አስከሬን ማቃጠል ለክርስቲያኖች ተገቢ ነው?

በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አስከሬን ማቃጠልን የሚቃወም ሐሳብ አናገኝም።

የሰዎች አስከሬን ወይም አፅም እንደተቃጠለ የሚገልጹ ዘገባዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ። (ኢያሱ 7:25፤ 2 ዜና 34:4, 5) ይህ መሆኑ ሰዎቹ ክብር ያለው የቀብር ሥነ ሥርዓት እንደማይገባቸው የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አስከሬን ማቃጠል ሁልጊዜ እንዲህ ዓይነት ትርጉም የሚያስተላልፍ ነበር ማለት አይደለም።

ስለ ንጉሥ ሳኦልና ስለ ሦስቱ ልጆቹ ሞት የሚገልጸው ዘገባ ይህን ያሳያል። አራቱም የሞቱት ከፍልስጤማውያን ጋር ሲዋጉ ነበር። አንደኛው ልጅ የዳዊት ጥሩ ወዳጅና ታማኝ ደጋፊ የሆነው ዮናታን ነበር። በኢያቢስ ገለዓድ የሚኖሩ ጀግና እስራኤላውያን ስለተፈጠረው ሁኔታ በሰሙ ጊዜ የአራቱንም አስከሬን ፈልገው በማግኘት ካቃጠሉት በኋላ አጥንታቸውን ቀበሩት። ከጊዜ በኋላ ዳዊት እነዚህን እስራኤላውያን ላደረጉት ነገር አመስግኗቸዋል።—1 ሳሙ. 31:2, 8-13፤ 2 ሳሙ. 2:4-6

በቅዱሳን መጻሕፍት መሠረት ሙታን ያላቸው ተስፋ ትንሣኤ ነው፤ ይህም የሞተው ሰው በድጋሚ ሕያው እንደሚሆን ያሳያል። የሞተው ሰው አስከሬን ተቃጠለም አልተቃጠለ፣ ይሖዋ ግለሰቡን አዲስ አካል ሰጥቶ ወደ ሕይወት ከመመለስ አያግደውም። በንጉሥ ናቡከደነፆር ትእዛዝ በእቶን እሳት ተቃጥለው እንዲሞቱ የተፈረደባቸው ሦስቱ ታማኝ ዕብራውያን በዚህ መንገድ ቢጠፉ አምላክ ሊያስነሳቸው እንደማይችል በማሰብ አልፈሩም። (ዳን. 3:16-18) በናዚ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ከተገደሉ በኋላ አስከሬናቸው የተቃጠለ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። በፍንዳታዎች ወይም በሌሎች ምክንያቶች ሕይወታቸውን ያጡ የአምላክ አገልጋዮች በድናቸው ሊገኝ አልቻለም። ያም ሆኖ ትንሣኤ እንደሚያገኙ የተረጋገጠ ነው።—ራእይ 20:13

ይሖዋ አንድን ግለሰብ ከሞት ለማስነሳት የቀድሞ አካሉን አሰባስቦ ማገጣጠም አያስፈልገውም። አምላክ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ከሞት በማስነሳት በሰማይ እንዲኖሩ ካደረገበት መንገድ ይህን ማየት ይቻላል። “መንፈስ ሆኖ ሕያው” ከተደረገው ከኢየሱስ ጋር በሚመሳሰል መልኩ ቅቡዓን ክርስቲያኖችም መንፈሳዊ አካል ይዘው ይነሳሉ፤ ያም ቢሆን ከሞት የሚነሱት እነዚያው ግለሰቦች ራሳቸው ናቸው። ከቀድሞ ሥጋዊ አካላቸው ውስጥ ወደ ሰማይ ይዘው የሚሄዱት አንድም ክፍል አይኖርም።—1 ጴጥ. 3:18፤ 1 ቆሮ. 15:42-53፤ 1 ዮሐ. 3:2

ትንሣኤ ማግኘት አለማግኘታችን የተመካው በአስከሬናችን ላይ በሚደርሰው ነገር ላይ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ የሰጣቸውን ተስፋዎች ለመፈጸም ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ እንዳለው ባለን እምነት ላይ ነው። (ሥራ 24:15) እርግጥ ነው፣ አምላክ ከዚህ በፊት የሞቱ ሰዎችን እንዴት እንዳስነሳና ወደፊትም ቢሆን ይህን እንዴት እንደሚያከናውን ሙሉ በሙሉ መረዳት አንችልም። ይሁን እንጂ ይሖዋ ቃሉን እንደሚፈጽም እንተማመናለን። ይሖዋ ኢየሱስን በማስነሳት “ዋስትና ሰጥቷል።”—ሥራ 17:31፤ ሉቃስ 24:2, 3

ክርስቲያኖች ከአስከሬን ጋር በተያያዘ የአካባቢውን ባሕል፣ የሰዎችን አመለካከት እና የአገሩን ሕግ ከግምት ማስገባታቸው ተገቢ ነው። (2 ቆሮ. 6:3, 4) እንግዲያው አስከሬን የማቃጠል ጉዳይ ለግለሰቡ ወይም ለቤተሰቡ የተተወ ውሳኔ ነው።