“የይሖዋ ዓይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉ።”—1 ጴጥ. 3:12

1. ከሃዲ በሆነው የእስራኤል ብሔር ምትክ የይሖዋን ስም እንዲሸከም የተመረጠው ድርጅት የትኛው ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤን ያቋቋመው እንዲሁም በዘመናችን እውነተኛውን አምልኮ እንደገና ያደራጀው ይሖዋ ነው። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ከሃዲ በሆነው የእስራኤል ብሔር ምትክ የይሖዋን ስም እንዲሸከም የተመረጠው፣ የክርስቶስን የመጀመሪያ ተከታዮች ያቀፈው ድርጅት ነው። የአምላክን ሞገስ ያገኘው ይህ አዲስ ድርጅት ኢየሩሳሌም በ70 ዓ.ም. ስትጠፋ መትረፍ ችሏል። (ሉቃስ 21:20, 21) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተፈጸሙት እነዚህ ሁኔታዎች በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች የሚያጋጥሟቸውን ነገሮች የሚጠቁሙ ናቸው። የሰይጣን ሥርዓት በቅርቡ ይጠፋል፤ የአምላክ ድርጅት ግን በመጨረሻዎቹ ቀኖች ከሚመጣው ጥፋት ይተርፋል። (2 ጢሞ. 3:1) ይህ እንደሚፈጸም እርግጠኞች የምንሆነው ለምንድን ነው?

2. ኢየሱስ ስለ ‘ታላቁ መከራ’ ምን ብሏል? ታላቁ መከራ የሚጀምረውስ መቼ ነው?

2 ኢየሱስ በማይታይ ሁኔታ የሚገኝበትን ጊዜና የዚህን ሥርዓት መደምደሚያ አስመልክቶ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን ታላቅ መከራ ይከሰታል።” (ማቴ. 24:3, 21) ይሖዋ በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ የምታመለክተውን ‘ታላቂቱን ባቢሎን’ በፖለቲካ ኃይሎች በመጠቀም  ሲያጠፋት ከዚህ በፊት ሆኖ የማያውቀው ይህ ታላቅ መከራ ይጀምራል። (ራእይ 17:3-5, 16) ከዚያ በኋላስ ምን ይሆናል?

ሰይጣን የሚወስደው እርምጃ አርማጌዶን እንዲጀመር ያደርጋል

3. የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላ በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ምን ዓይነት ጥቃት ለመሰንዘር ሙከራ ይደረጋል?

3 የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላ ሰይጣንና በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም በይሖዋ አገልጋዮች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በማጎግ ምድር የሚገኘውን ጎግን’ በተመለከተ የሚከተለውን ትንቢት ይናገራል፦ “አንተና ወታደሮችህ ሁሉ፣ ከአንተም ጋር ያሉት ብዙ ሕዝቦች እንደ ማዕበል ትወጣላችሁ፤ ምድርን እንደሚሸፍን ደመናም ትሆናላችሁ።” የይሖዋ ምሥክሮች የጦር ሰራዊት ስለሌላቸውና በምድር ላይ ካሉት ሕዝቦች ሁሉ ሰላማዊ ስለሆኑ እነሱን ማጥፋት ቀላል ሊመስል ይችላል። ይሁንና በእነሱ ላይ ጥቃት መሰንዘር እንዴት ያለ ሞኝነት ይሆናል!—ሕዝ. 38:1, 2, 9-12

4, 5. ሰይጣን የአምላክን አገልጋዮች ለማጥፋት ሙከራ ሲያደርግ ይሖዋ ምን እርምጃ ይወስዳል?

4 ሰይጣን የአምላክን ሕዝቦች ለማጥፋት ሲሞክር ይሖዋ ምን ያደርጋል? የአጽናፈ ዓለሙ የበላይ የሆነው ይሖዋ፣ ሕዝቦቹን ለመጠበቅ ሲል እርምጃ ይወስዳል። ይሖዋ በአገልጋዮቹ ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት በእሱ ላይ እንደተቃጣ ጥቃት አድርጎ ይመለከተዋል። (ዘካርያስ 2:8ን አንብብ።) በመሆኑም በሰማይ ያለው አባታችን እኛን ለማዳን ፈጣን እርምጃ ይወስዳል። (መዝ. 34:7፤ 103:20, 21) ይሖዋ ሕዝቦቹን ለማዳን የሚወስደው ይህ እርምጃ የሰይጣን ዓለም በአርማጌዶን ይኸውም “ሁሉን ቻይ [በሆነው] አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን” ሲጠፋ ይደመደማል።—ራእይ 16:14, 16

5 አርማጌዶንን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ትንቢት ይዟል፦ “‘እግዚአብሔር ከሕዝቦች ጋር ይፋረዳልና፣ ታላቅ ጩኸት እስከ ምድር ዳርቻ ያስተጋባል፤ በሰው ሁሉ ላይ ፍርድን ያመጣል፤ ክፉዎችንም ለሰይፍ ይዳርጋል’ ይላል እግዚአብሔር። የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ፤ ጥፋት፣ ከአገር ወደ አገር እየተዛመተ መጥቶአል፤ ብርቱ ዐውሎ ነፋስ፣ ከምድር ዳርቻ ተነሥቶአል። በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር የተገደሉት ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር በሁሉ ስፍራ ተረፍርፈው ይታያሉ፤ እንደ ጕድፍ በምድር ላይ ይጣላሉ እንጂ፣ አይለቀስላቸውም፤ ሬሳቸውም አይሰበሰብም፤ አይቀበርምም።’” (ኤር. 25:31-33) ይህ ክፉ ሥርዓት በአርማጌዶን ይጠፋል። የሰይጣን ዓለም ሲደመሰስ የይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ግን ይተርፋል።

በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ድርጅት እድገት እያደረገ ያለው ለምንድን ነው?

6, 7. (ሀ) ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባላት የሚሰበሰቡት እንዴት ነው? (ለ) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ምን ዓይነት እድገት አግኝተናል?

6 በዛሬው ጊዜ ያለው የአምላክ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ያልጠፋውና እድገት እያደረገ ያለው በድርጅቱ ውስጥ የታቀፉት ሰዎች የእሱ ሞገስ ስላላቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የይሖዋ ዓይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉ፤ ጆሮዎቹም ምልጃቸውን ለመስማት የተከፈቱ ናቸው” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (1 ጴጥ. 3:12) እዚህ ላይ ጻድቃን ከተባሉት መካከል “ታላቁን መከራ አልፈው የመጡ” “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ይገኙበታል። (ራእይ 7:9, 14) ከጥፋቱ የሚተርፉት እነዚህ ሰዎች “ሕዝብ” ብቻ ሳይሆን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ይሆናሉ። “ታላቁን መከራ አልፈው” ከሚመጡት ከእነዚህ ሰዎች አንዱ እንደምትሆን ይሰማሃል?

7 እጅግ ብዙ ሕዝብ የተባሉት ሰዎች የሚሰበሰቡት እንዴት ነው? እነዚህ ሰዎች የሚሰበሰቡት፣ ኢየሱስ የመገኘቱ ምልክት አንዱ ገጽታ እንደሆነ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ በመሆኑ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴ. 24:14) በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ የአምላክ ድርጅት የሚያከናውነው ዋነኛ ሥራ ይህ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ በሚያካሂዱት የስብከትና የማስተማር ሥራ አማካኝነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክን “በመንፈስና በእውነት” ማምለክ የሚችሉት እንዴት  እንደሆነ ተምረዋል። (ዮሐ. 4:23, 24) ለምሳሌ ያህል፣ ከ2003 እስከ 2012 ባሉት አሥር የአገልግሎት ዓመታት ውስጥ ከ2,707,000 በላይ ሰዎች ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን ለማሳየት ተጠምቀዋል። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከ7,900,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ያሉ ሲሆን ሌሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በተለይ በየዓመቱ በሚከበረው የመታሰቢያው በዓል ላይ ከእነዚህ ክርስቲያኖች ጋር ይሰበሰባሉ። እርግጥ ነው፣ ቁጥራችን በመጨመሩ አንኩራራም፤ ምክንያቱም “የሚያሳድገው አምላክ” ነው። (1 ቆሮ. 3:5-7) ያም ቢሆን የእጅግ ብዙ ሕዝብ ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረና ታላቅ እየሆነ እንዳለ በግልጽ ማየት ይቻላል።

8. በዘመናችን ያለው የይሖዋ ድርጅት ከፍተኛ እድገት ያደረገው ለምንድን ነው?

8 ይሖዋ፣ ምሥክሮቹን እየደገፋቸው በመሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ቁጥር ከፍተኛ እድገት አሳይቷል። (ኢሳይያስ 43:10-12ን አንብብ።) እንዲህ ዓይነት እድገት እንደሚኖር የሚከተለው ትንቢት ይጠቁማል፦ “ታናሽ የሆነው ሺህ፣ ከሁሉም የመጨረሻው ታናሽ ኀያል መንግሥት ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ጊዜውም ሲደርስ ይህን በፍጥነት አደርጋለሁ።” (ኢሳ. 60:22) በአንድ ወቅት የቅቡዓን ቀሪዎች ቁጥር ‘ትንሽ’ የነበረ ቢሆንም ሌሎች መንፈሳዊ እስራኤላውያን ወደ አምላክ ድርጅት በመምጣታቸው ቁጥራቸው ሊጨምር ችሏል። (ገላ. 6:16) ባለፉት ዓመታት ይሖዋ ሕዝቦቹን ስለባረካቸው እጅግ ብዙ ሕዝብ እየተሰበሰበ ነው፤ ይህም የይሖዋ ሕዝቦች ቁጥር እያደገ መሄዱን እንዲቀጥል አድርጓል።

ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀው ምንድን ነው?

9. በአምላክ ቃል ውስጥ የተገለጸውን አስደሳች የወደፊት ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

9 ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆንን የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት በአምላክ ቃል ውስጥ የተገለጸውን አስደሳች የወደፊት ሕይወት ማግኘት እንችላለን። ሆኖም ይህን ለማግኘት ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቃቸውን ነገሮች ማሟላት ይኖርብናል። (ኢሳ. 48:17, 18) እስቲ በሙሴ ሕግ ሥር ስለነበሩት እስራኤላውያን መለስ ብለን እንመልከት። ሕጉ የተሰጠበት አንዱ ዓላማ ከፆታ ሥነ ምግባር፣ ከንግድ ጉዳዮች፣ ከልጆች አስተዳደግ፣ ሌሎችን በአግባቡ ከመያዝ እና እነዚህን ከመሳሰሉት ሌሎች ነገሮች ጋር በተያያዘ ጠቃሚ የሆኑ መመሪያዎች እንዲኖሩ በማድረግ ለእስራኤላውያን ጥበቃ እንዲሆንላቸው ነበር። (ዘፀ. 20:14፤ ዘሌ. 19:18, 35-37፤ ዘዳ. 6:6-9) እኛም ከአምላክ መመሪያዎች ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለሳችን ይጠቅመናል፤ ደግሞም የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ከባድ እንደሆነ አይሰማንም። (1 ዮሐንስ 5:3ን አንብብ።) እንዲያውም የአምላክ ሕግ ለእስራኤላውያን ጥበቃ እንዳስገኘላቸው ሁሉ እኛም ከይሖዋ አምላክ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለሳችን ጥበቃ ያስገኝልናል፤ ከዚህም ባሻገር ምንጊዜም “በእምነት ጤናሞች” እንድንሆን ይረዳናል።—ቲቶ 1:13

10. መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እና በየሳምንቱ የቤተሰብ አምልኮ ለማድረግ ጊዜ መመደብ ያለብን ለምንድን ነው?

10 የይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል በተለያዩ መስኮች ወደፊት እየተጓዘ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስላለው እውነት ያለን ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ግልጽ እየሆነ ነው። “የጻድቃን መንገድ ሙሉ ቀን እስኪሆን ድረስ፣ ብርሃኑ እየጐላ እንደሚሄድ የማለዳ ውጋጋን” በመሆኑ ይህ የሚጠበቅ ነው። (ምሳሌ 4:18) ሆኖም ራሳችንን እንደሚከተለው በማለት መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘ስለ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶች ባለን ግንዛቤ ረገድ በቅርቡ የተደረጉትን ማስተካከያዎች አውቃቸዋለሁ? መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ የማንበብ ልማድ አለኝ? ጽሑፎቻችንን በጉጉት አነብባለሁ? ከቤተሰቤ ጋር በየሳምንቱ የቤተሰብ አምልኮ አደርጋለሁ?’ ብዙዎቻችን እነዚህን ነገሮች ማድረግ ያን ያህል ከባድ እንዳልሆነ እናውቃለን። ሆኖም እነዚህን ነገሮች ለማከናወን ጊዜ መመደብ ያስፈልገናል። በተለይ ታላቁ መከራ በጣም በቀረበበት በአሁኑ ጊዜ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት መቅሰማችን፣ ያወቅነውን ነገር በተግባር ማዋላችን እንዲሁም መንፈሳዊ እድገት ማድረጋችን ወሳኝ ነገር ነው!

11. በጥንት ዘመን የነበሩት በዓላት እና በአሁኑ ጊዜ የምናደርጋቸው ስብሰባዎች ጠቃሚ የሆኑት በየትኞቹ መንገዶች ነው?

 11 የይሖዋ ድርጅት ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ለሰጠው ማስጠንቀቂያ ትኩረት እንድንሰጥ የሚሳስበን ለእኛው ጥቅም ሲል ነው፦ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት አንድ ላይ መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ እርስ በርስ እንበረታታ።” (ዕብ. 10:24, 25) እስራኤላውያን የሚያከብሯቸው ዓመታዊ በዓላትም ሆኑ ለአምልኮ የሚያደርጓቸው ሌሎች ስብሰባዎች በመንፈሳዊ ያጠናክሯቸው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በነህምያ ዘመን እንደተከበረው ልዩ የዳስ በዓል ያሉት ወቅቶች አስደሳች ነበሩ። (ዘፀ. 23:15, 16፤ ነህ. 8:9-18) እኛም ከጉባኤና ከትላልቅ ስብሰባዎች ተመሳሳይ ጥቅም እናገኛለን። እንግዲያው ደስተኞችና በመንፈሳዊ ጤናሞች እንድንሆን ተብለው ከሚደረጉት ከእነዚህ ዝግጅቶች የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ጥረት እናድርግ።—ቲቶ 2:2

12. የመንግሥቱን ስብከት ሥራ እንዴት ልንመለከተው ይገባል?

12 የአምላክ ድርጅት አባላት በመሆናችን “የአምላክን ምሥራች በማወጁ . . . ቅዱስ ሥራ” መካፈል የሚያስገኘውን ደስታ እያጣጣምን ነው። (ሮም 15:16) በዚህ “ቅዱስ ሥራ” መካፈላችን “ቅዱስ አምላክ” ከሆነው ከይሖዋ ጋር ‘አብረን ለመሥራት’ አስችሎናል። (1 ቆሮ. 3:9፤ 1 ጴጥ. 1:15) ምሥራቹን መስበካችን የይሖዋ ቅዱስ ስም እንዲከበር አስተዋጽኦ ያደርጋል። ደግሞም “ደስተኛ [የሆነውን] አምላክ ክብራማ ምሥራች” መስበክ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ታላቅ መብት ነው!—1 ጢሞ. 1:11

13. በመንፈሳዊ ጤናሞች መሆናችንና በሕይወት መኖራችን የተመካው በምን ላይ ነው?

13 አምላክ ከእሱ ጋር በመጣበቅና ድርጅቱ የሚያከናውናቸውን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በመደገፍ መንፈሳዊ ጤንነታችንን እንድንጠብቅ ይፈልጋል። ሙሴ እስራኤላውያንን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና ርግማንን በፊትህ እንዳስቀመጥሁ ዛሬ ሰማይንና ምድርን ምስክር አድርጌ እጠራብሃለሁ። እንግዲህ አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ፤ ይኸውም አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትወድ፣ ቃሉን እንድታደምጥና ከእርሱ ጋር እንድትጣበቅ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ሕይወትህ ነው፣ ለአባቶችህ፣ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ሊሰጣቸው በማለላቸው ምድር ረጅም ዕድሜ ይሰጥሃል።” (ዘዳ. 30:19, 20) ሕይወት ማግኘታችን የአምላክን ፈቃድ በማድረጋችን፣ እሱን በመውደዳችን፣ ቃሉን አዳምጠን በመታዘዛችንና ከእሱ ጋር በመጣበቃችን ላይ የተመካ ነው።

14. አንድ ወንድም ስለ ይሖዋ ድርጅት ምን ተሰምቶታል?

14 ምንጊዜም ከአምላክ ጋር ተጣብቆ የኖረውና ከድርጅቱ እኩል ይጓዝ የነበረው ወንድም ፕራይስ ሂዩዝ በአንድ ወቅት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከ1914 በፊት ካለው ጊዜ አንስቶ . . . ስለ ይሖዋ ዓላማዎች የሚገልጸውን እውነት በማወቄ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከምንም በላይ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነገር ከሚታየው የይሖዋ ድርጅት ጋር ተጣብቆ መኖርን ነው። ቀደም ሲል ያገኘሁት ተሞክሮ፣ በሰብዓዊ አስተሳሰብ መመካት ትልቅ ስህተት እንደሆነ አስተምሮኛል። እዚህ መደምደሚያ ላይ ከደረስኩ በኋላ፣ ምንጊዜም በዚህ ታማኝ ድርጅት ውስጥ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ። ደግሞስ የይሖዋን ሞገስና በረከት ማግኘት የሚቻልበት ምን ሌላ መንገድ አለ?”

ከአምላክ ድርጅት ጋር ወደፊት መጓዝህን ቀጥል

15. ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳቦች ጋር በተያያዘ ማስተካከያዎች ሲደረጉ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ የሚያሳይ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌ ስጥ።

15 በግለሰብ ደረጃ የይሖዋን ሞገስና በረከት ማግኘት የምንፈልግ ከሆነ ድርጅቱን መደገፍ እንዲሁም ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ባለን ግንዛቤ ላይ የሚደረጉ ማስተካከያዎችን መቀበል ይኖርብናል። እስቲ የሚከተለውን ምሳሌ እንመልከት፦ ኢየሱስ ከሞተ በኋላ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ለሕጉ ይቀኑ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ሕጉን መተው ከብዷቸው ነበር። (ሥራ 21:17-20) ይሁንና ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የጻፈው  ደብዳቤ፣ እነዚህ ክርስቲያኖች የተቀደሱት “ሕጉ በሚያዘው መሠረት [በሚቀርቡ]” መሥዋዕቶች አማካኝነት ሳይሆን “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖ በቀረበው የኢየሱስ ክርስቶስ አካል አማካኝነት” እንደሆነ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። (ዕብ. 10:5-10) አይሁዳውያን ከሆኑት ክርስቲያኖች አብዛኞቹ አመለካከታቸውን አስተካክለው በመንፈሳዊ እድገት እንዳደረጉ ጥርጥር የለውም። እኛም መጽሐፍ ቅዱስንና ጽሑፎቻችንን በትጋት ማጥናት እንዲሁም ስለ አምላክ ቃል ካለን ግንዛቤ ወይም ከስብከቱ ሥራችን ጋር በተያያዘ ማስተካከያዎች ሲደረጉ ለመቀበል ፈቃደኞች መሆን ይኖርብናል።

16. (ሀ) በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሕይወት አስደሳች እንዲሆን የሚያደርጉት የትኞቹ በረከቶች ናቸው? (ለ) አንተ በግልህ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለማግኘት የምትጓጓው ነገር ምንድን ነው?

16 ለይሖዋና ለድርጅቱ ምንጊዜም ታማኝ የሚሆኑ ሁሉ የአምላክ በረከት አይለያቸውም። ታማኝ የሆኑ ቅቡዓን በሰማይ ከክርስቶስ ጋር አብረው ወራሾች የመሆን ታላቅ መብት ያገኛሉ። (ሮም 8:16, 17) ተስፋችን በምድር ላይ መኖር ከሆነ ደግሞ በገነት ውስጥ መኖር ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን መገመት እንችላለን። በይሖዋ ድርጅት ውስጥ በመሆናችን፣ አምላክ ቃል ስለገባው አዲስ ዓለም ለሰዎች የመናገር አስደሳች መብት አግኝተናል! (2 ጴጥ. 3:13) መዝሙር 37:11 “ገሮች . . . ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” ይላል። “ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ” እንዲሁም “በእጃቸው ሥራ . . . ደስ ይላቸዋል።” (ኢሳ. 65:21, 22) ጭቈና፣ ድህነት እና ረሃብ አይኖርም። (መዝ. 72:13-16) ታላቂቱ ባቢሎን ስለምትጠፋ ከዚያ በኋላ ማንንም አታሳስትም። (ራእይ 18:8, 21) የሞቱ ሰዎች ትንሣኤ የሚያገኙ ሲሆን ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። (ኢሳ. 25:8፤ ሥራ 24:15) ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል! እንደ እነዚህ ያሉት ቅዱስ ጽሑፋዊ ተስፋዎች ሲፈጸሙ በግለሰብ ደረጃ መመልከት እንድንችል፣ መንፈሳዊ እድገት ማድረጋችንን መቀጠል እንዲሁም ከአምላክ ድርጅት ጋር ወደፊት መጓዝና ምንጊዜም ከድርጅቱ እኩል መሄድ ይኖርብናል።

በገነት ውስጥ ስትኖር በዓይነ ሕሊናህ ይታይሃል? (አንቀጽ 16ን ተመልከት)

17. ከይሖዋ አምልኮና ከድርጅቱ ጋር በተያያዘ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

17 የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በጣም እየተቃረበ በመሆኑ ምንጊዜም በእምነት ጠንካሮች መሆን እና ይሖዋ ከአምልኮ ጋር በተያያዘ ያደረጋቸውን ዝግጅቶች ከልብ ማድነቅ ይኖርብናል። መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ ዓይነት አመለካከት ነበረው፤ እንደሚከተለው በማለት ዘምሯል፦ “እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤ እርሷንም እሻለሁ፤ ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣ በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው።” (መዝ. 27:4) እንግዲያው ሁላችንም ከአምላክ ጋር ተጣብቀን እንኑር፤ ከሕዝቡ ጋር እኩል እንራመድ እንዲሁም ከይሖዋ ድርጅት ጋር ወደፊት መጓዛችንን እንቀጥል።