“አንድ ሰው አምላክን የሚወድ ከሆነ አምላክ ይህን ሰው ያውቀዋል።”—1 ቆሮ. 8:3

1. አንዳንድ የአምላክ ሕዝቦች ራሳቸውን ያታለሉት እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ተናገር። (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

አንድ ቀን ማለዳ ላይ፣ ሊቀ ካህናቱ አሮን ዕጣንና ፍም የተጨመረበት ጥና ይዞ በይሖዋ ማደሪያ ድንኳን ደጃፍ ላይ ቆሟል። ከእሱ ትንሽ ራቅ ብለው ደግሞ ቆሬና 250 ሰዎች እያንዳንዳቸው ለይሖዋ የሚቀርብ ዕጣን የተጨመረባቸው ጥናዎችን ይዘው ቆመዋል። (ዘኍ. 16:16-18) እነዚህን ሰዎች ለማያውቃቸው ሰው፣ ሁሉም ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ይመስሉ ይሆናል። ይሁንና ከአሮን በስተቀር ሌሎቹ፣ የክህነት መብቱን ለመንጠቅ የሚፈልጉ እብሪተኞችና ዓመፀኞች ናቸው። (ዘኍ. 16:1-11) እነዚህ ሰዎች፣ ይሖዋ አምልኳቸውን እንደሚቀበል በማሰብ ራሳቸውን አታልለው ነበር። ሆኖም ልባቸውን ማንበብና ግብዝነታቸውን መመልከት ለሚችለው ለይሖዋ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ስድብ ነው።—ኤር. 17:10

2. ሙሴ ምን ተናግሮ ነበር? የተናገረው ነገርስ ተፈጽሟል?

2 ይህ ሁኔታ ከመፈጸሙ ከአንድ ቀን በፊት ሙሴ “የእርሱ የሆነው . . . ማን መሆኑን እግዚአብሔር ነገ ጠዋት ይለያል” በማለት ተናግሮ ነበር። (ዘኍ. 16:5) ሙሴ እንዳለውም ይሖዋ፣ የእሱን እውነተኛ አምላኪዎች ከሐሰተኞቹ ለያቸው፤ ይህን ያደረገው ‘እሳት ከእሱ ዘንድ ወርዳ [ቆሬንና] የሚያጥኑትን ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች እንድትበላቸው’ በማድረግ ነው። (ዘኍ. 16:35፤ 26:10) በዚህ ጊዜ ይሖዋ አሮንን ከእነዚህ ሰዎች ጋር አለማጥፋቱ፣ አሮንን ትክክለኛው ካህንና እውነተኛው የአምላክ አገልጋይ አድርጎ እንደተቀበለው የሚያሳይ ነው።—1 ቆሮንቶስ 8:3ን አንብብ።

3. (ሀ) በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመን ምን ዓይነት ሁኔታ ተከስቶ ነበር? (ለ) ይሖዋ በሙሴ ዘመን በዓመፀኞች ላይ እርምጃ መውሰዱ ምን እንድንገነዘብ ያደርገናል?

 3 ከ1,500 ዓመታት ገደማ በኋላ በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመንም ተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ክርስቲያን ነን የሚሉ አንዳንድ ሰዎች የሐሰት ትምህርቶችን ማስተማር ጀመሩ፤ ይሁን እንጂ እንዲህ እያደረጉም የክርስቲያን ጉባኤ አባል ሆነው ቀጥለው ነበር። አስተውሎ ላልተመለከተ ሰው እነዚህ ከሃዲዎች ከሌሎቹ የጉባኤ አባላት የሚለዩበት ነገር ያለ ላይመስል ይችላል። ይሁንና እነዚህ ሰዎች የሚያስፋፉት ክህደት ለታማኝ ክርስቲያኖች አደገኛ ነበር። የበግ ለምድ የለበሱት እነዚህ ተኩላዎች “የአንዳንዶችን እምነት [ማፍረስ]” ጀምረው ነበር። (2 ጢሞ. 2:16-18) ሆኖም ይሖዋ ይህን ጉዳይ ተመልክቶታል፤ ጳውሎስም ቢሆን ከበርካታ ዘመናት በፊት ቆሬና ግብረ አበሮቹ የዓመፅ አካሄድ ሲከተሉ አምላክ የወሰደውን እርምጃ ስለሚያውቅ ይሖዋ ይህን ሁኔታ እንዳስተዋለ እርግጠኛ ነበር። እስቲ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመልከት።

‘እኔ ይሖዋ አልለወጥም’

4. ጳውሎስ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነበር? ይህን ስሜቱን ለጢሞቴዎስ የገለጸለትስ እንዴት ነው?

4 ይሖዋ፣ ለእሱ በሚያቀርቡት አምልኮ ረገድ ግብዝ የሆኑ ሰዎችንም ሆነ ለእሱ ታዛዥ የሆኑትን ለይቶ እንደሚያውቅ ጳውሎስ እርግጠኛ ነበር። ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ የተጠቀመባቸው ቃላት ስለዚህ ጉዳይ ምን ያህል እርግጠኛ እንደሆነ ያሳያሉ። ጳውሎስ፣ ከሃዲዎች በተወሰኑ የጉባኤው አባላት መንፈሳዊነት ላይ እያደረሱ ስላሉት ጉዳት ከገለጸ በኋላ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ይሁን እንጂ ‘ይሖዋ የእሱ የሆኑትን ያውቃል’ እንዲሁም ‘የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ከክፋት ይራቅ’ የሚል ማኅተም ያለበት ጠንካራው የአምላክ መሠረት ጸንቶ ይኖራል።”—2 ጢሞ. 2:18, 19

5, 6. ጳውሎስ “ጠንካራው የአምላክ መሠረት” የሚለውን ሐረግ መጠቀሙ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው? ይህ አገላለጽ ጢሞቴዎስ ላይ ምን ስሜት አሳድሮ ሊሆን ይችላል?

5 ጳውሎስ እዚህ ጥቅስ ላይ የተጠቀመባቸው ቃላት ትኩረታችንን የሚስቡት ለምንድን ነው? “ጠንካራው የአምላክ መሠረት” የሚለው አገላለጽ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እዚህ ቦታ ላይ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “መሠረት” የሚለውን ቃል የተለያዩ ነገሮችን በምሳሌያዊ መንገድ ለመግለጽ ይጠቀምበታል፤ ለአብነት ያህል፣ ይህ ቃል ምድራዊቷ ኢየሩሳሌም የጥንቷ እስራኤል ዋና ከተማ መሆኗን ለመግለጽ ተሠርቶበታል። (መዝ. 87:1, 2 የ1980 ትርጉም) ኢየሱስ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተው ሚናም ከመሠረት ጋር ተወዳድሯል። (1 ቆሮ. 3:11፤ 1 ጴጥ. 2:6) ለመሆኑ ጳውሎስ ስለ “ጠንካራው የአምላክ መሠረት” ሲናገር በአእምሮው ምን ይዞ ነበር?

6 ጳውሎስ ስለ “ጠንካራው የአምላክ መሠረት” የገለጸው በዘኍልቍ 16:5 ላይ ሙሴ፣ ስለ ቆሬና ግብረ አበሮቹ ከተናገረው ሐሳብ ጋር አያይዞ ነው። ጳውሎስ በሙሴ ዘመን የተከናወነውን ሁኔታ የጠቀሰው ጢሞቴዎስን ሊያበረታታውና ይሖዋ የዓመፅ ድርጊትን እንደሚመለከት ብሎም እርምጃ እንደሚወስድ ሊያስታውሰው ፈልጎ እንደሆነ ግልጽ ነው። ከበርካታ ዘመናት በፊት ቆሬ የይሖዋን ዓላማ ማደናቀፍ እንዳልቻለ ሁሉ በጉባኤ ውስጥ የነበሩት ከሃዲዎችም ይህን ማድረግ አይችሉም። እርግጥ ጳውሎስ “ጠንካራው የአምላክ መሠረት” ምን እንደሚያመለክት በዝርዝር አልተናገረም። ይሁንና የተጠቀመባቸው ቃላት ጢሞቴዎስ፣ ይሖዋ ነገሮችን በሚያከናውንበት መንገድ ላይ እንዲተማመን እንደረዱት ጥርጥር የለውም።

7. ይሖዋ፣ ጽድቅና ታማኝነት የሚንጸባረቅበት እርምጃ እንደሚወስድ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

7 የይሖዋ የላቁ መሥፈርቶች ምንጊዜም አይለወጡም። መዝሙር 33:11 “የእግዚአብሔር ሐሳብ . . . ለዘላለም ይጸናል፤ የልቡም ሐሳብ ለትውልድ ሁሉ ነው” ይላል። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችም የይሖዋ አገዛዝ፣ ምሕረቱ ወይም ታማኝ ፍቅሩ እንዲሁም ጽድቁና ታማኝነቱ ለዘላለም ጸንተው እንደሚኖሩ ይገልጻሉ። (ዘፀ. 15:18፤ መዝ. 106:1፤ 112:9፤ 117:2) ሚልክያስ 3:6 ‘እኔ ይሖዋ አልለወጥም’ ይላል። በተመሳሳይም ያዕቆብ 1:17 “[ይሖዋ] ቦታውን እንደሚቀያይር ጥላ አይለዋወጥም” በማለት ይናገራል።

 በይሖዋ ላይ እምነት እንድናሳድር የሚያደርግ “ማኅተም”

8, 9. ጳውሎስ በተጠቀመበት ምሳሌ ላይ ከገለጸው “ማኅተም” ምን ትምህርት እናገኛለን?

8 ጳውሎስ በ2 ጢሞቴዎስ 2:19 ላይ የተጠቀመበት ምሳሌያዊ አገላለጽ፣ መልእክት የተቀረጸበትን አንድ መሠረት እንድናስብ ያደርገናል፤ መልእክቱ መሠረቱ ላይ በማኅተም የታተመ ያህል ነው። በጥንት ጊዜ በአንድ ሕንፃ መሠረት ላይ ጽሑፍ መቅረጽ የተለመደ ነበር፤ ይህ የሚደረገው ሕንፃውን ማን እንደሠራው ወይም የማን ንብረት እንደሆነ ለመጠቆም ሊሆን ይችላል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መካከል እንዲህ ያለ ምሳሌ የተጠቀመው የመጀመሪያው ሰው ጳውሎስ ነው። * ‘በጠንካራው የአምላክ መሠረት’ ላይ የተቀረጸው ማኅተም ሁለት መልእክቶችን የያዘ ነው። የመጀመሪያው “ይሖዋ የእሱ የሆኑትን ያውቃል” የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ከክፋት ይራቅ” ይላል። ይህም ዘኍልቍ 16:5 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ ያስታውሰናል።—ጥቅሱን አንብብ።

9 ጳውሎስ በተናገረው ምሳሌ ላይ ከገለጸው “ማኅተም” ምን ትምህርት እናገኛለን? የይሖዋ ለሆኑ ሰዎች፣ የአምላክ መሥፈርቶችና መሠረታዊ ሥርዓቶች በሁለት ዓቢይ እውነቶች ሊጠቃለሉ ይችላሉ፦ (1) ይሖዋ ለእሱ ታማኝ የሆኑትን ይወድዳል እንዲሁም (2) ይሖዋ ክፋትን ይጠላል። ታዲያ ይህ ሐሳብ በጉባኤ ውስጥ ከተነሳው ክህደት ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

10. ከሃዲዎች የሚያደርጉት ነገር በጳውሎስ ዘመን በነበሩት ታማኝ ክርስቲያኖች ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር?

10 ጢሞቴዎስና ሌሎች ታማኝ ክርስቲያኖች በመካከላቸው ያሉት ከሃዲዎች በሚያደርጉት ነገር ተረብሸው እንደሚሆን የታወቀ ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ ከሃዲዎች የጉባኤው አባል ሆነው እንዲቀጥሉ ለምን እንደተፈቀደላቸው ጥያቄ አንስተው ሊሆን ይችላል። እንዲያውም እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ይሖዋ በእነሱ የታማኝነት አቋምና በከሃዲዎቹ የግብዝነት አምልኮ መካከል ያለውን ልዩነት እየተመለከተ መሆን አለመሆኑ አሳስቧቸው ሊሆን ይችላል።—ሥራ 20:29, 30

የክህደት ዝንባሌ ያላቸው ክርስቲያኖች በጢሞቴዎስ ላይ ተጽዕኖ እንዳላሳደሩበት ግልጽ ነው (ከአንቀጽ 10-12ን ተመልከት)

11, 12. የጳውሎስ ደብዳቤ የጢሞቴዎስን እምነት አጠናክሮለታል የምንለው ለምንድን ነው?

11 የጳውሎስ ደብዳቤ፣ የጢሞቴዎስን እምነት እንዳጠናከረለት ጥርጥር የለውም፤ ታማኙ አሮን ትክክል መሆኑ ሲረጋገጥ ብሎም ግብዝ የሆኑት ቆሬና ተባባሪዎቹ ሲጋለጡ፣ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ሲያጡ እንዲሁም ሲጠፉ የነበረውን ሁኔታ ጢሞቴዎስ እንዲያስታውስ ይህ ደብዳቤ ረድቶት መሆን አለበት። የጳውሎስን ሐሳብ በሌላ መንገድ ብንገልጸው፣ አስመሳይ ክርስቲያኖች በጉባኤ ውስጥ ቢኖሩም እንኳ ይሖዋ እንደ ሙሴ ዘመን ሁሉ በጳውሎስ ዘመንም የእሱ የሆኑትን ማወቅ ይችላል እንደ ማለት ነው።

 12 ይሖዋ መቼም ቢሆን አይለወጥም፤ በመሆኑም እምነት ሊጣልበት ይችላል። እሱ ክፋትን ይጠላል፤ እንዲሁም ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞችን እሱ በወሰነው ጊዜ ይፈርድባቸዋል። ጢሞቴዎስም ቢሆን “የይሖዋን ስም የሚጠራ” ክርስቲያን እንደመሆኑ መጠን አስመሳይ ክርስቲያኖች ከሚያሳድሩት ክፉ ተጽዕኖ መራቅ እንዳለበት ተነግሮታል። *

ከልብ የመነጨ አምልኮ መቼም ቢሆን ከንቱ አይቀርም

13. ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

13 ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የጻፈው ሐሳብ እኛንም በመንፈሳዊ ሊያበረታታን ይችላል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሖዋ ለእሱ የምናሳየውን ታማኝነት በሚገባ እንደሚያውቅ መገንዘባችን የሚያበረታታ ነው። ይሖዋ ለእሱ ታማኝ የሆኑትን ከማወቅ ባለፈ የእሱ ለሆኑት ከልብ ያስባል። መጽሐፍ ቅዱስ “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ” ይላል። (2 ዜና 16:9) እንግዲያው ‘በንጹሕ ልብ’ ተነሳስተን ለይሖዋ የምናደርገው ነገር መቼም ቢሆን ከንቱ እንደማይሆን ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—1 ጢሞ. 1:5፤ 1 ቆሮ. 15:58

14. ይሖዋ የማይቀበለው ምን ዓይነት አምልኮ ነው?

14 ይሖዋ በግብዝነት የሚቀርብ አምልኮን የማይቀበል መሆኑም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው። የይሖዋ “ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ [ስለሚመለከቱ]” እሱ “በፍጹም ልባቸው” የማይታመኑበትን ሰዎች ለይቶ ማወቅ ይችላል። ምሳሌ 3:32 ይሖዋ “ጠማማ” ወይም ተንኮለኛ የሆነን ሰው፣ በሌላ አባባል በድብቅ ኃጢአት እየፈጸመ ታዛዥ መስሎ ለመታየት የሚሞክርን አስመሳይ ሰው ‘እንደሚጸየፍ’ ይናገራል። እንዲህ ያለው ተንኮለኛ ሰው ሌሎችን ለጊዜው ማታለል ይችል ይሆናል፤ ሆኖም ሁሉን ቻይና ጻድቅ የሆነው ይሖዋ “ኀጢአቱን የሚሰውር” ሰው እንዲሳካለት አይፈቅድም።—ምሳሌ 28:13፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:24ን እና ዕብራውያን 4:13ን አንብብ።

15. ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን አይገባም? ለምንስ?

15 አብዛኞቹ የይሖዋ ሕዝቦች ለእሱ የሚያቀርቡት አምልኮ ከልብ የመነጨ ነው። አንድ የጉባኤው አባል ግብዝነት የሚንጸባረቅበት አምልኮ በማቅረብ ሆን ብሎ ይሖዋን ለማታለል ይሞክራል ተብሎ አይጠብቅም። ያም ቢሆን እንዲህ ያለው ሁኔታ በሙሴ ዘመንም ሆነ በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከተከሰተ ዛሬም ቢሆን ሊከሰት ይችላል። (2 ጢሞ. 3:1, 5) ይህ ሲባል ታዲያ የእምነት ባልንጀሮቻችን ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት መጠራጠር አለብን ማለት ነው? በፍጹም! ስለ ወንድሞቻችንና ስለ እህቶቻችን መሠረተ ቢስ የሆነ ጥርጣሬ ማዳበር ተገቢ አይደለም። (ሮም 14:10-12ን እና 1 ቆሮንቶስ 13:7ን አንብብ።) ከዚህም በላይ የጉባኤውን አባላት ታማኝነት የመጠራጠር አዝማሚያ ካለን ይህ የእኛንም መንፈሳዊነት ይጎዳል።

16. (ሀ) ግብዝነት በልባችን ውስጥ ሥር እንዳይሰድድ ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) “ ዘወትር ራሳችሁን መርምሩ፤ . . . ራሳችሁን ዘወትር ፈትኑ” ከሚለው ሣጥን ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

16 እያንዳንዱ ክርስቲያን “የራሱን ሥራ ምንነት [መፈተን]” አለበት። (ገላ. 6:4) ኃጢአተኞች ስለሆንን ለይሖዋ ከልብ የመነጨ አምልኮ እንዳናቀርብ የሚያደርጉ ዝንባሌዎችን ሳይታወቀን ልናዳብር እንችላለን። (ዕብ. 3:12, 13) በመሆኑም ይሖዋን የምናገለግልበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ በየጊዜው ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል። ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቃችን ተገቢ ነው፦ ‘ይሖዋን የማመልከው ስለምወደውና ሉዓላዊነቱን ስለተቀበልኩ ነው? ወይስ ይበልጥ ትኩረት የማደርገው ወደፊት በገነት ውስጥ በማገኛቸው በረከቶች ላይ ነው?’ (ራእይ 4:11) በእርግጥም ማንኛችንም ብንሆን አካሄዳችንን መመርመራችንና በልባችን ውስጥ በትንሹም ቢሆን ግብዝነት እንዳይኖር መጠንቀቃችን ይጠቅመናል።

ታማኝነት ደስታ ያስገኛል

17, 18. ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ከልብ የመነጨ መሆን ያለበት ለምንድን ነው?

17 ለይሖዋ ከልብ የመነጨ አምልኮ ለማቅረብ ጥረት ማድረጋችን ብዙ በረከቶች ያስገኝልናል።  መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ኀጢአቱን የማይቈጥርበት፣ በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው፣ እርሱ ቡሩክ ነው” ብሏል። (መዝ. 32:2) በልባቸው ውስጥ ምንም ዓይነት ግብዝነት የማይገኝ ሰዎች ይበልጥ ደስተኞች ናቸው፤ እንዲሁም ወደፊት ፍጹም የሆነ ደስታ የማግኘት ተስፋ ይኖራቸዋል።

18 ይሖዋ፣ መጥፎ ሥራ የሚሠሩ ወይም ሁለት ዓይነት ሕይወት የሚመሩ ሰዎችን እሱ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ በማጋለጥ “በጻድቁና በኀጢአተኛው መካከል፣ እግዚአብሔርን በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል [ያለው] ልዩነት” በግልጽ እንዲታይ ያደርጋል። (ሚል. 3:18) እስከዚያው ድረስ ግን “የይሖዋ ዓይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉ፤ ጆሮዎቹም ምልጃቸውን ለመስማት የተከፈቱ ናቸው” የሚለውን ሐሳብ ማወቃችን የሚያበረታታ ነው።—1 ጴጥ. 3:12

^ አን.8 ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ይህን ደብዳቤ ከላከ ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በኋላ የተጻፈው ራእይ 21:14 የ12ቱ ሐዋርያት ስሞች ስለተጻፉባቸው 12 “የመሠረት ድንጋዮች” ይገልጻል።

^ አን.12 የሚቀጥለው የጥናት ርዕስ፣ ከክፋት በመራቅ ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።