም እንኳ ይህን ማድረግ እስከ አሁን ከተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያ ጋር የሚጋጭ ነው። በመሆኑም የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ከከሃዲዎች ሙሉ በሙሉ እንርቃለን።

ከከሃዲዎች ጋር ከመከራከር ተቆጠቡ (አንቀጽ 10ን ተመልከት)

11. ‘የማይረባና ትርጉም የለሽ የሆነ ክርክር’ እንዲነሳ ምክንያት ሊሆን የሚችለው ምንድን ነው? ክርስቲያን ሽማግሌዎች ጥሩ ምሳሌ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?

11 ከክህደት በተጨማሪ የጉባኤውን ሰላም ሊያደፈርሱ የሚችሉ ሌሎች ነገሮችም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ከመዝናኛ ምርጫ ጋር በተያያዘ የአመለካከት ልዩነት መኖሩ ‘የማይረባና ትርጉም የለሽ የሆነ ክርክር’ ሊያስከትል ይችላል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ክርስቲያኖች የይሖዋን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የሚጥሱ መዝናኛዎችን የሚያበረታቱ ከሆነ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ጭቅጭቅ ላለመፍጠር በማሰብ እንዲህ ያለውን ድርጊት በቸልታ ማለፍ የለባቸውም። (መዝ. 11:5፤ ኤፌ. 5:3-5) በሌላ በኩል ደግሞ ሽማግሌዎች የራሳቸውን አመለካከት እንዳያራምዱ መጠንቀቅ አለባቸው። ለክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች የተሰጠውን የሚከተለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማሳሰቢያ በታማኝነት መከተል ይኖርባቸዋል፦ “በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክ መንጋ ጠብቁ፤ . . . የአምላክ ንብረት በሆኑት ላይ ሥልጣናችሁን በማሳየት ሳይሆን ለመንጋው ምሳሌ በመሆን ጠብቁ።”—1 ጴጥ. 5:2, 3፤ 2 ቆሮንቶስ 1:24ን አንብብ።

12, 13. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች በመዝናኛ ምርጫ ረገድ ያላቸው አቋም ምንድን ነው? ለዚህ መሠረት የሚሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች የትኞቹ ናቸው? (ለ) በአንቀጽ 12 ላይ የተገለጹት መሠረታዊ ሥርዓቶች ከተለያዩ የግል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚሠሩት እንዴት ነው?

12 የይሖዋ ድርጅት ፊልሞችን፣ የቪዲዮ ጨዋታዎችን፣ መጻሕፍትን ወይም ሙዚቃዎችን አንድ በአንድ በመመርመር ልንርቃቸው የሚገቡ መዝናኛዎችን የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያ አያወጣም። ለምን? መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ ሰው ‘ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችል የማስተዋል ችሎታውን’ እንዲያሠለጥን ያበረታታል። (ዕብ. 5:14) ቅዱሳን መጻሕፍት አንድ ክርስቲያን መዝናኛ ሲመርጥ ከግምት ሊያስገባቸው የሚገቡ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዘዋል። በሁሉም የሕይወታችን ክፍሎች ግባችን ‘በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ምን እንደሆነ ምንጊዜም መርምሮ ማረጋገጥ’ ሊሆን ይገባል። (ኤፌ. 5:10) መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብ ራሶች የተወሰነ ሥልጣን እንዳላቸው ስለሚያስተምር አንድ የቤተሰብ ራስ የቤተሰቡ አባላት ሊዝናኑባቸው የማይገቡ ነገሮችን መምረጥ ይችላል። *1 ቆሮ. 11:3፤ ኤፌ. 6:1-4

13 እስከ አሁን ያየናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚሠሩት በመዝናኛ ምርጫ ረገድ ብቻ አይደለም። እንደ አለባበስና አጋጌጥ፣ ጤንነትና አመጋገብ እንዲሁም እነዚህን ከመሳሰሉ ሌሎች የግል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ያለን አመለካከትም  ክርክር ሊያስነሳ ይችላል። እንግዲያው ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች እስካልተጣሱ ድረስ የይሖዋ ሕዝቦች እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ ከመከራከር መራቃቸው ጥበብ ነው፤ ምክንያቱም “የጌታ ባሪያ . . . ሊጣላ አይገባውም፤ ከዚህ ይልቅ ለሰው ሁሉ ገር [ዘዴኛ፣ NW የ2013 እትም የግርጌ ማስታወሻ]፣ . . . ሊሆን ይገባዋል።”—2 ጢሞ. 2:24

ከመጥፎ ጓደኝነት ራቁ!

14. ጳውሎስ ከመጥፎ ጓደኝነት የመራቅን አስፈላጊነት ለማጉላት የትኛውን ምሳሌ ተጠቅሟል?

14 ‘የይሖዋን ስም የሚጠሩ ከክፋት መራቅ’ የሚችሉበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው? ክፉ ነገር ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር የቅርብ ወዳጅነት ከመመሥረት መቆጠብ ነው። ጳውሎስ ስለ “ጠንካራው የአምላክ መሠረት” ከተናገረ በኋላ የጠቀሰው ሌላ ምሳሌም ትኩረት የሚስብ ነው። ስለ “አንድ ትልቅ ቤት” የገለጸ ሲሆን በቤቱ ውስጥ ስላለው ነገር ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ ሳይሆን የእንጨትና የሸክላ ዕቃም ይኖራል፤ አንዳንዱ ክብር ላለው ዓላማ የሚያገለግል ሲሆን ሌላው ግን ክብር ለሌለው ዓላማ ያገለግላል።” (2 ጢሞ. 2:20, 21) ጳውሎስ አክሎም “ክብር ለሌለው ዓላማ” ከሚያገለግሉ ዕቃዎች ‘እንዲርቁ’ ክርስቲያኖችን መክሯቸዋል።

15, 16. ጳውሎስ ስለ “አንድ ትልቅ ቤት” ከተናገረው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

15 የዚህ ምሳሌ ትርጉም ምንድን ነው? ጳውሎስ ዘይቤያዊ አነጋገር በመጠቀም የክርስቲያን ጉባኤን ከአንድ “ትልቅ ቤት” እንዲሁም እያንዳንዱን የጉባኤ አባል በቤቱ ውስጥ ካለው “ዕቃ” ጋር አነጻጽሯል። በቤት ውስጥ ያሉ አንዳንድ ዕቃዎች ንጽሕናቸው ሊጓደል ወይም መርዛማ በሆኑ ነገሮች ሊበከሉ ይችላሉ። የቤቱ ባለቤት እንዲህ ያሉ ዕቃዎችን ንጹሕ ከሆኑት ዕቃዎች ለምሳሌ ምግብ ለማብሰል ከሚጠቀምባቸው ዕቃዎች ይለያቸዋል።

16 በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች በአኗኗራቸው ንጹሕ ለመሆን የሚፈልጉ ከሆነ የአምላክን መመሪያዎች መጣስን ልማድ ካደረጉ በጉባኤ ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች ጋር የቅርብ ጓደኝነት ላለመመሥረት ጥረት ማድረግ አለባቸው። (1 ቆሮንቶስ 15:33ን አንብብ።) በጉባኤ ውስጥ እንዲህ ያለ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ከሆነ ከጉባኤ ውጭ ካሉት ሰዎች ጋር የቀረበ ግንኙነት ላለመመሥረት በመጠንቀቅ ከእነሱ ‘መራቃችን’ የበለጠ  አስፈላጊ እንደሆነ ጥያቄ የለውም! ምክንያቱም ከእነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ ‘ገንዘብ የሚወዱ፣ ለወላጆች የማይታዘዙ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ አምላክን ከመውደድ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ’ ናቸው።—2 ጢሞ. 3:1-5

ፈጣንና ቆራጥ አቋም ስንወስድ ይሖዋ ይባርከናል

17. ታማኝ እስራኤላውያን ከክፋት እንዲርቁ የተሰጣቸውን መመሪያ ሙሉ በሙሉ የታዘዙት እንዴት ነው?

17 መጽሐፍ ቅዱስ፣ እስራኤላውያን “ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳኖች ራቁ” ሲባሉ ምን ዓይነት ቆራጥ እርምጃ እንደወሰዱ በግልጽ ይናገራል። ዘገባው ሕዝቡ “ወዲያውኑ ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳኖች . . . ራቁ” ይላል። (ዘኍ. 16:24, 27 NW) ሕዝቡ ምንም ሳያመነታ ፈጣን እርምጃ ወስዷል። እንዲያውም ጥቅሱ መመሪያውን ሙሉ በሙሉ እንደታዘዙ ሲገልጽ “ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳኖች፣ ከዙሪያቸውም ሁሉ ራቁ” ይላል። ታማኝ እስራኤላውያን ቸልተኞች በመሆን ራሳቸውን ለአደጋ አላጋለጡም። እንዲሁም የታዘዙት በግማሽ ልብ አይደለም። ከይሖዋ ጎን በመቆምና ከክፋት በመራቅ ረገድ ቁርጥ ያለ አቋም ወስደዋል። ከዚህ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

18. ጳውሎስ “ከወጣትነት ዕድሜ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ምኞቶች ሽሽ” በማለት ለጢሞቴዎስ የሰጠው ምክር ምን ትርጉም አለው?

18 ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ለመጠበቅ ፈጣንና ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። ጳውሎስ፣ ለጢሞቴዎስ “ከወጣትነት ዕድሜ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ምኞቶች ሽሽ” የሚል ምክር የሰጠው ይህን ለመግለጽ ነው። (2 ጢሞ. 2:22) በወቅቱ ጢሞቴዎስ አዋቂ ምናልባትም በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ሰው ነበር። ይሁንና “ከወጣትነት ዕድሜ ጋር ተያይዘው [የሚመጡ]” ሞኝነት የሚንጸባረቅባቸው ምኞቶች ዕድሜ ስለጨመረ ብቻ የሚጠፉ ነገሮች አይደሉም። ጢሞቴዎስ እንዲህ ያሉ ምኞቶች ሲመጡበት ከእነሱ ‘መሸሽ’ ነበረበት። በሌላ አባባል ጢሞቴዎስ ‘ከክፋት መራቅ’ ነበረበት። “ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው” የሚለው የኢየሱስ ምክርም ተመሳሳይ መልእክት ያስተላልፋል። (ማቴ. 18:9) በዛሬው ጊዜ ይህን ምክር ተግባራዊ የሚያደርጉ ክርስቲያኖች መንፈሳዊነታቸውን ለአደጋ የሚያጋልጥ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ያለምንም ማመንታት ፈጣንና ቆራጥ እርምጃ ይወስዳሉ።

19. በዛሬው ጊዜ አንዳንድ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ከመንፈሳዊ አደጋ ለመጠበቅ ቆራጥ እርምጃ የወሰዱት እንዴት ነው?

19 የይሖዋ ምሥክር ከመሆናቸው በፊት አልኮል ከመጠን በላይ የመጠጣት ችግር የነበረባቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች መጠጥ ከነጭራሹ ላለመቅመስ ወስነዋል። ሌሎች ደግሞ፣ አንዳንድ መዝናኛዎች በራሳቸው ስህተት ባይሆኑም እንኳ ድክመቶቻቸው እንዲያገረሹባቸው ሊያደርጉ ስለሚችሉ ከእነዚህ መዝናኛዎች ርቀዋል። (መዝ. 101:3) ለምሳሌ አንድ ወንድም የይሖዋ ምሥክር ከመሆኑ በፊት ሥነ ምግባር የጎደለው ሁኔታ በሚንጸባረቅባቸው የዳንስ ዝግጅቶች ላይ አዘውትሮ ይገኝ ነበር። እውነትን ከሰማ በኋላ ግን የይሖዋ ምሥክሮች በሚያዘጋጇቸው ግብዣዎች ላይ እንኳ መደነስ አቆመ፤ እንዲህ ያለ ውሳኔ ያደረገው፣ ውዝዋዜው ከቀድሞ ሕይወቱ ጋር የተያያዙ ተገቢ ያልሆኑ ምኞቶችን ወይም ሐሳቦችን እንዳይቀሰቅስበት ስለሚፈራ ነው። እርግጥ ነው፣ ክርስቲያኖች ከአልኮል መጠጥ፣ ከዳንስ ወይም እንደ እነዚህ ከመሳሰሉት በራሳቸው መጥፎ ያልሆኑ ነገሮች ሙሉ በሙሉ እንዲርቁ አይጠበቅባቸውም። ይሁን እንጂ ማንኛችንም ብንሆን መንፈሳዊነታችንን አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ነገሮች ለመራቅ ቆራጥ በመሆን አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ እንድንወስድ ይጠበቅብናል።

20. ‘ከክፋት መራቅ’ ቀላል ባይሆንም እንኳ ምን ማወቃችን ያጽናናናል?

20 በአምላክ ስም የመጠራት መብታችን ትልቅ ኃላፊነት ያስከትላል። ‘ከክፋት መራቅ’ እንዲሁም ‘ከክፉ መሸሽ’ ይኖርብናል። (መዝ. 34:14) እውነት ነው፣ እንዲህ ማድረግ ቀላል የሚሆነው ሁልጊዜ አይደለም። ይሁን እንጂ ይሖዋ “የእሱ የሆኑትን” እና የጽድቅ ጎዳናውን የሚከተሉትን ምንጊዜም እንደሚወድዳቸው ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው።—2 ጢሞ. 2:19፤ 2 ዜና መዋዕል 16:9ሀን አንብብ።

^ አን.12 jw.org ላይ ስለ እኛ > ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች በሚለው ሥር የሚገኘውን “አንዳንድ ፊልሞችን፣ መጻሕፍትን ወይም ዘፈኖችን ትከለክላላችሁ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።