ትዳሩ በፍቺ የፈረሰ የምታውቀው ሰው ሊኖር ይችላል። በዛሬው ጊዜ ፍቺ በጣም የተለመደ ስለሆነ ምናልባትም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የገጠማቸው ብዙ ሰዎችን ታውቅ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በፖላንድ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው ከሦስት እስከ ስድስት ዓመታት በትዳር የኖሩ 30 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሰዎች የመፋታት አጋጣሚያቸው ከፍተኛ ነው፤ ደግሞም ፍቺ በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ ብቻ የሚያጋጥም አይደለም።

እንዲያውም የስፔን የቤተሰብ መምሪያ ተቋም “በአውሮፓ ትዳር ከሚመሠርቱ ሰዎች መካከል ግማሾቹ እንደሚፋቱ አኃዛዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ” በማለት ሪፖርት አድርጓል። በሌሎች የበለጸጉ አገሮችም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

ግራ የሚያጋቡ ስሜቶች ውርጅብኝ

ከዚህ የተለመደ ሁኔታ ጋር ተያይዘው የሚመጡት ነገሮች ምንድን ናቸው? በምሥራቅ አውሮፓ ያሉ ተሞክሮ ያካበቱ የትዳር አማካሪ የሚከተለውን ታዝበዋል፦ “በባለትዳሮቹ መካከል ያለው ዝምድና የሚፈርሰውና ይህን ተከትሎ የሚመጣው የስሜት ቀውስ የሚያጋጥመው ፍቺው በይፋ ከመፈጸሙ በፊት ጭምር ነው።” አክለውም፣ ብዙውን ጊዜ ፍቺን ተከትለው “እንደ ንዴት፣ ጸጸት፣ ብስጭት፣ ተስፋ መቁረጥና ኃፍረት ያሉ ከባድ ስሜቶች” እንደሚመጡ ገልጸዋል። ይህ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ራስን የማጥፋት ሐሳብ እንዲመጣባቸው ያደርጋል። “ፍቺው በፍርድ ቤት ሲፈጸም ቀጣዩ ምዕራፍ ይጀምራል። ትዳሩ የፈረሰው ግለሰብ የባዶነትና የባይተዋርነት ስሜት ሊቆጣጠረው እንዲሁም ‘አሁን ማን ነኝ ማለት ነው? መኖሬስ ምን ትርጉም አለው?’ ብሎ ሊያስብ ይችላል።”

ኤቫ ከጥቂት ዓመታት በፊት ምን ተሰምቷት እንደነበረ አስታውሳ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ፍቺው በፍርድ ቤት ከተፈጸመ በኋላ ጎረቤቶቼና የሥራ ባልደረቦቼ መጠቋቆሚያ ያደርጉኛል ብዬ ስላሰብኩ በከፍተኛ የኃፍረት ስሜት ተዋጥኩ። በጣም ተናድጄ ነበር። ከሁለት ትናንሽ ልጆቼ ጋር ብቻዬን ስለቀረሁ እነሱን እንደ እናትም እንደ አባትም ሆኜ ማሳደግ ነበረብኝ።” * ለ12 ዓመታት የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለገለ አደም የተባለ አንድ ተወዳጅ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ለራሴ የነበረኝን አክብሮት አጣሁ፤ በዚህም የተነሳ አንዳንድ ጊዜ በጣም የምናደድ ከመሆኑም ሌላ ከሰው ሁሉ ብርቅ ደስ ይለኛል።”

ስሜታቸውን ለማረጋጋት የሚያደርጉት ትግል

አንዳንዶች የወደፊት ሕይወታቸው በጣም ስለሚያስጨንቃቸው ፍቺው ከተፈጸመ ከዓመታት በኋላም እንኳ ስሜታቸው የተረጋጋ እንዲሆን ማድረግ ያታግላቸዋል። ሌሎች ለእነሱ ምንም ደንታ እንደሌላቸው ያስቡ ይሆናል። ስለዚህ ጉዳይ መጣጥፍ የምታዘጋጅ አንዲት ሴት እንደተናገረችው ፍቺ የፈጸሙ ሰዎች “ልማዶቻቸውን መለወጥና ችግሮቻቸውን እንዴት ለብቻቸው መጋፈጥ እንዳለባቸው መማር” ይኖርባቸዋል።

ስታኒስዋፍ የተባለ ወንድም እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “በተፋታን ጊዜ የቀድሞ ባለቤቴ ሁለቱን ትናንሽ ሴት ልጆቼን እንዳላይ ከለከለችኝ። ይህም ለእኔ የሚያስብልኝ ሰው እንደሌለ፣ ሌላው ቀርቶ ይሖዋም ጭምር እንደተወኝ እንዲሰማኝ አደረገ። መኖር አስጠላኝ። ከጊዜ በኋላ ግን አስተሳሰቤ በጣም ስህተት እንደነበረ ተገነዘብኩ።” በፍቺ የተለያየች ቫንዳ የምትባል አንዲት እህት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ስታስብ ስጋት ገብቷት ነበር፤ እንዲህ  ብላለች፦ “ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የእምነት አጋሮቼን ጨምሮ ሁሉም ሰዎች እኔንና ልጆቼን ዞር ብለው እንደማያዩን ተሰምቶኝ ነበር። ይሁን እንጂ ልጆቼ የይሖዋ አምላኪዎች እንዲሆኑ አድርጌ ለማሳደግ ስጣጣር ወንድሞች ከጎናችን በመሆን ምን ያህል እንደረዱን ተመልክቻለሁ።”

እንደዚህ ካሉት አስተያየቶች መረዳት እንደሚቻለው አንዳንዶች ፍቺ ከፈጸሙ በኋላ አሉታዊ በሆኑ ስሜቶች ይዋጣሉ። ምንም ዋጋ እንደሌላቸውና ትኩረት ማግኘት የማይገባቸው እንደሆኑ አድርገው በማሰብ ስለ ራሳቸው መጥፎ ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል። ከዚህም ሌላ በዙሪያቸው ያሉትን ሊተቹ ይችላሉ። በዚህም የተነሳ ጉባኤው ፍቅር እንደሌለውና በችግራቸው እንዳልደረሰላቸው ማሰብ ይጀምሩ ይሆናል። ሆኖም የስታኒስዋፍ እና የቫንዳ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ትዳራቸው በፍቺ የፈረሰ ወንድሞችና እህቶች የእምነት አጋሮቻቸው በእርግጥ እንደሚያስቡላቸው መገንዘባቸው አይቀርም። እንዲያውም የእምነት ባልንጀሮቻቸው በዚህ ወቅት ልዩ እንክብካቤ ያደርጉላቸዋል፤ እርግጥ ነው፣ መጀመሪያ ላይ ይህን ማስተዋል ሊከብዳቸው ይችላል።

በብቸኝነት ሲዋጡ እንዲሁም ተፈላጊ እንዳልሆኑ ሲሰማቸው

ምንም ያህል ጥረት ብናደርግም እንኳ ትዳራቸው በፍቺ የፈረሰ የእምነት አጋሮቻችን አልፎ አልፎ በብቸኝነት ስሜት ሊዋጡ እንደሚችሉ ማስታወስ ይገባናል። በተለይ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የደረሰባቸው እህቶች የሚያስብላቸው ሰው እንደሌለ ሊሰማቸው ይችላል። አሊፂያ እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “ከተፋታሁ ስምንት ዓመታት አልፈዋል። ሆኖም አሁንም ድረስ የበታችነት ስሜት የሚሰማኝ ጊዜ አለ። እንዲህ ባሉ ወቅቶች ብቻዬን መሆን እመርጣለሁ፤ ከዚያም ማልቀስና መተከዝ እጀምራለሁ።”

ትዳሩ በፍቺ የፈረሰ አንድ ሰው እንዲህ ያሉ ስሜቶች ቢያጋጥሙት የሚያስገርም አይደለም፤ ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ራስን ማግለል ተገቢ እንዳልሆነ ይመክራል። ይህን ምክር የሚቃረን አካሄድ መከተል ‘መልካሙን ጥበብ ሁሉ’ ወደ መተው ያመራል። (ምሳሌ 18:1 የ1954 ትርጉም) ይሁንና በፍቺ የተነሳ ብቸኝነት የተሰማው ግለሰብ፣ ተቃራኒ ፆታ ካለው ሰው በተደጋጋሚ ምክር ወይም ማጽናኛ ለማግኘት መሞከር የጥበብ አካሄድ እንዳልሆነ ማስተዋል ይኖርበታል። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ተገቢ ያልሆነ የፍቅር ስሜት እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል።

ትዳራቸው በፍቺ የፈረሰ የእምነት አጋሮቻችን የተለያዩ አሉታዊ ስሜቶች ይፈራረቁባቸው ይሆናል፤ ለምሳሌ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሲያስቡ ስጋት ሊያድርባቸው፣ የብቸኝነት ስሜት ሊያጠቃቸው ወይም እንደተተዉ ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። እንዲህ ዓይነቶቹ ስሜቶች ሊያጋጥሙ የሚችሉ ብሎም ለመቋቋም የሚያስቸግሩ እንደሆኑ መረዳት እንዲሁም እንደዚህ ያሉ ወንድሞችና እህቶችን በታማኝነት በመደገፍ ረገድ ይሖዋን መምሰል ይኖርብናል። (መዝ. 55:22፤ 1 ጴጥ. 5:6, 7) ለእነሱ የምንሰጠውን ማንኛውም እርዳታ ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በእርግጥም ትዳራቸው በፍቺ የፈረሰ የእምነት አጋሮቻችን በጉባኤው ውስጥ ካሉ እውነተኛ ወዳጆቻቸው ድጋፍ ማግኘት ይችላሉ።—ምሳሌ 17:17፤ 18:24

^ አን.6 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።