በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ሚያዝያ 2014

ደፋር ሁን—ይሖዋ ረዳትህ ነው!

ደፋር ሁን—ይሖዋ ረዳትህ ነው!

“በሙሉ ልብ ‘ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ . . .’ እንላለን።”—ዕብ. 13:6

1, 2. ብዙ ስደተኞች ወደ ቤተሰባቸው ሲመለሱ ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

“ውጭ አገር ሳለሁ በኃላፊነት ቦታ ላይ እሠራ ስለነበር ጥሩ ደሞዝ ነበረኝ። ይሁን እንጂ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስጀምር ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ኃላፊነት እንዳለብኝ ይኸውም የቤተሰቤን ሰብዓዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ፍላጎታቸውንም ማሟላት እንደሚጠበቅብኝ ተገነዘብኩ። በመሆኑም ወደ ቤተሰቤ ለመመለስ ወሰንኩ።” ይህን የተናገረው ኤድዋርዶ * የተባለ አንድ ወንድም ነው።—ኤፌ. 6:4

2 ኤድዋርዶ ወደ ቤተሰቡ ለመመለስ መወሰኑ ይሖዋን እንደሚያስደስተው ገብቶታል። ይሁን እንጂ ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰችው እንደ ማሪሊን ሁሉ እሱም ከቤተሰቡ ጋር ያለውን ዝምድና ለማደስ ረጅም ጊዜና ከፍተኛ ጥረት ይጠይቅበታል። በዚያ ላይ ደግሞ በኢኮኖሚ ደካማ በሆነ አገር ውስጥ እየኖረ ቤተሰቡን ማስተዳደር አለበት። ታዲያ ቤተሰቡን ለማስተዳደር የሚያስችለውን ገንዘብ የሚያገኘው እንዴት ነው? በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎች ምን ዓይነት እርዳታ ሊያደርጉለት ይችላሉ?

ከይሖዋና ከቤተሰብህ ጋር ያለህን ዝምድና ማደስ

3. አንድ ወላጅ ከቤተሰቡ ተለይቶ መኖሩ በልጆቹ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

3 ኤድዋርዶ እንዲህ ብሏል፦ “ልጆቼ የእኔ አመራርና ፍቅር ይበልጥ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ላይ ችላ እንዳልኳቸው ተረዳሁ። ከእነሱ ጋር አብሬ ስላልኖርኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን አንብቤላቸው፣ አብሬያቸው ጸልዬ፣ አቅፌያቸው ወይም አጫውቼያቸው አላውቅም።” (ዘዳ. 6:7) የመጀመሪያ ልጁ የሆነችው አና፣ ሁኔታውን  አስታውሳ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “አባታችን ከእኛ ጋር ባለመኖሩ የስሜት መቃወስ አጋጥሞኝ ነበር። በአካል የመገናኘት አጋጣሚ ስላልነበረን የምናውቀው ድምፁንና መልኩን ብቻ ነበር። በመሆኑም ተመልሶ በመጣበት ወቅት ሲያቅፈኝ እንግዳ ነገር ሆነብኝ።”

4. አንድ አባት ከቤተሰቡ ተለይቶ መኖሩ የራስነት ኃላፊነቱን እንዳይወጣ እንቅፋት የሚሆንበት እንዴት ነው?

4 በተጨማሪም አንድ አባት ከቤተሰቡ ተለይቶ መኖሩ የራስነት ኃላፊነቱን እንዳይወጣ እንቅፋት ይሆንበታል። የኤድዋርዶ ባለቤት የሆነችው ሩቢ እንዲህ ብላለች፦ “በቤቱ ውስጥ እንደ አባትም፣ እንደ እናትም መሆን ነበረብኝ፤ በመሆኑም አብዛኛውን ውሳኔ የማደርገው እኔ ነበርኩ። ኤድዋርዶ ሲመለስ ግን ለራስነት ሥልጣን መገዛትን መማር ነበረብኝ። አሁንም እንኳ ባለቤቴ አብሮን መኖሩን ስለምረሳ ራሴን ማስታወስ የሚያስፈልገኝ ጊዜ አለ።” (ኤፌ. 5:22, 23) ኤድዋርዶ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “ልጆቻችን አንዳንድ ነገሮችን ማድረግ ሲፈልጉ የሚያስፈቅዱት እናታቸውን ነበር። በመሆኑም ውሳኔ ስናደርግ ሁለታችንም ተመካክረን እንደሆነ ለልጆቻችን ማሳየት እንዳለብን ተገነዘብን፤ እኔም ብሆን የራስነት ኃላፊነቴን ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ መወጣት የምችልበትን መንገድ መማር ነበረብኝ።”

5. አንድ አባት ከቤተሰቡ መለያየቱ ያስከተለውን ጉዳት ለመጠገን ምን አደረገ? ምን ውጤትስ አገኘ?

5 ኤድዋርዶ ከቤተሰቡ ጋር ያለውን ዝምድና ለማደስ እንዲሁም መንፈሳዊነታቸውን ለማጠናከር ሲል የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ቆርጦ ነበር። “ዋናው ግቤ፣ በቃልም ሆነ ምሳሌ በመሆን ማለቴ ይሖዋን እንደምወድ በመናገር ብቻ ሳይሆን መውደዴን በተግባር በማሳየት እውነትን በልጆቼ ልብ ውስጥ መትከል ነበር” ብሏል። (1 ዮሐ. 3:18) ታዲያ ይሖዋ ኤድዋርዶ ያደረገውን ጥረት ባርኮለታል? አና ውጤቱን ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ጥሩ አባት ለመሆን እንዲሁም ከእኛ ጋር ለመቀራረብ ያደረገው ጥረት ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። በጉባኤ ውስጥ መንፈሳዊ እድገት ሲያደርግ ስንመለከት ደስ አለን። ይህ ዓለም ከይሖዋ ሊያርቀን እየሞከረ ነበር። ይሁን እንጂ ወላጆቻችን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንደሚያተኩሩ ስንመለከት እኛም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ጀመርን። አባዬ ሁለተኛ ከእኛ እንደማይለይ ቃል ገባልን፤ ደግሞም ቃሉን ጠብቋል። እንዲህ ባያደርግ ኖሮ ዛሬ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ላልገኝ እችል ነበር።”

ኃላፊነቱን መውሰድ

6. በጦርነት ወቅት የነበሩ አንዳንድ ወላጆች ምን ትምህርት አግኝተዋል?

6 አንዳንድ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት፣ በባልካን አገሮች ጦርነት በተነሳበት ጊዜ የነበሩ የይሖዋ ምሥክር ልጆች ወቅቱ ለኑሮ አስቸጋሪ ቢሆንም ደስተኞች ነበሩ። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? በጦርነቱ ምክንያት ሥራ መሄድ ያልቻሉ ወላጆች ቤት ስለሚውሉ ጊዜያቸውን ከልጆቻቸው ጋር በማጥናት፣ በመጫወትና በማውራት ያሳልፉ ስለነበር ነው። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ልጆች ከገንዘብ ወይም ከስጦታ ይበልጥ የሚፈልጉት ከወላጆቻቸው ጋር መሆንን ነው። በእርግጥም የአምላክ ቃል እንደሚናገረው ወላጆች ለልጆቻቸው ትኩረትና ሥልጠና የሚሰጧቸው ከሆነ ልጆች ይጠቀማሉ።—ምሳሌ 22:6

7, 8. (ሀ) ከስደት የተመለሱ አንዳንድ ወላጆች ምን ስህተት ይሠራሉ? (ለ) ወላጆች፣ ልጆቻቸው የሚሰማቸውን ቅሬታ እንዲያስወግዱ ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

7 ለሥራ ከቤተሰባቸው ተለይተው የሄዱ ወላጆች ከስደት በሚመለሱበት ጊዜ ልጆቻቸው በእነሱ ሊበሳጩ ወይም ለእነሱ ምንም ግድ ላይኖራቸው ይችላል፤ የሚያሳዝነው ግን አንዳንድ ወላጆች በዚህ ጊዜ “ለእናንተ ብዬ ይህን ሁሉ መሥዋዕትነት ከፍዬ እንዴት ምስጋና ቢስ ትሆናላችሁ?” የሚል ምላሽ ይሰጣሉ። ይሁን እንጂ በልጆቹ ላይ የሚታየው እንዲህ ያለው ባሕርይ የሚመጣው አብዛኛውን ጊዜ ወላጃቸው ከእነሱ በመለየቱ ምክንያት ነው። ታዲያ አንድ ወላጅ ይህን ችግር ለመፍታት ምን ማድረግ ይችላል?

8 የቤተሰብህን ስሜት ይበልጥ መረዳትና ለእነሱ አሳቢነት ማሳየት እንድትችል እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው። ከዚያም ከቤተሰብህ ጋር በጉዳዩ ላይ ስትነጋገር ለችግሩ መከሰት የአንተም ድርሻ እንዳለበት አምነህ ተቀበል። ከልብህ ይቅርታ መጠየቅህም ሊረዳህ ይችላል። የትዳር ጓደኛህና ልጆችህ ነገሮችን ለማስተካከል የምታደርገውን ያልተቋረጠ ጥረት ሲመለከቱ ዝምድናችሁን ለማደስ ምን ያህል እንደቆረጥክ ማስተዋላቸው አይቀርም። በዚህ ረገድ ጽናትና ትዕግሥት ማሳየትህ ቀስ በቀስ የቤተሰብህን ፍቅርና አክብሮት ሊያስገኝልህ ይችላል።

 ‘ለቤተሰብ አባላት የሚያስፈልገውን ማቅረብ’

9. ‘የራሳችን ለሆኑት የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማቅረብ’ ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮችን ለማግኘት መሯሯጥ የሌለብን ለምንድን ነው?

9 በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ማሟላት ካልቻሉ ልጆች ወይም የልጅ ልጆች “ለወላጆቻቸውና ለአያቶቻቸው የሚገባቸውን ብድራት” እንዲከፍሉ ሐዋርያው ጳውሎስ መመሪያ ሰጥቷል። በሌላ በኩል ደግሞ ጳውሎስ ሁሉም ክርስቲያኖች ለዕለት የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ይኸውም ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ካሏቸው በዚህ ረክተው እንዲኖሩ አሳስቧል። በመሆኑም የተመቻቸ ሕይወት ወይም ለወደፊቱ ጊዜ የሚሆን አስተማማኝ የገንዘብ ምንጭ እንዲኖረን ስንል ብቻ የምንሯሯጥ መሆን የለብንም። (1 ጢሞቴዎስ 5:4, 8ን እና 1 ጢሞቴዎስ 6:6-10ን አንብብ።) አንድ ክርስቲያን ‘የራሱ ለሆኑት የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማቅረብ’ በቅርቡ በሚያልፈው በዚህ ዓለም ላይ ሀብታም መሆን አያስፈልገውም። (1 ዮሐ. 2:15-17) ‘ሀብት ባለው የማታለል ኃይል’ ወይም ‘በኑሮ ጭንቀት’ እንዳንሸነፍ መጠንቀቅ አለብን፤ አለበለዚያ ቤተሰባችን ጽድቅ በሚሰፍንበት የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኘውን ‘እውነተኛ ሕይወት አጥብቆ እንዳይይዝ’ እንቅፋት እንፈጥራለን!—ማር. 4:19፤ ሉቃስ 21:34-36፤ 1 ጢሞ. 6:19

10. ከገንዘብ ጋር በተያያዘ አምላካዊ ጥበብ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

10 ይሖዋ የተወሰነ ገንዘብ እንደሚያስፈልገን ያውቃል። ይሁን እንጂ ገንዘብ የአምላካዊ ጥበብን ያህል ሊጠብቀን ወይም በሕይወት ሊያኖረን አይችልም። (መክ. 7:12፤ ሉቃስ 12:15) አብዛኞቹ ሰዎች ለሥራ ወደ ውጭ አገር መሄድ ምን ያህል ወጪ እንደሚያስወጣ አይገነዘቡም፤ እዚያ ሄደውም ቢሆን የሚፈልጉትን ያህል ገንዘብ የማግኘታቸው ጉዳይ ዋስትና የለውም። እንዲያውም ከባድ ችግር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ብዙዎቹ ወደ አገራቸው የሚመለሱት በባሰ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቀው ነው። አምላክን በነፃነት ከማገልገል ይልቅ ገንዘብ ላበደራቸው ሰው ባሪያ ይሆናሉ። (ምሳሌ 22:7ን አንብብ።) መጀመሪያውንም ቢሆን እንዲህ ዓይነት ዕዳ ውስጥ አለመግባት የጥበብ እርምጃ ነው።

11. ቤተሰቦች ባወጡት በጀት መሠረት መኖራቸው በገንዘብ ረገድ የሚገጥማቸውን ችግር ለመቀነስ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

11 ኤድዋርዶ ከቤተሰቡ ጋር አብሮ ለመኖር ባደረገው ውሳኔ ለመጽናት ከፈለገ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ማስተዋል የታከለበት እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ያውቅ ነበር። እሱና ባለቤቱ፣ የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች ግምት ውስጥ በማስገባት በጀት አወጡ። ያወጡት በጀት ከዚህ በፊት ይገዟቸው የነበሩ ነገሮችን ለመግዛት ነፃነት እንደማይሰጣቸው ግልጽ ነው። ያም ቢሆን ሁሉም ተባባሪነታቸውን ያሳዩ ከመሆኑም ሌላ ያን ያህል ለማያስፈልጉ ነገሮች ገንዘብ አላወጡም። * ኤድዋርዶ “ልጆቼን ከግል ትምህርት ቤት በማስወጣት ጥሩ የሕዝብ ትምህርት ቤት ፈልጌ አስገባኋቸው” ብሏል። ከቤተሰቡ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ጋር የማይጋጭ ሥራ ማግኘት እንዲችል እሱና ቤተሰቡ ጸልየው ነበር። ታዲያ ይሖዋ ለጸሎታቸው መልስ የሰጣቸው እንዴት ነው?

12, 13. አንድ አባት ቤተሰቡን ለማስተዳደር ምን እርምጃዎችን ወሰደ? አኗኗሩን ቀላል ለማድረግ ቁርጥ አቋም በመውሰዱ ይሖዋ የባረከውስ እንዴት ነው?

12 ኤድዋርዶ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት፣ ወጪዎቻችንን መሸፈን ከብዶን ነበር። ያጠራቀምኩት ገንዘብ እያለቀ ሄደ፤ ገቢዬም ቢሆን ወጪዎቻችንን ለመሸፈን የሚያስችል አልነበረም፤ በዚያ ላይ በጣም ይደክመኝ ነበር። ያም ቢሆን በሁሉም ስብሰባዎች ላይ እንካፈል የነበረ ሲሆን አገልግሎትም አብረን እንወጣ ነበር።” ኤድዋርዶ ከቤተሰቡ ለወራት ወይም ለዓመታት ሊነጥለው የሚችል ሥራ መያዝ ይቅርና ስለዚያ እንኳ ላለማሰብ ቆርጦ ነበር። “ከዚህ ይልቅ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት ስለተማርኩ በአንዱ ሥራ ባጣ በሌላው አገኛለሁ” በማለት ተናግሯል።

ቤተሰብህን ለማስተዳደር የተለያዩ ዓይነት ሥራዎችን መሥራትን ልትማር ትችላለህ? (አንቀጽ 12ን ተመልከት)

13 ኤድዋርዶ ዕዳውን ወዲያው ከፍሎ ማጠናቀቅ ስላልቻለ የበለጠ ወለድ መክፈል ግድ ሆኖበታል። ይሁን እንጂ ይህን እንደ ትልቅ ኪሳራ አልቆጠረውም፤ ምክንያቱም ከቤተሰቡ ጋር አብሮ በመኖር ይሖዋ ከወላጆች የሚጠብቀውን ነገር ማድረጉ የበለጠ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንደሆነ ተሰምቶታል። ኤድዋርዶ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “አሁን የማገኘው ገቢ ውጭ አገር ሳለሁ ከማገኘው 10 እጥፍ በላይ ያነሰ ነው፤ ይሁንና ተርበን አናውቅም። ‘የይሖዋ እጅ አጭር አይደለም።’ እንዲያውም አቅኚዎች ለመሆን ወሰንን። የሚገርመው ነገር፣ ከጊዜ በኋላ የኢኮኖሚው ሁኔታ እየተሻሻለ  ሲመጣ ለኑሮ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ማሟላት እየቀለለልን ሄደ።”—ኢሳ. 59:1

ዘመዶች የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ መቋቋም

14, 15. አንድ ቤተሰብ ቁሳዊ ነገሮችን ከመንፈሳዊ ነገሮች እንዲያስቀድም የሚደርስበትን ጫና መቋቋም የሚችለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ቤተሰቡ ጥሩ ምሳሌ መሆኑ ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?

14 በብዙ አካባቢዎች፣ ሰዎች ለዘመዶቻቸውና ለወዳጆቻቸው ገንዘብና ስጦታ የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። “መስጠት ባሕላችን ነው፤ ደግሞም እንዲህ ማድረግ ደስ ይለናል” በማለት ኤድዋርዶ ተናግሯል፤ አክሎ ግን እንዲህ ብሏል፦ “ገደብ ማበጀት የሚኖርብን ጊዜ አለ። ለዘመዶቼ የምችለውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ብሆንም ይህን የማደርገው የቤተሰቤን መንፈሳዊ ፍላጎትና የምናደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች እስካልነካ ድረስ እንደሆነ በዘዴ ላስረዳቸው እሞክራለሁ።”

15 አንድ ሰው ከቤተሰቡ ጋር ለመሆን ሲል ወደ አገሩ በሚመለስበት ወይም ከቤተሰቡ ላለመለየት ሲል ወደ ውጭ አገር የመሄድ አጋጣሚውን ሳይጠቀምበት በሚቀርበት ጊዜ የእሱን እጅ የሚጠብቁ ዘመዶቹ ሊበሳጩ፣ ሊያፌዙበት ወይም ሊያዝኑበት ይችላሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ ጨካኝ አድርገው ይመለከቱት ይሆናል። (ምሳሌ 19:6, 7) ይሁን እንጂ የኤድዋርዶ ልጅ አና እንዲህ ብላለች፦ “ዘመዶቻችን ለቁሳዊ ነገሮች ስንል መንፈሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች እንዳልሆንን ሲያውቁ በሕይወታችን ውስጥ መንፈሳዊ ነገሮችን ምን ያህል ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ማስተዋል ይጀምራሉ። እነሱ የፈለጉትን ሁሉ የምናደርግላቸው ከሆነ ግን ይህን እንዴት መረዳት ይችላሉ?”—ከ1 ጴጥሮስ 3:1, 2 ጋር አወዳድር።

በአምላክ ላይ እምነት ማሳደር

16. (ሀ) አንድ ሰው ‘የውሸት ምክንያት እያቀረበ ራሱን ሊያታልል’ የሚችለው እንዴት ነው? (ያዕ. 1:22) (ለ) ይሖዋ የሚባርከው ምን ዓይነት ውሳኔዎችን ነው?

16 የትዳር ጓደኛዋንና ልጆቿን ጥላ ወደ አንድ የበለጸገ አገር የሄደች አንዲት እህት እዚያ ላሉት ሽማግሌዎች እንዲህ ብላለች፦ “እኔ እዚህ እንድመጣ ቤተሰባችን ትልቅ መሥዋዕትነት ከፍሏል። እንዲያውም ባለቤቴ የሽምግልና መብቱን አጥቷል። ስለዚህ ይሖዋ ይህን ውሳኔያችንን እንደሚባርከው ተስፋ አደርጋለሁ።” ይሖዋ በእሱ ላይ እምነት እንዳላቸው የሚያሳይ ውሳኔ የሚያደርጉ ሰዎችን ምንጊዜም እንደሚባርክ የታወቀ ነው፤ ይሁን እንጂ ከእሱ ፈቃድ ጋር የሚቃረን በተለይ ደግሞ ሳያስፈልግ ቅዱስ የሆኑ የአገልግሎት መብቶችን እንድንተው የሚያደርግ ውሳኔ ካደረግን እንዴት ሊባርከን ይችላል?—ዕብራውያን 11:6ን እና 1 ዮሐንስ 5:13-15ን አንብብ።

17. ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት የይሖዋን መመሪያ መጠየቅ ያለብን ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

17 የይሖዋን መመሪያ መጠየቅ ያለብህ አንድ ውሳኔ  ከማድረግህ ወይም አንድ ዓይነት ግዴታ ውስጥ ከመግባትህ በፊት እንጂ ከዚያ በኋላ መሆን የለበትም። ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱንና ጥበቡን እንዲሰጥህ እንዲሁም እንዲመራህ ጠይቀው። (2 ጢሞ. 1:7) ራስህን እንዲህ እያልህ ጠይቅ፦ ‘ይሖዋን መታዘዝ የምፈልገው እስከ ምን ድረስ ነው? በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኛ ነኝ?’ መልስህ አዎ ከሆነ፣ በፊት ከነበረህ የኑሮ ደረጃ ዝቅ ማለት ቢጠይቅብህም እንኳ እሱን ለመታዘዝ ፈቃደኛ ነህ? (ሉቃስ 14:33) ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር እንዲሰጡህ ስለ ጉዳዩ ሽማግሌዎችን አማክር፤ እንዲሁም እነሱ የሚሰጡህን ምክር ተከተል። እንዲህ ካደረግህ ይሖዋ እንደሚረዳህ በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳለህ ታሳያለህ። ሽማግሌዎች ለአንተ ሊወስኑልህ አይችሉም፤ ነገር ግን ዘላቂ ደስታ የሚያስገኝ ውሳኔ እንድታደርግ ያግዙሃል።—2 ቆሮ. 1:24

18. ቤተሰብን የመንከባከብ ኃላፊነት የተጣለው በማን ላይ ነው? ይሁን እንጂ ሌሎች በየትኞቹ አጋጣሚዎች እርዳታ ሊያበረክቱ ይችላሉ?

18 የቤተሰብ ራሶች፣ ቤተሰባቸውን በየዕለቱ የመንከባከብን “የኃላፊነት ሸክም” ከይሖዋ ተቀብለዋል። የተለያዩ ጫናዎችና ፈታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም እንኳ ከቤተሰባቸው ሳይለዩ ይህን ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉትን ሁሉ ልናደንቃቸውና ልንጸልይላቸው ይገባል። እነዚህ ቤተሰቦች አደጋዎች፣ ድንገተኛ የጤና ችግር ወይም ሌሎች ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ለእነሱ እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅርና አሳቢነት ለማሳየት ጥሩ አጋጣሚ እናገኛለን። (ገላ. 6:2, 5፤ 1 ጴጥ. 3:8) ታዲያ ድንገተኛ ሁኔታ ሲያጋጥም የገንዘብ እርዳታ ልትሰጧቸው ወይም በአካባቢያቸው ሥራ እንዲያገኙ ልትረዷቸው ትችላላችሁ? እንዲህ ማድረጋችሁ ከቤተሰባቸው ተነጥለው ሌላ ቦታ እንዲሠሩ የሚደርስባቸውን ጫና ቀላል ያደርግላቸዋል።—ምሳሌ 3:27, 28፤ 1 ዮሐ. 3:17

ይሖዋ ረዳትህ እንደሆነ አስታውስ!

19, 20. ክርስቲያኖች ይሖዋ እንደሚረዳቸው እርግጠኛ መሆን የሚችሉት ለምንድን ነው?

19 መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ያሳስበናል፦ “አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ አሁን ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ። ምክንያቱም [አምላክ] ‘ፈጽሞ አልተውህም፣ በምንም ዓይነት አልጥልህም’ ብሏል። ስለዚህ በሙሉ ልብ ‘ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?’ እንላለን።” (ዕብ. 13:5, 6) ታዲያ ይህን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

20 በማደግ ላይ ባለ አገር ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሽማግሌ ሆኖ ያገለገለ አንድ ወንድም እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ሰዎች ብዙውን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በጣም ደስተኛ እንደሆኑ አስተያየት ይሰጣሉ። ሌላው ቀርቶ ድሃ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮችም እንኳ ጥሩ እንደሚለብሱና በኑሮም ቢሆን ከሌሎች የተሻሉ መስለው እንደሚታዩ አስተውለዋል።” ይህም ኢየሱስ መንግሥቱን ለሚያስቀድሙ ሰዎች የገባው ቃል እውነት መሆኑን የሚያሳይ ነው። (ማቴ. 6:28-30, 33) አዎን፣ የሰማዩ አባትህ ይሖዋ ይወድሃል፤ አንተም ሆንክ ልጆችህ ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንድታገኙ ይፈልጋል። “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ።” (2 ዜና 16:9) ይሖዋ፣ ከቤተሰብ ሕይወትና ከቁሳዊ ፍላጎታችን ጋር የተያያዙትን ጨምሮ ሁሉንም ትእዛዛት የሰጠን ለእኛ ጥቅም ሲል ነው። እነዚህን ትእዛዛት ስንከተል እሱን እንደምንወደውና በእሱ እንደምንታመን እናሳያለን። “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነውና፤ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባዶች አይደሉም።”—1 ዮሐ. 5:3

21, 22. በይሖዋ ለመታመን የወሰንከው ለምንድን ነው?

21 ኤድዋርዶ “ከባለቤቴና ከልጆቼ ርቄ የኖርኩባቸውን ጊዜያት እንደገና መመለስ እንደማልችል አውቃለሁ፤ ሁልጊዜ እየተጸጸትኩ እኖራለሁ ማለት ግን አይደለም” በማለት ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቼ ሀብታም ቢሆኑም ደስተኛ አይደሉም። ከባድ የቤተሰብ ችግርም አለባቸው። የእኛ ቤተሰብ ግን በጣም ደስተኛ ነው! እንዲሁም በዚህ አገር ያሉ ወንድሞች ምንም እንኳ ድሆች ቢሆኑም መንፈሳዊ ነገሮችን በሕይወታቸው ውስጥ እንደሚያስቀድሙ ስመለከት እደነቃለሁ። ሁላችንም ኢየሱስ የገባው ቃል እውነት እንደሆነ በሕይወታችን እየተመለከትን ነው።”—ማቴዎስ 6:33ን አንብብ።

22 በመሆኑም ደፋር ሁን! ምርጫህ ይሖዋን መታዘዝ ይሁን፤ እንዲሁም በእሱ ታመን። ለአምላክህ፣ ለትዳር ጓደኛህና ለልጆችህ ያለህ ፍቅር የቤተሰብህን መንፈሳዊ ፍላጎት የማሟላት ኃላፊነትህን ትወጣ ዘንድ እንዲያነሳሳህ እንመኛለን። ይህን ካደረግህ ‘ይሖዋ ረዳትህ መሆኑን’ በሕይወትህ ማየት ትችላለህ።

^ አን.1 ስሞቹ ተቀይረዋል።

^ አን.11 በመስከረም 2011 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “ገንዘብን በአግባቡ መጠቀም—እንዴት?” የሚለውን ተከታታይ ርዕስ ተመልከት።