በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ሰኔ 2014

‘አምላክህን ይሖዋን ውደድ’

‘አምላክህን ይሖዋን ውደድ’

“አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።”—ማቴ. 22:37

1. በአምላክና በልጁ መካከል ያለው ፍቅር ሊያድግ የቻለው እንዴት ነው?

የይሖዋ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ‘አብን እንደሚወደው’ ተናግሯል። (ዮሐ. 14:31) በተጨማሪም ኢየሱስ “አብ ወልድን ይወደዋል” ብሏል። (ዮሐ. 5:20) ይህ የሚያስገርም አይደለም። ምክንያቱም ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ለዘመናት የአምላክ “ዋና ባለሙያ ነበር።” (ምሳሌ 8:30) ይሖዋና ኢየሱስ አብረው መሥራታቸው ወልድ ስለ አብ ባሕርያት በሚገባ ለማወቅ አስችሎታል፤ ከዚህ አንጻር ወልድ አባቱን እንዲወደው የሚያደርጉ እጅግ በጣም ብዙ ምክንያቶች አሉ ሊባል ይችላል። በመሆኑም እርስ በርስ መቀራረባቸው በመካከላቸው ያለው ፍቅር እያደገ እንዲሄድ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ምንም ጥያቄ የለውም።

2. (ሀ) ለአንድ ሰው ፍቅር ማዳበር ምን ይጠይቃል? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 ለአንድ ሰው ፍቅር እንዲኖረን ከተፈለገ ግለሰቡን በጥልቅ መውደድ ይኖርብናል። መዝሙራዊው ዳዊት “ጕልበቴ እግዚአብሔር ሆይ፤ እወድሃለሁ” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 18:1) እኛም እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊኖረን ይገባል፤ ምክንያቱም ይሖዋን የምንታዘዘው ከሆነ እሱም እኛን ይወደናል። (ዘዳግም 7:12, 13ን አንብብ።) ይሁንና ልናየው የማንችለውን አምላክ መውደድ እንችላለን? ለመሆኑ አምላክን መውደድ ሲባል ምን ማለት ነው? ይሖዋን እንድንወደው የሚያነሳሱን ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ለአምላክ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችለውስ እንዴት ነው?

 አምላክን ልንወደው እንችላለን የምንለው ለምንድን ነው?

3, 4. ይሖዋን መወደድ እንችላለን የምንለው ለምንድን ነው?

3 “አምላክ መንፈስ ነው”፤ በመሆኑም ልናየው አንችልም። (ዮሐንስ 4:24) ይሁንና ይሖዋን ልንወደው እንችላለን፤ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይም ይህን ፍቅር እንድናሳይ ታዝዘናል። ለምሳሌ፣ ሙሴ እስራኤላውያንን “አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደድ” ብሏቸዋል።—ዘዳ. 6:5

4 ለአምላክ ጥልቅ ፍቅር ሊኖረን ይችላል የምንለው ለምንድን ነው? መንፈሳዊ ፍላጎትና ፍቅር የማሳየት ችሎታ እንዲኖረን አድርጎ ስለፈጠረን ነው። መንፈሳዊ ፍላጎታችንን በተገቢው መንገድ ስናረካ ለይሖዋ ያለን ፍቅር ይጨምራል፤ ይህ ደግሞ ደስታ ያስገኝልናል። ኢየሱስ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው” ብሏል፤ ምክንያቱም “መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነው።” (ማቴ. 5:3) አንድ መጽሐፍ፣ ሰዎች በተፈጥሯቸው ያላቸውን የአምልኮ ፍላጎት አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የሰው ልጅ ከእሱ ይበልጥ ኃያል የሆነን አንድ አካል ለማግኘት ያደረገው ፍለጋና በእሱ ለማመን ያደረገው ጥረት ዓለም አቀፋዊ መሆኑን ስንመለከት ሁኔታው ሊያስደንቀን፣ ሊያስገርመንና ሊያስደምመን ይገባል።”—ማን ዳዝ ኖት ስታንድ አሎን፣ በአብርሃም ሞሪሰን የተዘጋጀ

5. አምላክን መፈለግ ከንቱ ድካም እንዳልሆነ እንዴት ማወቅ እንችላለን?

5 አምላክን መፈለግ ከንቱ ድካም ነው? በፍጹም፣ ምክንያቱም አምላክ ፈልገን እንድናገኘው ይሻል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በፓርተኖን አቅራቢያ በሚገኘው በአርዮስፋጎስ ለተሰበሰበው ሕዝብ ምሥክርነት በሰጠበት ጊዜ ይህን ግልጽ አድርጓል። ፓርተኖን፣ የጥንቷ አቴንስ ከተማ ጠባቂ አምላክ እንደሆነች ተደርጋ የምትታየው የአቴና ቤተ መቅደስ ነው። ጳውሎስ “ዓለምንና በውስጡ ያለውን ነገር ሁሉ የፈጠረው አምላክ፣ . . . በእጅ በተሠሩ ቤተ መቅደሶች ውስጥ [እንደማይኖር]” ሲናገር በቦታው እንደነበርክ አድርገህ አስብ። ሐዋርያው ጳውሎስ ቀጥሎ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “[አምላክ] በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩም የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤ የተወሰኑትን ዘመናትና የሰው ልጆች የሚኖሩበትንም ድንበር ደነገገ፤ ይህንም ያደረገው ሰዎች አምላክን እንዲፈልጉትና አጥብቀው በመሻት እንዲያገኙት ብሎ ነው፤ እንዲህ ሲባል ግን እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ነው ማለት አይደለም።” (ሥራ 17:24-27) አዎ፣ ሰዎች አምላክን ፈልገው ማግኘት ይችላሉ። ከሰባት ሚሊዮን ተኩል የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክን ‘ፈልገው’ ማግኘት ችለዋል፤ ደግሞም ለእሱ ፍቅር አላቸው።

አምላክን መውደድ ሲባል ምን ማለት ነው?

6. ኢየሱስ እንደገለጸው “ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ” የትኛው ነው?

6 ለይሖዋ ያለን ፍቅር ከልብ የመነጨ መሆን አለበት። ኢየሱስ፣ አንድ ፈሪሳዊ “መምህር፣ ከሕጉ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው ነው?” ብሎ በጠየቀው ጊዜ የሰጠው መልስ ይህን ግልጽ ያደርገዋል። ኢየሱስ “‘አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።’ ይህ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው” በማለት ለፈሪሳዊው መለሰለት።—ማቴ. 22:34-38

7. አምላክን (ሀ) “በሙሉ ልብ” (ለ) “በሙሉ ነፍስ” (ሐ) “በሙሉ አእምሮ” መውደድ ሲባል ምን ማለት ነው?

7 ኢየሱስ አምላክን ‘በሙሉ ልባችን’ መውደድ እንዳለብን ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? ይሖዋን በመላው ምሳሌያዊ ልባችን መውደድ እንደሚኖርብን ማመልከቱ ነው፤ ይህም በምኞታችን፣ በስሜታችንና በፍላጎታችን ላይ ይንጸባረቃል። በተጨማሪም ‘በሙሉ ነፍሳችን’ ማለትም በመላ ሕይወታችን እሱን መውደድ ይኖርብናል። ከዚህም ሌላ ‘በሙሉ አእምሯችን’ ይኸውም የማሰብ ችሎታችንን ሙሉ በሙሉ ተጠቅመን ልንወደው ይገባል። በመሆኑም ምንም የምናስቀረው ነገር ሳይኖር ይሖዋን ሙሉ በሙሉ መውደድ አለብን።

8. አምላክን በተሟላ መንገድ የምንወደው ከሆነ ምን እንድናደርግ እንነሳሳለን?

8 አምላክን በሙሉ ልባችን፣ ነፍሳችንና አእምሯችን የምንወደው ከሆነ ቃሉን በትጋት እናጠናለን፤ በሙሉ ልባችን ፈቃዱን እናደርጋለን፤ እንዲሁም የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት እናውጃለን።  (ማቴ. 24:14፤ ሮም 12:1, 2) ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር ካለን ወደ እሱ ይበልጥ እንቀርባለን። (ያዕ. 4:8) እርግጥ ነው፣ አምላክን እንድንወደው የሚያነሳሱንን ምክንያቶች በሙሉ ዘርዝረን መጨረስ አንችልም። ጥቂቶቹን ግን እስቲ እንመልከት።

ይሖዋን እንድንወደው የሚያነሳሱን ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

9. የፈጠረንን ብሎም የሚንከባከበንን አምላክ እንድትወደው የሚያነሳሳህ ምንድን ነው?

9 ይሖዋ ፈጣሪያችን ነው፤ ደግሞም ይንከባከበናል። ጳውሎስ “ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው” ብሏል። (ሥራ 17:28) ይሖዋ ምድርን ምቹ መኖሪያ አድርጎ ሰጥቶናል። (መዝ. 115:16) እንደ ምግብ ያሉ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችንም ይሰጠናል። ጳውሎስ ጣዖት አምላኪ ለሆኑት የልስጥራ ነዋሪዎች ‘ሕያው ስለሆነው አምላክ’ ሲነግራቸው “መልካም ነገሮች በማድረግ ለራሱ ምሥክር ከማቅረብ ወደኋላ አላለም፤ ከሰማይ ዝናብ በማዝነብ እንዲሁም ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠት የተትረፈረፈ ምግብ ያቀርብላችኋል፣ ልባችሁንም በደስታ ይሞላዋል” ያላቸው ለዚህ ነው። (ሥራ 14:15-17) ታዲያ ይህ ታላቁን ፈጣሪያችንን ብሎም በፍቅር የሚንከባከበንን አምላክ እንድንወደው አያነሳሳንም?—መክ. 12:1

10. አምላክ ኃጢአትንና ሞትን ለማስወገድ ያደረገውን ዝግጅት ማወቃችን ምን ስሜት ያሳድርብናል?

10 አምላክ ከአዳም የወረስነውን ኃጢአትና ሞት ለማስወገድ ዝግጅት አድርጓል። (ሮም 5:12) በእርግጥም “አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ለእኛ እንዲሞት በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል።” (ሮም 5:8) ንስሐ የምንገባና በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት የምናሳድር ከሆነ የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት እንችላለን፤ ይህን ስናስብ ልባችን ለይሖዋ ባለን ፍቅር እንደሚሞላ ምንም ጥርጥር የለውም።—ዮሐ. 3:16

11, 12. ይሖዋ የትኞቹን ተስፋዎች ሰጥቶናል?

11 ይሖዋ ‘ውስጣችን በደስታና በሰላም እንዲሞላ የሚያደርግ ተስፋ ሰጥቶናል።’ (ሮም 15:13) አምላክ የሰጠን ተስፋ የእምነት ፈተናዎችን በጽናት ለመቋቋም ያስችለናል። ‘እስከ ሞት ድረስ ታማኝነታቸውን የሚያስመሠክሩ’ ቅቡዓን በሰማይ “የሕይወትን አክሊል” ይቀበላሉ። (ራእይ 2:10) በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያላቸው ደግሞ ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ ከሆነ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ዘላለማዊ በረከት ያገኛሉ። (ሉቃስ 23:43) ታዲያ እንዲህ ያለው ተስፋ ምን እንዲሰማን ያደርጋል? ውስጣችን በደስታና በሰላም እንዲሞላ አያደርግም? ‘የመልካም ስጦታ ሁሉና የፍጹም ገጸ በረከት’ ምንጭ የሆነውን ይሖዋን ከልብ እንድንወደውስ አያነሳሳንም?—ያዕ. 1:17

12 አምላክ አስደሳች የሆነ የትንሣኤ ተስፋ ሰጥቶናል። (ሥራ 24:15) የምንወደውን ሰው በሞት በምናጣበት ጊዜ በጥልቅ እንደምናዝን የታወቀ ነው፤ ያም ሆኖ ትንሣኤ እንዳለ ስለምናውቅ ‘ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች አናዝንም።’ (1 ተሰ. 4:13) ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ በሞት ያንቀላፉትን በተለይም እንደ ኢዮብ ያሉ ቅን ሰዎችን ለማስነሳት ይጓጓል። (ኢዮብ 14:15) የሞቱ ሰዎችን በትንሣኤ ስንቀበል የሚኖረውን ደስታ እስቲ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ይሖዋ አስደናቂ የሆነውን የትንሣኤ ተስፋ መስጠቱ ልባችን ለእሱ ባለን ፍቅር እንዲሞላ የሚያደርግ አይደለም?

13. አምላክ ከልብ እንደሚያስብልን የሚያሳየው ምንድን ነው?

13 ይሖዋ ከልብ ያስብልናል። (መዝሙር 34:6, 18, 19ን እና 1 ጴጥሮስ 5:6, 7ን አንብብ።) አፍቃሪው አምላክ ለእሱ ታማኝ የሆኑትን ሰዎች ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ ነው፤ እኛም ‘በጎቹ’ እንደመሆናችን መጠን ይህንን ማወቃችን የደኅንነት ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል። (መዝ. 79:13) በተጨማሪም አምላክ በመሲሐዊው መንግሥት አማካኝነት የሚያከናውናቸው ነገሮች ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳያሉ። በአምላክ የተመረጠው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ዓመፅን፣ ግፍንና ክፋትን ከምድር ላይ ካስወገደ በኋላ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና በመስጠት ይባርካቸዋል። (መዝ. 72:7, 12-14, 16) አሳቢ የሆነው አምላካችን እንዲህ ያሉ ተስፋዎችን መስጠቱ እሱን በሙሉ ልባችን፣ ነፍሳችን፣ ኃይላችንና አእምሯችን እንድንወደው ያነሳሳናል ቢባል አትስማማም?—ሉቃስ 10:27

14. አምላክ የትኛውን ውድ መብት በመስጠት አክብሮናል?

14 ይሖዋ የእሱ ምሥክሮች የመሆን ውድ  መብት በመስጠት አክብሮናል። (ኢሳ. 43:10-12) ሉዓላዊነቱን የመደገፍና በዚህ ውጥንቅጡ በጠፋ ዓለም ውስጥ ለሰዎች እውነተኛ ተስፋ የማብሰር መብት ስለሰጠን አምላክን ከልብ እንወደዋለን። ከዚህም በላይ ይህን ምሥራች በእምነትና በልበ ሙሉነት እንናገራለን፤ ምክንያቱም ይህ ምሥራች የተመሠረተው ምንጊዜም ቃሉን የሚጠብቀው እውነተኛው አምላክ ባስጻፈው መጽሐፍ ላይ ነው። (ኢያሱ 21:45ን እና ኢያሱ 23:14ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ ይሖዋን እንድንወደው የሚያደርጉንን ምክንያቶች ዘርዝረን መጨረስ አንችልም። ታዲያ ለእሱ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

ለአምላክ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

15. የአምላክን ቃል ማጥናታችንና ተግባራዊ ማድረጋችን የሚረዳን እንዴት ነው?

15 የአምላክን ቃል በትጋት በማጥናትና የተማርነውን ተግባራዊ በማድረግ። እንዲህ ማድረጋችን ይሖዋን እንደምንወደውና ቃሉ ‘ለመንገዳችን ብርሃን’ እንዲሆን ከልብ እንደምንፈልግ ያሳያል። (መዝ. 119:105) የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥመን እንደሚከተሉት ያሉ ማረጋገጫዎች ያበረታቱናል፦ “አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም።” “ምሕረትህ ደግፎ ያዘኝ። የውስጤ ጭንቀት በበዛ መጠን፣ ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት።” (መዝ. 51:17፤ 94:18, 19) ይሖዋ መከራ ለሚደርስባቸው ሰዎች ምሕረት ያሳያል፤ ኢየሱስም ቢሆን ለሰዎች ያዝናል። (ኢሳ. 49:13፤ ማቴ. 15:32) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን ይሖዋ ፍቅራዊ አሳቢነት እንደሚያሳየን በግልጽ ማየት እንድንችል የሚረዳን ሲሆን ይህ ደግሞ እሱን በጥልቅ እንድንወደው ያነሳሳናል።

16. አዘውትረን መጸለያችን ለአምላክ ያለን ፍቅር እንዲጨምር የሚያደርገው እንዴት ነው?

16 አዘውትሮ ወደ አምላክ በመጸለይ። መጸለይ ‘ጸሎት ሰሚ’ ወደሆነው አምላክ ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል። (መዝ. 65:2) አምላክ ለጸሎታችን መልስ እንደሰጠን ስናስተውል ደግሞ ለእሱ ያለን ፍቅር ይበልጥ ጥልቅ እየሆነ ይሄዳል። ለምሳሌ ልንሸከመው ከምንችለው በላይ እንዳንፈተን ማድረጉን አስተውለን ሊሆን ይችላል። (1 ቆሮ. 10:13) የሚያስጨንቅ ነገር አጋጥሞን ወደ ይሖዋ ከልብ ተነሳስተን ምልጃ ባቀረብንበት ወቅት ወደር የሌለውን “የአምላክ ሰላም” ሰጥቶን ሊሆን ይችላል። (ፊልጵ. 4:6, 7) አንዳንድ ጊዜ ልክ እንደ ነህምያ በልባችን የምንጸልይበት ወቅት ይኖራል፤ በዚህ ጊዜም ቢሆን ይሖዋ መልስ እንደሰጠን አስተውለን ይሆናል። (ነህ. 2:1-6) ‘በጽናት ስንጸልይ’ እና ይሖዋ ላቀረብነው ልመና መልስ እንደሰጠን ስንመለከት  ለእሱ ያለን ፍቅር ይጨምራል፤ ይህ ደግሞ ወደፊት የሚያጋጥመንን የእምነት ፈተና ለመወጣት አምላክ እንደሚረዳን እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል።—ሮም 12:12

17. ይሖዋን የምንወደው ከሆነ ለስብሰባ ምን ዓይነት አመለካከት ይኖረናል?

17 በጉባኤ፣ በልዩ፣ በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የመገኘት ልማድ በማዳበር። (ዕብ. 10:24, 25) እስራኤላውያን ስለ ይሖዋ ለመስማትና ለመማር ይሰበሰቡ ነበር፤ ይህም እሱን እንዲያከብሩትና ሕጉን እንዲታዘዙ አነሳስቷቸዋል። (ዘዳ. 31:12) አምላክን ከልባችን የምንወደው ከሆነ ፈቃዱን ማድረግ ሸክም አይሆንብንም። (1 ዮሐንስ 5:3ን አንብብ።) በመሆኑም ምንም ነገር ስብሰባን አቅልለን እንድንመለከት ሊያደርገን አይገባም። ለይሖዋ መጀመሪያ ላይ የነበረንን ፍቅር ምንም ነገር እንዲያሳጣን አንፈልግም።—ራእይ 2:4

18. ለአምላክ ያለን ፍቅር ከምሥራቹ ጋር በተያያዘ ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?

18 ‘የምሥራቹን እውነት’ በቅንዓት በማወጅ። (ገላ. 2:5) ለአምላክ ያለን ፍቅር “ስለ እውነት . . . በድል አድራጊነት” ወደ አርማጌዶን ስለሚገሰግሰውና መሲሐዊ ንጉሥ ስለሆነው ስለ ውድ ልጁ እንድናውጅ ያነሳሳናል። (መዝ. 45:4፤ ራእይ 16:14, 16) አምላክ ስላሳየን ፍቅር እንዲሁም ቃል ስለገባልን አዲስ ዓለም ለሰዎች በማሳወቅ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!—ማቴ. 28:19, 20

19. ይሖዋ መንጋውን ለመጠበቅ ሲል ያደረገውን የእረኝነት ዝግጅት ማድነቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

19 አምላክ መንጋውን ለመጠበቅ ሲል ያደረገውን የእረኝነት ዝግጅት በማድነቅ። (ሥራ 20:28) ክርስቲያን ሽማግሌዎች የይሖዋ ስጦታ ናቸው፤ ደግሞም የሚያደርጉት ነገር ሁሉ ለእኛው ጥቅም ነው። ሽማግሌዎች “ከነፋስ መከለያ፣ ከወጀብም መጠጊያ . . . በበረሓም እንደ ውሃ ምንጭ፣ በተጠማም ምድር እንደ ትልቅ ቋጥኝ ጥላ” ናቸው። (ኢሳ. 32:1, 2) ኃይለኛ ነፋስ በሚነሳበት ወይም ከባድ ዝናብ በሚጥልበት ወቅት መጠለያ ማግኘት ምንኛ የሚያስደስት ነው! የፀሐዩ ትኩሳት በሚበረታበት ጊዜ በቋጥኝ ጥላ ሥር ብንሆን አመስጋኝ እንደምንሆን ጥርጥር የለውም! እነዚህ ዘይቤያዊ አገላለጾች ሽማግሌዎች የሚሰጡን መንፈሳዊ እርዳታና ማበረታቻ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲታየን ያደርጋሉ። በመካከላችን ሆነው አመራር የሚሰጡንን መታዘዛችን ለእነዚህ ‘የወንዶች ስጦታ’ አድናቆት እንዳለን የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ ለአምላክና የጉባኤው ራስ ለሆነው ለክርስቶስ ፍቅር እንዳለን በግልጽ ያሳያል።—ኤፌ. 4:8፤ 5:23፤ ዕብ. 13:17

ይሖዋ ለመንጋው ከልባቸው የሚያስቡ እረኞችን ሾሟል (አንቀጽ 19ን ተመልከት)

ለአምላክ ያላችሁ ፍቅር እያደገ ይሂድ

20. አምላክን የምትወደው ከሆነ በያዕቆብ 1:22-25 መሠረት ምን ታደርጋለህ?

20 ከይሖዋ ጋር ያለህ ወዳጅነት በፍቅር ላይ የተመሠረተ ከሆነ ‘ሰሚ ብቻ ሳይሆን ቃሉን የምታደርግ ትሆናለህ።’ (ያዕቆብ 1:22-25ን አንብብ።) ‘ቃሉን የሚያደርግ’ አንድ ሰው እምነት ስለሚኖረው በስብከቱ ሥራ በቅንዓት እንደ መካፈልና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ እንደ ማድረግ ያሉ መልካም ሥራዎችን ያከናውናል። ይሖዋን ከልብ ከወደድከው እሱ ከአንተ የሚጠብቅብህን ነገሮች በሙሉ የሚያካትተውን “ፍጹም ሕግ” ትታዘዛለህ።—መዝ. 19:7-11

21. የምናቀርበው ልባዊ ጸሎት ከምን ጋር ሊመሳሰል ይችላል?

21 ለይሖዋ አምላክ ያለህ ፍቅር አዘውትረህ ልባዊ ጸሎት እንድታቀርብ ይገፋፋሃል። በቤተ መቅደሱ ውስጥ በየዕለቱ ይቀርብ የነበረውን ዕጣን በማሰብ ሳይሆን አይቀርም መዝሙራዊው ዳዊት ለይሖዋ እንዲህ ሲል ዘምሯል፦ “ጸሎቴ በፊትህ እንደ ዕጣን ትቈጠርልኝ፤ እጄን ማንሣቴም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ትሁን።” (መዝ. 141:2፤ ዘፀ. 30:7, 8) ትሕትና በሚንጸባረቅበት መንገድ የምናቀርበው ልመና፣ አጥብቀን የምናቀርበው ምልጃ እንዲሁም ከልባችን ተነሳስተን የምናቀርበው ውዳሴና ምስጋና ግሩም መዓዛ እንዳለው ዕጣን በአምላክ ፊት ተቀባይነት እንዲኖረው ምኞታችን ነው።—ራእይ 5:8

22. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የምንመለከተው ስለ ምን ዓይነት ፍቅር ነው?

22 ኢየሱስ አምላክን ብቻ ሳይሆን ባልንጀራችንንም መውደድ እንዳለብን ተናግሯል። (ማቴ. 22:37-39) ለይሖዋና ለመሠረታዊ ሥርዓቶቹ ያለን ፍቅር ከሌሎች ሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረንና ባልንጀራችንን እንድንወድ የሚረዱን እንዴት እንደሆነ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።