“የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ዐይኖች በሁሉም ስፍራ ናቸው፤ ክፉዎችንም ደጎችንም ነቅተው ይመለከታሉ።”—ምሳሌ 15:3

1, 2. የይሖዋ ዓይኖች ለክትትል ሲባል ከሚተከሉ ካሜራዎች የሚለዩት እንዴት ነው?

በብዙ አገሮች ውስጥ የትራፊክ ፍሰትን ለመቆጣጠር እንዲሁም አደጋ ሲደርስ ፎቶግራፍ ለማንሳት ሲባል የክትትል ካሜራዎችን መትከል የተለመደ እየሆነ መጥቷል። አንድ መኪና አደጋ አድርሶ በሚሰወርበት ጊዜ ባለሥልጣናቱ ግለሰቡን ተከታትለው ለመያዝ እንዲችሉ እነዚህ ካሜራዎች ትልቅ እርዳታ ያበረክታሉ። በእርግጥም እንዲህ ያሉ ሰው ሠራሽ ዓይኖች በየቦታው መኖራቸው ሰዎች ከተጠያቂነት ለማምለጥ የሚያደርጉት ሙከራ አዳጋች እንዲሆን አድርገዋል።

2 ታዲያ በየቦታው የተተከሉት እነዚህ የክትትል ካሜራዎች ስለ አፍቃሪው አባታችን ስለ ይሖዋ ምን ያስታውሱናል? መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ዓይኖች “በሁሉም ስፍራ ናቸው” ይላል። (ምሳሌ 15:3) ይሁንና ይሖዋ የሚከታተለን በእኛ ላይ ስህተት ለመፈላለግ ብሎ ነው? ወይም ደግሞ ጥፋት ስንሠራ ጠብቆ ለመቅጣት ስለሚፈልግ ነው? (ኤር. 16:17፤ ዕብ. 4:13) በፍጹም! ይሖዋ የሚመለከተን በግለሰብ ደረጃ ስለሚወደንና የእኛ ደኅንነት ስለሚያሳስበው ነው።—1 ጴጥ. 3:12

3. በዚህ ርዕስ ላይ የአምላክን አሳቢነት የሚያሳዩ የትኞቹን አምስት መንገዶች እንመለከታለን?

3 አምላክ በዓይኑ የሚከታተለን ስለሚወደን መሆኑን እንድንገነዘብ ምን ሊረዳን ይችላል? ይሖዋ የሚከታተለን ስለሚወደን መሆኑን የሚያሳዩ አምስት  መንገዶችን እስቲ እንመልከት። ይሖዋ (1) መጥፎ አዝማሚያችንን ተመልክቶ ያስጠነቅቀናል፤ (2) የተሳሳተ እርምጃ ስንወስድ ያርመናል፤ (3) በቃሉ ውስጥ በሚገኙ መሠረታዊ ሥርዓቶች አማካኝነት ይመራናል፤ (4) የተለያዩ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ይረዳናል፤ እንዲሁም (5) በውስጣችን መልካም ነገር ተመልክቶ ወሮታውን ይከፍለናል።

ይሖዋ ያስጠነቅቀናል

4. ይሖዋ ቃየንን ‘ኃጢአት በደጁ እያደባች’ እንደሆነ ያስጠነቀቀው ለምንድን ነው?

4 እስቲ በመጀመሪያ ይሖዋ በልባችን ውስጥ መጥፎ ዝንባሌ ማቆጥቆጥ ሲጀምር የሚያስጠነቅቀን እንዴት እንደሆነ እንመልከት። (1 ዜና 28:9) ይህ፣ ይሖዋ እኛን የሚመለከተን ለጥቅማችን እንደሆነ ከሚያሳዩ መንገዶች አንዱ ነው፤ ለምሳሌ ያህል ቃየን፣ የይሖዋን ሞገስ በማጣቱ የተነሳ ‘ክፉኛ በተናደደ’ ጊዜ አምላክ ምን እንዳደረገ ልብ በል። (ዘፍጥረት 4:3-7ን አንብብ።) በዚህ ጊዜ ይሖዋ ቃየንን ‘መልካም እንዲያደርግ’ አሳሰበው። እንዲህ ካላደረገ ‘ኃጢአት በደጁ እያደባች’ እንደሆነ በመግለጽ አስጠነቀቀው። ከዚያም “ተቈጣጠራት” አለው። አምላክ ይህን ያለው ለምንድን ነው? ቃየን ለማስጠንቀቂያው ምላሽ በመስጠት በእሱ ዘንድ ‘ተቀባይነት እንዲያገኝ’ ስለፈለገ ነው። ቃየን ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና ጠብቆ ማቆየት የሚችለው በዚህ መንገድ ነው።

5. ጤናማ ያልሆኑ ፍላጎቶች በውስጣችን ማቆጥቆጥ ሲጀምሩ ይሖዋ የሚያስጠነቅቀን በምን መንገዶች ነው?

5 ስለ እኛስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋ በልባችን ውስጥ ያለውን ነገር ይመለከታል፤ ዝንባሌያችንን ወይም አንድን ነገር ለማድረግ የተነሳሳንበትን ምክንያት ከእሱ መደበቅ አንችልም። አፍቃሪው አባታችን የጽድቅ ጎዳናን እንድንከተል ይፈልጋል፤ ያም ሆኖ የጀመርነውን ጎዳና እንድንቀይር አያስገድደንም። በተሳሳተ አቅጣጫ መጓዝ ስንጀምር በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ያስጠነቅቀናል። እንዴት? መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ስናነብ ብዙውን ጊዜ መጥፎ ዝንባሌዎችንና ጤናማ ያልሆኑ ፍላጎቶችን ለማሸነፍ የሚረዱን ጥቅሶች እናገኛለን። በተጨማሪም በጽሑፎቻችን ላይ፣ እኛ እየታገልን ስላለው ችግር የሚያብራራና ችግሩን እንዴት እንደምንቋቋም የሚገልጽ ሐሳብ ይወጣል። በጉባኤ ስብሰባዎችም ላይ ሁላችንም በተገቢው ጊዜ ምክር እናገኛለን።

6, 7. (ሀ) በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ታሳቢ አድርገው የሚዘጋጁ ትምህርቶች አምላክ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልህ የሚያሳዩ ናቸው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ከሚሰጥህ ማሳሰቢያ ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

6 ይሖዋ ቀደም ሲል በተጠቀሱት መንገዶች የሚያስጠነቅቀን መሆኑ አፍቃሪ አምላክ እንደሆነና እያንዳንዳችንን በግለሰብ ደረጃ የሚመለከተን ስለሚያስብልን እንደሆነ ያሳያል። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ከበርካታ መቶ ዘመናት በፊት ነው፤ የአምላክ ድርጅት ጽሑፎችን የሚያዘጋጀው በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ነው፤ በስብሰባዎች ላይ የሚሰጡት ምክሮችም ቢሆኑ የሚዘጋጁት መላውን ጉባኤ ታሳቢ በማድረግ ነው። ያም ሆኖ ይሖዋ በእነዚህ መንገዶች ተጠቅሞ ምክሩ ለአንተ ተብሎ እንደተዘጋጀ እንዲሰማህ በማድረግ መጥፎ ዝንባሌህን ማስተካከል እንድትችል ይረዳሃል። ከዚህ አንጻር እነዚህ ዝግጅቶች ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልህ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው ሊባል ይችላል።

በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናችን በዙሪያችን ካሉ አደገኛ ሁኔታዎች ይጠብቀናል (አንቀጽ 6ን እና 7ን ተመልከት)

7 ከአምላክ ማስጠንቀቂያዎች ጥቅም ማግኘት ከፈለግን በመጀመሪያ እሱ ከልብ እንደሚያስብልን መገንዘብ አለብን። ከዚያም ለቃሉ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ማለትም አምላክን የሚያሳዝኑ መጥፎ አስተሳሰቦችን ከአእምሯችን ለማውጣት መጣር ይኖርብናል። (ኢሳይያስ 55:6, 7ን አንብብ።) የሚሰጠንን ማስጠንቀቂያ የምንሰማ ከሆነ ከብዙ ጣጣዎች እንጠበቃለን። ይሁን እንጂ ለመጥፎ ዝንባሌዎች ብንሸነፍስ? አፍቃሪው አባታችን በዚህ ጊዜ የሚረዳን እንዴት ነው?

አሳቢ የሆነው አምላካችን እርማት ይሰጠናል

8, 9. ይሖዋ በአገልጋዮቹ አማካኝነት የሚሰጠው ምክር በጥልቅ እንደሚያስብልን የሚያሳየው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

8 ይሖዋ እርማት የሚሰጠን መሆኑ እንደሚያስብልን ያሳያል። (ዕብራውያን 12:5, 6ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ ምክር ወይም ተግሣጽ መቀበል ላያስደስተን ይችላል። (ዕብ. 12:11) ይሁን እንጂ ምክር  የሚሰጠን ሰው አስቀድሞ ምን ነገሮችን ግምት ውስጥ እንደሚያስገባ ለማሰብ እንሞክር። ይህ ግለሰብ በቅድሚያ ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለንን ዝምድና የሚያበላሽ ምን ነገር እያደረግን እንዳለ ለማወቅ ጥረት ያደርጋል፤ ስለ ስሜታችንም ይጠነቀቃል፤ እንዲሁም አካሄዳችንን ለውጠን ይሖዋን የምናስደስት እንድንሆን የሚረዳ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለማካፈል በፈቃደኝነት ጊዜውንና ጉልበቱን መሥዋዕት ያደርጋል። ይህ ደግሞ የምክሩ ምንጭ የሆነው ይሖዋ ምን ያህል እንደሚያስብልን የሚያሳይ ነው።

9 ሰዎች የሚሰጡን ምክር የይሖዋን አሳቢነት እንደሚያንጸባርቅ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እስቲ እንመልከት። አንድ ወንድም ወደ እውነት ከመምጣቱ በፊት ፖርኖግራፊ የመመልከት ልማድ ነበረው፤ እውነትን ሲሰማ ግን ከዚህ ልማዱ ተላቀቀ። ይሁንና የቀድሞ ልማዱ ልክ እንደተዳፈነ እሳት በውስጡ ነበር። አዲስ ሞባይል ስልክ ሲይዝ መጥፎ ልማዱ ተቀጣጠለ። (ያዕ. 1:14, 15) በስልኩ ተጠቅሞ የፖርኖግራፊ ድረ ገጾችን መመልከት ጀመረ። አንድ ቀን፣ ከአንድ ሽማግሌ ጋር የስልክ ምሥክርነት እየሰጠ ሳለ ሽማግሌው አድራሻ ማውጣት ስለፈለገ የእሱን ስልክ ተዋሰ። ሽማግሌው ስልኩን መጠቀም ሲጀምር የፖርኖግራፊ ድረ ገጾች ብቅ አሉ። ይህ ሁኔታ በመንፈሳዊ አደጋ ላይ ለነበረው ለዚህ ወንድም ለበጎ ሆነለት። በጥሩ ጊዜ ላይ ምክር አገኘ፤ የተሰጠውን እርማትም ተቀበለ፤ በመሆኑም መጥፎ ፍላጎቱን ማሸነፍ ቻለ። አፍቃሪው የሰማዩ አባታችን በድብቅ የምንሠራውንም ኃጢአት ጭምር የሚመለከት ከመሆኑም ሌላ ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሳችን በፊት የሚያርመን በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን!

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠቅመናል

10, 11. (ሀ) አምላክ መመሪያ የሚሰጥህ በምን መንገድ ነው? (ለ) አንድ ቤተሰብ የይሖዋን መመሪያዎች መከተል ጥበብ እንደሆነ በራሱ ተሞክሮ የተመለከተው እንዴት ነው?

10 መዝሙራዊው “በምክርህ መራኸኝ” ብሏል። (መዝ. 73:24) መመሪያ በሚያስፈልገን ወቅት ይሖዋን ‘ማወቅ’ ማለትም በቃሉ አማካኝነት ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት መገንዘብ እንችላለን። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረጋችን የሚጠቅመን በመንፈሳዊ ብቻ አይደለም፤ ይህን ማድረግ ቁሳዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት የሚረዳን ጊዜም አለ።—ምሳሌ 3:6

11 ለዚህ ምሳሌ እንዲሆነን በፊሊፒንስ በሚገኝ ማስባቲ የተባለ ተራራማ ክልል የሚኖር አንድ ጭሰኛ ወንድም ያጋጠመውን ሁኔታ እስቲ እንመልከት። ይህ ወንድም ትልቅ ቤተሰብ ቢኖረውም እሱና ባለቤቱ የዘወትር አቅኚዎች ሆነው ያገለግላሉ። አንድ ቀን፣ መሬቱን እንዲለቅቁ የሚገልጽ ማስታወሻ ከመሬቱ ባለቤት ሲደርሳቸው በጣም ደነገጡ። ይህ ማስታወሻ የተላከላቸው ለምንድን ነው? የማጭበርበር ድርጊት እንደሚፈጽሙ በሐሰት ስለተከሰሱ ነው። ይህ ወንድም ቤተሰቡን የት  እንደሚያኖር ቢያሳስበውም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ ያዘጋጃል። የፈለገ ነገር ቢሆን ሁልጊዜም የሚያስፈልገንን ይሰጠናል።” ይሖዋም ይህን ወንድም አላሳፈረውም። ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ቤተሰቡ መሬቱን ለቅቀው መሄድ እንደማያስፈልጋቸው ተነገራቸው። የመሬቱ ባለቤት ሐሳቡን የቀየረው ለምንድን ነው? ቤተሰቡ ክስ ቢሰነዘርባቸውም በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በመመራት ጉዳዩን አክብሮት በተሞላበትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንደያዙት ስላስተዋለ ነው። ይህ ሁኔታ የመሬት ባለቤቱን በጣም ስላስገረመው በቦታው እንዲቆዩ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የሚያለሙት ተጨማሪ መሬት ሰጣቸው። (1 ጴጥሮስ 2:12ን አንብብ።) በእርግጥም ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች መቋቋም እንድንችል በቃሉ አማካኝነት መመሪያ ይሰጠናል።

በፈተናዎች እንድንጸና የሚረዳ ወዳጅ

12, 13. አንዳንዶች ይሖዋ የሚደርስባቸውን መከራ የሚመለከት ስለ መሆኑ እንዲጠራጠሩ የሚያደርጓቸው ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

12 አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ፈታኝ ሁኔታ ያጋጥመን ይሆናል። ለምሳሌ ሥር የሰደደ ሕመም፣ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የቤተሰብ ተቃውሞ ወይም የማያቋርጥ ስደት ሊያጋጥመን ይችላል። አሊያም ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ካለ አንድ ሰው ጋር ከባድ አለመግባባት ይፈጠር ይሆናል።

13 ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንድም የተናገረው ነገር ጎድቶሃል እንበል። በዚህ ጊዜ ‘እንዴት በአምላክ ድርጅት ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር ይፈጠራል!’ ብለህ ታማርር ይሆናል። እንዲያውም ይህ ወንድም በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት የተሰጠው ከመሆኑም ሌላ በሌሎች ዘንድ አክብሮት ያተረፈ ነው። በመሆኑም ‘እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል? ይሖዋ ይህን እያየ እንዴት ዝም ይላል? እርምጃ አይወስድም እንዴ?’ ብለህ ታስባለህ።—መዝ. 13:1, 2፤ ዕን. 1:2, 3

14. ከግለሰቦች ጋር በምንጋጭበት ወቅት አምላክ ጣልቃ የማይገባበት አንዱ ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል?

14 ይሖዋ በጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ የማይገባበት በቂ ምክንያት ሊኖረው ይችላል። ለአብነት ያህል፣ ሌላኛው ወገን ጥፋተኛ እንደሆነ አድርገህ ብታስብም ይሖዋ ነገሩን የሚመለከትበት መንገድ የተለየ ይሆናል። ምናልባትም በእሱ እይታ አንተ ከምታስበው በላይ ጥፋተኛ ሆነህ ልትገኝ ትችላለህ። እንዲያውም የተጎዳህበትን አስተያየት በሚገባ ካሰብክበት ለአንተ ጠቃሚ የሆነ ምክር ሊሆን ይችላል። የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ወንድም ካርል ክላይን በሕይወት ታሪኩ ላይ ወንድም ራዘርፎርድ በአንድ ወቅት ግልጽ የሆነ ተግሣጽ እንደሰጠው ተናግሯል። በኋላ ላይ ወንድም ራዘርፎርድ ወንድም ክላይንን ሲያገኘው ፈገግ ብሎ “ታዲያስ ካርል!” በማለት ሰላምታ ሰጠው። ወንድም ክላይን ግን በተሰጠው ተግሣጽ ተቀይሞ ስለነበር እያጉተመተመ ሰላምታውን መለሰ። ወንድም ራዘርፎርድ፣ ወንድም ክላይን እንዳኮረፈ ስለገባው በዲያብሎስ ወጥመድ ውስጥ እንዳይወድቅ አስጠነቀቀው። ወንድም ክላይን ከጊዜ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አንድ ወንድም በተናገረው ሐሳብ በተለይም ኃላፊነት ኖሮት አስተያየት በሚሰጠን ጊዜ የምንቀየም ከሆነ ዲያብሎስ መግቢያ ቀዳዳ እንዲያገኝ በር እንከፍትለታለን።” *

15. ይሖዋ በሚደርስብህ ፈተና እንዲረዳህ በምትጠባበቅበት ጊዜ ትዕግሥት እንዳታጣ ምን ሊረዳህ ይችላል?

15 በሌላ በኩል ደግሞ የፈተናው ጊዜ ማቆሚያ እንደሌለው ሲሰማን ትዕግሥት እናጣ ይሆናል። ታዲያ በዚህ ጊዜ ሁኔታውን መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? በአንድ አውራ ጎዳና ላይ መኪና እየነዳህ እያለ የትራፊክ መጨናነቅ አጋጠመህ እንበል። የትራፊክ መጨናነቁ መቼ እንደሚቀልል አይታወቅም። በዚህ ተበሳጭተህ በሌላ መንገድ ለመሄድ ብትሞክር የባሰውን መንገዱ ሊጠፋህና ያሰብከው ቦታ ለመድረስ ከጠበቅከው ጊዜ በላይ ሊወስድብህ ይችላል፤ በትዕግሥት ብትጠብቅ ግን ይህን ያህል ጊዜ አይወስድብህ ይሆናል። በተመሳሳይም በአምላክ ቃል ከተጠቀሰው ጎዳና ሳትወጣ የምትጓዝ ከሆነ ያሰብከው ቦታ መድረስህ አይቀርም።

16. ይሖዋ መከራ ሲደርስብን ቶሎ ጣልቃ የማይገባበት ሌላው ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል?

16 ይሖዋ መከራ ሲደርስብን ቶሎ ጣልቃ የማይገባው አስፈላጊ ሥልጠና እንድናገኝ ስለሚፈልግ ሊሆን ይችላል። (1 ጴጥሮስ 5:6-10ን አንብብ።)  እርግጥ ነው፣ ፈተና የሚያመጣብን አምላክ አይደለም። (ያዕ. 1:13) አብዛኛውን ጊዜ የመከራ መንስኤው ‘ጠላታችን ዲያብሎስ’ ነው። ያም ቢሆን አምላክ የሚያጋጥሙንን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተጠቅሞ በመንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል። አምላክ የሚደርስብንን መከራ ይመለከታል፤ እንዲሁም ‘ስለ እኛ ስለሚያስብ’ ፈተናው “ለጥቂት ጊዜ” ብቻ እንዲቆይ ያደርጋል። መከራ ሲደርስብህ ይሖዋ በአሳቢነት እንደሚከታተልህና መውጫ መንገዱን እንደሚያዘጋጅልህ እምነት አለህ?—2 ቆሮ. 4:7-9

ይሖዋ ወሮታህን በመክፈል ይባርክሃል

17. ይሖዋ የሚመለከተው እነማንን ነው? ለምንስ?

17 አምላክ እኛን የሚመለከትበት የመጨረሻው ምክንያት በጣም የሚያጽናና ነው። ይሖዋ በባለ ራእዩ አናኒ አማካኝነት ለንጉሥ አሳ እንዲህ ብሎት ነበር፦ “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ።” (2 ዜና 16:9) እርግጥ ነው፣ አሳ በፍጹም ልቡ በአምላክ አልታመነም፤ አንተ ግን ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግህን የምትቀጥል ከሆነ ‘ያበረታሃል።’

18. የምታደርገውን መልካም ነገር የሚመለከተው እንደሌለ በሚሰማህ ጊዜ ምን ነገር ማስታወስ ይኖርብሃል? (መግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

18 አምላክ ‘መልካሙን እንድንፈልግ፣’ ‘መልካሙን እንድንወድድ’ እና ‘መልካም የሆነውን ነገር እንድናደርግ’ ይጠብቅብናል፤ እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ‘ይራራልናል’ ወይም ሞገሱን ያሳየናል። (አሞጽ 5:14, 15፤ 1 ጴጥ. 3:11, 12) ይሖዋ ጻድቃንን ይመለከታል እንዲሁም ይባርካቸዋል። (መዝ. 34:15) ሲራና ፉሐ የተባሉትን ዕብራውያን አዋላጆች እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እስራኤላውያን ግብፅ ውስጥ በባርነት ሥር በነበሩበት ወቅት እነዚህ ሁለት ሴቶች ከፈርዖን ይልቅ አምላክን እንደሚፈሩ አሳይተዋል፤ ፈርዖን ከዕብራውያን የሚወለዱትን ወንዶች ልጆች በሙሉ እንዲገድሉ ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር። እነዚህ ሴቶች ለአምላክ ባላቸው ጥልቅ አክብሮት የተነሳ ሕሊናቸው ስላልፈቀደላቸው ሳይሆን አይቀርም ልጆቹ በሕይወት እንዲተርፉ አድርገዋል። ሲራና ፉሐ እንዲህ በማድረጋቸው ይሖዋ ከጊዜ በኋላ ቤተሰብ በመስጠት ባረካቸው። (ዘፀ. 1:15-17, 20, 21) ያደረጉት መልካም ነገር ከይሖዋ እይታ የተሰወረ አልነበረም። አንዳንድ ጊዜ፣ ያደረግነውን መልካም ነገር ማንም ሰው ልብ እንደማይለው ሊሰማን ይችላል። ይሖዋ ግን ይመለከተዋል። የምናደርገውን መልካም ነገር በሙሉ የሚያስተውል ከመሆኑም በላይ ወሮታችንን ይከፍለናል።—ማቴ. 6:4, 6፤ 1 ጢሞ. 5:25፤ ዕብ. 6:10

19. አንዲት እህት፣ የምንሠራው መልካም ሥራ ከይሖዋ እይታ እንደማይሰወር የተገነዘበችው እንዴት ነው?

19 በኦስትሪያ የምትኖር አንዲት እህት፣ በትጋት ያከናወነችው ሥራ ከአምላክ እይታ እንዳልተሰወረ ተረድታለች። ይህች እህት የሃንጋሪ ተወላጅ ስለሆነች የእሷን ቋንቋ የምትናገርን አንዲት ሴት እንድታነጋግር አድራሻ ተሰጣት። በተሰጣት አድራሻ መሠረት ወዲያውኑ ወደዚህች ሴት ቤት ብትሄድም በሩን የሚከፍትላት አላገኘችም። በተደጋጋሚ ቤቷ በመሄድ ሴትየዋን ለማግኘት ብትሞክርም አልተሳካላትም። አንዳንድ ጊዜ ቤት ውስጥ ሰው እንዳለ ብትጠረጥርም በሩን የሚከፍትላት አላገኘችም። በዚህ ጊዜ ጽሑፎችን፣ ደብዳቤዎችን፣ አድራሻዋንና ሌሎች መረጃዎችን ትታ ትሄድ ነበር። አንድ ዓመት ተኩል ያህል ከተመላለሰች በኋላ በመጨረሻ በሩ ተከፈተላት! አንዲት ሴት ወጣችና በፈገግታ ተቀበለቻት፤ ከዚያም “ግቢ። ያስቀመጥሽልኝን ነገሮች በሙሉ አንብቤያለሁ፤ ያንቺን መምጣትም ስጠባበቅ ነበር” አለቻት። ይህች ሴት የኬሞቴራፒ ሕክምና ስለምትከታተል ከሰዎች ጋር መገናኘት አልቻለችም። ሴትየዋ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። በእርግጥም እህት ትጋት የተሞላበት ጥረት በማድረጓ አምላክ ወሮታ ከፍሏታል!

20. ይሖዋ የሚመለከተን መሆኑን ስታስብ ምን ይሰማሃል?

20 ይሖዋ የምታከናውነውን ነገር በሙሉ ተመልክቶ ወሮታህን መክፈሉ አይቀርም። አምላክ የሚመለከትህ መሆኑን ማወቅህ ምን ስሜት ያሳድርብሃል? ይሖዋ ይህን የሚያደርገው ለክትትል እንደሚያገለግሉ ካሜራዎች ከአንተ ስህተት ለማግኘት እንደሆነ አድርገህ አታስብ። በመሆኑም ስለ አንተ ከልብ ወደሚጨነቀው አሳቢ አምላክ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ለመቅረብ ጥረት አድርግ!

^ አን.14 የወንድም ክላይን የሕይወት ታሪክ በጥቅምት 1, 1984 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ ወጥቷል።