በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ሐምሌ 2014

‘እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ’

‘እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ’

‘“እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ” ይላል ይሖዋ።’—ኢሳ. 43:10

1, 2. (ሀ) ምሥክር መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? የዓለም የመገናኛ ብዙኃን ሳያደርጉ የቀሩት ትልቅ ነገር ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ የዚህ ዓለም የመገናኛ ብዙኃን እገዛ የማያስፈልገው ለምንድን ነው?

ምሥክር መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? አንድ መዝገበ ቃላት እንደሚገልጸው ምሥክር የሚባለው “ስለአየው፣ ስለሰማው፣ ስለሚያውቀው ነገር . . . ቃሉን የሚሰጥ” ሰው ነው። በፒተርማርትጽበር፣ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከ160 ለሚበልጡ ዓመታት ሲታተም የቆየን አንድ ጋዜጣ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ጋዜጣው በአሁኑ ጊዜ ዘ ዊትነስ (ምሥክር) በመባል ይታወቃል። የጋዜጦች ዓላማ በዓለም ላይ የተከናወነውን ነገር በትክክል መዘገብ ስለሆነ ለዚህ ጋዜጣ እንዲህ ያለ ስያሜ መሰጠቱ ተገቢ ነው። የዚህ ጋዜጣ የመጀመሪያ አዘጋጅ ጋዜጣው “ምንም ሳይጨምርና ሳይቀንስ ሙሉውን እውነት” እንደሚናገር ገልጿል።

2 የሚያሳዝነው ግን የዚህ ዓለም የዜና ማሠራጫዎች በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን እውነታዎች በአብዛኛው ችላ ብለዋቸዋል፤ አልፎ ተርፎም በተዛባ መንገድ አቅርበዋቸዋል። ለምሳሌ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በጥንት ዘመን በኖረው በነቢዩ ሕዝቅኤል አማካኝነት ከተናገረው ‘አሕዛብ እኔ ይሖዋ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ’ ከሚለው ሐሳብ ጋር በተያያዘ የዚህ እውነተኝነት ታይቷል። (ሕዝ. 39:7) ይሁን እንጂ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ በዚህ ዓለም ያሉት የመገናኛ ብዙኃን እገዛ አያስፈልገውም። ስለ እሱና ባለፉት ዘመናትም ሆነ አሁን ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ ስላደረጋቸው ነገሮች ለብሔራት ሁሉ የሚያውጁ ወደ ስምንት ሚሊዮን ገደማ ምሥክሮች አሉት። ይህ የምሥክሮች ሠራዊት አምላክ ወደፊት ለሰው ልጆች ለማምጣት ቃል የገባቸውን በረከቶችም ያውጃል። እኛም ለምሥክርነቱ ሥራ ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነ በኢሳይያስ 43:10 ላይ ከተመሠረተው አምላክ ከሰጠን ስም ጋር ተስማምተን  እንደምንኖር እናሳያለን፤ ጥቅሱ “እናንተ ምስክሮቼ፣ የመረጥሁትም ባሪያዬ ናችሁ” ይላል።

3, 4. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አዲስ ስም ያገኙት መቼ ነው? ስለዚህ ስም ምን ተሰምቷቸው ነበር? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 በይሖዋ ስም መጠራት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ምክንያቱም እሱ ‘የዘላለም ንጉሥ’ ነው። ይሖዋ “ስሜም ለዘለዓለም ይኸው ነው፤ ወደፊት በተከታታይ በሚነሣው ትውልድ ሁሉ የምታሰበው በዚህ ስም ነው” በማለት ተናግሯል። (1 ጢሞ. 1:17፤ ዘፀ. 3:15፤ ከመክብብ 2:16 ጋር አወዳድር።) በ1931 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው ስም መጠራት ጀመሩ። ወንድሞች በዚህ ስም በመጠራታችን የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ የጻፏቸው በርካታ ደብዳቤዎች በዚህ መጽሔት ላይ ወጥተዋል። ለምሳሌ በካናዳ የሚገኝ አንድ ጉባኤ የሚከተለውን ደብዳቤ ጽፏል፦ “‘የይሖዋ ምሥክሮች’ እንደሆንን የሚገልጸውን ምሥራች በመስማታችን በጣም ተደስተናል፤ እንዲሁም በዚህ አዲስ ስም ለመጠራት ብቁ ለመሆን ቆርጠን ተነስተናል።”

4 በአምላክ ስም የመጠራት መብትህን እንደምታደንቅ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? የይሖዋ ምሥክሮች የተባልነው ለምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሰህ ማስረዳትስ ትችላለህ?

በጥንት ጊዜ የነበሩ የአምላክ ምሥክሮች

5, 6. (ሀ) እስራኤላውያን ወላጆች ስለ ይሖዋ የሚመሠክሩት እንዴት ነበር? (ለ) እስራኤላውያን ወላጆች ምን እንዲያደርጉም ታዝዘዋል? በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆችስ ይህን ማድረግ ያለባቸው ለምንድን ነው?

5 በኢሳይያስ ዘመን የነበረ እያንዳንዱ እስራኤላዊ የይሖዋ ‘ምሥክር’ ነበር፤ ብሔሩ በአጠቃላይ ደግሞ የአምላክ “ባሪያ” ነበር። (ኢሳ. 43:10) እስራኤላውያን ወላጆች ስለ ይሖዋ የሚመሠክሩበት አንደኛው መንገድ አምላክ ከአባቶቻቸው ጋር ስለነበረው ግንኙነት ለልጆቻቸው ማስተማር ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ሕዝቡ በየዓመቱ ፋሲካን እንዲያከብሩ በታዘዙ ወቅት እንዲህ ተብለው ነበር፦ “ልጆቻችሁ ስለ ሥርዐቱ ምንነት ሲጠይቋችሁ፣ ‘ግብፃውያንን በቀሠፈ ጊዜ፣ በግብፅ ምድር የእስራኤላውያንን ቤት አልፎ በመሄድ ቤታችንን ላተረፈ፣ ለእግዚአብሔር የፋሲካ መሥዋዕት ነው’ ብላችሁ ንገሯቸው።” (ዘፀ. 12:26, 27) በተጨማሪም እስራኤላውያን ወላጆች፣  ሙሴ በግብፁ መሪ ፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ቀርቦ እስራኤላውያን ይሖዋን በምድረ በዳ እንዲያመልኩ እንዲፈቅድላቸው በጠየቀው ጊዜ ፈርዖን “እንድታዘዘውና እስራኤልን እንድለቅለት ለመሆኑ ይህ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ማነው?” በማለት እንደመለሰለት ለልጆቻቸው ነግረዋቸው ይሆናል። (ዘፀ. 5:2) ከዚህም ሌላ ፈርዖን ያነሳው ጥያቄ፣ ግብፅ በአሥር መቅሰፍቶች ከተመታችና እስራኤላውያን ቀይ ባሕር ላይ ከግብፅ ሠራዊት ካመለጡ በኋላ የማያሻማ መልስ እንዳገኘ ወላጆች ለልጆቻቸው ተርከውላቸው መሆን አለበት። ይሖዋ ጥንትም ሆነ ዛሬ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው። የእስራኤል ብሔርም ይሖዋ እውነተኛና የገባውን ቃል የሚፈጽም አምላክ ለመሆኑ የዓይን ምሥክር ነበር።

6 የይሖዋን ስም የመሸከም መብታቸውን ከፍ አድርገው የሚመለከቱ እስራኤላውያን እነዚህን አስደናቂ ክንውኖች ለልጆቻቸው ብቻ ሳይሆን የሌላ አገር ዜጋ ለሆኑ ባሪያዎቻቸውም ተናግረው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። በሌላ በኩል ደግሞ እስራኤላውያን፣ ከቅድስና ጋር በተያያዘ የአምላክን መሥፈርቶች እንዲጠብቁ ልጆቻቸውን ማሠልጠን እንዳለባቸውም ተነግሯቸው ነበር። ይሖዋ “እኔ . . . አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ብሏል። (ዘሌ. 19:2፤ ዘዳ. 6:6, 7) ይህ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ወላጆች ሊከተሉት የሚገባ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! እነሱም በቅድስና ረገድ የአምላክን መሥፈርቶች እንዲጠብቁ ልጆቻቸውን በማሠልጠን ለአምላክ ታላቅ ስም ክብር እንዲያመጡ ሊረዷቸው ይገባል።—ምሳሌ 1:8ን እና ኤፌሶን 6:4ን አንብብ።

ልጆቻችንን ስለ ይሖዋ ማስተማር ለስሙ ክብር ያመጣል (አንቀጽ 5, 6ን ተመልከት)

7. (ሀ) እስራኤላውያን ለይሖዋ ታማኝ መሆናቸው በዙሪያቸው በነበሩት ብሔራት ላይ ምን ውጤት ነበረው? (ለ) በአምላክ ስም የሚጠሩ ሁሉ ምን ኃላፊነት አለባቸው?

7 እስራኤላውያን ታማኝ ሆነው ሲመላለሱ ስለ አምላክ ስም ጥሩ ምሥክርነት ይሰጡ ነበር። ሕዝቡ እንዲህ ተብለው ነበር፦ “የምድር አሕዛብ ሁሉ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ስም መጠራትህን ያያሉ፤ ይፈሩሃልም።” (ዘዳ. 28:10) የሚያሳዝነው ግን ከእስራኤላውያን ታሪክ መመልከት እንደሚቻለው አብዛኛውን ጊዜ ታማኞች አልነበሩም። በተደጋጋሚ ጊዜያት ይሖዋን ትተው ጣዖታትን ያመልኩ ነበር። ይባስ ብሎ ደግሞ እንደሚያመልኳቸው የከነዓን አማልክት ጨካኞች በመሆን ልጆቻቸውን መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ እንዲሁም ድሆችን ይጨቁኑ ነበር። እኛም የምንጠራው እጅግ ቅዱስ በሆነው አምላክ ስም እንደመሆኑ መጠን እሱን በመምሰል ምንጊዜም ቅዱሳን ለመሆን ጥረት እንድናደርግ የሚያበረታታ ግሩም ትምህርት እናገኛለን።

“እነሆ፤ አዲስ ነገር አደርጋለሁ”

8. ይሖዋ ለኢሳይያስ ምን ተልእኮ ሰጠው? ኢሳይያስስ ምን ምላሽ ሰጠ?

8 ይሖዋ እስራኤላውያንን አስደናቂ በሆነ መንገድ ከምርኮ ነፃ እንደሚያወጣቸው አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ኢሳ. 43:19) የኢሳይያስ መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ምዕራፎች በዋነኝነት የሚናገሩት በኢየሩሳሌምና በአቅራቢያዋ ባሉ ከተሞች ላይ ስለሚመጣው ጥፋት ነው። የሰዎችን ልብ ማንበብ የሚችለው ይሖዋ፣ ኢሳይያስ መጥፎ ምላሽ እንደሚገጥመው ቢያውቅም እንኳ የማስጠንቀቂያውን መልእክት ማወጁን እንዲቀጥል አዞታል። ኢሳይያስ የሕዝቡ ምላሽ ግራ ያጋባው ከመሆኑም ሌላ የአምላክ ብሔር ንስሐ የማይገባው እስከ መቼ እንደሆነ ለማወቅ ፈልጎ ነበር። ታዲያ አምላክ ምን ምላሽ ሰጠው? “ከተሞች እስኪፈራርሱና፣ የሚኖሩባቸው እስኪያጡ፣ ቤቶችም ወና እስኪሆኑና፣ ምድርም ፈጽሞ ባድማ እስክትሆን ድረስ” እንደሆነ ገለጸለት።—ኢሳይያስ 6:8-11ን አንብብ።

9. (ሀ) ኢሳይያስ ስለ ኢየሩሳሌም የተናገረው ትንቢት የተፈጸመው መቼ ነው? (ለ) በዘመናችን ንቁ መሆን እንዳለብን የሚጠቁመው የትኛው ማሳሰቢያ ነው?

9 ኢሳይያስ ይህን ተልእኮ የተቀበለው በንጉሥ ዖዝያን የግዛት ዘመን የመጨረሻ ዓመት ማለትም በ778 ዓ.ዓ. ገደማ ነበር። የነቢይነት ሥራው ለ46 ዓመታት ያህል ይኸውም በንጉሥ ሕዝቅያስ የግዛት ዘመን ውስጥ ቢያንስ እስከ 732 ዓ.ዓ. ድረስ ዘልቋል። ኢሳይያስ ትንቢቱን የተናገረው ኢየሩሳሌም በ607 ዓ.ዓ. ከመጥፋቷ ከ125 ዓመታት በፊት ነው። በመሆኑም የአምላክ ብሔር ምን እንደሚያጋጥመው ከረጅም ጊዜ በፊት ግልጽ ማስጠንቀቂያ  ተሰጥቶ ነበር። በዛሬው ጊዜም ይሖዋ፣ ወደፊት ምን እንደሚመጣ በሕዝቡ በኩል ግልጽ ማሳሰቢያ እንዲሰጥ እያደረገ ነው። መጠበቂያ ግንብ መጽሔት የሰይጣን ክፉ አገዛዝ በቅርቡ እንደሚያበቃና በምትኩ የኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት እንደሚጀምር ከመጀመሪያው እትሙ አንስቶ ለ135 ዓመታት ለአንባቢዎቹ ሲያሳውቅ ቆይቷል።—ራእይ 20:1-3, 6

10, 11. በባቢሎን የነበሩት እስራኤላውያን የትኛው የኢሳይያስ ትንቢት ሲፈጸም ተመልክተዋል?

10 ለባቢሎናውያን እጃቸውን የሰጡ በርካታ ታዛዥ አይሁዳውያን ኢየሩሳሌም ስትጠፋ በሕይወት የተረፉ ሲሆን ወደ ባቢሎን በግዞት ተወስደዋል። (ኤር. 27:11, 12) በዚያም 70 ዓመት ከቆዩ በኋላ የሚከተለው አስደናቂ ትንቢት ሲፈጸም የዓይን ምሥክር መሆን ችለዋል፦ “እናንተን የሚታደግ የእስራኤል ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ይላል፥ ‘እናንተን ለማዳን በባቢሎን ላይ የሚዘምት ሠራዊት እልካለሁ፤ የከተማይቱን ቅጽር በሮች እሰባብራለሁ።’”—ኢሳ. 43:14 የ1980 ትርጉም

11 ከዚህ ትንቢት ጋር በሚስማማ መልኩ ጥቅምት 539 ዓ.ዓ. አንድ ቀን ምሽት ላይ ታሪክን የቀየረ ክስተት ተፈጠረ። የባቢሎን ንጉሥና መኳንንቱ በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ በተማረኩ ቅዱስ ዕቃዎች ወይን ጠጅ እየጠጡና በሰው እጅ የተሠሩ አማልክቶቻቸውን እያወደሱ ሳለ የሜዶንና የፋርስ ወታደሮች ባቢሎንን ተቆጣጠሯት። ባቢሎንን ያንበረከከው ቂሮስ፣ በ538 ወይም በ537 ዓ.ዓ. አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው የአምላክን ቤተ መቅደስ እንዲገነቡ መመሪያ ሰጠ። እነዚህ ክንውኖች እንደሚፈጸሙና ይሖዋ ንስሐ የገቡ ሕዝቦቹ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሱ የሚያስፈልጋቸውን እንደሚያሟላላቸው ብሎም ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ቃል መግባቱን ኢሳይያስ አስቀድሞ በትንቢት ተናግሮ ነበር። አምላክ፣ ስለ ሕዝቡ ሲናገር “ለራሴ ያበጀሁት ሕዝብ ምስጋናዬን ያውጅ ዘንድ ይህን አደርጋለሁ” ብሏል። (ኢሳ. 43:21፤ 44:26-28) በግዞት የነበሩት ሕዝቦች ወደ አገራቸው ከተመለሱና በኢየሩሳሌም የይሖዋን ቤተ መቅደስ እንደገና ከገነቡ በኋላ፣ ብቻውን እውነተኛ አምላክ የሆነው ይሖዋ ምንጊዜም ቃሉን እንደሚፈጽም ምሥክር መሆን ችለዋል።

12, 13. (ሀ) የይሖዋ አምልኮ እንደገና ሲቋቋም ከእስራኤላውያን ጋር እነማን ተባብረው ነበር? (ለ) “ሌሎች በጎች” ‘የአምላክን እስራኤል’ ሲደግፉ ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል? ወደፊትስ ምን ተስፋ አላቸው?

12 እስራኤላውያን ያልሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ እንደገና የተቋቋመው ብሔር አባላት ሆኑ፤ ከጊዜ በኋላም በርካታ አሕዛብ የአይሁድን እምነት ተቀብለዋል። (ዕዝራ 2:58, 64, 65፤ አስ. 8:17) በዛሬው ጊዜ የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” አባላት የሆኑት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ‘የአምላክ እስራኤል’ የተባሉትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች በታማኝነት ይደግፋሉ። (ራእይ 7:9, 10፤ ዮሐ. 10:16፤ ገላ. 6:16) እጅግ ብዙ ሕዝብም አምላክ ለሕዝቦቹ በሰጠው የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው ስም ይጠራሉ።

13 በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት እጅግ ብዙ ሕዝብ፣ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ የይሖዋ ምሥክር መሆን ምን ይመስል እንደነበር ከሞት ለተነሱ ሰዎች የመናገር ልዩ አጋጣሚ ያገኛሉ። ይህን ማድረግ የምንችለው ግን በአሁኑ ወቅት እንደ ስማችን  የምንኖርና ምንጊዜም ቅዱስ ለመሆን ጥረት የምናደርግ ከሆነ ብቻ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ኃጢአተኞች በመሆናችን፣ ምንም ያህል ጥረት ብናደርግ የይሖዋን የቅድስና ደረጃ ማሟላት ስለማንችል በየዕለቱ ይሖዋ ይቅር እንዲለን መጠየቅ ይኖርብናል፤ ምንጊዜም ቅዱስ ለመሆን ጥረት የምናደርግ ከሆነ በአምላክ ቅዱስ ስም መጠራት እጅግ በጣም ታላቅ መብት መሆኑን እንደተገነዘብን እናሳያለን።—1 ዮሐንስ 1:8, 9ን አንብብ።

የአምላክ ስም ትርጉም

14. ይሖዋ የሚለው ስም ትርጉሙ ምንድን ነው?

14 በአምላክ ስም የመጠራት መብታችንን ይበልጥ ለማድነቅ እንድንችል በስሙ ትርጉም ላይ ማሰላሰላችን ጠቃሚ ነው። ብዙውን ጊዜ “ይሖዋ” ተብሎ የሚተረጎመው መለኮታዊው ስም ድርጊትን ከሚገልጽ የዕብራይስጥ ግስ የተገኘ ሲሆን “መሆን” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። በመሆኑም ይሖዋ የሚለው ስም “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ፍቺ አለው። ይህ ፍቺ፣ ይሖዋ የጽንፈ ዓለምና የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ፈጣሪ በመሆን ያከናወነውን ተግባር ብሎም ዓላማውን በመፈጸም ረገድ የሚኖረውን ሚና ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል። ከታሪክ እንደታየው ሰይጣንም ሆነ ሌላ ማንኛውም ተቃዋሚ ወደ ፍጻሜው እየገሰገሰ ያለውን የአምላክ ፈቃድ ለማደናቀፍ ምንም ያህል ጥረት ቢያደርግም ይሖዋ ፈቃዱና ዓላማው ፍጻሜውን እንዲያገኝ ማድረጉን ይቀጥላል።

15. ይሖዋ በስሙ ትርጉም ላይ የተንጸባረቀውን የማንነቱን አንድ ገጽታ የገለጸው እንዴት ነው? ( “ትልቅ ትርጉም ያለው ስም” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

15 አምላክ ሕዝቡን እየመራ ከግብፅ እንዲያወጣ ሙሴን ባዘዘው ጊዜ የስሙን ትርጉም ለማብራራት “መሆን” ከሚለው ቃል ጋር ተዛማጅ የሆነ ግስ በመጠቀም የማንነቱን አንድ ገጽታ ገልጿል፤ በዚህ ወቅት ግሱን የተጠቀመው በአንደኛ መደብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ሙሴን ‘መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ’ [ወይም “የምሆነውን እሆናለሁ”]” አለው። በመቀጠልም ‘እስራኤላውያንን “‘እሆናለሁ’ ወደ እናንተ ልኮኛል” በላቸው’ አለው።” (ዘፀ. 3:14 NW የ2013 እትም የግርጌ ማስታወሻ) ስለዚህ ይሖዋ በማንኛውም ሁኔታ ዓላማውን ለመፈጸም መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሆናል። ይሖዋ በአንድ ወቅት ባሪያዎች ለነበሩት እስራኤላውያን ነፃ አውጪ፣ ጠባቂና መሪ ከመሆኑም ሌላ ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ሁሉ የሚያሟላ አምላክ ሆኖላቸዋል።

አድናቆታችንን ማሳየት

16, 17. (ሀ) በአምላክ ስም የመጠራት መብታችንን እንደምናደንቅ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

16 በዛሬው ጊዜም ይሖዋ፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ ፍላጎቶቻችንን በሙሉ በማሟላት ከስሙ ትርጉም ጋር የሚስማማ ነገር እያደረገ ነው። ይሁንና የአምላክ ስም ትርጉም፣ መሆን የሚፈልገውን እንደሚሆን የሚገልጽ ብቻ አይደለም። የስሙ ትርጉም፣ ዓላማውን ለመፈጸም ሲል ምሥክሮቹ እንዲያከናውኑ የሚያደርጋቸውን ነገሮችም ያካትታል። በዚህ ላይ ማሰላሰላችን በአምላክ ስም የምንጠራ እንደመሆናችን መጠን ከዚህ መጠሪያችን ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለሳችንን እንድንቀጥል ያነሳሳናል። በኖርዌይ ላለፉት 70 ዓመታት ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክር ሆነው ያገለገሉ ኮረ የተባሉ የ84 ዓመት አረጋዊ እንዲህ ብለዋል፦ “የዘላለም ንጉሥ የሆነውን ይሖዋን ማገልገልና በእሱ ቅዱስ ስም ከሚጠሩት ሕዝቦች አንዱ መሆን ታላቅ ክብር እንደሆነ ይሰማኛል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለሰዎች መናገርና ይህን እውነት ተረድተው ፊታቸው በደስታ ሲፈካ ማየት መቻል ታላቅ መብት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚጠቅመን እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ቤዛው ሰላምና ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንደሚያስገኝላቸው ለሰዎች ማስተማር ከፍተኛ እርካታ ያስገኝልኛል።”

17 በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ፣ ስለ አምላክ የማወቅ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ እንደመጣ አይካድም። ይሁንና እንደ ወንድም ኮረ ሁሉ አንተም ሰሚ ጆሮ አግኝተህ ለአንድ ሰው ስለ ይሖዋ ስም ስታስተምር ከፍተኛ እርካታ አይሰማህም? ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነን ሳለ የኢየሱስም ምሥክሮች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ይህ ጥያቄ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።