በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ሚያዝያ 2014

ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚችል የለም

ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚችል የለም

“ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል የለም፤ . . . ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም።”—ማቴ. 6:24

1-3. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ብዙ ቤተሰቦች ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ምን ችግር ያጋጥማቸዋል? አንዳንዶች ችግሩን ለመፍታት የሚሞክሩትስ እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) (ለ) ልጆችን በማሳደግ ረገድ የትኛው አሳሳቢ ጉዳይ ይነሳል?

ማሪሊን * የተባለች ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ጄምስ በየቀኑ ከሥራ የሚመለሰው በጣም ዝሎ ነው፤ ያም ቢሆን ኑሯችን ከእጅ ወደ አፍ ነበር። በመሆኑም የእሱን ሸክም ማቅለልና ለልጃችን ለጂሚ አብረውት የሚማሩ ልጆች ያሏቸውን አንዳንድ ጥሩ ጥሩ ነገሮች መግዛት ፈለግሁ።” ማሪሊን ዘመዶቻቸውን ለመርዳትና ለወደፊቱ ጊዜ የሚሆን ገንዘብ ለማጠራቀምም አሰበች። ብዙ ጓደኞቿ ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ወደ ውጭ አገር ሄደዋል። ይሁንና ነገሩን ቆም ብላ ስታስብበት የተደበላለቀ ስሜት ተሰማት። ለምን ይሆን?

2 ማሪሊን፣ የምትወደውን ቤተሰቧን እንዲሁም አዘውትረው የሚያከናውኑትን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ትታ መሄዷ አስፈራት። በሌላ በኩል ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ ወደ ውጭ አገር የሄዱ አንዳንድ ሰዎች ቤተሰባቸው በመንፈሳዊ እንዳልተጎዳ አሰበች። ይሁንና ‘ጂሚን ሌላ አገር ሆኜ እንዴት ላሳድገው እችላለሁ?’ የሚለው ጉዳይ አስጨነቃት። በእርግጥ ልጇን በኢንተርኔት አማካኝነት “በይሖዋ ተግሣጽ” እና ምክር ማሳደግ ትችላለች?—ኤፌ. 6:4

3 ማሪሊን ጉዳዩን ለሌሎች አማከረች። ባለቤቷ፣ ትታው እንድትሄድ ባይፈልግም ልሂድ ካለች ግን እንደማይከለክላት ተናገረ። ሽማግሌዎችና አንዳንድ የጉባኤው አባላት ደግሞ ወደ ውጭ አገር እንዳትሄድ መከሯት፤ የተወሰኑ እህቶች ግን እንድትሄድ ገፋፏት። “ቤተሰብሽን የምትወጂ ከሆነ መሄድ አለብሽ። እዚያም ሄደሽ ይሖዋን ማገልገል ትችያለሽ” አሏት። ማሪሊን በውሳኔዋ  ባትደሰትም ጄምስንና ጂሚን ተሰናብታ ለሥራ ወደ ባሕር ማዶ ሄደች። “ብዙ አልቆይም” በማለት ቃል ገባችላቸው።

የቤተሰብ ኃላፊነትና የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች

4. ብዙዎች ቤተሰባቸውን ትተው የሚሰደዱት ለምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ ልጆቻቸውን ጥለው የሚሄዱትስ ለማን ነው?

4 ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ በከፋ ድህነት ውስጥ እንዲማቅቁ አይፈልግም። (መዝ. 37:25፤ ምሳሌ 30:8) ከጥንትም ጀምሮ ቢሆን ሰዎች ድህነትን ለማሸነፍ ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች አንዱ ወደ ሌላ ቦታ መሰደድ ነው። ያዕቆብ ቤተሰቡ በረሃብ እንዳያልቅ ልጆቹን ምግብ እንዲገዙ ወደ ግብፅ ልኳቸው ነበር። * (ዘፍ. 42:1, 2) በአንጻሩ ግን በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ቤታቸውን ጥለው የሚሰደዱት ስለተራቡ አይደለም። ምናልባት በከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቀው ሊሆን ይችላል። ሌሎች ደግሞ ተቸግረው ሳይሆን የቤተሰባቸውን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ስለሚፈልጉ ነው። የኢኮኖሚው ሁኔታ እያሽቆለቆለ ባለበት በዚህ ጊዜ ውስጥ እነዚህን ግቦቻቸውን ለማሳካት ሲሉ ብዙዎች በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ቤተሰባቸውን ጥለው ይሰደዳሉ። በዚህ ጊዜ በአብዛኛው ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆቻቸውን ለአንደኛው ወላጅ፣ ለታላቅ ወንድም ወይም እህት፣ ለአያቶች፣ ለዘመዶች አሊያም ለጓደኞች ትተው ይሄዳሉ። በስደት ወደ ሌላ አካባቢ የሚሄዱ ሰዎች የትዳር ጓደኛቸውን ወይም ልጆቻቸውን ጥለው መሄድ ቢያሳዝናቸውም አብዛኞቹ ምንም አማራጭ እንደሌላቸው ይሰማቸዋል።

5, 6. (ሀ) ኢየሱስ ደስታና አስተማማኝ ሕይወት ማግኘት ስለሚቻልበት መንገድ ምን አስተምሯል? (ለ) ኢየሱስ ከቁሳዊ ነገር ጋር በተያያዘ ምን ብለው እንዲጸልዩ ተከታዮቹን አስተምሯቸዋል? (ሐ) ይሖዋ የሚባርከን እንዴት ነው?

5 በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ብዙ ሰዎችም ድሆችና ችግረኞች ነበሩ፤ በመሆኑም የበለጠ ገንዘብ ቢኖራቸው ደስታቸው እንደሚጨምርና ሕይወታቸውም ይበልጥ አስተማማኝ እንደሚሆን ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። (ማር. 14:7) ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ ተስፋቸውን በቁሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያደርጉ አልፈለገም። ከዚህ ይልቅ የማይጠፋ ሀብት ሊሰጥ በሚችለው በይሖዋ እንዲታመኑ ፈልጎ ነበር። ኢየሱስ እውነተኛ ደስታና አስተማማኝ ሕይወት ማግኘታችን የተመካው በቁሳዊ ነገሮች ወይም በእኛ ጥረት ላይ ሳይሆን ከሰማዩ አባታችን ጋር በምንመሠርተው ዝምድና ላይ እንደሆነ የተራራ ስብከቱን በሰጠበት ወቅት አብራርቷል።

6 ኢየሱስ፣ በጸሎት ናሙናው ላይ ያስተማረን አስተማማኝ የገንዘብ ምንጭ እንዲኖረን ሳይሆን “የዕለቱን ምግባችንን” ማለትም ለዕለት የሚያስፈልገንን ያህል ብቻ እንድንለምን ነው። አድማጮቹን በግልጽ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት ማከማቸት ተዉ። ከዚህ ይልቅ . . . በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ።” (ማቴ. 6:9, 11, 19, 20) ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት እንደሚባርከን እምነት መጣል እንችላለን። አምላክ ይባርከናል ሲባል ስላደረግነው ነገር ያደንቀናል ማለት ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የሚያስፈልገንን ነገር በሙሉ ያሟላልናል። በእርግጥም እውነተኛ ደስታና አስተማማኝ ሕይወት ማግኘት የምንችልበት ብቸኛው መንገድ ገንዘብ ሳይሆን ተንከባካቢ በሆነው አባታችን ላይ እምነት መጣል ነው።—ማቴዎስ 6:24, 25, 31-34ን አንብብ።

7. (ሀ) ይሖዋ፣ ልጆችን የማሳደግ ኃላፊነት የሰጠው ለማን ነው? (ለ) ልጆችን በማሳደግ ረገድ ሁለቱም ወላጆች መሳተፍ ያለባቸው ለምንድን ነው?

7 ‘ከሁሉ አስቀድሞ የአምላክን ጽድቅ መፈለግ’ ሲባል ይሖዋ ለቤተሰብ ኃላፊነት ያለው ዓይነት አመለካከት መያዝንም ይጨምራል። የሙሴ ሕግ ወላጆች ለልጆቻቸው መንፈሳዊ ሥልጠና የመስጠት ኃላፊነት እንዳለባቸው ይገልጻል፤ ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ለክርስቲያን ወላጆችም ይሠራል። (ዘዳግም 6:6, 7ን አንብብ።) አምላክ ይህን ኃላፊነት የሰጠው ለአያቶች ወይም ለሌላ ሰው ሳይሆን ለወላጆች ነው። ንጉሥ ሰለሞን “ልጄ ሆይ፤ የአባትህን ምክር አድምጥ፤ የእናትህንም ትምህርት አትተው” ብሏል። (ምሳሌ 1:8) ይሖዋ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማሠልጠንና ለማስተማር ሁለቱም ከልጆቻቸው ጋር አብረው እንዲኖሩ ይጠብቅባቸዋል። (ምሳሌ 31:10, 27, 28) ልጆች በተለይ ከመንፈሳዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከወላጆቻቸው  ብዙ ነገር ሊማሩ የሚችሉት ወላጆቻቸው በየዕለቱ እርስ በርሳቸው ስለ ይሖዋ ሲያወሩ በመስማት እንዲሁም ምሳሌያቸውን በመመልከት ነው።

ያልተጠበቁ መዘዞች

8, 9. (ሀ) አንደኛው ወላጅ ከቤተሰቡ ተነጥሎ ሲኖር አብዛኛውን ጊዜ በቤተሰቡ ውስጥ ምን ለውጦች ሊከሰቱ ይችላሉ? (ለ) ተለያይቶ መኖር ከስሜትና ከሥነ ምግባር አንጻር ምን ጉዳት ሊያስከትል ይችላል?

8 ብዙዎች፣ ወደ ሌላ አገር በሚሰደዱበት ጊዜ እዚያ ሊያጋጥሟቸው ስለሚችሉ አደገኛ ሁኔታዎች ያስባሉ፤ ቤተሰባቸውን ጥለው መሄዳቸው ስለሚያስከትለው መዘዝ የሚያስቡት ግን ከስንት አንድ ናቸው። (ምሳሌ 22:3) * ማሪሊን ባሕር ማዶ ከሄደች በኋላ ብዙም ሳትቆይ ቤተሰቧን ትታ መሄዷ ስሜታዊ ሥቃይ አስከተለባት። ባለቤቷና ልጇም ቢሆኑ መለያየቱ ከባድ ሆኖባቸው ነበር። ጂሚ እናቱን “ጥለሽኝ የሄድሽው ለምንድን ነው?” በማለት በተደጋጋሚ ይጠይቃት ነበር። ጊዜ ጊዜን እየወለደ ሄዶ ማሪሊን ለመመለስ ባሰበችበት ጊዜ ሳትመለስ ዓመታት ተቆጠሩ፤ በዚህ ወቅት በቤተሰቧ ላይ ባየችው ለውጥ መረበሽ ጀመረች። ጂሚ ለእሷ ያለው ስሜት እየቀዘቀዘ የሄደ ከመሆኑም ሌላ እንደ በፊቱ ከእሷ ጋር ማውራት እየከበደው መጣ። “ለእኔ የነበረው ፍቅር ጠፋ” በማለት ማሪሊን በሐዘን ተናግራለች።

9 ወላጆችና ልጆች ተለያይተው መኖራቸው ከስሜትና ከሥነ ምግባር አንጻር በሁለቱም ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። * በተለይ ደግሞ ልጆቹ በዕድሜ ትንሽ ከሆኑና ተለያይተው የሚቆዩበት ጊዜ እየረዘመ ከመጣ ጉዳቱም የዚያኑ ያህል ከባድ ይሆናል። ማሪሊን ይህን ያደረገችው ለእሱ ብላ እንደሆነ ጂሚን ልታስረዳው ሞክራ ነበር። ጂሚ ግን እናቱ ይህን ያደረገችው ስለማትወደው እንደሆነ ተሰምቶታል። መጀመሪያ አካባቢ በመሄዷ በጣም ይበሳጭ ነበር። በኋላ ላይ ግን ልትጠይቃቸው ተመልሳ ስትመጣም መበሳጨት ጀመረ። ከወላጆቻቸው ተለይተው በሚያድጉ ልጆች ላይ እንደሚታየው ሁሉ ጂሚም እናቱ ጥላው በመሄዷ እሷን የመታዘዝም ሆነ የመውደድ ግዴታ እንደሌለበት ተሰማው።—ምሳሌ 29:15ን አንብብ።

ልጃችሁን በኢንተርኔት አማካኝነት ልታቅፉት አትችሉም (አንቀጽ 10ን ተመልከት)

10. (ሀ) ቤተሰብን ጥሎ መሄድን ቁሳዊ ነገር በመላክ ለማካካስ መሞከር በልጆች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? (ለ) በሌላ አገር ሆነው የወላጅነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚሞክሩ ወላጆች ምን ማድረግ አይችሉም?

10 ማሪሊን ቤተሰቧን ጥላ መሄዷ የፈጠረውን ክፍተት ገንዘብና ስጦታ በመላክ ለማካካስ ብትሞክርም ከልጇ ጋር የነበራት ቅርበት እየጠፋ እንደመጣ ተገነዘበች፤ እንዲሁም ሳይታወቃት ልጁ ቁሳዊ ነገሮችን ከመንፈሳዊ ነገሮችና ከቤተሰቡ አስበልጦ እንዲመለከት እያደረገችው እንደሆነ አስተዋለች። (ምሳሌ 22:6) ጂሚ “ተመልሰሽ እንዳትመጪ። እዚያው ሆነሽ ስጦታ ላኪልኝ” ይላት ነበር። ማሪሊን በደብዳቤ፣ በስልክ ወይም በኢንተርኔት እየተያዩ በመነጋገር ልጅ የማሳደግ ኃላፊነቷን መወጣት እንደማትችል ገባት። “ልጃችሁን በኢንተርኔት አማካኝነት  ልታቅፉት ወይም ደህና እደር ብላችሁ ልትስሙት አትችሉም” ብላለች።

ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ተለያይታችሁ ስትኖሩ ምን አደገኛ ሁኔታ ሊያጋጥማችሁ ይችላል? (አንቀጽ 11ን ተመልከት)

11. (ሀ) ለሥራ ሲባል ተለያይቶ መኖር ትዳርን የሚነካው እንዴት ነው? (ለ) አንዲት እህት ወደ ቤተሰቧ መመለሷ የግድ አስፈላጊ መሆኑን እንድትገነዘብ ያደረጋት ምንድን ነው?

11 ማሪሊን ከይሖዋም ሆነ ከባለቤቷ ከጄምስ ጋር ያላት ግንኙነት አደጋ እያጠላበት መጣ። ለጉባኤም ሆነ ለአገልግሎት ጊዜ የምታገኘው በሳምንት አንድ ቀን ወይም ከዚያ ያነሰ ጊዜ ነበር፤ በዚያ ላይ ደግሞ የአሠሪዋን የፆታ ጥያቄ መቋቋም ነበረባት። ማሪሊንና ጄምስ ችግር ሲያጋጥማቸው አንዳቸው ሌላውን በቅርብ ማማከር ስለማይችሉ ሁለቱም ከሌላ ሰው ጋር ፍቅር የያዛቸው ከመሆኑም ሌላ ለፆታ ብልግና ሊሸነፉ ምንም አልቀራቸውም ነበር። ምንም እንኳ ምንዝር ባይፈጽሙም አንዳቸው የሌላውን ስሜታዊና ፆታዊ ፍላጎት እንዲያሟሉ የሚያዝዘውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ እንዳልተከተሉ ማሪሊን ተገነዘበች። ድንገት የሚመጣላቸውን ሐሳብ ወዲያው ማካፈል፣ እንደፈለጉ መተያየት፣ ፈገግታ መለዋወጥ፣ መደባበስ፣ መተቃቀፍ፣ ‘የፍቅር’ መግለጫዎችን ማሳየት ወይም ለትዳር ጓደኛ ‘የሚገባውን’ ማድረግ አልቻሉም። (ማሕ. 1:2፤ 1 ቆሮ. 7:3, 5) እንዲሁም ከልጃቸው ጋር ሆነው በኅብረት ይሖዋን ማምለክ አልቻሉም። ማሪሊን እንዲህ ብላለች፦ “አዘውትረን የቤተሰብ አምልኮ ማድረግ ከታላቁ የይሖዋ ቀን ለመትረፍ ወሳኝ እንደሆነ በአንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ አዳመጥኩ፤ በዚህ ጊዜ ወደ ቤተሰቤ መመለስ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። መንፈሳዊነቴን እንዲሁም ከቤተሰቤ ጋር ያለኝን ግንኙነት እንደ አዲስ መጀመር ነበረብኝ።”

ጥሩ ምክርና መጥፎ ምክር

12. ከቤተሰባቸው ተነጥለው ለሚኖሩ ወላጆች የትኛውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ልናካፍላቸው እንችላለን?

12 ማሪሊን ወደ ቤተሰቧ ለመመለስ ውሳኔ ስታደርግ ሰዎች የሰጧት ምላሽ የተለያየ ነበር። ውጭ አገር ሳለች የነበረችበት ጉባኤ ሽማግሌዎች፣ እምነትና ድፍረት በማሳየቷ አመሰገኗት። ይሁን እንጂ እንደ እሷ ከትዳር ጓደኛቸውና ከቤተሰባቸው ተለይተው ውጭ አገር የሚኖሩ አንዳንዶች በውሳኔዋ አልተደሰቱም። የእሷን ጥሩ ምሳሌ ከመከተል ይልቅ እንድትቀር ሊያሳምኗት ሞከሩ። እንዲህ አሏት፦ “በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመልሰሽ መምጣትሽ አይቀርም። ወደ አገር ቤት ከተመለስሽ ኑሮሽን እንዴት ልታሸንፊ ነው?” ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉ ተስፋ የሚያስቆርጡ አስተያየቶችን ከመሰንዘር ይልቅ ‘ወጣት ሴቶች ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን የሚወዱ እንዲሆኑ’ እንዲሁም ‘በቤት ውስጥ እንዲሠሩ’ ይኸውም በራሳቸው ቤት ውስጥ እንዲሠሩ መምከር ይኖርባቸዋል፤ “ይህም የአምላክ ቃል እንዳይሰደብ ያደርጋል።”—ቲቶ 2:3-5ን አንብብ።

13, 14. ከዘመዶች ይልቅ ይሖዋን ማስቀደም እምነት የሚጠይቀው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

13 ለሥራ ወደ ውጭ አገር የሚሄዱ ብዙ ሰዎች ያደጉት ለባሕል እንዲሁም ለዘመዶች በተለይም ለወላጆች ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ በሚሰጥ ማኅበረሰብ ውስጥ ነው። እንዲህ ባሉ አገሮች የሚኖር አንድ ክርስቲያን ይሖዋን የሚያስደስተውን ነገር ለማድረግ ሲል የአካባቢውን ልማድ ወይም የዘመዶቹን ፍላጎት ላለመከተል መምረጥ እምነት ይጠይቅበታል።

 14 ካሪንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ እንዲህ ብላለች፦ “ልጄ ዶን በተወለደበት ወቅት እኔም ሆንኩ ባለቤቴ የምንኖረው በውጭ አገር ነበር፤ በዚያን ጊዜ አካባቢ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምሬ ነበር። ቤተሰቦቼ በሙሉ እኔና ባለቤቴ በኑሮ እስክንቋቋም ድረስ ዶንን ወደ አገር ቤት ልኬ ወላጆቼ እንዲያሳድጉት ጠብቀው ነበር።” ይሁንና ልጇን እሷ ራሷ ማሳደግ እንደምትፈልግ ሲረዱ ባለቤቷን ጨምሮ ዘመዶቿ እንደ ሰነፍ በመቁጠር ሳቁባት። ካሪን እንዲህ ብላለች፦ “እውነቱን ለመናገር፣ በወቅቱ ዶንን ለጥቂት ዓመታት ወላጆቼ እንዲያሳድጉት መስጠት ምን ችግር እንዳለው ሙሉ በሙሉ አልተረዳሁም ነበር። ያም ቢሆን ይሖዋ ልጃችንን የማሳደግ ኃላፊነት የሰጠው ለእኛ ለወላጆቹ እንደሆነ አውቅ ነበር።” በሌላ ጊዜ ደግሞ ካሪን እንደገና ስታረግዝ አማኝ ያልሆነው ባለቤቷ እንድታስወርድ ነገራት። ካሪን ቀደም ሲል ባደረገችው ጥሩ ውሳኔ እምነቷ ተጠናክሮ ስለነበር በዚህ ጊዜም ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ቆረጠች። በአሁኑ ጊዜ እሷም ሆነች ባለቤቷ እንዲሁም ልጆቿ ባለመለያየታቸው በጣም ደስተኞች ናቸው። ካሪን ልጆቿን ሌሎች እንዲያሳድጉላት አድርጋ ቢሆን ኖሮ ውጤቱ ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ይሆን ነበር።

15, 16. (ሀ) አንዲት እህት ከወላጆቿ ተነጥላ ማደጓ ምን ተጽዕኖ እንዳሳደረባት ግለጽ። (ለ) ይህች እህት የራሷን ልጅ እሷ ካደገችበት በተለየ መንገድ ለማሳደግ የወሰነችውስ ለምንድን ነው?

15 ቪኪ የተባለች የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ታናሽ እህቴን ከእነሱ ጋር አስቀርተው እኔን ለአያቴ ሰጥተውኝ ስለነበር ለተወሰኑ ዓመታት ያደግሁት ከእሷ ጋር ነው። እንደገና ከወላጆቼ ጋር መኖር ስጀምር ለእነሱ ያለኝ ስሜት ተቀይሮ ነበር። እህቴ ለእነሱ በነፃነት ሐሳቧን ትገልጽ፣ ታቅፋቸው እንዲሁም በጣም ትቀርባቸው ነበር። እኔ ግን ወላጆቼን መቅረብ ይከብደኝ ነበር፤ ትልቅ ሆኜም ጭምር የውስጥ ስሜቴን ለእነሱ መግለጽ ይቸግረኝ ነበር። እኔና እህቴ፣ ወላጆቼ ዕድሜያቸው ሲገፋ እንደምንጦራቸው ነግረናቸዋል። እኔ ይህን የማደርገው እንዲሁ ኃላፊነት እንዳለብኝ ተሰምቶኝ ሲሆን እህቴ ግን ይህን የምታደርገው በፍቅር ነው።

16 “አሁን ደግሞ እናቴ፣ እኔን ለእናቷ እንደሰጠችኝ ሁሉ እኔም ልጄን ለእሷ ሰጥቼ እንድታሳድግልኝ ፈለገች። ፈቃደኛ አለመሆኔን በዘዴ ነገርኳት” በማለት ቪኪ ተናግራለች። “እኔና ባለቤቴ ልጃችንን በይሖዋ መንገድ ራሳችን ማሳደግ እንፈልጋለን። ከዚህም ሌላ ወደፊት ከልጄ ጋር የሚኖረኝ ግንኙነት እንዲበላሽ አልፈልግም።” ቪኪ፣ ለስኬት የሚያበቃው ብቸኛው መንገድ ይሖዋንና መመሪያዎቹን ከቁሳዊ ነገሮችም ይሁን ከዘመዶች ማስቀደም እንደሆነ ተገንዝባለች። ኢየሱስ በግልጽ እንደተናገረው “ለሁለት ጌቶች” ይኸውም ለአምላክና ለሀብት “ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል የለም።”ማቴ. 6:24፤ ዘፀ. 23:2

ይሖዋ ጥረታችን ‘እንዲከናወንልን’ ያደርጋል

17, 18. (ሀ) ክርስቲያኖች ምንጊዜም አማራጭ አላቸው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) የሚቀጥለው ርዕስ ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል?

17 አባታችን ይሖዋ፣ በሕይወታችን መንግሥቱንና ጽድቁን ካስቀደምን የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ እንደሚያሟላልን ቃል ገብቷል። (ማቴ. 6:33) ከዚህ አንጻር እውነተኛ ክርስቲያኖች ምንጊዜም አማራጭ አላቸው። ይሖዋ ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥመን የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ሳንጥስ ችግሩን ማሸነፍ የምንችልበት ‘መውጫ መንገድ’ እንደሚያዘጋጅልን ቃል ገብቶልናል። (1 ቆሮንቶስ 10:13ን አንብብ።) ይሖዋን ‘በትዕግሥት ከተጠባበቅነው’ እንዲሁም ጥበብና መመሪያ እንዲሰጠን በመለመን ብሎም ትእዛዛቱንና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በመከተል ‘በእሱ እንደምንታመን’ ካሳየን ጥረታችን ‘እንዲከናወንልን’ ወይም እንዲሳካልን ያደርጋል። (መዝ. 37:5, 7) ይሖዋን እንደ ጌታችን በመቁጠር እሱን ብቻ ለማገልገል የምናደርገውን ልባዊ ጥረት ምንጊዜም ይባርካል። እሱን የምናስቀድም ከሆነ ሕይወታችን ‘ይከናወንልናል’ ወይም ይሳካል።—ከዘፍጥረት 39:3 ጋር አወዳድር።

18 ይሁን እንጂ ተለያይቶ መኖር ያስከተለውን ጉዳት ለመጠገን ምን ማድረግ ይቻላል? ከቤተሰባችን መለየት ሳያስፈልገን ለኑሮ የሚያስፈልገንን ለሟሟላት ምን ጠቃሚ እርምጃዎችን መውሰድ እንችላለን? ሌሎች በዚህ ረገድ ትክክለኛውን ውሳኔ እንዲያደርጉ በፍቅር ልናበረታታቸው የምንችለውስ እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

^ አን.1 ስሞቹ ተቀይረዋል።

^ አን.4 የያዕቆብ ልጆች ወደ ግብፅ በሄዱባቸው ወቅቶች ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው የቆዩበት ጊዜ ከሦስት ሳምንት አይበልጥም። በኋላ ላይ ያዕቆብና ወንዶች ልጆቹ በግብፅ ለመኖር ሲሄዱ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውንም ወስደዋል።—ዘፍ. 46:6, 7

^ አን.8 በየካቲት 2013 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “የስደት ሕይወት—የሚታሰበውና እውነታው” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.9 ከተለያዩ አገሮች የተገኙ ሪፖርቶች እንዳመለከቱት የትዳር ጓደኛን ወይም ልጆችን ጥሎ ለሥራ ወደ ውጭ አገር መሰደድ ለከባድ ችግሮች መንስኤ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ነው። ከእነዚህ ችግሮች መካከል ግብረ ሰዶም፣ አንደኛው የትዳር ጓደኛ ወይም ሁለቱም ምንዝር መፈጸማቸው አሊያም በአባትና በልጅ መካከል የሚፈጸም የፆታ ግንኙነት ይገኙበታል፤ በልጆቹ ላይ ከሚደርሱት ችግሮች መካከል ደግሞ የባሕርይ ለውጥ፣ የትምህርት ውጤት መቀነስ፣ ግልፍተኝነት፣ ውጥረት፣ የመንፈስ ጭንቀት ወይም ራስን ለማጥፋት መሞከር የሚጠቀሱ ናቸው።