በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ግንቦት 2014

 ከታሪክ ማኅደራችን

‘ገና መሠራት ያለበት ብዙ የመከር ሥራ አለ’

‘ገና መሠራት ያለበት ብዙ የመከር ሥራ አለ’

ጆርጅ ያንግ መጋቢት 1923 ሪዮ ዴ ጄኔሮ ደረሰ

ጊዜው 1923 ነው። በሳኦ ፓውሎ፣ የድራማና የሙዚቃ አዳራሹ በሕዝብ ተጨናንቋል! ጆርጅ ያንግ ንግግሩን በሚንቆረቆር ድምፅ ሲያቀርብ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ንግግሩን ሲያቀርብ እያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር ወደ ፖርቱጋልኛ እየተተረጎመ ነው። በቦታው የተገኙት 585 ተሰብሳቢዎች በሙሉ በትኩረት ያዳምጣሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ስክሪኑ ላይ በፖርቱጋልኛ ይታያሉ። በፕሮግራሙ መደምደሚያ ላይ ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም! የተሰኘው ቡክሌት መቶ ቅጂዎች በእንግሊዝኛ፣ በጀርመንኛ፣ በጣሊያንኛና በፖርቱጋልኛ ለተሰብሳቢዎቹ ታደሉ። ንግግሩ ጥሩ ውጤት አስገኝቷል! ይህን ንግግር በተመለከተ ወሬው ስለተዛመተ ከሁለት ቀን በኋላ ሌላ ንግግር በሚቀርብበት ጊዜ አዳራሹ ጢም ብሎ ሞልቶ ነበር። ይሁን እንጂ ለዚህ ሁሉ መነሻው ምን ነበር?

በ1867 ሳራ ቤሎና ፈርግሰን የተባለች ሴት ከቤተሰቧ ጋር ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ብራዚል ሄደች። በ1899 ሳራ ታናሽ ወንድሟ ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ብራዚል ያመጣቸውን አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ካነበበች በኋላ እውነትን እንዳገኘች ተገነዘበች። ሳራ እንደ እነዚህ ያሉ ጽሑፎች ለማንበብ ስለጓጓች በእንግሊዝኛ ቋንቋ መጠበቂያ ግንብ እንዲደርሳት ኮንትራት ገባች። በመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት እጅግ ስለተደሰተች ለወንድም ቻርልስ ቴዝ ራስል “አንድ ሰው ምንም ያህል ሩቅ ቦታ ቢኖር [ምሥራቹ] ሊደርሰው እንደሚችል እኔ ሕያው ማስረጃ ነኝ” በማለት ጽፋለት ነበር።

ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም! (በፖርቱጋልኛ)

ሳራ ፈርግሰን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ለማካፈል አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ አድርጋለች፤ ያም ቢሆን እሷንና ቤተሰቧን ጨምሮ በብራዚል ያሉ ቅን ሰዎችን ሁሉ ማን ይበልጥ ሊረዳቸው እንደሚችል ዘወትር ያሳስባት ነበር። በ1912 በፖርቱጋልኛ የተተረጎመውን ሙታን የት ናቸው? የሚለውን ትራክት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ቅጂዎች ወደ ሳኦ ፓውሎ የሚያመጣ ሰው እንዳለ ከብሩክሊን ቤቴል ተነገራት። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በቅርቡ ወደ ሰማይ እንወሰዳለን ብለው እንደሚጠብቁ ባነበበች ቁጥር እንደምትገረም በ1915 ገልጻ ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ አመለካከቷን ስትገልጽ እንዲህ በማለት ጽፋ ነበር፦ “በብራዚልና በመላው ደቡብ አሜሪካ ያሉት ሰዎችስ እንዴት ሊሆኑ  ነው? ወንድሜ ሆይ፣ . . . ደቡብ አሜሪካ በጣም ሰፊ የምድር ክፍል መሆኑን ስታስብ መሠራት ያለበት ብዙ የመከር ሥራ እንዳለ መገንዘብህ አይቀርም።” በእርግጥም ገና የሚሠራ ብዙ የመከር ሥራ ነበር!

በ1920 አካባቢ ስምንት ወጣት ብራዚላውያን መርከበኞች፣ የጦር መርከባቸው በምትጠገንበት ወቅት በኒው ዮርክ ከተማ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተው ነበር። ወደ ሪዮ ዴ ጄኔሮ ሲመለሱ በቅርቡ ያወቁትን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ለሌሎች አካፈሉ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ይኸውም መጋቢት 1923 ጆርጅ ያንግ የተባለው ፒልግሪም ወይም ተጓዥ የበላይ ተመልካች ወደ ሪዮ ዴ ጄኔሮ ሄደ፤ በዚያም ፍላጎት ያላቸው ሰዎችን አገኘ። በርካታ ጽሑፎች ወደ ፖርቱጋልኛ እንዲተረጎሙ ዝግጅት አደረገ። ብዙም ሳይቆይ ወንድም ያንግ በወቅቱ 600,000 ነዋሪዎች ወደነበሯት ሳኦ ፓውሎ ከተማ ሄደ። እዚያም በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው ንግግር ከመስጠቱም ሌላ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተሰኘውን ቡክሌት አደለ። “ብቻዬን በመሆኔ ፕሮግራሙን ለማስተዋወቅ በጋዜጦች ከመጠቀም ሌላ አማራጭ አልነበረኝም” በማለት በሪፖርቱ ላይ ጽፏል። እነዚህ ንግግሮች “በብራዚል በነበረው አይ ቢ ኤስ ኤ ስም የተዋወቁትና ለሕዝብ የቀረቡት የመጀመሪያዎቹ የሕዝብ ንግግሮች” መሆናቸውን አክሎ ጽፏል። *

ወንድም ያንግ ንግግር በሚያቀርብበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ስክሪኑ ላይ ይታዩ ነበር

በታኅሣሥ 15, 1923 መጠበቂያ ግንብ ላይ ስለ ብራዚል የወጣው ሪፖርት እንዲህ ይላል፦ “ሥራው የተጀመረው ሰኔ 1 ከመሆኑና በዚያ ወቅት ምንም ጽሑፍ ካለመኖሩ አንጻር ጌታ ሥራውን የባረከበት መንገድ አስደናቂ ነው።” ሪፖርቱ አክሎም ወንድም ያንግ በሳኦ ፓውሎ የሰጣቸውን 2 ንግግሮች ጨምሮ ከሰኔ 1 እስከ መስከረም 30 ባሉት ጊዜያት ውስጥ 21 የሕዝብ ንግግሮችን እንዳቀረበና በጠቅላላው 3,600 ተሰብሳቢዎች እንደተገኙ ገልጿል። በሪዮ ዴ ጄኔሮ የመንግሥቱ መልእክት ቀስ በቀስ እየተስፋፋ ነበር። በፖርቱጋልኛ የተዘጋጁ ከ7,000 በላይ የሚሆኑ ጽሑፎቻችን በጥቂት ወራት ውስጥ ብቻ ለሕዝብ ተሰራጭተዋል! ከዚህም በላይ መጠበቂያ ግንብ ከኅዳር-ታኅሣሥ 1923 እትም አንስቶ በፖርቱጋልኛ ቋንቋ መውጣት ጀመረ።

ሳራ ቤሎና ፈርግሰን፣ በብራዚል የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ኮንትራት የገባች የመጀመሪያዋ ሰው

ጆርጅ ያንግ፣ ሳራ ፈርግሰንን ሄዶ ጎበኛት፤ መጠበቂያ ግንብ በወቅቱ የተፈጸመውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “እህት እሱ ወደነበረበት ክፍል ስትገባ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ምንም አልተናገረችም። በመጨረሻም የወንድም ያንግን እጅ ይዛ ፊቱን ትኩር ብላ እየተመለከተች ‘እውነት እያየሁት ያለሁት ፒልግሪም ነው?’ አለችው።” ብዙም ሳይቆይ እሷና አንዳንድ ልጆቿ ተጠመቁ። እህት ሳራ ይህን አጋጣሚ ለማግኘት 25 ዓመታት ጠብቃለች! የነሐሴ 1, 1924 መጠበቂያ ግንብ በብራዚል 50 ሰዎች እንደተጠመቁና ከእነዚህም አብዛኞቹ የሪዮ ዴ ጄኔሮ ነዋሪዎች መሆናቸውን ተናግሯል።

ይህ ከሆነ ወደ 90 የሚጠጉ ዓመታት አልፈዋል፤ በአሁኑ ጊዜ ግን “በብራዚልና በመላው ደቡብ አሜሪካ ያሉት ሰዎችስ እንዴት ሊሆኑ ነው?” ብለን መጠየቅ አያስፈልገንም። በብራዚል ከ760,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን እየሰበኩ ናቸው። እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ በመላው ደቡብ አሜሪካ የመንግሥቱ መልእክት በስፓንኛ፣ በፖርቱጋልኛና በሌሎችም በርካታ የአካባቢው ቋንቋዎች እየተሰበከ ነው። በ1915 ሳራ ፈርግሰን “ገና መሠራት ያለበት ብዙ የመከር ሥራ እንዳለ” መናገሯ ትክክል ነበር።—በብራዚል ካለው የታሪክ ማኅደራችን

^ አን.6 አይ ቢ ኤስ ኤ የሚለው ምህጻረ ቃል ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበርን ያመለክታል።